22/08/2026
እንኳን አደረሳችሁ 🙏
ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን እረፍት ሲያስቡት ሊቃውንት አባቶቻችን “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ፣ ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ” “መዋቲ ለሆነ ሰው ሞት ይገባዋል የማርያም ሞት ግን ለሁሉም ይገርማል” ይላሉ፡፡ ይህስ እንደምን ነው ቢሉ፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በ64 ዓመቷ በጥር በ21 ቀን በ49 ዓ.ም አርፋለች፡፡ ጥር ልደታ ሰኞ ነበር፣ ስምንት፣ አስራ አምስት፣ ሃያ ሁለት እያለ ሰኞ ላይ ይውላል፡፡ እመቤታችን እሁድ በ21 አርፋለች፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያት በአጎበር አድርገው ሊቀብሯት ሲሔዱ፣ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና ከዚህ ቀደም ልጇን ተነሳ አረገ እያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ፡፡ አሁን ደግሞ እሷን ተነሳች አረገች እያሉ ሊያወርኩን አይደለምን? ለምን ስጋዋን በእሳት አናቃጥለውም ብለው ተነሱ፡፡ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊም ተራምዶ አጎበሯን ቢይዘው መልአክ ሁለት እጁን በሰይፍ ቀጣውና ተንጠልጥሎ ቀረ፡፡ ኋላም ማረው ብላ እመቤታችን አማልዳው መልሶለታል፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱሳን ሐዋርያት ደንግጠው ተበታተኑ፡፡
እመቤታችንንም ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ነጥቆ በገነት አኖራቸው፡፡ ቆይቶ ዮሐንስን አግኝተው የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ አሉት። እርሱም በገነት ከእፀ ሕይወት ስር አለች አላቸው፡፡ እነርሱም ዮሐንስ ይህን ድንቅ ነገር አይቶ እኛ ሳናይ ቀረን ብለው በነሐሴ መባቻ ጾም ጀመሩ፡፡ ነሐሴ እንደ ጥር ሁሉ ሰኞ ነው የሚብተው፡፡ ከሰኞ እስከ ሰኞ 8፣ ከሰኞ እስከ ሰኞ 15 ይሆናል፡፡ እሁድ በ14 ጌታችን ቅዱስ ስጋዋን ሰጥቷቸው ቀብረዋታል፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ አልነበረም፡፡ ከሦስት ቀን በኋላ በ16 እንደ ልጇ ከሙታን ተነስታ ስታርግ እርሱ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ሲመለስ አገኛት፡፡ በጣም አዘነ፣ ተበጸበጻ “እንደኔ ያለ እድለ ቢስ ማን አለ ቀድሞ የልጅሽን የጌታዬን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁ አሁን ደግሞ ያንቺን” በማለት ከሚጓዝበት ደመና ሊወድቅ ቃጣው፡፡ እመቤታችንም “አይዞህ አትዘን ወንድሞችህ ትንሣኤዬን እርገቴን አላዩም አንተ ግን አይተሃል፤ እመቤታችን ተነሳች አረገች ብለህ ንገራቸው” ብላ የያዘችውን ሰበን (መግነዝ) ሰጥታ ሰደደችው፡፡
እርሱም ሐዋርያትን ሲያገኛቸው “የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ?” አላቸው፡፡ “አግኝተን ቀበርናት” አሉት፡፡ “ተው ይህ ነገር አይመስልም ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር?” ሲላቸው ቅዱስ ጴጥሮስ ተቆጥቶ አንተ ወትሮውንም መጠራጠር ልማድህ ነው፣ ብቻህን ተጠራጥረህም አትቀርም ሌላውንም ታጠራጥራለህ ብሎ ወደ መቃብሯ እየሮጠ ሔዶ ቢከፍተው አጣት፤ ደንግጦ ቆመ፡፡ ቶማስም አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ተነሳች አረገች አላቸው፡፡
እነርሱም በዓመቱ ቶማስ ትንሳኤሽን እርገትሽ አይቶ እኛ ሳናይ ቀረን ብለው በነሐሴ አንድ ቀን ጾም ጀምረው ሁለት ሱባኤ ጾመው በአስራ አምስት አጠናቀዋል፡፡ በትንሣኤዋ ቀን በ16 ጌታችን እርሷን መንበር አድርጎ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካሕን ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሰናይ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ አቁርቧቸዋል፡፡ እርሷንም እንዲህ አድርጎ አክብሯታል፡፡ ሊቃውንት አባቶች “ወተቄረበት በእደ ወልዳ” እንዲሉ እርሷም በልጇ እጅ ቆርባለች፡፡
የንግስተ ሰማይ ወምድር ልመናዋ፣ ክብራ፣ የልጇ የወዳጇ ቸርነት በኛ ላይ አድሮ ይኑር አሜን!!!
√ የዩቲዩብ ገጻችንን
https://youtube.com/?si=gKXqEbltFIjp0p3h
√ ፌስቡክ ገጻች
https://www.facebook.com/Nairobi-Meserete-Haimanot-Sunday-School
√ የቴሌግራም ገጻችንን
https://t.me/MesreteHaimanot27
ቤተሰብ ይሁኑ ለሌሎች ያጋሩ