09/09/2026
እንጃ ምን እንደሆንኩ ፣ አላውቅም ዘንድሮ፣
ዶሮ ዶሮ አይሸትም ፣ የእማምዬ ጓሮ፣
ጠጅ ጠጅ አይሸትም ፣ ያባብዬ ደጅ፣
እንደሀገር ሰክሬ ፣ ተንገዳገድኩ እንጅ።
መቆምና መውደቅ ፣ መሔድ እስኪያቅተኝ
ከእማምዬ ጓሮም
ካባብዬ ደጅም ፣ ባሩድ ነው ሚሸተኝ ።
እንጃ ምን እንደሆንኩ ፣ ምንድነው ችግሩ፣
ባሩድ ባሩድ ብቻ ፣ ሚሸተኝ ምድሩ፣
አፍንጫዬ ታሟል ፣ ወይ ታሟል ሀገሩ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ...
ላዲስ ዓመት ብስራት ፣ መድፍ ለመተኮስ፣
ሮኬት ለማፈንዳት ፣ ርችት ለመለኮስ፣
"እንዳትደነግጡ"
የሚል ሀሳብ ያለው ፣ መግለጫ ይወጣል።
የለመዱት ነገር ፣ ምን ያስደነግጣል?
በላይ በቀለ ወያ✍️