Debre Medanit Medhane Alem Page

Debre Medanit Medhane Alem Page This a way to keep everyone updated and a means to communicate. Our church is a place for spiritual healing and renewal.

04/10/2026
03/30/2026

የሚሰገድባቸውና የማይሰገድባቸው ጊዜያት
==================================
ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በሃይማኖት ይዘትም (Content of Faith) ሆነ በሃይማኖት ሥርዐት (Expression of Faith) ፍጽምት ነች፡፡ የሃይማኖት ይዘቷ (ዶግማዋ) ይህ ይቀረዋል ተብሎ የማይጨመርበት በእግዚአብሔር አንድ ጊዜ ፍጹም ሆኖ ለቅዱሳን የተሰጠ ነው፡፡ (ይሁዳ 3) እግዚአብሔርን የምታመልክበት ሥርዐትም እንዲሁ መንፈስ ቅዱስ በመራቸው ቅዱሳን ሰዎች የተቀነነ ቅዱስ ሥርዐት ነው፡፡ ጊዜንና ቦታን በመዋጀትም (ግንዛቤ ውስጥ በማስገባትም) እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሥርዐትን እንድትሠራ ቀኖና አለ፡፡

ከዚህ አንጻር ስግደትንም በተመለከተ መች ሊሰገድ እንደሚገባና መች እንደማይሰገድ ሥርዐትን ሠርታልናለች እንጂ እንዲሁ በዘፈቀደ እንዲተገበር ቸል አላለችም፡፡



†† ሀ. የሚሰገድባቸው ጊዜያት ††

የሚከተሉት እንዲሰገድባቸው የታዘዙ ጊዜያት ናቸው፤
† 1ኛ. በጸሎት ጊዜ ስግደትን ከሚያነሣ አንቀጽ ሲደርስ †
ፍትሐ ነገሥቱ እንዲህ ይላል፡- “የሚሰገድባቸው ጊዜያቶችና ቁጥሮች በቤተ ክርስቲያን ተጽፈዋል፡፡ የሚጸልይ ሰው በጸሎት ጊዜ ስግደትን ከሚያነሣ አንቀጽ ሲደርስ ለልዑል እግዚአብሔር ይስገድ” ፍት. መን. አን. 14 ቁ. 536
ለጸሎት በምንዘጋጅበት ጊዜ ከሚያስፈልጉ 6 ነገሮችም አንዱ ስግደት መሆኑን ፍትሐ ነገሥቱ ከላይ በተጠቀሰው አንቀጽ ከቁጥር 528-535 ድረስ ይገልፃል፡፡ ስለዚህ በጸሎት ጊዜ ስግደትን የሚያነሣ ንባብ ስናገኝ እንዲሁም ስግደትን የሚያነሣ ንባብ ባናገኝም መስገድ ከስድስቱ የጸሎት ይዘቶች አንዱ ነውና መስገድ ይገባል፡፡

† 2ኛ. በጾም ወራት †

ጾም የሚቀደሰው በጸሎት ፣ በምጽዋት ፣ በዕንባና በስግደት ነው፡፡ ስለዚህ በጾም ወራት ጾማችንን ቅዱሱ የሚቀበለው ቅዱስ ጾም ለማድረግ መስገድ ተገቢ ነው፡፡

† 3ኛ. በሰሙነ ሕማማት †

ሰሙነ ሕማማት በጾም ፣ በጸሎት ፣ በስግደት የሚከበር ልዩ በዓል ነው፡፡ ጾሙም ስግደቱም ጸሎቱም የሚበረታበት የመጨረሻው የዐቢይ ጾም ሳምንት ነው፡፡ (ስለ ሰሙነ ሕማማትና ስግደት እግዚአብሔር ቢፈቅድ በቀጣይ ክፍል በዝርዝር እንጽፋለን)

† 4ኛ. በቅዳሴ ጊዜ †

በቅዳሴ ጊዜ መስገድ እንደሚገባ “ስግዱ ለእግዚአብሔር በፍርሐት” ፣ “ንስግድ” ፣ “አድንኑ አርእስቲክሙ ቅድመ እግዚአብሔር አምላክነ” ፣ “በንስሐ ውስጥ ያላችሁ ራሳችሁን ዝቅ ዝቅ አድርጉ” እና የመሳሰሉት የቅዳሴ ይዘቶችና ምንባቦች (ዜማዎች) ምስክር ናቸው፡፡ እዚህ ጋ ቅዳሴ ምሥጢርነቱና አምልኮነቱ ሲገለፅ አንዱ ይዘቱ ስግደት መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

† 5ኛ. በንስሐ ጊዜ †

“በንስሐ ውስጥ ያላችሁ ራሳችሁን ዝቅ ዝቅ አድርጉ” የሚለው ንባብ በንስሐ ውስጥ መስገድ እንደሚገባ የሚያመለክት ነው፡፡ (ራስን ዝቅ በማድረግ መስገድ በክፍል አንድ እንዳየነው አድንኖ እንደሚባል ልብ ይሏል፤) ሌላው ሊታወስ የሚገባው ጉዳይ የንስሐ አባቶች በንስሐ ውስጥ ላሉ ልጆቻቸው ስግደትን ቀኖና አድርገው መስጠታቸው ነው፡፡ ስለዚህ ስግደት የንስሐ ሕይወት አንዱ አካል ነው፡፡

† 6ኛ. ስንሳለም †

ቤተ ክርስቲያንን ስንሳለም መስገድ ተገቢ ነው፡፡ ስንሳለም እንዲህ እያልን ነው፡-
“ሰላም ለኪ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፣ አምሳለ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት፣ ማኅደረ መለኮት፣ ምስኣል ወምስጋድ ወመሥተሥርየ ኃጢአት”
ስንሳለም በምንናገረው አጭር ጸሎት ውስጥ “...ምስአል ወምስጋድ” ማለታችን መስገድ እንደሚገባን የሚጠቁም ነው፡፡ መስቀልን ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ፣ ቅዱሳት ሥዕላትን ፣ ቅዱሳት ቦታዎችን ፣ ...ወዘተ ስንሳለም በተመሳሳይ መልኩ መስገድ ተገቢ ነው፡፡



†† ለ. የማይሰገድባቸው ጊዜያት ††

የሚሰገድባቸው ጊዜያት እንዳሉት ሁሉ የማይሰገድባቸው ጊዜያትም አሉ፡፡ እነዚህ ስግደት የተገዘተባቸው ጊዜያት የሚከተሉት ናቸው፡፡

† 1ኛ. በዕለተ እሑድ †

ከአልቦ ነገር ወይም ከምንም (ex-nihilo – from nothingness) የተፈጠረ ፍጥረት ሁሉ ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ ጠፍቶ ወደ ምንምነት ሲቀየር ከማይጠፉ ከአምስቱ ፍጥረታት አንዷ ሰንበት ናት፡፡ ጌታ የተነሣባት ፣ ዳግምም የሚመጣባት ዕለት ናት፡፡ በዚህና በሌሎች ምክንያቶችም ሰንበተ ክርስቲያን እሑድ በዓል ነች፡፡ ስለዚህ በዕለተ እሑድ መስገድ የተከለከለ ነው፡፡

ይህንን ፍትሐ ነገሥቱ እንዲህ በማለት ይገልፀዋል፡- “ከአድንኖና ከአስተብርኮ በቀር እስከ ምድር መስገድን የሚተዉባቸው የታወቁ ጊዜያቶች እነዚህ ናቸው፡፡ ኒቅያ 20፣ በዕለተ እሑድና በበዓለ ሃምሳ ወራት፣...” ፍት.መን. አን. 14 ቁ. 537
ይህንን ይበልጥ ሲያጸናው በሰንበታትና በበዓላት አንቀጹ እንዲህ ሲል ደግሞታል፡- “በእሑድና በተከበሩት በዓላት ቀን ስግደት አይገባም፤ እነዚህ የደስታ ቀኖች ናቸውና” ፍት. መን. አን. 19 ቁ. 715

† 2ኛ. በበዓለ ሃምሳ ወራት †

በዓለ ሃምሳ የፍስሐና የሰላም ጊዜ ነው፡፡ ስሙ እንደሚጠቁመው ሃምሳውም ቀን በሙሉ በዓል ነው፡፡ በዓል ስለሆነም እንደ ፋሲካና እንደ ልደት እንበላበታለን እንጂ ረቡዕና አርብ ቢሆን እንኳን አንጾምበትም፡፡ በበዓልነቱ ጾም እንደተሻረበት ስግደትም እንዲሁ ይሻርበታል፡፡ ከላይ እንዳየነው ፍትሐ ነገሥቱም በፍት.መን. አን. 14 ቁ. 537 በእሑድ መስገድን ሲከለክል በበዓለ ሃምሳም እንዲሁ ከልክሏል፡፡

† 3ኛ. በጌታችን በዓላት †

ፍትሐ ነገሥቱ “በእሑድና በተከበሩት በዓላት ቀን ስግደት አይገባም፤ እነዚህ የደስታ ቀኖች ናቸውና” (ፍት.መን. አን. 19 ቁ. 715) ካለ በኋላ “የተከበሩት በዓላት” ያላቸው የትኞቹን እንደሆነ ሲዘረዝር ትስብእት/ጽንሰት ፣ ልደት ፣ ጥምቀት ፣ ሆሣዕና ፣ ትንሣኤ ፣ ዕርገት ፣ በዓለ ሃምሳ ፣ ደብረ ታቦር በማለት ከጌታ ዘጠኝ ዐበይት በዓላት 8ቱን ይገልፃል፡፡ ሳይገለፅ የቀረው ስቅለት ነው፤ ያልተገለፀበትም ምክንያት በስቅለት ስግደት ስለማይከለከል ነው፡፡ (ይህንን በክፍል ሦስት በዝርዝር ለማየት እንሞክራለን) ስለዚህ ከስቅለት በቀር በጌታ ዐበይት በዓላት (በተቀሩት በ8ቱ) ስግደት የተከለከለ ነው፡፡

ፍትሐ ነገሥቱ ይህንን ሲያጸና በአንቀጽ 14 እንዲህ ብሏል፡- “መስገድን የሚተዉባቸው የታወቁ በዓላት እነዚህ ናቸው.... ኒቅያ 32፣ በጌታችን በዓላትና በእመቤታችን በዓላት” ፍት.መን. አን. 14 ቁ. 536-537፡፡

† 4ኛ. የእመቤታችን በዓላት †

ከላይ ያየነው የፍትሐ ነገሥት ንባብ በፍት. መን. አን. 14 ቁ. 536-537 ድረስ በጌታ በዓላት መስገድ እንደተከለከለው ሁሉ በእመቤታችን በዓላትም መከልከሉን ይጠቁመናል፡፡ ይህንን ሥርዐት እንዴት እንደምንተገብርና የማይሰገድበት የእመቤታችን በዓል የትኛው እንደሆነ ከታች በ6ኛ ቁጥር እንመለከተዋለን፡፡

† 5ኛ. ሥጋውንና ደሙን ከተቀበሉ በኋላ †

የሥርዐት ምንጫችን የሆነው ፍትሐ ነገሥት አሁንም በዚህ ዙሪያ እንዲህ ብሏል፡- “መስገድን የሚተዉባቸው የታወቁ በዓላት እነዚህ ናቸው... ሥጋውንና ደሙን ከተቀበሉ በኋላ” ይላል፡፡ ፍት. መን. አን. 14 ቁ. 536-537፡፡

ሥጋውንና ደሙን ከተቀበልን በኋላ ከሚሰገድለት እንጂ ከማይሰግደው ጋር አንድ መሆናችንን ለማጠየቅና ለቅዱስ ሥጋውና ለክቡር ደሙ ክብር ስንል ዝቅ ብለን አንሰግድም፡፡

† 6ኛ. በ12 ፣ በ21 ፣ በ29 †

ከሌሎቹ የግዝት ወቅቶች ይልቅ እነዚህ ዕለታት በአብዛኛው ምዕመን የታወቁ ናቸው፡፡ ዕለታቱን የግዝት ያደረገው ሥርዐት ምንጭ ከላይ ያየናቸው የፍትሐ ነገሥት ምንባባት ናቸው፡፡

በ29 በዓለ ወልድ ብለን የጌታን በዓላት እንደምናስብ ይታወቃል፡፡ በፍትሐ ነገሥትም የጌታችን በዓላት እንደማይሰገድባቸው ሲጠቀስ ምንም እንኳን በአንቀጽ 19 ከ9ኙ ዐበይት በዓላት ስምንቱን ቢገልፅም አንቀፅ 14 ግን ከላይ እንዳስነበብነው “የጌታችን በዓላት የእመቤታችን በዓላት” ብሎ ማለፉን መርጧል፡፡

የጌታችን በዓላት የተባሉ ከ9ኙ የጌታ በዓላት ውጪ 9 ንዑሳን በዓላትም አሉ፡፡ እነዚህም ስብከት ፣ ብርሃን ፣ ኖላዊ ፣ ግዝረት ፣ ልደተ ስምዖን ፣ ቃና ዘገሊላ ፣ ደብረ ዘይት ፣ ጌና ፣ መስቀል ናቸው፡፡ ፍትሐ ነገሥቱ በእነዚህ ዙሪያ የዘረዘረው ግልፅ ነገር የለም፡፡ ሆኖም የጌታ በዓላት ስለሆኑና በጌታ በዓላት ደግሞ ስግደት ስለተከለከለ ፣ አባቶቻችን እነዚህን የጌታ (የወልድ) በዓላት በአንድነት ወር በገባ በ29 በዓለ ወልድ ብለን እንድናስብና፣ ዕለቱም ስለ በዓላቱ የግዝት ዕለት እንዲሆን የተደረገ ይመስላል፡፡ ስለዚህ አይሰገድበትም፡፡

ከዘጠኙ ዐበይትና ከዘጠኙ ንዑሳን በዓላት ውጪ ሰሙነ ሕማማትና ሰሙነ ትንሣኤም የጌታ በዓላት በመባል ይታወቃሉ፡፡ ሰሙነ ሕማማት በስግደት እንዲከበር ቤተ ክርስቲያን ታዛለች፡፡ (ይህን በዝርዝር በክፍል 3 እናያለን)፡፡ ሰሙነ ትንሣኤን ግን ከሰሙነ ሕማማት በተለየ ሁኔታ እናከብረዋለን፡፡ ሰሙነ ትንሣኤ የሚባለው ከትንሣኤ በኋላ ያለው እስከ ዳግም ትንሣኤ ያሉትን ቀናት የያዘው ሳምንት ነው፡፡ ሰሙነ ሕማማትን በፍጹም ሐዘን ፣ በጾም ፣ በስግደት እንዳከበርበው ሁሉ ሰሙነ ትንሣኤን ደግሞ በፍጹም ደስታ እንድናከብረው ትዕዛዝ አለ፡፡ ስለዚህ ሰሙነ ሕማማትን ስቅለትን በዋናነት በማሰብ በብዙ ስግደት ስናከብር ሰሙነ ትንሣኤን ደግሞ ትንሣኤውን በማሰብ በብዙ ደስታ ካለ ስግደት እናከብረዋለን፡፡

ፍትሐ ነገሥቱ የማይሰገድባቸውን ጊዜያት ሲጠቅስ “የጌታችን በዓላት የእመቤታችን በዓላት” ማለቱን ከላይ ጠቅሰናል፡፡ የጌታን ንዑሳን በዓላት ወር በገባ በ29 አስበን እንደማንሰግደው ሁሉ የእመቤታችንንም በዓላት በ21 አስበን አንሰግድም፡፡ ስለዚህ ወር በገባ በ21 ሁሌም የግዝት በዓል ነው፤ አይሰገድበትም፡፡
12 የቅዱስ ሚካኤል በዓል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የቅዱስ ሚካኤል በዓል ከሌሎች የመላእክት በዓላት ተለይቶ መከበሩ ለምንድነው ቢሉ “የቅዱስ ሚካኤል በዓል መላእክትን ወክሎ ወርኃዊ ሆኖ እንዲከበር ታዟል” (በዓላት ፣ ዲ.ን. ብርሃኑ አድማስ ፣ ገጽ 124)፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን በ12 እንዳይሰገድና እንደ ታላላቅ በዓላት በደስታ እንዲከበር ሥርዐትን ሠርታለች፡፡

የሚሰገድባቸውና የማይሰገድባቸው ዕለታት ሲገጥሙ ምን ይደረጋል? ለምሳሌ የግዝት በዓላት በሰሙነ ሕማማት ቢውሉ ምን ይደረጋል? የእነዚህን መልስ የያዘውንና ሰሙነ ሕማማት ላይ ያተኮረውን የስግደት ጽሑፍ በቀጣይ ክፍል ይጠብቁ፡፡

ረድዔተ እግዚአብሔር አይለየን፡፡

ዲ/ን ሕሊና በለጠ

01/07/2026

የደብረ መድኃኒት መድኃኔ ዓለም ካቴድራል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ኮሎምበስ ኦሃዮ የገና ዋዜማ የቀጥታ ስርጭት፣ዜል 6143014554

11/13/2025
07/06/2025

Address

4295 East Broad Street
Whitehall, OH
43213

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Debre Medanit Medhane Alem Page posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share