05/21/2026
ዕርገተ ክርስቶስ
“አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ” /መዝ ፵፮ ፥ ፭/።
እንኳን ለብርሃነ ዕርገቱ አደረሳችሁ !!!
መ/ር ጌታቸው በቀለ
የጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በተከበረ በዐርባኛው ቀን የሚውለው ዐቢይ በዓል “ዕርገት” ይባላል፡፡ ዕርገት ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ዐበይት በዓላት አንዱ ነው፡፡
ጌታችን ከትንሣኤው በኋላ ለቅዱሳን ሐዋርያት ለአርባ ቀናት እየተገለጸ፣ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት መጽሐፈ ኪዳንን፣ ትርጓሜ መጻሕፍትን፣ ምሥጢራትን፣ ሕግጋትንና ቀኖናተ ቤተ ክርስቲያንን ሲያስተምር ቆይቶ ወደ ቀደመ ዙፋኑ ወደ ሰማይ በክብር በምስጋና ማረጉን በደስታ የምንዘክርበት ዐቢይ በዓል ነው፡፡
ዘመነ ዕርገት
በዓለ ዕርገት በየዓመቱ በዓሉ የሚውልበት ዕለት ሐሙስን ባይለቅም ቀኑ ግን የአጽዋማትና በዓላት ማውጫ ቀመርን ተከትሎ ከፍ እና ዝቅ ይላል፡፡ በዚህ መሠረት የዘንድሮው በዓለ ዕርገት ግንቦት ፲፫ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም ይውላል ማለት ነው፡፡ ከጌታችን የዕርገት በዓል ጀምሮ (ከበዓለ ትንሣኤ ዐርባኛው ቀን) እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ ዋዜማ (ዐርባ ዘጠነኛው ቀን) ድረስ ያለው ወቅትም “ዘመነ ዕርገት” ተብሎ ይጠራል፡፡ /ኪዳነ ወልድ ክፍሌ(1948)፡፡ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፡፡ ገጽ ፯፻፷/፡፡
ዐርገ በስብሐት
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተነሣ በኋላ ዕለቱን ወደ ሰማይ አላረገም፡፡ ዐርባ ቀን ለሐዋርያት በሥጋ እየተገለጠና እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት እያስተማራቸው ቆየ፡፡ በዐርባኛው ቀን ደቀ መዛሙርቱን እስከ ቢታንያ አወጣቸው፡፡ እጆቹን አንሥቶ ባረካቸው፡፡ በአርባኛው ቀን ሐዋርያትን ሰብስቦ ዓለምን ዞረው እንዲያስተምሩ መመሪያ ሰጥቶ ለዚህም ኃይል የሚሆናቸው መንፈስ ቅዱስን እስከሚልክላቸው ድረስ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዝዞ ዐረገ፡፡ “እነርሱ በተሰበሰቡ ጊዜ ጌታ ሆይ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን?” ብለው ጠየቁት፡፡ ይኸውም “አቤቱ በዘሩባቤል የሄደችውን መንግሥት ለእስራኤል ልጆች የምትመልሰው መቼ ነው?” ሲሉት ነው፡፡ እርሱም “አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውንና ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልሰጣችሁም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ በኢየሩሳሌም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” አላቸው፡፡ “…ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዐይናቸው ሰውራ ተቀበለችው” እንዲል /ሐዋ.፩፥፩-፱/፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰማይ ትኩር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፤እነሆ ነጫጭ(ብሩህ) ልብስ የለበሱ ሁለት ቅዱሳን መላእክት በሰው አምሳል ተገልጠው በአጠገባቸው ቆሙ፡፡ “የገሊላ ሰዎች ሆይ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ክርስቶስ በብርሃን፣ በሥልጣን በቅዳሴ ሲያርግ እንዳያችሁት ዳግመኛ በብርሃን በሥልጣን በቅዳሴ ሲመጣ ታዩታላችሁ” አሏቸው፡፡
የጌታችን ዕርገት በነቢያት ትንቢት
የጌታችን ዕርገቱ በነቢያት አስቀድሞ የተነገረ ነው፡፡ እግዚአብሔር የራቀውን አቅርቦ፣ የረቀቀውን አጉልቶ ስለገለጠላቸው ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ (በይባቤ መላእክት፣ በቅዳሴ) ዐረገ” ብሏል /መዝ. ፵፮፥፭/፡፡ ዳግመኛም “ወደ ላይ ዐረግህ ምርኮን ማረክህ” ብሏል /መዝ.፷፯፥፲፰/፡፡ ሦስተኛም “በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ላረገ ለእግዚአብሔር ዘምሩ” በማለት የዕርገቱን ነገር አስቀድሞ ተናግሯል /መዝ.፷፯፥፴፫/፡፡ ከዚህም የምንረዳው “እግዚአብሔር ዐረገ” በማለት የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት መስክሯል፡፡
የጌታችን ዕርገት በኃይሉና በሥልጣኑ
አዳም በተፈጠረ በዐርባ ቀኑ አግኝቶ ኋላ በምክረ ከይሲ ያጣውን የጸጋ ልጅነትን እንደመለሰለት ለማጠየቅ፤ ለዐርባ ቀናት ለሐዋርያት እየተገለጸ መነሣቱን ሲያስተምራቸው ከቆየ በኋላ፤ በዐርባኛው ቀን ሁሉንም ወደ ቢታንያ አውጥቶ በአንብሮተ እድ ባርኮ፣ የሥልጣነ ክህነትን ጸጋ ሰጥቷቸው በክብር በምስጋና ዐርጓል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማረጉ መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት ለመላክ፣ የባሕርይ አምላክነቱን ለመግለጽ በተዋሐደው ሥጋ በክብር እንዳረገ ዳግመኛ በታላቅ ግርማ ዓለምን ለማሳለፍ ተመልሶ እንደሚመጣ ለማጠየቅ ነው፡፡
ጌታችን ያረገው ከደብረ ዘይት ተራራ ነው /ሉቃ.፳፬፥፶-፶፫/፡፡ ጌታችን በዘመነ ሥጋዌው ሲያስተምር “እንግዲህ የሰው ልጅ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ይሆናል?” በማለት እንደገለጸው፤ ዕርገቱ ክብሩ በሚገለጽበት በየማነ አብ፣ በዘባነ ኪሩብ ለመቀመጥ ነው /ዮሐ.፮፥፷፪/፡፡ ይህንንም ቅዱስ እስጢፋኖስ “እነሆ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” በማለት ገልጾታል/ሐዋ. ፯፥፶፯/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም “…በሥጋ የተገለጠ፣ በመንፈስ የጸደቀ፣ ለመላእክት የታየ፣ በአሕዛብ የተሰበከ፣ በዓለም የታመነ፣ በክብር ያረገ” ሲል ገልጾታል/፩ኛ ጢሞ.፫፥፲፮/፡፡ /አባ ጎርጎርዮስ (1974)፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ፡፡ አዲስ አበባ፤ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ታተመ፤ ገጽ 131/፡፡
የጌታችን ዕርገት ልዩ የሆነበት ምሥጢር
የጌታችን ዕርገት አስቀድመው ካረጉ ከእነ ኤልያስ፣ ከእነ ዕዝራ ሱቱኤል፣ ከእነ ሄኖክ ይለያል፡፡ እነርሱ ዐረጉ ቢባሉ በራሳቸው ሥልጣን አይደለም፡፡ ሄኖክን እግዚአብሔር እንዳሳረገው በኦሪት ዘፍጥረት ተገልጾ ይገኛል፡፡ “ሄኖክ አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ አልተገኘም፤ እግዚአብሔር ወስዶታልና” ይላል /ዘፍ.፭፥፳፬/፡፡ ዕዝራ ሱቱኤልንም መላእክት ወደ ብሔረ ሕያዋን እንዳስገቡት ተገልጿል፡፡ “ይህን ሁሉ ጽፎ ያን ጊዜ መላእክት ዕዝራን ይዘው እንደሱ ያሉ ደጋግ ሰዎች ወዳሉበት ወደ ብሔረ ሕያዋን ወሰዱት” ይላል /ዕዝራ ሱቱኤል ፲፫፥፵፱/፡፡
ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላካዊ ኃይሉና በሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ ወደ ሰማይ የወጣው በኃይሉና በሥልጣኑ ነው፡፡ የአዳም ሰባተኛ ትውልድ ሄኖክ ያረገው በራሱ ኃይል ሳይኾን እግዚአብሔር ወስዶት ነው/ዘፍ.፭፥፳፬/፡፡ ነቢዩ ኤልያስም በእሳት ሠረገላ ያረገው በራሱ ኃይል ሳይሆን እግዚአብሔር ወስዶት ነው/፪ኛ ነገ.፪ ፥፲፩/፡፡ እኛንም በትንሣኤ ዘጉባኤ ነፍሳችንን ከሥጋችን አዋሕዶ ትንሣኤ ዘለክብር አስነሥቶ ወደ ሰማይ እንደሚያሳርገን እናምናለን፡፡ ይህንንም ራሱ ባለቤቱ “እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትኾኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኀዋለሁ በማለት እውነተኛ ተስፋ ሰጥቶናል” /ዮሐ.፲፬፥፫/፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እኛ አገራችን በሰማይ ነውና” ያለው ለዚህ ነው /ፊል.፫፥፪/፡፡
ቅዱሳን አባቶች ሃይማኖታቸው የጸና ምግባራቸው የቀና የክርስቶስን አምላክነትና የማዳኑን ምስጢር ቅዱሳት መጻሕፍትን መረጃ በማድረግ በጸሎተ ሃይማኖት ድንጋጌያቸው ገልጸውልናል፡፡ የ318 አባቶች የሃይማኖት ውሳኔ በመጨረሻው አንቀጽ “ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ፤ ዳግመ ይመጽእ በስብሐት ይኮንን ሕያዋነ ወሙታን ወአልቦ ማኅለቅት ለመንግሥቱ” (በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ፡፡ ዳግመኛም በክብር ይመጣል በሕያዋንና በሙታን ይፈርድ ዘንድ፤ ለመንግሥቱ ፍጻሜ የለውም፡፡) ብለው ወስነዋል፡፡ ወልድ ሰው የኾነበትን ቅዱስ ዓላማ ፈጽሞ ወደላከው ወደ አባቱ በክብር ዐረገ፤ በክብር ዙፋኑም ተቀመጠ፤ የወረደው ሌላ የዐረገው ሌላ አይደለም ለማለት ዐርገ በስብሐት ሲሉ አባቶች ተናገሩ፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስም “ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም እርሱም በሰማይ የሚኖር የሰው ልጅ ነው” ሲል የሰው ልጅ ክርስቶስ በባሕርይ ክብሩ በመለኮታዊ ሥልጣኑ ሁሉን ለማድረግ የሚችል ሁኖ በሰማይ እንደሚኖር ገልጦ ተናገረ /ዮሐ.3፣13/፡፡
በዓለ ዕርገት በቤተክርስቲያን
ዕርገት በምእመናኑ ዘንድ እንደ ትንሣኤና ልደት ዝግጅት ባይደረግበትም በቤተክርስቲያን ግን የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥበት ማኅሌቱ፣ ቅዳሴው፣ ይባቤው የሚደረግበት ዕለት ነው፡፡ /ብርሃኑ አድማስ (2002)፡፡ በዓላት፡፡ አዲስ አበባ፤ ሜጋ ማተሚያ ቤት፤ ገጽ 88/፡፡ ዕለቱ በቤተክርስቲያን ትውፊቷ መሠረት ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ ክህነትን የሰጠበት በመሆኑ ልዩ መታሰቢያነትና ምስጢር ያለው ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጌትነቱን ሥርዐት የፈጸመበት፣ ከሊቀ ጳጳስነት ጀምሮ እስከ ዓፃዌ ኆኅትነት ያለውን መዓርግ የሰጠበት፣ ወደ ላከው ወደ ባሕርይ አባቱ ወደ አብ ያረገበት በአብ ዕሪና የተቀመጠበትን በዓለ ዕርገትን ማክበር እንዲገባ ሊቃውንቱ በፍትሐ ነገሥት አዘዋል፡፡ “ሥርዐቱንና መዓርጋቱን ሁሉ የፈጸመበትንና ወደላከው ወደ እግዚአብሔር አብ ያረገበትን በአብ ቀኝ የተቀመጠበትን የጌታችንና የመድኃኒታችንን በዓለ ዕርገት አክብሩ” /ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው፤ አንቀጽ 19፤ ቁጥር 736 እና 740/፡፡
እንደ ማጠቃለያ
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት “እኔ ብሄድ ይሻላችኋል፤ እኔ ካልሄድሁ ጰራቅሊጦስ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ከሄድሁ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ፡፡” ብሏል /ዮሐ. ፲፮፡፯/፡፡ እርሱ በአካል ስለሚለያቸው የሐዘን ሰሜት እንዳይሰማቸው የሚያጽናና መንፈስ እንደሚልክላቸው “አብ በስሜ የሚልከው መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል” ብሎ ነግሯቸዋል /ዮሐ. ፲፬፥፮/። ይህንን ተስፋ በማመን ጌታችን ሲያርግ ወደ ሰማይ ትኩር ብለዉ ይመለከቱ የነበሩት ደቀ መዛሙርት በሃምሳኛዉ ቀን መንፈስ ቅዱስ ወርዶላቸዋል። እኛም ዕርገቱን እያሰብን ዓይናችንን ወደ ሰማይ እናነሳለን።
ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችን ያዘዛቸውን ትዕዛዝ ለመፈጸም እስከ ሕይወት ፍጻሜ ድረስ በመታመን አደራቸውን እንደተገበሩ ሁሉ በሐዲስ ኪዳን ያለን ምእመናንም ጌታችን የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠብ የሰጠንን የትሕትናን አደራ፤ በመስቀል በመቸንከር ያሳየንን መከራን የመቀበል አደራ፤ በገዛ ሥልጣኑ ከሙታን በመነሣት የነገረንን ትንሣኤ ዘጉባኤን ተስፋ በማድረግ በምክረ ካህን በፈቃደ እግዚአብሔር እየኖርን ክርስቲያናዊ ምግባራትን ከሃይማኖት ጋር አስተባብረን ልንይዝ ይገባል።
በዓለ ዕርገትን ስናከብርም በጸሎት፣ በምስጋናና በቅዳሴ ሊሆን ይገባል፡፡ ዕርገት የድልና የክብር በዓል ነው። በቤተክርስቲያን ተገኝቶ በሥርዓተ ቅዳሴ በመሳተፍ፣ በምስጋና፣ ጸሎትና የቅዱስ ቊርባን በመቀበል ከጌታችን ጋር ያለንን ኅብረት ማጽናት ይገባል። ዘለዓለማዊ ሕይወትን እያሰብን በሃይማኖት ጸንተን፣ ሕጉን ትእዛዙን ጠብቀን እንድንኖር እግዚአብሔር ማስተዋሉንና ጥበቡን ያድለን፡፡ አሜን፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር ከበዓሉ በረከት ረድኤት ይክፈለን፤ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
ዋቤ መጻሕፍት
✍️ መጽሐፍ ቅዱስ
✍️ ሃይማኖተ አበው
✍️ ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜ
✍️ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ
✍️ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ
✍️ በዓላት