ኢየሱስ ክርስቶስ፡ የእምነታችን ራስና ፈጻሚ

  • Home
  • Ethiopia
  • Wolkite
  • ኢየሱስ ክርስቶስ፡ የእምነታችን ራስና ፈጻሚ

ኢየሱስ ክርስቶስ፡ የእምነታችን ራስና ፈጻሚ Look Unto Jesus Christ: The Author & Perfecter of Our Faith (Heb. 12:2)

09/08/2026

ወርቁ ለምን ይደበስ?
=========
ልጄ ሆይ፥ የጌታን ቃል አክብር፥
"ሕጌን አትርሳ፥ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ።"
ብሎ መልካም ነግሮሃልና፥ አዎን ምክሩን ጠብቅ።
ብዙ ዘመናትና ረጅም ዕድሜ ሰላምም ይጨምሩልሃልና።
ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤
በልብህ ጽላት ጻፋቸው፥ በዘመንህ ሁሉ ያከብሩሃልና፥
አዎን ልጄ፥ በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም፥
ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህና።
መልካም ነውና፥ በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥
በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፥ አላስተዋይ እንዳትሆን፥
ጌታ ራቅ ካለህ ነገር ራቅ፥ ቅረብ ወዳለህም ቅረብ፤
ከቃሉ በላይ አስተዋይ የሆንህ አይምሰልህ፤
ልቤን ያውቃልና እያልህ፥ ሰውነትህን እንዳታታልል፥
በመንገድህ ሁሉ፥ በያንዳንዷ አረማመድህ እርሱን እወቅ፥
እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃልና፥ ቃሉን በልብህ ጠብቅ።
በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን፤
ክርስትና የክርስቶስ ሕይወት ሲሆን፥
አንተ ሞተህ እርሱ በአንተ ሲኖርብህ፥
አቤት የክርስቶስ መዓዛ ጠረን፥ በሚሞት ሥጋህ፥
ሕይወቱ ሲገለጥ፥ በጨለማ ላሉት ሲገለጥ ብርሃን፥
ለኃጢአት ተሰቅለህ፥ ለጽድቅ ሕያው ስትሆን፥
ነበር የክርስትና ሕይወት፥ ባዕምሮና በጥበብ ተሞልተህ ጸጋውን።
መች እንዳሻህ ልትጓዝ፥ ልታደርገው ደስ ያለህን፥
ደቀ መዝሙሩ የመሆንህ፥ ልኬቱ መቼ እንዲያ ሊሆን?
በስውር ልትታገልበት፥ እንኳን ያልተፈቀደልህን፤
ወንድምህን እንዳያሰናክለው፥ ስትተው ጥቅምህን፥
ሕይወትህ ክርስቶስ፥ መሞትህ ጥቅምህ ሲሆን፥
የመድረኩ መልዐክ እንዳሉህ፥ በየኑሮህም በመንፈሱ ስትመላለስ፥
ሲታይብህ ዘወትር፥ አፍህን የሞላው ወሬው በኑሮህ።
ይህ ለሥጋህ ፈውስ፥ ለአጥንትህም ጠገን ይሆንሃልና፥
እግዚአብሔርን ፍራ፥ ከክፋትም ራቅ ተብለህ፥
ይልቁን አቅፈኸው ስትተኛ፥ መነቀፊያ የሚሆንብህ፥
ለስንቱ ይተርፍ ይሆን፥ ምርት በጠበቁበት ገለባ፥
ትርፍ በጠበቁበት፥ ኪሳራው እየሰባ፥
ለጥመት ቅኝት፥ ለምሬት ጥፍጥና እየተገባ፥
ምን እየተነበበብህ ይሆን፥ ስትወጣ ስትገባ?
እንደመሰልህና ደስ እንዳሰኘህ ከሆነ የመገኛህ ስፍራ፥
የበዛ ልምላሜ የበዛ ፍሬ እያለ ተትረፍርፎ ካምላክ ጋራ፥
በክረምቱ ስትጠወልግ፥ አለ የባሕርይ ተራ፥
የስንቱ ልብ አይቁሰልብህ፥ እያለ ጸጋው የበዛ።
ኧረ ወርቁ ለምን ይደበስ? እንቁስ ለምን ይርከስ?
ጥፍጥናው ለምን ይምረር፥ ንጣቱስ ለምን ይጥቈር?
ከማንነቱ ነው ወይ ወይስ ከፍሬው?
በግ ነው ወይ ወይስ ተኩላው በበግ ለምድ?
ግራ ገብቶት ግራ አጋቢ፥ ስንቱ በዘመናችን አለ?
ተብሎ እንዳይጻፍ፥ ተመለስ ልጄ ቀን ሳለ።
አንዳች ነፍስን ሳታሰናክል፥ ከወፍጮ ድንጋይ የሚብስብህ፤
ካንገትህ ሳያርፍ ካራ፥ ተመለስ ልጄ፥ ጌታ አለጊዜህ ሳያፈርስህ፥
ቅጣቱን አታቃልል፥ከዓለም ጋር እንዳይኮነንብህ፤
ሲገሥጽህ ሰምተህ ተመለስ፥ ለንሥኃ ፍሬ ለቅድስና የሚሰጥህን።
በግ ከሆንህማ በግ ሆነህ ኑር፥ ሳታሰድብ የመስቀሉን በግ።
ጸጋው ካልገባን፥ የመማር ጸጋ እያለልን ቁጭ ብለን፥
ከቃሉ ገበታ ተገኝተን፥ እንደ በጎቹ ድምጹን እየሰማን፥
ከቅዱሱ ቅባት እንደተቀበልን፥ ከእውነተኛው መምህራችን፥
የሚያነጻን ቅዱሱ ቃል እያለልን፥ ልንኳተን ወደ ቃርሚያው ፥
ለምንስ እንራወጥ? እዚህም 'ያም እያልን በባዶ ገለባው፥
ሆዳችንን ልንሞላ፥ እንክርዳድ ተዘርቶብን ከ'ሾሃማው አፈር።
እኛስ መጻተኞች ሆነን፥ እንዳሻን የማንኖር፥
ዜግነታችን በላይ በሰማይ፥ የአብ ቤት ሀገር፥
ተስፋችን ፍጹም ደስታችን፥ ከዚያ የሚመጣ መድኃኒታችን፥
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና፥ ለውጦ የሚያከብር ሥጋችንን፥
ይህን ተስፋ ያደርግን እኛ ፥ ክፉ እንዳይነካን፤
እርሱ ንጹሕ እንደሆነ የምናነጻበት ራሳችንን፤
የእግዜር ፈቃድ፥ ወደ'ኛ ለቅድስና እንደሆነ አውቀን።
ወገባችንን ታጥቀን፥ በልክ ኖረን፥
ከመንፈሱ ጋራ፥ ማራናታ ጌታ ሆይ ቶሎ ናልን፥
እያልን እንጮኻለን፥ በጸጋው ራሳችንን እየገዛን።

19/07/2026

📌🌅 "የክርስቶስ መከራና ድል በመዝሙር 22"
==================
"አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? እኔን ከማዳንና ከጩኸቴ ቃል ሩቅ ነህን?!" (መዝሙር 22፥1)

👀 የ1954 ዓ.ም የቀ. ኃ.ሥ. የአማርኛው ትርጉም ከላይ የተጠቀሰውን ጥቅስ በአራት ነጥብ ሲዘጋው፥ ሁሉም የእንግሊዝኛ ዕትሞች ግን በጥያቄ ምልከት ይቋጩታል። ትክክለኛውሥርዐተ ነጥብ ጥያቄ ምልክት ቢሆንም የጥቅሱን ስሜቱን ለመረዳት እንዲያግዘን ቃለ አጋኖ አክዬበታለሁ።

✍️ይህ መዝሙር በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ልዩ ስፍራ አለው። መዝሙር 22 በዳዊት ሕይወት ከተከሰተ ታሪካዊ ጥላነት ተነስቶ፣ የክርስቶስን መከራና ድል ፍጹም በሆነ መንገድ የሚስል ቀጥተኛ ትንቢታዊ መዝሙር (Messianic Psalm) ነው።

🔥 የዳዊት መከራ፦ ዳዊት ይህንን መዝሙር የጻፈው በሳኦልና በጠላቶቹ ክፉኛ በታደነበት፣ ተስፋ በቆረጠበትና ፍጹም በተገለለበት እጅግ አስጨናቂ ወቅት እንደነበር ይታመናል (በተለይ በቅዒላ [ኬሊያ] ወይም በዚፍ በረሃ በነበረበት ጊዜ — 1 ሳሙኤል 23 ያንብቡት)። ጠላቶቹ ከበውት፣ አምላኩ የጣለው መስሎት በተሰማው ጥልቅ ስነ-ልቦናዊና አካላዊ ስቃይ ውስጥ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር የጮኸበት ጸሎት ነው።

✍️ የታሪኩ ውስንነት እና ትንቢታዊነት፦ ዳዊት የገዛ ሕይወቱን መግለጫ አድርጎ ቢጀምረውም፣ በመዝሙሩ ውስጥ ያሉት ዝርዝር መከራዎች ግን በዳዊት ታሪክ ውስጥ ፈጽሞ አልተከሰቱም። ዳዊት እጆቹንና እግሮቹን አልተቸነከሩም፤ ልብሱንም ማንም ዕጣ አልተጣጣለበትም። ይህ የሚያሳየው፣ ዳዊት ከመንፈስ ቅዱስ መነሳሳት የተነሳ ከራሱ አልፎ በሥጋና በደም ከጉልበቱ ወደፊት ከ1000 ዓመታት በኋላ ስለሚመጣው መሲሕ እየተነበየ እንደነበር ነው።

✍️ እንደሐዋርያቱ እና በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት እንዳሉት እንደ ጥንቱ አብያተክርስቲያናት፥ በየሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን (በየእሁዱ) በጌታ ማዕድ ዙሪያ ስንሰበሰብ፣ በፊታችን ያለው ኅብስቱና ጽዋ ተራ ሥርዓት ሳይሆን የክርስቶስን ፍጹም መከራና ዘላለማዊ ድል፥ ከአብ ጋር የታረቅንበት፥ ሕያዋን የሆንንበት፥ አንድ አካል የሆንንበትን በሕያውነት የሚያሳዩን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምልክቶች ናቸው። ይህንን እውነት በብሉይ ኪዳን ትንቢታዊ ጥላ (በመዝሙር 22) መነጽር ሦስት ታላላቅ እውነቶችን እናሰላስል፦

1. የሕማማቱና የሞቱ ጥልቀት (መከራው)

✍️ጌታ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሆኖ ይህንን ጥቅስ በከፍተኛ ድምፅ ሲጮኽ (ማቴዎስ 27፥46 ይመልከቱ)፣ እኛን በእርሱ አምነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን ዘንድ የእኛን ኃጢአት በሙሉ በራሱ ላይ ተሸክሞ ስለነበር፣ ከአብ የደረሰበትን የሕግ ፍርድና መለኮታዊ መተውን እያሳየን ነበር። ይህ ክፍል፥ ክርስቶስ ስለ'ኛ ኃጢአት የሆነውን የመከራውንና የስቃዩን ጥልቀት የሚያሳይ ነው። ይህም የሚያሳየው ከኃጢአት የዳንንበት መዳን ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለው እና እንዴት ባለው ፍቅር እንደወደደን በሚጢጢዬ አዕምሮአችን ከመታወቅ የሚያልፈውን መለኮታዊውን ፍቅሩን ነው።

✍️ይህ ሲገባን በመዳናችን ጉዳይ ሳይገባን ዘው ብለን እንዳሻን አፍ ሞልተን በሚያታልሉ ቃላት ክሽን አድርገን ከማውራት ቃሉ እሚለንን በመንፈሱ አሜን በማለት በትሕትና በመቀበል የመስቀሉ ቃል የመዳናችን ኃይልና ጥበብ እንደሆነ በስብከት ሞኝነት አሜን እንላለን። በሞኝነት ስብከት ሳይሆን በቃሉ እውነት እናምናለን። እስቲ ወደ ሥቃዩና መከራው ልመልሳችሁ።

"እኔ ግን ትል ነኝ ሰውም አይደለሁም የሰው ማላገጫ በሕዝብም ዘንድ የተናቅሁ ነኝ። እንደ ውኃ ፈሰስሁ አጥንቶቼም ሁሉ ተለያዩ ልቤ እንደ ሰም ሆነ፥ በአንጀቴም መካከል ቀለጠ። ኃይሌ እንደ ገል ደረቀ፥ በጕሮሮዬም ምላሴ ተጣጋ፥ ወደ ሞትም አሸዋ አወረድኸኝ።" (መዝሙር 22፥6፣14-15)።

ይህ ቃል ክርስቶስ ምናባዊ ሳይሆን፣ ከድንግል ማርያም የነሳውን እውነተኛ ሰዋዊ ሥጋና ደም ይዞ (ዕብራውያን 2፥11-18፤ 1ኛ ዮሐ. 4፥1-3) በመስቀል ላይ የደረሰበትን እውነተኛ የአካል ሥቃይ በግልጽ ይስልልናል። መለኮቱና ሰውነቱ ሳይለያዩ በዚያ የመከራ ሰዓት አብረው ነበሩ፤ ለዚህም ነው የፈሰሰው ደም በዘላለም መንፈስ ስለቀረበ ዓለምን የማዳን ዘላለማዊ ኃይል ያለው።

2. ከሕማማት ወደ ትንሣኤ የተሻገረ ድል

ይህ መዝሙር በብዙ ሥቃይ፥ መከራና ጩኸት ቢጀምርም፣ በለቅሶና በሽንፈት አያበቃም። ኦ አሜን፥ ሃሌሉያ❗️ እግዚአብሔር አብ ልጁን፥ ቅዱሱን መበስበስን ያይ ዘንድ በመቃብር ውስጥ አልተወውምና፤ በታላቅ ኃይል ከሙታን አስነሳው። ይህንን ድል እና ምርኮ፥ ሕዝበ እስራኤል ብቻ ሳይሆን አሕዛብም ሁሉ የሚገቡበት እና የሚገዙበት መንግሥት፥ እርሷም በብሉይ ኪዳን ምሥጢር ሆና ብትቆይም በሐዲስ ኪዳን ለቅዱሳን የተገለጠችው፥ በሞቱ አዲስ ሰው ሆና የተገኘች፥ አካሉ ናት፥ አንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያኑ። እንደሆነች ድሉን በማወጅ እና እርሱ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን የሚፈሩ የሚመጣው ትውልድ ሁሉ ይህን ድልና ጽድቅ በምስጋና እንደሚያውጅ ምዕራፉን በምስራች ድል እና ውዳሴ ይደመድማል።

✍️ይህ እውነት ሲገባን ስለቤተክርስቲያን እንዳሻን ከማውራት በቃሉ እውነት፥ ለክርስቶስ ጌትነትና ራስነት ቦታውን ወደ መስጠት እና በመንፈሱ ምሪት ወደ መገዛቱ እንመጣለን። እስቲ ክፍሉን አሁንም እንቃኝ፥

"ከአንበሳ አፍ አድነኝ፥ ብቻነቴንም አንድ ቀንድ ካላቸው። ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ፥ በጉባኤም መካከል አመሰግንሃለሁ። ... በታላቅ ጉባኤ ምስጋናዬ ከአንተ ዘንድ ነው። እርሱን በሚፈሩት ፊት ስእለቴን እሰጣለሁ" (መዝሙር 22፥21-24) ጌታ ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ መጀመሪያ የተናገረው ይህንን ቃል ነበር፦ "ወደ ወንድሞቼ ሂጂና..." (ዮሐንስ 20፥17)። በመስቀሉ ሞትና ትንሣኤ ምክንያት አማኞች ሁሉ የአንዱ አካል ወንድማማቾችና ካህናት የሆኑበት እውነተኛ የቤተክርስቲያን ምስል የተገለጠበት ነው።

3. በማዕዱ ዙሪያ የምናረጋግጠው እውነት

🎯 የትኩረት ማእከላችን፦ በማዕዱ ዙሪያ ሰዋዊ መዋቅሮችና ድርጅቶች ሁሉ ይፈርሳሉ። አማኞች ሁሉ በእኩልነት፣ በትሕትናና በጸጥታ በማይታየው በክርስቶስ ራስነት ሥር ይሰበሰባሉ። በድርጅቶች ወይም በሐይማኖቶች ስም፥ ሳይሆን በጌታ ስም ዙሪያ ይሰበሰባሉ [ማቴ. 18፥20]። በሕልውናው መገኘት ይባረካሉ። እርሱንና ሥራውን ያስባሉ፥ በእርሱም አብን ያመሰግናሉ። ከአንድ ኅብስት እና ጽዋ በመጠጣት ፍጹም አንድነታቸውንም ይገልጡበታል።

የ✍️ መዳን ፍጹም ዋስትና፦ የተቆረሰውን ኅብስቱና የፈሰሰውን ጽዋ ስንመለከት፣ ድኅነታችን በራሳችን ታማኝነት ላይ ሳይሆን በክርስቶስ የዘላለም መሥዋዕትነት ላይ ፍጹም መሆኑን አውቀን ልባችን በሰማያዊ ሰላም ይሞላል። በመዳናችን ደስታ ልባችን ይረካል። እግዚአብሔርንም ያመሰግናል።

✍️ በመዳኑ ደስታ ልቡ በጌታ ያልተደሰተ ሰው በጣም ምስኪንና ወደነዱት ሁሉ የሚነጒድ፥ እረኛውን ያላወቀ በምድረበዳ እንዳለች ቅብዝብዝ በግ ነው። የሁልጊዜ መንፈሳዊ ሕጻን እና ራስ ወደሆነው ክርስቶስ ፍጹም ሙላት ልክ እንዲያድግ ዘንድ በውስጥ ሰውነቱ በመንፈሱ ከመታወቅ የሚያልፈውን የተወደደበትን የክርስቶስ ፍቅር ለማወቅ የማይበረታ አማኝ ነው።

✍️ ወንድሜ፥ የክርስትና ሕይወት የተጀመረውም የሚቀጥለውም በክርስቶስ ፍቅር ነው። ይህ ፍቅር በውስጣችን በመንፈሱ የሚነድ የሁልጊዜ ትኩስ ነው። ክርስቶስም፥ ያለ እኔ ምንም [ምንም ማለት ለእኔና ለአንተ አንዳች ሩም አይሰጠንም]። ልታደርጉ አትችሉምና፥ በፍቅሬ ኑሩ። አለ።

👉 ይህ እንዴት ያለ፥ ነፍስ አሳራፊ፥ የስጋ ትምክህትንና ትዕብትን የሚያሳፍር የክርስትና መርህ ነው። "በፍቅሬ ኑሩ።" ገና ኃጢአተኞች ሳለን፥ በጎልጎታ አናት ላይ በመስቀል ላይ፥ በተገለጠው ፍቅሩ፥ በማይለዋወጠው ዘላለማዊው ፍቅሩ፥ ይህንኑ ፍቅር ዘወትር ማሰብ፥ ልብ እርሱ ባለበት፥ እኛም ከእርሱ ጋር በክብር ወዳለንበት በሰማያዊው ሥፍራ ያሸፍታል።

👉 ለመረዳትና ለአምልኮ፦ ዛሬ የምንቆርሰው ኅብስት በመዝሙር 22 ላይ "አጥንቶቼ ሁሉ ተለዩ" የተባለለትን የክርስቶስን እውነተኛ ሰዋዊ መከራ የሚያሳይ ሲሆን፤ የምንጠጣው ጽዋ ደግሞ መከራውን በድል አጠናቆ "ተፈጸመ" ብሎ የሰጠንን የዘላለም ሕይወት ዋስትና የሚያረጋግጥልን የድል ምልክት ነው።

📣 የተባረከውን ተስፋችንን ማወጅና መጠበቅ፥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን እንናገራለን! አብረን ካንተ ጋር ፊትህን እያየን በሰማያዊው ቤታችን እንድንኖር ዘንድ ማራናታ! አሜን ጌታ ሆይ ቶሎ ና!🕊✨

🖕 የመንፈስ ቅዱስ ታላቅ አገልግሎት፦ የክርስቶስን ማንነት፣ መከራና ፍጹም ሥራ መግለጥ 💦የመንፈስ ቅዱስ ዋነኛና ማዕከላዊ አገልግሎት ለራሱ ክብር መፈለግ ሳይሆን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ማክበ...
10/07/2026

🖕 የመንፈስ ቅዱስ ታላቅ አገልግሎት፦ የክርስቶስን ማንነት፣ መከራና ፍጹም ሥራ መግለጥ 💦
የመንፈስ ቅዱስ ዋነኛና ማዕከላዊ አገልግሎት ለራሱ ክብር መፈለግ ሳይሆን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ማክበርና መግለጥ ነው። መንፈስ ቅዱስ እንደ መብራት ነው፤ መብራት ራሱን አያሳይም፣ ይልቁኑ በክፍሉ ውስጥ ያለውን ውድ ዕቃ ወይም ማንንት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ የክርስቶስን የከበረ ማንነትና የመስቀል ሥራ ለአማኞች ልብ ያበራል።
"እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና።" ዮሐ. 16፥14።
መንፈስ ቅዱስ የክርስቶስን ክብርና ሥራ በሦስት ታላላቅ ምሶሶዎች ከፍሎ ይተነትንልናል፦
1. የክርስቶስ ኢየሱስ ቅዱስና ክቡር ማንነት (The Person of Christ)
መንፈስ ቅዱስ በቃሉ በኩል ለሰው ልጅ አእምሮና ልብ የሚገልጠው የመጀመሪያው እውነት የክርስቶስን ፍጹም ማንነት ነው። መንፈስ ቅዱስ ክርስቶስ ተራ ነቢይ ወይም አስተማሪ እንዳልሆነ የእርሱን ሁለት ፍጹም ባሕርያት (Divine and Human natures) በግርማ ይገልጣል፦
ሀ) ፍጹም አምላክነቱ (His Deity)፦ እርሱ ከዘላለም የነበረ፣ ዓለማት በእርሱ የተፈጠሩበት፣ የእግዚአብሔር የባሕርዩ መልክና የክብሩ መንጸባረቅ መሆኑን ያሳየናል (ዕብ. 1፥3)። መንፈስ ቅዱስ በልባችን ሲያበራ ክርስቶስን “ጌታዬና አምላኬ” ብለን እንድንሰግድለት ያደርገናል (1ኛ ቆሮ. 12፥3)።
ለ) ፍጹም ሰውነቱ (His Holy Humanity)፦ መለኮትነቱን ሳይተው በቅድስና ሥጋን ለብሶ መምጣቱን ያሳያል። ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እኛን መስሎ (ዕብ. 4፥15)፣ በፍጹም ቅድስናና ታዛዥነት ምድር ላይ መኖሩንና በእርሱ ውስጥ ምንም ኃጢአት እንዳልተገኘበት (1ኛ ጴጥ. 2፥22) መንፈስ ቅዱስ ይመሰክራል።
2. የክርስቶስ መከራና ሥቃይ (The Sufferings of Christ)
በጌታ እራት (Breaking of Bread) ስነስርዓት ላይ በጥልቀት ማሰብና ማሰላሰል እንዳለብን፣ መንፈስ ቅዱስ አማኞችን ይዞ የሚሄደው ክርስቶስ ስለ እኛ ወደተቀበለው መከራና ሥቃይ ምሥጢር ውስጥ ነው። ይህ ሥቃይ እንዲሁ ታሪካዊ መከራ ሳይሆን ሁለት ታላላቅ ገጽታዎች ያሉት መለኮታዊ መሥዋዕትነት ነው፦
ሀ) ከሰው የመጣው ሥቃይ (The Sufferings from Men)
ጌታ በሰው እጅ የተተፋበት፣ የተገረፈበት፣ የሾህ አክሊል የደፋበትና ምስማር የተቸነከረበት ሥጋዊና ስነ-ልቦናዊ ሥቃይ ነው። ይህ የሰው ልጅ ክፋትና ጥላቻ ፍጻሜውን ያገኘበት መከራ ነበር።
ለ) ከእግዚአብሔር የመጣው መለኮታዊ ሥቃይ (The Sufferings from God)
ይህ እጅግ ጥልቁና ሰብአዊ አእምሮ ሊመረምረው የማይችለው ሥቃይ ነው። በመስቀል ላይ በነበሩት በእነዚያ የሦስት ሰዓት ጨለማዎች ውስጥ፣ ክርስቶስ የእኛን ኃጢአት ተሸክሞ የእግዚአብሔርን ፍጹም የጽድቅ ቁጣና ፍርድ ብቻውን ቀመሰ።
👉 አብ ፊቱን በጉ ሆኖ ስለ እኛ ኃጢአት በተሰቀለው ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ሲያዞር፥ ክርስቶስ በአስፈሪ ብቸኝነት ውስጥ ሆኖ “አምላኬ አምላኬ ስለ ምን ተውኸኝ?” ብሎ ጮኸ (ማቴ. 27፥46)። መንፈስ ቅዱስ ይህንን መለኮታዊ ሥቃይ ሲገልጥልን፣ የኃጢአታችንን አስፈሪነትና የጌታን የፍቅር ስፋት አይተን በፊቱ እንድንቀልጥ ያደርገናል።
3. የፈጸመው ፍጹም ሥራ (The Finished Work of Christ)
መንፈስ ቅዱስ በመስቀል ላይ የተከናወነውን ሥራ “የተፈጸመና ድጋሚ የማይደገም” (Finished Work) ፍጹም ሥራ አድርጎ ይገልጠዋል። ጌታ በመስቀል ላይ “ተፈጸመ” (Tetelestai) ብሎ በጮኸ ጊዜ (ዮሐ. 19፥30)፣ ለደኅንነታችን የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ መቶ በመቶ ተጠናቋል።
መንፈስ ቅዱስ የዚህን ሥራ ውጤት ለአማኙ ልብ እንዲህ ያበስራል፦
👉 ፍጹም ማስተስረያ (Propitiation)፦ የክርስቶስ ደም የእግዚአብሔርን የጽድቅ ቁጣ ሙሉ በሙሉ አብርዷል (ሮሜ 3፥25)። እግዚአብሔር በክርስቶስ ሥራ ፍጹም ረክቷል።
👉 ፍጹም ቤዛነት (Redemption)፦ ከኃጢአትና ከሕግ እርግማን ባርነት በክርስቶስ ክቡር ደም ተገዝተን ወጥተናል (ኤፌ. 1፥7)። ዕዳችን ሙሉ በሙሉ ተሰርዟል።
👉 ፍጹም መታረቅ (Reconciliation)፦ ጠላቶች የነበርን እኛ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም ሰላምን አግኝተናል (ሮሜ ፭:፩)።
📌 ማጠቃለያ ሐሳብ
የእግዚአብሔር ጸጋ ወደ እኛ የሚፈሰው በዚህ በመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት አማካኝነት ነው። መንፈስ ቅዱስ የክርስቶስን ክቡር ማንነት፣ መከራና የፈጸመውን ሥራ በቃሉ ብርሃንነት ወደ ልባችን ሲያመጣው፦
1. ኃጢአተኛው በገዛ ጽድቁ መመካቱን ትቶ በመስቀሉ ሥራ ላይ ብቻ ይጥላል።
2. አማኙ ከበደለኝነት ክስና ፍርሃት ነፃ ወጥቶ በጸጋው መረጋጋትና ዕረፍት ያገኛል።
3. ጉባኤው (የቅዱሳን ኅብረት) ክርስቶስን በማምለክና ለእርሱ በመኖር በፍቅርና በእውነት ይታነጻል።
መንፈስ ቅዱስ ዛሬም በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚሠራው ታላቅ ሥራ ይህ ነው፦ ልባችንን ከምድራዊው ነገር ነቅሎ፣ በመስቀል ላይ የሞተውንና ዛሬ በሰማይ የከበረውን ክርስቶስን እንድንመለከት እና ዳግም መምጣቱን እንድንናፍቅ ዓይናችንን ማብራት ነው!

❣️ “በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት።” — ኤፌሶን 1፥7ይህ ጥቅስ የክርስትና እምነት የልብ ምት ነው። ሐዋርያ...
07/07/2026

❣️

“በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት።” — ኤፌሶን 1፥7

ይህ ጥቅስ የክርስትና እምነት የልብ ምት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን አማኞች የጻፈው ይህ ቃል፣ የክርስቶስን ቤዛነት እጅግ ባማረ ሁኔታ ይገልጠዋል። ይህንን ጥቅስ በሦስት ቁልፍ ማዕዘኖች እንመልከተው፡

1. "በውድ ልጁም" (In the Beloved Son)

👉 የማንነት መሠረት፦ እግዚአብሔር ለአማኞች የሚያደርገው ማንኛውም በረከት የሚገኘው "በልጁ ውስጥ" ነው።
👉 የፍቅር ግንኙነት፦ ክርስቶስ የአብ "የተወደደ ልጁ" (The Beloved Son) ነው። አብ ልጁን ለዘላለም ይወደዋል። እኛም በልጁ በኩል ወደዚህ የዘላለም ፍቅር ኅብረት ውስጥ ተጠርተናል። በውድ ልጁ የእግዚአብሔርን ክብር አየን፤ ፍጹም በረከቱም "በልጁ" በኩል ፈሰሰልን። ኢየሱስ ወደ አብ እንደጸለየልን፥
“አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ። እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን እኔም በእነርሱ፥ ስምህን አስታወቅኋቸው አስታውቃቸውማለሁ።”— ዮሐ. 17፥24፣26።

2. "በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን" (Redemption through His Blood)

👉 ቤዛነት፦ ይህ ቃል በንግድ ቋንቋ "ከባርነት ነጻ ለማውጣት የሚከፈል ዋጋ" ማለት ነው። እኛ የኃጢአት ባሪያዎች ነበርን፤ ክርስቶስ ደግሞ ከእግዚአብሔር ቁጣ፥ ከኃጢአት እስራት እና ከሞት ባርነት፥ ነጻ ሊያወጣን ራሱን አሳልፎ በመስጠት ዕዳችንን ሁሉ ከፈለ። እኛን ቅዱሳንና ሕያዋን ሊያደርገን ዘንድ ቅዱሱ ደሙን አፈሰሰልን፥ እንደ እኛ ሆኖ ስለ እኛ ሞተልን።
👉 የደሙ ዋጋ፦ የክርስቶስ ደም የሕይወቱ መገለጫ ነው። ደሙ መፍሰሱ ማለት ህይወቱ ማለፉ ነው። ይህም የኃጢአትን ዋጋ ሙሉ በሙሉ የከፈለ መለኮታዊ "የክፍያ ማረጋገጫ" ነው። ደሙ ካልፈሰሰ፣ የነፍስ ቤዛነት የለም።

3. "የበደላችን ስርየት"

✍️ የስርየት ሙሉነት፦ ስርየት ማለት "መሰረዝ" ማለት ነው። የነበረብንን የኃጢአት ዕዳ ጽሕፈት ክርስቶስ በመስቀል ላይ አጥፍቶታል። በውድ ልጁ፥ በክቡር ደሙ ኃጢአታችን ተሰርዮአል፥ በደላችንም ተወግዶአል።
✍️ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት፦ ስርየታችን የተገኘው በእኛ መልካም ሥራ ሳይሆን፣ "እንደ ጸጋው ባለ ጠግነቱ" መጠን ነው። እግዚአብሔር ስርየትን የሰጠን በቁጠባ ሳይሆን፣ እንደባለጠግነቱ መጠን፥ በማይለካ የጸጋው ሀብት ነው።
ለምን ይህ ጥቅስ አስፈላጊ ነው?
1. የማንነት ዋስትና፦ እኛ ተቀባይነት ያገኘነው በራሳችን ብቁነት ሳይሆን፣ "በተወደደው ልጁ" ውስጥ በመሆናችን ነው። ይህም ማለት ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን ነው።
2. የሰላም ምንጭ፦ ኃጢአታችን ተሰርዞ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ከአብ ጋር እንደታረቅን ሰላማችንም እንደ ተመለሰልን እናውቃለን። የኃጢአታችን ስርየት የአገኘነው ማለት ያለፈውንም፣ የአሁኑንም፣ የወደፊቱንም የኃጢአት ዕዳ በሙሉ የሚያካትት ነው።
3. የአምልኮ መነሳሻ፦ ለዚህ ታላቅ ዋጋ (ለክርስቶስ ደም) ምላሻችን ምንድን ነው? በእውነትና በመንፈስ የሚሆን አምልኮ እና ምስጋና (ኤፌ 1፥6፣12፣14)።

ተወዳጆች ሆይ፥ የእግዚአብሔር ጸጋ "ባለጠጋ" ነው። በዚህ ምሽት፥ በጸሎታችን መሠዊያ ላይ፥ ከቤተሰባችን ጋር ወይም በግላችን ስንቀርብ፥ የቀኑ ስህተቶቻችንን ወይም የህሊና ወቀሳዎቻችንን ከአምላካችን የጸጋ ባለጠግነት ሊበልጡ እንደማይችሉ እንወቅ። በደሙ የተገዛው የኃጢአት ስርየት ዛሬም ሙሉ ነው። ደሙ ዛሬምም ትኩስ ነው፥ ለእኛ ያለው ፍቅሩ ያው ነው። በኃጢአታችን ላይ እንፍረድ፥ ማናቸውንም የዛሬ ክሶች በደሙ ፊት እንግለጥ፥ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል እግዚአብሔር አብን እናመስግነው። በጸጋው ባለጠግነት ተደግፈን እንተኛ።

እንግዲህ "እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት" የተሰጠኝን ይህንን ስርየት ስናስብ፣ በእግዚአብሔር ፊት ያለን ድፍረት እና በሕይወታችን ውስጥ የምናሳየው የአምልኮ መንፈስ ምን ይመስላል? ይህ ጥቅስ የክርስቶስን የቤዛነት ሥራ እንዴት በጥሩ ሁኔታ እንደሚያጠቃልለው እንመልከት። ይህንን ስናሰላስል፣ የክርስቶስን ክብር ይበልጥ እንረዳለን።

====  ሕሊናችን እና የኃጢአተኝነት/የበደለኝነት ስሜት ወይም ክስ =====በሰው ውስጥ ያለው ሕሊና እና አንድ ሰው ኃጢአት ሲሠራ የሚመጣው የበደለኝነት ስሜት ወይም ክስ ያላቸውን ግንኙነትና...
04/07/2026

==== ሕሊናችን እና የኃጢአተኝነት/የበደለኝነት ስሜት ወይም ክስ =====

በሰው ውስጥ ያለው ሕሊና እና አንድ ሰው ኃጢአት ሲሠራ የሚመጣው የበደለኝነት ስሜት ወይም ክስ ያላቸውን ግንኙነትና በጸጋው ውስጥ ያለውን መፍትሔ መረዳት ለሁለንተናዊ ሰው መንፈሳዊ ነፃነት እጅግ አስፈላጊ ነው።

ከክፉ ሕሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን ሰውነታችንንም በጥሩ ውኃ ታጥበን በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ እንቅረብ፤— የዕብራውያን መልዕክት 10፥22።
ስለዚህ እኔ ደግሞ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ። — የሐዋርያት ሥራ 24፥16።

፩. ሕሊና ምንድን ነው?

ሕሊና እግዚአብሔር በእያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ ያስቀመጠው የውስጥ ምስክር ወይም ዳኛ ነው። “ሕሊና” የሚለው ቃል መሠረታዊ ትርጉሙ “ከእውቀት ጋር አብሮ መሆን” ማለት ሲሆን፣ አንድን ድርጊት ከመፈጸማችን በፊት ወይም ከፈጸምን በኋላ ያ ነገር መልካም ወይም ክፉ መሆኑን በውስጣችን የሚመሰክር መለኮታዊ መሣሪያ ነው።

📍ሕግ በሌላቸው ዘንድ፦ ሕሊና የሙሴ ሕግ ባልደረሳቸው አሕዛብ ዘንድ እንኳ ሳይቀር የእግዚአብሔር ሕግ በልባቸው መጻፉን የሚያረጋግጥ ምስክር ነው (ሮሜ 2፥14-15)።
📍ሕሊና ሕግ አይደለም፦ ሕሊና ራሱ ሕግ አይደለም፤ ነገር ግን በተቀበለው እውቀት መሠረት የሚፈርድ ዳኛ ነው። የሰው ልጅ ዕውቀትና አካባቢው በተበላሸ ቁጥር ሕሊናው ሊደነዝዝ፣ ሊረክስ ወይም ‘ፓራላይዚድ’ እንደሆነ አካል አልያም በጋለ ብረት እንደተተኮሰ ሥጋ፥ ስሜተ ንቃቱን እስኪያጣ ድረስ “ሊደነዝዝ” ይችላል (1ኛ ጢሞ. 4፥2)።

፪. የኃጢአተኝነት/የበደለኝነት ስሜት እና ክስ (Guilt & Condemnation)

አንድ ሰው እግዚአብሔር ያስቀመጠውን የጽድቅ መሥፈርት ሲጥስ፣ ሕሊናው ወዲያውኑ በውስጡ ክስ መመሥረት ይጀምራል። ይህ ክስ በሰውየው ላይ የበደለኝነት ስሜት (Guilt) ያመጣል።

የበደለኝነት ስሜት ሁለት ገጽታዎች አሉት፦

ሀ. እውነተኛ የበደለኝነት ክስ

ይህ ሰውየው በእግዚአብሔር የጽድቅ ዙፋን ፊት እውነተኛ ባለዕዳና ፍርደኛ መሆኑን የሚያሳይ መለኮታዊ እውነታ ነው። ሕሊና ይህንን ፍርድ በሰውየው ልብ ውስጥ ያስተጋባል።

ለ. የስሜት መረበሽና ፍርሃት፥

የበደለኝነት ስሜት በሰውየው ነፍስና ሥጋ ላይ ጭንቀትን፣ ሰላም ማጣትንና ከእግዚአብሔር መሸሽን ያመጣል። ልክ አዳም በበደለ ጊዜ እግዚአብሔርን ፈርቶ በዛፎች መካከል እንደተሸሸገው (ዘፍ. 3፥8)፣ ዛሬም የበደለኝነት ክስ ያለበት ሰው ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ይፈራል።

፫. ሕሊና ከሕግና ከጸጋ አንጻር ሲታይ

ሀ. በሕግ ሥር ያለው ሕሊና፥

ሕግ ለሕሊና የሚሰጠው ዕውቀት “ኃጢአተኛ ነህ፣ ቅጣት ይገባሃል” የሚል ነው። ስለዚህ በሕግ ሥራ ወይም በሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚኖር ሰው ሕሊናው መቼም ቢሆን ፍጹም ሰላምና እረፍት አያገኝም። ምክንያቱም በብሉይ ኪዳን የነበሩት መሥዋዕቶች እንኳ ሳይቀሩ ኃጢአትን ለጊዜው ይሸፍኑ ነበር እንጂ ሕሊናን ፈጽመው ማጽዳት አይችሉም ነበር (ዕብ. 10፥1-2)። ስለዚህም ሕጉ በየዓመቱ ኃጢአትን ያስታውስ ነበር። ይህም በየዓመቱ የእንስሳን መሥዋዕት ይሻ ነበር።

ለ. በጸጋ ሥር ያለው ሕሊና፥

የእግዚአብሔር ጸጋ ለሰው ልጅ ሕሊና ፍጹም መፍትሔ ሰጥቷል። ክርስቶስ በመስቀል ላይ የከፈለው መሥዋዕትነት የእግዚአብሔርን ፍጹም የጽድቅ ቁጣ ስላስታገሰ፣ አሁን በክርስቶስ ያመነ ሰው ሕሊናው ከሞተ ሥራና ከበደለኝነት ክስ ሙሉ በሙሉ ስላነጻው እግዚአብሔርን በእውነትና በመንፈስ ለማምለክ በክርስቶስ በኩል ወደ አብ የመግባት ድፍረት አለው ።

❣️ የክርስቶስ ኢየሱስ የደሙ ኃይል፦

“የኮርማዎችና የፍየሎች ደም በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ ሥጋን ለማንጻት የሚቀድሱ ከሆኑ፥ ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን?” (ዕብ. 9፥13-14)።

✍️ በክርስቶስ ያገኘነው ፍጹም ነፃነት፦ አሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት “ኩነኔ (ክስ) የለባቸውም” (ሮሜ 8፥1)። ሰይጣን ወይም የገዛ ልባችን እንኳ ቢከስሰን፣ ክርስቶስ ስለ እኛ እንደሞተና እንደጸደቅን ጸጋው ያበስረናል። ይህም ነጻነት በደሙ ከኃጢአታችን እና ከሰይጣን ባርነት ፍጹም አርነት በመውጣት በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው የሕይወት መንፈስ ሕግ፥ ይኸውም በውስጣችን በሚኖረው መንፈሱ ለክርስቶ የጽድቅ ባሪያዎች የሆንንበት የአዲስ ፍጥረት ሕይወት ነው።

📌 ማጠቃለያ ማሳሰቢያ ለወንዶች ቡድን (Application)

👉 አማኝ ከዳነ በኋላም ቢሆን ኃጢአት ቢሠራ፣ ሕሊናው ይወቅሰዋል። ነገር ግን ይህ የወቃሽ ሕሊና ስሜት አማኙን ወደ ተስፋ መቁረጥና ከጌታ ወደ መሸሽ ሊወስደው አይገባም። ይልቁኑ በአብ ዘንድ ወዳለን ጠበቃችን፥ በድካማችን ወደሚራራልን እና በጸጋው ወደሚረዳን ሊቀ ካህናታችን ፊት፥ ምሕረትን ይቀበል ዘንድ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እግዚአብሔር ወዳዘጋጀው የይቅርታ ምንጭ በመቅረብ ኃጢአትን መናዘዝ ይገባዋል (ዕብ. 4፥16 እና 1ኛ ዮሐ. 1፥9 ፤ 2፥1)።

👉 የእግዚአብሔር ጸጋ የበደለኝነትን ስሜት አስወግዶ፣ በክርስቶስ ፍጹም ሥራ ላይ የተመሠረተ “በጎና ንጹሕ ሕሊና” (1ኛ ጴጥ. 3፥21) ይሰጠናል። ወንድሞች በዚህ ነፃነት ውስጥ ሲመላለሱ፣ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያለ ፍርሃት በቅድስና ለመኖር ብቁ ይሆናሉ።

👉 በዕብራውያን መቅደስ ጥላዎች ውስጥ የነበረው የውኃ መታጠብና የመሥዋዕት ደም መረጨት ፍጻሜውን ያገኘው በክርስቶስ ፍጹም በቂነት ላይ ነው። የሊቀ ካህናችን የኢየሱስ ደም ከከንቱ የሃይማኖት ወግና ከክፉ ሕሊና ፍርሃት ነጻ አውጥቶ ወደ ጸጋው ዙፋን በድፍረት እንድንቀርብ አድርጎናል። ይህ የእምነት መረዳት አማኝን ከሕግ እና ከሞት ቀንበር አውጥቶ በሰማያዊው አቋም ዕረፍትና በእግዚአብሔር ፍጹም ልጅነት መተማመን ውስጥ ያቆመዋል።

ወንድሞች ሆይ፣ በጸጋ የምንኖር አማኞች እንደመሆናችን መጠን፣ የጌታን ቃል በየዕለቱ በመስማትና በመታዘዝ ሕሊናችንን ንጹሕ አድርገን የመጠበቅ ኃላፊነት አለብን (የሐዋ. 24፥16)። ዕውቀታችን በጸጋው ቃል ሲታነጽ፣ ሕሊናችን ከድካምና ከሕጋዊነት ወጥቶ እውነተኛውን የክርስቶስን ነፃነት ማጣጣም ይጀምራል።

👉 ደሙ የዋጃት ነፍስ በምድር ምልልሷ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ነውር የሌለባት ሕሊና ይዛ ለመኖር በቅድስና ትተጋለች። አማኝ በምንም ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ፣ በጸጋው ተደግፎ በየዕለቱ በጽድቅ ጎዳና ላይ ጉልበቱን ለመልካም ሥራ ያውላል። ይህን ፍጹም ልብ ያገኘው ሰው በክርስቶስ መንፈስ ሙላት፥ የጌታ ፈቃድ እውቀት ምን እንዲሆን በማወቅ በየሥፍራው ካሉ ቅዱሳንና እያንዳንዱ ሰው በቤቱ በጣሪያው ስር እንደ ተራራ ላይ ከተማ እያበራ፣ ለአምላኩ ሁልጊዜ ውዳሴንና ምስጋናን እያቀረበ፥ በጠማማው ትውልድ መካከል በቃሉና በኑሮው ምልክትና ምስክር ሆኖ ይኖራል።

===== ኃጢአት ምንድን ነው?===== “ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያሳያል።” (ሮሜ 5፥8)። በመጽሐፍ ቅዱስ እው...
30/06/2026

===== ኃጢአት ምንድን ነው?=====
“ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያሳያል።” (ሮሜ 5፥8)።

በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ኃጢአት እንዲሁ ማኅበረሰባዊ ስህተት ወይም ተራ የሥነ-ምግባር ጉድለት አይደለም። ኃጢአት በዋናነት ከእግዚአብሔር ፍጹም ቅድስናና ፈቃድ ማፈንገጥ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ኃጢአትን በተለያዩ መንገዶችና ቃላት ይገልጸዋል፤ ዋና ዋናዎቹ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉሞች የሚከተሉት ናቸው፦

1️⃣ ኃጢአት መለኮታዊውን ግብ መሳት ነው (Missing the Mark)

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ቋንቋ (በግሪክ) ኃጢአት የሚለው ቃል “ሐማርቲያ” (ἁμαρτία) ይባላል። ትርጉሙም “ግብን ወይም ዓላማን መሳት” ማለት ነው።
✔️ እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው ለእርሱ ክብርና ከእርሱ ጋር በኅብረት እንዲኖር ነው። ሰው ግን ከዚህ መለኮታዊ ዓላማና የእግዚአብሔር የጽድቅ መሥፈርት ጎደለ።
❌ አንድ ቀስት ወይም ጦር ወርዋሪ ወደ ዒላማው ወርውሮ ዒላማውን ሳይመታ ሲቀር “ግብ ሳተ” እንደሚባለው፣ የሰው ልጅም ሁሉ የእግዚአብሔርን ፍጹም የጽድቅ መሥፈርት መምታት አልቻለም። ስለዚህም የተፈጠረለት ዓላማ የእግዚአብሔር ክብር ጎድሎታል። ቃሉ እንዲህ እንደሚል፥
"ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል..." — ሮሜ 3፥23።

2️⃣ ኃጢአት ሕግን መተላለፍ ወይም ዓመጽ ነው (Lawlessness or Rebellion)

ኃጢአት ማለት እግዚአብሔር ያስቀመጠውን መለኮታዊ ድንበርና ሕግ ሆን ብሎ መጣስ፣ በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ስልጣን ላይ ማመፅና “በራሴ መንገድ እመራለሁ” ማለት ነው። ይህም አንተ ጌታዬ አይደለህም ማለት ነው።
"ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ ዓመፅን ደግሞ ያደርጋል፥ ኃጢአትም ዓመፅ ነው።" — 1ኛ ዮሐ. 3፥4።

3️⃣ ኃጢአት በኢየሱስ አለማመን ነው (Unbelief)

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስ ወደ ዓለም ሲመጣ ሰዎችን ስለ ምን እንደሚወቅስ ሲናገር፣ ትልቁና መሠረታዊው ኃጢአት በእርሱ አለማመን መሆኑን ገልጿል። እግዚአብሔር ልጁን ልኮ ሳለ፣ የሰጠውን የእውነት ምስክርነት አለመቀበልና አለማመን ኃጢአት ነው። "...ስለ ኃጢአት፥ በእኔ ስለማያምኑ ነው..." — ዮሐ. 16፥9።
4️⃣ መልካሙን አውቆ አለማድረግ

ኃጢአት ክፉ ነገርን መፈጸም ብቻ አይደለም፤ ሊደረግ የሚገባውንና እግዚአብሔር የሚፈልገውን መልካም ነገር አውቆ አለማድረግም ራሱ የአለመታዘዝ ኃጢአት ነው።
"እንግዲህ መልካም ለማድረግ አውቆ ለማያደርገው ኃጢአት ነው።" — ያዕቆብ 4፥17።

📌 መጽሐፍ ቅዱስ ኃጢአትን የሚያቀርብበት ሁለት ገጽታዎች፥

በሰው ሕይወት ውስጥ ያለውን ኃጢአት በሁለት መልኩ ወይም ዐይነት ይስተዋላል፦
🔤. የኃጢአት ተፈጥሮ (የኃጢአተኝነት ሥር)፦ ከአዳም የወረስነውና በውስጣችን ያለው ክፉ የኃጢአት ዝንባሌ (የሥጋ ፈቃድ) ነው። ይህ የኃጢአት ሥር ነው።
🔤. የኃጢአት ድርጊቶች (የኃጢአቶች ፍሬ ወይም በደል)፦ ከውስጣችን ካለው ክፉ ተፈጥሮ የሚወጡትና በተግባር የምንፈጽማቸው ክፉ ሥራዎች (ውሸት፣ ስርቆት፣ ቅናት፣ ምንዝርና...) ናቸው። እነዚህ የኃጢአት ፍሬዎች ናቸው።

⚫️🦞 ኃጢዕ (The Sinner፥ ባለቤቱ ወይም ሰው ያለበት ሁኔታው)

“ኃጢዕ” (በግዕዝ ቃሉ ሲሆን) ማለት ኃጢአተኛ ማለት ሲሆን፣ የኃጢአት ባሕርይ የተቆጣጠረውንና በኃጢአት ተግባር ውስጥ የሚኖረውን ሰውየውን (The Person/The Subject of the sin and sins) ወይም የሰውን ፍጹም የረከሰና የተበላሸ መንፈሳዊ ሁኔታ ያሳያል።

ኃጢዕ ማለት ከእግዚአብሔር የጽድቅ መሥፈርት የራቀ፣ በበደሉ ምክንያት የሞተና የእግዚአብሔር ቁጣ ያለበት ምስኪን ኃጢአተኛ ሰው ነው። ከሰው ውድቀት በኋላ፥ ከአዳም ዘር የሚወለደው ሕጻን ልጅ እንኳ ቢሆን በዓመጻ ተፀንሶ በኃጢአት እንደሚወለድ፥ የኃጢአት መዘዝ ምን ያህል የሰውን ልጅ እንደበከለው ንጉሡ ዳዊት (መዝ. 51፥5) ያሳየናል።

የጸጋው መፍትሔ፦ እግዚአብሔር አንዳች ስንኳ ጻድቅ ሰው እንደሌለ አየ፥ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ ተደነቀም ስለዚህ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት፥ ጽድቁም አገዘው። አንዲያ ልጁን ወደዚህ ምድር የላከው እኛን ኃጢአተኞችን እንዲሁ በመውደድ ነው። አንዲያ ልጁም፥ ክርስቶስ ኢየሱስ ገና ኃጢአተኞች ሳለን፥ ስለ “ኃጢአተኞች” በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በመሞት የአብን ፍቅር በአደባባይ ገለጠው (ኢሳ. 59፥16፤ ሮሜ 5፥8)።

💡 ታላቁ የምሥራች (The Remedy)

🔊 የሰው ልጅ በዚህ የኃጢአት በሽታና ፍርደኝነት ውስጥ ተዘፍቆ ሙት ስለሆነ፣ ራሱን ማዳን ፈጽሞ አልቻለም። ለዚህ ነው የእግዚአብሔር ጸጋ ያስፈለገው።

🔔ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሲሞት የኃጢአታችንን ፍሬዎች (ድርጊቶቻችንን ወይም በደሎቻችንን) ይቅር ለማለት ብቻ ሳይሆን፣ የኃጢአትን ሥር (የድሮውን ማንነታችንን) አብሮ ሰቅሎልናል (ሮሜ 6፥6፤ (፩ ዮሐ. 1፥7)።)። በክርስቶስ ፍጹም ሥራ ያመነ ሰው በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው በሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአት ኩነኔና ኃይል፥ ከሞት ሕግ ነፃ ወጥቷል (ሮሜ 8፥2)!
📣 የእግዚአብሔር የታመነ ጸጋ፥ "እናንተ ደካሞች ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።" ብሎ በተጣራው በክርስቶስ ኢየሱስ ተገልጦ፥ እነዚህን ሦስቱንም ችግሮችበአንድ ላይ ፈውሷል፦ ኃጢአቶቻችንን በደሙ አጥቧል፣ ከኃጢአት አገዛዝ ነፃ አውጥቶናል፣ እኛን ኃጢዓኑን ደግሞ የእግዚአብሔር ቅዱሳንና ልጆች አድርጎናል።
በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን።

======   ====== 👉 እግዚአብሔር ሕግን የሰጠበትን መለኮታዊ ዓላማ በብሉይና በአዲስ ኪዳን ብርሃን በትክክል መረዳት፣ ከሕጋዊነት አደጋ ለመጠበቅ፥ በተገለጠው መለኮታዊው ፍቅር እንድንኖ...
29/06/2026

====== ======
👉 እግዚአብሔር ሕግን የሰጠበትን መለኮታዊ ዓላማ በብሉይና በአዲስ ኪዳን ብርሃን በትክክል መረዳት፣ ከሕጋዊነት አደጋ ለመጠበቅ፥ በተገለጠው መለኮታዊው ፍቅር እንድንኖርበትና እንድናድግበት ዘንድ በእምነትና በትሕትና በጸጋ ላይ ጸጋ እንዲበዛልን፥ እና የጸጋውን ታላቅነት ለማድነቅ ቁልፍ መሠረት ነው።
1. በብሉይ ኪዳን ሕግ የተሰጠበት ዓላማ
በብሉይ ኪዳን ሕግ (በተለይም የሙሴ ሕግ) የተሰጠው ሰውን ለማዳን ሳይሆን የሚከተሉትን መለኮታዊ ዓላማዎች እንዲፈጽም ነበር፦
✍️ የእግዚአብሔርን ፍጹም ቅድስናንና የጽድቁን ልኬት ለመግለጥ፦ ሕጉ እግዚአብሔር ምን ያህል ቅዱስና ጻድቅ እንደሆነ፣ ከሕዝቡም የሚጠብቀው የጽድቅ ልኬት ምን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ ያሳያል (ዘሌ. 19፥2)።
✍️ የሰውን አቅም ማጣት ማሳየት፦ ሰው በራሱ ጥረት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት እንደማይችልና ሕጉ ኃጢአትም በትእዛዝ ምክንያት “ያለ ልክ ኃጢአተኛ ይሆን” ዘንድ ያረጋግጣል (ሮሜ 7፥13)።
✍️የእግዚአብሔርን ልዩ ሕዝብ (እስራኤልን) ከሌላው ዓለም ለመለየት፦ እስራኤላውያን መሲሑ (ክርስቶስ) እስኪመጣ ድረስ በሥርዓትና በጥንቃቄ፥ ከአሕዛብ ጣኦታትና ርኩሰት ተለይተውና፥ ተጠብቀው የሚኖሩበት የአጥር ወይም የቅጥር ሚና ነበረው (ገላ. 3፥23-24፤ ኤፌ. 2፥14)።
2. በአዲስ ኪዳን ሕግ የተሰጠበት ዓላማ (በክርስቶስ ብርሃን)
በአዲስ ኪዳን መገለጥ ውስጥ፣ ቅዱስና ጻድቅ የሆነው ሕጉ ቀደም ሲል የነበረውን አገልግሎት አጠናቆ፥ መንፈስ ቅዱስ ዓለምን ስለ ኃጢአት፥ ስለ ፍርድ እና ስለጽድቅ ሲወቅስ በክርስቶስ የሚያምኑቱን በጸጋው ወደሚጸድቁበትና ወደ ሚድኑበት እውነት፥ ታማኝ አገልጋይ ወይም ሞግዚት በመሆን እንደሚከተለው ይገለጣል፦
✍️ ኃጢአትን የማሳወቅ (ምርመራ)፦ በአዲስ ኪዳን ሕግ የሚሠራው ልክ እንደ ኤክስሬይ (X-ray) ወይም መስተዋት ነው። በሰው ልብ ውስጥ ተሸሽጎ ያለውን ክፉ ኃጢአት አውጥቶ ያሳያል፤ “ኃጢአት በሕግ በኩል ይታወቃልና” (ሮሜ 3፥20)።
✍️ ሰውን ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚት መሆን፦ ሕጉ ሰውን ሙሉ በሙሉ አቅም ያሳጣዋል፣ ይኮንነዋል፣ ይፈርጃል። ሰውየው በራሱ ተስፋ ሲቆርጥ “ከዚህ ለሞት ከተሰጠ ሰውነት የሚያድነኝ ማን ነው?” ብሎ ወደ ክርስቶስ ጸጋ እንዲሮጥ ያደርገዋል። ስለዚህ ሕጉ ወደ ክርስቶስ የሚመራ “ሞግዚታችን” ሆኗል (ገላ. 3፥24)።
✍️የክርስቶስን ፍጹም ታዛዥነት ማሳያ መሆን፦ ክርስቶስ ሕጉን ለመሻር ሳይሆን ለመፈጸም መጣ (ማቴ. 5፥17)። እኛ ልንፈጽመው ያልቻልነውን ሕግ እርሱ ሙሉ በሙሉ ፈጽሞ የሕግ ፍጻሜ ሆነልን (ሮሜ 10፥4)።
3. የእግዚአብሔር ጸጋ በብሉይ ኪዳን እና ከሕግ ጋር የነበረው ግንኙነት
እግዚአብሔር በባሕርዩ የማይለወጥ በመሆኑ፣ ጸጋው በአዲስ ኪዳን ብቻ ሳይሆን በብሉይ ኪዳንም ጎልቶ ይታይ ነበር፦
✍️ በመጀመሪያው ውድቀት (በኤደን)፦ አዳምና ሔዋን እርሱን በበደሉ ጊዜ የገዛ እራሳቸውን ዕራቁትነት በበለስ ቅጠል ለመሸፈን ሞከሩ (ይህ የሰው ጥረት ወይም የሕግ ሥርዓት ምሳሌ ነው)። እግዚአብሔር ግን በቁርበት ‘ርቃናቸውን ሸፈናቸው (ዘፍ. 3፥21)። ይህ ደም ሳይፈስ ስርየት እንደሌለና የርቃናችን መሸፈኛ ከእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ እንደሚገኝ የሚያሳይ የመጀመሪያው የጸጋ ጥላ ነው።
✍️ በኖኅና በአብርሃም ሕይወት፦ ኖኅ በፍርድ መካከል “በእግዚአብሔር ፊት ጸጋን ወይም ሞገስን አገኘ” (ዘፍ. 6፥8)፤ አብርሃምም ጣዖት ያመልክ በነበረበት ምድር ሳለ (ኢያሱ 24፥2) ያለምንም መልካም ሥራ በሉዓላዊ ጸጋ ተጠርቶ በእምነት ጸደቀ (ዘፍ. 15፥6፤ ሮሜ 4፥3)።
✍️በመሥዋዕቱ ሥርዓትና በታቦቱ መክደኛ፦ ሕጉ “ኃጢአት የሠራች ነፍስ ትሞታለች” ሲል፣ ጸጋው ደግሞ በታቦቱ መክደኛ (Mercy Seat) ላይ በሚረጨው በኃጢአተኛው የመተኪያ እንስሳ ደም ኃጢአቱን ይሸፍን ነበር (ዘሌ. 1፥4፤ 16፥14)። የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን የዳኑት ወደፊት ሊመጣ ባለው በክርስቶስ መሥዋዕትነትና በጸጋው ላይ እምነት በመጣል ነው (ሮሜ 4፥5-8)።አሁን ግን፥ በጥላና በምሳሌ ተሸፍኖ የነበረው ጸጋ፣ በአዲስ ኪዳን በአካሉ በኢየሱስ ክርስቶስ በግልጽና በሙላት ተሰጥቶናል (ዮሐ. 1፥16-17)።
4. በሕግ እና በጸጋ ስር ያለ ሕይወት ልዩነት
🔗 ሕግ (የብሉይ ኪዳን መሠረት)፦ “ይህንን አድርግ” ይላል ➔ ፍጻሜው ኩነኔና ሞት ነው (2ኛ ቆሮ. 3፥7)። ኃጢአትን ይከለክላል እንጂ የማሸነፍ ኃይል አይሰጥም።
🔐🗝 ጸጋ (የአዲስ ኪዳን እውነት)፦ “ክርስቶስ ሁሉን አድርጎአል” ይላል ➔ ፍጻሜው ጽድቅ፣ ሰላምና የዘላለም ሕይወት ነው (ሮሜ 6፥23)። ጸጋ ኃጢአትን ይቅር ከማለት ባለፈ፣ ኃጢአትን እንድንክድና በቅድስና እንድንኖር በውስጣችን የሚሠራ መለኮታዊ ኃይል ነው።
📌 የትምህርቱ ጭብጥ መልዕክት
የተወደዳችሁ ወንድሞችና እህቶች ሆይ! ከዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት የምንረዳው፥ ሕጉ መሲሑ እስኪመጣ ድረስ እስራኤልን ለይቶ ያቆየ ጊዜያዊ ቅጥርና ሞግዚት ነበር። ክርስቶስ መጥቶ በመስቀል ላይ ያንን ከፋፋይ አጥር (የሕግን ሥርዓት) ስለሻረው ግድግዳው ፈርሷል፤ ሕጉም አብቅቷል (ገላ. 3፥19፤ ኤፌ. 2፥14-15)። ዛሬ ዳግመኛ ወደዚያ የሕግና የባርነት አጥር ውስጥ ልንመለስ፥ የጸጋንም መንፈስ ልናክፋፋ አይገባም።
1. በጸጋው ነፃነት በሕይወት መንፈስ ሕግ መኖር፦ አሁን ከጸጋ በታች ነን እንጂ ከሕግ በታች አይደለንም። በሥጋ ለኃጢአት ሞተን በመንፈስ ለጽድቅ የምንታዘዝ ባሪያዎች በመሆናችን ጽድቅ እንጂ ኃጢአት አይገዛንም (ሮሜ 6፥14-16)።
2. በአዲስ ኪዳን አንድነት መመላለስ፦ ከፋፋዩ አጥር ስለፈረሰ፣ ዛሬ በአጥቢያ ጉባኤ መካከል ምንም ዓይነት የዘር፣ የፆታ ወይም የባህል ክፍፍል ሳይኖረን በክርስቶስ አንድ ሆነን በእውነተኛ ሰማያዊ ፍቅርና አንድነት (Fellowship) እንመላለስ (ገላ. 3፥28)።
ቅጥሩን አፍርሶ በደሙ ወደ አባቱ ቤት ያስገባንና በጸጋው ያቆመን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስሙ ለዘላለም የተባረከ ይሁን! ማራናታ!

27/06/2026

!
በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፥ መንገዱም ትልቅ ነውና፥ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።ማቴ. 7፥13-14።
ይህ የጌታችንና የመድኃኒታችን የክርስቶስ ኢየሱስ ግሩም ትምህርት የጥፋቱ ሰፊ መንገድ እና የሕይወቱ ጠባብ ደጅ በፊታችን ያቀርባል።

1. ሰፊው ደጅና ትልቁ መንገድ፦ የብዙኃኑ ፍሰት

"ወዮ! ወዳጆቼ ሆይ፣ ወደ ገሃነም የሚወስደው መንገድ ምንኛ የተመቸና ሰፊ ነው! ለመሆኑ ያንን መንገድ ለመከተል ምን የሚያስፈልግ ይመስላችኋል? ምንም! ዝም ብላችሁ በባሕርይችሁ ፍሰት መሄድ ብቻ ይበቃል። ወደ ጥፋት ለመውረድ ታላቅ ጥረት አያስፈልግም፤ ዓለም በምትነፍስበት አቅጣጫ መነዳት፣ የሥጋን ፈቃድ መከተል፣ እና ከብዙኃኑ ጋር አብሮ መጓዝ ብቻውን በቂ ነው።

የሕይወትን ቃል ሰምቶ ያላመነ ነፍስ፥ በነፍሱም የሕይወት እውነተኛው መንገድ የቱ ነው ብሎ፥ በቅዱስ ቃሉ መልስ ያልተመለሰለት እና መልሱን አውቆ በእውነት ላይ ቤቱን ያልሠራው ሰው ራሱን ይፈትሽ። ሁለቱ ብቻ እንጂ ሦስት አማራጮች የሉትምና በጠበበው ደጅ ያልገባ ሰው ጎዳናው በሰፊው መንገድ ላይ ነው። ሆኖም ግን ዛሬ ሆኖ ሳለ፥ ሳይመሽ ቀኑ፥ በእግዚአብሔር ጸጋ ማምለጥ ይቻለዋል።

ያ የጥፋት መንገድ 'ትልቅ' ነው፤ ምክንያቱም ሁሉንም ዓይነት ኃጢአተኞች ያስተናግዳል። በዚያ መንገድ ላይ ለአምላክ የለሹ፣ ለቀጣፊው፣ ለዝሙተኛው ብቻ ሳይሆን፣ ለየትኛውም ስሑት ሐይማኖቶች፥ 'ደግ ሰው ነኝ' ለሚለው ግን ግን ክርስቶስን ለማይከተለው ግብዝ ሃይማኖተኛም ጭምር ሥፍራው በዚያው ነው። ብዙዎች በደስታና በጭብጨባ ይጓዙበታል፤ የልባቸውን ተድላና የሥጋቸውንም ምኞት ሁሉ ይፈጽሙበታል። ነገር ግን መጨረሻው የዘላለም ጥፋትና እሳት ነው! ኦ! የብዙኃኑን ቁጥር አይታችሁ አትታለሉ፤ ፈቃዱና ሳያውቁና ሳያደርጉ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ በሚሉትም በሐይማኖቶችም ድርጅቶችም ስም አትሸወዱ። ወደ ገሃነም የሚወርዱት ስብስቦች ታላቅ መሆን መንገዱን እውነት አያደርገውም።"

2. የጠበበው ደጅና የቀጠነው መንገድ፦ የጸጋው ምርጫ

"ነገር ግን ተመልከቱ! እዚያ ጋ ሌላ ደጅ አለ—እርሱም የጠበበው ደጅ ነው። ይህ እውነተኛው የጸጋ ደጅ ነው። የጸጋ? አዎን። ታዲያ፥ ይህ ደጅ ለምን ጠበበ? ምክንያቱም ጸጋ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊ ምኞትን ክደን በጽድቅ እንድኖር ያስተምረናልና ኃጢአታችንን ተሸክመን ልንገባበት አንችልም። የአሻውን ሁሉ እየፈጸመ፥ የዓለምን ስምና ክብር፣ የራስን ጽድቅና ኩራት ይዞ በዚህ ደጅ መግባት አይቻልም። በክርስቶስ ጽድቅ ብቻ እንጂ። ይህም ጽድቅ የራስን ጽድቅንና ዓመጽን የሚጸየፍ እንጂ ከዓመጽ ጋር የሚተባበር አይደለም። በዚህ ደጅ ለመግባት ራስን መካድ፣ 'እኔ ኃጢአተኛ ነኝ፣ በክርስቶስ መስቀል ብቻ እድናለሁ' ብሎ በንስሐ መንበርከክን ይጠይቃል።

መንገዱም 'የቀጠነ' ነው ይላል ቃሉ። ወገኔ በራሳችን መንገድ ከመዋጋት በክርስቶስ ኢየሱስ በመሆን በማይወሰድብን በክርስቶስ ሰላም አረፍን እንጂ ክርስቲያናዊ ሕይወት የጦር ሜዳ እንጂ በቅንጦት አልጋ ላይ መተኛትም አይደለም። የክርስትናን ሕይወት ዓለም ትጠላዋለች፣ ሰይጣን ይዋጋዋል፣ ሥጋችንም ይቃወመዋል። ከእነዚህ ከሦስቱ ዐይነተኛ ጠላቶቻችን ጋር መንፈሳዊ ውጊያ ላይ ነን። ከሰፊው መንገድ የሚወረወርብን የክፉዎችን ፍላጻን ለመመከት፥ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው።

ግባችንም፥ የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃ ሁሉ አንስተን፥ የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እያፈረስን፥ ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ መማረክ ነው። በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችን ተጫምተው ቆመው ለሚጠፉትም የመዳንን እውነት ቃል በማብሰር በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን መዳን ከዘላለም ክብር ጋር እንዲያገኙ ስለ ተመረጡት በነገር ሁሉ እንጸናለን።
ነገር ግን ይህ መንገድ የቀጠነ ቢሆንም፣ በውስጡ የሚራመዱት ቅዱሳን ግን ሰማያዊ ሰላምና ነጻነት አላቸው! በዚያ መንገድ ላይ በዘላለም መንፈስ ያቀረበው ያ የክርስቶስ ደም ዛሬም ትኩስ ነው፥ አልደረቀም ፈሳሽ ነው፤ የጌታም የቅርብ ኅብረት ከአማኙ ጋር አብሮት ነውና ያጸናዋል።"

3. "የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው"፦ ልብን የሚሰብር እውነት፥

"ይህ ቃል ለኃጢአተኞች ሁሉ የተገለጠውን የጸጋ መንገድ ትተው፥ እንደ ፈሪሳውያን እና እንደ ሰዱቃውያን ሕግን ለሚሰብኩ እና ጸጋውን በሴሰኝነት ለሚለውጡ ወዮላቸው። ይህም የእግዚአብሔርን የፍቅር ልብ ለሚያውቁ አገልጋዮችን ሁሉ ሊያስለቅስ የሚገባ እውነት ነው! ወደ ሕይወት የሚወስደውን መንገድ የሚያገኙት 'ጥቂቶች' ናቸው። ለምን? ሰዎቹ ስለማይፈልጉትና መንገዱን ስለሚንቁት ነው። ብዙዎች ጠባቡን መንገድ ሲያዩ ይደነግጣሉ፤ ራሳቸውን መካድ ስለሚከብዳቸው ወደ ሰፊው መንገድ ይመለሳሉ።

እናንተ ዛሬ የምትሰሙኝ ነፍሳት ሆይ! እናንተ የትኛው መንገድ ላይ ናችሁ? ከብዙኃኑ ጋር ወደ ጥፋት እየፈሰሳችሁ ነው ወይስ ከጥቂቶቹ ጋር ወደ ዘላለም ሕይወት እየተጓዛችሁ? ዛሬውኑ ምርጫችሁን አሳምሩ!" ቁርጣችሁን እወቁ። ወደ ክርስቶስ ያመጣችሁ ምንድን ነው? ኃጢአታችሁ ስለከበደችአችሁ ወይስ ምን? አዎን ችግር መከራ የማይገባው ሰው አይደለሁም፥ ግና ከብዙ ችግራችሁና መከራችሁ፥ ከብዙ እንባችሁና ከልዩ ልዩ ዐይነት ስቃያችሁ ልታርፉ ፈልጋችሁ ወደ ክርስቶስ መጥታችሁ ችግራችሁ ተንከባልሎ ደስ እየተሰኛችሁ ከሆነ፥ ዳሩ ግን ስለ ኃጢአታችሁ እና ስለበደላችሁ እስካሁን ከቅዱሱ ጋር ፊት ለፊት ካልተገናኛችሁ ገና ከነ ኃጢአታችሁ ናችሁ። ገና አልዳናችሁም።

ስለዚህ ይህ የወንጌል ጥሪ ወደ እናንተ ነው። የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአለና። አዎን፥ ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ። (ሉቃ. 19፥10፤ 1ኛ ጢሞ. 1፥15)።

🔥የወንጌል ጥሪ፦ በኃጢአት፥ በዚህ ዓለም ዓመጽ ነፍሳችሁ ለታወከችባችሁ፥ ሰላም ርቆአችሁ፥ እረፍትን ፍለጋ ለምትንከራተቱ፥ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።” እናንተ ደካማችሁ ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ ወዳለው ወደ ኢየሱስ ኑ። የጸጋ ሁሉ አምላክ፥ የምሕረት እጁ ሰፊ፥ ፍቅሩም እጅግ ጥልቅና እጅግም ከፍ ያለ፥ ማዳኑም ኃያል ነውና። እሱ ያሳርፋችኋል። ለነፍሳችሁም እረፍትን ታገኛላችሁና አሁኑኑ ኑ፥ በጠበበው ደጅ ግቡ! አታመንቱ፤ ሞት በደጃችሁ ላይ ቆሟል። ሰፊው መንገድ መጀመሪያው ቢያምርም መጨረሻው ግን ሞት ነው። ጠባቡ ደጅ ግን ወደ ዘላለም ክብርና ወደ አባታችን ቤት ያደርሳል። ራሳችሁን አዋርዱ፣ ክርስቶስን ብቻ እመኑ፤ እርሱ ራሱ ደጁና መንገዱ ነውና!"

🕰 ሕግና ጸጋ 🧭የሕግ እና የጸጋ (Law vs. Grace) ልዩነትንና ግንኙነትን ማወቅና መለየት በክርስትና ሕይወት ውስጥ እጅግ መሠረታዊና ወሳኝ ነው።ሕግና ጸጋ (Law vs. Grace)✍️ ...
26/06/2026

🕰 ሕግና ጸጋ 🧭
የሕግ እና የጸጋ (Law vs. Grace) ልዩነትንና ግንኙነትን ማወቅና መለየት በክርስትና ሕይወት ውስጥ እጅግ መሠረታዊና ወሳኝ ነው።

ሕግና ጸጋ (Law vs. Grace)
✍️ ሕግ (The Law)፦ ሕግ እግዚአብሔር ከሰው ልጅ የሚፈልገውን የጽድቅ መሥፈርትን ያሳያል፤ ይህም የጽድቅ መሥፈርት ልኬት የራሱ የእግዚአብሔር ጽድቅ ያህል ነው። ነገር ግን ሕግ ያንን መሥፈርት ለመፈጸም የሚያስችል አቅም ለሰው አይሰጥም። ስለሆነም፥ ሕግ ሰውን ይኮንናል (ሮሜ 3፥20)።
❣️ ጸጋ (Grace)፦ ሰው ሊያደርገው ያልቻለውንና የእግዚአብሔርን የጽድቅ መሥፈርት ክርስቶስ በመስቀል ላይ እንዲፈጽምለት ያደርጋል፤ ከዚያም የተፈጸመውን ጽድቅ ለሰው በነፃ ይሰጣል። ጸጋ ሰውን በእምነት እንዲሁ ያድናል (ኤፌ. 2፥8)።

📌 አስቀድሜ እንዳልኳችሁ "ሕግንና ጸጋን" በትክክል መለየት እጅግ አስፈላጊ ነው። ሁለቱም ከእግዚአብሔር የመጡ ቢሆኑም፣ ዓላማቸውና የሚሠሩበት መንገድ ፈጽሞ የተለያየ ነው።
የሕግና የጸጋ ዋና ዋና ልዩነቶች
ዋና ዋና መሥፈርቶቹ፥ የሚከተሉት ናቸው።
👉የተሰጠበት መንገድ፦
ሕግ፥ በሙሴ በኩል ተሰጠ (ዮሐ. 1፥17)።
ጸጋ፦ በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ (ዮሐ. 1፥17)።
👉የሰው ድርሻ፦
ሕግ፥ "ይህንን አድርግና በሕይወት ኑር" ይላል (ገላ. 3፥12)።
ጸጋ፥ "ክርስቶስ ሁሉን ፈጽሞታል፣ እመን" ይላል (ዮሐ. 19፥30)።

👉የሚያመጣው ውጤት፦
ሕግ፥ ኃጢአትን ያሳውቃል፣ ቍጣን ይሠራል (ሮሜ 4፥15)።
ጸጋ፥ ኃጢአትን ይቅር ይላል፣ ሰላምን ይሰጣል (ሮሜ 5፥1)።
👉ለማን ነው?
ሕግ፦ ለዓመጸኞች እና በራሳቸው ጽድቅ ለሚመኩ። (1ኛ ጢሞ. 1፥8-11)።
🎯 ሰው እንደሚገባ ቢሰራበት ሕግ መልካም እንደ ሆነ እናውቃለን፤ ይኸውም፥ ለበደለኞችና ለማይታዘዙ፥ ለዓመጸኞችና ለኃጢአተኞች፥ ቅድስና ለሌላቸውና ለርኵሳን፥ አባትና እናትን ለሚገድሉ፥ ለነፍሰ ገዳዮችና ለሴሰኞች፥ ከወንድ ጋርም ለሚተኙ፥ በሰዎችም ለሚነግዱ፥ ለውሸተኞችም በውሸትም ለሚምሉ፥ የብሩክ እግዚአብሔርንም ክብር እንደሚገልጥ ለእኔ አደራ እንደ ተሰጠኝ ወንጌል የሆነውን ደኅና ትምህርት ለሚቃወም ለሌላ ነገር ሁሉ ሕግ እንደ ተሰራ እንጂ ለጻድቅ እንዳልተሰራ ሲያውቅ ነው።

ጸጋ፦ ለኃጢአተኞች በሙሉ፥ ድካማቸውንና ኃጢአታቸውን ላመኑ ምስኪኖች (1ኛ ጢሞ. 1፥15)።

1. ሕግ እንደ መስተዋት ነው፤
ሕግ ልክ እንደ መስተዋት በፊታችን ላይ ያለውን ቆሻሻ (ኃጢአትን) ያሳየናል እንጂ ቆሻሻውን ሊያጥብልን ወይም ሊያነሣልን አይችልም። መስተዋት ፊትን አያጥብም። ሕግ የሰውን ኃጢአተኛነትና ፍጹም አቅም ማጣት ቁልጭ አድርጎ በመግለጥ፣ ሰው ወደ አዳኙ ወደ ክርስቶስ እንዲሮጥ ያደርገዋል (ገላ. 3፥24)። ሕግ ወደ ክርስቶስ ዘወር ካላልን አሳባችንን ያደነዝዛል፥ የጌታን ፊት እያየን ከክብር ወደ እንዳንለወጥ ፊቱን እንዳናይ መጋረጃን ያጥልብናል።

2. ጸጋ እንደ ፈዋሽ ምንጭ ነው

ሕግ ያጋለጠውን ኃጢአተኝነትንና የተኮነነውን ማንነት ጸጋ በክርስቶስ ደም ፍጹም አድርጎ ያጥበዋል፣ ያነጻዋልም። ሕግ "ዕዳህን ክፈል" ብሎ ሲያስረን፣ ጸጋ ግን "ዕዳህ ሁሉ ተከፍሏል" ብሎ በነፃ ይቀበለናል።

"ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ።"ብ—ዮሐ. 1፥17። ጸጋ በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ፥ ጨለማንም ከእኛ ላይ ገፍፎ አርነትን የሰጠን ነው። ጸጋ የጽድቅን አገልግሎት ለእኛ የሰጠን ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር የምንለወጥበት ነው። — 2ኛ ቆሮ. 3:17። ይህ

✍️ ማሳሰቢያ፥

የአማኝ ሕይወት በመንፈስ ተጀምሮ በመንፈስ የሚፈጸም ነው(ገላ. 3፥3)። ከዳነ በኋላም ቢሆን ወደ ሕግ ሥርዓት ሊመለስ አይገባም። በጸጋ የጀመርነውን ሕይወት በሕግ ሥራ ልንፈጽመው አንችልም። በክርስቶስ ያገኘነው ነፃነት ግን ለሥጋ ፈቃድ ማድረጊያ ሳይሆን፣ በጸጋው ኃይል እግዚአብሔርን በፍቅርና በቅድስና የምናገለግልበት ነው።

🎯 ይህም ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ፤ ነገር ግን የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆንነውን ሁሉ የሆንነው ከእርሱ ነው። ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።(1ኛ ቆሮ. 1፥ 29-31፤ 8፥6፤ ሮሜ. 11፥36 )።

25/06/2026

🎯 🎁 ለሚያምኑት ሁሉ የሚሠራ የእግዚአብሔር ጸጋ❣️ 💝🔐
_____________________________________
"ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና።" ቲቶ 2፥11።

ይህች ጥቅስ ክፍለ-ዘመናት የማይሻሩት፥ ዓመታት የማይለውጡት የክርስትና እምነት እና የወንጌል ማዕከላዊ ማጠቃለያ ናት።

፩. መግቢያ፡ ጸጋ ምንድን ነው?

ትርጉሙ፦ ልንከፍለው ወይም በሥራችን ልናገኘው የማንችለው፣ ነገር ግን እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በነፃ የሰጠን መለኮታዊ ሞገስ (የማይገባን መለኮታዊ ስጦታ) ነው። ፦ ደኅንነት ወይም ድነት የሚመጣው በሰው ጥረት፣ በሃይማኖት ትጋት ወይም በሕግ አጠባበቅ ሳይሆን፣ ሙሉ በሙሉ ከእግዚአብሔር ልብ ከፈለቀውና ከሰዎች ዋጋን ከማይጠይቅ ከጸጋው፥ ከነፃ ስጦታው ነው።

ምንጩ፦ ሙሉ በሙሉ ከእግዚአብሔር ፍቅርና ሉዓላዊ ፈቃድ የመነጨ እንጂ በሰው ብቃት፣ በሃይማኖታዊ ትጋት ወይም በዘር ሐረግ ላይ ያልተመሠረተ (ኤፌ. 2፥8-9፥ ቲቶ 1፥2) ነው።

፪. የጸጋው ስፋት

“...ሰዎችን ሁሉ የሚያድን...”፦ ምንም ያህል የገዘፈ ኃጢአት ቢኖር እንኳ፣ ይህ ጸጋ የማያድነውና የማይለውጠው አንድም ኃጢአተኛ የለም። ደግሞም የአዳም ዘር ሆኖ ኃጢአት የሌለበት አንድም ስንኳ የለም። ድነት በሰው ጥረት ሳይሆን በዚህ ጸጋ ሙሉ በሙሉ የሚጠናቀቅ ነው። ይህ ጸጋ፥ አንዳንዶች እንደሚሉት ለተወሰኑ ሰዎች የሚሠራ ሳይሆን፥ ለሰው ልጅ ሁሉ፥ ለዓለም ኃጢአት በሙሉ እኩል የቀረበ ዳሩ ግን “በክርስቶስ ኢየሱስ ለሚያምኑት ሁሉ ለማዳን የሆነ የእግዚአብሔር ኃይል” ነው (ዮሐ. 3፥16 ፤ ቲቶ 2፥11፤ ሮሜ. 1፥16)። እግዚአብሔር ማንም በራሱ ብቃት ሊደርስበት የማይችለውን የዘላለም ደኅንነት አስቀድሞ በልጁ፥ አሁን ደግሞ ያንኑ በክርስቶስ የተፈጸመውን እውነት በመንፈሱ በአገልጋዮቹ በኩል ለዓለም ሁሉ በነፃ ያውጃል።

፫. የጸጋው መገለጥ

“...ተገልጦአልና፤” ፦ የጸጋ መገለጥ ታሪካዊ እውነት ነው። ጸጋ ዝም ብሎ ረቂቅ ሐሳብ ወይም በሕግ ቀለም የተገለጠ የማይደረስበት ረቂቅ እውነት አይደለም። ይልቁኑ በታሪክ ውስጥ በሰው አካል ሕይወት ሆኖ የተገለጠ የእግዚአብሔር ፍቅር እና የማዳን ኃይል እውነት ነው። ይህ ጸጋ በሕያው አካል በኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ መስቀል ላይ ቁልጭ ፍንትው ብሎ በብዙ መከራና ስቃይ ‘ርቃኑን ተንጠልጥሎ በመሰቀል እና በመሞት በግልጽ ታይቷል። ይህ የጸጋ መገለጥ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

📌 ጥቅሱን በጥልቀት ማስተዋል

"ጸጋ" የሚለው ቃል እውነተኛ ትርጉሙና ውበቱ ሊታየን የሚችለው የእኛ የሰው ልጅ ፍጹም ውድቀት፣ በኃጢአት መሞትና አቅም ማጣት ውስጥ መሆኑ ነው። ከድንግል ማርያም ከተወለደው ከቅዱሱ ከእግዚአብሔር ልጅ ከኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር፥ ከአዳምና ከሔዋን የተወለደ ሰው አንድም ሳይቀር በበደሉ ምክንያት የጠፋ፣ ራሱን በራሱ ለማዳን ፍጹም አቅም የሌለው ምስኪን ፍጡር ነበር።

በዚህ ጨለምተኝነት ውስጥ እግዚአብሔር ያደረገው ነገር ቢኖር እኛ ልንከፍለው የማይቻለንን የኃጢአት ዕዳ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕትነት ከፍሎ፣ ለእኛ ፈጽሞ የማይገባንን የጽድቅ፣ የሰላምና የዘላለም ሕይወት በረከት በነፃ ማደሉ ነው።
ስለዚህ ይህ "በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የተሰጠ መለኮታዊ ሞገስ ወይም ጸጋ"፦

🚥መልካም ሥራ ለሚሠሩት የሚከፈል ደመወዝ ወይም ሽልማት አይደለም፦ ሰው በገዛ ሥራው ከአገኘው ዕዳ ወይም ክፍያ ይሆናል እንጂ ጸጋ ሊሆን አይችልም (ሮሜ 11፥6)። ጸጋ ማለት እግዚአብሔር ለደካሞችና ለኃጢአተኞች የሚዘረጋው የመለኮታዊ የፍቅር እጅ ነው።
🚥ከምሕረት ይልቃል፦ ምሕረት ሊደርስብን ከሚገባው መለኮታዊ ቅጣት በርኅራኄው ማምለጣችን ሲሆን፤ ጸጋ ግን ከዚያም አልፎ ፈጽሞ የማይገባንን ሰማያዊ ክብርና ልጅነት በክርስቶስ በኩል በነፃ እንድንቀበል ያደረገ የእግዚአብሔር ቸርነትና ለጋሲነት ነው።

🚥መመካትን ሁሉ ያስቀራል፦ ደኅንነታችን በክርስቶስ ፍጹም ሥራ ላይ ብቻ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ማንም ሰው በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ "በመልካም ሥራዬ፥ በአርባ ቀን ጾም ጸሎቴ አልያም ሱባኤ ገብቼ፥ በገዛ ብርታቴ አገኘሁት" ብሎ ሊመካ አይችልም።

🚥ሊገዙት የሚችሉት ሸቀጥ አይደለም፦ በገንዘብ፣ በስልጣን ወይም በዕውቀት አይገዛም።
"ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም።" — ኤፌሶን 2፥8-9።

ለሕይወት የሚሆን ተግባራዊ ጥያቄ

👉 ዛሬ በሕይወታችሁ ከእግዚአብሔር ጋር ያላችሁ ግንኙነት የተመሠረተው በገዛ ራሳችሁ የጽድቅ ሥራና ትጋት ላይ ነው ወይስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በፈጸመው ፍጹም ጸጋ ላይ? ማንም ሰው በእግዚአብሔር ፊት ሊመካ አይችልም፤ ትምክህታችንም ሆነ መቆሚያችን ያ የከበረው ጸጋው ብቻ ነው። ማረፊያችንና መቆሚያችን ያ የታመነው የእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ነው።

👉 👁 ይህ ቃል የሚቀጥሉትን ጥቅሶች (ቁ. ፲፪-፲፫) ስንመለከት ሙሉ ሥዕል ይሰጠናል። ያዳነን ይህ ጸጋ በደኅንነት ብቻ አያቆምም፤ ይልቁኑ በአሁኑ ዘመን ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊነትን ክደን በቅድስና እንድንኖር ያስተምረናል፤ ወደፊትም የክብር ሙሽራችንን ጌታ ኢየሱስን በተባረከ ተስፋ እንድንጠብቅ ያበረታናል። ዛሬ በገዛ ራሳችሁ ጉልበት ለመቀደስ ከመታገል ውጡና፣ በክርስቶስ በተገለጠው በዚህ ፍጹም በቂ በሆነው ጸጋ ላይ ሙሉ በሙሉ እረፉ! ማራናታ! ጌታ ሆይ፥ አሜን ቶሎ ና!

Address

Wolkite

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when ኢየሱስ ክርስቶስ፡ የእምነታችን ራስና ፈጻሚ posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Shortcuts

Share