16/09/2026
የባህርዳር-ደሴ ካቶሊክ ጽ/ቤት ሰራተኞች የ2019 ዓ.ም የአዲስ አመት የስራ መክፈቻ እና ያለፈው አመት የስራ ግምገማ የጋራ መድረክ ተካሄደ፤
ባህርዳር መስከረም 05/2019 ዓ.ም
በባህርዳር-ደሴ ሰበካ የካቶሊክ ጽ/ቤት ሰራተኞች የ2019 ዓ.ም የጋራ መድረክ ከሰበካው ጽ/ቤት ሰራተኞች ጋር ተካሄደ።
የመድረኩን መርሃ ግብር የባህርዳር-ደሴ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ልሳነክርስቶስ ማቴዎስ በጸሎት በመክፈት መርሃ ግብሩ እንዲጀምር አድርገዋል።
የጋራ መድረኩ ዋና ዓላማ በ2018 ዓ.ም የተከናወኑ ሥራዎችን፣ የተገኙ ውጤቶችን፣ ያጋጠሙ ችግሮችንና የተገኙ ሰኬቶችን በመገምገም ለ2019 ዓ.ም የተሻለ የሥራ አፈጻጸም አቅጣጫ ማስቀመጥ ነበር።
በተጨማሪም ሰራተኞች የሥራ ልምዳቸውን እንዲለዋወጡ፣ የተሻለ የትብብር የሥራ ባህል እንዲገነቡ እና ከአዳዲስ የጽ/ቤቱ ሰራተኞች ጋር እንዲተዋወቁ ዕድል ፈጥሯል።
በመድረኩ ላይ የሰበካው ጽ/ቤት ዳይሬክተር ክቡር አባ ስንታየሁ ገላው በ2018 ዓ.ም በጽ/ቤቱ የተከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎችን አቅርበዋል። በተጨማሪም የ2019 ዓ.ም የሥራ አቅጣጫዎችን በማስረዳት የጽ/ቤቱን ራዕይና ተልዕኮ ለሰራተኞች ገለጻ አድርገዋል።
በሌላ በኩል በካቶሊክ ማኅበራዊ ትምህርት (Catholic Social Teaching – CST) ዙሪያ ገለጻ ተደርጓል። በሥራ ቦታ የካቶሊክ ማኅበራዊ ትምህርት ያለው ተግባራዊ ትርጉም፣ ሰራተኞች በሙያቸው ለማኅበረሰቡ ሊያበረክቱ የሚችሉት አስተዋጽኦ፣ እንዲሁም በሥራ ቦታ ፍትሃዊነትን፣ ክብርንና አገልግሎትን ማስፈን ስለሚቻልበት መንገድ ተብራርቷል።
የጽ/ቤቱ የፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ደጀን ይግዛው በበኩላቸው በሰበካው ስለሚከናወኑ የልማትና የፕሮጀክት ሥራዎች ሰፊ ገለጻ አድርገዋል።
በገለጻቸውም በሰበካው በተለያዩ አካባቢዎች ስለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች፣ የምግብ ዋስትና ፕሮጀክቶች፣ የውሃ፣ የሶላር ኃይልና የመጸዳጃ ቤት ፕሮጀክቶች እንዲሁም ሌሎች የልማት ሥራዎች በመጥቀስ በ2018 ዓ.ም የተገኙ ውጤቶችን አብራርተዋል።
በተለይም በአማራ ክልልና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በልማት ዘርፍ የተከናወኑ ሥራዎችን በማስታወስ ለተጠቃሚዎች ስለተደረጉ ድጋፎችና ስለተፈጠሩ የልማት ዕድሎች አብራርተዋል።
እንዲሁም የአቅም ግንባታ (Capacity Building) ሥራዎች በሀገረ ስብከቱ በሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ ስላላቸው ሚና በማብራራት የሰራተኞችን አቅምና የሥራ አፈጻጸም በማጠናከር የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ገልጸዋል።
አቶ ደጀን በተጨማሪም በ2018 ዓ.ም በሥራ ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመጥቀስ በተለይም ከሰራተኞች የሥራ ጫናና ከተለያዩ የሥራ አካባቢ ተግዳሮቶች ጋር በተያያዘ ለ2019 ዓ.ም የተሻለ የሥራ አቅጣጫ መያዝ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በመድረኩ የሥራ ሥነ-ምግባር (Work Ethics) የቡድን ሥራ (Teamwork) እና ጤናማ የሥራ ባህል አስፈላጊነትም በወንድም አቦነህ ተነስቷል። ሰራተኞች በጋራ በመስራት እርስ በርሳቸው በመደጋገፍና በተጠያቂነት መንፈስ በመስራት የሰበካውን ተልዕኮ ለማሳካት ያላቸውን ሚና ማጠናከር እንደሚገባ ተገልጿል።
በመጨረሻም በ2018 ዓ.ም ለተከናወኑ ሥራዎች ሰራተኞች ያበረከቱት አስተዋጽኦ በማድነቅ በ2019 ዓ.ም በተሻለ ትብብር፣ በተጠያቂነትና በትጋት እንዲሰሩ የሚያበረታቱ መልዕክቶችና ምስጋናዎች ቀርበዋል።
የጋራ መድረኩም በብፁዕነታቸው በቀረበ ጸሎትና ቡራኬ ተጠናቋል።
መስከረም 05/2019 ዓ.ም.
© የባህር ዳር–ደሴ ሃገረ ስብከት ኮሚኒኬሽን ቢሮ
ለበለጠ መረጃ የባህር ዳር–ደሴ ሀገረ ስብከት የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችን ይጎብኙ።
X (Twitter): https://x.com/Bahirdardessie
Instagram: https://www.instagram.com/ebdcs2025
TikTok: https://www.tiktok.com/
YouTube: https://youtube.com/