Philologus66

Philologus66 ይህ ገጽ ወንጌላዊና ኃላፋዊውን የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ በአማርኛ ቋንቋ ያስተዋውቃል። This page introduces the evangelical and preterist eschatological doctrine in Amhric audience.

ባወጣው ባወርደው አልገባህ፣ አልከሰትልህ ያለኝ አንድ ነገር፣ ኢየሱስ እንደተናገረው በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ይጠባበቁት ለነበሩ ለትውልዱ ዘመን አማኞች በክብር እንደተመለሰ፣ በዚያው...
02/02/2025

ባወጣው ባወርደው አልገባህ፣ አልከሰትልህ ያለኝ አንድ ነገር፣ ኢየሱስ እንደተናገረው በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ይጠባበቁት ለነበሩ ለትውልዱ ዘመን አማኞች በክብር እንደተመለሰ፣ በዚያው ዘመን አመጸኛይቱ እስራኤል ላይም በእሳት ፍርድ እንደተገለጠ፣ የዳግመኛ ምጽአቱም ተስፋ ያኔ እንደተፈጸመ መቀበል የሚቸግራቸው ወንጌል አማኝ ክርስቲያኖች በእውነት የሚያነቡት መጽሐፍ ቅዱስን ነው፣ ወይስ 😂መጽሐፈ ዶሮ😂?

ፕሪቴሪዝም፣ የተፈጸመው ወንጌል ቅዱሳት መጻህፍት ላይ ብቻ ቆሞ እምነቱን መከላከልና ክህደትን መፋለም የሚችል የነጠረ ትምህርት ነው። ሊሰሙትና ሊያውቁት ለሚወዱ ትንቢት ሁሉ አንድም ሳይቀር መፈጸሙን እያበሰረ ለቅዱሳን ሁሉ ታላቅ መጽናናትን ይሰጣል። ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተስፋ ቃሉ ዳግም ተመልሷል የሚለው እምነታችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንደሆነ በብዙ የቃሉ ምስክርነት አረጋግጠናል። ታሪክም ይህ ኢየሱስ ተመልሶ መጥቷል የሚለውን እምነታችንን በብዙ ማስረጃ ይደግፋል። እኛም ቃሉን ዋቢ አድርገን ይህንን ለመመስከር አንታክትም። ሰዎች ሁሉ ይህንን እውነት ያውቁ ዘንድ አይናቸው እንዲከፈትና ያየነውን አይተው ደስ እንዲላቸው፣ ክርስትናንም በዚህ በተፈጸመ ወንጌል ብርሃን እንዲመላለሱበት፣ ዳግመኛ ምጽአቱም ለክርስቲያኖች ሁሉ ያስገኘውን የድል አድራጊነት ህይወት እንዲለማመዱ ከማድረግ በቀር ሌላ መሻት የለንም። ስለፕሪቴሪዝም በብሎገሬ ላይ ጽፌ የለጠፍኩትን ዘለግ ያለ ጽሁፍ ታነቡ ዘንድ ጋብዣችኋለሁ፤ እነሆ ሊንኩ፦

የነገረ ፍጻሜ አቋማችን (ፕሪቴሪዝም) መግቢያ የአለም ፍጻሜ ቀርቦአልን? የምንኖረውስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ወይም በመጨረሻው ዘመን ውስጥ ነውን? የክርስቶስ መመለሻስ ቀርባልን? ከዚህስ በ.....

ክርስትናችንን በአይነቱ ልዩ ከሚያደርጉት፣ እምነቱን፣ አስተምህሮውንና ልምምዱን በፍጹምነት ከሚገልጡ መታወቅያዎቹ ዋናው ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እውነተኛው አምላክ ያገ...
01/08/2025

ክርስትናችንን በአይነቱ ልዩ ከሚያደርጉት፣ እምነቱን፣ አስተምህሮውንና ልምምዱን በፍጹምነት ከሚገልጡ መታወቅያዎቹ ዋናው ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እውነተኛው አምላክ ያገኘነውና ለአለም የምናስተዋውቀው ብርሃን ነው። ይህም የእውነተኛው አምላክ ብርሃን የዘላለም ሕይወት ነው "እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት" ብሏልና። እውነተኛው አምላክ ሥላሴ ነው፣ ሥላሴም እውነተኛው አምላክ ነው። ምስጢረ ሥላሴ፣ "በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ" ሲል ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ለቤተክርስቲያን የገለጠው ትምህርት ነው። ቤተክርስቲያን ከዚህ ብርሃን ውጭ ልትሆን አይገባትም፣ አዘውትራም ልትማረው፣ ልትጠብቀውና ልታመልከው ይገባታል። የቅድስት ሥላሴን መሰረታዊ አስተምህሮ ለቅዱሳን ሁሉ ማካፈል ለሚወዱ፣ በገባኝ ልክ አካፍለው ዘንድ ጽፌ የለጠፍኩትን በብሎገሬ ላይ ማግኘት ትችላላችሁ፤ ሊንኩን በድጋሚ ከዚህ ማስታወቂያ ግርጌ አኖራለሁ። በአገር ኛው የመንፈሳዊ ጽሁፎች ዘርፍ ሥላሴን በተመለከተ የተጻፉ ግሩም ግሩም ስራዎች መኖራቸውን ባውቅም፣ (ለምሳሌ በአባ መሠረት ስብሃት ለአብ "ሥላሴ በተዋህዶ"፣ እንዲሁም "ትምህርተ ሥላሴ" በዶ/ር እሸቱ አባተ) ምናልባት እነርሱን ለማግኘት ዕድሉ የሌላቸው ቢኖሩ ወይም በቅዱሳን ዘንድ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ብዥታ ቢኖር ብዬ ብዕሬን መዝዣለሁ። የጻፍሁትን በቅድሚያ ለራሳችሁ አንብቡት፤ ከዚያም ሌሎች ጋር እንዲደርስ በቻላችሁት መጠን ላይክ፣ ሼር፣ ኮፒ፣ ፔስት፣ ፕሪንት ወዘተ እያደረጋችሁ አሰራጩት። በነጻ ያገኛችሁትን በነጻ ስጡ። ፍላጎቴ በሶሻል ሚድያ በሚከተሉኝ ሁሉ መነበቡ ነው። ምናልባት ከዚህ ጽሁፌ በኋላ በጌታ ትምህርት የማልጠቅማቸውንና ምንም ብጽፍ የማያነቡልኝን፣ ጽሁፍህ ረዘመ፣ አያዝናናም ወዘተ...፣ በሚል ምክንያት የሌሎችን ቦታ አጣብበው የያዙትን አንዳንዶችን ልሰናበታቸው እችላለሁ። ስሜት ቀስቃሽ ከሆኑ የዘመኑ ትምህርቶችና ስብከቶች በመለስ፣ ሥርና መሰረታችንን አጥልቀው በሚቆፍሩን፣ አጥብቀው በሚመሰርቱን፣ አጽንተው በሚያቆሙንና ፈጽመው በሚገነቡን የቃሉ እውነቶች ላይ እናተኩር።

https://gizachewkr.blogspot.com/2025/01/blog-post.html?m=1

ግዛቸው።

ቅድስት ሥላሴ እንደ መነሻ በተወሰኑ ምንባባት ርዕሰ ጉዳያችንን መመልከት እንጀምር። ማርቆስ 1፥ 9-11 ”በዚያ ወራትም ኢየሱስ ከገሊላ ናዝሬት መጥቶ ከዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ። .....

10/06/2024

የአሕዛብ ዘመን ተፈጽሟል!!

ኢየሱስ የአሕዛብ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም ትረገጣለች በማለት ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸው ይህ ጉዳይ ምንድን ነው? ወይስ ምን ነበር? ከዚህ በኋላስ ይህ የአሕዛብ ዘመን መጨረሻው ወደፊት ቅርብ ነውን?

ሉቃስ 21፥ 23-24 “በዚያን ወራት ለእርጕዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው፤ ታላቅ ችግር በምድር ላይ፥ በዚህም ሕዝብ ላይ ቍጣ ይሆናልና፤ በሰይፍ ስለትም ይወድቃሉ፤ ወደ አሕዛብ ሁሉም ይማረካሉ፤ የአሕዛብም ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች።”

የአህዛብ ዘመን የጀመረው፣ የሚፈጸሙውስ መቼ ነው? የአህዛብ ዘመን የጀመረው ባቢሎን ኢየሩሳሌምንና ይሁዳን ስትቆጣጠር እንደሆነ ዘመን መዳቢዎች (Dispensationalists) ሊነግሩን ይሞክራሉ። ከእነርሱም መካከል አንዳንዶች ደግሞ የአሕዛብ ዘመን በ1967 ዓ.ም ላይ እንዳበቃ ይናገራሉ። ዘመነኞቹ ደግሞ ገና ወደፊት የሚያበቃ ነው ይሉናል። የቃሉ አማኝና ተማሪ ነኝ ባይ ማንም ሰው ቢሆን፣ የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል እና በጥቅሉ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ የንባብ ክፍል በተቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከተገለጠው ትምህርት ነጥሎ ሊተረጉምም ሆነ ክፍሉ ከተነገረበት መጽሐፍ ተፈጥሮ በተለየ ሊረዳው እንደማይቻልና እንደማይገባ መገንዘብ ያስፈልገዋል። ምንም ቢሆን ከመፅሃፍ ቅዱስ የተወሰደ የትኛውም ምዕራፍ ምንባቡ ከተወሰደበት ክፍል ተነጥሎ ሊተረጎምም ሆነ ሊብራራ አይችልም። እንዲሁም የትኛውንም የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ወይም ምዕራፍ አስቀድሞ በተደረሰበት ቅድመ ግንዛቤ፣ ወይም ሲነገረንና ሲመስለን በኖረው ቅድመ እሳቤ ፣ ወይም ብዙሃኑ በተቀበለውና በተለመደው የአተረጓጎም ዘዴ ተርጉሞ ማቅረብ አይቻልም። ቃሉ ራሱን በራሱ እንዲተረጉም የማይፈቅድ ተርጓሚ ነኝ ባይ ሁሉ ይስታል፣ ሌሎችንም ያሳስታል።

ለምሳሌ እንደ ራንዳል ፕራይስ ያሉ፣ Pretrib Premillennialists “የአህዛብ ዘመን ፍጻሜ” የሚለውን ቃል ሲተረጉሙ በሮሜ 11፥ 25 ላይ ካለው “የአሕዛብ ሙላት” ከሚለው ጋር ያገናኙትና ሁለቱም ጥቅሶች ገና ወደፊት ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ይጠባበቃሉ፤ በዚህም ጊዜ “ሁሉም እስራኤል” ንስሐ ይገቡና፣ ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሱ ለዘላለም እንዳይጠፉ አይሁድ ኢየሱስን እንደ መሲሕ ይቀበላሉ፤ ሲሉ ያስተምራሉ። በዚህም እይታቸው ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ70 ዓ.ም ከሆነው ጥፋት ጀምሮ እነርሱ ገና ይመጣል ብለው እንደሚጠባበቁት እስከ መጪው እድሳት ድረስ ያለውን ጊዜ “የመረገጥ” ዘመን ወይም ባድማ የመሆን ጊዜ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። በርካታ ኮሜንታተሮችም፣ (ለምሳሌ፣ አልበርት ባርነስ፣ አዳም ክላርክ፣ ቤዛ፣ ባለአራት ወንጌል፣ JFB እና ሌሎችም) በዚሁ መስመር እያሰቡ ይህንኑ አመለካከት ይጋራሉ።

ጆኤል ቢ. ግሪንም በሉቃስ ወንጌል ማብራሪያው ላይ በገጽ 739 ላይ “የአህዛብ ዘመን” የሚለውን ሁለት መንታ ትርጓሜ አለው፣ አንዱ በኢየሩሳሌም ላይ የተነገረውን የእግዚአብሔርን ፍርድ በማስፈጸም ረገድ አሀዛብ የእግዚአብሔር ወኪል የመሆን ሚናቸውን ሲያመለክት፣ ከዚህ በላቀ ግን በአህዛብ መካከል የወንጌሉ የምስራች የሚታወጅበትን ጊዜ ያመለክታል ይላል:: ይህ በሉቃስ “የአህዛብ ዘመን” የተሰኘ ሃረግ በጳውሎስ የሮሜ መልዕክት ከተነገረው “የአህዛብ ሙላት” ከሚለው ጽንሰ አሳብ ጋር ለምን እንደሚሳከር አይገባኝም።

ዲ. ኤ. ካርሰን አርታኢው በሆነበት NIV Biblical Theology Study Bible የሉቃስ ወንጌል ማብራርያው ላይ ይህንን ጥቅስ ሲተረጉም በዚሁ ፍሰት [ከሰባ ሊቃናት የብሉይ ኪዳን የግሪክ ትርጉም] በዘካርያስ 12፥ 3 “በዚያም ቀን ኢየሩሳሌምን ለአሕዛብ ሁሉ ከባድ ድንጋይ አደርጋታለሁ፤ የሚሸከሙአት ሁሉ እጅግ ይቈስላሉ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በላይዋ ላይ ይከማቻሉ።” የሚለውን ጠቅሶ እንዲህ ይላል፦ ምንም እንኳ ይህ ጊዜ በሮሜ 11፥ 25 የተጻፈውን የአሕዛብን መዳን ሊመሰክር ቢችልም፣ የአሕዛብ ዘመን እርሱም አሕዛብ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚያሳድዱበት ጊዜ ማለት ነው። ይህም ተፈጽሟል፤ ይልና፣ አክሎም እግዚአብሔር ቁጣውን እንደሚገድበው ይህ ይጠቁማል (ማቴዎስ 24፥ 22፤ ማርቆስ 13፥ 20) ይላል። ኤፍ. ኤፍ ብሩስም አርታኢው በሆነበት የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ ይህንንው ጥቅስ አንስቶ የአሕዛብ ጊዜ እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ ትረገጣለች የሚለውን የቁጥር 24 ቃል “ሲተረጉም ይህ ምናልባት የአሁኑን አለም ስርዓት መጨረሻ ያመለክታል”፤ ይልና ፍጻሜውን ከዚህ ዘመናዊ አለም መጻኢ ጊዜ ጋር ያገናኘዋል።

ለእንግሊዝኛ አንባብያን የተዘጋጀው የኤሊኮት ማብራርያም በጥቅሱ ላይ የሚያቀርበው ትንታኔ፣ የእስራኤል ቅጣትና የኢየሩሳሌም ጥፋት ገደብ ሊኖረው እንደሚገባ፣ ሁለቱም የሚታደሱበት አንድ ቀን እንዳለ፣ ከጠቅላላው የቅዱስ ጳውሎስ ሐሳብ ጋር እንደሚስማማ የሚታወቅ ነው፤ ሲል በዚህ አንቀጽ ላይ የተገለጸውን ሐሳብ ያስተጋባል። በሮሜ 9-11፣ የተሰጠውን ትምህርትም በማምጣት በተለይ በሮሜ 11፥ 25፣ “የአሕዛብ ሙላት እስኪገባ ድረስ”፣ የሚለውን ጥቅስ ሉቃስ “የአሕዛብ ዘመን” ሲል ከሚጠራው ጊዜ ጋር በማገናኘት ያ ጊዜ የአህዛብ የተሻሉ፣ ወቅቶች ናቸው፣ እነርሱም እስኪፈጸሙ ድረስ” የሚሉትን ቃላት ያስተገባሉ” ሲል ይተረጉማል። የቤንሰን ኮመንታሪም ስለዚሁ ጉዳይ ማብራሪያ ሲሰጥ “የአሕዛብ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ - ማለት አሕዛብን ለመለወጥ በእግዚአብሔር ምክር የተወሰነውን ጊዜ የሚያካትት ነው፣ ይልና፣ ቀጥሎም ሐዋርያው ​​ጳውሎስ ለዚህ ክፍል ግልጽ ማብራሪያ በሮሜ 11፥ 25 ላይ ሰጥቶናል ሲል ያክላል። ይህም የሉቃስ ወንጌል የትንቢቱ ክፍል በዳንኤል 9፥ 27 ላይ ኢየሩሳሌምን እስከ ፍጻሜ ድረስ ባድማ ያደርጋታል ለሚለው ትንቢታዊ ቃል መልስ ይሰጣል፤ በዚህ ሕዝብ ላይ ቁጣ ይፈስሳል፣ ምድሪቱንም ባድማ ያደርጋታል ይላል። እዚህ ላይ ያለው የሁለቱም ምንባቦች ትርጉም እንደሚያሳየው፣ በሉቃስ ላይ ከተነገረው ጥፋት በኋላ፣ ኢየሩሳሌም ባድማ ሆና ትቀጥላለች፣ እግዚአብሔር የወሰነውን ቁጣ በእርሷ ላይ እስኪያፍሥባት ድረስ፥ አሕዛብም ወደ እግዚአብሔር ዘወር እስኪሉ ድረስ ይህ በምደሪቱ ላይ የተወሰነው ቁጣ አይጠናቀቅም ይላል።

የሆነው ሆኖ እንደ ሜየር እና ላይትፉት ያሉ ተርጓሚዎች ደግሞ ይህ የአህዛብ ዘመን ሙላት በ70 ዓ.ም ላይ ሙሉ በሙሉ እንደተፈጸመ አድርገው ለበኩረ ተደራስያኑ አውድ ተስማሚ በሆነ መንገድ ያዩታል። ለምሳሌ፣ ሜየር “የአህዛብ ዘመን” የሚለውን ቃል ትርጉም “. . . መለኮታዊ ፍርድ በፓሮዥያው እስከሚጠናቀቅ፥. . . እንዲህ አይነቱ የአሕዛብ ዘመን በራሳቸው በበኩረ ተደራስያኑ የሕይወት ዘመን (ቁጥር 28) ላይ የሚያበቃና፣ የሚያልቅ ነው (ሉቃ. 21፥ 25-27) …. ስለዚህም እነዚያ ካይሮስ (አይነተኛ ጊዜዎች) የሆኑ የጊዜ መደቦች እንደ ረጅም የጊዜ ቆይታ ሊቆጠሩ አይችሉም…” ሲሉ ይረዱታል።

በተመሳሳይም ላይትፉት የተባሉ ኮሜንታተርም ይህ “የአሕዛብ ዘመን” የተሰኘው የጊዜ ምዕራፍ ምልክቶቹን ባዩት የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ትውልድ ወቅት እንዳበቃ ይገነዘባሉ፣ እንዲህም ይላሉ:- “… ከዚህ ከቁጥር 32 ይልቅ የበለጠ ግልጽ ሊባል የሚችል ነገር የለም፣ “እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም”። የሚገርመው ነገር ይህ ዘመን ወደ ፊት ድጋሚ እንዳይታይ ሆኖ መነገሩ ነው… ”፤ ማለትም፣ ከአሁን በኋላ መታየት ወይም መደገም የሌለበት አስገራሚ ነገር ነው…[ምክንያቱም] እነዚህ ቃላቶች በጠቅላላው በምዕራፉ ውስጥ ትርጉምን አመልካች [ጠቋሚ] ናቸው…”

ሜየርም ሆኑ ላይትፉት ሁለቱም (በተለይ ከቁጥር 25-28 እና 32 የተጠቀሰውን) የፍጻሜውን ጊዜ የሚያመለክቱ በርካታ ጥቅሶችን በዐውደ-ምንባቡ አገባብ ጠቅሰው አቅርበዋል። ከዚህ በታች የተዘረዘሩት በርካታ የዐውደ-ምንባቡ ፍንጮችም በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የተከሰተው ይህ “መረገጥ” እና “የአሕዛብ ዘመን” የተሰኙ ጽንሰ አሳቦች ፍጻሜእቸውን የሚያገኙ እንደሆነ በግልጽ ያሳያሉ።

ጌታ ኢየሱስ በሉቃስ 21፥ 20 ላይ “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ።” ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ አይነተኛ ምልክት ሲሰጣቸው፥ ኢየሱስ እየተናገረ የነበረው በዘመኑ ለነበሩት ደቀ መዛሙርቱ ነው እንጂ፣ ወደ ፊት በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ለሚመጡ ትውልዶች አይደለም። ይህም አይነተኛ ምልክት ኢየሱስ ሲናገር በዙሪያው ሆነው ሲሰሙት የነበሩትን ደቀመዛሙርቱን ብቻ የሚመለከት ካልሆነ ሌላ በየትኛወም ዘመን እና ትውልድ ያለን ሰው አይመለከትም።

ሉቃስ 21፥ 22 “የተጻፈው ሁሉ እንዲፈጸም ይህ የበቀል ጊዜ ነውና።” ኢየሱስ በብሉይ ኪዳን ስለተተነበዩት አጠቃላይ ስለሆኑ በርካታ ክንውኖች እየተናገረ ነው፣ እነዚህም ሁሉ (ማለትም “መረገጥን” እና “የአሕዛብ ዘመን”ን ጨምሮ) ተፈጻሚ የሚሆኑት በእነዚያ “የበቀል ቀናት” ይኸውም በዘመኑ የነበሩ ደቀመዛሙርት በሕይወት እያሉ ነው።

ሉቃስ 21፥ 23-27 “በዚያን ወራት ለእርጕዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው፤ ታላቅ ችግር በምድር ላይ፥ በዚህም ሕዝብ ላይ ቍጣ ይሆናልና፤ በሰይፍ ስለትም ይወድቃሉ፤ ወደ አሕዛብ ሁሉም ይማረካሉ፤ የአሕዛብም ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች። በፀሐይና በጨረቃም በከዋክብትም ምልክት ይሆናል፤ በምድር ላይም አሕዛብ ከባሕሩና ከሞገዱም ድምፅ የተነሣ እያመነቱ ይጨነቃሉ፤ ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ፤ የሰማያት ኃይላት ይናወጣሉና። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል።”

ጌታ ኢየሱስ በአይሁዶች እና በሮማውያን መካከል ስለሚደረገው ጦርነት እና በመጨረሻም ምን እንደሚመጣባቸው በግልጽ እየነገራቸው ነው። በአጭሩ፦
ብዙዎቻቸው በሰይፍ ስለት ተገድለው ይወድቃሉ፤ እንደ ጆሴፈስ እና ሌሎች የታሪክ ምሁራን ዘገባ ከሆነ በእነዚያ አይሁድ በቀሰቀሱት አመጽ እና የሮማውያን ወታደሮች የከተማይቱን ቅጥር ሰብረው በህዝቡ ላይ በከፈቱት ዘግናኝ ጦርነት ከአሥራ አንድ መቶ ሺህ በላይ ሰዎች በሰይፍ እንደተገደሉ ይገመታል። ይህ በኢየሩሳሌም ላይ የተደረገው ከበባ ግልጽ ወታደራዊ ጭፍጨፋ ነበር።
የቀሩት ይማረካሉ፤ ይህ ቀደም ባለው ታሪካቸው ከለዳውያን በእነርሱ ላይ ድል ተቀዳጀው ወደ ምድራቸውና ወደ ሕዝባቸው በምርኮ አግዘው እንደወሰዷቸው አይነት አይደለም፤ አዎ ያኔ ከአሁኑ በተሻለ የተወሰዱት ወደ አንድ ህዝብና አገር ነው፤ አሁን ግን በዚህኛው ምርኮ እርስ በርሳቸው ለመገናኘትና ሃሳብ ለመለዋወጥ እስከማይችሉ ድረስ፥ እርስ በርሳቸውም እስከማይዋሃዱ ድረስ በምድር ላይ ተንሰራፍተው ወዳሉ ወደ አሕዛብ ሁሉ ይበተናሉ።
ኢየሩሳሌም ራሷ በአሕዛብ ተረግጣለች። ዓመፀኛና ክፉ ከተማ፣ ነገሥታትንና አውራጃዎችን የምትጎዳ፣ ስለዚህም የተጠላች ከተማ ተደርጋ ባድማ እስክትሆን ድረስ ሮማውያን ራሳቸውን ገዥ አድርገው ይሰለጥኑባታል። ምድሪቱ የተነገረባትን መለኮታዊ የበቀል ጊዜ ለመንገር ግን ያዳግታል። ይህ የትንቢት ቃል የተፈጸመበት መንገድ በእውነቱ አስገራሚ እንደሆነ ጥቂት የታሪክ ማሳያዎችን እናንሳ:-

አይሁዶች ከሮማውያን ጋር ባደረጉት ዘግናኝ ጦርነት ሞትን እና ግዞትን አስተናግደው ውድመት ከደረሰባቸው በኋላ፣ የሮማው ቄሳር ቬስፓሲያን የመንግስቱ ወኪሎች ለሆኑ ባለስልጣናት መላውን የይሁዳ ምድር እየሸነሸኑ እንዲሸጡ ትዕዛዝ አውርዶ ነበር፣ "በዚያን ጊዜ ቄሳር የአይሁድን ምድር በሙሉ እንዲሸጡ ለባሱስ እና ለሊቤርየስ ማክሲሞስ አቃቤ ህግ ትዕዛዝ ጻፈ፤ በዚያም ምንም አይነት ከተማን መልሶ አልሠራም፥ ነገር ግን አገራቸውን በሙሉ የራሱ ገንዘብ አድርጎ ያዘ፥ በዚያም ስምንት መቶ ወታደሮችን ብቻ ትቶ ከኢየሩሳሌም ሠላሳ ምዕራፍ የምትሆን ኤማሁስ የምትባል መኖሪያን ይሰፍሩባት ዘንድ ሰጣቸው። ለአይሁድም ሁሉ ተበትነው በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ ላይ ግብር ጣለባቸው፥ እንደ ቀድሞው ዘመን ለኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ይከፍሉ እንደበረው ሁሉ፣ እያንዳንዳቸውም ሁለት ድርሃም ወደ ማዘዣው ጣቢያ ያመጡ ዘንድ አዘዛቸው፥ በዚያን ጊዜም አይሁድ የነበሩበት አስከፊ ሁኔታ ይህ ነበር። በተለይ ኢየሩሳሌም፣ ከመላ ግዛቷ ጋር፣ በአህዛብ እጅ የወደቀች፣ የቄሳሩ የቬስፓዢያን የግሉ ንብረት ሆናለች፣ በዚያም ሊኖሩ ምርጫቸው ላደረጉ አሕዛብም ተቸብችባ ተሸጠች። ኢየሩሳሌም በዚህ ሁኔታ ባድማና ውድማ ሆና እንደቀጠለች ዲዮ ሲናገር፣ ንጉሠ ነገሥት አድሪያን መልሶ እንዲያሠራት፣ እንዲቀመጥባትም ቅኝ ግዛት የሚያደርጋትን ወኪል ልኮ ኤልያ ብሎ ሰየማት። ነገር ግን ሁኔታውን ቀይሮ ጽዮንን እና ቤዛታን ትቶ ጌታችን ወደ ተሰቀለበት ቀራንዮ ድረስ ተስፋፍቶ ያዘ። ከዚህም በላይ አድሪያን አንድም አይሁዳዊ ወደ ኢየሩሳሌም አካባቢ እንዳይጠጋና እንዳይገባ አስገዳጅ ሕግ እንዳወጣ ዩሴቢየስ በታሪካዊ ዘገባው ነግሮናል። ስለዚህ አይሁዶች ከርስታቸው እየተሳደዱ ተነቅለው ሲወጡ ብዙ እንግዶች ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ገቡ፣ ከተማዋም የሮማውያን ቅኝ ግዛት ሆነች። በኋለኛው ዘመን ግን ጁሊያን፣ ጌታችን ስለ አይሁድ ሕዝብ የተናገረው ትንቢት መፈጸሙ በአሕዛብ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደረና የመለወጣቸውም ዋና ምክንያት እንደነበረ በማስተዋሉ፣ ሃይማኖቱን ክዶ ይህንን ድጋፍ ከክርስትና ለመንፈግ ወስኖ ነበር። ያኔም አይሁዶች የራሳቸውን መሬት እንዲይዙ በማምጣትና ሃይማኖታዊ ሥርአታቸውን እንዲፈጽሙ የሲቪል መንግስት አይነት ፈቀደላቸው። አይሁድ ጸሎትና መስዋዕት የሚያቀርቡት በዚያ ስፍራ ብቻ እንደሆነ ያውቅ ስለነበር ለዚሁ ዓላማው ሲል ኢየሩሳሌምን እንደገና ለመገንባትና ቤተ መቅደሱን በጥንታዊ መሠረቱ ላይ ለማቆም ወስኖ ነበር። በዚህም እቅዱ መሰረት ለአይሁድ ማህበረሰብ ደብዳቤ ጽፎ ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ ጋብዟቸው ነበር፤ ደብዳቤውም ከሌሎች ሥራዎቹ መካከል አሁንም ድረስ አለ። ከሌሎች ብዙ ነገሮች ጋር ሲያበረታታቸውም፦ “ከብዙ ዓመታት ጀምሮ ልትቀመጡባት ስትመኟት የነበረችውን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን እኔ ራሴ ባለኝ አቅም ሁሉ እሠራታለሁ አኖራታለሁም” ይላቸው ነበር። ንጉሠ ነገሥቱም ታላቅ ዝግጅት አድርጎ ቤተ መቅደሱን እንደገና በመገንባት እቅዱን መፈጸም ጀመረ፤ ነገር ግን እርሱ ለሥራው ያሰማራቸው ሠራተኞች ግልጽ በሆነ በእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ወዲያውኑ ስራውን ለማቆምና ከስፍራው ለመሸሽ ተገደዱ። አሚያኑስ ማርሴሊኑስም ስለዚህ ሁኔታ ሲናገር “በኢየሩሳሌም ትልቅ ዋጋ ያለው ቤተ መቅደስ ለመሥራት ወሰኖ ነበር” ሥራውንም ያፋጥነው ዘንድ ለአንጾኪያው አሊጲዮስ ሰጠው ነገር ግን አሊፒዮስ በታላቅ ትጋት ሥራውን ለመፈጸም እየጣረ ሳለ፣ ስለ ስራውም ለግዛቲቱ ገዥ በማስረዳት ላይ እያለ ከህንጻው መሠረት አጠገብ እጅግ አስፈሪ የሆኑ የእሳት ኳሶች መፈንዳት ጀመሩ፣ ፍንዳታውም ተደጋጋሚ እና ለብዙ ጊዜ የቀጠለ በመሆኑ በፍንጣሪውና በሚተፋው እሳት ሠራተኞችን በማቃጠል ገደላቸው፣ ሰውም የማይደረስበትን ቦታ ሁሉ አቃጠለው፤ እሳቱ ያለማቋረጥ ስላባረራቸው በዚህ ምክንያት ስራው ቆመ። ይህም ክስተት እና እውነታው የተረጋገጠው በአይሁዳዊው ዘሙት ዳዊት ሲሆን፣ ጁሊያንም ይህ ሙከራ በራሱ እግዚአብሔር እንደተደናቀፈ በሐቀኝነት መስክሯል። በተመሳሳይም በናዚያንዜን እና በክሪሶስቶም በግሪኮች፣ በአምብሮስ እና በሩፊን በላቲን መካከል ነገሩ ሲነገር ኖሯል፣ ክስተቱም በተከሰተበት ጊዜ በህይወት የኖሩት፣ እንዲሁም እነዚህ ነገሮች ከተከሰቱ በኋላ ባሉት የሃምሳ አመታት ጊዜ ውስጥ ቆይተው ታሪኩን የፃፉና የአይን ምስክሮች ሆነው በህይወት ከነበሩ መካከል ቴዎዶሬት እና ሶዞሞን፣ ፊሊስተርዮስ፣ አርያን፣ ፎቲየስ እና የኖቫታውያን ደጋፊ የነበረው ሶቅራጥስ ይጠቀሳሉ። ስለዚህ፣ አይሁዶች እና አረማውያን፣ በሮም ንጉሠ ነገሥት እየተመሩ፣ ጌታችን በኢየሩሳሌም ከተማና በቤተመቅደስዋ ላይ “እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል” ሲል የተናገረውን ወድሞ የመቅረት ትንቢት ለማደናቀፍ ኃይላቸውን ሁሉ አንድ አድርገው ቢያስቡም፣ ያሰቡትንም ቢያደረጉ፣ መለኮታዊ እርግማን ያለባትን ከተማ መልሰው ሊያነሷት ግን አልቻሉም።

ጌታ ኢየሱስ ስለ እነዚያ “የበቀል ቀኖች” በድጋሚ ሲናገር ይህ አጠቃላይ ክንውን እንደማይቀር ነግሯቸዋል፣ እነርሱም ፦
ነፍሰ ጡር የሆኑ እርጉዞች እና ህጻናትን የሚያጠቡ ሴቶች በዚያን ጊዜ “ታላቅ ጭንቀት” ይደርስባቸዋል
የአይሁድ ሕዝብ ላይም “ቁጣ” ይደርስባቸዋል
“በሰይፍ ስለትም ይወድቃሉ፣”
“ወደ አሕዛብ ሁሉ ተማርከው ይወሰዳሉ”
ከእግር በታችም “የተረገጡ” ይሆናሉ፤
“በፀሐይ፣ በጨረቃና በከዋክብት ላይ ያሉ ምልክቶች” ይደረጋሉ፣
“ድንጋጤ”፣ “ግራ መጋባት” እና “ፍርሃትም” ይሆንባቸዋል፣
“የሰማያት ኃይላትም ይናወጣሉ” እንዲሁም
“የሰው ልጅ ሲመጣ ያዩታል፤ የሚሉት ናቸው።

እነዚህም ክንውኖች “በእነዚያ ቀናት” ውስጥ የሚፈጸሙ እንደሆኑ በግልጽ ያመለክታል። ይህ በአይሁድ ላይ እንደሚደርስ ሉቃስ የሚነግረን የበቀልና የቁጣ ቀን የአይሁድ ህዝብ ታላቁ መከራ ነው እንጂ የቤተክርስቲያን ታላቁ መከራ አይደለም። እርግጥ ኢየሱስም ሆነ የአዲስ ኪዳን ጸሓፍያን የህንን ታላቁ መከራ የተሰኘውን ሃረግ በቤተ ከርስቲያንም ሆነ በአይሁድ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን መከራ ለማመላከት ተጠቅመውበታል። ሉቃስ 21፥ 24 ላይ ያለው ግን ሮማውያን በየሩሳሌምና በመላው የአይሁድ ሕዝብ ላይ የሚያደርሱትን ጥፋት የሚያመለክት ነው። ታሪክ አዋቂው ጆሴፈስም እነዚህን ሁሉ ነገሮች በታሪካዊው ድርሳኑ ውስጥ ጠቅሶ ዘግቧቸዋል። የሚያጠቡ እናቶች ጡት ያልጣሉ ጨቅላ ልጆቻቸውን ቀቅለው የበሉበትን ታሪክ፤ በአይሁድ ላይ የደረሰባቸውን በቀል እና በከተማቸው መካከል በሰይፍ ስለት ተገድለው ስለመውደቃቸው፤ በሰማይ ኃይላት ላይ ሰለታዩ ምልክቶች በዝርዝር ያስነብበናል። አለማቀፍ የፕሪቴሪስት ማህበር ፕሬዚዳንት የሆኑት ስቲቨን ኤድዋርድም የነዚህን ክስተቶች ዝርዘር ታሪካዊ ፍጻሜ አደራጅተው ለንባብ ባበቁት ጥልቅ ጥናታዊ ሰነድ ሌሎችን በርካታ የታሪክ ምሁራን ጠቅሰው በማስረጃ ያቀርባሉ

ሉቃስ 21፥ 28 “ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ።”

ጊዜን አመልካች በሆኑ በእነዚህ ክንውኖች መካከል ለተፈጻሚነታቸው ምንም አይነት የጊዜ ልዩነት የለም። ኢየሱስ ከላይ የተጠቀሱትን እነዚህን ዘጠኙንም ክንውኖች (“እነዚህ ነገሮች” ሲል) እንደ አንድ አጠቃላይ የክስተቶች ስብስብ ጠቅሷቸዋል፣ እነዚህም በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ደቀ መዛሙርቱ በህይወት እያሉ የሚያዩአቸው ጉዳዮች ነበሩ፣ እነርሱም “እነዚህ ነገሮች” የተባሉትን ክንውኖች ሲያዩ በዚህ መንገድ ቤዛቸው እንደቀረበ ያውቃሉ ማለት ነው።

ሉቃስ 21፥ 31-32 “እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።”

ኢየሱስ እዚህ ላይ “እናንተ” ሲል የሚጠቅሳቸውና በእርሱ ዘመን የነበሩ ደቀ መዛሙርቱ “እነዚህ ነገሮች” የተባሉ ክንውኖች ሲፈጸሙ እንደሚያዩ፣ ከሚያዩትም ነገር የተነሳም (ማለትም መረገጡን እና የአሕዛብን ዘመን ጨምሮ) በዚህ የእግዚአብሔር መንግሥት ልትመጣ እንደ ቀረበች እንደሚያውቁ ይነግራቸዋል። ይህም ፍጻሜ ሌላ ባዕድ ፍጻሜ ሳይሆን በመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን፣ በደቀ መዛሙርቱ የህይወት ዘመን የሚጠበቅ ብቸኛ ፍጻሜ መሆኑን ንግግሩ ይበልጥ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። በንግግሩ ሁለት ጊዜ (ቁ. 22፣ 24) “እነዚህ ነገሮች” የሚለው ቃል ጥቅም ላይ እንደዋለ አስተውሉ (ቁ.22፣ 32)። ምናልባት የቀሩ ጥርጣሬዎች ቢኖርባቸው እንኳ ኢየሱስ እርሱ ስለተናገራቸው ስለ እነዚህ ጉዳዮች፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ሁሉም ነገር እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም” ሲል ጉዳዩን በመኃላ በማረጋገጥ ሁሉንም ጥርጣሬ ያስወግዳል። ይፈጸማሉ የተባሉት እነዚህ ጉዳዮች “ይህ ትውልድ” በተባለው የዚያን ዘመን ትውልድ ውስጥ የሚከናወኑ ነገሮች መሆናቸውን እንዳንጠራጠር ኢየሱስ በመኃላ አስሮታል። መጻኢነት ግን የሚጠራጠረው ይህንን የእግዚአብሔር ልጅ መኃላ ነው። በዚህ አውድ ውስጥ የተጠቀሱት ሁሉም ክንውኖች የሚፈጸሙት የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ትውልድ ከማለፉ በፊት ነው። ትንቢቱ አልተፈጸመም በሚል ሌላ ብዙ ተረት የመሰለ ‘የሊቃውንትን’ ግራ-ገብ ማብራሪያ ተቀብሎ እርሱኑ እንደበቀቀን ከማስተጋባትና ሃሰትን ከማመን ይልቅ፣ ጌታ ኢየሱስ በእውነት መኃላ የተናገረውን ብቻ አምኖ ትንቢቱ በተያዘለት ቀነ ቀጠሮ ተፈጽሟል ብሎ መቆም ይመረጣል።

ላይትፉት ከላይ እንደተናገሩት፣ ኢየሱስ ከዚህ የበለጠ በንግግሩ ግልጽ ሊሆን አይችልም። ከቁጥር 20-32 የተጠቀሱት ሁሉም ክንውኖች በአንድ ላይ የተጠቃለሉት “ሁሉ” (ቁ. 22)፣ “ነገሮች” (ቁ. 26)፣ “እነዚህ ነገሮች” (ቁ. 28፣ ቁ. 31) በሚሉት ቃላት ነው (። ልብ አድርጉ “ሁሉም ነገር” (ቁ. 32) ማለትም እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሚፈጸሙበት ጊዜው ደግሞ (“እናንተ” እና “የእናንተ” የተባሉት ከቁጥር 20፣ 28 እና 31-32 ይመልከቱ) እነርሱ ራሳቸው በዘመኑ የነበሩት ደቀ መዛሙርት አሁንም ይህንንው ፍጻሜ “ለማየት” “በእነዚያ የበቀል ቀናት” (ቁ. 22-23) በሕይወት ይኖራሉ (ቁ. 20፣ 27፣ እና 31) ተብሏል። በዚህ ላይ የቀረ ጥርጣሬ ካለ፣ ኢየሱስ ሲናገር (ቁ. 32) እነዚህ ሁሉ ክንውኖች ማለትም “የመረገጡ” ጊዜ እና “የአሕዛብ ዘመን”ን ጨምሮ ይፈጸማሉ የተባሉት ነገሮች ሁሉ ተፈጻሚ የሚሆኑት “ይህ ትውልድ የተባለው የትውልድ ጊዜ ከማለፉ በፊት ነው ሲል የፍጻሜውን ጊዜ አንዴ አስረግጦ ነግር ጨርሷል። እዚህ ላይ ምንም ለመወዛገብ እድል የሚሰጥ ነገር የለም። ‘የመረገጡ’ እና “የአሕዛብ ዘመን” የሚባለው ምንም ይሁን ምን በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ትውልድ ውስጥ ሊፈጸሙ የተወሰኑ ክንውኖች አድርገን ልንገነዘባቸው ይገባል።

በተጨማሪም፣ በቁጥር 22 ላይ እዚህ የተጠቀሱት ሁሉም ክስተቶች በብሉይ ኪዳን እንደተተነበዩ ኢየሱስ ተናግሯል። ይህም “ብሉይ ኪዳን “የመረገጡን” እና “የአሕዛብን ጊዜ” የሚተነበየው በየትኛው ክፍል ነው? የሚል ጥያቄን ሊያስነሳ ይችላል፤ መልሱም በቀላሉ የሚገኘው ሉቃስ 21፥ 20ን በማቴዎስ 24፥ 15 ካለው ተመሳሳይነት ጋር ስናነጻጽርና ስናስተያየው ነው። ኢየሱስ ስለ “ጥፋት ርኩሰት” ሲናገር ምንጩን ከዳንኤል መጥቀሱን ልብ ይሏል። ስለዚህ በዳንኤል ላይ ስለ “መረገጥ” እና ስለ “አሕዛብ ዘመን” የሚናገሩ ሐሳቦችን ስናገኝ እምብዛም ሊያስገርመን አይገባም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ መረገጥና ስለ አሕዛብ ዘመን ተጠቅሶ የምናገኘው በዳንኤል ብቻም አይደለም። አንዳንዶቹን አለፍ አለፍ ብለን እንመልከት፡-

ሰቆ.ኤር 1፥ 15 “ጌታ ኃያላኖቼን ሁሉ ከውስጤ አስወገዳቸው፤ ጕልማሶቼን ያደቅቅ ዘንድ ጉባኤን ጠራብኝ፤ ጌታ ድንግሊቱን የይሁዳን ልጅ በመጥመቂያ (የወይን መጥመቂያ) እንደሚረገጥ አድርጎ ረገጣት።” በዚህ ጥቅስ የወይን መጥመቂያውን ረገጣ የሚያሳየውን ስዕል ልብ አድርጉ። በ70 ዓ.ም. የአይሁድን ፍርድ በተመለከተ በራእይ መጽሐፍ በተነገረው ቃል ውስጥም ይኸው ተመሳሳይ ንግግር ጥቅም ላይ ውሏል፦ “መልአኩም ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው፥ በምድርም ካለው ከወይን ዛፍ ቈርጦ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሔር ቍጣ መጥመቂያ ጣለ። የወይኑም መጥመቂያ ከከተማ ውጭ ተረገጠ፥ እስከ ፈረሶች ልጓምም የሚደርስ ደም ርቀቱ ሺህ ስድስት መቶ ምዕራፍ ሆኖ ከመጥመቂያው ወጣ” (ራእይ 14፥ 19-20)። ይህ ቃል እንዴት እንደተፈጸመ በጥቂቱ አመልክቼ ወደኤርምያስ ሰቆቃ እመለሳለሁ።

ስዕሉን ተመልከቱ፣ መልአኩ ማጭዱን ወደ ምድር ጥሎ የምድርን ወይን ሰበሰበና ፍሬውን ታላቁ የእግዚአብሔር ቁጣ ወደሚጠመቅበት ወደ መጥመቂያው ጣለው (ይህንን ተመሳሳይ ስዕል በነዚህም ክፍሎችም ማየት ይቻላል፦ ኢሳ. 63፥ 1-6፤ ኤር 25፥ 29-33፤ ሰቆ. 1፥ 15፤ ሉቃ 19፥ 42-44)። የወይን መጭመቂያው ከትልቅ ድንጋይማ አለት ተፈልፍሎ የተሰራ ወይም በድንጋይ የተገነባ ጉድጓድ ሆኖ ወይኑ እየተቆረጠ የሚጣልበት እና ጭማቂው ተንጠፍጥፎ እስኪወጣ ድረስ በሰው እግር የሚረገጥበት ቦታ ነው። የወይኑ ደምም ከመጭመቂያው ጉድጓድ በታች ባለው ትንሽ ቀዳዳ ውስጥ ይንጠባጠባል፣ ከዚያም በየማድጋው ውስጥ ይደረጋል። የምድር ወይን በሆነችው በእስራኤል ላይ የፈሰሰው የእግዚአብሔር ቁጣም ይህን ይመስላል። በእርግጥ ይህንን በዓይነ ሕሊና ለመሳል አያስቸግርም። በ70 ዓ.ም የጸደይ ወቅት፣ የእስራኤል ሕዝብ የፋሲካን በአል ለማክበር በኢየሩሳሌም በተሰበሰቡ ጊዜ፣ ሮማውያን በድንገት ከተማይቱን ከበቡ፣ በቅጥሮቿ ውስጥ ያለውን ሕዝብ እንዳይወጣና እንዳይገባ አጥምደው ዘግተው፣ ከተማይቱ እስክትፈርስ ድረስ አምስት ወራት የፈጀውን የኢየሩሳሌምን ከበባ ጀመሩ፤ ረገጣው የጀመረው ያኔ ነው።

ዮሐንስ በራእዩ ይህ የወይን መጥመቂያ ከከተማው ውጭ ሲረገጥ ተመልክቷል። በተለመደው መንገድ ጭማቂውን ከወይኑ ፍሬ አሟጦ በማውጣት ዘዴ፣ ጭማቂው ሙሉ በሙሉ ወጥቶ እስኪያልቅ ድረስ በወይን መጭመቂያው ውስጥ መረገጥ አለበት፤ ሳይጨመቅ ባክኖ የሚቀር ወይም የሚያመልጥ የወይን ፍሬ የለም። ይህ የወይን መጭመቂያ ግን ከከተማው ውጭ ተረገጠ። በውስጧ ያለው የደም ጠብታ ፈስሶ እስኪያልቅ ድረስ ሮማውያን ከከተማይቱ ውጭ ሆነው እሳትና ሞት የሚተፉ የጦር መሣሪያዎቻቸውን ያለማቋረጥ በእየሩሳሌም ላይ እያወረዱና እያዘነቡ ኢየሩሳሌምን ይረግጧት ጀመር።

የወይኑ መጭመቂያ “እስከ ፈረስ ልጓም” ድረስ ተረገጠ፣ ማለት ደሙም ከመጥመቂያው እስከ ሽህ ስድስት መቶ ምዕራፍ ድረስ እስከ ፈረሶች ልጓሞች ድረስ ወጣ ማለት ነው። እንደ ጆሴፈስ ዘገባ በኢየሩሳሌም ብቻ 1,337,490 ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ ተነግሯል። ይህ ምልክት በእስራኤል እና በኢየሩሳሌም ላይ የፈሰሰውን አስፈሪውን የእግዚአብሔርን ቁጣ አስከፊ ተፈጥሮ ያሳያል። ቁጣው የተገለጠበት ቋንቋ ምሳሌያዊ ነው፣ ነገር ግን ጆሴፈስ የከተማዋን ውድመት አስመልክቶ ከሰጠው ቀጥተኛ መግለጫ ጋር በእጅጉ ይስማማል። ሲናገርም፦ “ከተማይቱ በሞላ በደም ተጥለቀለቀች፤ በብዙ ቤቶች የነደደ እሳትም በተገደሉት ሰዎች ደም ጠፋ” ይላል፤ እልቂቱም እጅግ በጣም ብዙ ነበር። ለፈሰሰው ለእያንዳንዱ ሰው ደም ስድስት ሳንቲም ከፍታ ደም እንኳ ብንወስድ ጎርፍ ሆኖ ወደ ሄኖም ሸለቆ የገባው የደም መጠን ከሁለት ሚሊዮን ጋሎን ደም በላይ ይደርስ ነበር። ከሰሜን እስከ ደቡብ (1600 ምዕራፍ ወይም ከ182 እስከ 200 ማይል ርቀት) መላውን የፓለስታይን ምድር የሰዎች ደም ሞላው።

የከተማይቱም መከላከያ በረሃብና በጦርነት በተዳከመ ጊዜ በመጨረሻ ላይ የሮማውያን ጦር የቅጥሩን የተወሰነ ክፍል ደርምሰው ወደ ከተማይቱ ገባና የጭፍጨፋ ሥራውን አጠናቀቀ። በእየሩሳሌም ላይ ስለተፈጸመው ስለዚህ ነገር አስፋፍቶ መግለጫ መስጠትም ሆነ ጥቂት ቃላት ተጠቅሞ በተሻለ ሁኔታ ዕልቂቱን መገለጽ በእውነት አይቻልም።

ከፍ ሲል በተጠቀሰው በሰቆቃወ ኤርምያስ ያለው ንግግርም ከዚህ በታች በቀረበው የቃሉ አጠቃቀም፣ አገባብና ታርጉሙን ልብ በሉ፦

እግዚአብሔር ኃያላኖቼን ሁሉ በውስጤ አደቀቀ፤ የብላቴኖቼንም ብርታት ወደ ሚሰብርበት ጊዜ ውስጥ ስቦ እስገብቶኛል። አሕዛብም ከጌታ ዘንድ በሆነ የአዋጅ ድምጽ በሜምራ [ሎጎስ ወይም ቃል] ትእዛዝ ወደ ይሁዳ ቤት ገብተው ደናግሉን አረከሱ፣ የወይን ፍሬ በሰው ሲረግጥ ከወይን መጭመቂያው የወይን ጠጅ እንደሚፈስ እንዲሁ የድንግልናቸውን ደም አፈሰሱ። ይህ ትርጉም ኢየሩሳሌም በመለኮታዊ ፍርድ የደረሰባት መከራ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ያሳያል፣ ይህም መለኮታዊ ፍርድንና ጥፋትን እጅግ ግልጽና አሳዛኝ የሆነ ምስልን ያሳያል። በአዲሱ መደበኛ ትርጉም “በውስጤ ያሉትን ተዋጊዎች ሁሉ እግዚአብሔር ተቃወመ፣ ጎልማሶቼን ለማድቀቅ ሰራዊት በላዬ ጠራ፤ ድንግሊቱን የይሁዳ ሴት ልጅ፣ እግዚአብሔር በወይን መጭመቂያ ውስጥ ረገጣት።” በሚል ተገልጧል።

እዚህ በሰቆቃወ ኤርምያስ 1፥ 15 ላይ “ረገጣት” የሚለው ቃል የኃላፊ ጊዜ አመልካች ግስ መሆኑን ተመልከቱ። ይህ መረገጥ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ586 የሆነ እንጂ ከዚያ በኋላ መረገጡ (እንደ ቀጣይ ጥፋት ሆኖ) እስከአሁን የቀጠለ አልነበረም። ይህ “መረገጥ” በተወሰነለት ቀጠሮ በባቢሎናውያን የአህዛብ መንግስት (በ586 ዓክልበ.) ተፈጽሞ ያለፈ አንድ ነገር ነው። ያ መረገጥ በ586 ዓክልበ በኢየሩሳሌም ላይ የተወሰነው “የአሕዛብ ጊዜ” ነበር። ያም ጊዜ፣ ኤርምያስ ሰቆቃውን በጻፈበት ወቅት ያኔ ጨርሶ አልፎ ነበር። ከተማይቱም ሆነች በጠቅላላ ምድሪቱ ወድመው ነበሩ፣ ዳሩ ግን (እንደ ራንዳል ፕራይስ እና ሌሎች መጻኢያን ተርጓሚዎች እንደሚመስላቸው) ያ ቀጣይነት ያለው ጥፋት እንደ መረገጥ የሚወሰድ አልነበረም።

ኤርምያስ ይህን የኃዘን እንጉርጉሮ የጻፈው ናቡከደነፆር በ586 ዓክልበ. ስላደረሰው የኢየሩሳሌም ጥፋት ለማዘን ነው። በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ለነበሩት አይሁዳውያን ኢየሩሳሌም ጠላት በሆኑ በአሕዛብ (እንደ ወይን መጭመቂያ) የመርገጧን አሳብን ኢየሱስ አንስቶ ሲናገር ለእነርሱ ጨርሶ የማያውቁት አዲስና እንግዳ ነገር አልነበረም። ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ በተደጋጋሚ የተከሰተ የታሪካቸው አካል ነው። ከሁሉ በላይ የሚታወሰው ግን በ586 ከክልበ. ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ላይ ያደረሰው ጥፋት ነው። የሰቆቃወ ኤርምያስ መጽሐፍ የተጻፈው የአሕዛብ መንግስት በሕዝቡ ላይ ያደረሰውን ታላቅ “መረገጥ” አስመልክቶ ሙሾ እና የሐዘን እንጉርጉሮ ለማውረድ ነው። ይህ በናቡከደነፆር የተደረገ ‘መረገጥ’ “የተቀጠረ” ጊዜ” እንደሆነ ኤርምያስ መናገሩን ልብ አድርጉ። በእርግጥ፣ በሉቃስ 21፥ 24 ውስጥ የተካተቱት አራቱም ነገሮች (ኢየሩሳሌም ለተወሰነ ጊዜ በአሕዛብ መረገጧን ጨምሮ፣) እዚህ በሰቆቃወ ኤር. 1፥ 15 ውስጥ ይገኛሉ። ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን በአንድ ቀን አላሸነፋትም። በኋላ ላይ ሮማውያን እንዳደረጉት ሁሉ እርሱም ያኔ ከተማይቱን በተመሳሳይ ጊዜ ከበባ ማድረግ ነበረበት። ጦርነቱ በቬስፔዥያን (67 ዓ.ም.) ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ቲቶ የከተማይቱን ቅጥር ንዶ በመዝለቅ ቤተ መቅደሱን እስካቃጠለበት ጊዜ ድረስ (70 ዓ.ም.) ሦስት ዓመት ተኩል ያህል ቆይቶ ነበር።

እዚህ በሰቆቃወ ኤርምያስ. 1፥ 15 የተነገረው "የተቆረጠ ጊዜ" [ማለትም፣ ጎልማሶቿን ለማድቀቅ የጠራው ጉባኤ ወይም የብላቴኖቿን ጉልበት የሚሰብርበት የተወሰነ ጊዜ] እንዲሁም "የመረገጡ" ሀሳቦች በሉቃስ 21፥ 24 ላይ ካየናቸው “ከአሕዛብ ዘመን” እና “ከመረገጥ” ሃሳቦች ጋር በእጅጉ ተመሳሳይ ናቸው። “የተቀጠረው (የተወሰነው ጊዜ” ወይም “የአህዛብ ጊዜ” የሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ወይም “አርባ ሁለት ወር” ሆኖ ከሚታይበት በቀር እነዚያን ሁለቱንም ሃሳቦች በራዕ 11፥ 2 ላይም በድጋሚ እናገኛቸዋለን።

በራዕ 11፥ 2 “በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው አትለካውም፤ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል።”

ስለዚህ እዚህ ላይ ሰቆቃወ ኤርምያስ 1፥ 15፣ በሉቃ.21፥ 24፣ እና በራእ.11፥ 2 መካከል ብዙ መመሳሰል አለ። ሦስቱም ምንባባት ተመሳሳይ የሆኑት እነዚህ አራቱም ጉዳዮች (ማለትም አሕዛብ፣ ለአህዛብ የተወሰነው የመርገጥ ጊዜ፣ ኢየሩሳሌም፣ የኢየሩሳሌም መረገጥ) አሏቸው። ሰቆቃወ ኤርምያስ እነዚያን አራት ጉዳዮች በ586 ዓክልበ. የኢየሩሳሌምን ጥፋት ለማመልከት ተጠቅሞባቸዋል።

ራእይ 11፥ 2 ባቢሎን ከተባለችው ከጋለሞታይቱ ከተማ መውደቅ ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ የሆኑ አራት ነገሮችን ይጠቅሳል። መረገጡ ለሦስት ዓመታት ተኩል ብቻ የፈጀ ክስተት እንደነበር በሁሉም ምንባባት ላይ ትርጉሙ ግልጽ ነው፡- እነዚያ የአሕዛብ ጭፍሮች ማጥፋትን በጨረሱ ግዜ መረገጡ ያበቃል። አህዛብ ከተማይቱን የሚረግጡበት ዘመን ገና ወደፊት ከሺህ ዓመታት በኋላ ስለሚሆን ጥፋት ጨርሶ አያመለክትም።

ራእይ 11፥ 2 ከሉቃስ 21፥ 24 ጋር በእጅጉ ተመሳሳይ ነው፣ እዚህ ላይ በግልጽ የሚናገረው የሦስት ዓመት ተኩል ጊዜም (42 ወራት) ነው። በሉቃስ 21፥ 24 ላይ የተጠቀሱት አራቱም ተመሳሳይ ጉዳዮች (አሕዛብ፣ ለአህዛብ የተወሰነው የመርገጥ ጊዜ፣ ኢየሩሳሌም፣ የኢየሩሳሌም መረገጥ)፣ እዚህ በራዕይ 11፥ 2 ውስጥ ተጠቅሰዋል። ይህ በጣም ግልጽ የሆነ ጥቅስ ስለ ሉቃስ 21፥ 24 ትርጉም ምንም አይነት ጥርጣሬ አይፈጥርብንም።

በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹት ነገሮች በሙሉ ሊፈጸሙ ያሉ ነገሮች ናቸው። [ዮሐንስ ራእዩን የጻፈው በ62-63 ዓ.ም አካባቢ ማለትም የአይሁድ-ሮም ጦርነት ከመጀመሩ ሦስት ዓመታት በፊት ነው።] ራእይ 11፥ 2 የሚያመለክተው ይህ የኢየሩሳሌም ርኩስ በሆኑ አሕዛብ የመረገጧ ጊዜ ለሦስት ዓመት ተኩል የሚቆይ ሲሆን፣ ይህም የመጨረሻው የደም ጠብታ ከወይን መጥመቂያው እስኪረገጥ ድረስ ነው። እንግዲህ ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል በወይን መጭመቂያ ውስጥ ስትረግጥ ማለት ምን እንደሚመስል አስቡ! ከእግራችሁ በታች ከዋለው የወይኑ ፍሬ ብዛት ውስጥ ምንም አይነት ያለ መጨመቅ የቀረ አንዳች ፍሬ አይኖርም። ይህስ የነበረው ቁጣው በአጭሩ የቆመ አልነበረም። ይልቁንም አይሁድ ሙሉ በሙሉ እስኪጠፉ ድረስ ያለማቋረጥ ቀጥሏል። ከዚያም ማምለጥ የሚባል ነገር አልነበረም። በተቀጠረለት ጊዜ ውስጥ የተያዘለትን ሙሉ የሆነ ኮርስ መጨረስ ነበረበት። ሁሉም ነገር ተፈጸሞ ባለቀ ጊዜ ብቻ ያኔ መረገጡ ቆመ፤ ያኔም ይረግጡ ዘንድ ለአሕዛብ የተወሰነው ጊዜ አብቅቷል።

“የአሕዛብ ዘመን” ቬስፓሲያን በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃቱን ከጀመረበት ጊዜ (67 ዓ.ም.) ጀምሮ በ70 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ረግጦና ደምስሶ እስኪያጠፋት ድረስ ረገጣው የሶስት ዓመት ተኩል ጊዜ ነበር። ዘመኑም እነዚህ ሁሉ ነገሮች የተፈጸሙበት “የበቀል ቀናት” ነበሩ። እዚህ ሉቃስ 21፥ 24 ላይ ዐውደ-ምንባብ ብቻ ንጉሥ ነው። በተለይም ከቁጥር 20-24 ያለውን አስተውሉ። ጌታ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እየቀረበ ያለውን ሠራዊት እንዲመለከቱ ለደቀ መዛሙርቱ ይነገራቸዋል። ከኢየሩሳሌም እና ከይሁዳ ፈጥኖ ለመውጣት እና ወደ ተራራዎች ለመሸሽ ይህ አይነተኛ ምልክት ይሆናቸዋል። በብሉይ ኪዳን የተነገረው ትንቢት ሁሉ ፍጻሜውን የሚያገኝበት የበቀል ጊዜ የሚጀምረውም ያኔ ነው። ያ የተወሰነው የኢየሩሳሌም ውድመት በብሉይ ኪዳን የተነገሩ እነዚያን ትንቢቶች ሁሉ ፍጻሜ ይሰጣቸዋል። በሉቃ 21፥ 22 ላይ “እንዲፈጸም” የሚለውን ቃል ልብ አድርጉ። እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? ይህ የሚፈጸመው በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ የበቀል እርምጃ በተወሰደበት ጊዜ፣ ሠራዊትም በላያቸው ሰፍሮ እነርሱንና ከተማቸውን ባድማ ባደረጋቸው በዚያ ዘመን ነው። ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ላይ አህዛብ ይረግጧታል ሲል የተናገረውን ትንቢት በተጨባጭ ፍጻሜ የሰጠው፣ በአውደ ምንባቡም መሰረት በብቸኝነትም ፍጻሜ ሊሰጠው በቂ የሆነው ክስተት የ70ው ዓ.ም ውድመት ነው።

ስለዚህ፣ መጻኢያን እንደሚያስቡት ይህ የአሕዛብ ዘመን ለትርጉምም ሆነ ለክስተቱ ፍጻሜ ክፍት ሆኖ የተተው ነገር አልነበረም። ተጀምሮ የሚያበቃበት የተወሰነ የመጨረሻ ነጥብ አለው። NIGTC [The New International Greek Testament Commentary] ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚል ተመልከቱ፤

እንደ ማርቆስ ዘገባ ከሆነ ይህ የሽብር ጊዜ ስለማጠሩ ምንም የተገለጸ ሀሳብ የለም። ሉቃስ ግን ከዚህ ይልቅ በአይሁዶች ላይ የሚደርሰውን ነገር እንደ ኤርምያስ ንግግር አንዳንዶች በሰይፍ ስለት ይወድቃሉ (ኤር. 20፥ 4–6፤ 21፥ 7) ሲል፤ እንደ ጳውሎስም… ታልፈው ይሰጣሉ (ሮሜ. 7፥ 23፤ 2 ቆሮ 10፥ 5፤ 2ጢሞ 3፥ 6) ሲል እንዲሁም በሌሎች ብዙዎች እንደተነገረው ወደ አሕዛብም በምርኮ ይጋዛሉ፣ ይወሰዳሉ (ጦቢት 1፥ 10፤ ዘዳ 28፥ 64)… ኢየሩሳሌምም ራሷ ‘ትረገጣለች’ (ሉቃስ 10፥ 19) ሲል በግልጽ አስፍሯል። …ነገር ግን ይህ ሁሉ የጊዜ ገደብ የተደረገለት ወቅት ሲሆን፣ ይኸውም የተወሰነው ጊዜ፣ በዚህ በሉቃስ ዘገባ መሰረት የአሕዛብ ዘመን ተብሎ የሚጠራው ነው። አህዛብ በእስራኤል ላይ እንዲያደርጉት የተፈቀደላቸውን የእግዚአብሔርን ፍርድና በቀል ሁሉ ይፈጽሙና ኢየሩሳሌምን ይረግጡ ዘንድ መለኮት በወሰነውና በቀጠረው ጊዜ እንዲሆን የተመደበ ነበር። ይህ በአይሁድ ላይ የሚደርስባቸው ፍርድ፣ ልክ ቤተ ክርስቲያን በታላቁ መከራ ወቅት እንደሚሆንላት አይነት ጊዜው እንደሚያጥር የሚጠቁም ነገር ጨርሶ የለም። ስለዚህ አስጨናቂ የፍርድ ጊዜ የተነገረው ነገር ሁሉ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን እስኪያገኝ ድረስ ይህ የቁጣ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ተሟጦ ማለቅ አለበት።

ኢየሱስ በተጨባጭ፣ እየተናገረ ያለው አሕዛብ አይሁዶችን እንደሚገድሉ፣ ወደ ሮም መንግሥት ሕዝቦች ሁሉ እንደሚማርኩ፣ እና ሙሴ ስለ ዘመኑ ፍጻሜ የተናገረው ነገር ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ አሕዛብ (ሮማውያን) በእነርሱ ላይ ሊያደርሱባቸው የተተነበዩ ጉዳዮች ሁሉ እስኪያደርጉባቸው ድረስ - እነርሱም የድል ጊዜያቸው እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌምን ፈጽሞ እንደሚያጠፏት ነበር። ሮማውያንም አይሁዶችን ፈጽመው እስኪያጠፏቸው ድረስ በምድሪቱ ውስጥ ቆዩ።

ይህንን የሶስት ዓመት ተኩል የጊዜ ወሰን የመረገጥን” ሃሳብ በቅርብ በአውደ ምንባቡ ውስጥ ያለ ሃሳብ ሆኖ በዳንኤል ምዕራፍ 7 ውስጥም ሶስት ጊዜ የተደጋገመ ሆኖ እንደገና እናገኘዋለን።

ዳንኤል 7፥ 7 “ከዚህም በኋላ በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የምታስፈራና የምታስደነግጥ እጅግም የበረታች፥ ታላላቅም የብረት ጥርሶች የነበሩአት አራተኛ አውሬ ነበረች፤ ትበላና ታደቅቅ ነበር፥ የቀረውንም በእግርዋ ትረግጥ ነበር፤ ከእርስዋም በፊት ከነበሩት አራዊት ሁሉ የተለየች ነበረች፤ አሥር ቀንዶችም ነበሩአት።”

ዳንኤል 7፥ 19 “ከዚህም በኋላ ከቀሩት ሁሉ ተለይታ እጅግ ስለምታስፈራው፥ ጥርሶችዋም የብረት ጥፍሮችዋም የናስ ስለሆኑት፥ ስለምትበላውና ስለምታደቅቀው የቀረውንም በእግርዋ ስለምትረግጠው ስለ አራተኛይቱ አውሬ፥”

ዳንኤል 7፥ 23 “እንዲህም አለ፦ አራተኛይቱ አውሬ በምድር ላይ አራተኛ መንግሥት ትሆናለች፤ እርሱም ከመንግሥታት ሁሉ የተለየ ይሆናል፥ ምድሪቱንም ሁሉ ይበላል፥ ይረግጣታል ያደቅቃትማል።”

ዳንኤል 7፥ 25 “በልዑሉም ላይ ቃልን ይናገራል፥ የልዑልንም ቅዱሳን ይሰባብራል፥ ዘመናትንና ሕግን ይለውጥ ዘንድ ያስባል፤ እስከ ዘመንና እስከ ዘመናት እስከ እኵሌታ ዘመንም በእጁ ይሰጣሉ።”

በራእይ 11፥ 2 እና በዳንኤል 7፥ 7-25 የተጠቀሱት ምንባባት ይህ “የመረገጥ” ክስተት በሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ እንደሚፈጸም ሁለቱም ያመለክታሉ። ስለዚህ ኢየሱስ በደብረ ዘይት ፍካሬው ላይ (ማቴዎስ 24 እና ምስስሎቹ) በእርግጥም የዳንኤልን ንግግር እያጣቀሰ ከሆነ፣ እንግዲያውስ እርሱ እንደሚለው፣ በሉቃስ 21፥ 24 ላይ የተጠቀሰው ይህ “የኢየሩሳሌም መረገጥ” በእርግጠኝነት የሚያመለክተው የሦስት ዓመት ተኩሉን ጊዜ መሆኑን ያሳያል። ያኔም ሮማውያን መጥተው ኢየሩሳሌምን አወደሙ (67-70 ዓ.ም.) ያም የጊዜ ምዕራፍ እንደ ኢየሱስ ትምህርትና እንደነብያቱ ቃል ከሆነ አሕዛብ አይሁድን የሚረግጡበት ጊዜ ነበር። ያ የተወሰነው “በአሕዛብ የተረገጡበት ጊዜ” ከ70 በኋላ ስላለው የጥፋት ዘመን እና አሁን ወደ ሁለት ሺህ ዓመታት የዘመን ርዝመት ስለሚጠጋ የአይሁድ ዲያስፖራ ትውልድ አይናገርም። በራዕዩም ሆነ በዳንኤል የተነገረው የመረገጥ ዘመን አጭር የሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ሲሆን እርሱም በ70 ዓ.ም የሚያበቃ መሆኑን በግልጽ ያመለክታሉ።

ይህንን ጥቅስ አስመልክቶ ከላይ መግቢያዬ ላይ የጠቀስኳቸውን ጨምሮ በርካታ በመጻኢያን የተዘጋጁ ኮሜንታሪዎችን ለማገላበጥ ሞክሬአለሁ። በተጨማሪም እንደ ጄ.ኤስ. ራሰል፣ ሚልተን ቴሪ፣ ጆን ኤል ብሬይ፣ ኤፍ.ደብሊው ፌራር፣ ሜየር፣ እና ላይትፉት ያሉ መምህራን ባዘጋጁአቸው ጽሁፎች ርዕሰ ጉዳዩን እንዴት በአውዱ መሰረት መልስ እንደሰጡበት ለማየት ዕድሉን አግኝቻለሁ። እዚህ ላይ ሁሉንም ጠቅሶ ለማሳየት የቦታና የጊዜ ውስንነት ይገድበናል። ከዚህም ባለፈ የሙት ባሕር ጥቅልሎች መጽሐፍ ቅዱስን፣ የኩምራን ዶክመንቶችን፣ ፊሎ፣ ጆሴፈስ፣ ዮሲፖን፣ ታልሙድ፣ ሚድራሽ፣ ዞሃር፣ ታርጉምስ፣ ፕሴውዴፒግራፋ፣ ሴፕቱጀንት እና አፖክሪፋ የተባሉትን የዕብራይስጥ፣ የግሪክ እና የእንግሊዝኛ ጽሑፎችን ማስረጃ ጠቅሰው ስለ መረገጥ እና ስለ አህዛብ ዘመን ምንነት እንዴት ተመሳሳይ ቋንቋ እንደሚጠቀሙ ያሳዩበትን የተለያዩ ፕሪቴሪስት ጸሐፍያንን ስራዎችንም መዳሰስ ያስፈልጋል። በኮምፒውተር በመታገዝም የተለያዩ ድረ ገጾች ላይ ፍለጋን አድርጎ ተጨማሪ ብርሃን የሚፈነጥቁ የምርምር ግብአቶችን ማሰስም ይገባል። ይህ ግን ለትጉሃን የቃሉ ተማሪዎች ብቻ ነው።

ቀጥሎ በሚቀርቡ ዝርዝር የቅዱሳት መጻህፍት ምንባባት ላይ ያለው የመጀመሪያው “የአሕዛብ ዘመን” የሚለውን ተመሳሳይ ሐረግ እንደሚጠቀሙ ያሳያል።

ሕዝቅኤል 30፥ 3 “የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው፥ የደመና ቀን፥ የአሕዛብ ጊዜ ይሆናል።”

አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህንን ሐረግ የሚገልጹት እንዴት እንደሆነ እነሆ ተመልከቱ፡- “የሕዝቦች ጊዜ” [WEB፣ ASV፣ Darby] እና “የአሕዛብ ዘመን” [ጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኪጄቪ]፤ “(ወራሪ) ብሔራት (በሌሎች ብሄራዊ አገሮች ላይ)፤ የሚያደርሱት የጥፋት ሰዓት” [ታናካህ] ወይም “አሕዛብ የሚያደርሱት የጥፋት ቀን/ ጊዜ” (አዲሱ መደበኛ ትርጉምና NASB)። በዚህ አይነተኛ አውድ ውስጥ፣ (የአህዛብ ጊዜ) የሚለው ሐረግ በግብፅ፣ በኢትዮጵያ፣ በፑት፣ በሉድ፣ በአረቢያ እና በሊቢያ ሕዝቦች ላይ በናቡከደነፆር እጅ የሚፈጸመውን የጥፋት ጊዜን የሚያመለክት ይመስላል። እነዚያ የአህዛብ አገሮች በእስራኤል ላይ የጥፋቷ “ጊዜ” በደረሰ ወቅት ተሳልቀውባት ነበር። አሁን ደግሞ እነርሱ ራሳቸው ህመሙ የሚሰማቸው ተራቸው ወይም "ጊዜያቸው" ነበር። ይህ አይነቱ ትርጉም በሕዝቅኤል ዘመን ከነበረውና አንዱ ከሆነው የነብዩ ኤርምያስ ቃል ጋር ሲነጻጸር የበለጠ ተመሳሳይነት ያለው ይመስላል።

ኤርምያስ 27፥ 7 “የገዛ ራሱም ምድር ጊዜ እስኪመጣ ድረስ አሕዛብ ሁሉ ለእርሱና [ለናቡከደነጾር] ለልጁ ለልጅ ልጁም ይገዛሉ፤ በዚያን ጊዜም ብዙ አሕዛብና [ሜዶንና ፋርስ] ታላላቆች ነገሥታት [ቂሮስ፣ ዳርዮስ] እርሱን ያስገዙታል።” እዚህ ላይ ይመጣል የተባለው “ጊዜ” የሚያመለክተው የቀደመው ወራሪ ሊመጣ ባለው ወራሪ ጦር በወራቱ እንዲጠፋ የተደረገበትን ጊዜ የሚያመለክት መሆኑ በጣም ግልፅ ይመስላል፤ እንጂ ከዚያ በኋላ ላልተወሰነው የጥፋት ዘመን የሚያመለክት ፈጽሞ አይደለም።

ማርቆስ 13፥ 33 “[የተቀጠረው/ የተወሰነው] ጊዜ(ው) መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፤ ጸልዩም።” [ይህ ከሉቃስ 21፥ 24 ጋር ትይዩ የሆነ ምንባብ ነው። ይህ ፍርድ፣ እርሱም “የተወሰነው ጊዜ” ቀደም ሲል ካነሳነው ከሰቆቃወ ኤርምያስ 1፥ 15 ጋር፤ እንዲሁም ከዳንኤል፡ 8፥ 19፤ 11፥ 27፤ 11፥ 29፤ እና 11፥ 35 ጋር የሚመሳሰል ነው። ለሰው ልጆች ዘመናትን ወስኖ የሚሰጥ ሉዓላዊው አምላክ መሆኑን በሐዋርያት ሥራ 17፥ 26 ላይ ጳውሎስ በግልጽ ይናገራ።

[Qumran War Scroll] 1QM 15:1] ለእስራኤል የጭንቀት ጊዜ ነውና፥ ከአሕዛብም ሁሉ ጋር ለመዋጋት የተወሰነው ጊዜ ነው። የእግዚአብሔርም አላማ ዘላለማዊ ቤዛነትን ማምጣት ነው። [ይህ በብርሃን ልጆች እና በጨለማ ልጆች መካከል ያለውን የምጽአት ፍጻሜ ጦርነት የሚገልጽ ከጦርነት የመጽሐፍ ጥቅልል ​​የተገኘ እጅግ አስደማሚ ምንባብ ነው። ይህ ጦርነት “አሕዛብ ሁሉ” ለጦርነት ወደ እርስዋ የሚመጡበትና በላይዋ ላይ የሚሰለፉበት “ለእስራኤል የጭንቀት ጊዜዋ” እንደሚሆን ልብ በሉ። ስለ ተወሰነው ጊዜ እና ስለ አሕዛብ ህዝቦች የሚናገረውን ተመልከቱ። እነዚህ ሁለቱም ጉዳዮች ማለትም የአህዛብ በእርሷ ላይ መምጣት እና የጭንቀቱ ጊዜ በሉቃስ 21፥ 24 ውስጥም የሚገኙ ናቸው። ይህ የጦርነት መጽሐፍ ጥቅልል ​​በ70 ዓ.ም ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊት አስቀድሞ የተጻፈ ነው። ይህም የሚያሳየው በሉቃስ 21፥ 24 ላይ ያለው የቃላት አጠቃቀም አግባብነት ለክርስቲያናዊ ቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ ተወስኖ የሚያገለግል እንዳልሆነ ያሳያል። በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን እና ከዚያ በፊት በኤሴናውያን እና በሌሎች የኩምራኒያውያን ቡድኖችም እንኳ ለብቻው ጥቅም ላይ ይውል እንደነበር እናያለን።]

ሴፈር ዮሲፖን- የካርቴጅ ንጉሥ ሃኒባል እሱና መላ ሰራዊቱ ከነሙሉ ኃይሉ ሄዶ ምድራችንን [ጣሊያንን] ረግጦ፣ ምሽጎቻችንን አፍርሶ የሠራዊታችንን ብዛት በሰይፍ አላጠፋምን? እኛ እናንተ ላይ አድርገን እንደነበረው ለብዙ ቀናት በከበባ ውስጥ አቆየን; ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን ያዝነው…[እንግዲህ እዚህም ላይ ያለው ይህ የመረገጥ ሃሳብ የሚጠቁመው ጥፋትን ለማመልከት ነው እንጂ እንደ ተራዘመ ጥፋት የሚታይ አይደለም]።

1ኛ መቃብ 4፥ 6 “በዚያን ጊዜ ደግሞ አሕዛብ መጥተው እንዳይረግጡት የጽዮንን ተራራ በረጃጅም ቅጥርና በጽኑ ግንብ ዙሪያ ሠሩ።” [እዚህም ላይ የመረገጥን ሃሳብ የሚጠቀመው ጥፋትን ለማመልከት ነው እንጂ እንደ ተራዘመ ጥፋት አይደለም።]

ሄኖክ 99፥ 2…“ወዮላቸው … የዘላለምን ሕግ ለሚተላለፉ… በምድር ላይ በእግራቸው ይረገጣሉ” [እዚህም ላይ የመረገጥን ሃሳብ የሚጠቀመው ጥፋትን ለማመልከት ነው እንጂ እንደ ተራዘመ ጥፋት አይደለም]

እነዚህ ቀኖናዊ ያልሆኑ ምንባባት እያንዳንዳቸው የመረገጥን ሐሳብ እንዴት እንደሚገልጹ ልብ በሉ። በሚያጠፋ የጠላት ጦር ተከቦ መደምሰስን የሚያመለክት የአጭር ጊዜ ቆይታን እንጂ ከዚያ ጥፋት በኋላ የሚቆይ የተራዘመ የጥፋት ጊዜን የሚያመለክት አይደለም። ሙሉ በሙሉ መጥፋትን የሚያመለክቱ ሌሎች ተመሳሳይ የ"መረገጥ" አጠቃቀሞችን የሚያንጸባርቁ ምንባባትን ከተለያዩ ቀኖናዊ ከሆኑና ካልሆኑ ምኝጮች ተመልከቱ፣ ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ግሪክ ቴስታመንት ኮሜንታሪ (NIGTC) በሉቃስ 21፥ 24 ላይ ማብራሪያ ሲያቀርብ፣ “እነዚህ ማጣቀሻዎች የሚያሳዩት በትንቢት ውስጥ ያለውን ጭብጥ እንጂ” ቀድሞ ያልነበረ በኢየሱስ እና በአዲስ ኪዳን ጸሃፊዎች እንደ አዲስ የተፈጠረ ነገርን አይደለም፤ ይላል።

ከርዕሰ ጉዳዩ ጭብጥ በስተጀርባ ስላለው መሰረታዊ ትርጉም ተጨማሪ ግንዛቤን ለማግኘት እንዲረዳን ተመሳሳይ የጥፋት ጽንሰ ሐሳብ የሚስተናገድባቸውን ዘዳ 28፥ 45-68 እና ዳንኤል 12፥ 7 ሁለቱንም ክፍሎች ማስተያየት ይጠቅማል። በተሉይ በሉቃ 21፥ 24 ላይ “የአሕዛብ ዘመን እስኪፈጸም” የሚለውን ሐረግ በዘዳ ምዕራፍ 28-33 በኋለኛው ዘመን ጠማማ እና ክፉ በሆነው የእስራኤል ትውልድ ላይ “ፈጽሞ እስኪጠፉ ድረስ” የሚተላለፈውን የፍርድ ውሳኔ (ዘዳ 31፥ 29፤ 32፥ 5፤ 32፥ 20፤ ሐዋ 2፥ 40 እና ፊልጵ 2፥ 15) አስተያዩ። ኢየሱስ “የአሕዛብ ዘመን” ሲል የሚናገረው ሙሴ በዘዳግም ምዕራፍ 31-32 ላይ እንደተነበየው አይሁዶች የሚሸነፉበት፣ የሚገደሉበት፣ የሚባረሩበት እና የሚበተኑበትን ከሮማውያን (ከአሕዛብ) ጋር ስለሚደረገው ጦርነት ነው። ኢየሱስ ይህን በአሕዛብ የሚረገጡበትን ጊዜ ሲተነብይ በዘዳግም 28-33 ላይ የተጻፈውን በግልፅ ያሳሰበ ይመስላል።

በዘዳ 28-33፣ ሙሴ በቃል ኪዳኑ ፍርድ የሚቀበለውን የመጨረሻው

From the day I heard it was going to be published, I was determined to read it.Thank you Dr. Cindye Coates.
06/08/2024

From the day I heard it was going to be published, I was determined to read it.
Thank you Dr. Cindye Coates.

መጻኢያን ስለ ፍጥረትና በጥቅሉ ስለ ዩኒቨርስ ዕጣ ፈንታ ባላቸው ሥነ መለኮታዊ አስተንትኖና በነገረ ፍጻሜ አስተምህሯቸው ሊያስታርቋቸው ከማይችሏቸው ጥቅሶች መካከል እነዚህን ሁለቱን እስቲ እዩ...
05/26/2024

መጻኢያን ስለ ፍጥረትና በጥቅሉ ስለ ዩኒቨርስ ዕጣ ፈንታ ባላቸው ሥነ መለኮታዊ አስተንትኖና በነገረ ፍጻሜ አስተምህሯቸው ሊያስታርቋቸው ከማይችሏቸው ጥቅሶች መካከል እነዚህን ሁለቱን እስቲ እዩዋቸው፦

“የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል” (2ጴጥሮስ 3፥ 10)

“የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና። ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፥ በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፤ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው” (ሮሜ 8፥ 19-21)

እኔ ምለው፣ መጻኢነትን የመሰለ ዋሾ፣ ዘመን መዳቢነትን የመሰለም መንታ ምላስ አስተምህሮ ይኖር ይሆንን?

ተመልከቱ፣ በሁለቱ የተለያዩ ጥቅሶች ላይ ምን እንደሚያስተምሩ፦

ጌታ ሲመጣ አንዴ “አለም በእሳት ተቅጥላ ትጠፋለች”፣ “ፍጥረት ሁሉ ያበቃለታል” ይሉና፤ ደግሞ መልሰው ጌታ ሲመጣ “ፍጥረት ይታደሳል”፣ “ከጥፋትም ነጻ ይወጣል” ይሉናል።

ከመጻኢያን መካከል ጴጥሮስንና ጳውሎስን በማስታረቅ እነዚህን ሁለት ጥቅሶች ሊተረጉምልኝ የሚቻለው አንድ ሰው ይኖር ይሆንን?
እንደ ሌባ ሆኖ በሚመጣው በሚጠበቀው የጌታ ቀን፣ “ፍጥረት ይቀልጣል”፣ “ምድርም ይቃጠላል” እያለ ያስተማረ ሰው መልሶ “ፍጥረት ከጥፋት ነጻ ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ይደርሳል” ቢል ባንድ ራስ መንታ ምላስ አያደርገውምን? የትኛውን እንመን? ይሄ ምን አይነት የተወዛገበ ስነ ፍጻሜ ነው?
መጽሐፍ ግን አይዋሽም፣ እርስ በርሱ የተምታታ ትምህርትም የለውም።
እነዚህ ጥቅሶች በየአውዳቸው የያዙትን ስነ ፍጻሜአዊ ቁም ነገር ያስተማርኩበትን ልጥፎቼን ከብሎገሬ ላይ እንድታነቡ ግብዣዬ ነው

https://gizachewkr.blogspot.com/2024/01/blog-post.html?m=1

https://gizachewkr.blogspot.com/2024/05/blog-post.html?m=1

04/22/2024

የዳግመኛ ምጽአቱ ጊዜ ተራዝሟልን?

ጌታ ኢየሱስ በዳግመኛ ምጽአቱ ተመልሶ ለመምጣት በሺህዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ዘግይቶ እንደሚመለስ አስተምሮ ነበር ወይ? ለዚህ ጥያቄ መልሳቸው “አዎን! አስተምሮ ነበር” ብለው የሚሉ የቃሉ አንባብያን ብዙውን ጊዜ በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ወደተዘገቡ ወደሚከተሉት ሁለት ምንባባት ጠቅሰው ያመለክታሉ። በአስሩ ቆነጃጅት ምሳሌ፣ ሙሽራው ራሱ ጌታችንን የሚወክል ሲሆን፣ እርሱም በዚያ ምሽት ሁሉም እንቅልፍ እንቅልፍ እስኪላቸውና እስከ እኩለ ለሊት ድረስ መምጫውን እንዳዘገየ በንባብ ክፍሉ ተነግሯል (ማቴ. 25፥ 1–13)። በተመሳሳይም፣ መክሊትን በተቀበሉ ባሮች ምሳሌ፣ ጌታው የተባለው ራሱን ጌታችንን የሚወክል ሲሆን ፣ እርሱም ወደ ሩቅ አገር ተጉዞ “ከብዙ ዘመን በኋላ” እንደተመለሰ (ማቴ. 25፥ 14–30) ተነግሯል። በእነዚህ በሁለቱም ምሳሌዎች ገጸ ባህርዩ በሙሽራው ወይም በጌታው የተወከለው ጌታ ኢየሱስ፣ ረዘም ላለ ጊዜ፣ ምናልባትም (አንዳንድ የድህረ-ሺህ ዓመታት እምነት አራማጆች እንደሚሉት) በሺህዎችና በአስር ሺህዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሳይመጣ እንደሚዘገይ ወይም ምጽአቱ ከመሆኑ በፊት ብዙ ዘመን እንደሚያልፍ ተናግሯል፣ ሲሉ ይደመጣሉ።

ይህንን መደምደሚያ ውድቅ ለማድረግ ሁለት ዋና ዋና ምላሾችን ከራሱ ከምንባብ ክፍሉ ልንገራችሁ፦

# በመጀመሪያ፣ በምሳሌው ውስጥ ሙሽራው ተመልሶ የመጣው እነዚያው ቆነጃጅት በህይወት እያሉ መሆኑን ማስተዋል ይገባል፣ የሚል ነው። በቆነጃጅቱ ምሳሌ ላይ ሙሽራው የተመለሰው እነዚያው ያልተዘጋጁ ቆነጃጅት ገና በህይወት እያሉና ዘይት ሊገዙ በሄዱበት ወቅት ነው፤ ስለዚህ እነርሱ ገና በሕይወት እያሉ በገዛ ዘመናቸው ያኔውኑ ምጽአቱ ሳይደርስ አልቀረም። መክሊትን በተቀበሉ ባሮች ምሳሌም ውስጥም ያየነው እንደሆነ ጌታው ሊቆጣጠራቸውና አደራውን ከትርፉ ጋር መልሶ ሊረከብ ተመልሶ የመጣው ወደነዚያው መክሊቱን ወደ ሰጣቸው የሰዎች ቡድን ነው። ወደ እነርሱም ተመልሶ መክሊታቸውን እንዴት እንደተጠቀሙበት ካየ በኋላ ከእነርሱ መካከል በጎ ያደረጉትን ሸልሟቸዋል። ከእነርሱም መካከል ክፉ ያደረጉትን ዘልፎ ቀጥቷቸዋል። ይህ በግልጽ የሚያሳየን ተመልሶ የመጣው አደራውን በተቀበሉት ሰዎች የሕይወት ዘመን ውስጥ መሆኑን ነው። ጌታ አደራውን ወደተቀበሉት እንጂ አደራውን ሲሰጥ ወዳልነበሩት ሰዎች አልመጣም፣ አይመጣምም።

ጌታ ኢየሱስ ይህንን በማቴዎስ ወንጌል የተዘገበ ንግግሩን ሲያደርግ ጊዜው በ30 ዓ.ም አካባቢ ነበር - ተመልሶ ለመምጣት ተስፋ የሰጠውም እርሱ እየተናገራቸው በነበሩት ሰዎች የሕይወት ዘመን/ትውልድ ውስጥ የመሆኑ እውነታ ኢየሱስ ስለ ዳግም ምጽአቱ በሌሎች በርካታ የአዲስ ኪዳን ምንባባትና መግለጫዎች ውስጥ ከተናገራቸው ሌሎች ንግግሮቹ ጋር ፍጹም ይዛመዳል። ለምሳሌ፣ በማቴዎስ 16፥ ​28 ላይ፣ ኢየሱስ “እውነት እላችኋለሁ በዚህ ከሚቆሙት ሰዎች መካከል [የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን አድማጮቹን ነው]፣ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ” ብሏል። በማቴዎስ 24፥ 30-34 ላይም፣ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፡- “የሰው ልጅ በኃይልና በታላቅ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል… ይህ ሁሉ (ዳግመኛ ምጽአቱን ጨምሮ) እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም" በማለት ተናግሯል። (በተጨማሪ ማቴዎስ 10፥ 23 እና 26፥ 64 ላይ ያለውን ተመልከቱ)።

ኢየሱስ በማቴዎስ ወንጌል ባሉት ሁለት ምሳሌዎች ውስጥ ከተናገረውና በነዚህ ንግግሮቹ ከተገለጠው አመጣጡ በተለየ ሊታሰብና ሊገመት የሚችል ሌላ አመጣጥን በሌላ በየትም የንባብ ክፍል ተናገሮ እንደነበር ሊጠቁም የሚችል አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ በየትኛውም የአዲስ ኪዳን ገጽ ማግኘት አይቻልም። ኢየሱስ በእርግጠኝነት ስለ ሌላ አይነት መምጣት ተናግሮ ቢሆን ኖሮ፣ የወንግሉ ጸሐፊ ማቴዎስም ያንንው በዘገበልን ነበር። ስለ ዳግም ምጽአቱም ሆነ ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች በወንጌላዊው የተዘገበ ማንኛውም የኢየሱስ ንግግር መነበብ ያለበትም በአውዱ ውስጥ ነው፣ እንጂ የራሳችንን ግምትና ትርጉም በምንባቡ ውስጥ ለመሰንቀር ምንም መብት የለንም። እንደዚያ በማድረግ ቃሉን ለራሳችን ፍጆታ ግምቶቻችን ውስጥ የምንፈልገው ከሆነም ይህ Exegesis [ኤክሰጀሲስ] ሳይሆን Eisegesis [ኢይሴጀሲስ] ይሆናል። [ማስታወሻ፣ Eisegesis ማለት፡- “የአንድን ሰው ቅድመ-ግምት እና የአስተሳሰብ ዝንባሌውን በምንባብ ውስጥ አስገብቶ (ሰንቅሮ) ማንበብ” ማለት ነው። በሌላ በኩል ግን Exegesis ፡- “የንባብ ክፍሉ ራሱ ስለራሱ እንዲናገር ማድረግ” ማለት ነው።]

ኢየሱስ በምሳሌዎቹ ውስጥ ስለ ሌላ መምጣት እየተናገረ ቢሆን ኖሮ፣ በእርግጥ ኢየሱስ ራሱ ወይም ማቴዎስ እንዲሁ ያለ ነገር ይናገሩ ነበር! ያንን ግን አላደረጉም።.

# ሁለተኛ፣ ዳግመኛ ምጽአቱ ረዘም ላለ ጊዜ ይዘገያል እንጂ ቶሎ አይሆንም ሲሉ ይጠብቁ የነበሩት በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ዓመፀኛ ሰዎች ናቸው እንጂ ጻድቃን የሆኑ የቤተክርስቲያን ቅዱሳን አልነበሩም። በምሳሌዎቹ በክፉ አገልጋይ ምሳሌ የጠቀሳቸው፣ "ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል" ያሉትን እነዚህን ሰዎች ጌታ ኢየሱስ “ክፉ ባርያዎች” ብሏቸዋል (ማቴ. 24፥ 48)። ጳውሎስም “የጨለማ ልጆች” በማለት ገልጿቸዋል (1 ተሰ. 5፥ 3-5)። ጴጥሮስም “ዘባቾች” ብሏቸዋል (2ጴጥ. 3፥ 3-4)። ጻድቃን ግን ኢየሱስ በቅርቡ እንደሚመጣ ያምኑና ይጠባበቁ፣ ያስጠነቀቁም ነበር (ያዕ. 5፥ 7፣ 1 ጴጥ. 4፥ 17፣ ፊልጵ. 4፥ 5፣ ራዕ. 22፥ 6–12)።

ኢየሱስ በእስሩ ቆነጃጅት ምሳሌ ስለ “መዘግየት” መናገሩ እውነት ነው፣ (ይህም በ30 ዓ.ም ላይ የተነገረ ነው)። በ60 ዓ.ም ላይ ግን፣ የዕብራውያን ጸሐፊ፦ "ሊመጣ ያለው ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይመጣል አይዘገይምም" (ዕብራ. 10:36) ሲል መዘግየት እንደማይኖር በግልጽ ተናግሯል።

የኢየሱስ በምሳሌዎቹ ያነሳው "የመዘግየት" ሀሳብ ለአርባ ዓመት (ለአንድ ትውልድ) የሚቆየውን መዘግየት ነበር፣ እንጂ ይሄን ያህል በሺህዎች ለሚቆጠር ዘመን ሳይመጣ ይቆያል ማለት አይደለም። ይልቁንም፣ ኢየሱስ በፍርድ ከመገለጡ በፊት ለትውልዱ ሰዎች እሱ ማን እንደሆነ ለማወቅና ወደ ንስሃ ለመምጣት የሚያስችል በቂ ጊዜ እየሰጣቸው ነበር፤ ጴጥሮስም ስለዚሁ ነገር ሲያመለክት፦ “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ [ስለ መምጣቱ] አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉም ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለእኛ ይታገሣል” (2ጴጥ. 3፥ 9) ብሏል። ይህ ትእግስት ወይም በመዘግየት ሃሳብ የተገለጠ የቆይታ ጊዜ፣ ጌታ ኢየሱስ ፍርዱን ከማምጣቱ በፊት የገዛ ትውልዱ ሰዎች እርሱ ማን እንደሆነ እንዲያውቁና እንዲያምኑበት ዕድል እንዲያገኙ በጊዜው ለነበሩት ሰዎች በምሕረት የተሰጣቸው ነበር። ሆኖም ጌታ ኢየሱስ ከፍ ሲል በማቴዎስ ወንጌል እንዳየነውና በእነዚያ የጊዜ መግለጫዎች ላይ ደጋግሞ እንደተናገረው ይህ መዘግየት የተባለው የቆይታ ጊዜ ማብቂያው “ይህ ትውልድ” ከተባለው ዘመን አያልፍም።

እዚህ ላይ በግልጽ የሚታየውን ንጽጽር ልብ በሉ፤ ጌታ ኢየሱስ በ30 ዓ.ም አካባቢ የዳግመኛ ምጽአቱን ጊዜ አስመልክቶ የተናገረውን ንግግር አስተያዩ። በ30 ዓ.ም ላይ፣ ኢየሱስ በአንድ ትውልድ ውስጥ እንደገና ተመልሶ እንደሚመጣ ተናግሮ ነበር (ማቴ. 10፥ 23፤ 16፥ 28፣፤ 24፥ 30–34፤ 26፥64)። ሆኖም ከሠላሳ አምስት ወይም ከዚያ ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ፣ “ይህ ትውልድ” በተባለው ዘመን መሟጠጫ ላይ፣ ኢየሱስ አሁንም በመልአኩ አማካኝነት “እነሆ፣ እኔ በቶሎ እመጣለሁ…" (ራዕይ. 22፥ 7፣ 10). ማለቱን ልብ በሉ። በመካከል ያለው ወደ ሠላሳ አምስት ዓመት ያህል የሚጠጋ የጊዜ መደብ መሆኑንም አስተውሉ።

ጌታ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንደሚመጣ በገባላቸው የተስፋ ቃል መሰረት፣ በ70 ዓ.ም ላይ ኢየሩሳሌምና መቅደስዋ በወደሙ ጊዜ፣ ዳግመኛ በፍርድ ተመልሶ መጥቷል። ይህንን የተፈጸመ የዳግመኛ ምጽአቱን የፕሪቴሪስት ነገረ ፍጻሜ አቋማችንን አስረግጠን የምንናገርበት ደርዘን ሙሉ ውስጣዊ የቃሉ ማስረጃና ውጫዊ የታሪክ ምስክርነት ለማወቅ፣ ለመጠየቅና ስታምኑ የኖራችሁትን የመጻኢነት አቋም በቃሉ ሚዛን ላይ አስቀምጦ ለመለካት የሚይስችሏችሁ፣ በዚህም የቃሉ ትምህርት ላይ በተቃውሞ ሊቀርቡ በሚችሉ ልዩ ልዩ ክርክሮች ምካቴ የሚሆኑ ሃሳቦችን የሚጠቁሙ ተጨማሪ ጽሁፎችን ማየት ቢያስፈልጋችሁ፣ ብሎገሬን እንድትጎበኙ እጋብዛለሁ።

https://gizachewkr.blogspot.com/2023/12/blog-post.html?m=1

ግዛቸው።

ዳግመኛ ምጽአትን መጠባበቅ ይገባናልን? በዚህ ርዕሰ ጉዳይ የተለያዩ ጥሁፎችንና ልጥፎችን በማህበራዊ ሚዲያ ማጋራቴ ይታወሳል፣ የገባኝን የእግዚአብሔር ቃል እውነት ለማካፈል ዛሬም የተ...

Address

2235 Glenallan Avenue
Silver Spring, MD
20906

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Philologus66 posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Place Of Worship

Send a message to Philologus66:

Share