Ethiopian evangelical church in Lebanon/Beirut

Ethiopian evangelical church in Lebanon/Beirut Contact information, map and directions, contact form, opening hours, services, ratings, photos, videos and announcements from Ethiopian evangelical church in Lebanon/Beirut, Religious Center, Beirut.

መጠበቅ አድክሞን ይሆን?
26/11/2019

መጠበቅ አድክሞን ይሆን?

መጠበቅ ሲያቅተን፡- ከዓላማችን ፈጥነን ለመወጣት በመወሰናችንና የእርሱን አብሮነት ማስተዋል አቅቶን ልንጎዳ እንደምንችል አውቀን መጠበቅን እንማር፡፡

07/01/2019

የገናን በዓል ፕሮግራም (2019)
የእሁድ መልዕክታችን ፡- ቀን ፡ 06/01/2019
ሰባኪ ፡- መጋቢ ኤልያስ ገብሬ
የትምህርቱ ዋና ሀሳብ ‹‹ ጥሩ ዕድሎችን (አጋጣሚዎችን) እንጠቀምባቸው ››
የዕለቱ ትምህርት ክፍል ፡- (ማቴ. 2፥1-6)

ጥሩ ዕድሎችን (አጋጣሚዎችን) ሳንጠቀምባቸው እንዳናልፍ ልንጠነቀቅ ይገባናል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ጥሩ ዕድሎችና አጋጣሚ የሚመስሉ ነገሮችን የተጠቀሙባቸው እንዳሉ ሁሉ ያጋጠማቸውን ዕድል (ጥሩ አጋጣሚዎች) ሳይጠቀሙባቸው ያለፉ በርካቶች ናቸው፡፡ ክርስቶስ በተወለደበት በዚያን ዘመን ሰብአ ሰገል የተወለደበትን ሥፍራ ባያውቁም ያንን ሥፍራ ለማድረግ እረጅም ጉዞ ተጉዘው ሲመጡና ሲጠይቁ፥ የት እንደሚወለድ መረጃው የነበራቸው ካህናትና የህዝቡ ጻፎች ግን ግድ የለሾች ነበሩ፡ ጥሩ አጋጣሚዎችን (ዕድሎችን) ሳንጠቀምባቸው የምናልፍባቸው ምክንያቶች፡-

1ኛ. ነገሮችን በግድ የለሽነት መመልከታችን (ዘፍ.25፥26-30)

ያዕቆብ የእርሱ ላልሆነ ብኩርና ትኩረት ሲሰጥ ዔሳው ግን የራሱ ለሆነ በእጁ ላለ ብኩርና ግድ የለሽ ነበረ፡፡ ያዕቆብ እያንዳንዱን አጋጣሚ ለሚፈልገው ዓላማ ለማዋል ሲተጋ ዔሳው ግን በእያንዳንዱ አጋጣሚ ለያዘው ነገር ግድ ሲያጣ እንመለከታለን፡፡ የተሰጠንን ዕድሎች ሳንጠቀምባቸው ስንቀር ፊት ለፊታችን ጨለማና ለቅሶ የበዛበት ብቻ ይሆናል፡፡ ግድየለሽነት ጥሩ ዕድሎችን ያበላሽብናል፡፡ በግድየለሽነት ባበላሸናቸው ዕድሎች ማንን ተጠያቂ እናደርግ ይሆን? ጥሩ ዕድሎችንና አጋጣሚዎችን በግድ የለሽነት የምናሳልፈው፡- በአለመብሰላችን (ልጆች በመሆናችን) እና በድንዛዜ ውስጥ በመገኘታችን ነው፡፡

2ኛ. ለመልካም ምክር ጆሮአችንን አለመስጠታችን (ሩት. 3፥1-5)

ሩት ከሞአብ ወደ ቤተልሔም የመጣችበት ወቅት ጥሩ ወቅት ነበር በቤተልሔም እርሻ የሚታጨድበትና የሚሰበሰብበት ወቅት ነበር፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን እንደ ዕድል ሩት ለቃርሚያ በወጣችበት ጊዜ በቦኤዝ እርሻ ላይ ተገኝታ ነበረች፡፡ (ሩት. 2፥3) ሩት ከቃርሚያ ህይወት እንድትወጣና ይህን አጋጣሚ ተጠቅማ ወደ ተሻለ ሕይወትና ኑሮ እንድትገባ ኑኃሚን መከረቻት፡፡ ዛሬ ብዙ ጥሩ አጋጣሚዎች የሚያልፉን ለመልካም ትምህርቶችና ምክሮች ጆሮ አለመስጠታችን አይደለምን? ምክርን የሚሰሙ ሰዎች አጋጣሚውን (ዕድሎችን) ተጠቅመው፡- እራሳቸውን ለጥሩ (ለመልካም) ነገር ያዘጋጃሉ (ሩት. 3፥3) ፤ የሕይወት ለውጥን ለማምጣት እርምጃ ያደርጋሉ (ሩት. 3፥3) እና ውጤት በሕይወታቸው እስኪታይ ድረስ መጠበቅ ይችላሉ (ሩት. 3፥18)

3ኛ. ክፉ ውሳኔ (ጥቅም የሌለው ጎጂ የሆነ ውሳኔ) (ሉቃ. 23፥39-43)

ክፉ ውሳኔ ስንወስን እንድንጠቀምባቸው የተሰጡንን ዕድሎች (ጥሩ አጋጣሚዎች) መጠቀም አለመቻላችንን ያሳያል፡፡ ከክርስቶስ ጋር የተሰቀሉት ሁለቱ ወንበዴዎች ጥሩ ውሳኔ ቢወስኑበት ይህ አጋጣሚ በጣም ጥሩ እንደሆነ ጥሩ ውሳኔ ከወሰነው ወንበዴው ሰው መማር እንችላለን፡፡ እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ መልካም አጋጣሚ ቀርቦላቸው ነገር ግን ልክ እንደ አንደኛው ወንበዴ ሳይጠቀሙበት የሚቀሩ ብዙ ናቸው፡፡ ጥሩ ውሳኔ መወሰን ሲያቅተን መጥፎ ውሳኔን መወሰናችን አይቀርም፡፡

በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በኢትዮጵያ በጣም ጥሩና በጎ የሆኑ ዕድሎች መጥቶልናል፡፡ ማለትም በዲሞክሪያሲ የሚያምኑ፣ ሀገራዊ ራዕይ ያላቸው፣ የወደፊት እጣ ፈንታችንን ሊያቃኑ የሚደክሙ፤ ነገር ግን ይህንን ዕድል በጥሩ ሳንጠቀምበት ብናልፍ ማን ይሆን ተጠያቂው? እንደ ሀገርስ መቀጠል የሚያስችሉ ሁኔታዎች ይገጥሙን ይሆን? እንደ እኔ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊያን ሁላችን ይህ ዕድል እንዳይበላሽ ተባብረን ልንቆምና የአንድነትን መዝሙር ልንዘምር ይገባናል፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ውሳኔው የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነው፡፡

07/10/2017

‹‹ወይ አሜን››

አሜን ስትል ምን ገብቶህ ነው?
ወይስ አንተ ስትቀልድ ነው?
ስለ ሁሉም አሜን ብለህ
እስከ መቼስ ትዘልቃለህ?
በስሜትህ ስትገፋ
ሳታስተውል ስትለፋ
አሜን ብልህ የጠራኽው
ካስተዋልከው የእርሱ ስም ነው፡፡

ምን ዓይነት ነው ይሄ ትውልድ
በአሜን ብቻ ሁሉን ሚንድ
ሁሉን አምኖ የሚነዳ
ባዶ ሕይወት ባዶ ጓዳ
ስሜት ብቻ የለው ተስፋ
በፈተና እየጠፋ ለአሜን ብቻ እየለፋ፡፡

እኔስ ሰልችቶኛል ዝም ብሎ አሜን ማለት
ገለባ ሲመገብ ለማይረባ ሕይወት
በሠው ሠራሽ ታምር ከእውነት ሲሸፍት፡፡

እስቲ መልስልኝ ‹ክቡር የእግዚአብሔር ሰው›
በማያጠግብ ተስፋ ሕዝቡን ከሞላኽው
ሰማይ እያደረስክ እንዲህ እያነጠርከው
ከምላስ በማይወርድ አሜን እያስባልከው
ሰውን በመበዝበዝ ከአምላክ ካጋጨኽው
አንተስ መጨረሻህ ፍጻሜህ ምንድነው?

በውሸት ሕልሞችህ ትውልድ አሜን እንዲል
ሙዚቀኛው ሲጮኽ እሱም እልል ሲያስብል
በጥጃ አምልኮ ትውልድ ሲንከባለል
በቅዱስ መንፈስ ስም እራስህን ስታቀል
አያስፈራህም ወይ የአምላኬ በቀል
ፍሬ በሌለው ቃል ትንቢትህን ስትቀጥል
ሐፍረት የማይሰማህ ሕዝቡን አሜን ስትል፡፡

እኔስ አሻፈረኝ ዝምብዬ አሜን አልል
በገና ቢሰማ ሁሉንም ቢያማልል
ከበሮው ቢመታ ሁሉን እልል ቢያስብል
እኔማ ገብቶኛል የት ጋ አሜን እንድል
አትድከም ወንድሜ እኔም እንደ እነዛ ዝም ብዬ አሜን አልል፡፡
መጋቢ ኤልያስ ገብሬ

07/10/2017

‹…እስከ መቼ…..››

1) 1ሳሙ.16፡1)

ለተናቀው ቦታ ሰጥተህ
ለአዲስ ነገር በር ዘግተህ
በማይረባው ጊዜ ፈጅተህ
እስከ መቼ ታለቅሳለህ?

ብታይ አንተ ቀና ብለህ
ለገለባው ማልቀስ ትተህ
ስትነሳ ለለውጥ ሕይወት ተዘጋጅተህ
ከእስከ መቼ ትወጣለህ፡፡

2) 1ነገስ.18፡21

ማንከስ በዝቶ ማስመሰሉ
ክብር የለው ማታለሉ
ለምን አንዱን አይከተሉ
እስከ መቼስ ሊቀጥሉ
በኃጢአታቸው ሊቃጠሉ
ምን ያደርጋል ማባበሉ?

3) ዕን.1፡2
እስከ መቼ ይሆን እኔ ኡ ኡ ምለው
ሃይሉ እርቆኝ ምማፀነው
ፍትህ ጠፍቶ ስጨነቅ ነው፡፡
እስከ መቼ በግፈኞች
አቅም በዝቶ ለጨካኞች
ሲፈነጩ ኃጢአተኞች
ፍርዱ የለህም ለአመፀኞች፡፡

እስከ መቼ ልጩኽ መቼ ትመጣለህ?
ማንም ያልሰማውን ታላቅ ስራ ሠርተህ
በሚያስደንቅ ክብርህ ዘመኔን አድሠህ
እኔ ብጠብቅህ መቼ ትደርሳለህ
የክርክር መልሴን በእጆችህ ይዘህ
ቃላት በማይገልጠው. ክብር ቤቱን ሞልተህ፡፡
መጋቢ ኤልያስ ገብሬ

07/10/2017

‹‹ነቢይነት ለእኔ…. ››

የቃሉ አገልጋዮች የሰላም አርበኞች
ቃላቸው ጠብ አይል ለአምላክ ቀናተኞች
ለተጠቁ ሁሉ ተከራካሪዎች
ተቆርቋሪ ናቸው.የድሃው አጋሮች
አካፋዮች እንጂ.አይደሉም እነርሱ ቀማኛና ሌቦች፡፡
አቅጣጫ አመላካች የአምላክ መልዕክተኞች
ለሚመጣው ትልውልድ መንገድ ጠራጊዎች

የህጉ አስተማሪ ደግሞም አማካሪ
አዋጅ ነጋሪዎች ምስራች አብሳሪ
አይደሉም እነርሱ የንዋይ አፍቃሪ፡፡

አስብ እንደገና
ተመልክተህ. መዝንና
እንደ ልድያ ቅረብና
እንደ ቤርያ ሰዎች ልብህን አስፋና
በቃል ታጠቅና በመንፈስ ጽናና
ከዋሾ ነቢያት እራስህን አድን. እውነትን ያዝና፡፡

በሐሰት ቃላቸው እየሰጡን ተስፋ
ላይ እና ታች እያልን እንዲህ ስንለፋ
በሰው ሰራሽ ተአምር ሰው እየተገፋ
ሐሰተኛው ቆሞ ክፋትን ሲያስፋፋ
የፀጋውን መንፈስ በድፍረት ሲያክፋፋ
ማስተዋል አልቻለም እራሱም ሲጠፋ፡፡

የበዓል ነቢያቶች የሕዝቡ ሟርተኞች
እውነትን አያውቁ የአንድነት ጠሮች
እየከፋፈሉ የእግዚአብሔርን ልጆች
እንቅፋት ሆነዋል ለአምላክ አገልጋዮች፡፡

ቃል አላቸው እነርሱ
በእግዚአብሔር መንፈስ ተሞልተው ሲነሱ
የነገስታቶቹን . ሰይፋቸውን ሳይፈሩ
መልዕክትን ሲያደርሱ እሳት ሲለኩሱ
ለመከራው ጽዋ እጃቸውን ሲያነሱ
ለንዋይ ለክብር ያልተጎነበሱ
በመንፈስ ቅደስ ኃይል ክብር እንዲለብሱ
ተስፋን በሰጣቸው ታምነው በንጉሡ
ከታላላቆቹ ከሁሉም አነሱ፡፡

የእናንተማ ሰዎች
ነቢያት ነን ባዮች
ሊሞዝየሙን አምጡት.ይገባኛል ባዮች
የመስቀሉ ጠላት. የወንጌል ሸቃጮች
መከራ አያውቃቸው የምቾት አርበኞች፡፡

በነቢዩ ኤርሚያስ የሠራው መንፈሱ
የባከኑ ሁሉ ፈጥነው እንዲታደሱ
ዛሬ አስነስቶኛል ህዝቡ እንዲመለሱ፡፡
ምን ይዘሃል ብለው ከጠየቁኝ
ደግሞም እንደነዚያ እኔንም ካሰቡኝ፡፡
የሚያፈርሰው ቃሉን በአፌ ላይ አድርጎአል
እሾህ ኩርንችቱን ፈጽሞ ይነቅላል
ከማፍረስ በኋላ እራሱ ይተክላል፡፡

በሐሰት ነቢያት ላይ በቃል እነሳለሁ
የማስመሰልና የማታለል መንፈስ በስሙ እሰብራለሁ፡፡
ዛሬ መልዕክት አለኝ ለዋሾ ነቢያት
በቃ ተመለሱ ከበለዓም እብደት፡፡
በበቀሉ ቅባት ተቀብቼ ቢያዩኝ
ስለ ኤልዛቤል ቤት.ፈቅደው ቢያወያዩኝ
ድርድር አላውቅም ወርውሩአት እያልኩኝ
በቃሉ እውነት ላይ ዛሬም ቆሜያለሁኝ፡፡

ስለዚህ ወገኔ አስተውለህ ውጣ
በሐሰት ነቢያት ሕይወትህን አትጣ፡፡
መርምርና እወቅ ያንን ቅዱስ መንፈስ
ወደ ቃሉ ገስግስ ህይወትህ እንዲታደስ
ከትንቢትም በላይ የፀና ቃል አለህ
ከእረሱ ስትስማማ ዘላለም ታርፋለህ፡፡
መጋቢ ኤልያስ ገብሬ

12/11/2015

2) ግራ በመጋባት ውስጥ ያለ ሰው የሚታይበት ምልክት ፡-

ትምህርት አምስት. በትንሽ በትልቁ ማልቀስና ምሬት ማሰማት ፡- (ዘፍ.21፡16)

ግራ የተጋባ ሰው በትንሽ በትልቁ ሲያለቅስና ሲያማርር በተደጋጋሚ ይሰማል፡፡አጋርም ፡- ‹‹ ፊት ለፊትም ተቀመጠች ቃልዋንም አሰምታ አለቀሰች፡፡ ›› በማለት በምን ዓይነት የምሬት ህይወትና ሀዘን ውስጥ መኖሩዋን ይጠቁመናል፡፡ዛሬ ልዩ ልዩ ችግሮች ሲያጋጥመን አንዳንዶቻችን ጥቂት ሙከራ እናደርግና ወዲያው ወደ ተስፋ መቁረጥ ወደ ለቅሶ ውስጥ እንገባለን፡፡ሌሎቻችን ደግሞ ገና ያላሰብናቸው ነገሮች ሲያጋጥመን ግራ መጋባት ውስጥ ስንገባ ምንም ዓይነት ሙከራ ሳናደርግ በምሬትና በማልቀስ ያለንበትን ግራ መጋባት እናሳያለን፡፡ማንኛውም ሰው ችግሮችና የሚያሳዝኑ ነገሮች ሲያጋጥመው ማልቀሱ መመረሩ አይቀርም፡፡ነገር ግን ምሬት ከአፋቸው የማይጠፋ ትንሽ ከተነኩ በእንባ የሚታጠቡ ሰዎች አሉ፡፡እነዚህ ዓይነት ሰዎች መፍትሔ ያልተሰጠው ግራ መጋባት ሕይወት ውስጥ እንዳሉ ያመለክታል፡፡

ወገኖቼ ስሜታችንን ለመግለጽና በውስጣችን የታመቀውን ነገር ለማውጣትና ለተንፈስ ማልቀሳችን መልካም ነው፡፡ነገር ግን ሰሚ አለው ወይ ? ለምሳሌ ሐና በእግዚአብሔር ፊት ትመረር ነበረ ሲል የሃና ምሬት ወዴት እንደሆነና ውጤቱም ምን እንደነበረ ቃሉ በግልጽ ያሳየናል፡፡ዛሬ የእኛ ምሬት ወዴት ነው ለቅሶአችንስ ወዴት ነው ? እስከ መቼስ ነው የምናለቅሰው ? ውጤቱስ ምን ይሆን ? ምንም እንኳን ችግራችን ቢያስለቅሰንም ያለቀስነው ወደ አምላካችን ባይሆንም ለፍጥረቱ የሚራራው አምላክ ግን ያንን ጩኽትና ምሬታችንን ይሰማል፡፡እርሱን ማየት እንድንችል እንደ ጥያቄአችን ሁኔታ ይመልሳል፡፡ነገር ግን ወደ እርሱ የሚደረገው ጩኽትና ለቅሶ ሲጠናቀቅ ውስጣችን በመረጋጋት ይሞላል፡፡ነገር ግን በየሄድንበት በሆነውም ባልሆነውም የምናለቅስ ከሆነ ወይ ልማድ ሆኖብናል ወይንም ደግሞ ትልቅ ግራ መጋባት ውስጥ እንዳለን ይጠቁማል፡፡ስለዚህ ግራ ያጋባን ነገር ምን እንደሆነ ማስተዋልና ተገቢ የሆነ እርምጃ ልንወስድበት ይገባል፡፡

12/11/2015

2) ግራ በመጋባት ውስጥ ያለ ሰው የሚታይበት ምልክት ፡-
ግራ ሲገባን ግራ እንደገባን በድርጊቶቻችን በሁኔታዎቻችንና በምወስናቸው ውሳኔዎቻችን ጭምር እናመለክታለን እንጂ ‹‹ ግራ ግብት ብሎኛል ›› ስላልን ብቻ አይደለም የሚታወቀው፡፡ከዚሁ ከአጋር ሕይወት ግራ መጋባትዋን የሚገልጡ ድርጊትና ተግባሮችዋ ውስጥ ጥቂት ነጥቦችን በማንሳት መውሰድ የሚገባንን ትምህርት እንውሰድ፡፡
ትምህርት አራት. ያላረፈ (ያልተረጋጋ) ሕይወት ፡- ቃሉ ሲናገር ፡- ‹‹ በቤርሳቤህ ምድረ በዳ ተቅበዘበዘች ›› ይላል፡፡ ‹‹ ተቅበዘበዘች ›› የሚለው ቃል ለአንድ ላላረፈ አንድ የሚፈልገውን ነገር ለማግኘት ሲል ያለ ትክክለኛ ምሪት ወጥቶ የሚፈልገውን ነገር ሳያገኝ የሚሄድበትን ነገር ሳያውቅ ሲልም ብዙ ምዕራፍ ከመጓዙ የተነሳ ያለበትም ስፍራ ይጠፋውና ለመመለስም ሆነ ወደ ፊትም ለመሄድ አቅጣጫው ይጠፋበትና ይቅበዘበዛል፡፡
ዛሬስ ስንቶቻችን ነን እንደዚህ በሚመስል የመቅበዝበዝ ሕይወት ውስጥ እየኖርን ያለነው ? ዛሬ እኔና እናንተ በክርስቶስ ኢየሱስ የከበደንን ሸክም ሁሉ በእርሱ ላይ ጥለን ልናርፍ የተጠራን ሰዎች ነን፡፡ነገር ግን በልዩ ልዩ ምክኒያቶችና በሚያጋጥሙን ድንገተኛ ችግሮችና አሳዛኝ ነገሮች ውስጥ ስናልፍ በእርሱ ላይ ማረፍ ችለናል ወይንስ ደግሞ ልክ እንደ አጋር በችግሮቻችን ተደናግጠን ያልተረጋጋና ያላረፈ ሕይወት ጀምረናል፡፡አጋር የተቅበዘበዘችው የራስዋን ሕይወትና የልጅዋን ሕይወት የሚታደግ ውሃን ፍለጋ ነበር፡፡የሚያስገርመው ነገር ቢኖር ምድረበዳ ላይ ውሃን አገኛለሁ ብሎ ማሰብ ጅልነት ነው፡፡ነገር ግን ማረፍ ያቃታት አጋር ለጥያቄዋ ምላሽ በማይገኝበት በምድረበዳ ነበር፡፡ምክኒያቱም ምድረ በዳ ማንንም አያሳርፍም፡፡ምድረ በዳ የሚያቋርጡበት ወይንም የሚያልፉበት እንጂ የሚኖርበት አይደለም፡፡
ኑኃሚን ለሩት ስትናገር ፡- ‹‹ ልጄ ሆይ መልካም እንዲሆንልሽ ዕረፍት አልፈለግሽምን ? ›› (ሩት. 3፡1) ሩት እንደ አጋር ባትቅበዘበዝም ነገር ግን ማረፍ የሚቻልበትን መንገድ መጓዝ ትታ በቃርሚያ ሕይወት መመላለስን ልማድ አድርጋው ነበር፡፡ አቅጣጫ ጠፍቶብን እንደ አጋር ስንቅበዘበዝ እንደ ሩት ደግሞ ተመሳሳይ ሕይወት ስንኖር እግዚ/ር ያየልንን ማየት አለመቻላችንንና በግራ መጋባት ውስጥ መኖራችንን ያመለክታል፡፡

https://www.youtube.com/attribution_link?a=ksnRBigDm6I&u=%2Fwatch%3Fv%3Dh8TnzPtDcBc%26feature%3Dshare
10/11/2015

https://www.youtube.com/attribution_link?a=ksnRBigDm6I&u=%2Fwatch%3Fv%3Dh8TnzPtDcBc%26feature%3Dshare

እምነታችን ከመጽሐፍ ቅዱስ (ከቃሉ) አንጻር ሲመዘን ፡- በሚል ርዕስ ስለ እምነት የገባንና ስለ እምነት ለሌሎች ስለምንገልፀው ነገር የያዝነውን መረዳት እንድንፈትሽ ያደርገናል፡፡ በዚህም ትልቅ ርዕስ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነውን አስተምሮ እንድንከ...

07/11/2015

1) ግራ መጋባት ለምን ይታይብናል ? (ዘፍ.21፡11-21)

ሦስተኛ ፡- የምንሄድበት መንገድ አቅጣጫው ሲጠፋብን (ዘፍ.21፡14)

የምንሄድበት መንገድ አቅጣጫው ሲጠፋብን የሆነ ቦታ ላይ ቆመን ግራ በመጋባት ውስጥ እንመላለሳለን፡፡አጋር ፡- ‹‹ እርሷም ሄደች በቤርሳቤህም ምድረበዳ ተቅበዘበዘች፡፡ ›› የሚለው ቃል መንገዱስን ጀምራው ነበረ ነገር ግን ወዴት እንደምትሄድ ባለማወቋ ምክኒያት ግራ በመጋባት ውስጥ ሆና ተቅበዘበዘች፡፡

ወዴት መሄድ እንዳለበት የማያውቅ ሰው ብዙ ጊዜ ግራ የገባው ሰው ነው፡፡ወዴት እንደሚሄድ የማያውቅ ሰው ማለት ስለሚሄድበት ስፍራ በዚያ ስፍራና በዚያ ጉዞ መሃል ላይ ምን እንደሚያጋጥመው ምንም ዓይነት መረጃ ስለሌለውና መጨረሻው የት እንደሆነ ምንም አይነት ፍንጭ የሌለው ሰው መንገድ ቢጀምርም መሀል ላይ ደርሶ ልክ እንደ አጋር ግራ መጋባቱ አይቀርም፡፡

ስለዚህ ሰው ሄዶ ሄዶ ብዙ ጊዜውንና ያለውን ሁሉ ስለሚያደርገው ጉዞ አባክኖ የሆነ ቦታ ላይ ደርሶ ከዚያ በኋላ በቀጣይነት ስለሚወስነው ውሳኔ ምን መወሰን ምን ማድረግ እንዳለበት ሲጠፋውና ጭንቅ ሲለው በጣም ከባድ በሆነ ግራ መጋባት ውስጥ ይገባል፡፡የምንሄድበትን መንገድ (አቅጣጫ) ጠፍቶብን ግራ መጋባት ውስጥ እንዳንገባ ጉዞ ከመጀመራችን በፊት ወዴት ሜድ እንዳለብን ማን መሪያአችን እንደሆነ የት መድረስ እንደፈለግን ልናውቅ ይገባናል፡፡

በሚቀጥለው ጽሑፋችን ደግሞ ፡-
2) ግራ በመጋባት ውስጥ ያለ ሰው የሚታይበት ምልክት የሚለውን እንመለከታለን፡፡

Address

Beirut
80287

Telephone

+9613369002

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Ethiopian evangelical church in Lebanon/Beirut posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Place Of Worship

Send a message to Ethiopian evangelical church in Lebanon/Beirut:

Share