Gateway to Heaven St. John Monastery in California

Gateway to Heaven St. John Monastery in California ኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ወቅድስት አርሴማ የኢ.ኦ.ተ. አንድነት ገዳም በካሊፎርኒያ
St. John the Baptist & St. Arsema Ethiopian Orthodox Tewohedo Monastery in California

  ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት በክብር ያረፉት ነሐሴ ፳፬ ቀን ነው። በዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በድምቀት ታከብረዋለች።አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከአባ...
08/30/2026


ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት በክብር ያረፉት ነሐሴ ፳፬ ቀን ነው። በዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በድምቀት ታከብረዋለች።

አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብ እና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኃረያ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ፲፪፻፲፪ ዓ.ም በቡልጋ አውራጃ ኢቲሳ በሚባል ቦታ ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በሦስተኛው ቀን እሑድ ከጠዋቱ በሦስት ሰዓት ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው‹‹አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፤ አንዱ አብ ቅዱስ ነው፤ አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው፤ አንዱ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ነው››በማለት ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ በተወለዱ በ፲፭ ዓመታቸው መዓርገ ዲቊናን፤ በ፳፪ ዓመታቸው ደግሞ መዓርገ ቅስናን ከግብጻዊው ጳጳስ አባ ጌርሎስ (ቄርሎስ) ተቀብለዋል፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በመጀመሪያ በወላጆቻቸው የወጣላቸው ስም ‹ፍሥሐ ጽዮን› ነበር፡፡

በአንድ ወቅት በሕፃንነታቸውም ወደ ጫካ ለአደን በሔዱበት ጊዜ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ ጸጋ መንፈስ ቅዱን አሳደረባቸው፡፡ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ወንጌል ወዳልተዳረሰበት ቦታ እንደሚልካቸውም አስረዳቸው፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ከአውሬ አዳኝነት ሰውን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመመለስ እንደ ተመረጡ፤ አጋንንትን የማውጣት፣ ተአምራትን የማድረግ ሥልጣን እንደ ተሰጣቸው፤ ስማቸውም ‹ተክለ ሃይማኖት› እንደሚባል፤ ትርጓሜውም ተክለ አብ፣ ተክለ ወልድ፣ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት እንደሆነ አበሠራቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ያላቸውን ንብረት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያንና ለነዳያን ሰጥተው ‹‹አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደ ተከፈተ ተውኹልህ›› በማለት ቤታቸውን ትተው ወንጌልን ለማስተማር ፈጥነው ወጡ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምረው በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክና ተአምራትን በማድረግ ብዙ አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፤ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መልሰዋል፡፡ አብያተ ክርስቲያናትንም አሳንጸዋል፡፡

በደብረ ሊባኖስ ገዳምም (ገዳመ አስቦ) ዋሻ በመግባትም ሁለቱን በፊት፣ ሁለቱን በኋላ ሁለቱን በቀኝ፣ ሁለቱን በግራ ስምንት ጦሮችን ተክለው እጆቻቸውን በትእምርተ መስቀል በመዘርጋት የክርስቶስን ሕማም፣ ሞትና ነገረ መስቀል በማሰብ በተመስጦ ሌሊትና ቀን ያለ ማቋረጥ በጾም፣ በጸሎት ተወስነው ሲጋደሉ፤ ከቊመት ብዛት የተነሣ በ፺፪ኛ ዓመታቸው ጥር ፬ ቀን ፲፪፻፹፱ ዓ.ም አንዲቱ የእግራቸው አገዳ ተሰብራለች፡፡ ደቀ መዛሙርቱም የመንፈሳዊ አባታቸውን ስባረ ዐፅም (የዐፅም ስባሪ) አክብረው በሥርዓት አኑረዋታል፡፡ እግራቸው እስኪሰበር የቆዩባቸው ዓመታትም ፳፪ ናቸው፡፡ ለሰባት ዓመታት በአንድ እግራቸው ቆመው ያለ ምግብና ያለ ውኃ በትኅርምት ሌሊትና ቀን እንደ ምሰሶ ጸንተው በትጋት ለሰው ዘር ዅሉ ድኅነትን ሲለምኑ ኖረዋል፡፡ ከሰባቱ ዓመታት ውስጥ ጥቂት ውኃ የቀመሱት በአራተኛው ዓመት ብቻ እንደ ነበረ መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል፡፡

አቡነ ተክለሃይማኖት ምድራዊ ሕይወታቸውን በተጋድሎና በሐዋርያዊ አገልግሎት ከፈጸሙ በኋላ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ የሚያልፉበት ቀን ተቃረበ፡፡ በዚህ ጊዜ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን መላእክት፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ወደ እርሳቸው በመምጣት የሚያርፉበት ዕለት መድረሱን ነገራቸው፡፡ የተጋድሏቸውን ጽናት አድንቆ በስማቸው መታሰቢያ ለሚያደርጉ፣ ለነዳያን ለሚመጸዉቱ ቤተ ክርስቲያን ለሚያሠሩ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸው በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ ስለ ተጋድሏቸው ጽናትም ‹‹በሰው እጅ የማይለካውን ይህንን የመንግሥት አዳራሽ ውሰድ›› በማለት የመለኮትን ነገር የሚናገር የእሳት አንደበት ያለው የጸጋ ልብስ አልብሷቸዋል፤ በመስቀል ምልክት ያጌጡ ሰባት የሕይወት አክሊላትንም አቀዳጅቷቸዋል፡፡

ጻደደቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት የዕረፍታቸው ጊዜ መቃረቡን ባወቁ ጊዜ የመንፈስ ልጆቻቸውን ጠርተው ጌታችን የነገራቸውን ሁሉ አስረድተው አባታዊ ምክርና ተግሣፅ ከሰጧቸው በኋላ ነሐሴ ፳፬ ቀን ከዚህ ዓለም ድካም ዐርፈዋል፡፡ የመንፈስ ልጆቻቸውም ለአንድ ቅዱስ አባትና ካህን በሚገባ ሥርዓት በማኅሌት፣ በዝማሬና በምስጋና ቀብረዋቸዋል፡፡ ጌታችንም ከእመቤታችንና ከቅዱሳን መላእክት ጋር ተገልጾላቸዋል፤ነፍሳቸውንም ‹‹የጠራሽ፣ ንጽሕት ነፍስ ሆይ ወደ እኔ ነዪ›› ብሎ በክብር ተቀብሏታል፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዚህ ዓለም የኖሩበት ዕድሜ ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከዐሥር ወር ከዐሥር ቀን ነው፡፡ በእናት አባታቸው ቤት ፳፪ ዓመት፤ በከተታ ፫ ዓመት፤ በይፋት ፱ ወር፤ በዳሞት ፲፪ ዓመት፤ በአማራ ፲ ዓመት፤ በሐይቅ ፲ ዓመት፤ በደብረ ዳሞ ፲፪ ዓመት፤ በትግራይና በኢየሩሳሌም ገዳማት ፩ ዓመት፤ ዳዳ በሚባል አገር ፩ ወር፤ በደብረ አስቦ ገዳም ፳፱ ዓመት ከ፲ ቀን መቆየታቸውን መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል (ገ.ተ.ሃ ፶፱፥፲፬-፲፭)፡፡

ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሕይወታቸውን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደ ገበሬ ታጥቀው ይህንን ዓለም ንቀው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው በብሕትውና ከመኖራቸው ባሻገር እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ የሰበኩ፤ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሐዋርያ ናቸው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያችንም ነሐሴ ፳፬ ቀን የዕረፍታቸውን በዓል በትላቅ ደስታ ታከብራለች፤ የጻድቁ በረከት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ከማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ የተወሰደ!

ምንጭ፡–መጽሐፈ ስንክሳር፣ ነሐሴ ፳፬ ቀን፣ገድለ ተክለ ሃይማኖት፡፡
-አሜሪካ
እንኳን አደረሳችሁ
የጻድቁ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ረድኤት በረከት ይደርብን!

ምትረተ ርእሱ ለዮሐንስ  በዓለ ንግሥ  በገዳማችን የመስከረም 2/2019 ዓ/ም አይቀርም! #ኆኅተ ሰማይ ገዳም ሚዲያ አሜሪካ
08/27/2026

ምትረተ ርእሱ ለዮሐንስ በዓለ ንግሥ በገዳማችን
የመስከረም 2/2019 ዓ/ም አይቀርም!

#ኆኅተ ሰማይ ገዳም ሚዲያ አሜሪካ

  ደራሲ   !!!!በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን  ለቅዳሴ ጸሎት ከምንጠቀማቸው  ቅዳሴያት በተለይ ቅዳሴ ማርያም በምዕመናን ልብ የተሳለ ነው ምሥጢረ ሥላሴን ምስጢረ ሥጋዌን የእ...
08/07/2026

ደራሲ !!!!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለቅዳሴ ጸሎት ከምንጠቀማቸው ቅዳሴያት በተለይ ቅዳሴ ማርያም በምዕመናን ልብ የተሳለ ነው ምሥጢረ ሥላሴን ምስጢረ ሥጋዌን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትን በግልጽ የያዘ ነው። ይህን ቅዳሴ ማርያምን ማን ነው የደረሰው ሕይወቱ ለእመቤታችን ያለው ፍቅር ምን ይመላል የሚለውን እንመለከታለን። ስለ አባ ሕርያቆስ ማንነት እንደቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት መሠረት ግብጻዊ የሆነ ለእመቤታችን ልዩ ፍቅር ያለው ታላቅ አባት እንደነበረ እንረዳለን።

አባ ሕርያቆስ ተወልዶ ያደገው በምድረ ግብጽ ሲሆን አካባቢው ብሕንሳ (ንሒሳ) ይባላል:: ይህቺ ቦታ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ጨምሮ በርካታ ቅዱሳንን ያፈራች ናት።

ቅዱሱ በዘመኑ የተለየ ማንነት የነበረው ሰው ነው:: ገና ከልጅነቱ እመ ብርሃንን የሚወዳት በመሆኑ ቅን የዋህና ገራገር ነበረ:: መቼም እመቤታችን ይወዳል ሲባል እንደ ዘመኑ በአፍ ብቻ እንዳይመስለን:: ቀንና ሌሊት ለፍቅሯ የሚተጋ ማዕበለ ፍቅሯ የሚያማታው ሰው ነበር እንጂ።

የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ስም ሲጠራ ምስጥ ብሎ ልቡናው ይሰወርበት ነበር:: ዘወትር የእርሷን ፍቅር ከማሰብ በቀር ሌላ ሥራ አልነበረውም:: የልጅነት ጊዜው ሲያልፍም ድንግልንና ቸር ልጇን ያገለግል ዘንድ መነነ::

ዘመኑ ዘመነ ሊቃውንት እንደ መሆኑ ሁሉም ያለትምህርት ሲተጉ እርሱ ግን ለጸሎትና ለደግነት ብቻ ነበር የሚተጋው:: ከትምሕርት ወገንም የሰሞን ጓዋዞች አንዳንድ ቅዳሴያትንና የዳዊትን መዝሙር ተምሮ ነበር::

በተለይ ግን የዳዊትን መዝሙር እየጣፈጠው መላልሶ መላልሶ ያመሰግንበት ነበር:: ከዳዊት መካከል ደግሞ መዝ. 44ን ፈጽሞ ይወዳት ነበር:: ይህቺ ጥቅስ የምትጀምረው "ጐስዐ ልብየ ቃለ ሠናየ" ብላ ነው:: የውስጧ ምሥጢርም ስለ ድንግል ማርያምና ስለ ክርስቶስ ነው::

አባ ሕርያቆስ ይህቺን መዝሙር በቃሉ አጥንቶ ቁሞም ተቀምጦም ተኝቶም ተነስቶም ያለ ማቁዋረጥ ይላት ነበር:: እየጣፈጠችው "ልቡናየ በጐ ነገርን አወጣ" እያለ ይዘምር ነበር:: በወቅቱ ታዲያ የብህንሳ ኤዺስ ቆዾስ በማረፉ ምትክ ሲያፈላልጉ መንፈስ ቅዱስ አባ ሕርያቆስን መረጠ::

ምንም አለመማሩ ቢያሰጋቸውም "በጸሎቱ በደግነቱ ሃገር ይጠብቃል" ብለው ሾሙት:: ነገር ግን ምንም በሥልጣን የበላያቸው ቢሆን ተማርን የሚሉ ሰዎች ይጠሉት ይንቁትም ነበር:: እርሱ ግን እንደ ጠሉኝ ልጥላቸው እንደ ናቁኝ ልናቃቸው ሳይል በፍቅር ያገለግል ነበር።

አንድ ቀን ታዲያ መንገድ ይወጣል በበርሃ ብቻውን እየተራመደ "ጐሥዐ ልብየ ቃለ ሠናየ" እያለ እየዘመረ ተመሥጦ ቢመጣበት መንገድ ሳተ:: እርሱ በምስጋናው ሲደሰት እግሩ ግን ከገደል ጫፍ ደርሶ ነበር:: ገደሉን ልብ አላለውም ነበርና ሳይታወቀው ወደ ገደሉ ውስጥ ተወረወረ::
በዚህ ጊዜ ደንግጦ ቢመለከት እጅግ ጥልቅ በሆነ ገደል ውስጥ ራሱን አገኘው:: ነገር ግን አንድም አካሉ አልተነካም:: ልብሱም አልቆሸሸም:: ለራሱ ተገርሞ ዙሪያ ገባውን ሲመለከት እርሱ ቁጭ ያለበት ብርሃንን የተሞላ የልብስ ዘርፍ ነበር::

"እመ ብርሃን!" ብሎ ሲጮህ የሰማይና የምድር ንግሥት የሆነች እመቤታችን ከፊቱ ቁማ ታየችው:: እመ አምላክን በገሃድ ቢያያት እንደ እንቦሳ ዘለለ:: የሚገርመው ደግሞ የተቀመጠበት የድንግል ማርያም የቀሚሷ ዘርፍ ነበር:: እመቤታችን አነጋገረችው ባረከችው። ፍቅሯ ቢመስጠው ከሰው ሳይገናኝ ምግብም ሳይበላ እዚያው ገደሉ ውስጥ ለ1 ዓመት ያህል በተመስጦ ቆይቷል::

በኋላ እመ ብርሃን መጥታ ከገደሉ አውጥታ ወደ ሐገሩ መለሰችው:: ከጥቂት ጊዜ በኋላም አንድ ፈተና ገጠመው:: አንድ ቀን እመቤታችን በተወለደችበት ግንቦት 1 ቀን ቅዳሴ "ማን ይቀድስ" ሲባል ሰዎቹ "አባ ሕርያቆስ ይሁን" አሉ::
እርሱ ግን "እኔ አይቻለኝም እናንተ ሊቃውንት ቀድሱ" አላቸው:: "አይሆንም" ብለው እርሱን አስገቡት:: ይህንን ያደረጉት ለተንኮል ነበር:: ልክ ወንጌል ተነቦ ፍሬ ቅዳሴ ሲመረጥ እርሱ " ቅዳሴ እግዚእን (የጌታ ቅዳሴን) ልቀድስ" ቢል እነርሱ "የሚቀደሰው የሊቅ ቅዳሴ ነው" አሉት::

ይህንን ያሉት እርሱ የሊቃውንቱን ቅዳሴ አያውቅምና በሰው ፊት እንዲዋረድ ነው:: እንዲህም ብለው ባለመማሩ ተሳለቁበት:: አባ ሕርያቆስ ግን እያዘነ ወደ መንበሩ ዞረ:: ድንግልንም "እመቤቴ መናቄን መገፋቴን ተመልከች" አላት::
ወዲያው ግን ድንግል ማርያም ወርዳ ቀጸበችው (ጠራችው):: በዘርፋፋው ቀሚሷ ላይም ረቂቅ የሆነ ቅዳሴን አሳየችው:: ደጉ ሰው ደስ ብሎት "ጐሥዐ ልብየ" ሲል 2ቱ እግሮቹ ከመሬት ከፍ አሉ:: እርሱም "ወአነ አየድእ ቅዳሴሃ ለማርያም" ብሎ እስከ ኃዳፌ ነፍሱ ድረስ አደረሰው::

ሕዝቡና ካህናቱ በሆነው ነገር ሲደነቁ: አንዳንዶቹ "ዝም ብሎ ነው የቀባጠረ" አሉ:: ቅዱሱ ግን ቅዳሴ ማርያምን በብራና ጠርዞ በሕዝቡ መካከል ድውይ ፈወሰበት:: እሳት ሳያቃጥለው ውሃ ሳይደመስሰው ቀረ::

መጽሐፈ ቅዳሴው ሙትንም አስነስቷል ከዚህች ሰዓት ጀምሮ በዘመኑ ቁጥር 1 ሊቅ ሆነ:: ብዙ መጻሕፍትን ተርጉሟል:: ሊቁ እንዲህ በንጹሕ ተመላልሶ ዐርፏል። አምላከ ቅዱሳን ሊቃውንት የድንግል እመቤታችንን ጣዕሟን ፍቀሯን ያሳድርብን:: የአበውን ሃብትና በረከትም አይንሳን::

ያለ ትናንት ቀዳማዊ ያለ ዛሬ ማዕከላዊ ያለ ነገ ደኀራዊ ዘመን የማይቆጠርለት ከዘመናት በፊት የነበረ ፍጥረታትን ያለድካም የፈጠረ የቸርነት ባሕሪዉ ጥልቀቱ የማይለካ ከምጥቀት በላይ ከጥልቀት በታች ያለውን ሁሉ የሚመረምር እንደ ቸርነቱ አባት እንደ መለኮቱ አምላክ የሆነዉ እግዚአብሔር ሀገራችንን ብሎም አለምን ይጠብቅልን።

ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደችልን ምሥራቃዊቷ እመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን እመ አምላክ ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ትጠብቅልን።ከክፉ ወረርሽኝና በሽታ ትከልለን ፣ትጠብቀን ፣ትሰውረን፣ ታድነን አሜን።

▮አሜሪካ▮

እንኳን አደረሳችሁ!

 #ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የጾመ ፍልሰታ ለማርያም መግባት አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ አባታዊ ቃለ በረከት አስተላለፉ።“መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ"በስመ አብ ወወልድ ወመ...
08/07/2026

#ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የጾመ ፍልሰታ ለማርያም መግባት አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ አባታዊ ቃለ በረከት አስተላለፉ።

“መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ"
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሓዱ አምላክ፣ አሜን !

በሀገር ውስጥና በመላው ዓለም የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች በሙሉ!

የሰውን ወገን ለማዳን የልጁ ማደሪያ ትሆን ዘንድ ድንግል ማርያምን የመረጠ መፍቀሬ ሰብእ እግዚአብሔር ኣምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ዓሥራ ስምንት ዓመተ ምሕረት ጾመ ማርያም ኣደረሰን ኣደረሳችሁ!
“ወእመሰ ታፈቅሩኒ ዕቀቡ ትእዛዝየ፡- ከወደዳችሁኝስ ትእዛዜን ጠብቁ" (ዮሐ.14፥15)፤
ፍቅር የሕያዋን ኣካላት ረቂቅ መገናኛ ነው፣ ሕያዋን ኣካላት በውጫዊው ግዙፍ ኣካላቸው በተወሰኑ ጊዜያትና ቦታ ይገናኛሉ ፤ ስለ ጋራ ጉዳያቸውም በጋራ ይመክራሉ፤ ይበልጥም ይቀራረባሉ፡፡

ይሁንና የሕያዋን ኣካላት ግንኙነት በኣካል በጊዜና በቦታ ብቻ የተወሰነ ኣይደለም፣ በፍቅረ መንፈስ ተገናኝተውም ይግባባሉ፣ ከኣካላዊ ግንኙነት በላይ የበለጠም ይኸው ፍቅረ መንፈስ ነው፤ ከዚህ ኣንጻር እግዚአብሔርንም ማግኘት የምንችለው በዚሁ ፍቅረ መንፈስ ሆነን በእምነት ዓይን ነው!

ይህም በመሆኑ ሓዋርያው ቅዱስ ዮሓንስ በመልእክቱ “በፍቅር የሚኖር በእግዚአብሔርይኖራል፣ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል" በማለት ያስተምረናል፣ (1ዮሐ. 4፥16) ይህም ማለት ከሱ ጋር በፍቅር ስንገናኝ፤ እሱም በኛ፣ እኛም በእሱ የመኖሩ ኩነት ይፈጠራል ማለት ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!

ጌታችን “አፍቅሮ ለእግዚአብሔር ኣምላክከ፤- አምላክህን እግዚአብሔርን ውደደው" በማለት በፍጹም ልባችን እንድንወደው፣ እንደዚሁም ራሳችንን በምንወድበት መጠን እርስ በእርሳችን እንድንዋደድ ማዘዙን እናውቃለን፤

የመውደዳችን መለኪያ ሚዛንና መገለጫ ምልክትም ትእዛዙን ማክበርና መጠበቅ እንደሆነ “ብትወዱኝስ ትእዛዜን ጠብቁ” በማለት ኣስተምሮናል
ከዚህ ኣኳያ ጌታን መውደድ ማለት ትእዛዙን በመጠበቅ የሚገለጽ ግዙፍ ነገር እንጂ ምናባዊና የማይታይ ድብብቆሽ ነገር ኣይደለም ማለት ነው፣

ጌታችንን የመውደድ ነገር ትእዛዙን በመጠበቅ የሚገለጽ ከሆነ ትእዛዙ ምንድን ነው? የሚለውን ማየት ኣስፈላጊ ይሆናል፤ ትእዛዙን በጥቅል ስናይ እግዚአብሔርንና ባልንጀራን በመውደድ እንደሚጠቃለል ራሱ ጌታችን ኣስገንዝቦናል፣

በተለይም በባልንጀራችን ላይ የምንከተለው መውደድ ከላይ እንደተገለጸው “እንደራስህ ኣድርገህ ውደድ" ተብለ በግልጽ ተቀምጦኣል፤
የሰው ባልንጀራ እነማን ናቸው? በሕይወት ያሉት ናቸው? ወይስ የሞቱት? ወገን ዘመድ? ወይስ የሰው ወገን በሙሉ የሚለውንም ማወቅ ኣስፈላጊ ነው፡፡

ጌታችን ነገሩን በዚህ ደረጃ ለያይቶ ኣላስቀመጠም፣ ለምን? ቢባል ባልንጀራ ማለት የተወሰነን የማኅበረ ሰብ ወገን የሚያሳይ ሳይሆን መላውን የሰው ወገን የሚገልጽ በመሆኑ፤ እንደዚሁም የሞቱም ሆኑ ያለነው ሁላችን በእሱ ፊት ሕያዋንና እርስ በእርሳችን ባልንጀሮች በመሆናችን ነው፤

በመሆኑም መዋደዳችንም ሆነ መከባበራችን በሕይወተ ሥጋ ሳለን ብቻ ሳይሆን ከዚያም በኋላ እስከ በሌለው ዕድሜ በመሆኑ ጌታችን በጊዜ በቦታና በከፊል ለይቶ ኣላስቀመጠም፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት !

ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምሮ ለ፲፭ ቀናት የምንጾመው የጾመ ማርያም መነሻ ምክንያቱ የእግዚአብሔርትእዛዝና ፍቅር ነው፣

እግዚአብሔር ሰውን በኣጠቃላይ በተለይም ደግሞ እንደፈቃዱ የኖሩ ቅዱሳንን እንድናከብርኣዞናል ክቅዱሳን ፍጥረታት መካክል ደግሞ ቅድስት ድንግል ማርያም የመጀመሪያውን ደረጃ ትይዛለች፤

ይህም በመሆኑ ከፍጥረት ወገን ከሏ ክብር የሚደርስ ባለመኖሩ ከሁሉም ኣብልጠን እናክብራታለን፤

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ደረጃ የድንግል ማርያምን ክብር ስትገልጽ ክእግዚአብሔርና ለባስያነ እግዚአብሔር ክሆኑ ቀደምት ኣበው ተምራ ነው!

በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው ዕውቁ ቅዱስና ዓለም ዓቀፋዊው አባት ቅዱስ ኤፍሬም የድንግል ማርያምን ክብር! ቅድስና እና ልዕልና ሲናገር “ይእቲ ተዓቢ እምኪሩቤል፡ ወትፈደፍድ እምሱራፌል፣ እስመ ኮነት ታቦተ ለአሓዱ ዘእምቅድስት ሥላሴ- እሷ ከኪሩቤል ትበልጣለች! ከሱራፌልም ትልቃለች፣ ከቅድስት ሥላሴ ኣንዱ ለሆነው ታቦት ወይም ማደሪያ ሆናለችና" በማለት አስተምሮናል፡፡

በመሆኑም ለስሟ መታሰቢያ በሆነው በዚህ ጾም ድንግል ማርያምን በዚህ ደረጃ ስናክብርትእዛዙን እንጠብቃለን፤ ትእዛዙን በመጠበቃችን ደግሞ እሱን መውደዳችንን እናረጋግጣለን ! እኛ ድንግል ማርያምን እንድንወዳት "እናታችሁ'' ብሎ እንዳዘዘ፣ እሷም ልትወደን “ልጆችዅ ተብላ ታዛለችና ስለኛ ትጸልያለች፡፡

በጸሎቷም ከመከራ ትታደገናለች፤ በኣጠቃላይ በእግዚአብሔር' በቅዱሳንና በእኛ መካከል ያለው ግንኙነት በዚህ ትእዛዝና ፍቅር በትዕይንተ ዓለም ባለች ቤተ ክርስቲያን ዘንድ የተሳሰረ ነው፡፡

ስለሆነም በዚህ የጾመ ፍልሰታ ለማርያም ሱባዔ የተራቡትን በመመገብ፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የተጣሎትን በማስታረቅ፤ የታመሙትንና የታስሩትን በመጠየቅ፤ ቅዱስ ቍርባንን በመቀበልና ለኃጢኣታችን የንሥሐ ሥርየትን በመለመን ሱባዔውን ልናሳልፍ ይገባል፡፡

በመጨረሻም

በሀገራችንም ሆነ በዓለም ዙሪያ ከባድ ስጋት የሆነው የፍጥረት ኣውዳሚ ጦርነትን በመለኮታዊ ጥበቡና ሥልጣኑ እንዲያስቆምልን በቅን ልቡና፤ በትሑት ሰብእና ሆነን እግዚአብሔርን በዚህ ሱባዔ እንድንጠይቀው ኣደራ ጭምር ኣባታዊ መልክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፤

የተባረከና የተቀደስ ጾም ያድርግልን፤

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣ አሜን!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእስ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘኣኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ነሐሴ 1 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ

_አሜሪካ

  ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን!ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ፀጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን፡፡ አእምሮውን ጥበቡን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን፡፡ቅድስት፣ ...
08/07/2026


ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን!

ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ፀጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን፡፡ አእምሮውን ጥበቡን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን፡፡

ቅድስት፣ ንጽሕት፣ ጽንዕት፣ ክብርት፣ ልዩ ሲል ነው፡፡

ንጽሕት አለ፦ ሌሎች ሴቶች ከነቢብ ከገቢር ቢነጹ ከሐልዮ አይነጹም፡፡ እርሷ ግን ከነቢብ፣ ከገቢር፣ ከሐልዮ ንጽሕት ናትና፡፡

ጽንዕትም አለ፦ ሌሎች ሴቶች ቢጸኑ ለጊዜው ነው፡፡ ኋላ ግን ተፈትሖ አለባቸው፡፡ እርሷ ግን ቅድመ ፀኒስ፣ ጊዜ ፀኒስ፣ ድኅረ ፀኒስ፤ ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ ድኅረ ወሊድ፣ ጽንዕት ናትና፡፡

ክብርትም አለ፦ ሌሎችን ሴቶች ብናከብራቸው ጸድቃንን ሰማዕታትን ወልደዋል ብለን ነው፡፡እርሷን ግን እመ አምላክ ወላዲተ አምላክ ብለን ነውና፡፡

ልዩም አለ፦ እናትነት ከድንግልና አስተባብራ የምትገኝ ከእመቤታችን በቀር ሌላ ሴት የለችምና፡፡

የእመቤታችንን ጣዕሟን በአንደበታችን፣ ፍቅሯን በልቡናችን ይሳልብን ያሳድርብን።

#እንኳን የጾመ ፍልሰታ ለማርያም በሰላም አደረሳችሁ

Join us for Saint John the Baptist Commemoration Day — September 12, 2026
07/30/2026

Join us for Saint John the Baptist Commemoration Day — September 12, 2026

 ‎በሰሜን አሜሪካ ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና ኦሪዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የገዳማችን መሥራች የሆኑት የብፁዕ  አባታችን አቡነ ቴዎፍሎስ  (ዶክተር)  ወላጅ እናት እማሆይ አየሁ ተመስገን (...
07/15/2026



በሰሜን አሜሪካ ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና ኦሪዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የገዳማችን መሥራች የሆኑት የብፁዕ አባታችን አቡነ ቴዎፍሎስ (ዶክተር) ወላጅ እናት እማሆይ አየሁ ተመስገን (ወለተ ማርያም) በተወለዱ በ85 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም ዐረፉ።

ሐምሌ ፰/፳፻፲፰ ዓ/ም

ጸሎተ ፍትሐታቸው ላይም የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊ/ል ኢሳይያስ ጤናው የሀገረ ስብከቱ የክፍል ኃላፊዎች፣በርካታ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በተገኙበት በጽርሐ ጽዮን አብማ ቅድስት ማርያም ካቴድራል ተከናውኖ ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል።

ገዳማችን ኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስና ቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም በእናታችን በእማሆይ አየሁ ተመስገን (ወለተ ማርያም) ዕረፍት የተሰማውን ኀዘን እየገለጽን ነፍሳቸው በአባቶቻችን በአብርሃም በይስሐቅ በያዕቆብ ዕቅፍ ያስቀምጥልን ለብፁዕነታቸውና ለሌሎች ወዳጅ ዘመዶቻቸውም መጽናናትን እንዲሰጥልን እንመኛልን ጸሎታችን ነው።

መረጃው የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሕዝብ ግንኙነት ነው።

07/10/2026

ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም
የሉቃስ ወንጌል 7:28
በመምህር አባ ወልደ ሰማዕት

07/10/2026

የካህናት ልብሰ ትክህኖ ፤ የመዘምራን ልብስ ፤ የአባቶች ካባ ፤ በትዕዛዝ በገዳማችን ውስጥ ማሰፋት ይችላሉ። በገዳማችን ውስጥ የሚሠሩ የተለያዩ መስቀሎች እና የእንጨት ስራዎችም ያገኛሉ። ቅዱሳት መጻህፍት እና ለስጦታ የሚሆኑ እቃዎችን ለመግዛት ወደ የገዳማችንን ንዋያተ ቅዱሳን መደብር ይጎብኙ።

07/09/2026

የመጥምቀ መለኮት ቅዱሰ ዮሐንስ ዓመታዊ በዓለ ንግስ

Address

69300 Vineyard Canyon Road
San Miguel, CA
93451

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Gateway to Heaven St. John Monastery in California posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Place Of Worship

Send a message to Gateway to Heaven St. John Monastery in California:

Shortcuts

Share