EOT Itali Bari Debre Haile St. george Church የኢጣሊ ደ/ኃ ቅ/ ጊዮርጊስ ቤ/ያን

  • Casa
  • Italia
  • Bari
  • EOT Itali Bari Debre Haile St. george Church የኢጣሊ ደ/ኃ ቅ/ ጊዮርጊስ ቤ/ያን

EOT Itali Bari Debre Haile St. george Church  የኢጣሊ  ደ/ኃ ቅ/ ጊዮርጊስ ቤ/ያን Informazioni di contatto, mappa e indicazioni stradali, modulo di contatto, orari di apertura, servizi, valutazioni, foto, video e annunci di EOT Itali Bari Debre Haile St. george Church የኢጣሊ ደ/ኃ ቅ/ ጊዮርጊስ ቤ/ያን, Chiesa, Str. s. gaetano, 19, Bari.

[ፈጥኖ የሚረዳን የቅዱስ ሚካኤል ክብር በሊቁ በቅዱስ ያሬድ ድጓ] ✍ [በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ]❖♥ የ99ኙ ነገደ መላእክት አለቃ ስለኾነው ስለ ቅዱስ ሚካኤል ክብር፣ ውበት፣ ምልጃ...
18/06/2020

[ፈጥኖ የሚረዳን የቅዱስ ሚካኤል ክብር በሊቁ በቅዱስ ያሬድ ድጓ]
✍ [በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ]
❖♥ የ99ኙ ነገደ መላእክት አለቃ ስለኾነው ስለ ቅዱስ ሚካኤል ክብር፣ ውበት፣ ምልጃ ማሕቶተ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ያሬድ በመጽሐፈ ድጓው እንዲኽ ይላል፡-
╬ “ክብረ ሚካኤል ናሁ ተዐውቀ
በትሕትናሁ ዐብየ ወልሕቀ
ዲበ አእላፍ ዘተሰምየ ሊቀ
ዘይትዐፀፍ መብረቀ ይተነብል ጽድቀ”

(የሚካኤል ክብረ እነሆ አኹን ታወቀ፤ በትሕናውም ፈጽሞ ላቀ ከፍ ከፍ አለ፤ በአእላፍ ነገደ መላእክት ላይ አለቃን የተባለ መብረቅን የሚጐናፀፍ ርሱ ጽድቅን ይለምናል) ይላል፡-

❖♥ የ99ኙ ነገደ መላእክት አለቃ ከመኾኑ ጋር ይልቁኑ ዮሐንስ በራእዩ በምዕ 8፡2 ላይ “በእግዚአብሔርም ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ” ካላቸው፤ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት በመዠመሪያ የሚጠቀሰው ቅዱስ ሚካኤል ነውና ሊቁ ያሬድ፡-

╬ ♥ “እስመ እምአፉሁ ይወጽዕ ነጐድጓድ
ሕብረ ክነፊሁ ያንበለብል ነድ
እምሊቃነ መላእክት የዐቢ በዐውድ
ሚካኤል ውእቱ መልአኩ ለወልድ”

(የወልድ አገልጋዩ ሚካኤል ነው፤ በዙሪያው ኹሉ ካሉት ከሊቃነ መላእክት ይበልጣል፤ የክንፉ መልክ ነባልባላዊ እሳትን ያቃጥላል፤ ከአንደበቱ ነጐድጓድ ይወጣልና) ይላል፨

╬ ♥“አዕበዮ ንጉሠ ስብሐት
ለሚካኤል ሊቀ መላእክት
ዘይስእል በእንተ ምሕረት
መልአከ ሥረዊሆሙ ለመላእክት”

(የምስጋና ባለቤት ክርስቶስ ለመላእክት ጭፍሮች አለቃቸው የኾነ ስለ ምሕረት የሚማልድ የመላእክት አለቃ ሚካኤልን ከፍ ከፍ አደረገው) በማለት ይጠቅሰዋል፡፡

❖♥ የስሙ ትርጓሜንም ስንመለከት ሚካኤል ማለት ቃሉ የዕብራይስጥ ሲኾን ሚ- ማለት “ማን”፤ ካ- “እንደ”፤ ኤል- “አምላክ” ማለት ነውና ሚካኤል ማለት “መኑ ከመ አምላክ” (ማን እንደ አምላክ) ማለት ነው፡፡

❖♥ የመልክአ ሚካኤል ደራሲም ይኽነን ይዞ
╬ “ሰላም ለዝክረ ስምከ ምስለ ስመ ልዑል ዘተሳተፈ
ወልደ ያሬድ ሄኖክ በከመ ጸሐፈ”

(የያሬድ ልጅ ሄኖክ እንደጻፈው ከልዑል ስም ጋር ለተባበረ ስም አጠራርኽ ሰላምታ ይገባል) ይለዋል፡፡

ቅዱስ ያሬድም፡-
╬ “መልአከ ፍሥሐ ሚካኤል ስሙ
ለመላእክት ውእቱ ሊቆሙ
መልአኮሙ ሥዩሞሙ
የሐውር ቅድሜሆሙ እንዘ ይመርሆሙ”

(ስሙ ሚካኤል የተባለ የደስታ መልአክ ለነገደ መላእክት አለቃቸው ነው፤ የተሾመላቸው አለቃቸው ርሱ እየመራቸው በፊት በፊታቸው ይኼዳል) ይላል

❖♥ በብሉይ ኪዳን ለአበው ነቢያት እየተገለጠ፤ ለሐዋርያትም በስብከት አገልግሎታቸው እየተራዳ፤ ለሰማዕታት፣ ለቅዱሳን አበው በተጋድሏቸው እየተገለጠላቸው አስደሳች መልኩን ያዩት ነበር።

❖♥ ይኽነን የቅዱስ ሚካኤልን ውበት ቅዱስ ያሬድ እንዲኽ ይገልጠዋል፡-
╬ “መልአከ ፍሥሐ ዘዐጽፉ መብረቅ
ሐመልማለ ወርቅ ሚካኤል ሊቅ”

(መጐናጸፊያው መብረቅ የኾነ የደስታ መልአክ፤ አለቃ ሚካኤል የወርቅ ዐመልማሎ ነው)

❖♥ የመልክአ ሚካኤል ደራሲም ይኽነን ውበቱን ሲገልጠው፡-
╬ “ሰላም ለአክናፊከ እለ በሰማያት ያንበለብሉ
ከመ ሠርቀ ፀሓይ ሥነ ጸዳሉ”

(የጸዳሉ ውበት እንደ ፀሓይ አወጣጥ የኾነ በሰማያት ለሚያንበለብሉ ክንፎችኽ ሰላምታ ይገባል) ይለዋል፡፡

❖♥ ቅዱስ ያሬድ ደግሞ፡-
╬ “ውእቱ ሊቆሙ ወመልአኮሙ ሚካኤል ስሙ
ዐይኑ ዘርግብ ልብሱ ዘመብረቅ
ሐመልማለ ወርቅ”

(ዐይኑ የርግብ (እንደ ርግብ የዋህ፣ ጽሩይ) የኾነ ልብሱ የመብረቅ መጐናጸፊያ የኾነለት የወርቅ ዐመልማሎ ስሙ ሚካኤል የተባለ ርሱ የመላእክት አለቃቸው መሪያቸው ነው) ይላል፡፡

❖♥ የቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነትና አማላጅነት ቅዱስ ያሬድ እንዲኽ ይገልጠዋል፡-
╬ በ፲ወ፬ቱ ትንብልናከ ዐቢይ ልዕልናከ
በመንክር ትሕትናከ
አስተምህር ለነ ሰአልናከ”

(በዐሥራ አራቱ ልመናኽ ምልጃኽ፤ በታላቅ ልዕልናኽ በሚያስደንቅም ትሕትናኽ ሚካኤል ትለምንልን ዘንድ ማለድንኽ)

╬ “ዘወሀበ ትንቢተ ለኤልዳድ ወሙዳድ
አመ ምጽአቱ ይምሐረነ ወልድ
ሰአል ለነ ሚካኤል መንፈሳዊ ነገድ
ከመ ንክሃል አምስጦ እምሲኦል ሞገድ”

(ለኤልዳድና ለሙዳድ የትንቢትን ጸጋ የሰጠ የሚኾን ወልድ በሚመጣ ጊዜ ይምረን ዘንድ ከረቂቅ ነገድ ወገን የኾንኸው ሚካኤል ከሲኦል እሳታዊ ሞገድ ማምለጥ እንችል ዘንድ ለእኛ ለምንልን) ይላል፡፡

╬ “ከናፍሪሁ ነድ ዘእሳት አልባሲሁ ዘመብረቅ ሚካኤል ሊቀ መላእክት ውእቱ ይዕቀብክሙ ነግሀ ወሠርከ ሌሊተ ወመዐልተ”

(ከናፍሮቹ የእሳት ልብሶቹ የመብረቅ የኾነ የመላእክት አለቃ ሚካኤል በተራኢነቱ በጠዋትም፤ በሠርክም፤ በቀንም በሌሊትም ይጠብቃችኊ) አለ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ፨

❤ ቅዱሳን መላእክት ሰው የጸለየውን ጸሎት ያቀረበውን መሥዋዕት ቅድመ እግዚአብሔር በማድረስ የእግዚአብሔርን ምሕረት ወደ ሰው በማምጣት ሰውን ከአምላካቸው ጋር በማማለድ ጸንተው ያሉ እንደኾኑ በብዙ ሥፍራ ላይ ተዘርዝሯል፡-
✍️ ለምሳሌ ያኽል ዘፍ 48፥15፤ ዘጸ 23፥20፤ መሳ 6፥11፤ ኢዮ 33፥23፤ መዝ 33፥7፤ 88፥6፤ 90፥11፤ 1ነገ 19፥5፤ 2ነገ 6፥15፤ ዳን 3፥17፤ 4፥13፤ 8፥15-19፤ ዘካ 1፥12፤ ማቴ 18፥10፤ ሉቃ 1፥19፤ 13፥6-9፤ 15፥7፤ ዮሐ 20፥11፤ የሐዋ 12፥6፤ ዕብ 1፥14፤ ራእ 8፥3-4ን ይመልከቱ)፡፡

❤ የቅዱስ ሚካኤል በረከት ይደርብን።

[በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ] [በድጋሚ የተለጠፈ]

በዓለ ጰራቅሊጦስ“ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም” /ዮሐ.14÷18/የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከምታከብራቸው ዘጠኙ ዐበይት (ታላላቅ) በዓላት መካከል አንዱ የጰራቅሊጦ...
06/06/2020

በዓለ ጰራቅሊጦስ

“ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም” /ዮሐ.14÷18/
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከምታከብራቸው ዘጠኙ ዐበይት (ታላላቅ) በዓላት መካከል አንዱ የጰራቅሊጦስ በዓል ነው፡፡

ጰራቅሊጦስ፡- ቃሉ ግሪክ ነው፡፡ ጰራቅሊጦስ ማለት መጽንዒ በእምነት የሚያጸና፣ መንጽሒ ከኃጢአት የሚያነጻ፣ ናዛዚ ያዘኑትን የሚያረጋጋ፣ መስተፍሥሒ፣ ያዘኑትን የሚያስደስት፣ ከሣቲ ምስጢርን የሚገልጽ ማለት ነው፡፡
ጰራቅሊጦስ፡- መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ የጰራቅሊጦስ በዓል ታሪክ እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም የሚሠራውን ሥራ ከጨረሰ በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያትን ወደ አባቴ እሄዳለሁ (አርጋለሁ) ሲላቸው ደነገጡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም መደንገጣቸውን አይቶ “ኢይደንግጽክሙ ልብክሙ እመኑ በአግዚአብሔር ወእመኑ ብየ እስመ ውስተ ቤተ አቡየ ብዙኅ ማኅደር ወምዕራፍ ቦቱ” (ልባችሁ አይደንግጥባችሁ በእግዚአብሔር እመኑ በእኔም እመኑ በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ ማለት በአባቴ ቤት በመንግሥተ ሰማያት ብዙ ማዕርገ ሀብታት አለ) (ዮሐ.14÷1) እንዲሁም /በዚሁ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14÷18/ “ኢየኀድገክሙ ዕጓለ ማውታ ትኩኑ” (ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም) ሲል መድኃኒታችን ኢየሱሰ ክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያትን አጽናንቷቸዋል፡፡

/በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 24 ቁጥር 49/ ላይም እንደተጻፈው የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያርግ ሲል ቅዱሳን ሐዋርያትን “አንትሙሰ ንበሩ ሀገረ ኢየሩሳሌም እስከ ትለብሱ ኃይለ እምአርያም” (እናንተ ግን ከላይ ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ተቀመጡ) አላቸውና ዐረገ በሐዋ.ሥራ ምዕራፍ 2- ከቁጥር 1 ጀምሮ እንደተጻፈው እነርሱም ይህን አምላካዊ ቃል መሠረት በማድረግ በኢየሩሳሌም በጽርሐ ጽዮን በማርቆስ እናት በማርያም ቤት ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው ተሰብስበው ሳሉ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዐረገ በአሥረኛው ቀን በተነሣ በሃምሳኛው ቀን ጧት በሦስት ሰዓት ለቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል ወረደላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ፍርሃት ከውስጣቸው ወጣ መንፈሳዊ ድፍረት አገኙ፡፡ አንድ የዕብራይስጥ ቋንቋ ብቻ ነበር የሚያውቁት ሰባ አንድ ዓይነት ቋንቋ (የአገሩ ሁሉ ቋንቋ) ተገለጸላቸው፡፡ ከእነርሱ ቋንቋ ጋር በሰባ ሁለት ዓይነት ቋንቋ ተናገሩ፡፡
የአገሩ ሁሉ ቋንቋ የተገለጸላቸውም ሁሉንም በአገሩ ቋንቋ እንዲያስተምሩ ነው፡፡ ከተለያየ ክፍለ ዓለም የመጡ ሰዎች ነበሩና እነዚህ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? እንዴት የእኛን አገር ቋንቋ ሊናገሩ ቻሉ? በማለት ተገረሙና አመንትተው እርስ በርሳቸው እንጃ ይህ ምን ይሆን? አሉ፡፡ ሌሎች ግን ጉሽ የወይን ጠጅ ጠጥተው ሰክረው ነው አሉ፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፡-የይሁዳ ሰዎች በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ፡- ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን ቃሎቼንም አድምጡ፡፡ ለእናንተ እንደመሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም ከቀኑ ገና ሦስተኛ ሰዓት ነውና፡፡ ነገር ግን ይህ በነቢዩ ኢዩኤል የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው፡- ይህም “እግዚአብሔር ይላል በኋለኛይቱ ቀን እንዲህ ይሆናል ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፣ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፣ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፡፡ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች አገልጋዮች ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ፡፡

ድንቆችንም በላይ በሰማይ ተአምራትን በታች በምድርም ምልክቶችን ደምን እሳትንና ጢስንም እሰጣለሁ የምትገለጠው ታላቅዋ የእግዚአብሔር ቀን ሳትመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል፡፡ የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” /ኢዩ.2÷28-32/ ይህን መሠረት በማድረግ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ልብን የሚነካ ትምህርት ሰጠ፡፡ ሕዝቡም ቅዱስ ጴጥሮስ በሰጠው ትምህርት ልባቸው ተከፈተ ቅዱስ ጴጥሮስንና ሌሎቹንም ሐዋርያት ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ? አሉአቸው፡፡ “ቅዱስ ጴጥሮስም ንስሓ ግቡ ኃጢአታችሁም ይሠረይ ዘንድ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ ኃጢአታችሁም ይሰረይላችኋል የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፡፡ የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነው፡፡ ስለዚህ ራሳችሁን ከዚህ ክፉ ዓለም አድኑ” ብሎ መከራቸው፡፡ በዚችም ዕለት ሦስት ሺህ ሰዎች አምነው ተጠመቁ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የሞቱና የትንሣኤው ምስክሮች ሆኑ፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በነሱ ላይ ሲያድር ለቤተክርስቲያን ጉዞ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ፡፡ ይህ የጰራቅሊጦስ በዓል በግሪኮች ቋንቋ ጰንጠቆስጤ ይባላል፡፡ ጰንጠቆስጤ ማለት ሃምሳኛ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ከተነሣ በኋላ ሃምሳኛው ቀን ነው፡፡ ይህም ዕለት በዓለ ሃምሳ፣ በዓለ ጰራቅሊጦስ ነው፡፡

እንዲሁም ታላቁ ሊቅ ቅ/ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን በዓል በሚገባ አነጋገር “የቤተክርስቲያን የልደት ቀን” ብሎታል፡፡ ይህ በዓል በብሉይ ኪዳን የእሸት በዓል (በዓለ ሰዊት) ይባላል፡፡ እስራኤል የነጻነት በዓላቸውን ከሚያከብሩበት ከበዓለ ፋሲካ ጀምረው ሃምሳውን ቀን በዓል አድርገው ይሰነብታሉ፡፡ በሃምሳኛው ቀን በዓለ ሰዊትን (የእሸት በዓላቸውን) ያከብራሉ፡፡ በሀገራቸው ከመጋቢት እስከ ግንቦት ያለው ወቅት በሀገራችን ከመስከረም እስከ ኅዳር እንዳለው የእሸት ወራት (የጸደይ ወራት) ነውና የእሸት በዓላቸውን የሚያከብሩት በኦሪት ዘሌዋውያን /ምዕራፍ 23÷10-17/ በታዘዘው መሠረት ማንኛውም እስራኤላዊ ገበሬ ከዘራው ሁሉ በየአይነቱ እሸቱን ቆርጦ ተሸክሞ ወደ ምኵራቡ ይመጣል፡፡ በቤተ መቅደስ የሚያገለግለው ካህን ተቀብሎ ባርኮ ጸልዮ የሚጠበሰው እየተጠበሰ የሚታሸው እየታሸ በማኅበር አንድነት ይበላል፡፡ ይህም “ቀዳምያት” ይባላል፡፡ የመጀመሪያው ማለት ነው፡፡ ከማንኛውም በረከት የመጀመሪያው በእግዚአብሔር ፊት መቅረብ፣ ለእግዚአብሔር መሰጠት እንዳለበት ታዟልና፡፡
በዚህ መሠረት ከበዓለ ጰራቅሊጦስ የምንማረው፡- ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያትን “እናንተ ግን ከላይ ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ተቀመጡ” ባላቸው መሠረት በኢየሩሳሌም ተቀምጠው ተስፋውን ሲጠባበቁ መንፈስ ቅዱስ ወርዶላቸዋል፡፡ ዛሬም መንፈስ ቅዱስ የሚወርድባት ኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን ናት “ሚ መጠን ግርምት ዛቲ ዕለት ወዕፅብት ዛቲ ሰዓት እንተ ባቲ ይወርድ መንፈስ ቅዱስ እመልዕልተ ሰማያት (ይህች ቀን ምን ያህል የምታስፈራ ናት? ይህች ሰዓት ምን ያህል የምታስጨንቅ ናት? መንፈስ ቅዱስ ከሰማየ ሰማያት የሚወርድባት) /ሥርዓተ ቅዳሴ/ ለቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ እንደ ወረደላቸው ለእኛም ሁል ጊዜ ይወርድልናል እንዲወርድልንም ሁል ጊዜ ወደ ቤተክርስቲያን መሄድ ይገባል፡፡ ከቤተክርስቲያን ተለይቶ ጽድቅ የለም፡፡”

ቤተ ክርስቲያን፡- የመንግሥተ ሰማያት በር ናት “ዛቲ ይእቲ ኆኅታ ለሰማይ (ይህች የሰማይ ደጅ ናት) /ዘፍ 28÷17/”
በዚህ መሠረት ለእኛም በ40 ቀንና በ80 ቀን የተሰጠን ጸጋመንፈስ ቅዱስ እንዳይለየን ሕጉን ትእዛዙን መጠበቅና ጧት ማታ ወደ ቤተ ክርስቲየን መገስገስ ይገባል፡፡
ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት" የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትና የቅዱሳን ተራዳኢነት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ከላዕከ ወንጌል በእደ ማርያም ይትባረክ /ቀሲስ/
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ትምህርትሥርጭት ኃላፊ

[በደብረ ምጥማቅ ከግንቦት 21-25 የአምላክ እናት የድንግል ማርያም  መገለጥና ስለውበቷ በኢትዮጵያ ሊቃውንት የቀረበላት ድንቅ ውዳሴ]✍ በመጋቤ ሐዲስ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ♥ ነቢየ እግዚአብሔር...
29/05/2020

[በደብረ ምጥማቅ ከግንቦት 21-25 የአምላክ እናት የድንግል ማርያም መገለጥና ስለውበቷ በኢትዮጵያ ሊቃውንት የቀረበላት ድንቅ ውዳሴ]
✍ በመጋቤ ሐዲስ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ
♥ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝ ፵፬፥፲፪ ላይ “ወለገጽኪ ይትመሐለሉ ኲሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር” (የምድር ባለጠጎች አሕዛብ ኹሉ በፊትሽ ይማለላሉ) በማለት ትንቢትን እንደተናገረላት ብዙዎች ቅዱሳን ቅድስት ድንግል ማርያምን ተገልጻላቸው የአምላካቸውን እናት ለማየት ተመኝተዋል፤ ብዙዎቹም ልመናቸው ተሰምቶላቸው የአምላክ እናት ተገልጻላቸው እጅግ አስደናቂ ውበቷን አይተዋል፡፡ ከነዚኽ ውስጥ በደብረ ምጥማቅ የነበሩ ምእመናን ሌሎችም ብዙዎች ንጹሓን ክርስቲያኖች ይገኙበታል፡፡

♥ ልጇ አስቀድሞ በዘመነ ሥጋዌዉ በደብረ ምጥማቅ እንደ ምትገለጽ በገባላት ቃል ኪዳን መሠረት ከኢትዮጵያ፣ ከግብጽ፣ ከአርመንያ፣ ከሶርያ፣ ከሮም፣ ከጽርዕ፣ ከፋርስ ሀገራት ተሰብስበው በደብረ ምጥማቅ ድንኳን ተክለው፤ አጐበር ጥለው ከግንቦት 21 ቀን ጀምረው እስከ 25 ቀን ድረስ በፍጹም ደስታ የድንግልን በዓሏን ያከብሩ ነበር።

♥ “ወድንግልሂ ታስተርእዮሙ በእሉ ኀምስ መዋዕል ዘእንበለ ጽርዐት ምስለ መላእክት ወጻድቃን ወሰማዕት ምስሌሃ” ይላል፤ እመቤታችን ከግንቦት 21-25 ያለማቋረጥ ከመላእክት ከሊቃነ መላእክት፤ በአካለ ነፍስ ካሉ ከነቢያት ከሐዋርያት፤ ከጻድቃን ከሰማዕታት፤ ከደናግል ከመነኮሳት ጋራ ኹና ትገለጽላቸው ነበር፤ አማኒውም ኢአማኒውም ያያት ነበር፤ ክርስትያኖች ይህንን ድንቅ ተአምር እያዩ እምነታቸው ሲጸናላቸው፤ ያላመኑት ደግሞ እያመኑ በመጠመቅ ሀብተ ውልድና ስመ ክርስትናን ይቀበሉ ነበር፡፡

♥ በጒልላቱ ላይ ስትገለጽ በውስጥ በአፍአ በነፍስ በሥጋ ንጽሕት የኾነችው የቅድስት ድንግል ማርያም የፊቷ ውበትና ብርሃን እጅግ ድንቅ ነበርና ካህናቱም ሕዝቡም ኹሉ ልክ እንደ ኤልሳቤጥ “የጌታችን እናት ለእኛ ትገለጪ ዘንድ እኛ ምንድን ነን?” እያሉ ይጮኹ ነበር፤ ርሷም ያለማቋረጥ ትባርካቸው ነበር፡፡

♥የእመቤታችን ፍቅር በእጅጉ የበዛለት አባ ጽጌ ድንግልም በደብረ ምጥማቅ በታላቅ ክብር ተገልጻ ለምእመናን የታየችው የአምላክ እናት ለርሱም ትገለጽለት ዘንድ በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፉ ላይ፡-

“አመ ትበርቂ በደብረ ምጥማቅ ኀምሰ ዕለታተ
ትእምርተ ገጽኪ ይርአይ እስከ ይትነሣእ ዘሞተ
ሚ መጠነ ማርያም ታሥተፌሥሒ ትፍሥሕተ
ኅድጊሰ ጽጌ ፍቅርኪ በጊዜ ንቃሑ መዓልተ
ብፁዕ ዘርእየኪ በሕልሙ ሌሊተ”

✍ (የፊትሽን መልክ ያይ ዘንድ የሞተ ሰው እስኪነሣ ድረስ በደብረ ምጥማቅ ለዐምስት ቀናት ያኽል በተገለጽሽ ጊዜ ማርያም ምን ያኽል ደስ ታሰኚ ኖሯል! በቀን የታየው የፍቅርሽ አበባ ይቅርና ሌሊት በሕልሙ ያየሽ ምስጉን ነው) በማለት ተማፅኗታል፡፡

♥ ዳግመኛም ይኸው ኢትዮጵያዊ ሊቅ በተመስጦ፡-
“ሥዕልኪ ጽግይተ ላሕይ ዘከመዝ ትኤድም በዓለም
እፎ ይሤኒ በሰማይ ላሕየ ገጽኪ ማርያም
ሐሤተ ትእምርትኪ እጽገብ አስተርእዪኒ በሕልም
እስመ አውዐየኒ ነደ ፍቅርኪ ፍሕም
አጥፍኦቶ ዘኢይክል ዝናም”

✍ (ማርያም ሥዕልሽ በዓለም እንዲኽ የምታበራ ከኾነ በሰማይ የፊትሽ መልክ ምን ያምር! አንቺን ከማየት የሚገኘውን ደስታ እጠግብ ዘንድ በሕልም ተገለጪልኝ፤ ዝናብ ሊያጠፋው የማይቻለው የፍቅርሽ እሳት አንድዶኛልና) ብሏል፡፡

♥ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ይኽነን መገለጧን በእንዚራ ስብሐት መጽሐፉ ላይ በአድናቆት ፡-

“ኦ ንግሥት ይገንዩ ለኪ ነገሥት ወለኪ ንግሥታት ይትቀነያ
ወኪያኪ የአኲታ ወለስምኪ ይገንያ
ወለኪ ይሰግዳ ወለክብርኪ የሐልያ
ጢሮስ ወሲዶና ሰብአ ግብጽ ወኢትዮጵያ
ፊንቂ ወሮምያ ማሮን ወአርማንያ
በሥነ ጸዳልኪ ይትፌሥሓ ወበላሕይኪ ይትሐሠያ”

✍ (ንግሥት ሆይ ነገሥታት ለአንቺ ያገለግላሉ፤ ንግሥታትም አንቺን ያመሰግናሉ፤ አንቺንም ያሞግሳሉ፤ ለስምሽም ያጐነብሳሉ፤ ለአንቺ የጸጋ ስግደትን ይሰግዳሉ፤ ለክብርሽም ምስጋናን ያቀርባሉ፡፡ ጢሮስና ሲዶና የግብጽና የኢትዮጵያ ሰዎች፣ ፊንቄና ሮምያ፣ ማሮንና አርማንያ በወጋገንሽ ውበት ደስ ይሰኛሉ፤ በደም ግባትሽም እሰይ ይላሉ) በማለት ገልጦታል፡፡

❤ ❖✔ ቅዱስ ያሬድ አባታችንም በማይ ኪራሕ ሳለ እመቤታችን ተገልጻለት ፊቷን ለማየት ታድሏልና ይኽነን በዐይኑ ያየውን ውበቷን በድጓው ላይ እንዲኽ ሲል ጽፎታል፡-

✍️ “አይ ይእቲ ዛቲ እንተ ትወርድ እምሰማይ፤ ብርህት ከመ ፀሓይ፤ አዳም ቆማ ወክሣዳ ከመ አርማስቆስ፤ መዐዛ አፉሃ ከመ ኮል”

(ከሰማይ የምትወርደው እንደ ፀሐይም የምታበራው ርሷ ማን ናት! አንገቷ እንደ ግንብ ቀጥ ያለ ነው፤ የአፏም መዐዛ እንደ እንኮይ ነው) በማለት በተመስጦ የተመለከተውን ውበቷን ተናገረ፡፡

❤ ❖✔ ይኽ የቤተ ክርስቲያን ጌጥ ቅዱስ ያሬድ በዚኽ ሳያበቃ በመላእክት እየተመሰገነች ስለተገለጸችለት ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ያየውን የውበቷን ነገር ሲናገር፦

✍ “እምኀበ መላእክት ትሴባሕ አዳም ሥና፤ መዐርዒር ቃላ ወኲሉ ነገራ በሰላም … እምወርኅ ወእምፀሓይ ይሤኒ ላሕያ …ከመ ፍሕሶ ቀይሕ ከናፍሪሃ ወከመ ኮል መዐዛ አፉሃ ወከመ ሮማን ቂሐተ መላትሒሃ … "

❤ (በመላእክት ትመሰገናለች፤ ደም ግባቷ ያማረ ነው፤ ቃሏ እንደ ማር የጣፈጠ፤ ነገሯ ኹሉ በሰላም የተመላ ነው … ውበቷ ደም ግባቷ ከጨረቃና ከፀሓይ ይልቅ ያምራል፤ ከንፈሮቿ ፍሕሶ እንደሚባል አበባ ቀይ ናቸው፤ የጒንጯ ቅላትም እንደ ሮማን ቅርፍት ነው) እያለ ሊቁ ማሕሌታይ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ይመሰክርላታል፤ አይ መታደል! አይ መባረክ!

❤ የእመቤታችን ጣዕመ ውዳሴዋ የበዛለት ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በእንዚራ ስብሐቱ ላይ ስለውበቷ በተመስጦ ሆኖ ያቀረበላትን ውዳሴ እነሆ፡-

☞ ☞ “ኦ ፍቅርት ውዕየ ልብየ በእሳተ ፍቅርኪ ወነደ ኅሊናየ እምኀልዮትኪ …” (ውዲቱ ሆይ በፍቅርሽ እሳት ልቤ ተቃጠለ፤ አንቺንም ከማሰብ የተነሣ ኅሊናዬ ነደደ፤ ለምስጋናሽ ቃሌን ከፍ ከፍ አደርጋለኊ፤ አንቺን ለማመስገንም አንደበቴን አከፍታለኊ፡፡ ንግሥት ሆይ አንደበቴ ቅንነትሽን በመናገር ደስ ይለዋል፤ ከንፈሮቼም በቸርነትሽ ጣዕም ነገር ደስ ይሰኛሉ፤ ሰላም እያልኹሽም ለስምሽ አጠራር እኔ እሰግዳለኊ (ኢሳ 49:23)፡፡

❤ንግሥት ሆይ የራስሽ ክፍክፋት ተፈጥሮ እንደ አሞራ ጥቁር የኾነ ጠጒርሽም እንደ ሐር የሚመስል ነው (መሓ 7:6)፤ የራስ ወርቅሽ የቃል ኪዳን ምልክት ነው፤ የንጽሕናሽ ብርሃንም እንደ ጧት ወገግታ ነው (መሓ 6:10)፡፡

❤ ግርምቲቱ ሆይ የቅንድቦችሽ ነበልባል (እሳት) የመብረቅ ፍንጣቂ ነው፤ ዐይኖችሽም እንደ ጨረቃ ምላት ብርሃንን የተመሉ ናቸው (መሓ 6:10)፤ ጆሮችሽም የደስታ በሮች ናቸው (ሉቃ 1:28)፤ የጒንጮችሽ ቅላትም እንደ ሮማን ቅርፍት ነው (መሓ 4:3)፡፡

❤ንግሥት ሆይ አፍሽ የበጎ መዐዛ መስኮት ነው፤ ከንፈሮችሽም የደስታ መፍሰሾች ናቸው (መሓ 4:9)፤ የአፍንጫሽ መዐዛም የበረሓ እንኮይ ነው (መሓ 7:9)፤ የጥርሶችሽ ንጣትም እንደሚያምር በረዶ ነው (መሓ 4:2)፡፡

❤ ምርጢቱ ሆይ የአንደበትሽ ሥር የወተት ምንጭ ነው፤ የንግግርሽ ቃልም እንደ ማር የጣፈጠ ነው (መሓ 4፡12)፤ የእስትንፋስሽ ቃልም የሽቱ ቅመም ብናኝ ነው፤ ጒረሮሽም፣ የማር ወለላ አረፋ ነው፡፡.

❤ የተሸለምሽ ያጌጥሽ ሙሽሪት ሆይ፤ የአንገትሽ መገናኛ (ቅርጽ) እንደ ወርቅ ዘንግ ነው (መሓ 1:11)፤ ትከሾችሽም የሰላምና የቅንነት ማረፊያዎች ናቸው፤ የጀርባሽ ልብስም የብርሃን ሐር ነው (ራእ 12:1)፤ ደረትሽም የዕውቀት አዳራሽ ነው፤ ጉያሽ የመለኮት (የጌታ) ማረፊያ ናቸው፤ እጆችሽም በንጽሕና አንባር የተሸለሙ ናቸው፤ ክንዶችሽም የንጉሥ (የጌታ) መጠጊያዎች ናቸው፤ ክርንሽም የኀይል ረድኤት ቦታ ነው፤ ክንዶችሽም የእሳት ምሳግ ናቸው፤ መኻል እጆችሽም ለመስጠት የተዘረጉ ናቸው፤ በጥፍሮችሽ የተጋረዱ ጣቶችሽ እንደ ወርቅ ፍቅፋቂ ነው::

❤ ሙሽሪት ሆይ ጡቶችሽ እንደ ወይን ፍሬ የተወደዱና ያማሩ ናቸው (መሓ 7:8) ፡፡ ጐኖችሽም በወርቅ ሐመልማል የተሣሉ (ያጌጡ) ናቸው (መዝ 67(68):13)፡፡ የማሕፀንሽ መቅደስ በአበባ (በጸጋ መንፈስ ቅዱስ) የታጠረ ነው፣ (መሓ 7/3) የልቡናሽ ጥልቀትም በቸርነት ቃል፤ ኲላሊቶችሽ የትእዛዝ ጽላት ናቸው፤ ኅሊናሽም የጥበብ መሠረት ነው፤ አንጀትሽም የይቅርታ ሣጥን ነው፤ የውስጥ ሰውነትሽም የቅዱሳን ቅድስት ምልክት ነው፤ የዕንብርትሽ ዙሪያም እንደ ማኅተም ቅርጽ ነው (መሓ 7:3)፤ ማሕፀንሽም የምስጋና ዙፋን ነው::

❤ የድንግልናሽም ምሳሌ፤ የታተመ የነቢያት መጽሐፍ ነው (ኢሳ 29:11)፤ የወገብሽ ትጥቅም የቅድስና ጸጋ ነው፤ ጒልበትሽም የአርያም (የሰማይ) ወገን ናቸው፤ የጭኖችሽ (የእግሮችሽ) አነዋወርም እንደ እብነ በረድ ምሶሶች ነው፤ እግሮችሽም ምሕረትን ለማድረግ የተፋጠኑ ናቸው፤ የማይታበዩ ጫማዎችሽም የጥበብ መድረክ ናቸው፡፡ እግርሽም በቅንነት ጐዳና የጸኑ ናቸው፤ የእግርሽ ጣቶችም በጥፋት ደንጊያ የማይሰነካከሉ ናቸው፤ ጥፍሮችሽም በላያቸው እንደ ብርሃን ብልጭ የሚሉ ናቸው፡፡

❤ የቁመናሽ አካልም እንደ ዘንባባ ያማረ ነው (መሓ 7:8)፤ የመልክሽ ደም ግባትም ለዐይን የተወደደ ነው፤ ድንግል ሆይ እጅግ በጣም አማርሽ፤ ከራስሽ እስከ እግርሽ ክፉ ነገር የለብሽም (መሓ 4:7)፤ ደም ግባትሽን የሚመስለው የለም፤ ኹለንተናሽንም የሚተካከለው የለም፡፡ ምርጢቱ ሆይ መልካም በኾነውና በጎም በኾነው ኹሉ መሰልኹሽ ነገር ግን ምስጋናሽን መጨረሽ አልቻልኹም፡፡)፡፡ (አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ)

♥ የመልክአ ማርያም ደራሲም የአምላኩን እናት ቅድስት ድንግል ማርያምን ፊቷን ለማየት ሽቶ በናፍቆት ኾኖ፡-

“ሰላም ለመልክእኪ ዘተሠርገወ አሜረ
ዘያበርህ ወትረ
ፍቅርትየ አንቲ እንተ ታበድሪ ፍቅረ
አርእዪኒ ገጸ ዚኣኪ ማርያም ምዕረ
ዘኢይሰምዖ ካልእ እንግርኪ ነገረ”

♥ (ኹልጊዜ (ዘወትር) የሚያበራ ፀሓይን ጌጥ ላደረገ መልክሽ ሰላምታ ይገባል፤ ፍቅርን የምትመርጪ (የምታስቀድሚ) አንቺ ፍቅረኛዬ ማርያም ሌላ የማይሰማው ነገርን እነግርሽ ዘንድ አንድ ጊዜ ያንቺን ፊት ግለጪልኝ) በማለት ተማፅኗታል፡፡

♥ በመኾኑም በደብረ ምጥማቅ የተገለጠችላቸው ምእመናን የአምላክን እናት አይተው እንደተደሰቱ፤ ዛሬም ለእኛ በመስቀል ሥር ከልጇ ለተቀበለችን ለአደራ ልጆቿ በረድኤት ትገለጽ ዘንድ አበው ካህናት ሌሊቱን በሰዓታት ምስጋና፦

✍ “ንዒ ኀቤየ ኦ ድንግል ምስለ ወልድኪ ፍቁርኪ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመ ትባርኪ ላዕሌነ” (ድንግል ሆይ ከተወዳጅ ልጅሽ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋራ ወደ እኔ ነዪ እኛን ትባርኪ ዘንድ (በእኛ ላይ በረከትን እንድታሳድሪ) በማለት ይማፀኗታል።

[የአምላክ እናት ሆይ ዛሬም ለእኛም በእጅጉ ለምንወድሽ ለልጆችሽ በረድኤት ትገለጪልን ዘንድ እንማፀንሻለን፡፡]
የቴሌግራም ገጼ https://t.me/joinchat/AAAAAFTyR7tztt08pN9U-w
✍ ከመጋቤ ሐዲስ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ

አርባ ቀንም ከእነርሱ ጋር ቆየ                    ሐዋ.1፡3                                                             ጌታችን ከትንሳኤው በኋ...
27/05/2020

አርባ ቀንም ከእነርሱ ጋር ቆየ
ሐዋ.1፡3

ጌታችን ከትንሳኤው በኋላ ከሐዋርያቱ ጋር ሲቆይ ምን እንዳስተማረ በዝርዝር መጽሐፍ ቅዱስ አልጠቀሰልንም፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ሉቃስ ቅዱሳን ሐዋርያቱን ከእነርሱ ስለመለየቱ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ወደ እነርሱ እንደሚመጣ በመንገር፤ በተለይም ከዚህ በፊት ያደረገውን ያስተማራቸውን እያጸና የእግዚአብሔር መንግስት በምድር ላይ እንዴት እንደምትሰፍን (እንድትሰበክ) ቅዱሳት መጽሕፍትን (የብሉይ) ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ ፤የዓለም ድኅነት እውን መሆኑን በማስረጃ (መጽሐፍትን)ጠቅሶ አስተምሯቸዋል፡፡ “ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው”። ይላል፡፡ ሐዋ. 1፡3

በቤተክርስቲያን አስተምህሮ የኪዳን ጸሎትም ከነዚህ ትምህርቶች መካከል እንደሚጠቀስ ያስረዳል፡፡ (መቅድመ ኪዳን ትርጓሜ)
በደሙ ፈሳሽነት የመሰረታትን ቤተክርስቲያን አምዶቹን ለማቆም አዲሲቷን ቤተክርስቲያን ለማዘጋጀት አርባ ቀንን ወሰደ፡፡ሙሴን በተራራ ላይ ለአይሁድ ቀዳሚቱን ሕግ (ሕገ ኦሪትን) ለእስራኤላውያን በሙሴ አማካኝነት ለመስጠት ሙሴን በተራራው ላይ አርባ ቀንና ሌሊት ማቆየት ነበረበት፡፡ ይህውም ሙሴን ለአዲስ ምሪት፤ ለአዲስ ሕግ ስሪት፤ ለነጻነት ወደ ተስፋይቱ ምድር መሪ አድርጎት ስለነበር ሙሴን አዘጋጀው፡፡ “ሙሴም ወደ ደመናው ውስጥ ገባ ወደ ተራራውም ወጣ፤ ሙሴም በተራራው ላይ አርባ ቀን አርባ ሌሊትም ቆየ ”።ዘጸ. 24፡18
ኤልያስ ከአክአብና ከኤልዛቤል እንዲሁም ከካህናተ ጣዖት ጋር በነበረው ትግል አንድ ጊዜ በተመገበው ምግብ አርባ ቀንና ሌሊት መጓዙን መጽሐፍ ቅዱስ ሲነግረን፣ እግዚአብሔር ይህንን ጊዜ አገልጋዮቹን ለልዩ ተልእኮ የሚያዘጋጅበት ጊዜ መሆኑን ያስረዳል፡፡ 1ኛ.ነገ. 19፡8

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከሞት ከተነሳ ከአርባ ቀን በኋላ ሕማምን ደግሳ ሞትን ከሰጠችው ከኢየሩሳሌም ወደ ሰማያዊ አባቱ በቀኙ ሊቀመጥ (ከአብ አባቱ ጋር ያለ መስተካከልን በስጋው ወደቀደመው ክብሩ ከሥጋዌ በፊት በነበረ የቃል ክብር መቀመጡን) ያመለክታል፡፡

ደቀመዛሙርቱን ወደቢታንያ ካወጣቸው በኋላ እጆቹንም አንስቶ ባረካቸው፡፡ “እስከ ቢታንያም አወጣቸው እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው”። ሉቃ 24፣50 በሰማይና በምድር ስልጣን ያላቸው፣ በመስቀል ላይ ለሰው ድህነት በተቸነከሩ እጆቹ የመጨረሻውን ቡራኬ ሰጠ፣ ስልጣነ ክህነትን መሰረተ፡፡ ከዚያም ሐዋርያቱ እያዩት ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ እያለ ወደ ሰማይ ተነጠቀ፡፡እንደ ኤልያስ የእሳት ሰረገላ አልተጫነም እንደ ሄኖክም አልተሰወረም፡፡ በአይናቸውም እያዩት የመሬትን ስበት ለቆ በርኅቀት (እየራቀ) ወደ ሰማይ ወጣ (አረገ) ፡፡ ይህም የጌታችን እርገት ቅዱስ ያሬድ እንደተረጎመው የቅዱሳንን (የክርስቲያኖችን) እርገት ያጠይቃል፣ ያመለክታል፡፡

ይህ የጌታችን እርገተ ሥጋ ነው፡፡ የቃል እርገት በማህጸን ተፈጽሟል፤ ይህውም እመቤታችን ይኩነኒ (እንደቃልህ ይሁንልኝ) ባለች ቅጽበት ቃል ከአባቱ ሳይለይ መጥቶ በማህጸነ ማርያም ስጋ ሆኖ አረገ፡፡

ሐዋርያት አሁንም ትኩር ብለው በማየት ላይ እንዳሉ እንደ ትንሳኤው ሁሉ መላእክት አስረጅ ሆነው የደስታ የምስራች ምልክት የሆነውን ነጭ ለብሰው ቀርበው ተናገሯቸው፡፡ የጌታም አገልግሎት የተጀመረውም ሆነ ሐዋርያቱም ከገሊላ አካባቢ የተጠሩ ስለነበሩ የገሊላ ሰዎች አሏቸው፡፡ “ደግሞም፦ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው”።

በዚህም ምልክት ዛሬ በሥጋ ሲያርግ ያዩት ኢየሱስ በአካል በተወጋ ጎኑና በተወጉ እጆቹ ምስክር አድርጎ ለፍርድ እንደሚመጣ መላእክት ነገሯቸው፡፡ ለዚህ ነው በጸሎተ ሃይማኖት “ወንሴፎ ትንሳኤ ሙታን ወህይወተ ዘይመጽእ” የሙታንን መነሳት የሚመጣውንም ሕይወት ተስፋ እናደርጋለን ብለን የምናምነው።

በጌታ እርገት ትንቢተ ነቢያት ተፈጽመዋል፡፡ ቅዱስ ዳዊት “አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ” መዝ.47፡5 በማለት ኢየሱስን ከስላሴ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር መሆኑን አስረዳን፡፡ “ዐርገ በስበሃት ውስተ ሰማያት” በክብር በምስጋና ወደሰማይ ዐረገ፡፡ በሚያስደንቅ ተአምራዊ ሁኔታ ከምድር ከፍ ከፍ በማለት ወደ ሰማይ ወጣ፡፡ ብሩህ ደመና ውስጥ ገባ፡፡ መላእክት በብርሃን በስልጣን በቅዳሴ አጅበውት የምስጋና ባለቤት በታላቅ ክብር ዐረገ፡፡ ይህንን በማድረግ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ የተቀበለውን የተላከበትን አላማ ታላቁን የማዳን ሥራ በመስቀል ላይ ፈጽሞ ወደ አባቱ መመለሱን ያስገነዝባል፡፡

ሌላው “ዐርገ ውስተ አርያም ጼዊወከ ጼዋ ወወሀብከ ጸጋከ ለእጓለመህያው “ወደ ላይ ዓረግህ፥ ምርኮን ማረክህ፥ ስጦታንም ለሰዎች ሰጠህ፥ ደግሞም ለዓመፀኞች በዚያ ያድሩ ዘንድ”። መዝ. 68፤14 እንዳለ ከሰይጣንና ከኃጢአት መውጊያ በታች ነበረውን የሰው ልጅ ከሰይጣን ማርኮ የራሱ አደረገ፤ የልጅነት ጸጋውን በቤተክርስቲያን በኩል ለሰው ልጅ ሰጠ፡፡ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ልባቸው በደስታ ተሞልተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ ይላል፡፡ በአእምሮአቸው ውስጥ የእግዚአብሄር ልጅ መሲህና ጌታ መሆኑን መጠራጠር አቆሙ፡፡ ተመልሶ መምጣቱንም ተስፋ አደረጉ፡፡ የመንፈስ ቅዱስን መምጣት በመጠበቅ በኢየሩሳሌም ይቆዩ ዘንድ አዘዘዛቸው፡፡ “እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ”። ሉቃ 24፡49

ጌታ በተሰቀለ ጊዜ ሐዋርያት ተበታትነው ከኢየሩሳሌም ወጥተው የነበሩም አልጠፉም፡ ዛሬ ግን እንዳይወጡ አዘዘ፡፡ ኢየሩሳሌም ከተባለች ቤተክርስቲያን መውጣት መንፈሳዊ ሃይል ያሳጣል፡፡ ከተስፋው ይለያል፡፡ በየመንደሩ ያለው ወሬ እንጂ ቃለ እግዚአብሄር አይደለም፤ ኃጢአት እንጂ ጽድቅ የለም፤ ሞት እንጂ ህይወትን ድህነት የለምና አትውጡ አላቸው፡፡ለሞቱና ትንሳኤው ምስክር ለመሆን ኋይልን መቀበል ይገባቸዋልና፡፡ ያውም በወቅቱ እይታ ያልተማሩ ከማሕበረሰቡ የተናቀውን ሥራ የሚሰሩ ዝቅተኛ ግምት ከሚሰጣቸው ማህበረሰብ የተጠሩ ደቀ መዛሙርን ለመንግስቱ ተስፋ ወጌልን አብሳሪ ማድረግ አስደናቂ ነው፡፡

በመንፈስ ቅዱስ ባልታደሰ ሰውነታቸው አህዛብ መከራ አጽንተውባቸው እንዳይክዱ፤ ያለመንፈስ ቅዱስ እውነተኛ ምስክር መሆን ስለማይቻል፡፡ራስንም ዓለምንም መለወጥ አይቻልምና፤ ምስክር ለመሆን ኃይልን መቀበል ይገባቸዋልና በኢየሩሳሌም ቆዩ አላቸው፡፡ ዮሐ. 15፡26

የኢየሱስ ክርስቶስ እርገት ክርስቶስን በዐይን ሳይሆን በእምነት ብቻ እንድናየው አደረገን ፡፡ እርገት ማየትን በማመን ተካ፡፡ የጌታ እርገት የመስቀሉ ፍሬ ነው፡፡ መከራን በመቀበል ወደ ክብር ይገባ ዘንድ ገባው ነበርና ነው፡፡ “ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን? አላቸው”። ሉቃ 24፡ 26፡፡ ጌታ

በማረጉ ሰውን ልጅ ባህርይ ወደ ቀደመ ክብሩ አስገባው፡፡ በሰው እጅ ባልተሰራች ሰማያዊ ውሳጤ መንጦላእት ሊቀ ካህናት ሆኖ ገባ አለ ቅዱስ ጳውሎስ፡፡

“ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፥የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም”። ዕብ. 9፡11

የሰው የጎሰቆለ ማንነት ከራሱና ከአባቱ ጋር አንዴ ለዘለአለም ካስታረቀ በኋላ ራሱ ፈራጅ ሆኖ ይኖራል፡፡ ዳግመኛም ይመጣል፡፡ ”የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል” ማቴ 25፡31

መ/ር ንዋይ ካሳሁን

27/05/2020

እንኳን ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ እርገት በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን።

14/05/2020

😭🔔🔔አዋጅ አዋጅ አዋጅ ወቅታዊ መዝሙር በመ/ር ምህረተአብ🙏

⛪እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ልደቷ በሰላም አደረሳችሁ⛪🤲 የበዓሉ ዝግጅት ተሰምተው ከማይጠገቡ መምህራን እነሆ❤😍https://youtu.be/ys0VW4tIh9w
09/05/2020

⛪እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ልደቷ በሰላም አደረሳችሁ⛪🤲
የበዓሉ ዝግጅት ተሰምተው ከማይጠገቡ መምህራን እነሆ❤😍
https://youtu.be/ys0VW4tIh9w

+++ የቀኝ ዐይን +++          ድንግል ማርያም    በመምህር  ብርሃኑ አድማስእንኳን ለበዓለ ልደታ ለማርያም ( ለግንቦት ልደታ) በሰላም አደረሳችሁ፡፡      በስመ አብ ወወልድ ወመ...
08/05/2020

+++ የቀኝ ዐይን +++
ድንግል ማርያም
በመምህር ብርሃኑ አድማስ
እንኳን ለበዓለ ልደታ ለማርያም ( ለግንቦት ልደታ) በሰላም አደረሳችሁ፡፡


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

አፍጣኒተ ረድኤት ማርያም በጊዜ ምንዳቤ ወአጸባ፤ ለዐይን እምቀራንባ፤ አንቲ ዉእቱ ረዳኢተ ያዕቆብ በቤተ ላባ፤ በኩሉ ኅሊናሃ ወበኩሉ አልባባ፤ዘኢታፈቅረኪ ነፍስ ትሠሮ እምሕዝባ፡፡

የነገረ ማርያም ሊቅ(Marian Doctor)እየተባለ የሚጠራዉ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ እመቤታችንን በብዙ ምሳሌ እየመሰለ፣ እየተረጎመና እያመሰጠረ ብዙ ጊዜ አመስግኗታል፡፡ ምንም እንኳ እኛ የምናዉቀዉ የምስጋና ድርሰቱ ለጸሎት የምንጠቀምበት ዉዳሴ ማርያም ቢሆንም ከትርጓሜና ከስብከቶቹ ዉጪ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ስንኝ ያላቸዉ የምስጋና ድርሰቶች(Hymns) መድረሱን ታሪክ ጸሐፊዉ ሶዝመን መዝግቦልናል፡፡ ከነዚህ የምስጋና ድርሰቶቹ መካከልም ‹‹በእንተ ልደት››(On Nativity) እና ‹‹በእንተ ቤተ ክርስቲያን››(On the Church)በተባሉ ትልልቅ ድርሰቶቹም እመቤታችንን ደጋግሞ ያመሰግናታል፡፡

በተጠቀሱት ሁለቱም ድርሰቶቹ ዉስጥ እመቤታችንን ለማመስገን ከተጠቀመባቸዉ ምሳሌዎች ዉስጥ አንዱ ዐይን ነዉ፡፡ ሊቁ ስለ ቤተክርስቲያን በደረሰዉ የምስጋና መዝሙሩ ዉስጥ እንዲህ ይላታል፤ ‹‹ዐይን ጥርት የሚለዉ ከፀሐይ ብርሃን ጋር ተዋሕዶ ከብርታቷ ኃ ይልን ከዉበቷም ነጸብራቅን ሲቀበል ነዉ፤ በዚህ ጊዜ በግለቷ ይሰነገላል፣ያበራል፤ በዉበቷም ያጌጣል፤… ልክ እንደዚሁ ማርያም ዐይን ናት፤ብርሃን (ጌታ) ማደሪያዉን በእርሷ አዘጋጀና መንፈሷን ጽሩይ አደረገ፤አሳቦቿን አጠራ፣ኅሊናዋንም ንጹሕ አደረገ፤የድንግልናዋንም ክብር አበራዉ ››/Hymns on the Church, 36, 1-2/፡፡ ሊቁ በዚሁ ድርሰቱ ዉስጥ ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ፤ ‹ለዚህ ዓለም ሁለት ዐይኖች ተሰጡት፤ ማየት ያልተቻላት የግራ ዐይን ሔዋን ስትሆን፣ የምታበራዉ የቀኝ ዐይን ደግሞ (እመቤታችን) ማርያም ናት፡፡በማታየዉ በጨለማዋ ዐይን ምክንያት መላዉ ዓለም ጨለመ፤ ስለዚህም ሰዎች በጨለማ ጥላ ዉስጥ ሆነዉ ሲዳብሱ ያገኙት ሁሉ አምላክ ፣ ሐሰቱም እዉነት መሰላቸዉ፡፡ነገር ግን ዓለም እንደገና በሌላ ዐይኑ ባበራና (ባየና) ሰማያዊዉ ብርሃንም በዚች ዐይን ሰሌዳ ዉስጥ ባንጸባረቀ ጊዜ ሰዎችም ቀድሞ ያገኙትን(ያመለኩትን) የኑሮአቸዉ ዉድቀት(የባሕርያቸዉ መጎስቆል) መሆኑን ተረድተዉ ወደ ማንነታቸዉ ተመለሱ (አንድነታቸዉን አገኙ)›› ይላል /Ibid, 37, 5-7/::

በዚህ መሠረት የእመቤታችን ልደት ዓለም ማየት የጀመረበት ዕለት ነዉ ማለት ነዉ፡፡ በርግጥም በነገረ ማርያም መጽሐፋችን ላይ እንደተገለጸዉ እመቤታችን በቴክታና በጥሪቃ(ሰባተኛ ቅድመ አያቶቿ) በታየዉ ሕልም መሠርት ዓለምን ሰፍኖበት ከነበረዉ ድቅድቅ የኃጢኣት ጨለማ እፎይታ የሰጠችዉ ጨረቃ እርሷ ናት፡፡ በጨለማ ሲያዩት የሚያስፈራዉና ሌላ ሌላ የሚመስለዉ ጉቶዉ፣ ቁጥቐጦዉ ፣ ድንጋዩ ፣ ጉብታዉ….ሁሉ ተራ ነገር መሆኑ የተጋለጠባት፤ ሰዎችም የሰገዱለት ሁሉ አምላክና ጌታ መሆኑ ቀርቶ ድንጋይ ጉብታ መሆኑን ማየት የጀመሩባት፣ ከደገኛዉ ፀሐይ ክርስቶስ መዉጣታ በፊት ከረጂሙ ዘመን ጨለማ ጭንቀት የተገላገልንባት ጨረቃ፣ ብርሂት የቀኝ ዐይን እመቤታችን ማርያም ናት፡፡ ስለዚህም ልደቷን የጨለማችን መገፈፍ፣ የዐይናችን ማየት፣ የብርሃናችንም መዉጣት ነዉና በፍጹም ደስታ እናስበዋለን፤ እናከብረዋለንም፡፡

ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምን የምናስታዉሰዉም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ብዙ በማመስገኑ ብቻ ሳይሆን ግሩም አደርጎ በማመስጠሩና እንዲህ ያለ ልዩ ልዩ ነገር በማምጣቱም ጭምር ነዉ፡፡ ለነገሩ ሰዉ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ከሆነ በኋላ ይህን ሁሉ ማድረጉ አያስደንቅም፡፡ የሆነዉ ሆኖ የእርሱን ያህል በልዩ ልዩ ሕብረ-አምሳል ያመሰገናት ያለ አይመስልም፡፡ሊቁ በልደት ድርሰቱም‹‹እናትህ አስደናቂ ናት፤ ጌታ ወደ እርሷ ገባና አገልጋይ ሆነ፤ እየተናገረ ገብቶ በእርሷ ዉስጥ ግን ዝም አለ፤ ወደ እርሷ በነጎድጓድ ድምፅ ገብቶ በእርሷ ዉስጥ ጸጥታን አሳደገ፤ የዓለሙ እረኛ ገብቶ በግ ሆኖ ተወለደ፤ እንደ በግም ‹ባ› እያለ ተገለጠ ››/On Nativity, 11, 6/ እያለ አስደናቂነቷን እየደጋገመ ይናገርላታል፡፡አንድ ብቻ ጨምሬ ወደ በዓሉ ልመለስ፡፡ቅዱሱ ሊቅ ጌታን እንዲህ ይለዋል፤ ‹‹አንተና እናትህ ብቻ ተወዳዳሪ የሌላችሁ ዉቦች ናችሁ፤ በአንተ ላይ ምንም ምን ትንታ(mark) በእናትህም ላይ እንከን(stain) የለም››/Carmina Nisibena, 27,8/፡፡ምንኛ ግሩም ምስጋና፣ እንዴትስ ያለ ፍቅር፣ እነደምንስ ያለ መረዳት ነዉ? መብቃት ነዋ! መብቃት! ከሌላ ከምን ይገኛል? እርሱ ካልገለጸ፡፡

ከቅዱስ ኤፍሬም ሌሎች ድርሰቶች የተነሳሁትና ርእሴንም በእርሱ ምስጋና ያደረገሁት እንዲሁ አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ዉዳሴ ማርያም እየተጣጣለና ድርሰቱም የእርሱ ሳይሆን የኢትዮጵያዉያን ነዉ (ምነዉ በሆነና ነበር) ፤ ወይም ደግሞ እርሱ ስለ ሌላ የደረሰዉን የእኛ ሰዎች የማርያም ምስጋና ነዉ ብለዉ ነዉ እንጂ እርሱስ እንዲህ አይልም መባል ስለተጀመረ እረሱ ስለ እርሷ ከደረሰዉ ወደ ግእዝ የተተረጎመዉ ትንሽ መሆኑንና ከላይ ለምሳሌነት ካቀርብኳቸዉ በላይ በዉዳሴ ማርያም ምን አዲስ ነገር አለ ለማለት ነዉ፡፡ ይህችን ታህል ጥቆማ ከሰጠሁ ቦታዉም ጊዜዉም የጽሑፉም ዓላማ በዚህ ጉዳይ ላይ መከራከር አይደለምና ወደ እናታችን በዓለ ልደት በረከት ላምራ፡፡

በርግጥም ፍጹም ልዩ

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በማይጠረጠር መልኩ ከፍጥረት ሁሉ ልዩ ናት፡፡ በድንድልና ላይ እናትነት፣ በክብረ ድንግልና ላይ ክብረ ወሊድ፣ በድንጋሌ ሥጋ ላይ ድንጋሌ ነፍስና ድንጋሌ ኅሊና የተሰጣት ከእርሷ በቀር ማንም የለም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ ምንም እንኳ ‹‹በልቧ ትጠብቀዉ ነበር››/ለቃ.2፣51/ ተብሎ እንደተጻፈዉ አትናገረዉ እንጂ ከፍጥረት ወገን እንደ እመቤታችን እርሱን ለማወቅ የተቻለዉ ፍጥረት የለም፡፡ ሊቁ ኦሪገን በሉቃስ ወንጌል ትርጓሜዉ ላይ እንደገለጸዉ ስለ አምላክ ፍጥረት ሊያዉቀዉ የሚቻለዉ የመጨረሻዉ የእዉቀት ደረጃ ላይ የደረሰችዉ እመቤታችን ብቻ ናት፡፡ እንደ እርሱ ትርጓሜ እመቤታችን ፍጡር ለፈጣሪዉ ክብር ሊጨምርለት እንደማይቻለዉ እያወቀች ‹‹ተዐብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር - ነፍሴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች›› ያለችዉ ፍጡር ሊረዳዉ የሚቻለዉ የመጨረሻዉ ደረጃ ላይ ደርሳ በዚያ መጠን ማመሰገኗን ስትገልጽልን ነዉ ይላል፡፡በርግጥም በዚህ መጠን ከርሷ በላይ ሊደርስ የሚቻለዉ እንዴት ሊኖር ይችላል? ይህ የሚያመለክተዉም ገና በምድር ሳለች ለፍጥረት የሚገባዉ ለዚህ የመጨረሻ ብቃት ከደረሰች ከዚህ ዓለም ከሔደች በኋላማ ይልቁንም እንዴት ያለዉን የተወደደዉንና ከፍጥረት ሁሉ የላቀዉን ምስጋና ታቀርብልን ይሆን? ምን ጥርጥር አለዉ? ልዩ የሆነዉን ልታቀርብ የሚቻላት ልዩ እናት፡፡

ለዚህም የበቃችዉ ራሷን ለሰዉ በሚቻለዉ ከፍተኛዉ መጠን እንደምትጠብቅ አስቀድሞ የሚያዉቅ ፈጣሪ እርሱም ደግሞ ጠበቃትና ከፍጥረት ወገን ልዩ ሆነች፡፡ ቀድም ብለን የተመለከትናቸዉ የቅዱስ ኤፍሬም ጥቅሶች የሚያረጋግጡልንም ይህንኑ ነዉ፡፡ ብርሂት የሆነች ዐይን ለሰዉነት መብራት የምትሆነዉ የፀሐይ ብርሃን ሲዋሐዳት እንደሆነዉ ሁሉ እርሷም በራሷ ብርሃነ ዐይን ንጽሐ ሥጋ ወኅሊና ላይ የብርሃን ጌታ ብርሃን የተባለ ጸጋዉን አሳድሮ ንጽሕናዋን ወደር የለሺ አደረገዉ፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ርብቃ ለይስሐቅ የታጨችበትን የሚናገረዉ አንቀጽ ላይ ‹‹ብላቴናይቱም መልክዋ እጅግ ያማረ፥ ወንድ የማያውቃት ድንግልም ነበረች››/ዘፍ. 24፣16/ የሚለዉን ሲተረጉም ‹ወንድ የማያዉቃት› የሚለዉን ለሥጋ ድንግልናዋ ከሰጠ በኋላ ‹ድንግልም ነበረች› ያለዉ ደግሞ ለመደጋገም ሳይሆን በኅሊናዋም ያልባከነች የተጠበቀች ነበረች ሲል ነዉ ይላል፡፡ ይሁን እንጂ እንደዚህ ያለችዉ ድንግል ርብቃ ድንገት(ለርሷ) ያገኘችዉና ማንነቱን እንኳ በዉል የማታዉቀዉ ሽማግሌ (የአብርሃም መልክተኛ) ቤተሰቦቿን በጠየቀዉ መሰረት ወላጆቿ ጠርተዉ ‹‹ከዚህ ሰው ጋር ትሄጃለሽን?›› ብለዉ በጠየቐት ጊዜ ሳታንገራግር ‹‹እሔዳለሁ›› አለች፤ መሰስ ብላም ተከተለችዉ፡፡/ዘፍ 24፣58/ እመቤታችን ግን የከበረ መልአክ ተገለጾ ሲያነጋግራት እንኳ የልቡናዋ በር ለወሊድ አልተንኳኳም፡፡ ለልማዱ ሴት ልጅ ‹‹ትጸንሻለሺ፣ ትወልጂያለሺ›› ቢሏት ምንም ብትመንን መልአክ ተግልጾ ከነገራት ‹‹ይህ እንዴት ይሆናል?›› ልትል አትችልም፤ እንዴት እንደሚሆንማ ጠንቅቃ ታዉቃለችና፡፡ እመቤታችን ከነዚህ ሁሉ ልዩ ስለሆነች ‹‹እፎኑ ይከዉነኒ ዝንቱ›› ስትል ፈጽሞ በታተመና እርሱን በሚያልፍ ኅሊና መልአኩን አስጨነቀችዉ፡፡ እርሱም‹‹ለእግዚአብሔር የሚሳነዉ ነገር የለም›› የምትል ጥቅስ አግኝቶ ፈተናዉን ተገላገለ፡፡ ሌላዉ ቀርቶ በዚህ ጥቅስ ተረትታ ብሥራቱን ስትቀበልም ‹‹ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ- እንዳልከዉ ይሁንልኝ›› ያለች አንተ እንዳልከዉ የአምላኬ ፈቃዱ ሆኖ እንበለ ዘርዕ፣ እንበለ ሩካቤ ከሆነና ተጸንሶ የሚወለደዉም እርሱ ከሆነ ይሁን ይደረግ አለቺ እንጂ ለሌላዉ ነገርማ ኅሊናዋ እንደታተመ ነዉ የቀረዉ፡፡‹‹ ልጄ ሆይ ስሚ፣ እዪ ጆሮሺንም አዘንብዪ፤ ወገንሺን የአባትሺንም ቤት እርሺ፣ ንጉሥ ዉበትሺን ወድዶአልና፤ እርሱ ጌታሺ ነዉና›› (መዝ 44÷12) ሲል አባቷ ዳዊት በትንቢት እንደተናገረዉ እርሷ ከሔዋናዊ ጠባይ ተለይታለችና፡፡ ሰሎሞንም‹‹ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሺ ዉብ ነዉ ፤ ነዉርም የለብሺም፤ ልቤን በፍቅር አሳበድሺዉ….›› ያለዉ ለዚህ ነበር፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ‹‹የታተመች ደብዳቤ›› ያላትም ለዚህ ነዉ/ኢሳ 28 ፤ 12/፡፡ ምክንያቱም ለልማዱ ደብዳቤ ከተጻፈ በኋላ ይታሸጋል፡፡ ስለ እርሷ የተነገረዉ ግን ከታተመ ወይም ከታሸገ በኋለ ተጻፈበት የሚል ነዉ፡፡ አብ በድንግልና አትሞ ሲያበቃ በዉስጧ አካላዊ ቃልን የጻፈባት ማንበብ የሚችሉም(እሥራኤል) ማንበብ የማይችሉም(አሕዛብ) እናነበዉ ዘንድ አንችልም ታትሟልና (በድንግልና በንጽሕና በክብር በምስጢር) አሉ ብሎ የተናገረላት ደብዳቤ እርሷ ናትና፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ጸጋ ለተሰጣቸዉ ሰዎች ብሥራት ሊያደርስ ሲመጣ ይህ የመጀመሪያዉ አልነበረም፤ ይሁን እንጂ ለዳንኤልም ሆነ ለጻድቁ ካህን ለዘካርያስ ለእርሷ እንዳደረገዉ ለእነርሱ መች አደረገ? እነርሱ እጅ ነሱት ሰገዱለት እንጂ እርሱ መቼ እጅ ነሳ ሰገደላቸዉ? ከዚህ በላይ ልዩ መሆን በእዉነት ወዴት ይገኛል፡፡

ፍጹም ልዩ መሆኗን ለማስረገጥ ያህል አንድ ነገር ብቻ ላክል፡፡ የጥንቶቹ የቤተክርስቲያን ሊቃዉንት ጌታ ለሐዋርያት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቛት ዘንድ የሰጠዉ ሁለት ጊዜ ነዉ ይላሉ፡፡ አንደኛዉ ብዙ ጊዜ ሲጠቀስ የምንሰማዉ ለቅዱስ ጴጥሮስ የተሰጠዉ ነዉ፡፡ይህም ‹‹በጎቼን አሰማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ እና ግልገሎቼን አሰማራ››/ዮሐ 21፣15-17/የሚለዉ ነዉ፡፡ ሁለተኛዉ ደግሞ ከዚህ ቀደም ብሎ በመስቀል ላይ የሰጠዉ ነዉ፤ በመስቀል ላይ ጌታ ለዮሐንስ ‹‹እነኋት እናትህ›› ሲል የሰጠዉ እርሷን ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንንም ነዉ ይላሉ፡፡ በነዚህ ሊቃዉንት ትርጓሜ መሠርት ሁለቱም ራሳቸዉን የቻሉ ምስጢራትን ይዘዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ሕጋዊ ስለነበር(በጋብቻ የተወሰነ ማለት ነዉ) የተሰጠዉም አደራ ይህንኑ የሚመለከትና በጎቹን እስከ ገላግልቶቻቸዉ(ምእመናን) የሚመለከት ነዉ፡፡ጌታ በወንጌል ‹‹በጎቼ ድምጼን ይለያሉ›› እንዳለዉ እነዚህ ድምጽ እንጂ ቃል መለየት የማይቻላቸዉ ምእመናን ናቸዉ፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ ግን ከዚህ ሁሉ በእጅጉ ይለያል፡፡ምክንያቱም እመቤታችን ራሷ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ብቻ ሳትሆን የፍጹማን ደናግልም ምሳሌ ናት፡፡ ስለዚህ ከደምጽ ያለፈ ቃላትን ምስጢራትን መለየት የሚቻላቸዉ ፍጹማንን የሚመለከተዉ አደራ የተሰጠዉ ለበቃዉ ብቻ ሳይሆን ለፍጹሙ ድንግል ለዮሐንስ ነዉ፡፡ ስለዚህ እመቤታችንን መግፋት ቤተክርስቲያንን መግፋት ነዉ፡፡ እርሷንም መቀበል የሚቻለዉ ዮሐንስን የመሰለ ንጹሕ ድንግል ነዉ፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ እንደሚለዉ ጌታ የሰጠዉ ድንግሊቱን ለድንግል፣ ድንግሉንም ለድንግል፤ ንጹሕንም ለንጹሕ ነዉ፡፡ መላእክት ሲጠብቐት ከኖሩ በኋላ መልአክ ለመሰለ ሰዉ ሰጣት እንጂ ለሌላ አልተሰጠችም፤ ሊቀበላት የሚቻለዉም የለም፡፡በተለይ ኦሪገን ይህንኑ በተረጎመበት አንቀጹ ስለ ቅዱሱ ብቃት ሲናገር ለእርሷም ‹‹እነሆ ልጅሽ›› አላት እንጂ ‹‹ልጅ ይሁንሽ›› አላላትም፤ ምክንያቱም ዮሐንስ በዚያ የመከራና የጭንቀት የፍርሃት ቀን በዕለተ ስቅለት ሳያፈራ ሳይሰቀቅ በእግረ መስቀሉ የተገኘዉ ቅዱስ ጳዉሎስ ‹‹እኔም አሁን ሕያዉ ሆኜ አልኖርም፤ ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል›› /ገላ 2፣20/ እንዳለዉ ዮሐንስ ራሱን ክዶ ስለነበር ለራሱ እየኖረ አይደለምና በእርሱ የሚኖረዉ ጌታ ነዉ፡፡ ‹‹አነሆ ልጅሽ›› ያላትም በእርሱ አድሬ ያለሁት እኔ ነኝ ማለቱ ስለሆነ ከእርሷ ሰዉ ከሆነ በኋላ ለማንም አልሰጣትም፤ በዮሐንስ አድሮ የተቀበላትም ራሱ ነዉ፤ ከዚያ በኋላ እርሷን ሊቀበል የሚቻለዉ የለምና ይላል፡፡ ስለዚህ አንድ ሰዉ እንኳንስ የእርሷን ነገር ለመንቀፍ ቀርቶ ለማመስገንም ትሰጠዉ ዘንድ ከፈለገ እንደ ዮሐንስ ራሱን በንጽሕና ይጠብቅ ፣ራሱንም ፈጽሞ ይካድ ባይ ነዉ፡፡

የአሁኖቹ ሰዎች እርሷን ባይቀበሉ፣ በእርሷ አማላጅነት ባያምኑ ለምን እንደነቃለን? እነዚህ በትንሽ ነገር እንኳ መታመን የማይቻላቸዉ የእርሷን ነገር ይረዱ ዘንድ ታላቁንና ሰማያዊዉን ምስጢር ማን አደራ ሊሰጣቸዉ ይችላል? አንዳንድ የዋኃን ደግሞ መሠርይ ተሐድሶዎች ስለ እርሷ የዘመሯቸዉን መዝሙር ተብየ ዘፈኖች እየተመለከቱ የታለላሉ፡፡ ይህ መናፍቃኑ ስለ እርሷ የሚሉትን መንገድ የተከተለ በእነርሱ ወዝ የታሸ ስለሆነ ተወዳጅ መሥዋዕት አይደለም፡፡ በኦሪት አንበሳዉ፣ ተኩላዉ፣ ቀበሮዉ፣ … የመሳሰለዉ አዉሬ የገደለዉን ሁሉ እንኳን ለመሥዋዕት ልናቀርበዉ ቀርቶ ልንበላዉም የተከለከለ ነዉ፡፡ ይህም ማለት በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱት አዉሬዎች የተባሉት (አጋንንት፣ ርኩሳን መናፍስት፣ መናፍቃን፣…. ደሙን ያፈሰሱትን ወይም በእነርሱ) የተሰዋዉን ሁሉ እንኳን ለእግዚኣብሔር ማቅረብ ለእኛም መንካት መርከስ ነዉ ማለት ነዉ፡፡ ‹አወሬ የቧጨረዉንም አትንካ› የሚል ንባብም ይገኛል፤ ይህ ሁሉ ከእነርሱ የተነካካዉን በዚህ ዓለም የዘፈንና የረከሰ መንፈስ የጎሰቆለዉን ምንም ለዐይንህ ቢያምርህ (በዘፈን ላደገ ሁሉ የእነርሱ የሚያምረዉ መሆኑ አይጠረጠርም) ፈጽመህ አትንካ ተብለን ታዘናልና መልከስከስ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ግጥሙ በኑፋቄ ዜማዉ በዘፈን ርኩሰት የተቧጨረ ርኩስ ነዉና፡፡እርሷ ቤተ ክርስቲያን ናት፤ የቤተክርስቲያናችንም ስጦታ ስለሆነች በእዉነት ልዩ ናትና ይህን በመሰለ መልኩ የተቧጨረዉን አናቀርብም፡፡

እንግዲህ ዛሬ ተወለደች የምንለዉ ይህችን ልዩ ድንግል ነዉ፡፡ስለዚህም የእርሷን በዓለ ልደት ማክበር ከዚህ ሁሉ በረከት መሳተፍ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር በእርሷ በኩል ለባሕርያችን ያደረገዉንም ክብር ማወቅና መቀበል ጭምር ነዉ፡፡

ከበዓሉ ምን እናገኛለን? የእርሷስ በዓል አልበዛምን?

አንዳንድ ሰዎች በእኛ ቤተክርስቲያን የጌታ በዓል አንሶ የእመቤታችን የበለጠ፤ እኛም ከርሱ ይልቃ ለርሷ የምናደላ የሚመስላቸዉ ቁጥራቸዉ በርከት ማለት ጀምሯል፡፡ ያለማወቅ ነዉና አይፈረድባቸዉም፡፡ ለነቀፋም የተሰለፉ ስለሆነ በ‹ምሰለ ፍቁር ወልዳ-ከተወደደዉ ልጇ ጋራ› በምንለዉ ሥዕል ዉስጥ እንኳ በሥዕሉ መጠን እየመሰላቸዉ ጌታ ያነሰ የሚመስላቸዉ ማስተዋል የራቃቸዉ ስለሆኑ በእነርሱ አንገረምም፡፡በቤተ ክርስቲያናችን ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ድረስ ከእናቱ ጋር መስደዱን፣ ከኅዳር ፲፬ ጀምሮ እስከ ልደቱ ይወርዳል ይወለዳል ሲሉ ትንቢት የተናገሩ የነቢያትን ጾም እየጾምን እርሱን እናስባለን፡፡ ከልደት እስከ ዐቢይ ጾም ድረስም በሥጋዌ፤ በአንድነት በሦስትነት መገለጡ አስተርእዮ እየተባለ ይታሰባል ይሰበካል፡፡ ከዚያም ዐቢይ ጾም ይገባል፤ ሁለንተናችን እርሱን በማሰብ ይሰበሰባል፤ ቃለ እግዚአበሔሩም ይህንኑ ያዘክራል፡፡ በትንሣኤዉም ሃምሳ ቀናትን እንደ አንድ ቀን እንደ ዕለተ ትንሣኤዉ በመቁጠር ትንሣኤዉን እንሰብካለን፡፡ ከዚህ በማሰከተልም ርዕደተ መንፍስቅዱስን በዓለ ጰራቅሊጦስን በጾም እናከብራለን፡፡በየወሩም በዓለ እግዚእ፣ መድኃኔዓለም፣ ኢየሱስ፣ አማኑኤል…. እያልን ከዘጠኙ ዓበይትና ከዘጠኙ ንዑሳን በዓላት በተጨማሪ በየአጥቢያቸዉ የሚታሰቡት ትዝ አይሏቸዉም፡፡ ሌላዉ ቀርቶ በየሳምንቱ ሁለት ቀናትን (ረቡዕ እና አርብ) በጾም ሁለት ቀናትን (ቀዳሚትንና እሑድን) በበዓል ለክርስቶስ መታሰቢያ የሰጠች ብቸኛ ቤተ ክርስቲያን የእኛይቱ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ብቻ መሆኗን አያስተዉሉም፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ የማርያም በዓል ከጌታ በዓል ይበልጣል ማለትን ምን ዓይነት አለማስተዋል ልንለዉ እንችላለን? ቢሆንስ በቅዱሳን በዓል ዋናዉ ተከባሪ ተመሰጋኝ ማን ሆነና ነዉ ይሄ ሁሉ ጩኸት? ስለዚህ በዚህም ስም አደረግነዉ በዚያ እግዚአብሔር በአከበራቸዉ ቅዱሳን ስም እስካደረግነዉ ድረስ በዓሉ ሁሉ የእግዚአብሔር ነዉ፡፡

የእመቤታችን በዓለ ልደትም በዚሁ መንፈስ የሚከበር በዓል ነዉ፡፡ነቢዩ ኢሳይያስ ቀደም ብሎ ‹‹ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ-ከእሴይ ሥር ወይም ግንድ በትር ትወጣለች››/ኢሳ 11፤6/ ብሎ ስለ ልደቷም ተናግሮላታል፡፡ ይህንንም ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በዉዳሴ ማርያም ዘቀዳሚት ድርሰቱ፤ ‹‹ በትረ ሃይማኖት ዘኢትጸንን ምስመኮሙ ለቅዱሳን-የቅዱሳን መደገፊያቸዉ ግያዝ የሱነማዊቷን ልጅ ከሞት ያስነሣባት ዘንድ ከነቢዩ ከኤልሳ ተቀብሎ እየተጠራጠረ እንደወሰዳት ያይደለሺ ጽነት ጥርጣሬ የሌለብሽ የሃይማኖት በትር አንቺ ነሽ›› ብሎ ተርጎሞልናል፡፡ አባ ጀሮምም ይህን የነቢዩን ትንቢት በትር ከግንዱ ላይ ተስተካክሎ የሚወጣ ግዳጂ ለመፈጸም የሚፈልግ ስለሆን የእመቤታችን ልዩ መሆን ያሳያል ይላል፡፡ በርግጥም ሊቃዉንቱ እንዳሉት ለቅዱሳን መደገፊያ ለአጋንንት ለመናፍቃን ደግሞ ማባረሪያ የሆነች በትር፤ ድንግል ማርያም፡፡ስለዚህ የእርሷን በዓል ማክበር ከዚህ ጥርጣሬ ከሌለዉ በረከት መሳተፍ ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ በአጠቃላይ የበዓላት ይልቁንም በክርስትና ጥቅማቸዉ ምንድን ነዉ የሚለዉን እንመልከትና እንፈጽም፡፡

በዓላትን በብዛት እንድናከብር ያዘዘን እግዚአብሔር ነዉ፡፡የምናከብራቸዉም ዝም ብለን አይደለም፡፡በተለይም በብሉይ ኪዳን በዓላት ብዙ የመሥዋዕት እንስሳትን ማቅረብና መሠዋት በጥብቅ የሚፈጸም ተእዛዝ ነበረ፡፡ የዚያ ሁሉ መሥዋዕትም ዓላማ ሥርየተ ኃጢኣትን ማስገኘት ነበር፡፡/ዘሌ ፲፯፣፲፩/ በአጭሩ በዓላቱን የማክበሩ ዓላማ ሥርየተ ኃጢኣትን ማሰገኘት ነዉ ማለት ነዉ፡፡በዚህ መሠረታዊ ምክንያት በእያንዳንዱ የኦሪት በዓል እጅግ ብዙ የመሥዋዕት እንስሳት ይቀርቡ ነበር፡፡በኦሪት በየዕለቱ ሁለት ሁለት ጠቦቶች፣ በየሰንበቱ ሁለት ተጨማሪ የበግ ጠቦቶች፣በየመባቻዉ ደግሞ ለየዕለቱ ከሚቀርበዉ በተጨማሪ ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አዉራ በግ፣ ሰባት የአንድ ዓመት የበግ ጠቦቶች፣ አንድ ፍየል ይቀርብ ነበር፡፡ የዓመታዊ በዓላት ደግሞ ከዚህ ሁሉ ይለያል፡፡ለምሳሌ የዳስ በዓሉን ብቻ ብንመለከት ከዕለቱ፣ ከሰንበቱና ከመባቻዉ እንዲሁም በፈቃድ ከሚቀርቡት በተጨማሪ 73 ወይፈኖች፣ 136 አዉራ በጎችና ጠቦቶች፣ 10 አዉራ ፍየሎች ይቀርቡ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ግን የእህሉን ቁርባንና ሌላዉን መሥዋዕት(ለኃጢኣት ፣ ለበደል፣….የሚባሉትን) ሳይጨምር ነዉ/ዘጸ ፳፱፣፴፰፣ ዘሌ ፳፬፣፭-፱፣ ዘኁ ፳፰፣፱-፲፭፣ዘኁ ፳፱/፡፡

‹‹ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና››/ዕብ 10፣1 / ተብሎ እንደተጻፈ እነዚህ ሁሉ ግን ምሳሌዎች ነበሩ፡፡ ሐዋርያዉ ቅዱስ ጳዉሎስ ‹‹ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም።ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በስራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።›› /ዕብ 5፣ 12-15/ እንዳለዉ ሊቃዉንቱ ለእኛ ወተት ወተቱን እየመገቡ ጠንካራዉን ምግብ አላቀረቡልንም ነበር፡፡ አሁን ግን እስኪ ይህን እንኳ እንሞክረዉ፡፡

በኦሪት እንደተጻፈዉ በፋሲካ የሚሠዋዉ ልዩ የደኅንነት መሥዋዕት በግ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነዉ፡፡‹‹በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር፥ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ። እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ›› /ዮሐ 1፣ 26/።ተብሎ ተጽፎአልና፡፡በሌሎቹ በዓላት የምናቀርባቸዉ ደግሞ ቀደም ብለን እንዳየነዉ ወይፈኑ፣ አዉራበጉ፣ ፍየሎቹ(ወንድም ሴትም ነዉ የሚቀርበዉ)፣ ሌላዉ ሁሉ የማን ምሳሌ ነዉ ማለታችን አይቀርም፡፡ ይህ ሁሉ የበዓል መሥዋዕት የቅዱሳን ምሳሌ ነዉ፡፡ ‹‹እንደ በጎች ሊበሉን ሰጠኸን፥ ወደ አሕዛብም በተንኸን›› /መዝ 44፣12/ ተብሎ ትንቢትም ተነግሮላቸዋልና።ጌታም በወንጌል ‹‹ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ።እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል›› /ማቴ 23፣35/ ሲል እንደተናገረዉ ቅዱሳን ለእምነታቸዉ መሥዋዕት ሆነዉ ቀርበዋል።ደማቸዉንም አንዱ እንደ ፍየል፣ ሌላዉ እንደ ወይፈን፣ ሌላዉም እንደ አዉራ በግ አፍስሰዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ የመሥዋዕት ዓይነቶች ለተለያየ የኃጢኣት ማስተሥረያ እነደነበሩት እነዚህም ደኅነትን ለመፈጸም ከተሰዋዉ በግ ከጌታ በኋላ ለምናምና ሁሉ ሥርየተ ኃጢኣትን እናገኝ ዘንድ የሚማልዱ ስለኛም ጭምር ደማቸዉን ያፈሰሱ ናቸዉ፡፡ ይሁን እንጂ የሌላዉ ጊዜ የመሥዋዕት እንስሳ የፋሲካዉን በግ ሊተካዉ እንደማይችልና የመሥዋዕቱም ዓይነት ፈጽሞ የተለያየ እንደ ሆነዉ ሁሉ የቅዱሳኑ መሥዋዕትነትና ሰማዕትነትም እንዲሁ የተለያየ መሆኑና የእነርሱም የእርሱን ሊተካ የማይችል መሆኑ ሊዘነጋ አይገባዉም፡፡እርሱ ኃጢኣትህ ተሠረየልህ(ሽ) እያለ ይቅር ሲል እነርሱ ግን የሚያስተሠርዩልን እየጸለዩ ነዉና፡፡ ከዚህ በመለስ ግን የጥንቶቹ ሊቃዉንት እንደተረጎሙልን የእነርሱ ተጋድሎና ሰማዕትነት የእኛ የሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች መሥዋዕቶች ናቸዉ፤ ስለእነርሱም ሥርየተ ኃጢኣትን እንቀበላለን፡፡ ሐዋርያዉ ቅዱስ ጳዉሎስም ‹‹በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል ››/ዕብ 4፣6/ ሲል የተናገረዉ ይህን የሚያረጋግጥልን ነዉ፡፡ ቀደም ብለን እንዳየነዉ የመሥዋዕቱ እንስሳት የበዙት ለእሥራኤል ለኃጢኣታቸዉ አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነዉ ሁሉ በሐዲስ ኪዳን ለምንኖር ለእኛም ብዙ ቅዱሳን መኖራቸዉ ይጠቅመናል፣ ኃጢኣታቸንም ያስተሠረይልናል፡፡ የመሥዋእቱ እንስሳት በሙሉ የተቆጠሩና የታወቁ እንደሆነዉ ሁሉ ቅዱሳኑም ምን ቢበዙም እንዲሁ የታወቁና የተቆጠሩ ናቸዉ፡፡

ዳዊት አባታችን ‹‹ዘይኌልቆሙ ለክዋክብት በምልኦሙ፣ ወይጼዉዖሙ ለኩሎሙ በበአስማቲሆሙ- ክዋክብትን በምልዓት ይቆጥራቸዋል፣ ሁሉንም በየስማቸዉም ይጠራቸዋል››/መዝ 146፣4/ ሲል እንደተናገረዉ ክዋክብት የተባሉ ቅዱሳን ሁሉ በእርሱ ዘንድ በባለሟልነት በቃል ኪዳን የታወቁ በመሥዋዕትነትም የተቆጠሩ ናቸዉ፡፡ ያ ሁሉ የ መሥዋዕት እንስሳ ፣ የጧቱና የሰርኩ፣ የሰንበቱና የመባቻዉ፣ የዓመት በዓላቱ፣ የየግለሰቡ የኃጢኣቱ፣ የበደሉ፣ የመንጻቱ፣…በዓይነት በዓይነት እንደሚታወቅ በእረሱም ዘንድ ተቀባይነት እነዳለዉ ሁሉ የየዕለቱ ቅዱሳንም እንዲሁ ይተወቃሉ፤ ጸሎታቸዉና ምልጃቸዉም በእርሱ ዘንድ የከበረ ነዉ፡፡ እመቤታችን ደግሞ ከነዚህ ሁሉ በግንባር ቀደምነት የምትጠራ ልዩ መሥዋዕታችን ናት፡፡በሁለተኛዉ ክፍለ ዘመን መጨረሻ የነበረዉ የሰረዴሱ መልይጦን/Melito of Sardis/ በፋሲካ መዝሙሩ ላይ እመቤታችንን የመሥዋዕቱን በግ የወለደችልን ንጽሕት ሴት በግ (fair ewe) ይላታል፡፡ ስለዚህ የእመቤታችን በዓለ ልደት ከብሉይ ኪዳን ሰዎች የተሻለ ሥርየተ ኃጢኣት የምናገኝበት ነዉና ከነዚያ በተሻለ በዓላችንን መንፈሳዊ አድርገን እናክብር፤ ከመንፈሳዊ በረከትም እንካፈል፡፡የደራሲዉንም ምስጋናና ምልጃ በመሰለ ምስጋና እንዲህ እንበላት፤‹‹ምንተኑ አዐስየኪ ዕሴተ፤በእንተ ኩሉ ዘገበርኪ ሊተ፤ማርያም ሠናይት ዘታፈቅሪ ምሕረተ፤ሶበሰ ተታአቀቢ ዘዚኣየ ኃጢኣተ፤ እምኢሐየዉኩ አሐተ ሰዓተ›› እያልን ለእርሷ በሚገባ ምስጋና እናመስግናት፡፡ ከዚህ የወጣ ሰዉ በመጀመሪያ እንደተመለከትነዉ ብርሂት ቀኝ ዐይኑን እንደገና እያሳወረ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡ እኛስ ለባሕርያችንን መመኪያ እርሷን የሰጠንን እግዚአብሔርን ‹‹ብርሂት የቀኝ ዐይን ድንግል ማርያምን ›› በዚህ ዕለት የሰጠኸን፣ ከዚህ ዓለም የድንቁርናና የኃጢኣት ጨለማም የገላገልከን ክብር ምስጋና ለአንተ ይሁን፤ አንተ ለመረጥካትና ላከበርካት ለእናትህም ምስጋና ይድረሳት እያልን አፋችንን ሞልተን እናመሰግናለን፡፡ ቀይ ዕንቁ እምነት ገንዘባቸዉ ያልተሰረቀባቸዉ ወይም በአዉሬዉ ዲያብሎስ ያልተቧጨሩት ሁሉ አብረዉን ያመሰግናሉ፡፡ ቀኝ ዐይናችን ሆይ ዛሬም በአንቺ ብርሃን እናያለንና እናመሰግንሻለን፡፡ እንኳን አንቺን አባትሺን አብርሃምን የሚባርኩት እንደሚባረኩ ልጂሽ አስቀድሞ በሙሴ በኩል በኦሪት ነግሮናልና፡፡

ወስብሓት ለእግዚአብሔር፡፡

Indirizzo

Str. S. Gaetano, 19
Bari
70122

Sito Web

Notifiche

Lasciando la tua email puoi essere il primo a sapere quando EOT Itali Bari Debre Haile St. george Church የኢጣሊ ደ/ኃ ቅ/ ጊዮርጊስ ቤ/ያን pubblica notizie e promozioni. Il tuo indirizzo email non verrà utilizzato per nessun altro scopo e potrai annullare l'iscrizione in qualsiasi momento.

Condividi

Digitare