19/04/2025
የብጹዕ አቡነ ሕርያቆስ የደቡብና ምዕራብ አፍሪካ የሀድያና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መልእክት
"ምንተ ተኀሥሣሁ ለሕያው ምስለ ምውታን"
"ሕያውን ከሙታን ጋራ ስለምን ትፈልጉታላችሁ"
ሉቃስ 24÷5
በደቡብና ምዕራብ አፍሪካ በሀድያና ስልጤ አህጉረ ስብከት እንዲሁም በመላው ዓለም የምትገኙ የመንፈስ ልጆቻችን እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ በሰላም አደረሳችሁ።
የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምን ከሲኦል ወደ ገነት ይመልሰው ዘንድ ደግሞም መከራ ነፍሳችንን ያጠፋ ዘንድ በዓውደ ቀራንዮ ከተሰቀለ በኋላ ክቡራን ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በሐዲስ መቃብር በቀበሩት ጊዜ የእውነት ጠላቶች አይሁድ "እውነትን ቀበርነው" ብለው ቢደሰቱም እውነት የሆነውን ክርስቶስን መቃብር እንደማያሸንፈው ስለሚያውቁ ግን ጠባቂዎችን አኑረው ነበር።
ሞትና መቃብር የማያሸንፈው ጠባቂ የማያቆመው ኃያሉ ክርስቶስ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ተነሳ። የኛ ተስፋ ትንሣኤም በትንሣኤው ተረጋገጠ። ሟቾች ሳይሆን ሕያዋን መሆናችንን ሰበከልን። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ "ፋሲካ ብሂል ማዕዶት ብሂል በዘቦቱ አዶነ እሞት ውስተ ሕይወት" እንዳለው ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከሲኦል ወደ ገነት ፣ ከግዞት ወደ ነጻነት የመሸጋገራችን ብርሀነ ትንሣኤው በዓለም ሁሉ ተንቦገቦገ።
ውድ የመንፈስ ልጆቻችን
መልአኩ በመቃብሩ ሽቱ ሊቀቡ ለመጡት ሴቶች "ሕያውን ከሙታን ጋር ለምን ትፈልጉታላችሁ?" እንዳላቸው እኛም ዛሬ ይህን የትንሣኤ ጌታ ወዴት እየፈለግነው ነው? ተስፋ ትንሣኤን ተስፋ በማድረግና በመልካም ሥራ ወይስ በዓለም ባለ ሁካታና ጫጫታ? ነዳያንን በማሰብ ወይስ ቁሳዊ ምቾትን በመፈለግ? ሥጋ ወደሙን በመቀበል ወይስ ምድራዊ መብል መጠጥን በማብዛት? በዓለማዊ ነገር ውስጥ ትንሣኤውን ማክበር ሕያዉን ከሙታን መንደር መፈለግ ነውና ትንሣኤን በትንሣኤው ንጉስ መንገድ በመጓዝ ልናከብረው ይገባናል።
ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ተነስቷል፤ መቃብሩ ባዶ ነው፤ ሕይወትን የሚሰጥ አምላክ በኃይልና በሥልጣን ሞትን ገድሎ በሞት ላይ አሸናፊዎች እንድንሆን ያደረገን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተመሰገነ ይሁን።
እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ።
አባ ሕርያቆስ
የደቡብና ምዕራብ አፍሪካ የሀድያና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ