ሃይማኖት አንድ ናት page

ሃይማኖት አንድ ናት page ከዘር ከፖለቲካ የጸዳ Page ነው

20/01/2022

+ አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? +

ልጅ እናቱን ‹አንቺ ሴት› ብሎ መጥራት በእኛ ሀገር ባሕልና በብዙ ቋንቋዎች ባሕል ፈጽሞ ያልተለመደ ነገር ነው፡፡ በተለይ በአደባባይ ሲሆን ይከብዳል:: ጌታ እናቱን ካልጠፋ ስም ለምን እንዲህ ብሎ ጠራት?

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ አከራካሪ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ የሚዳኘው በተጻፈበት ቋንቋ (Source language) እንጂ በተተረጎመበት ቋንቋ ባሕል አይደለም፡፡ ይህ አነጋገር በአይሁድ ዘንድ እና የዮሐንስ ወንጌል ላይ በተጻፈበት በግሪክ ቋንቋ የሚሠጠው ትርጉም በእኛ ዘንድ ካለው ትርጉም የተለየ ነው፡፡

በግሪኩ ‹‹አንቺ ሴት›› (gune = woman") ተብሎ የሚጻፍ ሲሆን ጌታችን እመቤታችንን ‹‹አንቺ ሴት›› ብሎ በጠራበት ሥፍራ ግን በግሪኩ ‹አንቺ ሴት› የሚለው ንባብ የተጻፈው ‹አንቺ ሴት ሆይ› (gynai "Dear woman") በሚል የአክብሮት አጻጻፍ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አነጋገር ደግሞ ነገሥታት ለንግሥቶቻቸው በሚጽፉአቸው ደብዳቤዎችም ላይ ጭምር ይጻፍ የነበረ እንደሆነ የቋንቋው ባለቤቶች የሆኑት ግሪካውያን አገናዝበው ጽፈዋል፡፡ ለምሳሌ አውግስጦስ የተባለው ንጉሥ ለግብፃዊቷ ንግሥት ለክሊዮፓትራ በጻፈው ደብዳቤ ላይ የተጠቀመው ቃል የግሪኩን ‹gynai› /ጋይናይ /አንቺ ሴት ሆይ/ የሚለውን የአክብሮት አጠራር እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

ጌታችን በቃና ሰርግ ቤት ‹አንቺ ሴት› ብሎ የተናገረው ንግግር የቁጣ አነጋገር ነው የሚሉ ሰዎችን ሃሳብ እንዳንቀበል የሚያደርገን ሌላው ምክንያት ደግሞ ጌታችን ‹አንቺ ሴት› የሚለውን አጠራር ለእናቱ የተናገረው በቃና ሰርግ ቤት ብቻ አለመሆኑ ነው፡፡ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እያለ በመጨረሻው ሰዓት ከመስቀሉ ሥር ቆማ መከራውን እያየች በጽኑ ኀዘን ላይ እያለች ‹‹አንቺ ሴት እነሆ ልጅሽ›› በማለት ዮሐንስን ለእርስዋ እርስዋን ለዮሐንስ ሠጥቷል፡፡

በልጅና በእናት መካከል ባለው ሥነ ልቡናዊ ትስስር ምክንያት ለእናት የልጅዋን ስቃይ ቆሞ መመልከት እጅግ ከባድ ስቃይን ያስከትልባታል፡፡ እመቤታችን እያንዳንዱ ችንካር በተወደደ ልጅዋ እጅ ውስጥ ሲቸነከር ልብዋ በኀዘን ይቸነከር ነበር፡፡ ታዲያ ‹አንቺ ሴት› የሚለው አነጋገር የቁጣ አነጋገር ከሆነ ጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ ‹በነፍስዋ የኀዘን ሰይፍ እያለፈባት› ያለችውን እናቱን እንዴት ይቆጣል?

በሰርግ ቤት ውስጥስ ስለጠየቀችው ተቆጣ ይባል ፤ በመስቀል ሥር የልጅዋን ስቃይ በዝምታ ስትመለከት የነበረችን እናት ልጅዋ በስቃዩ መካከል ትንፋሹን ሰብስቦ ‹‹ተቆጣት›› ብሎ ሊነገር እንዴት ይችላል? በስተግራው የተሰቀለው ወንበዴ ‹አንተስ ክርስቶስ አይደለህም› ብሎ ሲሰድበው መልስ ያልሠጠ ‹ከቁጣ የራቀ› አምላክ በእርሱ ስቃይ እየተሰቃየች ያለችውን እናቱን እንዴት ይቆጣል? (ሉቃ. ፳፫፥፴፱) ይህ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጽሐፍ ቅዱስ ከእናቱ ጋር በተነጋገረበት ስፍራ ‹እናቴ› ብሎ በመጥራት ወይም ‹ማርያም› በማለት ፈንታ ‹አንቺ ሴት› የሚለውን አጠራር መጠቀሙ እመቤታችን በኦሪት ዘፍጥረት በተጠራችበት ስም ለመጥራት እና እርስዋ ትንቢት የተነገረላት ዳግሚት ሔዋን ፣ ጌታችንም የዕባቡን ራስ የሚቀጠቅጠው ዘርዋ መሆኑን የሚያስረዳን ነው፡፡

በሊቃውንት ዘንድ የወንጌል መቅድም (Protevangelium / Protogospel) ወይም ‹የመጀመሪያው የነገረ ሥጋዌ ትንቢት› በመባል የሚታወቀው ‹‹በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ።›› የሚለው ትንቢት በእርስዋ መፈጸሙን ከምንረዳበት መንገድ አንዱ ጌታችን ‹አንቺ ሴት› ብሎ በመጥራቱ ነው፡፡ (ዘፍ. ፫፥፲፭)

በዕለተ አርብ በዕባብ የተመሰለው ዲያቢሎስ የጌታችንን ‹ሰኮና› በአይሁድ አድሮ ሲቀጠቅጥ ዋለ፡፡ ‹ዘርዋ› የተባለው ጌታም የዕባቡን ራስ እንዲሁ በመስቀሉ ቀጠቀጠው፡፡ በዚህ ወቅት እናቱን ደግሞ ‹አንቺ ሴት› ብሎ ጠራትና በትንቢቱ ላይ ያለችው ‹ሴቲቱ› እርስዋ መሆንዋን አስረዳን፡፡
የጻፈውን መተርጎም ልማዱ የሆነው ዮሐንስም ይህንን ጉዳይ የበለጠ ግልጽ በሚያደርግ ሁኔታ የሴቲቱን ፣ የልጅዋን እና የቀደመውን ዕባብ ማንነት በአንድ ምእራፍ ላይ አብራርቶ በራእዩ ጽፎልናል፡፡ ‹‹ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች። ... ዘንዶውም (እርሱም የቀደመው ዕባብ) በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ›› በማለት የዘፍጥረቱን ትንቢት በመተርጎም ሴቲቱ በእርግጥም ‹አሕዛብን በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ወንድ ልጅ የወለደችው› እመቤታችን መሆንዋን አስረድቶአል፡፡ (መዝ. ፪፥፱) ስለዚህ ጌታ ‹አንቺ ሴት› ማለቱ ጾታን ለማመልከት ብቻ ሳይሆን እመቤታችን የትንቢቱ ፍጻሜ መሆንዋን የሚያስረዳ የክብር አነጋገር ነው፡፡ (ራእ. ፲፪፥፩-፲፰)

እንዲሁም ለአዳም ሔዋን በተሠጠችው ጊዜ ‹‹ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል።›› ማለቱ (ዘፍ. ፪፥፳፫) ሴት የሚለውን ቃል ትርጉም ጾታን ከመግለጽ በላይ ‹ሥጋሽ ከሥጋዬ አጥንትሽም ከአጥንቴ› የሚል የእኔነት ትርጉም ያለው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ልዩነቱ የመጀመሪያው አዳም ከጎኑ ሔዋንን ያስገኘ ሲሆን ሁለተኛው አዳም ግን ከሁለተኛዋ ሔዋን የተገኘ ነው፡፡ ሆኖም ሁለተኛው አዳምም ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ የሁላችንን እናት ጥምቀትን (ቤተ ክርስቲያንን) አስገኝቷል፡፡

- ከአንቺ ጋር ምን አለኝ

‹‹ከአንተ / ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?› የሚለው አነጋገር በመጽሐፍ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን ስድስት ቦታ ፣ በሐዲስ ኪዳን ደግሞ በአምስት ቦታዎች ተጽፎ የምናገኘው አነጋገር ነው፡፡ ይህ ዐረፍተ ነገር በየተጻፈባቸው አገባቦች (contexts) ሁለት ዓይነት ትርጉም የሚሠጥ ሆኖ ይገኛል፡፡ የመጀመሪያው አገባብ አለመግባባትን የሚገልጽ አነጋገር ሲሆን ፤ ሁለተኛው አገባብ ደግሞ አክብሮትን ወይም ሰላም ጠያቂነትን የሚያሳይ አነጋገር ነው፡፡

አለመስማማትን የሚያሳይ የተግሣጽ ንግግር ሆኖ የምናገኘው በነቢዩ ኤልሳዕ ታሪክ ነው፡፡ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮራም ከይሁዳ ንጉሥ ከኢዮሳፍጥ ጋር ወደ ነቢዩ ኤልሳዕ መፍትሔ ለመጠየቅ መጥቶ ነበር፡፡ ኢዮራም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አድርጎ ስለነበር ኤልሳዕ ‹‹እኔ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ወደ አባትህና ወደ እናትህ ነቢያት ሂድ›› ብሎ መልሶለት ነበር፡፡ ኢዮራም ኤልሳዕን ለማነጋገር ሲሞክርም ኤልሳዕ በቁጣው ጸንቶ ‹‹አብሮህ ያለውን የይሁዳን ንጉሥ ባላፍር ኖሮ አንተን ባልተመለከትሁና ባላየሁ ነበር፡፡›› ብሎታል፡፡ (፪ነገሥ. ፫፥፲፫)

በዚህ ታሪክ ውስጥ በግልጽ ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ?› የሚለው ቃል ‹ከአንተ ጋር ምን ኅብረት አለኝ?› በሚል አገባብ ተቀምጧል፡፡ በተመሳሳይም እግዚአብሔር የጢሮስ ፣ የሲዶናና የፍልስጤም ግዛትን በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ስላደረሱት በደል እንደሚፋረዳቸው በተናገረበት አንቀጽ ‹‹ከእናንተ ጋር ለእኔ ምን አለኝ? በውኑ ብድራትን ትመልሱልኛላችሁን? ፈጥኜ ብድራታችሁን በእናንተው ላይ እመልሳለሁ›› በማለት ተናግሯል፡፡ በዚህም ስፍራ እንዲሁ ይህ አነጋገር ከቁጣ ጋር ተነግሮ ይገኛል፡፡ (ኢዮ. ፫፥፬)

ሁለተኛው አገባብ ደግሞ ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› የሚል ትርጉም የሚሠጠው አገባብ ነው፡፡ ንጉሥ ዳዊት ለእርሱ የተቆረቆሩ የጽሩያ ልጆች የሰደበውን ሳሚን ‹እንምታው ፣ እንግደለው› ሲሉ ‹‹እናንተ የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? እግዚአብሔር፦ ዳዊትን ስደበው ብሎ አዝዞታልና ይርገመኝ ለምንስ እንዲህ ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው?›› ብሎ ከልክሎአቸዋል፡፡ (፪ሳሙ. ፲፮፥፲) ተሳዳቢው ሳሚ መጥቶ ከእግሩ ሥር ተደፍቶ ይቅርታ ሲጠይቅም ዳግመኛ ‹‹እግዚአብሔር የቀባውን ሰድቦአልና ሞት ይገባዋል›› አሉ፡፡

ይህን ጊዜ ዳዊት ‹እናንተ የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? ዛሬ ስለ ምን ጠላቶች ትሆኑብኛላችሁ? ዛሬስ በእስራኤል ዘንድ ሰው ሊሞት ይገባልን? ዛሬስ በእስራኤል ላይ እንደ ነገሥሁ አላወቅሁምን?›› (፪ሳሙ. ፲፱፥፳፪)
በእነዚህ የንጉሡ ንግግሮች ውስጥ ‹ከእናንተ ጋር ምን አለኝ?› የሚለው ቃል በአክብሮት የተነገረ ባይሆንም መልእክቱ ግን ‹ምን ጠብ አለኝ› ማለት መሆኑን ከአገባቡ መረዳት ይቻላል፡፡ ምናልባት የመጨረሻው አገባብ ቁጣ ያዘለ ቢመስልም እንኳን እየተናገረ ያለው ለእርሱ ከእርሱ በላይ ለተቆረቆሩት ታማኝ ወታደሮቹ ጋር መሆኑን መርሳት የለብንም፡፡ እርሱም ‹ከእናንተ ጋር ምን አለኝ?› ያለውን ‹ለምን ጠላቶች ትሆኑብኛላችሁ?› ብሎ በማብራራት የንግግሩ ፍሬ ሃሳብ ‹ከእናንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ› እንደሆነ አሳይቶአል፡፡

ሌላው ማሳያ ደግሞ የግብፅ ንጉሥ ኒካዑ ንግግር ነው፡፡ ኒካዑ ካልተዋጋሁህ ብሎ ለመጣበት ለኢዮስያስ ፡- ‹‹የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? በምዋጋበት በሌላ ቤት ላይ ነው እንጂ በአንተ ላይ ዛሬ አልመጣሁም እግዚአብሔርም እንድቸኵል አዝዞኛል ከእኔ ጋር ያለው እግዚአብሔር እንዳያጠፋህ ይህን በእርሱ ላይ ከማድረግ ተመለስ ብሎ መልእክተኞችን ላከበት።›› (፪ዜና ፴፭፥፳፩) ይህ አነጋገር በትሕትና እና ‹ሆይ› በሚል የአክብሮት አጠራር የቀረበ ነው፡፡ በግልጽ ‹ልዋጋ የተነሣሁት ከሌላ ጋር ነው ፤ ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝና ነው የምዋጋው!› ነው ያለው፡፡ በእውነቱ ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ?› ማለት ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› ማለት መሆኑን ለማስረዳት ከዚህም የተሻለና ግልጽ ታሪክ የለም፡፡ ምክንያቱም ኢዮስያስ የተነሣው ለጠብ ነው፡፡ ኒካዑም በአክብሮት የነገረው ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› ብሎ ነው፡፡

እንደተጨማሪ ማሳያ የምናገኘው ደግሞ የእግዚአብሔር ሰው ኤልያስን በቤትዋ የተቀበለችው የሰራፕታዋ መበለት የተናገረችው ነው፡፡ ይህች ሴት ኤልያስ በቤትዋ በመገኘቱ በቤትዋ ያለው ምግብ ተባርኮ በረሃብ ዘመን እየተመገቡ ከከረሙ በኋላ ልጅዋ በጠና ታመመ፡፡ ይህን ጊዜ ሴቲቱ ወደ ኤልያስ ቀርባ ፡-

‹‹የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ኃጢአቴንስ ታሳስብ ዘንድ፥ ልጄንስ ትገድል ዘንድ ወደ እኔ መጥተሃልን? አለችው።›› (፩ነገሥ.፲፯፥፲፰)
ይህች ሴት ለነቢዩ በአክብሮት ያለችው ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› ነው፡፡ የቁጣና የተግሣፅ ንግግር ነው እንዳይባል መቼም ‹‹የእግዚአብሔር ሰው ሆይ...›› ብሎ የሚጀምር ቁጣ የለም፡፡ እንዲያውም በአንድ ሰው ስንቆጣ ማዕረጉን ትተን እንናገራለን እንጂ ማዕረግ ጠብቆ ቁጣ የለም፡፡

ወደ ሐዲስ ኪዳን ስንመጣ ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ?› የሚለውን ቃል የተናገሩት ዛሬ በወዳጆቻቸው አድረው ‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ማለት ስድብ ነው› እያሉ የሚበጠብጡን አጋንንት ናቸው፡፡ ከአዋቂ ጋር እንደ አዋቂ ፤ ካላዋቂ ጋር እንደ አላዋቂ ሆኖ ማደናቆር የአጋንንት ልማድ ነውና እነሱ በሚገባ ትርጉሙን ተረድተው እየተንቀጠቀጡ ለጌታ የተናገሩትን የአክብሮት አነጋገር ለእመቤታችን ሲሆን ትርጉሙ ሌላ ነው እያሉ ያውካሉ፡፡
‹‹እነሆም። ኢየሱስ ሆይ፥ የእግዚአብሔር ልጅ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ጊዜው ሳይደርስ ልትሣቅየን ወደዚህ መጣህን? እያሉ ጮኹ።›› (ማቴ. ፰፥፳፱)
‹‹እርሱም፦ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ።›› (ማር. ፩፥፳፬)
‹‹የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ አለ፤›› (ማር. ፭፥፯)
‹‹ ተው፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄሃለሁ፥ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱሱ አለ።›› (ሉቃ. ፬፥፴፬)
‹‹ኢየሱስንም ባየ ጊዜ ጮኾ በፊቱ ተደፋ በታላቅ ድምፅም። የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳትሣቀየኝ እለምንሃለሁ አለ›› (ሉቃ. ፰፥፳፰)

ምንም እንኳን አጋንንትን እንደ ማስረጃ በመጥቀስ ክብር ባንሠጣቸውም ‹የጠላት ምስክርነት የታመነ ነው› እንዲል (ትምህርተ ኅቡዓት/ትር.) የአጋንንቱ ንግግር ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ› የሚለው ቃል በአክብሮት ሊነገር የሚችል ‹ምን ጠብ አለኝ› የሚል ትርጓሜ ያለው መሆኑን በግልጽ ያስረዳል፡፡

ምክንያቱም ‹ከአንተ ጋር ምን አለን› ከማለታቸው ጋር ‹ኢየሱስ ሆይ ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ ፣ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ ፣ የእግዚአብሔር ቅዱሱ› የሚል የአክብሮት ንግግር ተናግረዋል፡፡ ከዚያም ‹እንዳታሠቃየኝ እለምንሃለሁ› የሚል ልመና ተከተለ፡፡ ልመናውም ከእግሩ ሥር እስከ መደፋት ድረስ የደረሰ ነበር፡፡ መቼም ከእግር ሥር ተደፍቶ የቁጣ ንግግር መናገር የማይታሰብ ነው፡፡
በአጠቃላይ ከላይ ባየነው የአገባብ ዝርዝር ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ?› ለሚለው ንግግር የሚያመዝነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉም ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ› የሚል ነው፡፡ በቃና ዘገሊላ ሰርግ ቤት ጌታችን ለእናቱ የተናገረው ‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?› የሚለው አነጋገርም ከአገባቡ እንደምንረዳው ሌሎች ስለ እርሱ በፍርሃት የተናገሩትን የአክብሮት የተነገረ ሲሆን ትርጉሙም ‹የጠየቅሽኝን እንዳላደርግልሽ የሚከለከለኝ ከአንቺ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› የሚል ነው፡፡ ይህን የሚያስረዳን መልሱ የእምቢታ ቢሆን ኖሮ አንደኛ እመቤታችን ልመናዋን ቀጥላ ‹እባክህን ልጄ ሆይ› ብላ ለማሳመን ትሞክር ይሆናል እንጂ ‹የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ› ብላ ለአገልጋዮቹ በልበ ሙሉነትና በእርግጠኝነት ትእዛዝ ልትሠጥ አትችልም ነበር፡፡

ሁለተኛ ደግሞ ጌታችን ከዚያ በኋላ ጋኖቹን ሙሉ ብሎ ተአምራቱን አያደርግም ነበር፡፡ እንዲያውም ጌታችን ‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ ጊዜዬ ገና አልደረሰም› ያላት በቁጣና በእንቢታ ከሆነ ለአገልጋዮቹ ‹የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ› ብላ መናገርዋ የበለጠ ቁጣውን የሚያነድ ነበር የሚሆነው፡፡ ለእርስዋ እንቢ እያላት ቁጣውን ከምንም ሳትቆጥር ሌሎች ሰዎችን ማዘዝዋ የበለጠ አያስቆጣም ወይ ሊባል ይችላል? ይህ ሁሉ የሚያሳየን ጌታችን አንዳች የቁጣ ንግግር አለመናገሩን ነው፡፡

አባ ጊዮርጊስም የጌታችን መልስ የጠብ ሳይሆን እንዲያውም የጥልቅ ፍቅር መሆኑን ሲገልጽ ‹‹በልቡ ውስጥ ለተከማቸ ፍቅሯ በሚሻል /በሚመጥን/ ነገር መለሰላት›› ‹‹ወአውስኣ ዘከመ ይኄይስ ለዘዝጉብ ፍቅረ ዚኣሃ ውስተ ልቡ›› ብሏል፡፡ (መጽሐፈ ምሥጢር) ስለዚህ ‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ› የሚለውን ንግግር የቁጣ ንግግር አድርጎ መተርጎም ጥቅሱን ከአገባቡ የወጣ ጥቅስ (Text out of context) ያደርገዋል፡

+ ጌታችን እናቱን ተቆጥቷት ይሆንን? +

የቃና ሰርግ ቤት ታሪክ ለጊዜው እናቆየውና አንድ ልጅ በአደባባይ በሰዎች ፊት እናቱን በምንም ምክንያት ቢቆጣ እንኳን ከሃይማኖት አንጻር ከሥነ ምግባርም አንጻር የሚደገፍ ሥራ አይደለም፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን ‹እናቱን በቁጣ ተናገራት› የሚለው አስተሳሰብም እንዲሁ ብዙ የሚያመጣው ጣጣ አለ፡፡ ‹‹እናትና አባትህን አክብር›› ‹‹እናቱን የሰደበ ይሙት›› የሚለውን ሕግ የሠራ አምላክ ‹እኔን ምሰሉ› እያለ ለሰው ልጆች አርኣያ ሊሆን በመጣበት በዚህ ዓለም ራሱ እናቱን በአደባባይ በሰው ፊት ያቃልላታል ብሎ ማሰብ እጅግ ከባድና ለብዙ ሰዎች የኃጢአትን በር ወለል አድርጎ ከፍቶ መረን የሚለቅ ነው፡፡ (ዘጸ. ፳፥፲፪ ፣ ፳፩፥ )
እመቤታችንን የጎዱ መስሏቸው ‹ጌታ እናቱን ተቆጣ› ብለው የሚሰብኩ ሰዎችም ሳያውቁት እየተናገሩ ያሉት በእመቤታችን ላይ ሳይሆን በራሱ በጌታችን ላይ ነው፡፡ ጌታችን ‹‹ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ማን ነው?›› ብሎ የተናገረ ንጹሐ ባሕርይ ነው፡፡ (ዮሐ. ፰፥፵፮) ‹የሚጤስን የጧፍ ክር የማያጠፋ ፣ የተቀጠቀጠ ሸንበቆን የማይሰብር› በአነጋገሩ ጭምት ነው፡፡ ስንክሳሩም ‹‹ወንድሜ ምእመን ሆይ ጌታችን ለንጽሕት እናቱ ለድንግል ማርያም ከአንቺ ጋር ምን አለኝ ጊዜዬ ገና አልደረሰም በማለቱ የክብርት እናቱን ቃል እንዳቃለለ አታስብ›› ይላል፡፡ (ስንክ. ጥር ፲፪ ቁ. ፵)
በማስከተልም ‹‹ጌታችን የሰማያዊውና የመለኮታዊ አባቱን ክብር እንደጠበቀ ይታወቅ ዘንድ እንዲሁ ከእርስዋ ፍጹም ሥጋንና ፍጽምት ነፍስን ነሥቶ ከመለኮቱ ጋር ያዋሐደውን የእናቱን ክብር ጠበቀ፡፡ በወንጌል ይታዘዛትና ይላላካት ነበር ተብሎ እንደተጻፈ›› ይላል፡፡ (ስንክ.ጥር ፲፪ ቁ. ፵፪)
በእርግጥም ጌታችን የባሕርይ አባቱን አብን ክብር እንደጠበቀ በራሱ አንደበት ‹‹አባቴን አከብራለሁ›› ሲል ተናግሯል፡፡ (ዮሐ. ፰፥፵፱) ለእመቤታችንና ለአሳዳጊው ዮሴፍም እንዲሁ ‹‹ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፥ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር።›› ተብሎ ተጽፎአል፡፡ (ሉቃ. ፪፥፶፩) እመቤታችን በቃና ዘገሊላ ስለ ወይኑ የነገረችውም የልጅዋን መታዘዝ በልብዋ ትጠብቀው ስለነበር እና እንደሚታዘዛት ታስብ ስለነበር ነው፡፡
እስቲ ነገሩን ሌሎች ከሚያዩበት ማዕዘን ለመመልከት እንሞክር፡፡ እውነት ግን ጌታችን እናቱን ሊቆጣ የሚችልበት ምን ምክንያት ነበረው? ከላይ እንደተመለከትነው የለመነችው ስለ ራስዋ ጥቅም አይደለም፡፡ በዚያ ላይ ልመናዋ ከሚያስፈልግ ነገር ውጪ ይደረግ የተባለ አላስፈላጊ የቅንጦት ልመና አይደለም፡፡ በሰርግ ቤት ሙሽሮችን ለዕድሜ ልክ ውርደት ሊዳርግ የሚችል የወይን ጠጅ እጥረት በተከሰተበት ሰዓት ‹ወይን እኮ የላቸውም› ብሎ ማመልከት እንኳን በሩኅሩኁ አምላክ ፊት ይቅርና በእኛ በጨካኞቹ የሰው ልጆች ፊት እንኳን ሊያስቆጣ የሚችል ነገር አይደለም፡፡
የለመነችው እንደ አይሁድ ምልክት ለማየት ጓጉታ አይደለም፡፡ እንደ ፈሪሳዊያንና ሰዱቃውያን ‹አይተን እንድናምንህ ምን ምልክት ትሠራለህ?› ‹ከሰማይ ምልክት ልናይ እንወዳለን› የሚል የፈተና ጥያቄ አልጠየቀችም፡፡ (ማቴ. ፲፮፥፩ ፤ዮሐ. ፮፥፳) ተአምር የማየት ምኞት አድሮበት እንደጠየቀው እንደ ሄሮድስም በአጋጣሚው ልጠቀምና ተአምር ልይ ብላም አይደለም፡፡ (ሉቃ. ፳፫፥፰) ደግሞስ ያለ ወንድ ዘር በማኅጸንዋ አድሮ በታተመ ድንግልና ሲወለድ ያየች እናት ሌላ ምን ተአምር ሊያስደንቃት ይችላል?
የሰርጋቸው ቀን የኀዘናቸው ቀን ሊሆን ስለተቃረበ ሙሽሮች ተጨንቃ መለመንዋ እንዴት የሚያስቆጣ ሊሆን ይችላል? ያለጊዜው ስለለመነችውና ስለቸኮለች ተቆጣት እንዳንል ልመናዋን ትንሽ ብታዘገየው ኖሮ ነገሩ ይፋ እየሆነ ፣ ሙሽሮቹ መዋረዳቸው ነው፡፡ ስለዚህ የደረሰችው በሰዓቱ ነው፡፡
የጌታችን አሠራር እንዲህ አልነበረም፡፡ የቅዱስ ጴጥሮስ አማት በንዳድ በታመመች ጊዜ እንዲፈውሳት ሲለምኑት እሺ ብሎ ንዳዱን ገሥፆ አላቀቃት፡፡ (ሉቃ.፬፥፴፱) የአንድ መቶ አለቃ ልጅ በታመመ ጊዜ የአይሁድ ሽማግሌዎች ሊያማልዱ በመቶ አለቃው ተልከው መጡ፡፡ ጌታችን ከይሁዳ ነገድ መሆኑን በማሰብም ‹‹ይህን ልታደርግለት ይገባዋል፤ ሕዝባችንን ይወዳልና ምኵራብም ራሱ ሠርቶልናል ብለው አጽንተው ለመኑት። ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ሄደ።›› የመቶ አለቃውንም ልጅ በመጨረሻ ፈወሰው፡፡ (ሉቃ. ፯፥፪-፮) እነዚህ ሰዎች ተአምር እንዲያደርግ ሲጠይቁት እሺ ያለ ጌታ እናቱ ስትለምነው ይቆጣል ብለን እንዴት እንቀበል? የአይሁድን ሽማግሌዎች እንኳን ያልተቆጣውን ጌታ በምን አንደበታችን እናቱን ተቆጣ ልንለው ይቻለናል?
ከሁሉ በላይ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ጸሎቴን ያልከለከለኝ ምሕረቱንም ከእኔ ያላራቀ እግዚአብሔር ይመስገን›› እንዳለው በረከሰ አንደበታችን ፣ በሚወላውል ልባችን ፣ በሚባክን ሃሳባችን ወደ እርሱ የምንጸልየውን የእኛን የኃጢአተኞቹን ጸሎት ለምን ጸለያችሁ ብሎ ያልከለከለ አምላክ ንጽሕት እናቱ በፍጹም ትሕትና ለለመነችው ልመና የቁጣ ምላሽ ሠጠ ማለት እንዴት እንደፍራለን? ዳዊት ‹‹በልቤስ በደልን አይቼ ብሆን ጌታ አይሰማኝም ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ሰማኝ የልመናዬን ድምፅ አደመጠ›› ብሏል፡፡ እርሱ በልቡ በደል ስለሌለ ጌታ ከሰማው በሃሳብዋ ድንግል የሆነች እናቱን እንዴት አልሰማትም እንላለን? (መዝ. ፷፮፥፲፱-፳)
እመቤታችን የጠየቀችው ይህን ያህል የማይጠየቅ ነገር ነው እንዴ? የመንግሥትህን እኩሌታ ፣ የሥልጣንህን ፈንታ ሥጠኝ አላለችውም፡፡ የጠየቀችው ስለ ድሆቹ ሙሽሮች ነው፡፡ እኛ በረባ ባልረባው ስንዘበዝበው የምንውለውና የምናድረው ታጋሽ አምላክ ለእናቱ ለእኛ የሠጠውን ነገር ይነሣል ማለት ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ ‹አብን አሳየንና ይበቃናል› ፤ ‹እሳት ከሰማይ ወርዶ ሕዝቡን ያጥፋቸው› ፤ ‹በግራ ቀኝህ አስቀምጠን› የሚሉ ደቀ መዛሙርትን ታግሶ ለሦስት ዓመት ከሦስት ወራት ያስከተለ ጌታ ቅድስት እናቱ ተገቢ ልመና በተገቢ ሰዓት ስትለምነው ሊቆጣ አይችልም፡፡
እንደ ወንጌሉ ብቻ ከሔድን ደግሞ እመቤታችን ከዚህ በፊትና በኋላ ምንም ነገር ስትለምነው አልተጻፈም፡፡ በወንጌል ለተጻፈው ለዚህ ብቸኛ ልመናዋም መልሱ ቁጣ ነው ብለን አምነን መቀመጥ ለእኛ ለኦርቶዶክሳውያን ፈጽሞ የሚዋጥልን ሃሳብ አይደለም፡፡ በልጅነትዋ ወልዳው ለተሰደደችው ፣ በነፍስዋ የኀዘን ሰይፍ ላለፈባት እናቱ አንዴ ብትለምነው ተቆጣ ብለን እንዴት እንናገራለን?
ጌታችን በዚህ ሰርግ ቤት እንኳንስ እንዲህ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የሚተረጉመው ‹ከአንቺ ጋር ምን ጠብ አለኝ› የሚል የአክብሮት ንግግር ተናግሮ ቀርቶ ፤ ለእናቱ የተናገረው በቀጥታና በግልፅ የቁጣ ንግግር ቢሆን ኖሮ እንኳን ጾመን ጸልየን ፣ ወድቀን ተነሥተን ምሥጢራዊ ትርጉሙን እንፈልጋለን እንጂ ሰማይና ምድር ቢነዋወጥ ‹ጌታ እናቱን ተቆጣ› ብለን አናምንም!!!

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ከቃና ዘገሊላ መጽሐፍ የተወሰደ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ! በኮሜንት መስጫው ሥር ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)

ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like, Subscribe እና Share ያድርጉ :-

የፌስቡክ ገጽ :- https://www.facebook.com/officialHenokhaile/
የቴሌግራም ቻናል : https://t.me/deaconhenokhaile
የዩቲዩብ ገጽ: https://www.youtube.com/channel/UCOaVsWC05aUjeqIEW3fWj7g

08/09/2020

+++ አትክልተኛ መስሏት ነበር +++

መቅደላዊት ማርያም በዕለተ እሑድ ገና ጨለማ ሳለ ወደ ጌታ መቃብር ልትሔድ ተነሣች፡፡ እርግጥ ነው በጨለማ መውጣት ያውም ለሴት ልጅ የሚያስፈራት ቢሆንም ለዚህች ቅድስት ግን ከክርስቶስ ሞት በላይ ሌላ ጨለማ ገዝፎ ሊታያት አልቻለም፡፡ የሕይወትዋ ብርሃን በመቃብር ውስጥ አድሮአልና ሌላ ብርሃን ነግቶ መንገድ እንዲያሳያት አልጠበቀችም፡፡ ለሰው ሁሉ የሚያበራውን መብራት ክርስቶስን ከመቃብር ዕንቅብ በታች ካኖሩት ሦስት ቀን መሆኑ እንጂ የቀንና ሌሊቱ ልዩነት አልታወቃትም፡፡ በእርግጥም ሰባት አጋንንት ከላይዋ ላይ አውጥቶላት የነበረችን ሴት የቱ ጨለማ የቱ ጋኔን ሊያስፈራት ይችላል? ‹‹ፍቅር ፍጹም ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል››ና ጨለማውን ሳትፈራ ይህች ሴት እስኪነጋ ልቆይ ሳትል ወደ ጌታችን መቃብር ገሰገሰች፡፡

እንደጠበቀችው ግን ጌታችንን በመቃብር አላገኘችውም፡፡ በዚያ የለም፡፡ በመቃብር አለመገኘቱ ለእርስዋም ሆነ ለደቀ መዛሙርቱ ተስፋ የሚያስቆርጥ ኀዘን ላይ የሚጥላቸው ነገር ሆነ እንጂ ‹‹እነሣለሁ›› ማለቱን እንዲያስታውሱ ምክንያት አልሆናቸውም፡፡ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን እንኳን ጲላጦስ ፊት ቀርበው ‹‹ያ አሳች በሕይወቱ ገና ሳለ፡- ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን›› ብለው ነበር፡፡ (ማቴ. 27፡63) ሐዋርያቱና ማርያም መግደላዊት ግን መቃብሩ ባዶ ሆኖ ሲያዩ እንኳን ‹እነሣለሁ› እንዳለ ትዝ አላላቸውም፡፡ ስለዚህ የእምነት ጉድለታቸውም ደቀ መዛሙርቱን ‹‹እናንተ የማታስተውሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ›› ብሎ ፤ እርስዋን ደግሞ ‹‹አትንኪኝ›› ብሎ ገሠፆአቸዋል፡፡ (ሉቃ. 24፡25፣ ዮሐ. 20፡ 17)

መግደላዊትዋ ጌታችንን በመቃብር ብታጣውም ‹በዚህ ከሌለማ ወደ ቤቴ ልሒድና ልረፍ› ከማለት ይልቅ በዚያው ቆማ ታለቅስ ጀመር፡፡ ከዚህ በኋላ በዕንባ በፈዘዙ ዓይኖችዋ ሁለት መላእክት ከመቃብሩ ግራና ቀኝ ሆነው ተቀምጠው አየች፡፡ ሳታስተውልም ‹‹ጌታዬን ወስደውታል›› አለቻቸው፡፡ (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳብራራው) መላእክቱ ወደ ውጪ ሲያዩ ዓይናቸውን ተከትላ ዘወር ስትል ጌታችንን ቆሞ አየችው፡፡ ሆኖም አላወቀችውም፡፡

‹‹ኢየሱስም አንቺ ሴት ስለ ምን ታለቅሻለሽ ማንንስ ትፈልጊያለሽ? አላት፡፡ እርስዋም የአትክልት ጠባቂ መስሏት ፡- ጌታ ሆይ አንተ ወስደኸው እንደሆንህ ወዴት እንዳኖርከው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ አለችው›› (ዮሐ. 20፡15)

ይህንን ተከትሎ ጌታችን ስላለማመንዋ ገሥፆአት ማንነቱን ገለጸላት፡፡ በዚህም ይህች ቅድስት ትንሣኤውን ከሰበኩ የጽዮን ልጆች አንዲትዋ ሆነች፡፡ የእስራኤልን ነጻ መውጣት የሙሴ እኅት ማርያም በከበሮ እንዳበሠረች ማርያምም የሰው ልጅን ነጻ መውጣት ያለ ከበሮ አወጀች፡፡ እርስዋን ብቻም ሳይሆን ሌሎች ሴቶችንም ዓርብ ዕለት እያለቀሱ ደረት እየመቱ ሞቱን በዕንባ አጅበዋልና እሑድ ዕለት የትንሣኤው ዜና አብሣሪዎች ለመሆን አበቃቸው፡፡ ሴት ልጅን ‹‹ደስ ይበልሽ›› በማለት የተጀመረው የአምላክ የማዳን ሥራም ሴት ልጅ ራስዋ ለሌሎች ‹‹ደስ ይበላችሁ›› ባይ እንድትሆን በማድረግ ተጠናቀቀ፡፡

ማርያም መግደላዊት ‹‹የአትክልት ጠባቂ መስሏት ነበርና ፡- ጌታ ሆይ አንተ ወስደኸው እንደሆንህ ወዴት እንዳኖርከው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ አለችው›› የሚለው ንግግር እንዲሁ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ምንም እንኳን ይህንን ቃል የተናገረችው ሳታውቀው ቢሆንም ንግግርዋ ግን ከስኅተትነቱ ይልቅ ቅኔነቱ የሚበልጥ ንግግር ነው፡፡ ‹‹አትክልተኛ መስሏት ነበር›› የሚለው ቃል ምንኛ ድንቅ ነው? አበው በትንቢተ ሕዝቅኤል 44ን ሲተረጉሙ ‹ከእውነት የሚሻል ስኅተት ከመግደል የሚሻል መሳት አለና›› ያሉት ይህንን ዓይነቱን ሳይሆን አይቀርም፡፡

ለመግደላዊት ማርያም ክርስቶስ አትክልተኛ መስሏት ነበር፡፡ ወይ ግሩም! ክርስቶስ በምድር በተመላለሰ ጊዜ ለሰዎች ‹ያልመሰላቸው› ምን ነገር አለ? እንደተወለደ ለአይሁድ ‹የዮሴፍ ልጅ መስሏቸው ነበር› ፣ ለሔሮድስ ደግሞ መንግሥቱን የሚቀናቀን ምድራዊ ንጉሥ መስሎት ነበር፡፡ ለኒቆዲሞስ ነቢይ መስሎት ነበር ፣ ለሳምራዊቷ ሴት ደግሞ መጀመሪያ ውኃ የሚለምን ተራ ሰው መሰላት ፣ በኋላ ደግሞ ነቢይ መስሎ ታይቷት ነበር፡፡ ክርስቶስ ለብዙዎ ያልመሰላቸው ምን አለ? ለግማሹ ኤልያስ ፣ ለአንዳንዱ ሙሴ ለሌላው ኢያሱ መሰለው፡፡ ለኤማሁስ ተጓዦች ‹መንገደኛ› ፣ ለሮም ወታደሮች ‹ወንጀለኛ› ፣ ለሔሮድስ መኳንንት ‹አስማተኛ› መስሏቸው ነበር፡፡ እኛ እርሱን እንድንመስል እርሱ እያንዳንዳችንን መስሎ ተሰደበ ተወቀሰ በመከራ ተሰቅሎ ሞተ፡፡ ዛሬ ደግሞ ለመግደላዊት ማርያም ‹‹አትክልተኛ›› መሰላት፡፡

ማርያም ሆይ በአንድ በኩልስ ልክ ብለሻል፡፡ ያየሽው እርሱ አትክልተኛ ነው፡፡ በእውነትስ አትክልተኛ ካልሆነ ‹‹አዳም ሆይ ወዴት ነህ›› እያለ በገነት ዛፎች መካከል ምን አመላለሰው? አንቺ አልተሳሳትሽም ‹‹ወይንን ተከልሁ አላፈራም ፣ ለወይኔ ያላደረግሁት ምን አለ? በእኔና በወይኔ መካከል ፍረዱ›› ብሎ የጠራን እርሱ አይደለምን? ‹‹ዘር ዘሪ ሊዘራ ወጣ ፣ ዘር ዘሪው እኔ ነኝ ፤ አጫጆቹ መላእክት ናቸው›› ብሎ በምሳሌ ያስተማረ እርሱ አይደለምን? ከዚህ በላይ አትክልተኛ ከየት ሊመጣ?
‹የወይን ሥፍራን ነበረችው ቅጥርም ቀጠረላት› በተባለችዋ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሁላችንን ከአብ ጋር ላንነቀል የተከለን ፣ የጎኑን ውኃ እያጠጣን ፣ በመስቀሉ እየኮተኮተ የሚያሳድገን ‹‹ጳውሎስ ሲተክል አጵሎስ ሲያጠጣ ጌታ ያሳድግ ነበረ›› የተባለለት አትክልተኛ እርሱ አይደለምን? ሦስት ዓመት ተመላልሶ ፍሬ እያጣብን አዘነ እንጂ ፣ እሾኽና አሜከላ እያበቀልን አስመረርነው እንጂ እርሱስ ብርቱ አትክልተኛ ነበር ፤ ስለዚህ መግደላዊት ማርያም ሆይ አትክልተኛ ቢመስልሽም አልተሳሳትሽም፡፡

‹‹ጌታ ሆይ አንተ ወስደኸው እንደሆንህ ወዴት እንዳኖርከው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ›› የሚለው ጥያቄም ቢሆን ከእውነታው አንጻር እጅግ ድንቅ ነው፡፡ ጌታን በእርግጥ ከመቃብር ማን ወሰደው? ማንስ አስነሣው? ራሱ አይደለምን፡፡ ማርያም ‹አንተ ወስደኸው እንደሆንህ ወዴት እንዳኖርከው ንገረኝ› አለችው፡፡ ማርያም ሆይ ጥያቄሽ ተገቢ ነው ፤ ብቻ አጥብቀሽ ጠይቂው ፤ የወሰደው እርሱ ራሱ ነው፡፡ ሥጋውን ከመቃብር ሕያው አድርጎ ነስነሥቶ የወሰደው ከፊትሽ ቆሟል፡፡ ማስረጃ ከፈለግሽ ‹‹ነፍሴን ደግሞ እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም ፤ ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ›› ብሎ ሲናገር ደቀ መዝሙሩ ዮሐንስ ሰምቶ ማስረጃ መዝግቦ ይዞበታል፡፡ አጥብቀሽ ያዢው! እንዳትለቂው! በፈቃዱ እንደሞተ ነፍሱንም ሊያኖራት ሥልጣን ያለው ከመቃብርም በሥልጣኑ የተነሣው እርሱ ነው፡፡ ማንም ወሰደው ሲሉ ብትሰሚ አትመኚ ፤ ኢየሱስን ከሙታን መካከል ወስዶ ሕያው ያደረገው ይኸው ከፊትሽ የቆመው አትክልተኛ ራሱ ኢየሱስ ነው፡፡

እግሮቹን ወድቀሽ ያዢ እንዳትለቂው ፤ ይህ አትክልተኛ ባዶ ያደረገው መቃብርን ብቻ እንዳይመስልሽ፡፡ ሲኦልን ብታዪ ምን ልትይ ነው? በዚህ ሁለት ቀን ውስጥ የራሱን መቃብር ባዶ ከማድረጉ በፊት የሲኦልን የብረት መወርወሪያ ሰባብሮ አእላፋት ነፍሳትን ዘርፎ ወደ ገነቱ ወርዶ ነበር፡፡ በዚያም ምርኮውን ሸሸገ፡፡ አሁን ደግሞ የቀረውን መቃብር ባዶ አድርጎት ቆሟልና እንዳትለቂው፡፡

መግደላዊት ማርያም ሆይ ‹‹አንተ ወስደኸው እንደሆንህ ወዴት እንዳኖርከው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ›› ያልሽው ንግግርሽ እንዴት ያለ ጸሎት ነው? ይኼንን እንኳን ለእኛም ጭምር አጥብቀሽ ጠይቂልን፡፡ ከልባችን መቃብር ውስጥ ጌታችንን ካጣነው ቆይተናል፡፡ ክቡር ሥጋውን ተቀብለን በውስጣችን ከያዝን ከሦስት ቀንም በላይ ብዙ ዘመን አልፎናል፡፡ ነገር ግን እርሱ እንደተለየን እየተሰማን ፣ ባዶነት እያስጨነቀን ነው፡፡ ከጲላጦስ ማኅተም የበለጠ የመስቀል ማዕተብ የታተመበት ሰውነታችን የጌታን ሥጋ ተቀብሎ ቢይዝም አሁን ግን ባዶነት እየተሰማን ፣ እርሱም ከእኛ እንደተለየን እየመሰለን ነው፡፡ በመቃብሩ ጠባቂዎች በካህናት ማሳበብ ፣ ‹እነርሱ ስላንቀላፉ ነው ጌታ ከእኛ ተወስዶ ባዶ ሆነን የቀረነው› ማለት ጲላጦስን እንኳን ማሳመን ያልቻለ ተራ ምክንያት ነውና ልናቀርበው አንደፍርም፡፡ ብቻ ባዶነት ሲበዛብን ‹አዳም ወዴት ነህ› ያለውን አትክልተኛ ጌታ ከሰውነታችን ጫካ ውስጥ ገብተን ‹‹ጌታ ሆይ ወዴት ነህ› እያልነው ነውና እባክሽን ጠይቂልን፡፡ እርሱ ወስዶብን ከሆነም ይንገረን፡፡ እንደ ዳዊት ‹መንፈስህን አትውሰድብኝ› እያልነው ጨክኖብን ከሆነም ይንገረን፡፡

ያኖረበትን የነገረሽ እንደሆን ግን እኛም እንዳንቺ እንድንወስደው ወደ ልባችን እንድናስገባው ንገሪን፡፡ ከዚያ በኋላ አውቀነው ‹ረቡኒ› (መምህር ሆይ) እንለዋለን፡፡ አትንኩኝ ቢለንም አናዝንም ‹‹ጌታ ሆይ አንተው በእጆችን ዳስሰን እንጂ አንዳስስህም ፣ ባዶነት ላስጨነቀው ውስጣችን ያለህበትን ንገረን እንጂ በረከሱ እጆቻችን ልንነካህ አንደፍርም፡፡ አንተን ዳስሶ እንደቶማስ ተቃጥሎ ከመጮኽ በአንተ ተዳስሶ መንጻትን እንመርጣለን›› ብለውሃል በይልን፡፡

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ሚያዝያ 23/2011 ዓ.ም.
ናዝሬት ፣ እስራኤል ተጻፈ
ፎቶ :- ለቡ መድኃኔዓለም

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ዘንድ ጸልዩ! ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like እና Share ያድርጉ
FB: https://www.facebook.com/officialHenokhaile/
Telegram: https://t.me/deaconhenokhaile
Instagram: https://www.instagram.com/p/CBnMF0nnhcQ/?igshid=549jvl607bv4
Youtube: https://www.youtube.com/channel/UCOaVsWC05aUjeqIEW3fWj7g

Address

Beirut

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when ሃይማኖት አንድ ናት page posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share