09/08/2026
ወርቁ ለምን ይደበስ?
=========
ልጄ ሆይ፥ የጌታን ቃል አክብር፥
"ሕጌን አትርሳ፥ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ።"
ብሎ መልካም ነግሮሃልና፥ አዎን ምክሩን ጠብቅ።
ብዙ ዘመናትና ረጅም ዕድሜ ሰላምም ይጨምሩልሃልና።
ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤
በልብህ ጽላት ጻፋቸው፥ በዘመንህ ሁሉ ያከብሩሃልና፥
አዎን ልጄ፥ በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም፥
ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህና።
መልካም ነውና፥ በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥
በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፥ አላስተዋይ እንዳትሆን፥
ጌታ ራቅ ካለህ ነገር ራቅ፥ ቅረብ ወዳለህም ቅረብ፤
ከቃሉ በላይ አስተዋይ የሆንህ አይምሰልህ፤
ልቤን ያውቃልና እያልህ፥ ሰውነትህን እንዳታታልል፥
በመንገድህ ሁሉ፥ በያንዳንዷ አረማመድህ እርሱን እወቅ፥
እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃልና፥ ቃሉን በልብህ ጠብቅ።
በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን፤
ክርስትና የክርስቶስ ሕይወት ሲሆን፥
አንተ ሞተህ እርሱ በአንተ ሲኖርብህ፥
አቤት የክርስቶስ መዓዛ ጠረን፥ በሚሞት ሥጋህ፥
ሕይወቱ ሲገለጥ፥ በጨለማ ላሉት ሲገለጥ ብርሃን፥
ለኃጢአት ተሰቅለህ፥ ለጽድቅ ሕያው ስትሆን፥
ነበር የክርስትና ሕይወት፥ ባዕምሮና በጥበብ ተሞልተህ ጸጋውን።
መች እንዳሻህ ልትጓዝ፥ ልታደርገው ደስ ያለህን፥
ደቀ መዝሙሩ የመሆንህ፥ ልኬቱ መቼ እንዲያ ሊሆን?
በስውር ልትታገልበት፥ እንኳን ያልተፈቀደልህን፤
ወንድምህን እንዳያሰናክለው፥ ስትተው ጥቅምህን፥
ሕይወትህ ክርስቶስ፥ መሞትህ ጥቅምህ ሲሆን፥
የመድረኩ መልዐክ እንዳሉህ፥ በየኑሮህም በመንፈሱ ስትመላለስ፥
ሲታይብህ ዘወትር፥ አፍህን የሞላው ወሬው በኑሮህ።
ይህ ለሥጋህ ፈውስ፥ ለአጥንትህም ጠገን ይሆንሃልና፥
እግዚአብሔርን ፍራ፥ ከክፋትም ራቅ ተብለህ፥
ይልቁን አቅፈኸው ስትተኛ፥ መነቀፊያ የሚሆንብህ፥
ለስንቱ ይተርፍ ይሆን፥ ምርት በጠበቁበት ገለባ፥
ትርፍ በጠበቁበት፥ ኪሳራው እየሰባ፥
ለጥመት ቅኝት፥ ለምሬት ጥፍጥና እየተገባ፥
ምን እየተነበበብህ ይሆን፥ ስትወጣ ስትገባ?
እንደመሰልህና ደስ እንዳሰኘህ ከሆነ የመገኛህ ስፍራ፥
የበዛ ልምላሜ የበዛ ፍሬ እያለ ተትረፍርፎ ካምላክ ጋራ፥
በክረምቱ ስትጠወልግ፥ አለ የባሕርይ ተራ፥
የስንቱ ልብ አይቁሰልብህ፥ እያለ ጸጋው የበዛ።
ኧረ ወርቁ ለምን ይደበስ? እንቁስ ለምን ይርከስ?
ጥፍጥናው ለምን ይምረር፥ ንጣቱስ ለምን ይጥቈር?
ከማንነቱ ነው ወይ ወይስ ከፍሬው?
በግ ነው ወይ ወይስ ተኩላው በበግ ለምድ?
ግራ ገብቶት ግራ አጋቢ፥ ስንቱ በዘመናችን አለ?
ተብሎ እንዳይጻፍ፥ ተመለስ ልጄ ቀን ሳለ።
አንዳች ነፍስን ሳታሰናክል፥ ከወፍጮ ድንጋይ የሚብስብህ፤
ካንገትህ ሳያርፍ ካራ፥ ተመለስ ልጄ፥ ጌታ አለጊዜህ ሳያፈርስህ፥
ቅጣቱን አታቃልል፥ከዓለም ጋር እንዳይኮነንብህ፤
ሲገሥጽህ ሰምተህ ተመለስ፥ ለንሥኃ ፍሬ ለቅድስና የሚሰጥህን።
በግ ከሆንህማ በግ ሆነህ ኑር፥ ሳታሰድብ የመስቀሉን በግ።
ጸጋው ካልገባን፥ የመማር ጸጋ እያለልን ቁጭ ብለን፥
ከቃሉ ገበታ ተገኝተን፥ እንደ በጎቹ ድምጹን እየሰማን፥
ከቅዱሱ ቅባት እንደተቀበለን፥ ከእውነተኛው መምህራችን፥
የሚያነጻን ቅዱሱ ቃል እያለልን፥ ልንኳተን ወደ ቃርሚያው ፥
ለምንስ እንራወጥ? እዚህም 'ያም እያልን በባዶ ገለባው፥
ሆዳችንን ልንሞላ፥ እንክርዳድ ተዘርቶብን ከ'ሾሃማው አፈር።
እኛስ መጻተኞች ሆነን፥ እንዳሻን የማንኖር፥
ዜግነታችን በላይ በሰማይ፥ የአብ ቤት ሀገር፥
ተስፋችን ፍጹም ደስታችን፥ ከዚያ የሚመጣ መድኃኒታችን፥
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና፥ ለውጦ የሚያከብር ሥጋችንን፥
ይህን ተስፋ ያደርግን እኛ ፥ ክፉ እንዳይነካን፤
እርሱ ንጹሕ እንደሆነ የምናነጻበት ራሳችንን፤
የእግዜር ፈቃድ፥ ወደ'ኛ ለቅድስና እንደሆነ አውቀን።
ወገባችንን ታጥቀን፥ በልክ ኖረን፥
ከመንፈሱ ጋራ፥ ማራናታ ጌታ ሆይ ቶሎ ናልን፥
እያልን እንጮኻለን፥ በጸጋው ራሳችንን እየገዛን።