20/05/2026
እጅግ በጣም የምንወዳቸውን እና የምንናፍቃቸውን ሚሲዮናዊያንን ወደ ሀገራቸው አሜሪካ ሸኝተናቸዋል!
ከዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ መጥተው ላለፉት በርካታ ዓመታት በሶዶ ክርስቲያን አጠቃላይ ሆስፒታል እንዲሁም በሌሎችም የኢትዮጵያ ክፍሎች በሕክምና ሚሲዮናዊነት እጅግ በጣም በከፍተኛ ርህራሄ፣ ፍቅር እና ትህትና ማህበረሰባችንን በሕክምና አገልግሎት ያገለገሉትን ሚሲዮናዊያንን፦ ዶ/ር ማርክ ካርነስ (የማሕጸን እና ጽንስ ሕክምና ሐኪም) እና ባለቤታቸው አሊሰን ካርነስ፣ ጆይ ፒየርሰን (የአይ.ሲ.ዩ ነርስ)፣ ዶ/ር ቲም ላቭ (የአጠቃላይ ቀዶ ሕክምና ሐኪም፣ የፓን አፍሪካን አካዳሚ ኦፍ ክርስቲያን ሰርጅንስ ፕሮግራም ዳይሬክተር) እና ባለቤታቸው ላውራ ላቭ ከነልጆቻቸው በዚህ ያለውን የአገልግሎት ጊዜያቸውን ስለጨረሱ በክብር ሸኝተናቸዋል።
ሚሲዮናዊያኑ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ደግሞም ለሶዶ ክርስቲያን አጠቃላይ ሆስፒታል በሚሲዮን አገልግሎት፣ ድሆችን በመርዳት፣ ካላቸው በማካፈል፣ ሕሙማንን በነጻ በማከም ወዘተ … እጅግ በጣም ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ከመሆናቸውም በላይ ሆስፒታሉ አሁን ላይ ለደረሰበት የሕክምና አድማስ እና ቴክኖሎጂ ትልቅ መሠረት የጣሉም ናቸው። በኢትዮጵያ በነበራቸው የአገልግሎት ጊዜ እጅግ በጣም ደስተኞች መሆናቸውን እና ሀገራችንን እንደቤታቸው እንደሚያስቡም ገልጸዋል።
በአገልግሎታቸው በርካቶች ተፈውሰዋል፣ ልጅ መውለድ ያልቻሉ ወልደዋል፣ ያለቀሱ ተጽናንተዋል፣ በርካቶች የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር ተካፍለዋል። እያዘኑ እና እያለቀሱ ወደ ሆስፒታላችን ለመጡ እልፍ ታካሚዎች በደስታ እና በሳቅ ለመመለሳቸው ምክንያት መሆን ችለዋል።
ዶ/ር ቲም ላቭ በሆስፒታሉ የአጠቃላይ ቀዶ ሕክምና ሐኪም በመሆን እንዲሁም የ ፓን አፍሪካን አካዳሚ ኦፍ ክርስቲያን ሰርጅንስ ፕሮግራም ዳይሬክተር ሆነው ለበርካታ ዓመታት በትጋት ያገለገሉ ሚሲዮናዊ ሲሆኑ በዛሬው ሽኝታቸው የሥራ ኃላፊነታቸውን ለምክትላቸው ዶ/ር ገዛኸኝ ጥላሁን አስረክበዋል። በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ እጅግ በጣም ደስተኛ እንደነበሩ የገለጹ ሲሆን ወደፊትም ከሆስፒታሉ ጋር ሊሠሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል፤ ለሆስፒታሉ አጠቃላይ ሠራተኞች “እግዚአብሔርን ነው የምታገለግሉት ወይስ ሥራ ብቻ ነው የምትሠሩት” የሚል ጥያቄን በማቅረብ እግዚአብሔርን ልናገለግል እንደሚገባን በምክራቸው አሳስበውናል።
የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤፍሬም ገ/ሥላሴ ፣ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አብርሃም አዴ እንዲሁም የሥራ ክፍል ኃላፊዎች ሚሲዮናዊያኑ ስለ ሠሯቸው ሥራዎች ከፍተኛ አድናቆትን እና ምስጋናን አቅርበዋል።