Chicago Yemsrach Evangelical Church

Chicago Yemsrach Evangelical Church Chicago Yemesrach Evangelical Church is a congregation where you can grow in a real relationship with God through faith.

07/24/2025

To our beloved family Ethiopian and Eritrean community in the Chicagoland area:
You are invited to join us for a special conference to worship and glorify our Lord and savior Jesus Christ.
Blessings to all!

03/29/2025

እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ

ክርስቲያኖች ያለን ትልቁ ተስፋ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ተመልሶ መምጣት ነው። ጌታችን በምድር ያለውን ስራውን ፈጽሞ ወደ አብ እንደሚሄድ ለደቀ መዛሙርቱ በነገራቸው ጊዜ በልባቸው ታውከው ነበር። ይህም ደግሞ ከጌታ ጋር መለየትን ስላልፈጉ ነበር። ይህንን ያየው ጌታ የደቀመዛሙርቱን ልብ የደገፈው የዳግም መምጣቱን ተስፋ በመስጠት ነበር። ጌታ እንዲህ አላቸው፡ “ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ” (ዮሐ. 14:1-3)። በዚህ ቃል ውስጥ የምናገኘው ትልቁ ተስፋ “ሁለተኛ እመጣለሁ” የሚለው ተስፋ ነው። ጌታችን ሁለተኛ ይመጣል። ሁለተኛ የሚመጣው የኛን የኃጢያት እዳ በመስቀል ላይ ሞቶ ለመክፈል አይደለም። ነገር ግን እርሱ ወዳለበት ክብር ሊወስደን ሁለተኛ ይመጣል።

ጌታችን ባረገበት እለትም የሰማይ መላእክት ይህንኑ እውነት አረጋግጠዋል። በሐዋሪያት ስራ ላይ እንደማናነበው ጌታችን ሐዋሪያቱን ለአርባ ቀናት አብሮአቸው ቆይቶ ስለ እግዚአብሔር መንግስትና ሊቀበሉት ስላላቸው የመንፈስ ቅዱስ ተስፋ አስተምሮአቸው እያዩት “ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው” (ሐዋ. 1፡ 9)። በዚያን ጊዜ ደቀመዛሙርቱ እርገቱን ትኩር ብለው እየተመለከቱ ሳለ መላእክት የዳግም መምጣቱን ተስፋ በማስተወስ አጽኗኗቸው። ዳግም ስለመምጣቱም “የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው” (ቁ. 11)። ጌታ በክብር በዳመናት ተሰውሮ እንዳረገው በክብር ደግሞ ተመልሶ ይመጣል።

ይህንኑ ተስፋ ሐዋሪያቱም በትምህርታቸው አስተላልፈውልናል። በ 1ኛ ተሰሎንቄ 5:13-18 ላይ ሐዋሪያው ጳውሎስ ቅዱሳኑ ተስፋ እንደሌላቸው እንደሌሎች እንዳያዝኑ ይመክራል (ቁ. 13)። ለዚህ ደግሞ የሚሰጠን ትልቁ ምክንያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተምልሶ ሲመጣ የሚሆነውን በማስታወስ ነው። ጌታችን “በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳል” (ቁ.16)። የጌታ ሁለተኛ መምጣት የተገለጠ ነው። በመላእክት ታጅቦ፣ በእሳት ነበልባልና በታላቅ የመለከት ድምጽ ነው የሚመጣው። በእርግጥ ጌታ ሲመጣ ቃሉ “ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል” (ራእይ 1:7) እንዲሚል አመጣጡ በግልጽና በታላቅ ክብር ነው። ጌታ ሲመጣ በጌታ ያንቀላፉት የማይበሰብሰውን የከበረ አካል ለብሰው አስቀድመው ይነሳሉ (1 ተሰ. 5:16፤ 1 ቆሮ. 15:51-52)። በሕይወት የምንቀር ቅዱሳን ደግም በቅጽበት አይን ተለውጠን የከበረውን አካል ለብሰን እንነጠቃለን (1 ተሰ. 5:17፤ 1 ቆሮ. 15:51-52)። ከዚያም ከጌታ ጋር ሁልጊዜ እንሆናለን። መጽሐፍ ቅዱስ “እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ” (1 ተሰ. 4:18) እንደሚለን የምንጽናናው በዚህ ታላቅ ተስፋ ነው። የመንፈስ ቅዱስና የቤተ ክርስቲያንም ናፍቆት የጌታችን ሁለተኛ መምጣት ነው። በራእይ 22:17 “መንፈሱና ሙሽራይቱም፦ ና ይላሉ። የሚሰማም፦ ና ይበል” እንደሚሚል እኛም አሜን ጌታችን ሆይ ቶሎ ና እንላለን። ማራናታ!

03/22/2025

አስደናቂ ጸጋ!

ጁን 17 ቀን 2015 በሳውዝ ካሮላይና ቻርልስተን ከተማ ዳይለን ሩፍ የተባለ የ21 አመት ወጣት በኢማኑዔል አፍሪካን ሜትድስት ዔፕስቆጶስ ቤተ ክርስትቲያን በመግባት በጸሎት ላይ ከነበሩት አማኞች መካከል ዋናውን መጋቢ ጨምሮ ዘጠኙን በጅምላ ገደለ። ወንጀሉ በዘረኝነት ተነሳሽነት የተፈጸመ በመሆኑና አማኞች ቤተ ክርስቲያን እያሉ የተፈጸመ በመሆኑ ዜናው መላው አገሪቱን አናወጠ። የአሜሪካንን ሕዝብ በጣም ያስደመመው ግን የሟች ቤተ ሰቦች ላይ የታየው አስደናቂ ጸጋ ነበር። አንጀታቸው በሐዘን የተኮማተረ ቢሆንም ግድያውን የፈጸመውን ሰው ግን ይቅር ብለንሃል አሉት። ከዚህም የተነሳ ይመስላል በፓስተሩ የቀብር ሥነ-ስረዓት ላይ ተገኝተው የሃዘን ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ኦባማ የንግግራቸውን ዋና ሃሳብ ያደረጉት አስደናቂ ጸጋ በሚል ሃሳብ ላይ ነበር። ፕሬዝዳንቱ በቅዱሳኑ ላይ የተገለጠው ጸጋ እጅግ ስላስገረማቸው ታዋቂውን “አስደናቂ ጸጋ” የተሰኘውን መዝሙር ከጉባዔውና ከተሰብሳቢው ጋር ዘምረዋል።
ጆን ኒውተን የተቀኘው ይህ አስደናቂ ጸጋ የተሰኘው ዝማሬ በርግጥም በኢየሱስ ክርስቶስ ወደኛ የመጣውን ወደር የሌለውን ጸጋ ይገልጻል። የመዝሙሩ አንጓ እንዲህ ይላል፦ “አስደናቂ ጸጋ ድምጹ እንዴት ጣፋጭ ነው፤ እንደኔ ያለውን ብኩን ያዳነው፤ ጠፍቼ ነበር አሁን ተግንቻለሁ፤ እውር ነበርኩ አሁን ግን አያለሁ።” ጆን ኒውተን ይህንን ዝማሬ የተቀኘው በ1779 ነው። ነገር ግን ዝማሬው ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ በብዙ አማኞች ይዘመራል። መዝሙሩ የጸጋውን ጥልቀትና ሃይል ይገልጻል። መዝሙሩ ጸጋው እንዴት ከጨለማ ወደ አስደናቂው የጌታ ብረሃን እንደመጣን ይናገራል። መዝሙሩ ጸጋው እንዴት እለት እለት እንደሚረዳን ያበስራል። እውነትም አስደናቂ ጸጋ!
ወገኖቼ፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደኛ የመጣው ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ ነው። ከዚህ ሙላት ደግም ሁላችንም ተቀብለናል። ወደኛ የመጣው የተትረፈረፈ ጸጋ ነው። ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ “በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናል” የሚለን። በማንኛውም የህይወት ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም፣ በከፍታና በዝቅታም — ሁልጊዜም ወደ ጌታ ዘወር ስንል ጸጋ አለ። በአንዱ ጸጋ ላይ ደግሞ ሌላ ጸጋ ይጨመራል። ሕጉ ፈጽሙ ይላል፤ ጸጋው ግን ተፈጽሟል ይላል። ሕጉ ወደ ላይ ውጡ ይላል፤ ጸጋው ግን ወደ ላይ ይስባል። ሕጉ ድካማችንን ያሳያል፤ ጸጋው ግን ድካማችንን ያግዛል። ሕጉ ይኮንናል፤ ጸጋው ግን ያጸድቃል። ወገኖቼ፦ የተሰጠን ጸጋ የሚያድን ጸጋ ነው። ደግምም በጽድቅ ለመኖር አቅምን የሚሰጥ ነው። እንግዲህ እንዲህ ያለ አስደነቂ ጸጋ ካለን ከኛ የሚጠበቀው እለት እለት ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት መቅረብና ጸጋውን መካፈል ነው። አሜን!

03/15/2025

መገለጡን እየናፈቁ በጸጋ መኖር

የእግዚአብሔር ቃል በቲቶ 2፡ 11-13 ላይ እንደሚያስተምረው የጌታን መገለጥ እየተጠባበቅን ስንኖር ራስን በመግዛት፣ በጽድቅና በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት እንኖራለን:: ቃሉ እንዲህ ይላል፦

ድነት የሚገኝበት የእግዚአብሔር ጸጋ ለሰዎች ሁሉ ተገልጧልና፤ ይህም ጸጋ በኀጢአት መኖርንና ዓለማዊ ምኞትን ክደን፣ በአሁኑ ዘመን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ፣ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት እንድንኖር ያስተምረናል፤ ይህም የተባረከ ተስፋችን የሆነውን የታላቁን የአምላካችንንና የአዳኛችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ በመጠባበቅ ነው... (ቲቶ 2:11-13) (አመት)

የእግዚአብሔር ጸጋ በመጀመሪያ የድነት ጸጋ ነው። ጸጋው ሰዎችን ሁሉ ለማዳን ተገልጧል። በክርስቶስ ኢየሱስ የተገለጠው የእግዚአብሔር ጸጋ ሰዎችን ሁሉ ያድናል። በጸጋው ማእቀፍ ሊገባ የማይችል ማንም የለም። ጸጋው ሲያድን ወንድ ሴት፣ ጥቁር ነጭ፣ ሃብታም ደሃ፣ የተማረ ያልተማረ … ወዘተ ሳይል ሰዎችን ሁሉ የሚያድን ነው። ቃሉ “ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም” እንደሚል (ኤፌ. 2:8-9) የእግዚአብሔር ጸጋ በእምነት የሚያድን ነው። ኢየሱስ ለኃጢያታችን እንደ ሞት፣ እንደ ተቀበረም በሶስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ እንደተነሳ ካመንን እንድናለን።

እንዲሁም የእግዚአብሔር ጸጋ ክርስቶስን እየመሰልን በቅድስና እንድኖር የሚያስችል ነው። ጸጋው በኀጢአት መኖርንና ዓለማዊ ምኞትን ያስክዳል። ጌታን ከተቀበልን በኋላ የጸጋው ኃይል በኛ ስለሚሰራ በኃጢያት እየተደሰትን ለመኖር አንችልም። በእርግጥ ኃጢያትን ልናደርግ እንችላለን። ለዚያም ደግሞ ከኃጢያት ሁሉ የሚያነጻው የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ዋስትና አለን። ደግሞም ጸጋው በፊት እንኖርበት የነበረውን ዓለማዊ ምኞትን ከውስጣችን የማውጣት ኃይል አለው። በዚህ ፋንታ ግን በዚህ በጣም ክፋት እና የኃጢያት ልምምድ በሞላበት ዓለም ውስጥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ፣ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት እንድንኖር ጸጋው ያስተምረናል። ራስን መግዛት በጣም ትልቅ ነገር ነው። እራሱን መግዛት የሚችል ሰው በሌላ ነገር አይገዛም። እራሳችንን መግዛት የምንችለው የእግዚአብሔር ጸጋ በሕይወታችን ሲሰራ ነው። በመቀጠልም ጸጋው በእውነተኛ መንፈስዊ ሕይወት እንድኖር ያስተምረናል። እውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ክርስቶስን እየመሰሉ መመላለስ ነው፤ እለት እለት ወደዚያ መልክ ማደግ ነው።

ጸጋው በሕይወታችን በልቀት የሚሰራው “የተባረከ ተስፋችን የሆነውን የታላቁን የአምላካችንንና የአዳኛችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ በመጠባበቅ” ውስጥ ነው። የጌታችንን መገለጥ በመጠባበቅ ሕይወት ስንኖር የእግዚአብሔር ጸጋ በሕይወታን በታላቅ ኃይል ይሰራል። ይህንኑ በማጽናት ቃሉ “ስለዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በጕጕት በመጠባበቅ ላይ ሳላችሁ፣ ማንኛውም መንፈሳዊ ስጦታ አይጐድልባችሁም” (1ቆሮ. 1:7) ይለናል። የጌታን መገለጥ እየተጠባበቅን ስንኖር የእግዚብሔር ጸጋ በሕይወታችን ይትረፈረፋል። ይህ ጸጋ ደግሞ በዚህ በወደቀ አለም ውስጥ በቅድስና እንድንኖር ያስችለናል። ወገኖቼ፦ የጌታችንን መገለጥ በጉጉት እየተጠባበቅን መኖር ይብዛልን። ማራናታ! ጌታ ኢየሱስ ሆይ ቶሎ ና! አሜን!

03/08/2025

የመጠባበቅ ሕይወት

በቤታችን በምናደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወቅት ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም መምጣት እየተነጋገርን ነበር። በዚህ መኃል መካከለኛዋ ልጃችን ያኤል አንድ ሃሳብ አነሳች። “ዳድ ጌታ ሲመጣ ምን እየሰራን ይመጣ ይሆን?” አለች። በጣም ጥሩ ሕይወት ፈታሽ ጥያቄ ነው። በእርግጥ ጌታ ሲመጣ ምን ኢየሰራን ይመጣ ይሆን? ጥያቄው በዚያች ቅጽበት ከምናደርገው ነገር ያለፈ ነው። ጌታ ሲመጣ ሕይወታችን በምን ተይዞ፣ ምን ላይ ትኩረት እያደረግን ይመጣ ይሆን? ጌታ ሲመጣ የዚያን ጊዜ በነቃ ሕይወት ሆነን ይመጣ ይሆን? በአግልግሎት እየተጋን ያገኘን ይሆን? ጌታ ሲመጣ በዚያን ጊዜ ከቅዱሳን ጋር በምልካም ግንኙነት ሆነን ያገኘን ይሆን? እነኚህ ጥያቆዎች ከጌታ መምጣት አኳያ ወይንም ወደ ጌታ ከመሂዳችን አኳያ ሕይወታችንን እንድፈትሽ ያደርጉናል።

በቤተ ክርስቲያናችን በዚህ አመት መሪ ጥቅሳችን የሆነው ሃሳብ በመንፈስ የጋለ ሕይወት መኖር ነው። ክፍሉ በሮሜ 12:11 ላይ የሚገኝ ሲሆን እንዲህ ይላል “ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ለጌታ ተገዙ።” ይኸው ቃል በአዲሱ መደበኛ ትርጉም ላይ “ጌታን ለማገልገል በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ እንጂ ከዚህ ትጋት ወደ ኋላ አትበሉ” ይላል። ክፍሉ ሁልጊዜ በመንፈስ ቅዱስ የተነቃቃ ሕይወት እንዲኖረን የሚያሳስብ ነው። ይህ ደግሞ ለአገልግሎት የተዘጋጀን ያደርገናል። ይህ አይነቱ የመንፈስ ግለት ሁልጊዜ ልንኖርበት የሚገባ እንደሆነም ክፍሉ ያስተምረናል። በመንፈስ የጋለ ሕይወት አንዱ መገለጫው የጌታን መምጣት በትጋት የሚጠባበቅ ሕይወት ነው። ማለትም መንፈሳዊ ግለት ሲኖረን የጌታን መምጣት እየተጠባበቅን እንኖራለን። በአንጻሩም ደግሞ የጌታን መምጣት እየተጠባበቅን ስንኖር በመንፈሳዊ ግለት እንኖራለን።

መጠባበቅ ኃይልን እንደሚያድስ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። በተለይም በኢሳያስ 40፡ 31 ላይ እንደተጻፈው “እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፥ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፥ አይደክሙም።” በዚህ ቃል ውስጥ ሁለት ነገሮች እናያለን። አንደኛ እግዚአብሔርን መተማመን ነው። ሁለተኛው ደግሞ መጠባበቅ። የእምነታችን መሰረቱና ማረፊያው እግዚአብሔር ራሱ ነው። በማንኛው ሁኔታ ውስጥ እርሱን ከታመንን የመጠባበቅ ሕይወት ውስጥ እንገባለን። መጠባበቅ ከመጠበቅ የተለየ ነው። መጠበቅ የሚያደክምና የሚያሰለች ነው። መጠባበቅ ግን ጉጉትና ናፍቆት አለው። የምንጠባበቀው ደግሞ እግዚብሔርን በመተማመን ሲሆን መጠባበቁ ከእምነት የሆነ እርግጠኝነት አለው። ለምሳሌ ፍቅረኛውን አንድ ቦታ ቀጥሮ የሚጠባበቅ ሰው ጉጉትና ናፍቆት አለው። በእርግጥ እንዲህ አይነቱ ልምምድ ወረፋን ከመጠበቅ የተለየ ነው።

ለኛ ለክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ቃል የሚሰጠን ትልቁ ተስፋ የጌታችን ተመልሶ መምጣት ነው። የመንፈስ ቅዱስና የቤተ ክርስቲያንም ናፍቆት የጌታችን መምጣት ነው። ራእይ 22:17 “መንፈሱና ሙሽራይቱም፦ ና ይላሉ። የሚሰማም፦ ና ይበል።” ጌታም ደግሞ ራሱ ተመልሼ መጥቼ ወስዳችኋለሁ ብሎናል። በዮሐንስ 14:3 ላይ ደግሞ “ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ” ብሎናል። መላእክትም “ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል” (ሐዋ. 1:11) በማለት የዳግም መምጣቱን ተስፋ ሰጥተውናል። ጌታችን በክብር ተምልሶ ይመጣል። ዳግም መምጣቱን እየተጠባበቅን እንድንኖር ጸጋ ይብዛልን። አሜን!

02/22/2025

በመንፈስ የተሞላ ሕይወትና ምስጋና

ባለፈው ሳምንት እንዳልነው በመንፈስ የተሞላ ሕይወት አንዱ መገለጫው አምልኮና ምስጋና ነው። የእግዚአብሔር ቃል በኤፌሶን 5:18 ላይ ሁልጊዜ በመንፈስ እንድንሞላ ይመክረናል። በመቀጠልም “በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ፤ ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ” (ቁ. 19-20) በማለት ለአምልኮና ለምስጋና ሕይወት ይቀሰቅሰናል። በመንፈስ መሞላትና የአምልኮና የምስጋና ሕይወት የተገናኙ ናቸው። ጠላት ሁልጊዜ እንድናጉረመርምና እንድናማርር ይፈልጋል። ያ ግን ለኛ የተሰጠን እድል ፋንታ አይደለም። እኛ የምንጸልይበት ጉዳይ ቢኖረንም እንኳን ማድረግ ያለብን በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ ነው። ስለዚህም ቃሉ “ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል” (ፊሊ. 4:6-7) ይለናል። እያመሰገንን ስንጸልይ እግዚአብሔር በሰላሙ ይሞላናል። ደግሞም በጠላቶቻችን ላይ ድልን ይሰጠናል።

በምስጋና የወጡ ድል ነስተዋል። በምስጋና ውስጥ ጠላታችን ይመታል። ጌታ ከኛ አፍ ምስጋና ሲወጣ ደስ ይለዋል። ጠላት ደግሞ ይቀጠቀጣል። በመዝሙር 8:1-2 ላይ የእግዚአብሔር ቃል ስለ ምስጋና እንዲህ ይላል፡ “አቤቱ ጌታችን፥ ስምህ በምድር ሁሉ እጅግ ተመሰገነ፥ ምስጋናህ በሰማዮች ላይ ከፍ ከፍ ብሎአልና። ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ ስለ ጠላትህ፥ ጠላትንና ቂመኛን ለማጥፋት።” እግዚአብሔር ምስጋናው በሰማይ ሞልቶ የተረፈ ነው። ጠላትን ለመምታት ግን ከኛ አፍ ምስጋናን ይሻል። ስናመሰግን እግዚአብሔርን እናከብረዋለን። በወደረኞቻችንም ላይ እርሱ የበላይ እንደሆነ እናውጃለን። እነ እዮሳፍጥ ጠላቶች በከበቡዋቸው ጊዜ ምህረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ የሚሉ ጌጠኛ ልብስ የለበሱ መዘምራንን አሰለፈ። ቃሉ እንደሚለን “ዝማሬውንና ምስጋናውንም በጀመሩ ጊዜ ይሁዳን ሊወጉ በመጡት በአሞንና በሞዓብ ልጆች በሴይርም ተራራ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር ድብቅ ጦርን አመጣባቸው፤ እነርሱም ተመቱ” (2 ዜና 20:22)። አስደናቂው ነገር የእግዚብሔር ሕዝብ ጠላቶች መመታት የጀመሩት ህዝቡ ዝማሬና ምስጋን በጀምሩ ጊዜ ነው።

ምስጋና በእግዚሔር ላይ መታመን ነው። ከከበበን ሁኔታ በላይ እግዚዝብሔር ይበልጣል ማለት ነው፤ እግዚአብሔር ያድነኛል ማለት ነው። ስለዚህ ዘማሪው ምን አለ? “ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፥ ከጠላቶቼም እድናለሁ” (መዝ. 18:3)። እግዚአብሔር ምስጋና ይበዛልንና ይትረፈረፍልን ዘንድ ይሻል። ደግሞ የምናመሰግንበት ብዙ ምክንያት አለን። ስለዚህም ቃሉ “እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ፤ ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥ ምስጋናም ይብዛላችሁ” (ቆላ. 2:6-7) በማለት “ሞልቶ የሚተርፍ ምስጋና” (አመት) እንድናቀርብ ይጠራናል። ስለዚህ በመንፈስ የተትረፈረፈ ምስጋና እያቀረብን እንመላለስ ዘንድ እለት እለት በመንፈሱ እንሞላ። አሜን!

02/16/2025

በመንፈስ የተሞላ ሕይወትና አምልኮ

በመንፈስ የተሞላ ሕይወት አንዱ መገለጫው አምልኮና ምስጋና ነው። የእግዚአብሔር ቃል በኤፌሶን 5:18 ላይ በመንፈስ ሁልጊዜ እንድንሞላ ይመክረናል። በመቀጠልም “በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ፤ ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ” (ቁ. 19-20) በማለት ለአምልኮና ለምስጋና ሕይወት ይቀሰቅሰናል። በመንፈስ መሞላትና የአምልኮና የምስጋን ሕይወት የተገናኙ ናቸው። ቃሉ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል” (ዮሐ. 4:24) እንደሚል እግዚአብሔር የሚመለከው በእውነትና በመንፈስ ነው። መንፈስ ቅዱስ ወደ እውነት ሁሉ ይመራናል ደግሞም እግዚብሔርን እንድናመለከው ያስችለናል። መንፈስ ቅዱስ ሁልጊዜ አብና ወልድን ስለሚያከበር (ዮሐ. 16:14) በመንፈስ ቅዱስ ስንሞላ በአምልኮና በመስጋና ውስጥ እንሆናለን።

እንዲሁም በመንፈስ ስንሞላ እርስ በእርሳችን በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊ ቅኔም እንነጋገራለን። አምልኮና ምስጋና የምናቀርብበት መንገድና አይነቱ ብዙ ነው። አምልኮና ውዳሴ ለእግዚአብሔር የሚቀብበት አንዱ መንገድ ሕብረት ነው። ምክንያቱም ቃሉ ለእግዚአብሔር መዝሙር፣ ውዳሴ እና መንፈሳዊ ቅኔ እያቀረብን እርስ በእርስ እንድንነጋገር ያሳስበናል። እርስ በእርስ መነጋገር የሚለው ሃሳብ ሕበረትን የሚያመክት ነው። ስለዚህ በመንፈስ የሆነው አምልኮአችንና ውዳሴአችን አንዱ የሚገለጥበት መንገድ ሕብረታችን ነው። ስለዚህም በስሙ ስንሰበሰብ አንዱ በመካከላችን የሚለቀቀው ጸጋ ዝማሬና አምልኮ ነው። (1 ቆሮ. 14:26) እንዲሁም ደግሞ በመንፈስ ስንሞላ ከልባችን አምልኮ ይፈልቃል። ቃሉ በዚሁ ስፍራ “ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ” (ኤፌ. 5:19) ይለናል። ይህም ማለት በመንፈስ ስንሞላ በግላችን ከልባችን የሚወጣ አምልኮና ዝማሬ አለ ማለት ነው። ስለዚህ በመንፈስ በተሞላ ሕይወት ውስጥ የሕበረት አምልኮ አለ። እንዲሁም ደግሞ ከልብ የሚወጣ የግል አምልኮ አለ።

በመቀጠል ደግሞ ቃሉ “ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ” (ቁ.20) ይለናል። ይህ ደግሞ ምስጋና ነው። ስለተደረገልን ማመስገን መልካም ነው፤ ተገቢም ነው። በዚህ ክፍል ደግሞ ቃሉ ያልተቋረጠ ምስጋና እንድናቀርብ ይመክረናል። “ሁልጊዜ ስለ ሁሉ... አመስግኑ።” ይህ ማለት ሁሉ ነገር በአይናችን ፊት መልካም ይሆናል ማለት አይደለም። ነገር ግን እግዚአብሔር ከነገሮቻችን በላይ ስለሆነ ከሁኔታው በላይ ሆኖ እግዚአብሔርን ማመስገን ማለት ነው። በእግዚአብሔር ታምነን ስናመሰግነው እግዚአብሔር ማዳኑን ያሳየናል። ቃሉም በመዝ. 50:23 ላይ እንደሚለን “ምስጋና የሚሠዋ ያከብረኛል፤ የእግዚአብሔርን ማዳን ለእርሱ የማሳይበት መንገድ ከዚያ አለ።” ምስጋና የድል መንገድ ነው። ምስጋና የጌታን ማዳን የምናይበት መንገድ ነው። ስለዚህ በክፍሉ እንዳየነው በመንፈስ በተሞላ ህይወት ውስጥ የሕብረት አምልኮ አለ፣ የግል የልብ አምልኮ አለ፣ ደግሞም ምስጋና አለ።

02/08/2025

በመንፈስ መሞላትና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማስተዋል

በኤፊሶን 5:18 ላይ ቃሉ “መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና” የሚል ትእዛዝ ይሰጠናል። በመንፈስ የተሞላ ሕይወት ዘመኑን ይዋጃል — “ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ” (ቁ. 16)። እንደዚሁም በመንፈስ የተሞላ ሰው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያስተውላል። ቃሉ ከዚህ አንጻር “ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ” (ቁ.17) ይላል። የእግዚአብሔር ፈቃድ ሳናስተውል መመላለስ ሞኝነት ነው። እግዚአብሔር ፍቃዱን በቃሉ ገልጾልናል። ለምሳሌ ቃሉ እንደ እግዚአብሔር ልጆች እንዴት መመላለስ እንዳለብን ይናገረናል። እንዲሁም ቃሉ ከቅዱሳን ጋር መሰበሰባችሁን ቸል አትበሉ ይለናል። ቃሉ ትጉና ጸልዩ ይለናል። ቃሉ በአገልግሎት እንድንተጋ ይመክረናል። ይህንን በቃሉ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ፍቃድ አለማድረግ ሞኝነት ነው። እግዚአብሔር ደግሞ ለእያንዳንዳችን ለሕይወታችን የሚሆን ፈቃድ አለው። ለዘመን የሚሆን ፈቃድ አለው። ለሕዝብ የሚሆን ፈቃድ አለው። ዘመናችንን ለመዋጀት ይህንን ማስተዋል ይገባል። ለምሳሌ ዳዊት ሲመላለስ ለማድረግ የሚያስበውን ነገር እግዚአብሔርን ይጠይቃል። “ልውጣን?” ብሎ ይጠይቃል። እግዚአብሔር ውጣ ሲለው ይወጣል። “ልውጣን” ብሎ መጠየቁ የእግዚአብሔርን ፍቃድ ማወቁ ነው። መውጣቱ ደግሞ ጊዜውን መዋጀቱ ነው።

የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንድናስተውል በቃሉ አእምሮአችን መለወጥ አለበት። በሮሜ 12:2 ላይ የእግዚአብሔር ቃል “መልካሙንና ደስ የሚያሰኘውን ፍጹም የሆነውንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅ እንድትችሉ አእምሮአችሁን በማደስ ሕይወታችሁ ይለወጥ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉት” (አመት) ይለናል። የእግዚአብሔር ፈቃድ መልካም ነው። የመልካምነት ምንጭ እግዚአብሔር እራሱ ነው። ከእርሱ ውጪ መልካምነት የለም። እግዚአብሔር የሰራው መልካም ነው። የእርሱ ፈቃድ የሆነው መልካም ነው። እንዲሁም የእግዚአብሔር ፈቃድ ደስ የሚያሰኝ ነው -- የእግዚአብሔር ፈቃድ የመንፈስ ቅዱስ ደስታ አለበት። መክብብ 2:25 “ያለ እርሱ ፈቃድ የበላ ደስ ብሎትም ተድላን የቀመሰ ማን ነው?” እንደሚል የእግዚአብሔር ደስታ ያለው በፈቃዱ ውስጥ ነው። ሰው ምንም ቢኖረው ከፈቃዱ ውጪ እርካታ የለውም። ደግሞም የእግዚአብሔር ፈቃድ ደግሞ ፍጹም ነው። ስህተት የለበትም። የምናሻሽለው አይደለም። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ በአእምሮአችን መታደስ አለብን። ያልታደሰ አእምሮ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሊያውቅ አይችልም።

በመንፈስ ቅዱስ ስንሞላ የእግዚአብሔርን ፍቃድ እንሳስተውላለን። በእግዚአብሔር ውስጥ ያለውን ኃሳብ የሚረዳው መንፈስ ቅዱስ ነው። ያን የመንፈስ ቅዱስን ሃሳብ የሚረዳው ደግሞ የታደሰ አእምሮ ነው። 1 ቆሮ. 2:10-12 ቃሉ እንዲህ ይለናል፡

ለእኛ ግን እግዚአብሔር በመንፈሱ አማካይነት ምሥጢሩን ገልጦልናል፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ጥልቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን ምሥጢር እንኳ ሳይቀር ሁሉን ነገር ይመረምራል። ስለ ሰው የሆነ እንደ ሆነ ከገዛ ራሱ መንፈስ በቀር በእርሱ ያለውን ሐሳብ የሚያውቅ ማን ነው? እንዲሁም ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር የእግዚአብሔርን አሳብ የሚያውቅ ማንም የለም። ከእግዚአብሔር የተሰጠንን ነገር እንድናውቅ የእግዚአብሔርን መንፈስ እንጂ የዚህን ዓለም መንፈስ አልተቀበልንም።

ስለዚህ በመፈስ የተሞላ ሕይወት ስንመላለስ አእምሮአችን በቃሉ ይታደሳል። ያን ጊዜ ደግም የእግዚአብሔርን ፈቃድን በመስተዋልና እንደ ፍቃዱ በመኖር ዘመኑን እንዋጃለን። አሜን!

02/01/2025

ጌታ እስኪመጣ ድረስ
የጌታ እራት ብዙ መንፈሳዊ በረከቶች አሉት። አንዱ ትልቁ በረከት የጌታ እራት የጌታችንን ዳግም መምጣት ያሳስበናል። ቅዱስ ቃሉ በ1ቆሮ. 11:26 ላይ እንደሚያስተምረን እንጀራውን በበላን ጊዜና ጽዋውን በጠጣን ጊዜ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን እንናገራለን። “ጌታ እስኪ መጣ” ድረስ የሚለው ሃረግ የጌታ እራት የጌታችንን ዳግም ምጽአት እየናፈቀን የምንፈጽመው መሆኑን ያስተምረናል። ጌታችንም ከሐዋሪያቱ ጋር ፋሲካን በተካፈለ ጊዜ ከዳግም መምጣቱ በኋላ የምንጠብቀውን እራት አስታውሶናል። በሉቃስ 14:22-25 ባላው ክፍል ጌታችን እንዲህ ብሏል፡
ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ሰጣቸውና፦ እንካችሁ፤ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፥ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ። እርሱም፦ ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው። እውነት እላችኋለሁ፥ በእግዚአብሔር መንግሥት ከወይኑ ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ደግሞ አልጠጣውም አላቸው።
በዚህ ክፍል የምናስተውለው የጌታ እራት ጌታችን በስጋው መቆረስ የኛን የኃጢያት ዋጋ መክፈሉን፣ እንዲሁም በደሙ አዲስ ኪዳንን ለኛ መክፈቱን ብቻ አይደለም። በዚህ ክፍል ውስጥ ታላቅ የዳግም መምጣቱ ተስፋ አለ። ጌታችን ስለሞቱ እየተናገረ በሞቱና በትንሳኤው በገባንበት የእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ ከጌታ ጋር የምንካፈለው እራት እንዳለ በማስታወስ “እውነት እላችኋለሁ፥ በእግዚአብሔር መንግሥት ከወይኑ ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ደግሞ አልጠጣውም” (ቁ. 25) ብላል። በሉቃስ ላይ ደግሞ ጌታ “በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ፥ ወደ ፊት ከዚህ [ፋሲካን] አልበላም” ብሏል (ሉቃስ 22:16)። እንዲሁም “የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከአሁን ጀምሮ ከወይኑ ፍሬ አልጠጣም” ብሏል (ቁ. 18)። ከእነዚህ ክፍሎች የምናስተውለው ለቅዱሳን የተዘጋጀ ከጌታ ጋር የምንካፈለው እራት አለ። ያ ቀን በዳግም ምጻቱ በመንግስቱ በሙላት መምጣት የሚሆን ነው። ይህንኑ ሃሳብ ቃሉ “ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው” (ራእይ 19:9) በማለት ያጸናዋል። እንግዲህ የጌታን እራት በምድር ስንወስድ የጌታችንን ዳግም መምጣትና ከጌታ ጋር የምንካፈለውን ታላቁን እራት እናስባለን።
የጌታ እራት ሌላው የሚያሳስበን እንዴት የጌታን መምጣት መጠባበቅ እንዳለብን ነው። ቃሉ እንዲሚለን እንጀራውን በበላን ጊዜና ጽዋውን በጠጣን ጊዜ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን እንናገራለን። የጌታችንን መምጣት የምንጠባበቀው ሞቱን እየተናገርን መሆን አለበት። ይህ በአንድ መልኩ ምስጋና እና አምልኮ ነው። ለኛ ደህንነት የተቆረሰውን የጌታን ስጋ፣ እንዲሁም በደሙ የተመረቀልንን ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበትን አዲስ መንገድ እያሰብን እናመሰግናለን። እንዲሁም “የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል” (ራእይ 5:12) እያልን እናመልካለን። በሌላ መልኩ ደግሞ ይህንን አለሙን ሁሉ በልጁ ደም ለመታረቅ የወደደውን አምላክ ለሌሎች በመናገር ወንጌሉን እናውጃለን። የጌታን እራት ስንወስድ የጌታን ሞት፣ በሞቱም የመጣውን ሕይወት፣ በዚህም ውስጥ ያለውን የፍቅር ብርታት እያሰብን እንደገና በመንፈስ ግለት ገብተን ወንጌሉን ለሌሎች የምናደርስበትን ኃይልና ብርታት እንቀበላለን። ሞቱን ስንናገር ፍቅሩን እንናገራለን። ፍቅሩን ስንናገር ማዳኑን እንናገራለን። እንደዚህ እየኖርን “ማራናታ” እንላለን። ወገኖቼ፡ ኢየሱስ ይመጣል። ማራናታ! ጌታ ኢየሱስ ሆይ ቶሎ ና!

01/26/2025

በመንፈስ መሞላትና ዘመኑን መዋጀት

በኤፊሶን 5:18 ላይ መጽሐፍ ቅዱስ “መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና” የሚል ትእዛዝ ይሰጠናል። በዚሁ ክፍል ላይ ቃሉ በማከል “ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ” (ቁ. 16) ይለናል። ሁልጊዜ በመንፈስ የምንሞላ ከሆነ ዘመናችንን እንዋጃለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ጊዜ” ወይንም “ዘመን” ለመሚለው ቃል ሁለት የግሪክ ቃላትን ይጠቀማል። አንደኛው “ካይሮስ” ሲሆን ሁለተኛው “ኩሮኖስ” ነው። “ኩሮኖስ” የሚገልጸው መጠናዊ ጊዜን (quantitative time) ሲሆን በደቂቃ፣ በሰአት፣ በቀን፣ በወር፣ በአመት የምንለካውን ጊዜ ያመለክታል። “ካይሮስ” ግን የሚያመለክተው ልቀታዊ ጊዜን (qualitative time) ነው። ስለዚህ “ካይሮስ” በጊዜው ውስጥ ያለውን ተጨባጭ እድል የሚያመለክት ነው። በኤፌሶን 5:16 ላይ ባለው ዘመኑን ወይንም ጊዜውን ዋጁ በሚለው ክፍል ውስጥ “ጊዜ” ወይንም “ዘመን” ተብሎ የተተረጉመው ቃል በግክሪኩ “ካይሮስ” የተባለው ቃል ነው።

ከላይ እንዳልነው በመንፈስ የተሞላ ሕይወት አንዱ መገለጫው ዘመኑን መዋጀት ነው። ዘመኑን መዋጀት ማለት በዘመኑ ውስጥ ያለውን (የሚወጣውን) መልካም እድል ለእግዚአብሔር ክብር ለሰዎችም ጥቅም መጠቀም መቻል ማለት ነው። ስለዚህም ነው በአገራችን ብሒል “ጊዜ ወርቅ ነው” የሚባለው። በእርግጥም ጊዜ እግዚአብሔር በሕይወታችን የሰጠን ዋና ሃብት (resource) ነው። በጊዜአችን ላይ ውሳኔዎችን እንወስናለን። ሕይወታችን ደግሞ የውሳኔዎቻችን ድምር ወጤት ነው። እያንዳንዱ ውሳኔ ደግሞ የእድል ዋጋ (opportunity cost) አለው። በዚህ ክፍል መጽሐፍ ቅዱስ ዘመኑን ዋጁ (redeem the time) በማለት የሚመክረን በዘመኑ ውስጥ ያለውን እድል እንዲሁ እዳናሳልፈው ነው። ይህንን ቃል NIV መጽሐፍ ቅዱስ “making the most of every opportunity” በማለት ይገልጸዋል። በእያንዳንዱ እግዚአብሔር በሚሰጠን ቀን/አመት ውስጥ እድል አለ። ስለዚህ ይህንን እድል (ቀን/አመት) ለእግዚአብሔር ክብር ለኛ ደግሞ ጥቅም መዋጀት (መጠቀም) አለበን። እኛ በቀኖቹ ውስጥ የሚመጡትን እድሎች ዋጅተን (የራሳችን አድርገን) ካልተጠቀምንባቸው በቀኖቹ ላይ ክፋት ይሰለጥናል።

መጽሐፍ ቅዱስ ቀኖቹን ሳንዋጅ የምንመላለሰውን ሕይወት እንደ ሞኝ መመላለስ ይለዋል። ቀኖቹን እየዋጀን የምንመላለሰውን ኑሮ ደግም እንደ ጥበበኛ መመላለስ ይለዋል። እኛ እንደ ሞኝ ሳይሆን እንደ ጥበበኛ እንድንመላለስ ቃሉ ይመክረናል። በጥበብ መመላለስ በፍቃዱ እውቀት ውስጥ መመላስ ማለት ነው። ስለዚህ ነው ዘመኑን ለመዋጀት በመንፈስ መሞላት ያለብን። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን የስምኦን ይህወት ነው። ስምኦን “የእስራኤልን መጽናናት ይጠባበቅ ነበር፤ ጻድቅና ትጉህም ነበረ፥ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበረ” (ሉቃስ 2:25)። ይህ ሰው “በጌታም የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንዳያይ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበር” (ቁ.26)። ጌታ በስረአቱ ለእግዚአብሔር እንዲሰጥ ወላጆቹ ወደ መቅደስ ባመጡት ጊዜ ቢዚያኑ ሰአት ስምኦን በመንፈስ ወደ መቅደስ ወጣ (ቁ. 27)። የእስራኤልንም መጽናናት ታቀፈ። ጌታንም አመሰገነ። ስምኦን ሁልጊዜ በመንፈስ የተሞላ ሰው ነበር። ስለዚህም ጊዜውን የዋጀ ሰው ነበር። በጊዜው ውስጥ የመጣውን እድል አላሳለፈውም። እኛም እንደዚሁ እግዚአብሔር በሰጠን ዘመን ውስጥ ያለውን እድል በመንፈስ ቅዱስ እየተመራን መጠቀም አለበን። ዘመን ይዞ የሚመጣቸው እድሎች አሉ። ከወገኖች ጋር ሕብረት የማድረግ እድል አለ፣ የማገልገል እድል አለ፣ ወንጌል የመስበክ እድል አለ፣ የመስራት እድል አለ፣ የመማር እድል አለ፣ መልካም የማድረግ እድል አለ… ወዘተ። ዘመኑን መዋጀት ማለት እነኚህን እድሎች መጠቀም ማለት ነው። በመንፈስ ቅዱስ እለት እለት እየተሞላን፣ ዘመናችንን እየዋጀን በጥበብ እንድመላለስ እግዚአብሔር ይርዳን። አሜን!

01/19/2025

ጸሎትና በመንፈስ የተሞላ ሕይወት

በመንፈስ ቅዱስ መሞላትና ጸሎት በብርቱ የተቆራኙ ናቸው። ከቃሉ እንደምንማረው እግዚአብሔር ለሚሹት መንፈሱን አብልጦ ይሰጣል። ከዚህ አንጻር ሉቃስ 11:13 እንዲህ ይላል፡ “እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፥ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?” ክፍሉ የሚናገረው ስለ እግዚአብሔር አባትነት ነው። ከላይ ጌታችን ሐዋሪያቱን ስለጸሎት ሲያስተምራቸው “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ” (ቁ. 2) ብላችሁ ጸልዩ አላቸው። ጸሎት በዋናነት የግንኙነት ጉዳይ ስለሆነ የሚጀምረው የእግዚአብሔርን አባትነት በመረዳትና በልጁ ባገኘነው ልጅነት በመቅረብ ነው። አባታችን ስንለምነው መንፈስ ቅዱስን አብልጦ ይሰጠናል። የጥያቄአችን መልስ ሁሉ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ ይሆንልናል። በዚህ ክፍል የምናስተውለው አንድ ነገር አለ። መንፈስ ቅዱስ አብልጦ የሚሰጠው “ለሚለምኑ” ነው። ይህ በጸሎትና የመንፈስ ቅዱስ ሙላትን በመቀበል መካከል ያለውን ጥብቅ ቁርኝት ያሳያል። መንፈስ ቅድስ ከኛ ጋር አለ። ነገር ግን በመንፈሱ ሁልጊዜ ለመሞላት በጸሎት መቅረብ ያስፍልገናል።

ሐዋሪያት በመንፈስ ቅዱስ ይሞሉ የነበረው እየጸለዩ ሳሉ ነው። በሐዋሪያት ስራ የምናየው ታላቅ የመንፈስ ቅዱስ መፍሰስ ከመሆኑ በፊት የጌታ ደቀ መዛሙርት በአንድ ልብ ሆነው አብረው ይጸልዩ ነበር። (ሐዋ. 1:14፡ “እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር።”) በቃሉ ላይ በቀጥታ ባይጻፍም በምን ጉዳይ እየጸለዩ እንደነበር ለመገመት እንችላለን። ጌታ ኢየሱስ ከማረጉ በፊት የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ሳይቀበሉ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዟቸው ነበር (ሐዋ. 1:4)። እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን እንደሚቀበሉ እና በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳርቻ የእርሱ ምስክሮች እንደሚሆኑ ነግሮአቸዋል (ቁ.8)። ስለዚህ እየጸለዩ የነበረው በዚህ የተስፋ ቃል ላይ ቆመው መንፈስ ቅዱስን እየፈለጉ እንደነበር ለመገመት እንችላለን። ስለሆነም በሐዋ. 2 ላይ እንደምናነበው እየተጉ ሳለ መንፈስ ቅዱስ በመካከላቸው ፈሰሰ። ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ። ስለዚህ ጉዳይ ቃሉ እንዲህ ይላል፡

በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው። እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው። በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር። (ሐዋ. 2፡ 1-4)

ይህ የሐዋሪያቱን አገልግሎት የቀየረ ክስተት ነበር። በመንፈስ ቅዱስ ከተሞሉ በኋላ ሐዋሪያቱ በሌሎች ልሳኖች ተናገሩ፤ ቃሉን በታላቅ ኃይልና መገለጥ ሰበኩ፤ ወንጌሉን በስልጣን አወጁ፤ ምልክቶችና ድንቆችም በመካከላቸው ቃሉን እያጸኑ ተከናወኑ። በጸሎትም እየተጉ እንደገና በመንፈስ ቅዱስ ይሞሉ ነበር። ለምሳሌ ጴጥሮስና ዮሐንስ ሽባውን ሰው ከፈወሱ በኋላ የካህናት አለቆችን ማስፈራሪያ ለወገኖቻቸው በተናገሩ ጊዜ የሐዋሪያቱ ምላሽ በአንድ ልብ በጸሎት መቅረብ ነበር። ቃሉ እንደሚለን “ከጸለዩም በኋላ ተሰብስበው የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፥ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ የእግዚአብሔርንም ቃል በግልጥ ተናገሩ” (ሐዋ. 4:31)። ይህ ዘመን የበለጠ በጸሎት እየቀረብን በመንፈሱ ተሞልተን የምናገለግለበት ዘመን ይሁንልን።

Address

5850 N Elston Avenue
Chicago, IL
60646

Opening Hours

Friday 7pm - 9pm
Sunday 10am - 3pm

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Chicago Yemsrach Evangelical Church posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share