05/01/2024
[አምላክ ሰው የሆነበት]
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አከባበር ከጥንት እስከ ዛሬ
********************
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በአብዛኛው የዓለም ሀገራት በጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ታኅሣሥ 25 ይከበራል።
የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች በብዛት በሚገኙባቸው እንደ ሩሲያ፣ ግሪክ፣ ዩክሬን እና ሮማኒያ ባሉ ሀገራት ደግሞ በዕሉ በጎርጎሮሳዊያኑ ጥር 7 ላይ ያርፋል።
በሀገራችን የልደት በዓል በየዓመቱ ታኅሣሥ 29 (በየአራት ዓመቱ /በዘመነ ዮሐንስ/ ደግሞ ታኅሣሥ 28) ላይ በተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ሥርዓቶች ተከብሮ ይውላል።
የልደት በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ፈጣሪ የሰውን ልጅ ለማዳን አንድያ ልጁን ለቤዛነት የሰጠበት (አምላክ ሰው የሆነበት) መሆኑ ስለሚታመን የሥጦታ በዓል ተደርጎ ይታሰባል።
ይህን መነሻ በማድረግ በመላው ዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖች በዕለቱ የተለያዩ ስጦታዎችን ይሰጣጣሉ።
በሀገራችንም በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለክርስቶስ ልደት በዓል (ለገና) ፖስት ካርድን ጨምሮ ሌሎች ስጦታዎችን መለዋወጥ እየተለመደ መጥቷል።
የገና ዛፍን (ክሪስማስ ትሪ) በቀለማት እና በተለያዩ ጌጣጌጦች አስውቦ መስቀል የተጀመረው በ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀርመን ውስጥ መሆኑ ይነገራል።
የልደት በዓልን በገና ዛፍ የማድመቅ ልምድ በእጅጉ እየተስፋፋ የመጣው ቪክቶሪያ ኢራ (ከ1837 እስከ 1901) ተብሎ በሚጠራው የእንግሊዝ ዘመነ መንግሥት ነው።
በአሁኑ ወቅት በዓለማችን በየዓመቱ ከ350 ሚሊዮን በላይ አርቴፊሻል የገና ዛፎች እንደሚሸጡ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በኢትዮጵያ የገና መምጣትን ተከትሎ “የገና ጨዋታ” በስፋት ይዘወተራል። በገና ጨዋታ ወቅት ግጥሞችን መደርደር የተለመደ ነው። “በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ”፤ በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ” እየተባለም ይገጠማል።
በተለይ ከበዓሉ ጋር በተያያዘ በየዓመቱ የባህል ስፖርት የሚከናወን ሲሆን ከተለያዩ ቦታዎች የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን በጃንሜዳ ተሰብስበው የገና ጨዋታ ውድድር ያካሂዳሉ።
የክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን በዓሉን የማኅበራዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ይጠቀሙበታል። በበዓሉ ወዳጅ ዘመድ ይጠያየቃል፤ ዕለቱን በአብሮነት ያሳልፋል።
የገና አባት መነሻ ታሪክ በ4ኛው ክፈለ ዘመን ኔዘርላንድስ ውስጥ የነበሩ ቅዱስ ኒኮላስ የተባሉ ጳጳስ ናቸው። እኚህ አባት በልግስናቸው ስመ-ጥር እንደነበሩ የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
ይህንኑ ምሳሌ በማድረግ የገና አባቶች (ሳንታ ክላውስ) የሚባሉ ሙሉ ቀይ እና ነጭ ልብስ በመልበስ እና ረጅም አርቴፊሻል ነጭ ፂም በማድረግ ለልጆች ከረሜላ ያድላሉ።
በኢትዮጵያ የገና አባት የሚባሉት የገና ጨዋታን የሚመሩ አባቶች ናቸው፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በከተማዎች አካባቢ የፈረንጆቹን የገና አባት (ሳንታ ክላውስ) መመልክቱ የተለመደ ሆኗል።
በኢዮብ መንግሥቱ