08/09/2023
# ሆሳዕና እናት ቃ/ሕ/ቤ/ክ
# ለተለያዩ ሥነ-ምግባራዊ ጉዳዮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምላሽ እና ውሳኔ :
1. መፋታት/ፍቺ እና እንደገና ማግባት
2. ድርብ ጋብቻ
3. አስካሪ መጠጦች
4. በንግድ፣ በመንግስት ሥራና በሥልጣን አከባቢ
የሚስተዋል የሥነ-ምግባር ጉድለትና ሙስና
5. ከባህል ጋር ተያይዞ የሚመጡ ልምምዶች
(የመስቀል በዓል, ጥሎሽ, መልስ, የሠርግ
ድግስ እና ባህላዊ ዳኞች)
መግቢያ
ሰይጣን ወደ ቤተ-ክርስቲያን አሾልኮ የሰደዳቸው እድፎች ብዛት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ እያንዳንዱ ቆሻሻ በቅዱስ ቃሉ ሳሙና ታጥቦ ሊጸዳ የሚገባው ነው፡፡ ነገር ግን ሁሉንም ሥነ-ምግባራዊ ጉዳዮች በአንዴ መፍታት ስለማንችል ጠንካራ ደቀ መዝሙራዊ ሥራ በመስራት የምንታገላቸው ናቸው፡፡ ለጊዜው ግን እጅግ አንገብጋቢ የሆኑትንና በስፋት በመካከላችን እየተስተዋሉ እንዳለ ጥቅምት 6/2015 የምህረት ዓመት በቤተ-ክርስቲያኒቱ መሪ ሽማግሌዎች፣ እናት መሪዎች፣ ወጣት መሪዎችና ወንጌላዊያን የጋራ ስብሰባ ታምኖባቸው የተዘረዘሩና ተነጋግረን መፍትሔ እንድናመጣ ሰባት ሥነ-ምግባራዊ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረናል፡፡
እነዚህን ሥነ-ምግባራዊ ጉዳዮች ስንመለከትና ውሳኔ ላይ ስንደርስ በዋናነት ሁለት መለኪያዎችን መሠረት አድርገን ነው፡፡ የመጀመሪያውና ቀዳሚው ከየትኛውም ሌላ መለኪያ ጋር የማናነጻጽረው መከሊያችን መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ቅዱሳት መጽሐፍት የአስተምህሮአችንም ሆነ የዕለት ተዕለት ኑሮአችን መሠረቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላል? የሚለው ጥያቄ የመጀመሪያውና ዋነኛው ጥያቄ ሲሆን፤ መጽሐፍ ቅዱስ የመለሰው መልስም የመጀመሪያውና ብቸኛው መልሳችን ነው፡፡
ቅዱሳት መጽሐፍትን ዋቢ አድርገን ካየን በኋላ በሁለተኝነት የተመለከትነው የቤተ-ክርስቲያንን ትውፊት ነበረ፡፡ ቤተ-ክርስቲያን ባለፈችባቸው ጎዳናዎች ብዙ ነገር አይታለች፤ ለገጠማት ነገሮችም ብዙ መልስ ሰጥታለች፡፡ በእኛ ዘመን የተከሰቱ ሥነ-ምግባራዊ ጉዳዮች ባለፉት ቅዱሳን ዘመን ተከስቶ መልስ ተሰጥቶባቸዋል፤ ስለዚህም ነው ከመጽሐፍ ቅዱሳችን ቀጥሎ የቤተ-ክርስቲያንን ትውፊት ለሥነ-ምግባራዊ ጉዳዮች ብያኔ ለመሰጠት የምንጠቀመው፡፡ በሁለተኝነት ደረጃ መሆኑ ግን እንዳይዘነጋ፡፡ በዚህ ጽሑፍ በእያንዳንዱ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ዋና ዋና ነጥቦቹንና ውሳኔዎቹን ብቻ በመዳሰስ አጥር አድርገን እናቀርባለን፡፡
1. መፋታት/ፍቺ እና እንደገና ማግባት
መጽሐፍ ቅዱስ የሚጀምረው በጋብቻ ሲሆን፤ የሚጨርሰውም በጋብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር ጋብቻን የመሠረተው ገና በመጀመሪያው መጽሐፍ በመጀመሪያው ምዕራፍ ነው፡፡ ይኸው በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት የተጀመረው ጋብቻ በክርስቶስና በቤተ-ክርስቲያን መካከል በሚደረገው ጋብቻ ይጠናቀቃል፡፡
ፍቺ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ተግባር ነው፤ ሰዎች ይፋቱ ዘንድ ፈቃዱ አይደለም፡፡ የቤተ-ክርስቲያናችም እምነት አቋም ፍቺን በጽኑ አውግዟል፡፡ ነገር ግን ፍቺ ነባራዊ የሰዎች ሕይወት ክስተት ነው፤ በመካከላችንም በዚህ ይሁን በዚያ ምክንያት ፍቺ የፈጸሙ አባላት መኖራቸው የአደባባይ ሐቅ ነው፡፡ ጥንትም ሆነ ዛሬ “በዚህና በዚያ ምክንያት መፍታት አልችልም ወይ?” የሚል ጥያቄ ይነሳል፤ ይህ ጥያቄ አንገብጋቢና የዘመኑ ጥያቄ ነው፤ ይህ ጥያቄ ትናንት ነበረ፣ ዛሬም አለ፣ ነገም የሚቀጥል ነው፡፡ ፍቺን በተመለከተ ክርስቲያኖች የሚያነሷቸውን ምክንያቶች ሁሉ ዘርዝረን ምላሽ ብንሰጥባቸው የተሸለ ነበረ፤ ነገር ግን ይህንን ማድረግ ስለማንችል ዋናኛውን ለፍቺ ምክንያት ነው ተብሎ የሚታሰበውን ዝሙትን እንመልከት፡፡
በትዳር ውስጥ የሚደረግ ውስልትናና አለመታመን የተበዳዩን አካልም ሞራልም እጅግ የሚጎ አስከፊ ድርጊት ነው፡፡ ክርስቲያኖች ከዝሙት በመሸሽና ለትዳር አጋር ታማኝ በመሆን ለእግዚአብሔር ያላቸውን ንጽሕናና ታማኝነት መግለጽ አለባቸው፤ ለዚህም የሚረዳውን ጸጋ መሻትና መደገፍ አለባቸው፡፡
በዝሙት ምክንያት የሚደረግ ፍቺንና እንደገና ማግባትን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ በዋናነት “በዝሙት ምክንያት” ጋብቻን መፍታት ይቻላል የሚሉ ሰዎች ዋና ማስረጃ አድርገው የሚያቀርቡትን የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 19 ትርክት በሚገባ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ለማቴ 19፡3-9 ጤናማውን የሥነ-አፈታት ሕግ ተከትለን ትርጉም ልንሰጠው ግድ ይላል፡፡
“ፈሪሳዊያንም ሊፈትኑት ቀርበው፣ “ለመሆኑ አንድ ሰው በማንኛውም ምክንያት ሚስቱን መፍታት ተፈቅዶአልን?” ሲሉ ጠየቁት፡፡ እርሱም [ኢየሱስም] መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አድርጎ እንደፈጠራቸው አላነበባችሁምን? እንዲህም አለ፤ ‘ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣመራል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ የተባለው በዚህ ምክንያት አይደለምን? ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው፡፡” እነርሱም “ታዲያ ሙሴ አንድ ወንድ የፍቺውን የምስክር ወረቀት ሰጥቶ ሚስቱን እንዲያሰናብታት ለምን አዘዘ?” አሉት፡፡ ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “ሙሴ የልባችሁን ጥንካሬ አይቶ ሚስቶቻችሁን እንድትፈቱ ፈቀደላችሁ እንጂ ከመጀመሪያው እንዲህ አልነበረም፤ እላችኋለሁ በትዳሯ ላይ ዝሙት ፈጽማ እስካልተገኘች ድረስ ሚስቱን ፈትቶ ሌላ ሴት የሚያገባ ሁሉ አመንዝራ ይሆናል፤ እርሷንም አመንዝራ ያደርጋታል፣ የተፈታችውንም ሴት የሚያገባ ያመነዝራል፡፡””
“በማኝኛውም ምክንያት” የሚሉት ቃላት ወሳኝ ናቸው፡፡ የዚህ መነሻው ደግሞ ዘዳ 24፥1 ነው፡፡ “ሰው ሴትን ወስዶ ቢያገባ፥ የእፍረት ነገር ስላገኘባት በእርሱ ዘንድ ሞገስ ባታገኝ፥ የፍችዋን ጽሕፈት ጽፎ በእጅዋ ይስጣት፥ ከቤቱም ይስደዳት።” ይላል፡፡ ይህንን የሙሴን ቃል በተመለከተ የአይሁድ ምሁራንና ሐይማኖታዊ መሪዎች ሁለት ዓይነት አመለካከት ያራምዳሉ፡፡
1. ቀዳሚዎቹ ሂሌል (Hillel) የሚሰኙ ሲሆን፤ እነዚህ ሰው በማንኛውም ምክንያት ለምሳሌ ወሲብ ላይ አላረካሽኝም፣ ወጥሽ አልጣፈጠኝም፣ ሙያ የለሽም ብሎ ብቻ በማንኛውም ምክንያት ሚስቱን መፍታት ይችላል፤ የሚፈታት ሴት የሚያገባት ካገኘች ዕድሏን እንድትሞክር ግን የፍቺዋን ጽሕፈት (ፈት መሆኗን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት) መስጠት አለበት፡፡
2. ሌላኛው አመለካከት ደግሞ ሻማዪ (Shamai) ይባላል፡፡ እነዚህኞቹ ፍቺ የሚፈቀደው በጋብቻ ውስጥ በሚፈጸም አቢይ በደል (Major Offense) ይህም ለጋብቻ ታማኝ በለመሆን ብቻ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ለጋብቻ አለመታመን (marital unfaithfulness) ደግሞ ከእነዚህ አንዱ ሊሆን ይችላልም ብለው ያምናሉ፡፡ የአንድ ጊዜ ዝሙት (a single act of adultery)፣ በእጮኝነት ጊዜ ታማኝ ሆኖ አለመገኘት፤ ከሌላ ማርገዝ ወይም ድንግል ሆኖ አለመገኘት (ማቴ 1፡19)፣ በዘመዳሞች መካከል የሚፈጸም ጋብቻ (ዘሌ 18፥6-18)፣ ዘወትራዊ የሆነ የዝሙት ተግባር (ማቴ 19፥9) ፡፡
ነገር ግን አብዛኛዎቹ የአዲስ ኪዳን ምሁራን በተደጋጋሚ የሚፈጸምን ወሲባዊ አለመታመን ወይም ዘወትራዊና ቋሚ ልምምድ ወደ መሆን የመጣ የዝሙት ተግባር ነው ለፍቺ ምክንያት ይሆናል ብለው የሚያስቀምጡት፡፡ በተቃራኒው በእኛ ሀገር በሚገኙ በርካታ ቤተ-ክርስቲያናት ትውፊት በስፋት የሚታየው አንድ ጊዜም ሆነ በተደጋጋሚ ዝሙት ከተገኘ መፍታት እንደሚቻል ነው፡፡
እንግዲህ ይህ ከላይ የተመለከትነው የአይሁዳዊያን ምሁራንና ሐይማኖታዊ መምህራን አመለካከት ነው፡፡ ኢየሱስ ግን እያለ ያለው ምንድነው?
ኢየሱስ እየተናገረ ያለው እርሱ አንዱ የስላሴ አካል ስለሆነ፤ የአደምና የሔዋን ጋብቻ ሲመሰረት እርሱ ነበረና በመጀመሪያ እግዚአብሔር ጋብቻን ሲያስብ የነበረውን ዓላማ እየተናገረ ነው፡፡ ፈጠሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፣ ሰው (ባል) አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣመራል ሁለቱም አንድ ስጋ ይሆናሉ፡፡ የጋብቻ ጥምረት በወላጅና በልጅ መካከል ካለው ጥምረት የሚበልጥ ነው፤ ከዚያ የጠነከረ ትስስር ነው የጋብቻ ትስስር፡፡ ስለዚህ ምን ይሁን ከተባለ፤ እግዚአብሔር አንድ ያደረጋቸውን፤ አንድ ስጋ የሆኑትን ወደ ፊት ሁለት ስጋ መሆን የማይችሉትን ሰዎች ሰው (ሰዋዊ ምክንያት ዝሙትን ጨምሮ) አይለየው እያለ ነው፡፡
ሙሴ ልባቸው እጅግ ጠንካራ ስለነበረ፣ ኀጢአተኛ ስለነበረ፣ ሚስቶቻቸውን እንደ ዕቃ እያወጡ መጣል ስላበዙ፣ ደስ ባለቸው ጊዜ ሁሉ እያባረሩ ስላስቸገሩ፤ የተጠቃውን ወገን ማለትም ሴቷን ለመርዳት ሲል ነው ያንን ሕግ ያወጣው፡፡ ስለዚህ በለትዳሮች እንዴት አብረን እንኑር ብለው የጥምረት ገመዳቸውን ስለማጥበቅ እንጂ ምን ምክንያት አግኝቼ ልፍታ በሚል አመለካከት መሞላት የለባቸውም፡፡
የኢየሱስ አስተምህሮ፦
“ያገባች ሴት ባልዋ በሕይወት ሲኖር ከእርሱ ጋር በሕግ ታስራለችና፤ ባልዋ ቢሞት ግን ስለ ባል ከሆነው ሕግ ተፈትታለች።” (ሮሜ 7፡2-3) ስለዚህ ከሞት በቀር ባልንና ሚስትን የሚለይ ነገር አይኖርም፡፡
“ሚስትም ከባልዋ አትለያይ፥ ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር ወይም ከባልዋ ትታረቅ፥ ባልም ሚስቱን አይተዋት ብዬ የተጋቡትን አዛቸዋለሁ፥ እኔ ግን አላዝም፥ ጌታ እንጂ። ሴት ባልዋ በሕይወት ሳለ የታሰረች ናት፤ ባልዋ ቢሞት ግን በጌታ ይሁን እንጂ የወደደችውን ልታገባ ነጻነት አላት።” (1 ቆሮ 7፡10-11፤ 39) ስለዚህ ከሞት በቀር ባልንና ሚስትን የሚለይ ነገር አይኖርም፡፡
“እርሱም፦ ሚስቱን ፈትቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ በእርስዋ ላይ ያመነዝራል፤ እርስዋም ባልዋን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች አላቸው።” (ማር 10፡10-11) ስለዚህ ከሞት በቀር ባልንና ሚስትን የሚለይ ነገር አይኖርም፡፡
ከላይ ከየናቸው ሦስት ጥቅሶች ሁለቱን የተናገራቸው ጳውሎስ ሲሆን አንዱን የተናገረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የንግግራቸው ዋና ዓላማ ፍቺ በማንኛውም ምክንያት እንደማይፈቀድ እንዲሁም የፈታ ሰው የፈታውን የራሱን አጋር እንጂ ሌላ ሰው ደግሞ ማግባት እንደማቻል በግልጽ ተቀምጧል፡፡
ይህንን ርዕስ የምንዘጋው ከላይ የሰጠነው ሰፊ ትንተና ትልቅ አጽንዖት እንዲሰጠው በመጠየቅ ነው፡፡ ነገር ግን በባለ ትዳሮች መካከል አንድኛው ወገን ዝሙት ቢፈጽምና ሌላኛው ወገን ያንን ኃጢአት በይቅርታ በማለፍ አብሮ የመኖር አቅም ካጣ እንዲፈታ የተፈቀደ ይመስላል፡፡ በማቴዎስ 5፥31 እና 19፥9 በዝሙት ምክንያት ፍቺ የተፈቀደ ይመስላል፤ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በተለይም አዲስ ኪዳን በየትኛውም ስፍራ በየትኛውም መንገድ ፍቺ የፈጸመ ሰው ድጋሚ እንዲያገባ ፍንጭ የሚሰጥ አንድም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ የለንም፡፡ ቤተ-ክርስቲያን ጋብቻን የተመለከተ ትልቁ ትምህርቷና መርኋ ጋብቻ ቅዱስ ነው፤ ፍቺም በጌታ ዘንድ የተጠላ ተግባር ነው የሚል ነው፡፡
2. ድርብ ጋብቻ
በኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ-ክርስቲያን የእምነት አቋም አንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ 2-5 እንዲሁም በአጥቢያ ቤተ-ክርስቲያናችን ውስጠ ደንብ አንቀጽ 30 ንዑስ አንቀጽ 4 በግልጽ እንደተቀመጠው ድርብ ጋብቻ ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ፣ ከክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባር ያፈነገጠ፣ የቤተ-ክርስቲያንን በጎ ትውፊት ያልተከተለ ስለሆነ የሚፈቀድ አይደለም፡፡
በሰው ልጆች ታሪክ የመጀመሪያው ድርብ ጋብቻ የታየው ዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ላይ ሲሆን ይህም ከሰው ልጆች ውድቀት በኋላ ኃጢአት ያስከተለው ክፉ መዘዝ እንጂ የእግዚአብሔር ፈቃድ አለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የጋብቻ መስራች የሆነው እግዚአብሔር ጋብቻን በተመለከተ ድንጋጌ ሰጪም ነው፡፡ ስለ ጋብቻ የተጠቀሰው የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚገኘው በዘፍ 2 ለይ ሲሆን እንዲህ ይነበባል፦
“እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት።……ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ በሚስቱም ይጣበቃል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። አዳምና ሚስቱ ሁለቱም ዕራቁታቸውን ነበሩ፥ አይተፋፈሩም ነበር።” (ዘፍ 2፡14፤ 24-25)
ከላይ የተጠቀሰው የመጀመሪያው የጋብቻ ጥቅስ የሚያወራው ስለ አንድ ባልና ስለ አንዲት ሚስት እንጂ ስለ አንድ ባልና ብዙ ሚስቶች ወይም አንድ ሚስትና ብዙ ባሎች አይደለም፡፡ የጋብቻ መስራቹ እርሱ እግዚአብሔር አንድ ወንድ ሰው አንድ ሴት ሰው ብቻ እንዲያገባ ነው የፈቀደው፡፡ በተጨማሪም ድርብ ጋብቻ መፈጸም በቤተ-ክርስቲያናችን ውስጠ ደንብ አንቀጽ 29.2.1 ተራ ቁጥር 2 መሠረት የተከለከለ ነው፡፡
ነገር ግን አንድ ሰው በጌታ ከመሆኑ በፊት ድርብ ጋብቻ የፈጸመ ሰው ወንጌልን ሰምቶ ጌታ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኙ አድርጎ ተቀብሎ ወደ ቤታክርስቲያናችን ቢመጣ እንዴት እናስተናግደው?
ወንጌል ወደ አካባቢያችን ሲገባ፤ ድርብ ጋብቻ የተለመደ የማህበረሰብ ልማድ ነበረ፡፡ የቤተ-ክርስቲያናችንን ትውፊት ያየን እንደሆነ በመጀመሪያዎቹ የወንጌል ዘመናት ድርብ ጋብቻ ፈጽመው ወደ ጌታ የሚመጡ ሰዎችን ማፋታቱ፥ ወይም አንዷን ብቻ አስቀርቶ ሌሎቹን ሁሉ መፍታቱ፥ ሴቶችን ባል አልባ፥ ልጆችን አባት አልባ አድርጎ የሚፈጥረው ማኅበረ ሰባዊ ቀውስ ቀላል አይሆንም። ከማኅበረሰባዊው ቀውስ በጠለቀ ስነ ልቡናዊው ጉዳትም ቀላል አይሆንም። ስለዚህ ከብዙ ትህትና ጋር ይህ ትውልድ ያንን መንገድ መከተል አለበት ብለን አናምንም፡፡ ስለሆነም እነዚህ ሰዎች ወደ ጌታ ሲመጡ ነፍሳቸው በዳነችበት ድነት በማንነታቸው ቤተ ክርስቲያን ትቀበላቸው። እነዚህ ሰዎች ወደ ጌታ ሲመጡ እንደነበሩ መቀበል አለብን።
3. አስካሪ መጠጦች
ከአስርት ዓመታት በፊት የአልኮል መጠጦች ጉዳይ በቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ጥያቄ ሆኖ የሚቀርብም የሚያከራክርም ጉዳይ አልነበረም፡፡ አሁን ላይ ግን በቤተ-ክርስቲያን አከባቢ በይፋ ከሚነሱ ምግባራዊ ጉዳዮች አንዱ ሆኗል፡፡ “መጠጣት አለብን/ መጠጣት ሊፈቀድልን ይገባል” ሲሉ በግልጽ የተቀመጠን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክልከላ በተለይም አዲስ ኪዳናዊ ጥቅስ የሚጠይቁ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ እርግጥ ነው በሥነ-መለኮትና በመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ዘንድ ይህ ርዕሰ ጉዳይ ግራጫ ቀጠና (grey zone) በመባል የሚታወቅ ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡
ይህ የተባለበት ምክንያት አስካሪ መጠጦችን በተመለከተ አዲስ ኪዳን ነጭም ሆነ ጥቁር አድርጎ ስላላወራው ነው፡፡ እውነት ለመነጋገር በአዲስ ኪዳን ውስጥ አልኮል ወይም አስካሪ መጠጥ አትጠጡ የሚል ቀጥተኛ ጥቅስ የለንም፡፡ ይህ ግን እንጠጣ የሚል ፈቃድ መስጠቱ እንደሆነ ተደርጎ መቆጠር የለበትም፡፡ አልኮልን በተመለከተ ወደ 247 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንዳሉ የመጽሐፍ ቅዱስ አጥኚዎች ይነገራሉ፤ እነዚህ በአውንታዊ፣ በአሉታዊና በመካከል (neutral) በሆነ መልኩ የተጠቀሱ ናቸው፡፡
“እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ የማይነቀፍ… የማይሰክር.. ” 1 ጢሞ 3፥2፤3
“ብርቱ ጉዳት የሚያስከትለውን የወይን ጠጅ በመጠጣት አትስከሩ፡፡ በዚህ ፈንታ ግን ለክርስቲያን እንደሚገባ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላችሁ ሁኑ፡፡” ኤፌ 5፡18 (ሕ.ቃ.ት)
በወይን ጠጅ መስከር ማለት በወይን ጠጅ ቁጥጥር ስር መሆን ማለት ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ መሞላት በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር መሆን ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ቀዳሚው ለክፋት ተከታዩ ለመልካም ሕይወት የሚያበቁ መገዛቶችን አመልካቾች ናቸው፡፡
በወይን ጠጅ መስከር ገንዘብን ማባከን፣ አእምሮን ማባካን፣ ኅሊናን ማባከን፣ ትዳርን ማባከን፣ አካልን ማባከን፣ ወዳጅነትን ማባከን፣ ጓደኝነትን፣ ወዳጅነትን፣ ክብርን፣ ስምን፣ አገልግሎትን ወዘተ ማባከን ነው፡፡ ማባከን ደግሞ እንዴት ይፈቀዳል?
ስለሆነም የቤተ-ክርስቲያናችን አባላት አስካሪ መጠጦችን መጠጣት አይፈቀድላቸውም፡፡
“ስለ ሆድህና ስለ በሽታህ ብዛት ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ እንጂ፥ ወደ ፊት ውኃ ብቻ አትጠጣ።” 1 ጢሞ 5፥23
ይህ እንደ ደንብ ወይም መመሪያ የምንወስደው ሳይሆን፤ ለአንድ ጢሞቴዎስ ለተባለ መጋቢ ለሆድ ሕመም መድሃኒት ይሆነው እንደሁ ብሎ ነው ጳውሎስ ያቀረበው፡፡ ደግሞም ሐኪም የሆነው ሉቃስ በወቅቱ ከጳውሎስ ጋር መኖሩ የወይኑ መታዘዝ ለሕክምና ጉዳይ መሆኑን ያሳምነናል፡፡ ስለዚህ ይህ ጥቅስ አስካሪ መጠጦችን ለመጠጣት ምንም መነሻ አይሰጠንም፤ ዛሬ ሆዳችንን ቢያመን ከቁጥር በላይ የሆኑ ባሕላዊና ዘመናዊ መድሃኒቶች አሉልንና፡፡
“ሥጋን አለመብላት ወይንንም አለመጠጣት ወንድምህም የሚሰናከልበትን አለማድረግ መልካም ነው።” ሮሜ 14፥21
“ስለዚህም መብል ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ፥ ወንድሜን እንዳላሰናክለው ለዘላለም ከቶ ሥጋ አልበላም።” (1ቆሮ 8፡13)
አዲስ ኪዳናዊው የኑሮ መርህ ይኸው ነው፡፡
አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ-ክርስቲያን በእምነት አቋም አንቀጽ 10 ንዑስ አንቀጽ 3 አስካሪ መጠጦችን በተመለከተ ያለችውንና ሁላችንም የምንገዛበትን አንቀጽ እንመለከት፡፡
የአልኮልነት ይዘትና ጠባይ ያላቸው አስካሪ መጠጦች (ጠላ፣ ጠጅ፣ ቢራ፣ አረቄ እና ሌሎችም) የእግዚአብሔር ማደሪያ እንዲሆንና ለክብሩና ለሰዎች ሁሉ ጥቅም በአግባብ መገልገያ ሊሆንና እንደ ታማኝ በለዐደራ መየዝ የሚገባውን ሰውነት የሚጎዱና ማህበራዊ አንድነትን በየደረጃው የሚያናጉ ስለሆነ አማኞች መጠቀም እንደሌለባቸው ታምናለች፡፡ (1 ቆሮ 3፡16-17)
በተመሳሳይ መልኩ የአጥቢያ ቤተ-ክርስቲያናችን ውስጠ ደንብ አንቀጽ 30 ተራ ቁጥር 17 አስካሪ የአልኮል መጠጦች በቤተ-ክርስቲያናችን እንደማይፈቀዱ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡
ስለዚህ ይህንን ጉዳይ ስናጠቃልል፤ መምጣት ያለብን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርህን መሠረት ወዳደረገ ውይይት ነው፡፡ እንግዲህ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት አስካሪ መጠጦች የሚያስከትሉትን መዘዞች በመጥቀስ ከዚያ የራቅን እንድንሆን መክረውናል፡፡ እንደምናምንበት የተስማማነውን የእምነት አቋማችንንና ውስጠ ደንባችንንም እንደዚያው፡፡
ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት በማድረግ፣ አዲስ ኪዳናዊ የኑሮ መርህ በመከተል፣ የቤተ-ክርስቲያናችንን እምነት አቋም በመጋራትና የቆየውን የቤተ-ክርስቲያን ትውፊት በመከተል በአጥቢያ ቤተ-ክርስቲያናችን የአልኮል መጠጦች የተወገዙ መሆናቸውን እናረጋግጣለን፡፡ ቅድስቲቱን የክርስቶስ ማህበር አስካሪ መጠጥ ከሚያመጣው እርኩሰትና እድፍ ማዳን ደግሞ የቤተ-ክርስቲያን መሪዎች ኀላፊነት መሆኑንም እንዲሁ፡፡
በመሆኑም ማንኛውም የቤተ-ክርስቲያናችን አባላት አስካሪ መጠጦችን ጠጥተው የተገኙ እንደሆነ፤ በመጀመሪያ ቤተ-ክርስቲያን ጠርታ ምክርና ትምህርት ትሰጣቸዋለች፡፡ ከቤተ-ክርስቲያን ምክርና ትምህርት በኋላ ከድርጊታቸው የማይታቀቡና አስካሪ መጠጦችን በመጠጣት የሚቀጥሉ ከሆነ ግን ድርጊቱ በቤተ-ክርስቲያኒቱ ውስጠ ደንብ አንቀጽ ገጽ 50 መሠረት የቅድስና ጉድለቶች ውስጥ ስለሚመደብ ከድርጊታቸው እንድታረሙ ቅጣት ትሰጣቸዋለች፡፡ ነገር ግን የቤተ-ክርስቲያንን የተግሰጽ እርምጃ ወስደውም በኋለ በድርጊታቸው የሚቀጥሉ ከሆነ ግን ከቤተ-ክርስቲያን አባልነታቸው ይሠረዛሉ፡፡
4.በንግድ፣ በመንግስት ሥራና በሥልጣን አከባቢ የሚስተዋል የሥነ-ምግባር ጉድለትና ሙስና
መጽሐፍ ቅዱስ በ1ኛ ቆሮ 10፡31 “እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት።” በማለት ጠቅላላ የክርስቲያናዊ ሕይወት መርህ ይሰጠናል፡፡ አሁን የምንነጋገረው ከላይ በርዕሱ ስለ ተጠቀሱት ሦስት የሙያ በለቤቶች ስለሆነ በልይታ እርሱን የተመለከተ ሀሳባችንን እናንሳ፡፡
የመንግስት ሥራና ሥልጣን
ስለሆነም በቤተ-ክርስቲያናችን የሚገኙ የመንግስት ሥልጣን ላይ የተቀመጡ ሰዎች፤ ፍትሕ ማስፈን፣ በንጹሕ ልብ ማገልገል፣ በዚያ ቦታ ያስቀመጣቸው እግዚአብሔር እንደሆነ በማመን በለዐደራነታቸውን በትጋት ይወጡ ዘንድ ይገባቸዋል፡፡ ይህ ሳይሆን ሲቀር አባሎቿን የመገሰጽ፤ ስለ ፍትሕና ፍርድ ማስተማር ያለባት ቤተ-ክርስቲያን ናትና ድርሻዋን በጌታ ዘንድ በማያስጠይቃት ልክ መወጣት አለባት፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ-ክርስቲያን ስለ መንግስት ባለሥልጣናት በአንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 4 እና 5 ያሰፈረችው እንዲህ ነው፦
“የመንግስት ባለሥልጣናት እግዚአብሔር ቦታ በታማኝነትና ቅንነት የሚሠሩ (ሮሜ 13)፤ ለሚመሯቸው ሰዎች/ዜጎች በመልካም ሥነ ምግባር ምሳሌ የሚሆኑ (1 ጴጥ 2፡13-14)፣ ሥልጣናቸውን ተገን በማድረግ ለራሳቸው ሀብት ለማካበት የማይስገበገቡና ለሙስና ያልተሰጡ (ዘዳ 17፡6-17) መሆን እንዳለባቸው ታምናለች፡፡”
ከታችኛው የቀበሌ መዋቅር እስከ ዞንና ከዚያ በላይ ባለው መዋቅር ውስጥ የሚሰሩና የመንግስት ኀላፊነት ላይ የተቀመጡ የቤተ-ክርስቲያናችን አባላት በተሾሙበት ቦታ ሁሉ ከጉቦና መማለጃ፣ ከቤተሰባዊነትና አድልዖ፣ ከስንፍናና ሥራ መበደል ወዘተ ተላቅቀው ብርሃንና ጨው በመሆን በመልካም ሥነ-ምግባራቸው መታወቅ አለባቸው፡፡ በተለይም ደግሞ “ማማለጃን አትቀበል ማማለጃ የዓይናማዎችን ሰዎች ዓይን ያሳውራልና፥ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና።” (ዘጸ 23፡8) እንዲሁም “ንጉሥ በፍርድ አገሩን ያጸናል መማለጃ የሚወድድ ግን ያፈርሰዋል።” (ምሳ 29፡4) ይላልና ከጉቦና ጥቅመኝነት በመላቀቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ፣ ክርስቲያናዊና ሰብዓዊ ሥነ-ምግባራቸውን መጠበቅ አለባቸው፡፡ በተጨማሪም ጎሰኝነትን፤ ፍትሕ ማዛባትንና በደሃ አደጉ ላይ መፍረድን በተመለከተ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ መመላለስ አለባቸው፡፡
ነጋዴዎች
በ1ቆሮ 10፡31 መሠረት የንግድ ሥራም ለእግዚአብሔር ክብርን መምጣት አለበት፡፡ የንግድ ሥራ እግዚአብሔርን የሚያከብረው ከዚያ ሥራ ሰዎች ሲጠቀሙ ነው፡፡ ሁሉም የቤተ-ክርስቲያናችን አባላት የሆኑ ነጋዴዎች ሥራቸውን መሥራት ያለባቸው በሀገሩ ላይ ከሚታየውና ከሚሰማው እሮሮ በጸዳ መልኩ መሆን አለባት፡፡
ንግዳችን አምልኮአችን ነው፡፡ ንግዳችን ለእግዚአብሔር የምናቀርበው መስዋዕታችን ነው፡፡ ንግዳችን እግዚአብሔርን የምናሳወቅበት መድረካችን ወይም ፑልፒታችን ነው፡፡ የአዲስ ኪዳኑ አምልኮ የእሁድ ቀን አምልኮ ብቻ አይደለም፣ የአዲስ ኪዳኑ አምልኮ አሥራትና መባ መስጠት ብቻ አይደለ፣ የአዲስ ኪዳን አምልኮ ሁለንተናን ለእግዚአብሔር መቀደስ ነው፤ ሁለንተናን ለእግዚአብሔር መስዋዕት አድርጎ ማቅረብ ነው (ሮሜ 12፥1)፡፡
“አባይ ሚዛን በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ ነው እውነተኛ ሚዛን ግን ደስ ያሰኘዋል።” ምሳ 11፥1
“ሁለት ዓይነት ሚዛንና ሁለት ዓይነት መስፈሪያ፥ ሁለቱ በእግዚአብሔር ፊት ርኩሳን ናቸው።” ምሳ 20፥10
“እንዲህም ትላላችሁ፤ መስፈሪያውን በማሳነስ፤ ዋጋውን ከፍ በማድረግ፣ በሐሰተኛ ሚዛን በማጭበርበር እህል እንድንሸጥ የወር መባቻ መቼ ያበቃል? ስንዴም ለገበያ እንድናቀርብ፣ ሰንበት መቼ ያልፋል? ድሃውን በብር፣ ችግረኛውንም በጥንድ ጫማ እንገዛለን፤ ግርዱን እንኳ በስንዴ ዋጋ እንሸጣለን” አሞጽ 8፥5-6
ስለሆነም ክርስቲያን ነጋዴዎች ከአባይ ሚዛን፣ እግዚአብሔር ከማይደሰትበት መሰፈሪያ፣ በገበያ ውስጥ ከሚደረግ አሻጥር ራሳቸውን በመቀደስ፤ እግዚአብሔር በሰጣቸውን የንግድ ሥራ ከሁሉ በፊት እግዚአብሔርን ማክበር ቀጥሎም ሕብረተሰቡን መጥቀም አለባቸው፡፡ እንዲህ ይሆኑም ዘንድ ቤተ-ክርስቲያን ጠንካራና ተግባራዊ ስልጠና በመስጠት ነጋዴዎችን ማብቃትና መቅረጽ ይጠበቅባታል፡፡
የቤተ-ክርስቲያናችን አባላት የሆኑና በተለያየ አገልግሎት የሚሳተፉ የመንግስት ሠራተኞች፣ ባለሥልጣናት እና ነጋዴዎች ከሥራቸው ጋር የተያያዘ ክስ ሲመሰረትባቸው፤ ከአገልግሎታቸው ታግደው ጉዳያቸው ይታያል፡፡ ከቀረበባቸው ክስ ነጻ ሆነው ከተገኙ ወደ አገልግሎታቸው ይመለሳሉ፡፡ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ግን የሥነ-ሥርዓት እርምጃ ይወሰድባቸዋል፤ ካልተመለሱ ከቤተ-ክርስቲያን አባልነት ይሰረዛሉ፡፡
5. ከባህል ጋር ተያይዞ የሚመጣ ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ ልምምዶች
የክርስቶስ ብቸኛ ቤዛዊ ሥራ ዋጅቶናል ስንል፣ ከኀጢአትና ባዕድ አምልኮ ጋር ትሥሥር ካለው ከየትኛው ባሕል ጭምር ማለታችን ነው። ባሕል ስንል፣ የማኅበራዊ ስብስባችን የጋራ ፋይዳ ነው። ይህም እምነታችንን፣ ዕሴቶቻችን፣ ቋንቋችንን፣ ርእዮተ ዓለማችንን፣ ሙዚቃ፣ ምግብ፣ ጋብቻ፣ የወንድ፣ የሴት የልጆች እንዲሁም ቤተ ሰባዊ ድርሻና ኀላፊነቶች በሙሉ ያጠቃለለ ማንነት ነው። ክርስቶስ በእነዚህ ፋይዳዎች ላይ ደባል ሆኖ አይደለም ያዳነን! ይልቁንም፣ የእርሱ ሕዝብ ያደረገን እነዚህን ማንነቶች ሁሉ በመለወጥ፣ በእርሱ ውስጥ በተገኘው ማንነት ለክብሩ እንድንኖርለት ነው። በአንድ ጊዜ ለክርስቶስም ከወንጌል ጋር ተቃርኖ ላለውም ባሕል መኖር አንችልም! በአንድ ጊዜ ለክርስቶስም ለሌላ ባህላዊ ክዋኔም መሰዋዕት ማቅረብ አንችልም፡፡ በአንድ ጊዜ ክርስቶስንም ማንነታችንንም አንደኛና ቀዳሚ ማድረግ አንችልም፡፡ በዚህ አግባብነት ኢሬቻ ባሕል ብቻ ሳይሆን ሃይማኖትም ነው። በየትኛውም መልኩ (ቢያንስ እንደ ወንጌላውያን አማኞች) ኅሊናችን ላይ ጫና ሳናደርግ፣ ሁለቱን መለያያት አንችልም። ይኸው እውነት በኢሬቻ ብቻ ላይ ሳይሆን፣ በሲዳማው ፍቼ ጨምበላላ፣ በወላይታው ጊፋታ፣ በሀዲያው ያሆዴ፣ በከምባታው መሳላ እንዲሁም በሌሎች ባሕላዊ በዓላት ላይ ባሉት ዕይታዎች ላይም አግባብነት አለው።
ወንጌል አጥላይ እውነት ነው፤ ክርስቶስም ደባል የማይፈልግ ብቸኛ ጌታ ነው፡፡ እግዚአብሔር እስራኤላዊያንን ጠዖታትን እንዳያመልኩ፣ ሌሎች አማልክት ለራሳቸው እንዳይሠሩ ከከለከለ፤ ዛሬ እኛን ለእኛ በልጁ ደም ለዋጀን፣ ዋጋ ከፍሎ ነጻ ላወጣን ሕዝቦቹ ቅይጥ አምልኮን የሚፈቅድበት፤ በእኛ ዘንድ ካሉ በርካታ አምልክት እንደ አንዱ ተቆጥሮ መሰንበት የሚፈልግበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ እነዚህ ባሕላዊ ክዋኔዎች ክርስቶስ በደሙ የሠራውን የማዳን ሥራ የሚያፈርሱ፣ ከነገድና ቋንቋ የዋጀንን የክርስቶስን ሥራ የሚቃወሙ፣ ክርስቶስ ያፈረሰውን የጥል ግድግዳ የሚገነቡ፤ ሰዎች በክርስቶስ ሳይሆን በጎሳቸው እንዲመኩ የሚያደርጉ፣ የቤተ-ክርስቲያንን አንድነት የሚሸረሽሩ፣ የወንጌልን አንድነት የመንፈስን አንድነት የሚቦረቡሩ ናቸው፡፡
ስለሆነም ማንኛውም የቤተ-ክርስቲያናችን አባል በየትኛውም እግዚአብሔር በማይከበርበትና አማኞች በማይታነጹበት ባህል ነክ ነገሮች መሳተፍ የለበትም፡፡ ይህንን ሲያደርግ የሚገኝ ሰው የክርስቶስን ደም ያክፋፋ፣ የመስቀሉንም ሥራ የናቀ ነውና በቤተ-ክርስቲያን ምክርና ግሳጼ ይሰጠዋል፡፡ ከቤተ-ክርስቲያን ምክርና ግሳጼ በኋላም ከተግባሩ የማይመለስ ከሆነ ግን ከቅድስት ቤተ-ክርስቲያን ጋር ምንም ዓይነት ሕብረት አይኖረውም ከአባልነት ይሰረዛል፡፡
የመስቀል በዓል
ኢትዮጵያ ውስጥ የመስቀል በዓል ሁለት ገጽታ አለው፡፡ አንዱ ገጽታው ሐይማኖታዊ ሲሆን ይህ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን የሚከበረው ነው፡፡ ሌላኛውና እኛ ባለንበት አካባቢ የሚከበረው የመስቀል በዓል ሐይማኖታዊ ሳይሆን ባሕላዊ ገጽታው ነው፡፡ አንድ ማኅበረሰብ ሃይማኖት ኖሮትም የባህል ወይም የትውፊት እስረኛ ሊሆን ይችላል። በሃይማኖትና ባህል መስተጋብር ሦስት ዓይነት አቀባበሎች ወይም መቀባበሎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ እንደ ሕዝብና እንደ ዜጋ፡፡
አንደኛ፦ ባህላችንን ከማክበራችን የተነሣ ከእምነታችንም የምናስቀድም ልንሆን እንችላለን፤
ሁለተኛ፦ የምናመቻምች እና በባህሉ የምንወሰድ ወይም ሁለቱንም ልናስደስት የምንታገል ልንሆን እንችላለን፤ ወይም
ሦስተኛ፦ ባህሉ ለእምነት መገዛት አለበት የምንል ሃይማኖተኞች ልንሆን እንችላለን፡፡ መስቀልን በተመለከተ ሁለተኛውና ሦስተኛ ላይ ያለን ይመስላል፡፡ አመቻማቾች ከሆንን ሰነበተ፡፡
መስቀል ስሙ አዲስ ኪዳናዊ ቢሆም በዓሉና አከባበሩ ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም። የአዲስ ኪዳኑ መስቀል የሚሸከሙት የደቀ መዝሙርነት መታወቂያ እንጂ የሚያከብሩት በዓል ሆኖም አያውቅም። ክርስቲያኖች በነዚህ በዓላት ሲሳተፉ ምን እያደረጉ መሆናቸውን በውል ማወቅ ይኖርባቸዋል።
ከላይ እንደተመለከትነው የመስቀል በዓልና አከባበሩ ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ተጽዕኖ እያስከተለ ያለ ጎጂ ባህል ስለሆነ ቤተ-ክርስቲያን ምዕመኖቿን ይህንን እንዳያደርጉ ማዘዝ ትችላለች፤ ይህንንም ትዕዛዟን የማይቀበል አባሏን መቅጣት ትችላለች፡፡
ስለዚህ ማንኛውም የቤተ-ክርስቲያናችን አባል የመስቀል በዓልን ማክበር የለበትም፡፡ በተጨማሪም አማኝ ያልሆነ ሆነ አማኝ የሆነ የቤተሰብ አባል ያላቸው የቤተ-ክርስቲያናችን አባላት የመስቀል በዓልን በተመለከተ ዘመዶቻቸውን በገንዘብ መደገፍ ይችላሉ ይሆናል እንጂ እነርሱ ሄደውም ሆነ ሥጋውን ወደ ከተማ አስመጥተው የመስቀልን በዓል ማክበር አይችሉም፡፡
ጥሎሽ
ጥሎሽን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ልምምዶች ስላሉና ለሴቷ ወላጆች ስጦታ ማቅረብ የተለመደ ስለሆነ አቅምን ባገናዘበ መልኩ ማንኛውም የቤተ-ክርስቲያናችን አባል የሆነ ለማግባት የተዘጋጀ ወጣትና ቤተሰቦቹ ለሴቷ ወላጆች የሚሰጡት ጥሎሽ ከአሥር ሺ (10000) ብር ያልበለጠ እንዲሆን ወስነናል፡፡ ስለዚህ ማንኛውም የቤተ-ክርስቲያናችን አባል ወጣት ይህንን ደንብ ማክበር ግዴታው ሲሆን ይህንን መመሪያ የሚጥሱና ያንንም ማድረጋቸው በማስረጃ ከተረጋገጠ በቤተ-ክርስቲያን የእርምት እርምጃ ይወሰድባቸዋል፡፡
መልስ
የቤተ-ክርስቲያናችን አባላት የሆኑ ተጋቢዎች መልስ ተጠርተው ሲሄዱ ስጦታ መስጠት የሚችሉት ለወላጆች እና አያቶች በሕይወት ካሉ ለአያቶች ብቻ እንዲሆን ወስነናል፡፡ በመልስ ፕሮግራም ከወላጆች ውጪ ለሌሎች ቤተ ዘመዶች ስጦታ መስጠት የተከለከለ ነው፡፡
የሠርግ ድግስ
ሰዎች ያለ ቤተ-ክርስቲያን ሥርዓት እንዲያገቡ ከሚያደርጉ ምክንያቶች ቀዳሚው ምክንያት የሠርግ ሥርዓት፣ ጥሎሽና ድግስ ፍራቻ ነው፤ እነዚህ ወጪዎች ደግሞ ለወጣቶችና ለቤተሰቦቻቸው እጅግ ፈተና ሆኗል፡፡ በኮሮና ወቅት የተደረጉ ሰርጎች ብዛት ለሰው ከሰርግ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ወጪዎች እንዴት አሳሳቢ እንደነበሩና፤ ብዙ ወጣቶች ያንን ሰው እንዲሰበሰብ የልተፈቀደበትን ጊዜ በመጠቀም ጋብቻ መመስረታቸው አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አሁንም ሰርግም ላይ የሚወጡ ወጭዎች እንድቀነሱና ሰዎች ከሠርጉ በላይ በሚመሰርቱት ጋብቻ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ማስተማር፡፡ በሰርግ ፕ/ም ስጦታ የሚቀርብ ከሆነም ለእናት እና አባት፤ አባት ከሌለ ደግሞ ለታላቅ ወንድም ብቻ ነው መሰጠት ያለበት፤ ከዘፍ 24፡54 የምናገኘው መርህ ይህ ነውና፡፡ ከዚህ ወጪ በሠርግ ድግስና በስጦታ ሰበብ አዳዲስ ተጋቢዎች ኑሮአቸው መናጋቱን ቤተ-ክርስቲያን አትፈቅድም፡፡ ምክራችን ወላጆችም ቢሆኑ ለልጆቻቸው የወደፊት ኑሮ አስፈላጊውን ነገር ይስጡ እንጂ ሰዎችን ለማስደመም ድግስ ባያዘጋጁ የሚል ነው፡፡
ባሕላዊ ዳኞች
ቤተ-ክርስቲያን ሰዎች በቤተሰባቸው አካባቢ የሚከሰቱ የተለያዩ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚጠቀሙትን የቤተሰብን ዳኝነት አትቃወምም፡፡ ነገር ግን ባህልን መሠረት አድርጎ በድግስ የሚጸድቅን ማንኛውንም ባሕላዊ ሹመት ለምሳሌ ገራድ፣ በርከፈት፣ አስማቼ፣ አበጋዝና የመሳሰሉትን ቤተ-ክርስቲያን አትቀበልም፤ በድግሱም የቤተ-ክርስቲያን አባላት መሳተፍ የለባቸውም፡፡ ይህንን ሹመት የተቀበሉ የቤተ-ክርስቲያናችን አባላት ካሉ አባል ሆነው መኖር ይችላሉ፤ ነገር ግን ከቡድን እስከ ቤተ-ክርስቲያን ድረስ በማንኛውም አገልግሎት መሳተፍ አይችሉም፡፡ የዛ ቤተሰብ አባል የሆነ ሰው መዋጮ ማውጣት አይፈቀድለትም፤ ይህንን እንዳደረገ በቤተ-ክርስቲያን ከታወቀ ይቀጣል፡፡
ቤተ-ክርስቲያን የባህል ዳኞች የሆኑ አባላቶቿ እውነተኛ ፍትሕ እንዲሰጡ፣ እውነተኛ ፍርድ እንዲፈርዱ፣ ከሙስናና ተማኝነት ማጣት የራቁ እንዲሆኑ ታስተምራለች።
እነዚህም ሰዎች ይህንን ተላልፈው ሲገኙ፤ በመንግስት ባለሥልጣናት ላይ እንዲወሰድ ያልነው የእርምት እርምጃ ይወሰድባቸዋል፡፡
ሆሳዕና እናት ቃ/ሕ/ቤ/ክ
ነሀሴ 2015 ዓ.ም