31/05/2026
‹‹ግንቦት 23››"ጰራቅሊጦስ" የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ከዘጠኙ ዐበይት በዓላት አንዱ ነው።
"ጲራቅሊጦስ"ማለት በልሳነ ጽርዕ “መጸናንዒ” ማለት ነው። ትርጕሙም በጽርዕ (ግሪክ) ቋንቋ ናዛዚ (የሚናዝዝ)፣ መጽንዒ (የሚያጸና)፣ መስተፍሥሒ (የሚያስደስት) ማለት ነው፡፡
ከሦስቱ አካላት አንዱ ለሆነው የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መጠሪያ ስም ነው፡፡
በዓለ ጰራቅሊጦስ ‘በዓለ ጰንጠቆስጤም’ እየተባለ ይጠራል፡፡ ይኸውም በግሪክ ቋንቋ ‘በዓለ ኀምሳ፣ የፋሲካ ኀምሳኛ ዕለት፣ በዓለ ሠዊት (የእሸት፣የመከር በዓል’) ማለት ነው፡፡
በዓለ ጰራቅሊጦስ ወይም በዓለ ጰንጠቆስጤ ከዘጠኙ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዐበይት በዓላት አንዱ ሲሆን መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የወረደበትን ቀን የምናስብበት በዓል ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኋላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ፲፪ቱ ደቀ መዛሙርት፣ ፸፪ቱ አርድእት፣ ፭፻ው ባልንጀሮችና ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት በኢየሩሳሌም ከተማ በአንድነት ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር፡፡
በሚያርግበት ጊዜም “እነሆ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” ሲል ለሐዋርያቱ በገባላቸው ቃል መሠረት ባረገ በ፲ኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ልኮላቸዋል፡፡ (ሉቃ.፳፬፥፵፱)
በሐዋርያት ሥራ እንደ ተጻፈው በበዓለ ጰራቅሊጦስ ማለዳ ሁሉም በአንድ ቦታ ተሰብስበው ሳሉ እንደ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ድንገት ከሰማይ መጥቶ የነበሩበትን ቤት ሞላው፡፡ በመቀጠልም እንደ እሳት የተከፋፈሉ የእሳት ላንቃዎች በሁሉም ላይ ሞላባቸው፡፡
በዚህ ጊዜ ሁላቸውም መንፈስ ቅዱስን ከተሞሉ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ባደላቸው መጠን በየአገሩ ቋንቋዎች ሁሉ መናገር ጀመሩ፡፡ (ሐዋ.፪፥፩-፬) ጌታችን መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት የላከበት ይህ ዐቢይ በዓል ጰራቅሊጦስ ይባላል፡፡
የአምላካችን እግዚአብሔር ቸርነት፣ የቅድስት ድንግል ማርያም እና የቅዱሳን ሐዋርያት አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን አሜን 🙏