05/12/2025
"የናግራን ሰማዕታት"
የአገረ ናግራን ሰማዕታት አባታቸውም ቅዱስ ኂሩት ይህም ዮስጢኖስ ለቊስጥንጥንያ በነገሠ በአምስተኛው ዓመት ለኢየሩሳሌም አባ ዮሐንስ ለእስክንድርያ አባ ጢሞቴዎስ ለቊስንጥንጥንያም አባ ጢሞቴዎስ ለአንጾኪያ አባ አውፍራስዮስ ሊቃነ ጳጳሳት ሁነው ሳለ በኢትዮጵያም ጻድቁ ካሌብ ነግሦ ሳለ በዚያን ወራት ለአይሁድ ስሙ ፊንሐስ የሚባል አይሁዳዊ ነገሠ።
በመጀመርያ ግን ሳባ የተባለች አገር በኢትዮጵያ ነገሥታት እጅ ውስጥ ነበረች የሮም ነገሥታት አስባስያኖስና ጥጦስ ከኢየሩሳሌም አይሁድን በአሳደዷቸው ጊዜ ይቺን ሳባን አይሁድ ወረሷት። በውስጧም በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ብዙዎች ክርስቲያኖች በሚኖሩባት ታላቅ ከተማ አለች ይህም የተረገመ አይሁዳዊ ፊንሐስ ሊአጠፋት በመጣ ጊዜ የዚችን የከበረች አገር በመስቀል ምልክት በዙሪያዋ ያለ ቅጽርዋን በበሮቿና በግንብ አጥርዋ ላይ ያሉ ብዙ አርበኞች ሠራዊትን አይቶ በምንም ምክንያት ሊገባባት ስለአልተቻለው ተቆጣ። እግዚአብሔር አጽንቷታልና ነገር ግን በውጭ ያገኛቸውን ገበሬዎች ገደለ ታናናሾችንም ማርኮ ለባሮቹ ሰጣቸው።
ይህም ዲያብሎስን የሚመስለው አይሁዳዊ የኦሪትና የነቢያት ፈጣሪ በሆነ በእግዚአብሔር ስም እየማለ በተንኰል መልእክትን ላከ እንዲህም አላቸው "እኔ ከእናንተ ጋር ጠብ አልሻም ከአገር ሰው አንዱን እንኳ ማጥፋት አልፈልግም ነገር ግን የከተማዋን አሠራርዋን አደባባዮቿን ገበያዎቿን ማየት እሻለሁ" ለአገር ሰዎችም የተናገረው እውነት መስላቸው። የካዕቢ ልጅ አባት ኂሩት "ይህን አይሁዳዊ አትመኑት ሐሰተኛ ነውና ደጁንም አትክፈቱለት" አላቸው አባት ኂሩትንም አልሰሙትም ደጁንም ከፈቱለትና ሰዎች ገንዘባቸውን እንዲዘርፋአቸው አዘዘ። ሁለተኛም ነባልባሉ ወደ አየር እስቲደርስ እሳትን አንድደው የአገሪቱን ኤጲስቆጶስ አባ ጳውሎስን እንዲአመጡት አዘዘ እርሱ እንደ ሞተም በነገሩት ጊዜ ዐፅሙን ከመቃብር አውጥቶ አቃጠለው።
ከዚህም በኋላ ቀሳውስትን ዲያቆናትን መነኰሳትን፣ አንባቢዎችንና መዘምራኑን በቀንና በሌሊት መጻሕፍትን በማንበብ የሚተጉትን ሰበሰበ እነርሱንም ከእሳት ውስጥ ጨመራቸው ቊጥራቸው አራት ሺህ ሃያ ሰባት ነፍስ ሆነ ክርስቲያኖችን በዚህ ሊአስፈራራቸው አስቧልና። ዳግመኛም የብረት ዛንጅር በቅዱስ አባት ኂሩት አንገት ውስጥ እንዲአስገቡ እጆቹንና እግሮቹንም እንዲአሥሩት አዘዘ ታላላቆችንና የአገሩን መኳንንትንም እንዲአሥሩአቸው ክርስቶስን የማይክደው ሁሉ እንዲህ ተሠቃይቶ በክፋ አሟሟት ይሞታል የሚል ዐዋጅ ነጋሪ እየጮኸ በከተማው ውስጥ እንዲአዞቸው አዘዘ።
ቅዱሳን ክርስቲያን ወገኖች በሰሙ ጊዜ እንዲህ እያሉ ጮኹ "እኛ ያመንበትንና በስሙ የተጠመቅንበትን ክብር ይግባውና ክርስቶስን አንክደውም ይህ ርጉም አይሁዳዊም ሰምቶ ወንዶችና ሴቶችን ወጣቶችንና ሕፃናትን ሽማግሎችን ሁሉንም እንዲገድሉ አዘዘና ገደሉአቸው ቊራቸውም አራት ሺህ ሁለት መቶ ኃምሳ ሁለት ነፍስ ሆነ።
ከዚህም በኋላ የቅዱስ ኂሩትን ሚስት ቅድስት ድማህን ከሁለት ሴቶች ልጆቿ ጋር ያዟት እነርሱም በቤታቸው መስኮት ከሚገባው በቀር ፀሐይ ያልነካቸው ናቸው ደርሰውም በአይሁዳዊ ንጉሥ ፊት በቆሙ ጊዜ እርሱም ሃይማኖታቸውን ያስክዳቸው ዘንድ በብዙ ተንኮል ሊሸነግራቸው ጀመረ እምቢ ባሉትም ጊዜ የራሳቸውን መሸፈኛ እንዲገልጧቸው አዘዘ የአገር ሴቶችም እስከ ሚያለቅሱ ድረስ ከልጆቿም የምታንስ አንዲቱ ዕድሜዋ ዐሥራ ሁለት ዓመት የሆነ ከንጉሡ ፊት ላይ ምራቋን ተፋችበት። ወታደሩም አይቶ ሰይፋን መዝዞ አንገቷን ቆረጠ የእኅቷንም አንገት ቆረጠ። ድማህ የልጆቿን ደም እንዲአጠጧት አዘዘ እርሷም ቀምሳ "የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አመሰግንሃለሁ እንደቊርባን መሥዋዕት የሆነውን የልጆቼን ደም እኔ ባሪያህ እንድቀምስ አድርገሃልና" አለች። በዚያንም ጊዜ ርሷንም በሰይፍ አንገቷን እንዲቆርጡ ዳግመኛ አዘዘ ተጋድሎአቸውንም ፈጸሙ።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ኂሩትን ከአሥር ቤት እንዲአመጡት ንጉሥ አዘዘ ከርሱም ጋር አንድ ሺህ አርባ እሥረኞች ሰዎች አሉ ሃይማኖቱንም ይተው ዘንድ አስገደደው። ቅዱስ ኂሩትም ንጉሡን እንዲህ አለው "ክብር ይግባውና ጌታዬን ኢየሱስ ክርስቶስን እያመለክሁት ስኖር ሰባ ስምንት ዓመት ሆነኝ እስከ አራት ትውልድ ለማየትም ደርሼአለሁ ዛሬም ስለ ከበረ ስሙ ምስክር ሁኜ ስሞት እጅግ ደስ ይለኛል። እኔኮ አስቀድሜ መሐላህን እንዳያምኑ ለወገኖቼ ነግሬአቸው ነበር አንተ ሐሰተኛ ነህና ነገር ግን ይህ ሁሉ በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው የሆነው ለዚህም ተጋድሎ ላደረሰኝ ለእርሱ ምስጋና ይሁን" ንጉሡም ይህን ሰምቶ ተቆጣ ወደ ወንዝም ወስደው በዚያ አንገቱን እንዲቆርጡት አዘዘ።
ቅዱስ አባት ኂሩትም በሰማ ጊዜ ደሰሰ አለው የሮምንና የኢትዮጵያን መንግሥት ያጸና ዘንድ የተረገመ አይሁዳዊውን መንግሥት ያጠፋ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ሕዝቡንም ባረካቸው። ከእርሳቸው ጋር በሰላምታ ተሰናበታቸው ከዚህም በኋላ የቅዱሳኑን ራሶቻቸውን ቆረጧቸው በዚያም የአምስት ዓመት ልጅ ያላት አንዲት ክርስቲያን ሴት ነበረች ከቅዱሳን ደም ወስዳ ተቀባች ልጅዋንም ቀባችው ወታደሮችም አይተው ከእሳት ጨመርዋት ልጅዋን ግን አይሁድ ወደእነርሱ ወስደው ወደ ንጉሥን አቀረቡት ንጉሡም "እኔን ትወዳለህ? ወይስ ክርስቶስ የሚሉትን?" አለው ሕፃኑም "እኔስ የእጁ ሥራ ነኝና ክርስቶስን እወደዋለሁ ይልቅስ ልቀቀኝ ወደ እናቴ ልሒድ" አለው በከለከለውም ጊዜ እግሩን ነከሰው አምልጦም ሩጦ ከእሳቱ ውስጥ ገባ። ሁለተኛም የዐሥር ወር ሕፃን እንደተሸከመች አንዲትን ሴት አመጧት እርሷም "ልጄ ሆይ ላዝንልህ አልቻልኩም" አለችው ያ ሕፃንም "እናቴ ሆይ በፍጥነት ወደ ዘላለም ሕይወት እንሒድ ይቺን እሳት ከዛሬ በቀር አናያትምና" አላት በዚያንም ጊዜ ከልጅዋ ጋር ወደ እሳት ውስጥ ተወረወረች።
የክርስቲያን ወገኖችም ይህን አይተው እኩሌቶቹ ወደ እሳት እኩሌቶቹም ወደ ሰይፍ ተቀዳደሙ የአይሁድ ጉባኤ ዕጹብ ዕጹብ ብለው እስኪያደንቁ ድረስ ከዚህም በኋላ እሳቱ በሰማይ ውስጥ መልቶ አርባ ቀን አርባ ሌሊት ታየ። የአይሁድ ንጉሥ ፊንሐስም ወደአገሩ በሔደ ጊዜ ወደ ነገሥታቱ ሁሉ በኃይሉ እየተመካ ላከባቸው የሮሜ ንጉሥ ዮስጢኖስም ሰምቶ ወደ እስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ወደ አባ ጢሞቴዎስ ላከ በአገረ ናግራን ለሚኖሩ የክርስቲያን ወገኖች ደማቸውን ይበቀል ዘንድ ለኢትዮጵያ ንጉሥ ለካሌብ መልእክት እንዲልክ ነው።
የኢትዮጵያ ንጉሥ ካሌብም መልእክት በደረሰው ጊዜ ፈጥኖ ተነሣ በዋሻ ከሚኖር ከአባ ጰንጠሌዎን በረከትን ተቀብሎ ከብዙ ሠራዊት ጋር በመርከቦች ተጭኖ ሔደ በደረሰም ጊዜ የሳባን ንጉሥ የፊንሐስን አገር አጠፋ ሰውም ሆነ እንስሳም ሆነ ሸሽቶ የሚያመልጥ እንኳ ምንም ምን ሳይቀር አጠፋቸው የናግራንን ከተማ ሕንፃዋን አደሰ የሰማዕታትንም መታሰቢያ አቆመ። ከዚህም በኋላ ወደ ሮሜ ንጉሥ ዮስጢኖስ ወደ እስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ጢሞቴዎስ የምሥራች ላከ እነርሱም ሰምተው እጅግ ደስ አላቸው እግዚአብሔርንም አመሰገኑት። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በእሊህ በናግራን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
† † †✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞ † † †
† ደ/መ/ቅ/ቂርቆስ/ሰ/ት/ቤት ጎንደር †
† Telegram † Facebook †