✙በስመ ሥላሴ✙
ህዳር ፯ በዓሉ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
“ሰማዕት ጣዕማ ለዛ ዓለም አማን ወከዓው ደሞሙ በእንተ እግዚአብሔር ወተዐገሱ ሞተ መሪረ በእንተ መንግስተ ሰማያት ተሣሃለነ በከመ ዕነየ ሣህልከ” ትርጉም (ሰማዕታት የዚህን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ፤ ደማቸውን ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ፤ ስለ መንግስተ ሰማያት መራራ ሞትን ታገሱ” (ውዳስ ማርያም ዘኃሙስ)
✙ሰማዕታት በእሳት ተቃጥለው በውሃ ተቀቅለዋል፤ በሰይፍ ተመትረዋል፤ በመጋዝ ተተርትረዋል፤ በመንኩራኩር ተፈጭተዋል፤ እንደ ከብት ቆዳቸው ተገፈዋል። ወደ ጥልቅ ባሕር ተጥለዋል። በዚህ ሁሉ ከሃይማኖታቸው አላፈገፈጉም። ይልቁኑ “ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ።
እነሆ፥ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው፥ አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ።” የሚለውን የተስፋ ቃል ለመፈጸም ብዙ መከራን ተቀብለዋል።
✙ቅዱሳን ሰማዕታት “እግዚአብሔርን ካዱ ለጣዖት ስገዱ፤ ሲባሉ እግዚአብሔርን አንክድም ለጣዖት አንሰግድም፤” በማለት በዓላውያን ነገስታት ፊት ቀርበው ሳያፍሩና ሳይፈሩ ስለ ፈጣሪያቸውን የመሰከሩ ናቸው። በዚህም ምክንያት ተዘርዝሮ የማያልቅ የመከራ ዓይነት ተቀብለው ለእግዚአብሔር ለፈጣሪያቸው ክብር ሲሉ ደማቸውን ያፈሰሱ፣ አጥንታቸውን የከሰከሱ ሕይወታቸውንም የሰጡ ናቸው።
✙የሊቀ ሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ በዛሬው ዕለት መከበሩ ስለ ሁለት ነገር ነው፤✙
✙ ፩. የመጀመሪያው በሕይወተ ሥጋ ሳለ ንጉስ ዱድያኖስ በርሃብ ይሙት ብሎ የምትልሰው የምትቀምሰው ከሌላ መበለት ቤት አስገብቶ ከምሶሶ ቢያስረው ምሶሶውን አለምልሞ ቤቷን በበረከት ሞልቶ ልጇም ዕውር ዓይን ጽቡሰ እግር ነበር ፈውሶታል።
✙ ፪. ሁለተኛው በዚህች ቀን የፋርስና የልዳ ፀሐይ የተርሴስና የቤሩት ኮከብ የባህርና የየብሰ ብርሃን የጌታችን የመድሐኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ምስክር የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረበት ቀን ነው፤ ይህንንም ቀን በመላ ኢትዮጰያ በተለይም በመዲናችን የሚገኘው አንጋፋው ገነተ ጽጌ አራዳ ጊዮርጊስ ታቦተ ህጉ ወጥቶ በደማቁ ይከበራል። ታሪኩ በአጭሩ እንዲህ ነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሚያዚያ 23 ቀን በሰማዕትነት ከሞተ በኃላ አጋልጋዮቹ እጅግ የከበሩ ልብሶችና ያማሩ ሽቶዎች አዘጋጁ በከበረ አገናነዝም ገነዙት በመርከብም ጭነው ወደ ትውልድ አገሩ ልዳ አመጡት ነገር ግን ቤተሰቦቹ በሙሉ ማለትም አባቱ ዘሮንቶስ እናቱ ቴዎብስታ እህቶቹ ማርታና እስያ እንዲሁም አጭተውለት የነበረች እጮኛው ሁሉም ሞተው አገኙዋቸው፤ እንድርያስ የሚባል አጎት ነበረው ስጋውን ተቀበላቸው አገሬው ተሰበሰበ የእየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳስ አባ ቴዎድሮስ ተጠርቶ መጣ ቤተክርስቲያኑን አነጹለት ስጋውንም በዚያ በክብር አኖሩት፤ በዚህች ቀን እጅግ ብዙ የሆነ ድንቅ ታአምራትና ታላላቅ ኃይላት ተደረጉ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቤተክርስቲያን ይህንን ቀን ታከብረዋለች።
✙ታሪክ ብለው ንጉሳችን አፄ ምኒሊክ አራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንን ሲሰሩ ከዚሁ ከልዳ የቅዱስ ጊዮርጊስ መቃብር ካለበት አፈሩን በመርከብ ከዚያም በበቅሎ አስጭነው አምጥተው ለቤተክርስቲያኑ መሰረት አድርገውታል። ቅጥሩን ዙርያውንም ነስንሰውታል ይላል። ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚከበርባቸው ሚያዚያ 23 እረፍቱ ህዳር 7 ቅዳሴ ቤቱ ጥር 23 ዝርዎተ አጽሙ ናቸው፤ በረከቱን ያድለን።
✙ጊዮርጊስ ሆይ ጨካኝ ቁጡ በሆነው በዱድያኖስ አደባባይ ልዩ ልዩ ተዓምራትህን እንደማድረግህ በጠዋት በማታ በከንቱ ነገር የሚነሳሱብኝ ጠላቶቼ ሁሉ እንደ አመድ በነው እንደ ጢስ ተነው ይጥፉ፡፡
✙ጊዮርጊ ሆይ ሰማዕታት ሁሉ አለቃ እንደመሆንህ ቀድሞ ሰብዓ ነገስታትን እንደደመሰስካቸው ነበልባላዊ በምትሆን ጸሎትህ ጠላቶቼን ደምስሳቸው፡፡
✙ተዓምረኛው ሰማዕት ሆይ ቀድሞ የቢፋሞንን ልጅ ከሰዕበተ ሃጢአት ሰውነቱን እንድቀደስከው መንግስተ ሰማያትን ለመውረስ እበቃ ዘንድ ሰውነቴን በፍጹም መቀደስ ከሃጢአት ርኩሰት ንጹህ አድርግልኝ፡፡
✙ተዓምረኛው ሰማዕት ሆይ ሙታንን የማስነሳት ሥልጣን ተሰጥቶሃልና አቤቱ ቤሩታዊትን ከአፈ ዘንዶ እንዳዳንካት እኔን ከእለተ እኪት ከዘመነ መንሱት በጸሎትህ አድነኝ፡፡
✙አቤቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ ሆይ ማረን፤አቤቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ ሆይ ራራልን፤ አቤቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ ሆይ ይቅር በለን፡ ለዘላለሙ አሜን፡፡
ምንጭ፡¬¬- መዝገበ ታሪክ ቁጥር ፩፣ ገድለ ጊዮርጊስ ምዕራፍ 9
✙የእግዚአብሔር፣ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት፣ የቅዱሳን አበው መነኮሳት፣ የቅዱሳት አንስት፣ የደናግላንና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ቃል-ኪዳናቸው ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን ይቆየን፡፡
✙ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡ አነሳስቶ ያስጀመረኝ አስጀምሮ ያስጨረሰኝ የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ይክበር ይመስገን አሜን፡
Alerts
Be the first to know and let us send you an email when Dessie Bilen Debre Genet kidus Giorgis church posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.