Debre Enku Weybla Maryam Sunday School

Debre Enku Weybla Maryam Sunday School Spiritual Communications and Posts only.

20/06/2021

የህይወት ስንቅ

የደብረ እንቁ ትውስታዎች በፎቶ
20/06/2021

የደብረ እንቁ ትውስታዎች በፎቶ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡  ታኅሳስ 24 ቀን የቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዓመታዊ የልደት በዓል  ቅዱስ ተክለ_ሃይማኖት  ሐዋርያዊ ልደት፤መልካም ዛፍ ...
02/01/2021

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡

ታኅሳስ 24 ቀን የቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዓመታዊ የልደት በዓል

ቅዱስ ተክለ_ሃይማኖት ሐዋርያዊ

ልደት፤

መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን የወለዱት ደጋጉ: ጸጋ_ዘአብ ካህኑና እግዚእ_ኃረያ ናቸው:: እርሱ በክህነቱ: እርሷ በደግነቷ: በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል::

በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ_ሚካኤል : ጸጋ ዘአብን ከሞት: እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል:: በኋላም የቅዱሱን መወለድ አብስሯቸዋል::

አቡነ ተክለ ሃይማኖት የጸነሱት መጋቢት 24, በ1206 (1196) ሲሆን የተወለዱት ታሕሳስ 24, በ1207 (1197) ዓ/ም ነው:: በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጸዋል:: ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል::

ዕድገት፤

የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው " ፍሥሃ_ጽዮን " ይሰኛል:: ይሕንን ስም ይዘው: አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል:: በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያት: ሐዲሳትን) ተምረዋል:: በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል:: ዲቁና ከወቅቱ ዻዻስ አባ_ጌርሎስ ተቀብለዋል::

መጠራት፤

አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ:: የክብር ባለቤት ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑ በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ::

የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ:

"ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን:: አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ:: ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ" ብሎ በግርማ ዐረገ:: ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ ጊዜ በኋላሰዓትን አላጠፉም:: ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ::

አገልግሎት፤

ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዻዻሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል አገልግሎትን ጀመሩ:: በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ ( ጽላልሽ ) አካባቢ ብቻ በ10ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ:: ያንጊዜ ኢትዮዽያ 2 መልክ ነበራት::

1.ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል: ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል::

2.ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ ተነቃቅቶ ነበር::

+ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ_ሐዋርያ አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው: ማርያኖችን (ጠንቁዋዮችን) አጥፍተዋል::

ገዳማዊ ሕይወት፤

ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮዽያን ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል:: እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በ3 ገዳማት በረድዕነት አገልግለዋል::

እነዚህም በአቡነ በጸሎተ_ሚካኤል ገዳም ለ12 ዓመታት: በአቡነ ኢየሱስ_ሞዐ_ዘሐይቅ ገዳም ለ7 ዓመታት: በደብረ ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለ7 ዓመታት: በአጠቃላይ ለ26 ዓመታት አገልግለዋል::
በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በኋላም ወደ ምድረ ሽዋ ዞረሬ ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለ22 ዓመታት ቆመው ጸልየዋል:: በተሰበረ እግራቸውም 6 ጦሮችን በግራና በቀኝ ተክለው ለ7 ዓመታት ጸልየዋል::

ስድስት ክንፍ፤

ኢትዮዽያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከኢትዮዽያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል:: ጻድቁ ምድረ እሥራኤል የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ: እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር::

የወቅቱ ሊቀ ዻዻሳት አባ_ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል:: ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በኋላ ነው:: ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር::

ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም:: በገሃድ:-
+በቤተ መቅደስ ብስራቱን
+በቤተ ልሔም ልደቱን
+በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን
+በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን
+በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር::

የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደሆነው ቀራንዮ ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ::
በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን_ድንግል_ማርያም ፈጥና ደርሳ ተክልየን ወደሰማይ አሳረገቻቸው::

በዚያም:-
+የብርሃን ዐይን ተቀብለው
+6 ክንፍ አብቅለው
+የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው
+ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው
+ከ24ቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው
+ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው
+"ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል::

ተአምራት፤

የተክልየ ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው::
*ሙት አንስተዋል
*ድውያንን ፈውሰዋል
*አጋንንትን አሳደዋል
*እሳትን ጨብጠዋል
*በክንፍ በረዋል
*ደመናን ዙፋን አድርገዋል::

ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን መሥርተዋል:: በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕጻናት አብረው ኑረዋል:: በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና::

ዕረፍት፤

ጻድቅ: ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን ሆነው መከራን በብዙ ተቀብለው: አእላፍ ፍሬን አፍርተው: በተወለዱ በ99 ዓመት: ከ8 ወር: ከ1 ቀናቸው ነሐሴ 24, በ1306 (1296) ዓ/ም ዐርፈዋል:: ጌታ: ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል:: 10 ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል::

የጻድቁ አባታችን ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት የቅድስናና የክብር ስሞች :-

1.ተክለ አብ: ተክለ ወልድ: ተክለ መንፈስ ቅዱስ
2.ፍስሐ ፅዮን
3.ሐዲስ ሐዋርያ
4.መምሕረ ትሩፋት
5.ካህነ ሠማይ
6.ምድራዊ መልዐክ
7.እለ ስድስቱ ክነፊሁ (ባለስድስት ክንፍ)
8.ጻድቅ ገዳማዊ
9.ትሩፈ ምግባር
10.ሰማዕት
11.የኢትዮዽያ መነኮሳት አለቃ
12.ፀሐይ ዘበፀጋ
13.የኢትዮዽያ ብርሃኑዋ
14.ብእሴ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ሰው)
15.መናኒ
16.ኤዺስ ቆዾስ (እጨጌ)

እነዚህ የአባታችን ስሞች እንደዘመኑ ሰው ለመሞጋገስ የወጡ ሳይሆኑ ሁሉም በትክክል ሥራዎቹንና ለቤተ ክርስቲያን የሆነላትን የሚያዘክሩ ናቸው:

አምላከ ቅዱሳን ወዳጆቹን ባጸናበት ቅዱስ መንፈሱ እኛንም ያጽናን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::
ታሕሳስ 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
2.ቅዱሳን ጸጋ ዘአብና እግዚእ ኃረያ
3.ቅዱስ አግናጥዮስ ሐዋርያ
4.ቅድስት አስቴር
5.አባ ፊሎንጐስ ሊቀ ዻዻሳት
6.አባ ዻውሊ ጻድቅ
7.ጻድቃን ቅዱሳን ዘከዲህ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
2.አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ ዘክብራን
3.ቅዱስ አጋቢጦስ (ጻድቅ ኤዺስቆዾስ)
4.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
5."24ቱ" ካኅናተ ሰማይ (ሱራፌል)
6.ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም (ኢትዮዽያዊ)
7.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ስለ ታህሳስ ፳፫ ካነበብኩት ላካፍላችሁ ። እናንተም ለሌሎች በማካፈልና በመውደድ ለሌሎች አዳርሱ። ስለ ቅዱስ ዳዊት ልበ አምላ...
02/01/2021

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ስለ ታህሳስ ፳፫ ካነበብኩት ላካፍላችሁ ። እናንተም ለሌሎች በማካፈልና በመውደድ ለሌሎች አዳርሱ።

ስለ ቅዱስ ዳዊት ልበ አምላክ

ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- "እግዚአብሔር ለዳዊት በእውነት ማለ: አይጸጸትም::" (መዝ. 131:11) አሁን በእግዚአብሔር መጸጸት ኑሮበት አይደለም:: ቅዱስ ዳዊት የማያጸጽት ፍጹም ወዳጅ መሆኑን ሲገልጥ ነው እንጂ:: ጌታ ቅዱስ ዳዊትን "እንደ ልቤ የሆነ: ፈቃዴን የሚፈጽም: ባሪያየን ዳዊትን አገኘሁት" (መዝ. 88:20) ብሎ ሲናገር ሰምተን እጅግ አደነቅን::

እንደ አምላክ ልብ ሆኖ መገኘት ምን ይረቅ?! ምንስ ይደንቅ?! ለዚህ አንክሮ ይገባል !! ጌታ ይቀጥልና ደግሞ "ዳዊትን እንዳልዋሸው አንድ ጊዜ በቅዱስነቴ ማልሁ" (መዝ. 88:35) ይላል::

ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ዳዊት 7 ሃብታት ሲኖሩት:-
1.ሃብተ ትንቢት
2.ሃብተ መንግስት
3.ሃብተ ክህነት
4.ሃብተ በገና (መዝሙር)
5.ሃብተ ፈውስ
6.ሃብተ መዊዕ (ድል መንሳት)
7.ሃብተ ኃይል ተብለው ይታወቃሉ::

በ7ቱ ስሞቹም:-
1.ጻድቅ
2.የዋህ
3.ንጹሕ
4.ብእሴ እግዚአብሔር
5.ነቢየ ጽድቅ
6.መዘምር እና
7.ልበ አምላክ ተብሎ ይጠራል::

ልደት፤

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ስለ ልደቱ ሲናገር "እስመ ናሁ በኃጢአት ተጸነስኩ-በኃጢአት ተጸነስኩ" ይላል (መዝ. 50:5) አበው እንደ ነገሩን የቅዱስ ዳዊት አባት ደጉ እሴይ ከነገደ ይሁዳ የኢዮቤድ ልጅ ነው::

ሚስቱን ሰሊብን አንድ ጐልማሳ በዝሙት ዐይን ሲፈልጋት ተመልክቶ ነበር:: አንድ ቀንም መንገድ ሔድኩ ብሎ ግን ያንን ጐልማሳ መስሎ ተመልሶ አብሯት አድሯል:: በዚያች በዚያች ሌሊትም ቅዱስ ዳዊት ተጸንሷልና እንዲህ ብሏል::

ዕድገት፤

ቅዱስ ዳዊት ከሕጻንነቱ ጀምሮ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ነበር:: ሕጸን ሳለ በእረኝነት በጐቹን አያስነካም ነበር:: አንበሳውን በጡጫ: ድቡን በእርግጫ: ነብሩን በሩጫ የያዙትን ያስጥላቸው ነበር:: በጥቂቱ በበግ እረኝነት ስለ ታመነ ለእሥራኤል እረኛ ሊሆን ተመርጧል::

መቀባት፤

እግዚአብሔር ሳዖልን ከናቀው በሁዋላ ከእሴይ ልጆች መካከል "እንደ ልቤ የሆነውን ቀብተህ አንግስልኝ" ቢለው ነቢዩ ሳሙኤል ቤተ ልሔም ገብቷል::

በዚያም ከኤልያብ እስከ አሚናዳብ: 7ቱን የእሴይን ልጆች ቢፈትን አልሆነም:: በቅዱስ ሚካኤል ጠቁዋሚነት ግን ከእረኝነቱ ዳዊት ተጠራ:: ገና ከርቀት ሲመጣ የዘይት ቀርኑ ቦግ ብሎ ተከፈተ::
በቅዱስ ዳዊት ራስ ላይም እንደ እሳት ፈላ:: በአምላክ ምርጫም በ12 ዓመቱ ንጉሥ ተባለ::

ዳዊትና እረጅሙ ጐልያድ፤

ኢሎፍላውያን በጠላትነት በተነሱባቸው ጊዜም ጐልያድ የሚሉት የጌት ሰው እሥራኤልን ሲያስጨንቅ ለ40 ቀናት ቆይቶ ነበር:: ለአምላኩ ስምና ክብር የሚቀና ቅዱስ ዳዊት ግን በድፍረት ገጥሞ በፈጣሪው ኃይል: በጠጠር ጥሎታል:: ከእሥራኤልም ሽሙጥን አርቁዋል:: ግን ቅዱሱ ብላቴና: ጐልያድ ደግሞ 6 ክንድ (3 ሜትር) የሚረዝም ሰው ነበር::

ስደት፤

ቅዱስ ዳዊት ንጉሥ እንዲሆን ተቀብቶ ዙፋን አልጠበቀውም:: ጠላታቸውን ጥሎ ስላዳናቸው ፈንታ: ሳዖልን በገና እየደረደረ ስለ ፈወሰው ፈንታም ሊገደል ተፈለገ:: ፈጣሪው ከእርሱ ጋር ባይሆንም ይገድሉት ነበር::

እርሱ ግን ለ18 ዓመታት በትእግስት ተሰደደ:: ከአንዴም ሁለት ሦስቴ ጠላቱን ሳዖልን አሳቻ ሥፍራ ላይ አግኝቶ በምሕረት ተወው:: በዚህ የዋሕነቱም በብሉይ ሆኖ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ" የምትለውን ሕግ ፈጸማት:: (ማቴ. 7:45, መዝ. 16:4)

ንግሥና፤

ቅዱስ ዳዊት የስደት ዘመኑ ሲፈጸም ሳዖል ሞተ:: ምን ጠላቱ ቢሆን 'የሳዖል ገዳይ ነኝ' ያለውን ተበቀለ:: ስለ ጠላቱም አለቀሰ:: 30 ዓመት ሲሆነው ነግሦ ለ7 ዓመታት በኬብሮን: ለ33 ዓመታት በኢየሩሳሌም (ጽዮን) ሕዝበ እግዚአብሔርን ጠብቁዋል::

በዘመኑም ጠላቶቹን ሁሉ ድል አድርጉዋል:: በልጁ አቤሴሎም እጅ መሰደድን: በሳሚ ወልደ ጌራ መሰደብንም ታግሷል::

ንስሃ፤

ቅዱሱ ንጉሥ ሁሉ ነገር የተሰጠው አባት ነው:: ሁሉ ሕይወቱም ለእኛ ት/ቤት ነው:: ሰው ነውና የኦርዮን ሚስት ቀምቶ: ኦርዮን አስገድሎ ነበር:: ጉዳዩን ነቢዩ ናታን በምሳሌ ሲነግረው ፍጹም ተጸጸተ::

ማቅ ለብሶ: አመድ ነስንሶ አለቀሰ:: መሬትንም በእንባው ክንድ አራሳት:: ሐረግ እስከ ማብቀልም ደረሰ:: እግዚአብሔርም ንስሃውን ተቀብሎ ከፍ ከፍ አደረገው:: በንስሃ ለምትገኝ ጸጋም ምሳሌ ሆነ::

ነቢይነት፤

በቤተ ክርስቲያን ትምሕርት ቅዱስ ዳዊትን የሚያህል ነቢይ (ምሥጢር የበዛለት) አልተገኘም:: 'ከዓለም በፊት እንዲህ ነበረ' ብሎ: ከዚያ ከስነ ፍጥረት እስከ ዳግም ምጽዓት የተናገረ እርሱ ነው::

ስለ መላእክት: ነቢያት: ሐዋርያት: ጻድቃን: ሰማዕታት: ደናግልና መነኮሳት ሁሉ መናገሩ ይደነቃል:: ስለ ድንግል ማርያምና ስለ መድኃኒታችን ክርስቶስም አምልቶ: አስፍቶ ተናግሯል:: 150 ምዕራፎች ባሉት መጽሐፈ ትንቢቱ ኃላፍያትንና መጻዕያትን ተመልክቷል::

ለዚህም አበው:-
"አልቦ ምስጢር ወአልቦ ትንቢት:
ዘኢተናገረ አቡነ ዳዊት" ይላሉ::

መዝሙር፤

ቅዱሱ ነቢይና ንጉሥ በጣም የሚታወቀው በዝማሬው ነው:: ለራሱ ባለ 10 አውታር : ለመዘምራኑ ደግሞ ባለ 8 አውታር በገናን አዘጋጅቶ ፈጣሪውን ያመሰግን ነበር:: 24 ሰዓት ሙሉ ስብሐተ እግዚአብሔር እንዳይቁዋረጥ 288 መዘምራንን በአሳፍ መሪነት መድቦ ነበር::

ራሱም በፍጹም ተመስጦ: ማር ማር እያለው እግዚአብሔርን ያመሰግነው ነበር:: "ቃልህ ለጉረሮየ ጣፋጭ ነው" እንዲል:: (መዝ. 118:103) የዳዊት መዝሙሩ ለአጋንንት ትልቅ ጠላት ነው:: ቅዱሳን መላእክትም በዳዊት መዝሙር ይዘምራሉ::

"በዘቦቱ ይሴብሑ ሰማያውያን ወምድራውያን" እንዲል::

ዳዊትና ጽዮን፤

ቅዱስ ዳዊት ጽዮንን አንጾ ጽላተ ኪዳኑን አመጣ:: ለአምላከ ያዕቆብ ማደሪያን ሊፈልግም ዐይኑ ከእንቅልፍ ተከለከለ:: (መዝ. 131:2) የፈጣሪውን ፈቃድ ሊጠይቅ ሱባኤ ቢገባ "አኮ አንተ ዘትነድቅ ሊተ ቤተ - አንተ ሳትሆን የሚሠራልኝ ልጅህ ነው" አለው::

አያይዞም የምሥጢረ ሥጋዌን ነገር ቢገልጥለት "ናሁ ሰማዕናሁ በኤፍራታ - እነሆ በኤፍራታ ሰማነው" ሲል ተናግሯል:: (መዝ. 131:6) የኪዳኑ ጽላት (ጽዮን) ከአቢዳራ ቤት ስትመጣ ከዙፋኑ ወርዶ: ከተራው ሕዝብ ጋርም ተቀላቅሎ በበገናና በመሰንቆ ተጫወተ::

ስለ ፈጣሪው ክብሩን ተወ:: ከዳን እስከ ቤርሳቤህ የሚገዛ ኃያል ንጉሥ ነበርና:: በጽዮን ፊት እየወደቀ: እየተነሳ: እየታጠቀ: እየፈታ ሲዘምርም ሚስቱ ሜልኮል ናቀችው:: እግዚአብሔር ግን ከፍ ከፍ አደረገው:: (ሳሙ. 6:16)

ክብረ ዳዊት፤

እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ሲል ኢየሩሳሌምን ብዙ ጊዜ ታድጉዋል:: ሰሎሞንና ሕዝቅያስን (ነገሥታቱን) ይቅር ያላቸው ስለ ባለሟሉ ስለ ዳዊት ነው::

የሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያዋ ቃል "የዳዊት ልጅ . . . " የምትል ናት:: (ማቴ. 1:1) ጌታችን "ወልደ ዳዊት" መባልን ወዷልና:: እንዲያውም ራሱ "እኔ የእሴይ ሥርና የዳዊት ዘር ነኝ" ሲል ተናግሯል:: (ራዕ. 22:16)

ዕረፍት፤

ነቢየ ጽድቅ: ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እሥራኤልን ለ40 ዓመታት መርቶ አረጀ:: 'ምነው ያ ኃያል የእግዚአብሔር ሰው ቶሎ አረጀ?' ቢሉ ከገድሉ ጽናት ሰውነቱ ተቀጥቅጦ ነበርና::

በዚያውም ላይ አንድ ቀን ስለ ሕዝበ አሥራኤል ቤዛ ይሆናቸው ዘንድ በቀሳፊ መልአክ ፊት ቆሞ ነበርና (ዜና. 21:16) ሰውነቱ ደከመ:: በዚህ ጊዜም ልጁን ሰሎሞንን አንግሦ በ70 ዓመቱ ከክርስቶስ ልደት ሺህ ዓመት በፊት በዚህች ቀን ዐርፏል::

ዳዊት በሰማይ፤

በራዕየ ጐርጐርዮስ እንደ ተጻፈው ቅዱስ ዳዊትን በሰማይ 99ኙ ነገደ መላእክት ከበውት ያመሰግናል:: ከርሱ ዝማሬ ግርማ የተነሳ የሰማያት ግዘፋቸው ይናወጻል:: በገድለ አቡነ ኪሮስ እንደ ተጻፈው ደግሞ ቅዱሳን ነፍሳቸው ከሥጋቸው የምትለየው በዳዊት በገና ጣዕመ ዝማሬ ነው::

በነገረ ማርያም ትምሕርት ደግሞ የቅዱስ ዳዊት ቤቱ ከልዑል አምላክ መንበር ሥር ነው::
እንግዲህ ምን እላለሁ! ስለ ቅዱስ ዳዊት ከዚህም በላይ መጻሕፍት ብዙ ይላሉ:: ክብሩ ታላቅ ነውና::

በእውነት . . . በእውነት . . . በእውነት . . . ያለ ሐሰት ለቅዱስ ዳዊት ክብርና ምስጋና ይገባል ።

አምላከ ዳዊት ስለ ከበረው ቃል ኪዳኑ ይማረን:: ከንጹሕ አምልኮው ይክፈለን:: በዝቶ ከተረፈ በረከቱም አይለየን::
ታሕሳስ 23 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ዳዊት ልበ አምላክ
2.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
3.አባ ሳሙኤል ጻድቅ
4.አባ ስምዖን ጻድቅ
5.አባ ገብርኤል ጻድቅ
6.አባ ይስሐቅ ጻድቅ

ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
2.ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን (ንጉሠ እሥራኤል)
3.ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ይህን የተቀደሰ ተግባር በሰው ፊት እንዲበራ ላደረጋችሁ  ዲያቆናት እና የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ወንድሞቼና እህቶቼ እጅግ በጣም አመሰግናችኋለሁ ። እግዚአብሔር አገልግሎታችሁንን ይባርክ...
01/01/2021

ይህን የተቀደሰ ተግባር በሰው ፊት እንዲበራ ላደረጋችሁ ዲያቆናት እና የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ወንድሞቼና እህቶቼ እጅግ በጣም አመሰግናችኋለሁ ። እግዚአብሔር አገልግሎታችሁንን ይባርክ ። ህፃናትን ያሳድግልን።

31/12/2020

የደብረ እንቚ ወይብላ ማርያም ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ባዘጋጀው የሦስት ቀን መርሃ ግብር የእሁድ ጧት በትንሹ እነሆ ። ይህን የተቀደሰ ተግባር በሰው ፊት እንዲበራ ላደረጋችሁ ዲያቆናት እና የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ወንድሞቼና እህቶቼ እጅግ በጣም አመሰግናችኋለሁ ። እግዚአብሔር አገልግሎታችሁንን ይባርክ ። ህፃናትን ያሳድግልን። አባቶቻችን ያቆይልን።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ። ኅዳር 6 ቀን ከሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት አንዱበዓለ ደብረ ቁስቁዋም የአርያም ንግሥት: የፍጥረታት ሁሉ እመቤት ድንግል ...
19/11/2020

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ።
ኅዳር 6 ቀን ከሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት አንዱ
በዓለ ደብረ ቁስቁዋም

የአርያም ንግሥት: የፍጥረታት ሁሉ እመቤት ድንግል ማርያም የባሕርይ አምላክ ልጇን አዝላ ወደ ምድረ ግብፅ ወርዳለች:: በወንጌል ላይ (ማቴ. 2:1-18) እንደተጻፈው ጌታችን በተወለደ በ2 ዓመቱ የጥበብ ሰዎች (ሰብአ ሰገል) ወደ ቤተ ልሔም መጥተው ሰግደውለት ወርቅ: እጣን: ከርቤውን ገበሩ: አገቡለት::

ንጉሥ ተወልዷል መባሉን የሰማ ሔሮድስ 144,000 ሕጻናትን ሲፈጅ በቅዱስ ገብርኤል ትዕዛዝ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 1 አምላክ ልጇን አዝላ: በአንዲት አህያ ጥቂት ስንቅ ቁዋጥራ: ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር ስደት ወጣች::

ከገሊላ ተነስታ በጭንቅ: በመከራ: በረሃብና በጥም: በሐዘንና በድካም: በላበትና በእንባ ተጉዛ በዚሕች ቀን ምድረ ግብፅ ገብታለች::

*የአምላክ እናቱ እሳትን አዝላ በብርድ ተንገላታለች::
*ለእኛ የሕይወት እንጀራን ተሸክማ እርሷ ተራበች::
*የሕይወትን ውሃ ተሸክማ ተጠማች::
*የሕይወት ልብስን ተሸክማ ተራቆተች::
*የሕይወት ፍስሐን ተሸክማ አዘነች::
*እመ አምላክ ተራበች: ተጠማች: ታረዘች: ደከመች: አዘነች: አለቀሰች: እግሯ ደማ: ተንገላታች::

ለሚገባው ይሕ ሁሉ የተደረገው ለእኛ ድኅነት ነው:: በእውነት ይህንን እያወቀ ለድንግል ማርያም ክብር የማይሰጥ ሰይጣን ብቻ ነው:: አራዊት: ዕፀዋትና ድንጋዮች እንኳ ለአመላክ እናት ክብር ይሰጣሉ::

አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍና ቅድስት ሰሎሜ ደግሞ የክብር ክብር ይገባቸዋል:: ከአምላክ እናት ከድንግል ማርያምና ከቸር ልጇ ጋር መከራ መቀበልን መርጠዋልና::

"መድኃኔ ዓለም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ተሰደደ? ለምን ስደቱን ወደ ግብፅና ኢትዮዽያ አደረገ?"

1.ትንቢቱን ይፈጽም ዘንድ:: በፈጣን ደመና ወደ ግብፅ እንደሚወርድ ተነግሯልና (ኢሳ. 19:1, ዕን. 3:7)

2.ምሳሌውን ለመፈጸም:: የሥጋ አባቶቹ እነ አብርሃም: ያዕቆብ (እሥራኤል): ኤርምያስ ወደዚያው ተሰደዋልና::

3.ከግብፅ ጣዖት አምልኮን ያጠፋ ዘንድ:: (ኢሳ. 19:1)

4.የግብፅና የኢትዮዽያ ገዳማትን ይቀድስ ዘንድ::

5.ሰው መሆኑ በአማን እንጂ ምትሐት እንዳልሆነ ለማጠየቅ:: (ሰው ባይሆን ኑሮ አይሰደድም ነበር:: ሔሮድስ ቢያገኘው ደግሞ ሊገድለው አይችልም:: ያለ ፈቃዱና ያለ ዕለተ ዐርብ ደሙ አይፈስምና:: )

6.ስደትን ለሰማዕታት ባርኮ ለመስጠት:: እና

7.የአዳምን ስደት በስደቱ ለመካስ ነው::

እመ ብርሃን ድንግል ማርያም ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት (ወይም ለ42 ወራት) በስደት የቆየችባቸው ቦታዎች አሉ:: ድንግል ማርያም ከርጉም ሔሮድስ ስትሸሽ መጀመሪያ የሔደችው ከገሊላ ወደ ሶርያ ደንበር (ደብረ ሊባኖስ) ነው::

በዚያ የሸሸጋት ቅዱስ ጊጋር መስፍኑ በሔሮድስ ሲገደል ወደ ምድረ ግብጽ ወረደች:: በግብጽም ለብዙ ጊዜ ከአንዱ ወደ ሌላው ስትሸሽ ቆየች::
"እንዘ ከመ በግዕት ግድፍት አመ ሳኮይኪ ውስተ ምድረ በዳ" እንዲል:: (እሴብሕ ጸጋኪ)

+ቀጥላም በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ገብታ ደብረ ቢዘን ላይ (አሁን ኤርትራ ውስጥ ነው) ዐረፈች:: ከደብረ ቢዘን በደብረ ዳሙ: አክሱም: ደብር ዓባይ: ዋልድባ አድርጋ እየባረከች ጣና ደርሳለች:: በጣና ገዳማትም: በተለይ በጣና ቂርቆስ ለ100 ቀናት ቆይታ ቀጥታ በጐጃም ወደ ሽዋ ሒዳ ደብረ ሊባኖስን ቀድሳለች::

ቀጥላም እስከ ደብረ ወገግና ደብረ ሐዘሎ ደርሳለች:: በእግሯ ያልደረሰችባቸውን የሃገራችን ክፍሎች በደመና ተጭና ዐይታ ባርካቸዋለች:: ከልጇም በአሥራትነት ተቀብላለች:: ሔሮድስ መሞቱን መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል የነገራትም እዚሁ ኢትደዮዽያ ውስጥ መሆኑን ትውፊት ያሳያል::

እመ ብርሃንም ከሃገራችን ሰዎች (ከሰብአ ኦፌር) የተቀበለችውን ስንቅና ስጦታ በ5 ግመሎች ጭና ከቅዱሳኑ ዮሴፍና ሰሎሜ ጋር በዚህች ቀን ደብረ ቁስቁዋም ውስጥ ገብተው ከድካም ዐርፈዋል:: ሐሴትንም አድርገዋል::

ዳግመኛም ከክርስቶስ ስደት 400 ዓመታት በኋላ በዚህች ቀን የግብጿ ደብረ ቁስቁዋም ታንጻ ተቀድሳለች:: የቅዱሳን ማደሪያም ሁናለች:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ390ዎቹ አካባቢ ድንግል እናቱን: ቅዱሳን ሐዋርያትን: አእላፍ መላእክትን: ጻድቃን ሰማዕታትን: አስከትሎ ወረደ::

የወቅቱ የግብጽ ፓትርያርክ ቅዱስ ቴዎፍሎስና ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ ቤተ ክርስቲያኑን አንጸው: ሕዝቡን ሰብስበው ይጠብቁት ነበርና ወርዶ ቀድሶላቸው ታላቅ ደስታ ሁኗል::

ስደቷን መሳተፍን ሽተው አበው:-
"እመ ኀሎኩ በጐይዮቱ ውእተ መዋዕለ:
እምተመነይኩ ኪያሁ በዘባንየ ሐዚለ:
ወበልሳንየ እልሐስ ዘአእጋሪሁ ጸበለ:
ወከመ አዕርፍ ምስሌሁ በትረ ዮሴፍ ኀበ ተተክለ:
ለወልደ ማርያም በሐጸ ፍቅሩ ልቡናየ ቆስለ::" እንዳሉ:: (ሰቆቃወ ድንግል)
እኛም እመ ብርሃንን ልንሻት ያስፈልገናል::

ይህቺ ቀን ለእኛ ለክርስቲያኖች ሁሉ እጅግ የደስታ ቀን ነውና ሐሴትን እናድርግ:: የሰማይና የምድር ጌታ ለእኛ ሲል ካደረገው ስደቱ በዚህች ቀን ተመልሷልና:: ስደቷን አስበን ካዘንን: መመለሷን አስበን ደስ ልንሰኝ ይገባልና::

"አብርሒ አብርሒ ናዝሬት ሃገሩ:
ንጉሥኪ በጽሐ ዘምስለ ማርያም መጾሩ" ልንልም ይገባል::

"ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕጻኗን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ:: አሕዛብንም ሁሉ በብረት ዘንግ ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ: ወንድ ልጅ ወለደች:: ልጇም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ:: ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቧት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ሥፍራ ወደ በረሃ ሸሸች:: " (ራዕይ. 12:4-7)

>

Some of the photo when celebrating the annversary of sunday school in  2020
10/11/2020

Some of the photo when celebrating the annversary of sunday school in 2020

16/06/2020

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !

በህይወታችን ትልቁ መሰረታዊ ጉዳይ የክርስትና ህይወት ሂደት ነው።የተወደደ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ በ 1ኛ ቆሮንቶስ 13፥11 "ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፥ እንደ ልጅም አስብ ነበር፥ እንደ ልጅም እቈጥር ነበር፤ጕልማሳ ኾኜ ግን የልጅነት ጠባይ ሽሬያለኹ" ያለው ህይወታችንን ለመምራት ስናስብ ልባችንን በእግዚአብሔር ቃል አድሰን እና አሳድገን ይህን ዓለም ሳንመስል ለሰማያዊው ክብር እንድንጨነቅ ነው።

በአእምሮው ህፃን የሆነ ሰው የህይወት መርህ የለውም : አይጠይቅም: አይመረምርም የመጣውም ነገር ሁሉ ይወስደዋል:: ስለዚህ በማደግ ሂደት ውስጥ ክርስትናንም ማሳደግ ተገቢ ነው።

መፅሃፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን: የቀደሙ ቅዱሳን አባቶቻችንም እንዳስተማሩን የክርስትና ህይወት በአንድ ቀን የሚጀመርና የሚገባደድ ሳይሆን እግዚአብሔር ላይ ስንደገፍ እየጠነከረ የሚሄድ ልምምድ ነው::

የምናጠነክረውም፦

1, በፀሎት፦ ፀሎት የህይወታችን ስንቅ ነው። የምንፀልየው በዋናነት የእግዚአብሔር ዓላማን ለማወቅ እንዲረዳን እና ተግባራዊ ክርስትና እንድንኖር መንፈስ ቅዱስ እንዲቀርበን ነው።

2, በፆም፦ በፀሎት በርትተን ስንፆም ፈቃደ ስጋችንን ለነፍሳችን በማስገዛት የነፍሳችንን ቁስል እንፈውሳለን:የሥጋም የነፍስንም በረከት እናገኛለን::

3, በንሥሐ፦ በ ፀሎት እና ፆም ስንበረታ ነፍሳችንን የቱ ጋር እንደበደልናት እንረዳለን ስለዚህም እናለቅሳለን:እንፀፀታለን፣አዝነን በይቅርታ መንፈስ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ እንወስናለን።

4, በቅዱስ ቁርባን፦ በፀሎት፣ፆም እና ንሥሐ ስንመላለስ ከአምላካችን ጋር አንድ የምንሆንበትን: ዘላለማዊ ሕይወትን የምናገኝበትን ሠማያዊ ሚስጥር እንካፈላለን።

በመንፈሳዊ ሆነ በዓለማዊ ህይወታችን እንበረታለን።

ስለዚህ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች በእነዚህ የክርስትና መንገዶች ለመመላለስ እርስ በእርስ መደጋገፍ ያስፈልገናል::

ወስብሐት ለእግዚአብሔር !

እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓል አደረሳቹሁ  ። በዓሉ ከሰላሳ ሦስቱ ዓበይት የእመቤታችን በዓላት አንዱ ሲሆን በዚሕች ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል እናቱ ...
16/06/2020

እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓል አደረሳቹሁ ።

በዓሉ ከሰላሳ ሦስቱ ዓበይት የእመቤታችን በዓላት አንዱ ሲሆን በዚሕች ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል እናቱ እግር ሥር ጠበል አፍልቋል::

ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
ድንግል ማርያም አምላክ ልጇን አዝላ ስደት ወጥታ ምድረ ግብጽ ትደርሳለች:: በወቅቱ ከደረሱባት ችግሮች አንዱ ደግሞ ረሃብና ጽሙ ነበር:: እንኳን ለስደተኛ በቤቱ ላለም ረሃብና ጥም እንዴት እንደሚከብድ የደረሰበት ያውቀዋል::

ለዛም ነው ሊቁ በቅዳሴው:-
"አዘክሪ ድንግል ረሃበ ወጽምዐ : ምንዳቤ ወኀዘነ : ወኩሎ ዐጸባ ዘበጽሐኪ ምስሌሁ" ያለው::

ታዲያ አንድ ቀን የበርሃው ፀሐይ አቃጥሏቸው ባረፉበት ድንግል እመቤታችን ውኃ ልመና ወጣች:: ብዙ ለመነች : ግን ጥርኝ እንኳ የሚሠጣት አጥታ በሐዘን ተመለሰች:: ስትመለስ ግን ይባስ ብሎ የልጇን ጫማ ሽፍቶች ወስደውት ደረሰች::

ያን ጊዜ ልጇን ታቅፋ "ውኃ ሳላገኝልሕ : ጫማሕንም አሰረቅኩብህ" ብላ ምርር ብላ አልቅሳለች::
"በከየት ወትቤ ማርያም ማዕነቅ::
እምሰብአ ሃገር አልቦ ዘየአምራ ለጽድቅ::
ሰአልክዎሙ ማየ ኢወሀሐቡኒ በሕቅ::
ወአሕጎልኩ ለወልድየ አሳእኖ ዘወርቅ::" እንዳለ ደራሲ::

ይሕንን የተመለከተ ልጇ የቆመችበትን መሬት ቢባርከው ሕይወትነት ያለው ማይ (ጠበል) ፈለቀ:: ጌታችን : እመቤታችን: ዮሴፍና ሰሎሜ ከውኃው ጠጥተዋል::

ሲሔዱ ግን ለእንግዶች ጣፋጭ (መድኃኒት) : ለአካባቢው ሰዎች ግን መራራ ሁኗል::
"ከመ ኢይስተይዋ ሰብአ ሐገር ለይእቲ ማይ አምረራ::
ወለርኁቃንሰ ፈውሰ ወጥዕምተ ገብራ::" እንዳለ መጽሐፍ:: (ሰቆቃወ ድንግል)

ከመቶዎች ዓመታት በኋላም ጌታ ጠበል ያፈለቀበት : ድንግል እመቤታችን የቆመችበት ቦታ ላይ በእመ ብርሃን ስም ቤተ ክርስቲያን ታንጿል:: ቅዳሴ ቤቱም ተከብሯል:: ጠበሉም ሲባርክና ሲፈውስ ይኖራል::

††† የጠበል በዓል †††

ዳግመኛ ዕለቱ የጠበል በዓል ተብሎም ይታሠባል:: ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስለ ጠበል ፈዋሽነት ሁሌ ብታስተምርም በዚህ ቀን ግን ልዩ ትኩረቷ ታደርገዋለች::

እግዚአብሔር በምክንያትም አለምክንያትም መፈወስ ይችላል:: ያለ ምክንያት በቃሉና በወዳጆቹ ቃል አድሮ "ዳን" ይላል:: ወይም ደግሞ በምክንያት በእመት (እምነት) : በጠበል : ቅዱስ ቃሉን በመስማት : በመስቀሉና በመጻሕፍት በመባረክ (በመታሸት) : በቅዱሳን አካል (በልብሳቸው : በበትራቸው : በጥላቸው በአጽማቸው . . .) ይፈውሳል::

እርሱ እግዚአብሔር ነውና በወደደውና በመረጠው አድሮ ያድናል ( ይፈውሳል):: (2ነገ. 5:10, ሐዋ. 3:6, 5:15, 19:11)

ዛሬ ግን የጠበል ፈዋሽነት በጉልህ ይነገራል:: (ዮሐ. 5:1, 9:7)

አምላከ ቅዱሳን ከደዌ ሥጋ : ከደዌ ነፍስ በምሕረቱ ይሠውረን:: ከድንግል እመቤታችን በረከትም ያሳትፈን::

ሰኔ 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.የእመቤታችን ድንግል ማርያም ቅዳሴ ቤት
2.የቅዱስ ውኃ (ጠበል) መታሠቢያ
3.ቅድስት ትምዳ እናታችን
4.ቅዱስ አውሎጊስ
5.አባ አትካሮን

ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
2.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
3.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
4.አቡነ ኪሮስ
5.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
6.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

ደብረ ምጥማቅ (ግንቦት 21) ከእመቤታችን 33ቱ በዓላት አንዱ ነው፤ በዚህ ቀን ግብጽ ደብረ ምጥማቅ በተባለ ቦታ በተሰራች ቤተክርስቲያን እመቤታችን ጻድቃንን መላእክትን አስከትላ ትገለጽላቸው...
29/05/2020

ደብረ ምጥማቅ (ግንቦት 21)

ከእመቤታችን 33ቱ በዓላት አንዱ ነው፤ በዚህ ቀን ግብጽ ደብረ ምጥማቅ በተባለ ቦታ በተሰራች ቤተክርስቲያን እመቤታችን ጻድቃንን መላእክትን አስከትላ ትገለጽላቸው ነበር፤ እስላምም ክርስቲያንም በግልጽ ይመለከቷት ነበር። ከየአገሩ ያሉ ሰዎች ይሰበሰባሉ ድንኳን ተክለው ሰቀላ ሰርተው አጎበር ጥለው ይከትማሉ፤ ድንግልም ከግንቦት 21 ቀን ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ሳታቋርጥ ትገለጽላቸው ነበር፤ ህዝቡ የተለያየ ጥያቄ ይጠይቃታል አዳም አባታችንን አሳይን ይሏታል ገሚሱ ነብዩ ዳዊትን ገሚሱ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሳይን ይሏታል አንዳንዱም ከዚህ ቀደም የሞተ ዘመዱን እንድታሳየው ይጠይቃታል፤ እርሷም ለሁሉም ፍቃዳቸውን ትፈጽምላቸው ነበር፤ አዳምን ስትጠራው ከሔዋን ጋር ዳዊትን ስትጠራው ከበገናው ጋር ቅዱስ ጊዮርጊስን ስትጠራው ከጸአዳ ፈረሱ ጋር ነው። ወይ ግሩም ታዲያ ይህ በዚያ ደጉ ዘመን ነበር፤ አሁን ግን ኃጢያታችን ሲበዛ በረድኤት ካልሆነ በገሃድስ ተገልጻ አትታይም ለበቁ ካልሆነ።

የአርያም ንግሥት: የሰማይና የምድር እመቤት: የሰውነታችንም መመኪያ ቅድስት ድንግል ማርያም በዚሕች ዕለት በምድረ ግብፅ ለተከታታይ ቀናት ተገልጻለች::

ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:

ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድረ ግብፅና ኢትዮዽያ በተሰደደ ጊዜ ከድንግል እናቱ: ከዮሴፍና ሰሎሜ ጋር ዛሬ ደብረ ምጥማቅ በሚባለው ቦታ ላይ አርፎ ነበር:: ቦታውን ባርኮ ለዘለዓለም ያንቺ መገለጫ ይሁን ብሎም ቃል ኪዳን ገብቶላት ነበር::

ጊዜው በደረሰ ሰዓት ደብረ ምጥማቅ ተገድሞ የበርካታ መነኮሳት ቤት ሆነ:: እመቤታችንም በልጇ ፈቃድ ግንቦት 21 ቀን አእላፍ መላእክትን: ጻድቃን ሰማዕታትን አስከትላት መጣች::

በዚያ ሕዝበ ክርስቲያንም: አሕዛብም ተሰብስበው ለ5 ቀናት ከእመ ብርሃን ጋር ይሰነብታሉ:: እንግዲህ ልብ በሉት:-
እንኩዋን የአርያም ንግስት: የአምላክ እናቱ እመቤታችንን ይቅርና በዚሕ ዓለም ሰይጣን ቤቱ ያደረጋቸውን: የመዝናኛው ኢንዳስትሪ ዝነኛ ሰዎችን ለማየት የዘመናችን ሰው እንዴት እንደሚቸኩል::

እመቤታችንን በአካል መመልከት አይደለም ስሟን መጥራት ነፍስን ከሥጋ መለየት የሚችል ጣዕምና ደስታ አለው:: ባይሆን ይሔ ለሚገባውና ላደለው ብቻ ነው::

የደብረ ምጥማቅና የአካባቢዋ ሰዎች ከእመቤታችን ጋር የሚቆዩባቸው ቀናት የዘለዓለም የሕይወት ስንቅ የሚይዙባቸው ናቸው:: ፈልገው የሚያጡት: ጠይቀው የማይፈጸምላቸው ምንም ነገር አልነበረም:: ነቢያት: ሐዋርያት: ጻድቃን: ሰማዕታት: ደናግል: መነኮሳት: መላዕክትና ሊቃነ መላእክት ለድንግል ማርያም ሲሰግዱ ይታዩ ነበርና:: እመ ብርሃንም እየመላለሰች ትባርካቸው ነበር::

እነዚያ እርሷን ያዩ ዐይኖች: በፊቷ የቆሙ እግሮች ክብር ይገባቸዋል:: 5ቱ ዕለታት ሲፈጸሙ ሕዝቡ እመቤታችንን በዕንባ ይሰናበቷታል:: እመ ብርሃንም በብርሃን መስቀል ባርካቸው ከቅዱሳኑ ጋር ታርጋለች::

ለአባት እናቶቻችን የተገለጠች እመቤታችን ለእኛም በረድኤት ትገለጽልን:: ጣዕመ ስሟ በአንደበታችን: ጣዕመ ፍቅሯ በልባችን ይደርብን::
ግንቦት 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅድስት ደብረ ምጥማቅ (የእመቤታችን መገለጥ)
2.አባ መርትያኖስ ጻድቅ (በዝሙት ላለመሰናከል እግራቸውን በእሳት ያቃጠሉ አባት)
3.ቅዱስ አሮን ሶርያዊ
4.ቅዱስ አሞጽ ነቢይ
ወርኀዊ በዓላት
1.አበው ጎርጎርዮሳት
2.አቡነ ምዕመነ ድንግል
3.አቡነ አምደ ሥላሴ

የምድር ባለጠጐች አሕዛብ በፊትሽ ይማለላሉ:: ለሐሴቦን ንጉሥ ልጅ ሁሉ ክብሯ ነው:: ልብሷ የወርቅ መጐናጸፊያ ነው:: በሁዋላዋ ደናግሉን ለንጉሥ ይወስዳሉ . . . በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ::
በምድርም ሁሉ ላይ ገዥዎች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ:: ለልጅ ልጅ ሁሉ ስምሽን ያሳስባሉ:: (መዝ. 44:12-17)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ከእመቤታችን ረድዔት በረከት ይክፈለን

[በደብረ ምጥማቅ ከግንቦት 21-25 የድንግል መገለጥ] ✍ በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
♥ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝ ፵፬፥፲፪ ላይ “ወለገጽኪ ይትመሐለሉ ኲሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር” (የምድር ባለጠጎች አሕዛብ ኹሉ በፊትሽ ይማለላሉ) በማለት ትንቢትን እንደተናገረላት ብዙዎች ቅዱሳን ቅድስት ድንግል ማርያምን ተገልጻላቸው ለማየት ተመኝተዋል፤ ብዙዎቹም ልመናቸው ተሰምቶላቸው የአምላክ እናት ተገልጻላቸው እጅግ አስደናቂ ውበቷን አይተዋል፡፡ ከነዚኽ ውስጥ በደብረ ምጥማቅ የነበሩ ምእመናን ሌሎችም ብዙዎች ንጹሓን ክርስቲያኖች ይገኙበታል፡፡

✔❖ ልጇ አስቀድሞ በዘመነ ሥጋዌዉ በደብረ ምጥማቅ እንደ ምትገለጽ በገባላት ቃል ኪዳን መሠረት ከኢትዮጵያ፣ ከግብጽ፣ ከአርመንያ፣ ከሶርያ፣ ከሮም፣ ከጽርዕ፣ ከፋርስ በምድረ በደብረ ምጥማቅ ድንኳን ተክለው፤ አጐበር ጥለው ከግንቦት 21 ቀን ዠምረው እስከ 25 ቀን ድረስ በፍጹም ደስታ የድንግልን በዓሏን ማክበር ይዠምራሉ፤ “ወድንግልሂ ታስተርእዮሙ በእሉ ኀምስ መዋዕል ዘእንበለ ጽርዐት ምስለ መላእክት ወጻድቃን ወሰማዕት ምስሌሃ” ይላል፤ እመቤታችን ከግንቦት 21-25 ያለማቋረጥ ከመላእክት ከሊቃነ መላእክት፤ ከነቢያት ከሐዋርያት፤ ከጻድቃን ከሰማዕታት፤ ከደናግል ከመነኮሳት ጋራ ኹና ትገለጽላቸው ነበር፤ አማኒውም ኢአማኒውም ያያት ነበር፤ ያመኑት ክርስትያኖች እምነታቸው ሲጸናላቸው፤ ያላመኑት ደግሞ እያመኑ ከእግዚአብሔር ወልድ ከልጇ ሀብተ ውልድና ስመ ክርስትና ይቀበሉ ነበር፡፡

✔❖ በጒልላቱ ላይ ስትገለጽ በውስጥ በአፍአ በነፍስ በሥጋ ንጽሕት የኾነችው የቅድስት ድንግል ማርያም የፊቷ ውበትና ብርሃን እጅግ ድንቅ ነበርና ካህናቱም ሕዝቡም ኹሉ ልክ እንደ ኤልሳቤጥ “የጌታችን እናት ለእኛ ትገለጪ ዘንድ እኛ ምንድን ነን” እያሉ ይጮኹ ነበር፤ ርሷም ትባርካቸው ነበር፡፡

✔❖ የእመቤታችን ፍቅር በእጅጉ የበዛለት አባ ጽጌ ድንግልም በደብረ ምጥማቅ በታላቅ ክብር ተገልጻ ለምእመናን የታየችው የአምላክ እናት ለርሱም ትገለጽለት ዘንድ በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፉ ላይ፡-
“አመ ትበርቂ በደብረ ምጥማቅ ኀምሰ ዕለታተ
ትእምርተ ገጽኪ ይርአይ እስከ ይትነሣእ ዘሞተ
ሚ መጠነ ማርያም ታሥተፌሥሒ ትፍሥሕተ
ኅድጊሰ ጽጌ ፍቅርኪ በጊዜ ንቃሑ መዓልተ
ብፁዕ ዘርእየኪ በሕልሙ ሌሊተ”
(የፊትሽን መልክ ያይ ዘንድ የሞተ ሰው እስኪነሣ ድረስ በደብረ ምጥማቅ ለዐምስት ቀናት ያኽል በተገለጽሽ ጊዜ ማርያም ምን ያኽል ደስ ታሰኚ ኖሯል! በቀን የታየው የፍቅርሽ አበባ ይቅርና ሌሊት በሕልሙ ያየሽ ምስጉን ነው) በማለት ተማፅኗታል፡፡

✔❖ የእመቤታችን ታማኝ ወዳጅ አባ ጽጌ ድንግል በተመስጦ በመኾን እጅግ ድንቅ የኾነችውን የአምላክን እናት ሥዕል ካየ በኋላ ይኽነን የምስጋና ቃላት ለርሷ ያቀርባል፡-
“ሥዕልኪ ጽግይተ ላሕይ ዘከመዝ ትኤድም በዓለም
እፎ ይሤኒ በሰማይ ላሕየ ገጽኪ ማርያም
ሐሤተ ትእምርትኪ እጽገብ አስተርእዪኒ በሕልም
እስመ አውዐየኒ ነደ ፍቅርኪ ፍሕም
አጥፍኦቶ ዘኢይክል ዝናም”
(ማርያም ሥዕልሽ በዓለም እንዲኽ የምታበራ ከኾነ በሰማይ የፊትሽ መልክ ምን ያምር! አንቺን ከማየት የሚገኘውን ደስታ እጠግብ ዘንድ በሕልም ተገለጪልኝ፤ ዝናብ ሊያጠፋው የማይቻለው የፍቅርሽ እሳት አንድዶኛልና) ብሏል፡፡

✔❖ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ይኽነን መገለጧን በእንዚራ ስብሐት መጽሐፉ ላይ፡-
“ኦ ንግሥት ይገንዩ ለኪ ነገሥት ወለኪ ንግሥታት ይትቀነያ
ወኪያኪ የአኲታ ወለስምኪ ይገንያ
ወለኪ ይሰግዳ ወለክብርኪ የሐልያ
ጢሮስ ወሲዶና ሰብአ ግብጽ ወኢትዮጵያ
ፊንቂ ወሮምያ ማሮን ወአርማንያ
በሥነ ጸዳልኪ ይትፌሥሓ ወበላሕይኪ ይትሐሠያ”

(ንግሥት ሆይ ነገሥታት ለአንቺ ያገለግላሉ፤ ንግሥታትም አንቺን ያመሰግናሉ፤ አንቺንም ያሞግሳሉ፤ ለስምሽም ያጐነብሳሉ፤ ለአንቺ የጸጋ ስግደትን ይሰግዳሉ፤ ለክብርሽም ምስጋናን ያቀርባሉ፡፡ ጢሮስና ሲዶና የግብጽና የኢትዮጵያ ሰዎች፣ ፊንቄና ሮምያ፣ ማሮንና አርማንያ በወጋገንሽ ውበት ደስ ይሰኛሉ፤ በደም ግባትሽም እሰይ ይላሉ) በማለት ገልጦታል፡፡

✔❖ ልቡናቸው በእጅጉ የበራላቸው አኹን እንዳለንበት ዘመን የቃላትም የምስጋናም ድርቅ ያላገኛቸው በምስጢር ባሕር የዋኙ ቀደምት ሊቃውንት ስለ አምላክ እናት ውበት አምልተው አስፍተው የጻፉ ሲኾን
(የቆጵሮሱ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ) እንዲኽ አላት፡-

✔☞ ☞ “She was grave and dignifified in all her action…” (እመቤታችን በኹሉም ርምጃዎቿ ጐበዝና የተከበረች ነበረች፤ የምትናገረው በጣም ጥቂት ሲኾን ርሱም ለማድረግ አስፈላጊ በሚኾንበት ብቻ ነበር፤ በጣም ዝግጁ ኾና የምትሰማና በቀላሉ ንግግር ለማድረግ የምትችል ናት፤ ለእያንዳንዱ ሰው አክብሮትና ክብር (ሰላምታ) ትሰጣለች፤ ቁመቷ መኻከለኛ ሲኾን አንዳንዶች ግን ቁመቷ ከፍ ያለ እንደነበር ይናገራሉ፤ ከእያንዳንዱ ሰው ጋር ያለምንም ፍርሀት በግልጽነት ያለምንም ሳቅና መጯጯኽ ትናገራለች፨

✔በተለይ ፈጽማ ለቁጣ የምትጋበዝ አልነበረችም፤ መልኳ እንደ ደረሰ የስንዴ አዝመራ ያማረ ጸጒሯ ቀይማ ነው፤ ዐይኖቿ ብሩሃትና የዋህ የኾኑ ቀለማቸውም ፈዘዝ ያለ ቡናማ ኾኖ የዐይኖቿ ብሌኖች የዘይት-አረንጓዴ ይመስላል፤ የዐይኖቿ ቅንድብ (ሽፋሽፍት) ከፊል ክብና ደማቅ ጥቁር ናቸው፤ አፍንጫዋም ረዥም፣ ከናፍሮቿ ቀይና ምሉእ ሲኾኑ በቃሎቿ ጣፋጭነት የተመላባቸው ነበሩ፨

✔ፊቷ ክብ ሳይኾን ግን እንቁላልማ ዐይነት ቅርጽ ነበረው፤ እጆቿ ረዥምና ጣቶቿም በጣም ረዣዥም ነበሩ፤ ከማንኛውም ያልተገባ ኩራት ሙሉ በሙሉ የነጻች ስትኾን ግድ የለሽነት ፈጽሞ ጨርሶ የለባትም ነበር፤ የሚመጡትን ነገራት በፍጹም ትሕትና ትቀበል ነበር፤ ተፈጥሯዊ ቀለማት ያላቸው (ማለትም በቤት ድር የተሠሩ) ልብሶችን ትለብስ ነበር፤ ይኽም በእጅጉ አብሯት የሚኼደው አለባበስና ይኽ እውነታ በራሷ ላይ በምታደርገው ቅዱስ ልብስ አኹን ቅሉ ሊረጋገጥ የሚችል እውነታ ነው፤ ለማጠቃለል ያኽል በመንገዶቿ ኹሉ በመለኮታዊ ጸጋ የተመላች ነበረች) ይላል፡፡

✔የመልክአ ማርያም ደራሲም የአምላኩን እናት ቅድስት ድንግል ማርያምን ፊቷን ለማየት ሽቶ በናፍቆት ኾኖ፡-
“ሰላም ለመልክእኪ ዘተሠርገወ አሜረ
ዘያበርህ ወትረ
ፍቅርትየ አንቲ እንተ ታበድሪ ፍቅረ
አርእዪኒ ገጸ ዚኣኪ ማርያም ምዕረ
ዘኢይሰምዖ ካልእ እንግርኪ ነገረ”
(ኹልጊዜ (ዘወትር) የሚያበራ ፀሓይን ጌጥ ላደረገ መልክሽ ሰላምታ ይገባል፤ ፍቅርን የምትመርጪ (የምታስቀድሚ) አንቺ ፍቅረኛዬ ማርያም ሌላ የማይሰማው ነገርን እነግርሽ ዘንድ አንድ ጊዜ ያንቺን ፊት ግለጪልኝ) በማለት ተማፅኗታል፡፡

✔ልክ እንደ ርሱ የአምላክን እናት ፊቷን ለማየት የተመኙ ብዙዎች ቅዱሳን ነበሩ፤ ለምሳሌም ያኽል ከቅዱሳን አበው መኻከል አባ ይሥሐቅ እመቤታችንን በፍጹም ልቡናው ከመውደዱ የተነሣ ከሠርክ ጸሎት በኋላ ሌሎች መነኮሳት ለመኝታ ወደ የበኣታቸው ሲኼዱ ርሱ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመኼድ በቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ፊት ቆሞ በፊቷ እየተማለለ ሦስት መቶ ስግደትን እየሰገደ፤ በእያንዳንዱ ስግደቱ ላይ “ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ አርእየኒ እመከ አሐተ ሰዓተ” (ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ለአንዲት ሰዓት እናትኽን አሳየኝ) እያለ በመጸለይ ለሰባት ዓመት ከቈየ በኋላ፤ በሰባተኛው ዓመት በታላቅ ግርማ ተገልጻለት የአምላክን እናት ፊት ለማየት በቅቷል።

ርሷም ምን እንደሚሻ ብትጠይቀው በታላቅ መንፈሳዊ ደስታ በመኾን የንግሥተ ሰማይ ወምድር የርሷን ገጽ ያዩ ዐይኖቹ ሌላ ነገርን ማየት እንደማይፈልጉና ከልጇ እንድታማልደው ብቻ እንደሚፈልግ ነግሯት፤ ርሷም ከሦስት ቀን በኋላ እንደሚያርፍ ክፍሉም ከርሷ ጋር መኾኑን ገልጻለት ባርካው ዐርጋ፤ መልኳን አይቶ በሦስተኛው ቀን ይኽ ቅዱስ አባት ዐርፏል፡፡

✔በመኾኑም በደብረ ምጥማቅ የተገለጠችላቸው ምእመናን የአምላክን እናት አይተው እንደተደሰቱ፤ ዛሬም ለእኛ ለልጆቿ በረድኤት ትገለጽልን ዘንድ አበው ካህናት ሌሊቱን በሰዓታት ምስጋና፦ “ንዒ ኀቤየ ኦ ድንግል ምስለ ወልድኪ ፍቁርኪ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመ ትባርኪ ላዕሌነ” (ድንግል ሆይ ከተወዳጅ ልጅሽ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋራ ወደ እኔ ነዪ እኛን ትባርኪ ዘንድ (በእኛ ላይ በረከትን እንድታሳድሪ) በማለት ይማፀኗታል፤ በገዳም በበረሓ ያሉት አበውም ምስጋናዋን በማድረስ ፍጹም በረከቷን ሽተው በፊቷ ይማለላሉ፤ ርሷም ባሉበት ገዳም እየተገለጸችላቸው እንደ ቅዱስ ኤፍሬም በረከቷን ታድላቸዋለች፡፡

✔የውበቷን ነገር ድንቅ በኾነ ቅኔያዊ አገላለጥ እንዲኽ አላት፦

☞ ☞ “ኦ ፍቅርት ውዕየ ልብየ በእሳተ ፍቅርኪ ወነደ ኅሊናየ እምኀልዮትኪ …” (ውዲቱ ሆይ በፍቅርሽ እሳት ልቤ ተቃጠለ፤ አንቺንም ከማሰብ የተነሣ ኅሊናዬ ነደደ፤ ለምስጋናሽ ቃሌን ከፍ ከፍ አደርጋለኊ፤ አንቺን ለማመስገንም አንደበቴን አከፍታለኊ፡፡ ንግሥት ሆይ አንደበቴ ቅንነትሽን በመናገር ደስ ይለዋል፤ ከንፈሮቼም በቸርነትሸ ጣዕም ነገር ደስ ይሰኛሉ፤ ሰላም እያልኹሽም ለስምሽ አጠራር እኔ እሰግዳለኊ፡፡

✔ንግሥት ሆይ የራስሽ ክፍክፋት ተፈጥሮ እንደ ጥቁር አሞራ የኾነ ጠጒርሽም እንደ ሐር የሚመስል ነው፤ የራስ ወርቅሽ የቃል ኪዳን ምልክት ነው፤ የንጽሕናሽ ብርሃንም እንደ ጧት ወገግታ ነው፡፡ ግርምቲቱ ሆይ የቅንድቦችሽ ነበልባል (እሳት) የመብረቅ ፍንጣቂ ነው፤ ዐይኖችሽም እንደ ጨረቃ ምላት ብርሃንን የተመሉ ናቸው፤ ጆሮችሽም የደስታ በሮች ናቸው፤ የጒንጮችሽ ቅላትም እንደ ሮማን ቅርፍት ነው፡፡

✔❖ ንግሥት ሆይ አፍሽ የበጎ መዐዛ መስኮት ነው፤ ከንፈሮችሽም የደስታ መፍሰሾች ናቸው፤ የአፍንጫሽ መዐዛም የበረሓ እንኮይ ነው፤ የጥርሶችሽ ንጣትም እንደሚያምር በረዶ ነው፡፡ ምርጢቱ ሆይ የአንደበትሽ ሥር የወተት ምንጭ ነው፤ የንግግርሽ ቃልም እንደ ማር የጣፈጠ ነው፤ የእስትንፋስሽ ቃልም የሽቱ ቅመም ብናኝ ነው፤ ጒረሮሽም፣ የማር ወለላ አረፋ ነው፡፡.

✔❖ የተሸለምሽ ያጌጥሽ ሙሽሪት ሆይ፤ የአንገትሽ መገናኛ (ቅርጽ) እንደ ወርቅ ዘንግ ነው፤ ትከሾችሽም የሰላምና የቅንነት ማረፊያዎች ናቸው፤ የዠርባሽ ልብስም የብርሃን ሐር ነው፤ ደረትሽም የዕውቀት አዳራሽ ነው፤ ጉያሽ የመለኮት ማረፊያ ናቸው፤ እጆችሽም በንጽሕና አንባር የተሸለሙ ናቸው፤ ክንዶችሽም የንጉሥ መጠጊያዎች ናቸው፤ ክርንሽም የኀይል ረድኤት ቦታ ነው፤ ክንዶችሽም የእሳት ምሳግ ናቸው፤ መኻል እጆችሽም ለመስጠት የተዘረጉ ናቸው፤ በጥፍሮችሽ የተጋረዱ ጣቶችሽ እንደ ወርቅ ፍቅፋቂ ነው::

✔❖ ሙሽሪት ሆይ ጡቶችሽ እንደ ወይን ፍሬ የተወደዱና ያማሩ ናቸው፤ ጒልበትሽም የአርያም (የሰማይ) ወገን ናቸው፤ የጭኖችሽ (የእግሮችሽ) አነዋወርም እንደ እብነ በረድ ምሶሶች ነው፤ እግሮችሽም ምሕረትን (ይቅርታን) ለማድረግ የተፋጠኑ ናቸው፤ የማይታበዩ ጫማዎችሽም የጥበብ መድረክ ናቸው፡፡

✔❖ እግርሽም በቅንነት ጐዳና የጸኑ ናቸው፤ የእግርሽ ጣቶችም በጥፋት ደንጊያ የማይሰነካከሉ ናቸው፤ ጥፍሮችሽም በላያቸው እንደ ብርሃን ብልጭ የሚሉ ናቸው፡፡ የቁመናሽ አካልም እንደ ዘንባባ ያማረ ነው፤ የመልክሽ ደም ግባትም ለዐይን የተወደደ ነው፤ ድንግል ሆይ እጅግ በጣም አማርሽ፤ ከራስሽ እስከ እግርሽ ክፉ ነገር የለብሽም፤ ደም ግባትሽን የሚመስለው የለም፤ ኹለንተናሽንም የሚተካከለው የለም፡፡ ምርጢቱ ሆይ መልካም በኾነውና በጎም በኾነው ኹሉ መሰልኹሽ ነገር ግን ምስጋናሽን መጨረሽ አልቻልኹም፡፡

✔❖ ጐኖችሽም በወርቅ ሐመልማል የተሣሉ (ያጌጡ) ናቸው፡፡ የማሕፀንሽ መቅደስ በአበባ (በአካላዊ ቃል)የታጠረ ነው፣ የልቡናሽ ጥልቀትም በቸርነት ቃል፤ ኲላሊቶችሽ የትእዛዝ ጽላት ናቸው፤ ኅሊናሽም የጥበብ መሠረት ነው፤ አንዠትሽም የይቅርታ ሣጥን ነው፤ የውስጥ ሰውነትሽም የቅዱሳን ቅድስት ምልክት ነው፤ የዕንብርትሽ ዙሪያም እንደ ማኅተም ቅርጽ ነው፤ ማሕፀንሽም የምስጋና ዙፋን ነው::
የድንግልናሽም ምሳሌ፤ የታተመ የነቢያት መጽሐፍ ነው።

✔ ❖ የወገብሽ ትጥቅም የቅድስና ጸጋ ነው፤ ጒልበትሽም የአርያም (የሰማይ) ወገን ናቸው፤ የጭኖችሽ (የእግሮችሽ) አነዋወርም እንደ እብነ በረድ ምሶሶች ነው፤ እግሮችሽም ምሕረትን (ይቅርታን) ለማድረግ የተፋጠኑ ናቸው፤ የማይታበዩ ጫማዎችሽም የጥበብ መድረክ ናቸው፡፡ እግርሽም በቅንነት ጐዳና የጸኑ ናቸው፤ የእግርሽ ጣቶችም በጥፋት ደንጊያ የማይሰነካከሉ ናቸው፤ ጥፍሮችሽም በላያቸው እንደ ብርሃን ብልጭ የሚሉ ናቸው፡፡

✔❖ የቁመናሽ አካልም እንደ ዘንባባ ያማረ ነው፤ የመልክሽ ደም ግባትም ለዐይን የተወደደ ነው፤ ድንግል ሆይ እጅግ በጣም አማርሽ፤ ከራስሽ እስከ እግርሽ ክፉ ነገር የለብሽም፤ ደም ግባትሽን የሚመስለው የለም፤ ኹለንተናሽንም የሚተካከለው የለም፡፡ ምርጢቱ ሆይ መልካም በኾነውና በጎም በኾነው ኹሉ መሰልኹሽ ነገር ግን ምስጋናሽን መጨረስ አልቻልኹም)፡፡ (አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ)
✔❖ በመስቀል ሥር በአደራ ከፈጣሪያችን ክርስቶስ የተሰጠሽን የአምላክ እናት ሆይ ዛሬም በእጅጉ ለምንወድሽ ለእኛ ለልጆችሽ ትገለጪልን ዘንድ እንማፀንሻለን፡፡ አሜን ።

“ዐርገ ሰማያተ በዐምደ ደመና፤ በደመና ወደሰማይ ዐረገ” (ቅዱስ ያሬድ) ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ይህን ቃል እንደተናገረው ዝማሬ በሚባለው የመጽሐፍ ክፍል   እናገኘዋለን። ሊቁ የጌታችን...
29/05/2020

“ዐርገ ሰማያተ በዐምደ ደመና፤ በደመና ወደሰማይ ዐረገ” (ቅዱስ ያሬድ)

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ይህን ቃል እንደተናገረው ዝማሬ በሚባለው የመጽሐፍ ክፍል እናገኘዋለን። ሊቁ የጌታችንን የማዳን ጉዞ ከፅንሰቱ ጀምሮ እስከ ዕርገቱ ብሎም እስከ ዳግም ምጽአቱ ከብሉያት እና ከሐዲሳት እያጣቀሰ አምልቶና አስፍቶ ያስረዳበትን ቃል ስለዕርገቱ በተናገረው የምስጋና ክፍል ውስጥ እናገኘዋለን፤ ሙሉ ንባቡም እንዲህም ነው።
“ዐርገ ሰማያተ በዐምደ ደመና፤ ለድንግል ዘፈትሐ ማኅፀና፤ ለደቂቀ እስራኤል ዘአውረደ መና፤ ውእቱኬ ዘአድኃና ለሶስና እምእደ ረበናት፤ ዐርገ ሰማያተ በዐምደ ደመና፤ በደመና ወደ ሰማይ ዐረገ፤ የድንግልን ማኅፀን የፈታ፣ ለእስራኤል ልጆች መናን ያወረደ፤ ሶስናን ከረበናት እጅ ያዳነ በደመና ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡” በዚህ ኃይለ ቃል ዐረገ የተባለው ማን ነው? በደመና ዐረገ የተባለውስ ምን ማለት ነው? የድንግልን ማኅፀን የፈታው፣ ለእስራኤል መናን ያወረደው፣ ሶስናን ከረበናት እጅ ያዳነው ማን ነው? የሚለውን እንመለከታለን።
ዐረገ የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የእርሱ ወደሰማይ ማረግ የሌለበት ቦታ ኑሮ ካለበት ቦታ ወደሌለበት ቦታ ሄደ ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የማዳን ሥራውን ፈጽሞ ወደባሕርይ አባቱ መመለሱን፤ የማዳን ሥራውን መፈጸሙን፤ በሥጋ በክብር ማረጉን ለመግለጽ ነው፡፡ (ዝማሬ ዘዕርገት)
ጌታችን ኢየሱስ በደመና ዐረገ መባሉ ሊቃውንት እንደሚነግሩን ደመና ክብሩና ልዕልናው በመሆኑ ነው። “ዘበእንተ ዕበይከ ትትሜሰል በደመና፤ ስለ ልዕልናህ በደመናት ትመሰላለህ” እያሉ ሊቃውንቱ ያመሰግኑታል። በሐዋርያት ሥራም “ወነሥአቶ ደመና ወዐርገ ሰማየ እንዘ እሙንቱ ይኔጽሩ ኀቤሁ፤ ደመናም ተቀበለችው፤ እነርሱም ወደእርሱ እያዩ ወደሰማይ ዐረገ” ተብሎ ተጽፏል። ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም “ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን፤ እግዚአብሔር በዕልልታ ጌታችንም በመለከት ድምፅ ዐረገ” በማለት እንደነገረን በክብር በይባቤ መላእክት ማረጉን ያስረዳል። (ሐዋ.፩፥፱፤ መዝ.፵፮፥፭)
በሌላ መልኩ በደመና ዐረገ የተባለው ደመና እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት፤ ከእርሷ በነሣው ሥጋ ዐረገ ማለት ነው። ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተቀምጦ ወደግብፅ ይመጣል” ብሎ አስቀድሞ በትንቢቱ የተናገረላት ደመና እመቤታችን በመሆኗ ነው። ሊቁ ቅዱስ ያሬድም “ደመናሰ ዘይቤ ይእቲኬ ማርያም እንተ ጾረቶ ዲበ ዘባና፤ ደመናስ የሚላት አምላክን በጀርባዋ የተሸከመችው ማርያም ናት” በማለት ያስረዳል። ስለዚህ “በደመና ዓምድ ዐረገ” ሲል ከድንግል ማርያም በተዋሐደው ሥጋ ወደሰማይ ዐረገ ማለት ነው። ከላይም እንደገለጽነው ዐረገ መባሉ በሥጋ እንጂ በመለኮቱማ ምሉዕ በኵለሄ፣ በሁሉም ቦታ፣ በሁሉም ጊዜ ምሉዕ ነው። (ኢሳ.፲፱፥፩)
ይህ በክብር በይባቤ መላእክት፣ ከማርያም በተዋሐደው ሥጋ በደመና ዐረገ የተባለው ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ከብሉይ ከሐዲስ እየጠቀሰ እንዲህ ያስረዳናል።

ሀ. የድንግልን ማኅፀን የፈታው ነው። “ለድንግል ዘፈትሐ ማኅፀና፤ የድንግልን ማኅፀን የፈታው ነው።” እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመላእክትም በሰውም አንደበት የተመሰከረላት፣ ጥንት ነቢያት ትንቢት የተናገሩላት፣ በኋላም ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል፣ የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ እናት ቅድስት ኤልሳቤጥ የመሰከሩላት ዘለዓለማዊት ድንግል ናት። ከዚህች ድንግል ማኅፀኗን ዙፋን አድርጎ በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና የተወለደው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” በማለት እንደተናገረው ከድንግል ማርያም የተወለደው አማኑኤል ተብሎ በነቢዩ ትንቢት የተነገረለት እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ኢሳ. ፯፥፲፬)

ለ. ለእስራኤል መናን ያወረደው ነው። ይህ በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና የተወለደው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእስራኤል መና እያወረደ አርባ ዓመት ሙሉ በበረሃ እስራኤልን የመራው ነው። ነቢዩ ዳዊት “በልዑ ወጸግቡ ጥቀ ወኢያህጥዖሙ እምዘ ፈቀዱ፤ በሉ፤ እጅግም ጠገቡ፤ ለምኞታቸውም አላሳጣቸውም” ተብሎ የተናገረለት አምላክ ወልደ አምላክ በተዋሐደው ሥጋ ወረደ፤ ተሰደደ፤ ጾመ፤ ተራበ፤ ተሰቀለ፤ ሞተ፤ ተነሣ፣ ዐረገ እየተባለ ይነገርለታል። በቦታ የማይወሰን አምላክ ቦታ ተወሰነለትና ወረደ፤ ዐረገ እየተባለም ተነገረለት። ስለዚህ ይህ በክብር ዐረገ የተባለው ማን ነው? የሚል ሰው ካለ ጥንት እስራኤልን በበረሃ መና እያወረደ ሲመግብ የኖረው ዛሬም ለዘወትርም መግቦቱ ለዐይን ጥቅሻ ያህል እንኳን የማያቋርጠው እግዚአብሔር ወልድ ነው። (መዝ.፸፯፥፳፱)

ሐ. “ውእቱኬ ዘአድኃና ለሶስና እምእደ ረበናት፤ ሶስናን ረበናት እጅ ያዳናት ነው።” በትንቢተ ዳንኤል ተጽፎ እንደምናገኘው ይህቺ ሶስና መልከ መልካም ባለትዳር ለትዳሯም ታማኝ ነበረች። ነገር ግን የአይሁድ መምህራን ከመልከ መልካምነቷ የተነሣ በዝሙት ተነደፉና ለፈቃደ ሥጋቸው ጠየቋት፤ እርሷ ደግሞ ከእነርሱ ኃላፊነትና ሥልጣን ይልቅ ለእግዚአብሔር መገዛት መረጠችና ምኞታቸውን ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆነችም። በዚህ ጊዜ እነርሱ አጥፍተው ደግሞ ወነጀሏትና “ከወንድ ጋር አግኝተናታል” ብለው በአይሀድ ሸንጎ አቆሟት፤ እርሷም ወደ እግዚአብሔር ጸለየች። የለመኑትን የማይነሣው የነገሩትን የማይረሳው አምላካችን እግዚአብሔር መላኩን ልኮ ከረበናቱ እጅ አዳናት።
ሊቁ ቅዱስ ያሬድም ብሉዩን ከሐዲስ አስማምቶ እየጠቀሰ በደመና ወደሰማይ ያረገው፣ ጥንት ጀምሮ ጥበቃው ያልተለየን፣ በዚህም ሶስናን ከረበናት እጅ ያዳነ አምላክ ወልደ አምልክ እንደሆነ ያስረዳናል። ሶስና በእግዚአብሔር በመታመኗ ምንም እንኳን መምህር በመሆናቸው ተሰሚነትን የሚያገኙ ቢመስላቸውም፣ እንዳሰቡትም በአይሁድ የፍርድ ሸንጎ ቢያቀርቧትም እርሷ ግን እውነተኛ ዳኛ እግዚአብሔር እንዳለ በማመን ዐይኗን ወደእግዚአብሔር አቀናች። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ቅሩብ እግዚአብሔር ለየዋሐነ ልብ፤ እግዚአብሔር በልባቸው የዋሐን ለሆኑ ቅርብ ነው” ብሎ እንደነገረ፤ በቅዱስ ወንጌልም ልበ ንጹሐን ብፁዓን ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና” ተብሎ እንደተጻፈው በንጹሕ ልብ እግዚአብሔርን ስለለመነች ከመጣባት መከራ አዳናት። (መዝ.፴፫፥፲፰)
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዓለ ዕርገትን 2 ጊዜ ታከብራለች:: አንዱ "ጥንተ በዓል": ሁለተኛው ደግሞ "የቀመር በዓል" ይሠኛል:: ጥንተ በዓል ማለት ጌታችን በትክክል ያረገበትን ቀን ያመለክታል::

የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በኪነ ጥበቡ (በሕማሙ: በሞቱ) ዓለምን አድኖ: 40 ቀን ለሐዋርያቱ መጽሐፈ ኪዳንን: ትምሕርተ ኅቡዓትን አስተምሯቸዋል::

በ40ኛው ቀን 120ውን ቤተሰብ ይዟቸው ወደ ቢታንያ ወጣ:: በዚያም እስከ ሊቀ ዽዽስና ድረስ ሾሟቸው: ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡም አዟቸው የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ጠብቁ ብሏቸዋል:: እየባረካቸው በተዋሐደው ሥጋ ወደ ሰማያዊ ዙፋኑ አርጉዋል::

ሰማያት: ምድር: ደመናት: ነፋሳት: መባርቅትና መላእክት: ፍጥረት በሙሉ አመስግኗል:: አይሁድ መናፍቃን እርገቱን ምትሐት ነው እንዳይሉ: ጌታችን ትንሳኤውን አማናዊ እንደሆነ ለማስረዳት በ40ኛው ቀን ዐረገ::

አንድም ራስ ባለበት ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሊኖሩ ይገባልና ጌታችን ዕርገቱን በገሃድ አደረገው:: "ዐርገ እግዚእ ከመ ያለቡ ዕርገተ ጻድቃን ንጹሐን" እንዲል::

(መዝ. 46:6)

" እስከ ቢታንያም አወጣቸው:: እጆቹንም አንስቶ ባረካቸው:: ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ:: ወደ ሰማይም ዐረገ:: እነርሱም ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ:: ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ:: " (ሉቃ. 24:50-53)

ከበረከተ ዕርገቱ ይክፈለን::

የእግዚአብሔር አምላካዊ ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሁሉ ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን።

Address

South Gondar
Debre Tabor
21

Telephone

+917289061214

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Debre Enku Weybla Maryam Sunday School posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share