30/05/2025
.................የዘሪው የሃሳብ ዘር...........
እኔነቴ፤ ለኔ በሚጠቅሙኝ ይልቁንም ለኔ በሚያስፈልጉኝን ጉዳዮች ላይ ትኩረቴን እንዳላደርግ ይከለክለኛል። ይሀውም በእግዚአብሔር መንገድ እንዳልጓዝ በማድረግ ነው።
ይልቁንም ሃሳቦቸ ሁሉ ለኔ ዘላቂ(የዘላለም) ትርፍ በማያስገኙልኝ ጥራጊ ጉዳዮች የተሞሉ ናቸው። በእግዚአብሔር ቃል ሚዛንነት ሲመዘኑም ረብ የሌላቸው ናቸው።
እኔነቴ ግን በእነዚህ ምድራዊ ሃሳቦችና ግቦች እኔን ከማድከም አልደከመም።
አንዳንድ ጊዜ በሮቹ በተቆለፉ እስር ቤት ዉስጥ ያለው ይመስል ከአፍአ ሲታዩ እጂግ ጠቃሚ በሚመስሉ በቈኤት የሌላቸው ምድራዊ ሃሳቦች ተከብቤ ከሃሳቦች መውጫ ቀዳዳ በማማተር እጨነለቃሁ።
ሃሳቦች እራሳቸውን አስጊጠው በወርቅ፣ በብርና በአልማዝ የተሸለመ ንጉስን መስለው ፤ እኔን ለማገልገል ንጉስ ለባለሟሉ የላካቸውን አገልጋዮች መስለውና ውብና የተወደዱ ሁነው በአእምሮየ(በውስጡ ሰውነቴ) ሚዛን ፊት ይቀርባሉ።
ሃሳቦችን በልምድ፣ በእውነትና በኅሊና ሚዛን መዝኖ መቀበል ወይም አለመቀበል ብቸኛው ስራው የሆነው አእምሮየ(የውስጡ ሰውነቴ) እነዚህን አጊጠውና ተውበው የቀረቡለትን ሃሳቦች ግን በሦስቱም ሚዛኖች ሳይመዝን እንደመልካም እንግዳ በተመረጠ ስፍራ ማረፊያ ያዘጋጅላቸዋል።
የውስጡ ሰውነቴም ሃሳቦችን ተቀብሎ ቦታ በሰጣቸው መጠን ሃሳቦቹ ተደላድለው ሌላ እነሱን የመሰሉ ሃሳቦችን ይወልዳሉ። ግዘፍ ነስተውም በቃላት፣ በስሜት ከፍ ሲልም በድርጊት ወደመገለጽ ያድጋሉ በዚሁ ሲገለጹም ደጋግሜ እመለከታለሁ።
እኔም ብዙ ግዜ የሃሳቦቸን ውጤት የምረዳው ከዚ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ነው። ቃላቶቸና ምግባሮቸንም(ድርጊቶቸን) በእግዚአብሔር ሚዛን ስመዝናቸው ቀለውና ተዋርደው ይገኛሉ።
ረብ የለሽ ሃሳቦች ተዘሩ የሚታጨዱትም እንዲሁ ሆኑ። ሰው የዘራውን ያጭዳልና። መራራ ዘርቶ ወይን የሚያጭድ ማነው። ቃላቶችና ምግባሮችን(ድርጊቶችን) ለማስተካከል ተደጋግሞ ቢሞከርም ማስተካከል አልተቻለም። ፍሬውን ሳይሆን የሚዘራውን ማስተካከል ይቀድማልና። ዘሪው መምረጥ የሚችለው መጀመሪያ የሚዘራውን ነው። የሚታጨደው ፍሬው ግን የማይቀየር ነው።
የውስጡ ሰውነቴም ቁልፉ ያለው የሃሳቦች ሚዛን ጋር እንደሆነ ተረዳ። ስለዚህም ለእያንዳንዷ በሰወች አእምሮ የምትፈጠር ሃሳብ "እሳትና ውሃ አቅርቤልሃለው ወደፈለከው እጅህን ስደድ" በሚለው የእግዚአብሔር ቃል ሚዛን ፤ ማለትም ማንኛውንም ሃሳብ በእግዚአብሔር ቃል፣ በእውነትና በመልካም ኅሊና ሚዛን መዝኖ መቀበል ወይም አለመቀበል(reject) ከሀሳብ ዘር ለሚታጨደውን ፍሬ መወሰኛ ማሕተም ነው።
ስለዚህም ከሃሳብ ዘር የሚታጨደው ፍሬ ቃልና ድርጊት(ንግግር እና ድርጊት) መክፈቻ ቁልፉም የሃሳብ ዘር ሚዛን እንደሆነ ተረዳሁኝ።
ተጻፈ በ ገብረ ማርያም...
ይካቲት 29, 2017 ዓ.ም