Let us discuss what Orthodox Christianity is

Let us discuss what Orthodox Christianity is ስለ ኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ እምነትና ታሪክ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃና ? የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ከ ዶግማዋን ፣ ቀኖናዋንና ትውፊቷን መሠረት ያደረጉ መንፈሳዊ ጽሑፎች ይቀረቡበታል

18/06/2015

ሒዱ እንጂ ተቀመጡ አልተባልንም (ክፍል አንድ)

በዲ/ን ዳንኤል ክብረት

(this preaching is taken from 'MEQIREZE TEWAHIDO" WEB PAGE)
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ይህ ጽሑፍ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ማኅበረ ቅዱሳን ሰኔ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ወደ ቡኢ ደብረ ሰላም በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ባዘጋጀው የበእንተ ወንጌል መርሐ ግብር ላይ ያስተማረው ትምህርት ነው፡፡ ስብከቱ አንድ ሰዓት ከዐሥር ደቂቃ የሚፈጅ ስለኾነ ወደ ጽሑፍ ሲቀየር ትንሽ በዛ ይላል፡፡ በመኾኑም በኹለት ክፍል እንዳቀርበው ተገድጃለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዲ/ን ዳንኤል ሲሰብክም የሚያነብ ስለሚመስል ብዙ የሚደጋገሙ ዐረፍተ ነገሮችን ስለሌሉበት፥ ያስተካከልኩት ነገር ቢኖር በጉባኤው ላልነበረ ሰው የማይረዱ ጥቃቅን ስንኞችን ብቻ ነው፡፡ ስለ ኹሉም መልካም መልካም ንባብ ይኹንላችሁ!!!

ይህንን ቃል የተናገረው ከዛሬ 700 ዓመት በፊት በደቡብ እስከ ባሌ ድረስ ተዘዋውሮ ያስተማረው፣ ለስብከተ ወንጌል ሲል ሕይወቱን የገበረው፣ በኋላም በቤተ ክርስቲያኒቱ ትልቅ ፍሬ ያፈራው፣ የታላቁ ጻድቅ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ፍሬዎች ከኾኑት ከ12ቱ መምህራነ ወንጌል አንዱ የኾነው ታላቁ አኖሬዎስ ነው፡፡ ቅዱስ አኖሬዎስ በባሌ፣ በምዕራብ ሸዋ ኹለት ታላላቅ ገዳማት ነበሩት፡፡ ኹለቱም በ16ኛ መ.ክ.ዘ. መጀመሪያ አጋማሽ ላይ ግራኝ አገሪቱን ባጠፋበት ጊዜ እንደጠፉ እስከ አሁን አልተመለሱም፡፡ አንዱ ገዳሙ ብቻ በደቡብ ወሎ ከደሴ ከተማ 12 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
ይኼ ታላቅ ሐዋርያ በደቡብ ኢትዮጵያ ታላቅ ሥራ ከሠሩት 12ቱ መምህራን አንዱ ነው፡፡ እየተዘዋወረ ሲያስተምር በወቅቱ የአከባቢው ገዢ የነበረና ገና ክርስትናን ያልተቀበለ አገረ ገዢው አስጠርቶ፡- “በእኔ አገር እኔ ሳልፈቅድልህ እኔ የማላውቀውን አዲስ ሃይማኖት ለምን ታስተምራለህ? አንተንስ እዚህ ቦታ ምን አመጣህ?” ብሎ በጠየቀው ጊዜ፡- “ገና እስከማናውቃቸው ቦታዎች ድረስ እንሔዳለን፡፡ በእግዚአብሔር ጉባኤ አንድ የኾንነውን፥ ነገር ግን እኛ በአካል ያላወቅናቸው ወንድሞቻችንን እስክናውቅ ድረስ አንደክምም፡፡ የእግዚአብሔር አገር ሰፊ ነው፡፡ የእግዚአብሔር አገር እስኪያልቅ ድረስ አገልግሎታችን አያልቅም” አለው፡፡ አገረ ገዢውም፡- “ለምን አንድ ቦታ ተቀምጠህ አትሠራም? አገሩን እየዞርክ ለምን ትረብሻለህ?” ብሎ ሲጠይቀው “እኛ’ኮ ሒዱ እንጂ ተቀመጡ አልተባልንም” አለው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዋና ፍሬ ነገርም ይኼው ነው፤ መሔድ፡፡
ለዐሥራ ኹለቱ የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት የተሰጠው ስያሜም ከመሔድ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሐዋርያ ማለት ሒያጅ ማለት ነው፡፡ በሐዋርያነት አገልግሎት ትልቁና የመጀመሪያው ሥራ መሔድ ነው፡፡ ከሚያውቁት ወደማያውቁት፣ ከተከበሩበት ወዳልተከበሩበት፣ በባሕል፡ በቋንቋ፡ በሐሳብ ከሚግባቡት ወደማይግባቡት፣ ከቅርቡ ወደ ሩቁ መሔድ ነው፤ ሐዋርያነት፡፡ ጌታችንም ከማረጉ በፊት ለሐዋርያት ኹለት ትእዛዛት ሰጥጻቸው ነበር፡፡ አንዱ በሐዋርያት ሥራ 1፡8 ላይ የተመዘገበ ሲኾን ኹለተኛውም “ሒዱና በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ኹሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚል ነው /ማቴ.28፡20/፡፡ ሦስት ኃላፊነቶችን ነው የተሰጣቸው፡፡ የመጀመሪያው መሔድ ነው፤ ኹለተኛው ማስተማር ነው፤ ሦስተኛው ተምረው ያመኑትን አጥምቆ ደቀ መዝሙር ማድረግ ነው፡፡ በዚሁ የወንጌል ሐሳብ መሠረት ደቀ መዝሙር ማድረግ ማለት ክርስቲያን ማድረግ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ደቀ መዛሙርት በኋላ “መጀመሪያ በአንጾክያ ክርስቲያን ተባሉ” ይላልና /ሐዋ.11፡26/፡፡
ደቀ መዝሙር ማድረግ ክርስቲያን ማድረግ ነው፡፡ የመጀመሪያው ትእዛዛቸው ግን ሒዱ ነው የተባሉት፡፡ “በዚህ በኢየሩሳሌም፣ በምታውቁት ቦታ፣ በለመዳችሁት ቦታ፣ ዓሣ ስታደምጡበት በኖራችሁት ቦታ፣ ቋንቋዉን ባሕሉን በምታውቁት ቦታ፣ ብዙ ዘመዶች፡ ብዙ ወዳጆች ባልዋችሁ ቦታ እንዳትቀመጡ፤ ሒዱ” ነው የተባሉት፡፡ እንዲያውም በቅዱስ እስጢፋኖስ ላይ የመጀመሪያው ሰማዕትነት ሲደርስና ሐዋርያት በየቦታው ሲበተኑ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት “ሒዱና ዓለምን በሙሉ አስተምሩ” የተባሉት ሐዋርያት እንዴት እንደሚኬድ ስለማያውቁትና ለመንገዱም አዲስ ስለነበሩ በዚያች በኢየሩሳሌም ከተማ አንዲት ማኅበር መሥርተው ለ7000 ማኅበረ እስጢፋኖስ ተቀምጠው ነበር፡፡ ከመላው ዓለም የመጡ አይሁድ፣ በኢየሩሳሌም የነበሩትም አይሁድ አንድ ኾነው እዚያ ነበሩ፡፡ ለብዙ ቀናትም እዛ ተቀመጡ፡፡ በመጨረሻ ግን ቅዱስ እስጢፋኖስ በሰማዕትነት ሲያርፍና በቤተ ክርስቲያን ላይ ፈተና ሲመጣ ኹሉም በየመንገዳቸው ወንጌልን እያስተማሩ ሔዱ፤ ተበተኑ /ሐዋ.8/፡፡ ከኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳሱ ከቅዱስ ያዕቆብ በስተቀር ኹሉም ተበተኑ፡፡ ሐዋርያት ብቻ ሳይኾኑ በዛች በማኅበረ ቅዱስ እስጢፋኖስ አማካኝነት የተማሩት ሌሎች ምእመናንም ጭምር አገሪቱን ትተው በሔዱበት ጊዜ በየመንገዳቸው ወንጌልን እያስተማሩ ነው የሔዱት፡፡ ይኼ የሚነግረን የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እኔና እናንተም የተጠራንበት አገልግሎት መሔድ መኾኑን ነው፡፡ ታላቁ አኖሬዎስም “ሒዱ እንጂ ተቀመጡ አልተባልንም” ነው ያለው፡፡
“እንዴት ነው የምንሔደው?” የሚለውን ደግሞ ጌታችን ከማረጉ ከጥቂት ሰዓታት በፊት በሐዋ.1፡8 ጀምሮ ነግሯቸዋል፡፡ “ሒዱና አስተምሩ ብለኸናል፤ መሔድ ግን ምንድነው? እንዲሁ ዝም ብሎ መሄድ ነውን?” የሚለው የሐዋርያት ጥያቄ ነበርና፡፡ ለዚህ ጌታችን መሠረቱን መሥርቶላቸዋል፡፡ “በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያ፣ እስከ ዓለም ዳርቻ ምስክሮቼ ትኾናላችሁ” በማለት፡፡ ይኼን ምስክርነት በአራት ደረጃ በአራት ምዕራፍ ከፍሎ ነው የነገራቸው፡፡ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያ፣ እስከ ዓለም ዳርቻ በማለት፡፡ በአንድ ጊዜ ወደ ዓለም ዳርቻ እንዲሔዱ አልነገራቸውም፡፡ በእነዚህ በአራቱ ደረጃዎች ግን እስከ መጨረሻው እስከ ዓም ዳርቻ ድረስ እንዲሔዱ ነግሯቸዋል፡፡ እስኪ አንድ በአንድ እንመልከታቸው፡፡

በኢየሩሳሌም ማለት ምንድነው?

ኢየሩሳሌም ከኦሪት ዘመን ጀምሮ የምትታወቅ የሰላም ከተማ ተብላ የተጠራች ከተማ ናት፡፡ ቤተ መቅደሱም ቤተ መንግሥቱም የነበረባት ከተማ ናት፡፡ የዳዊትና የሰለሞን ከተማ ናት፡፡ የመልከ ጼዴቅ ከተማ ናት፡፡ በክርስትና ደግሞ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቁን የማዳን ሥራ የፈጸመበት (የፈተረደበት፣ የተገረፈበት፣ የተሰቀለበት፣ የሞተበት፣ ከሙታን የተነሣበት፣ ያረገበትና መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት የላከበት) ሥፍራ ነው፡፡ የመጀመሪያዋም ቤተ ክርስቲያን (ጉባኤ ምእመናን፣ ጉባኤ ካህናት) የተመሠረተባት ቦታ ናት፡፡ ለቅዱሳት ቦታዎች (ለጎልጎታ፣ ለደብረ ዘይት) በጣም ቅርብ ቦታ ናት፡፡ ሐዋርያትም የነበሩት፣ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉት፣ አገልግሎታቸውንም የጀመሩት በኢየሩሳሌም ነው፡፡ በኢየሩሳሌም የጀመሩት አገልግሎት ግን በኢየሩሳሌም እንዲጨርሱት አይደለም የታዘዙት፡፡ በዓለም ዳርቻ እንዲጨርሱት ነው የታዘዙት፡፡
ኢየሩሳሌም በዚያን ጊዜ ለክርስትናው ምቹ ናት፡፡ ቢያንስ ብዙ ክርስቲያኖች አሏት፡፡ በቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት ያመኑት 3,000 ምእመናን ተጨምረዋል፡፡ ጌታችን መነሣቱን፣ ማረጉን የሚያውቁ ሌሎች ምእመናን አሉ፡፡ ማረፊያቸው ማለትም የማርያም ቤት እዚያ ነው ያለው፡፡ ጸሎት ለማድረግ የጌታችን መቃብር ቅርብ ነው፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ቅዱሳን ሐዋርያት በበዓለ ጰራቅሊጦስ መንፈስ ቅዱስ ወርዶላቸው በ72 ቋንቋ ሲናገሩ ያዩ የሰሙ ምስክሮች አሉ፡፡ ስለዚህ ይኼ ቦታ ምቹ ነው፡፡ በዚህ ነው ስምሪቱን እንዲጀመር ጌታችን ያዘዘው፡፡
ኢየሩሳሌም ምንድነው? ኢየሩሳሌም ቤተሰብ ነው፡፡ የስብከተ ወንጌል ስምሪት የሚጀመረው ከቤተሰብ ነው፡፡ የመጀመሪያው ጉባኤ፣ የመጀመሪያው የወንጌል አገልግሎት፣ የመጀመሪያው ትምህርት መሰጠት ያለበት ከባል፣ ከሚስት፣ ከልጆች ነው፤ ከቤተሰብ፡፡ አሁን ብዙዎቻችን በሰርክ ጉባኤ፣ እንደ በእንተ ወንጌልና ሐዊረ ሕይወት ባሉ ጉባኤያት፣ በየገዳማቱ በሚደረጉ ጉዞዎች ልናገኘው የምንሞክረውን ትምህርት በዛ አልነበረም ማግኘት የነበረብን፡፡ ከቤት ውስጥ ነበር ማግኘት የነበረብን፡፡ ይኼኛው (የሰርኩና የሌላው ጉባኤ) ያገኘነውን የምንሠራበት፣ የምናጠናክርበት፤ “ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም” እንደተባለ ወንጌል ምግብም ስለኾነ ይበልጥ የምንመገብበት እንጂ አዲስ ዕውቀት፣ መሠረታዊ ትምህርት የምናገኝበት አልነበረም መኾን የነበረበት፡፡ እንዲህ እየኾነ ያለው በኢየሩሳሌም አገልግሎት ስለሌለ ነው እንጂ፡፡ ከቤት ነበር መማር የነበረብን፡፡
ይኼንን ኹላችንም ከምናውቀው አንድ ታሪክ ምሳሌነት እንይ፡፡ ከታላቁ ኢትዮጵያዊው ሐዋርያ ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፥ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ኾነው እንዲወጡ ያደረጋቸው አንዱ መሠረት በቤታቸው ያገኙት ትምህርት ነው፡፡ ገድላቸው እንደሚነግረን በሰባት ዓመታቸው ነው አባታቸው ቁጭ አድርገው ከመዝሙረ ዳዊት ጀምረው ከዚያም ብሉይንና ሐዲስን ሌሎችንም የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት ጭምር ያስተማሯቸው፡፡ እስኪ ስንቶቻችን ነን በቤታችን ብሉይንና ሐዲስን ያለን? ስንቶቻችን ነን በቤታችን መጽሐፍ ቅዱስ የሚነበብልን ወይም የምናነብ? በስንቶቻችን ቤት ስንክሳር ይነበባል? በስንቶቻችን ቤት ገድለ ቅዱሳን ይነበባል? እዛ ስላልለመድነው ነው’ኮ ከፍ ስንል በቅዱሳት ገድላት ላይ ጥያቄ የምናነሣው፡፡ እንግዳ ትምህርት የሚመስለን ገና ከቤታችን ስላልለመድነው ነው፡፡
ለምንድነው እንጀራ ላይ ጥያቄ የማይነሣብን? ብዙዎቻችን በእንጀራ ላይ ጥያቄ የለብንም፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ እንጀራ ላይ ጥያቄ የለውም፡፡ እንደዉም አንድ ሰው ወደ ውጪ ሲሔድ ለመጀመሪያ ከቤተሰብ ላኩልኝ የሚለው እንጀራ ድርቆሽ ነው፡፡ ብዙ ነገር ይረሳል፤ እንጀራንና ሽሮን ግን አይረሳም፡፡ ለምን? ከሕፃንነታችን ጀምሮ፣ አንዳንዶቹ ሱስ ኾነባቸዋል እስኪሉን ድረስ ለእንጀራ ልዩ ፍቅር ያለን ስለ ምንም ምክንያት አይደለም፡፡ እንጀራ ውስጥ ምን ዓይነት ማዕድን እንዳለ እንኳን ያወቅነው በኋላ ነው፡፡ ለእንጀራ ልዩ ፍቅር ያለን እናቶቻችን፣ አባቶቻችን ከልጅነታችን አንሥተው ያጎረሱን ርሱ ስለኾነ ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲህ ከቤተሰብ ጀምረን ተምረን ቢኾን በኋላ እንግዶች አንኾንም ነበር፡፡ ለጥቅስ እንግዶች አንኾንም ነበር፡፡ ለስንክሳር፣ ለገድለ ቅዱሳን፣ ለቅዳሴው እንግዶች አንኾንም ነበር፡፡
(ጸጋ ዘአብ) አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በሰባት ዓመታቸው ነው ብሉይንና ሐዲስን ሌሎችንም ቅዱሳት መጻሕፍት ጨምረው ያስተማሯቸው፡፡ በዛ ሰዓት ነው ትምህርት መጀመር የነበረበት፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት’ኮ “አንድ ልጅ ሰባት ዓመት ሲሞላው ጾም ይጀምራል” የሚባለውም ዝም ብሎ አይደለም፡፡ ትምህርቱም አብሮ ስለሚጀምር ነው፡፡ ትምህርቱም ከጾም፣ ከጸሎት ጋር መኾን ስላለበት ጭምር ነው፡፡ ያ የሰባት ዓመት ዕድሜ ቅዱሳት መጻሕፍትን የሚማርበት፣ በኢየሩሳሌም የሚሰጠውን የወንጌል አገልግሎት የሚጀምርበት ዕድሜ ነው፡፡
ዛሬ ይህን ጽሑፍ የምናነብ ቤተሰቦች ይህን ይዘን መሔድ አለብን፡፡ “ለማስተማር የሚችል ዕውቀት የለንም” ብንል እንኳን በየቤታችን ቅዱሳት መጻሕፍትን አምጥተን እንደ ጥንቷ ቤተ ክርስቲያን እራት ከመበላቱ በፊት እንዲያነቡ ማድረግ እንችላለን፡፡ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን እራት ከመቅረቡ በፊት (ያውም እንደዛሬ መብራት ሳይኖር) እሳት እየነደደ ወይም ደግሞ ሌሎች በእሳት የሚሠሩ መብራቶች እየነደዱ ልጆች ተነሥተው፣ ልጆች እስኪደርሱ ድረስ ደግሞ የተመደበ ካህን ወይም ዲያቆን ወይም መሪጌታ መጥቶ እዚያ ቤት ውስጥ ወይም ደግሞ በቤተ ክርስቲያናችን ዛሬ የቆሎ ተማሪዎች የምንላቸው የአብነት ተማሪዎች በየቦታው ሲሰማሩ አንዱ ሥራቸው ይኼ ነበር፡፡ እዚያ ቤት ተጠግቶ፣ ምግብ እየተሰጠው፣ እየተማረ፣ ለቤተሰቡ ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍትን እያነበበ፡፡ እራት ከመበላቱ በፊት ገድለ ቅዱሳን፣ ስንክሳር ተነቦ ነው እራት የሚበላው፡፡

በባሕላችን አንድ አባባል አለ፤ “እራትና መብራት አይንሳን” የሚል፡፡ ኢትዮጵያውያን ምሳ ስለማይበሉ ነውን? ቁርስ ይንሳን ማለታቸው ነውን? ለምድነው እራት ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ለምንድነው? እራትና መብራት የተባለው ባሕላችን የገበሬው ባሕል ነው፡፡ ገበሬው ሲሠራ ነው የሚውለው፡፡ ምሳ የሚባለው በየዋለበት ሥፍራ ነው፡፡ የሚያጭደውም አጨዳ ቦታ፤ የሚያርሰውም እርሻ ቦታ፤ የሚነግደውም የንግዱ ቦታ ነው የሚበላው፡፡ ቤተ ሰብ የሚሰበሰበው እራት ላይ ነው፡፡ ከብት የያዘውም ከብቱን ይዞ ይመጣል፤ አራሹም ከግብርናው ይመለሳል፤ ቤት የዋለውም የቤት ሥራውን ጨርሶ ይጠብቃል፡፡ በኢትዮጵያውያን ባሕል እራት ትልቅ ነው፡፡ ከምግብነት ያለፈ የቤተሰቡን አንድነት የሚያስረዳ ነው፡፡
ይኼ የእኛ ባሕል ብቻ አይደለም፡፡ በባሕል የምንዛመዳቸው ሌሎች ምሥራቃውያንም ከምሳና ከቁርስ በላይ ትልቁ ትኩረታቸው እራት ነው፡፡ ጌታችንም በምሴተ ሐሙስ ሥጋዉንና ደሙን ለሐዋርያት የሰጠው በቁርስ አይደለም፤ በምሳ ሰዓት አይደለም፤ በእራት ነው፡፡ “የመጨረሻው እራት” የምንለውም ለዚያ ነው፡፡
እራት በእኛ ባሕል ትልቅ ቦታ አለው፡፡ የቤተሰቡ መሰብሰቢያ ነው፡፡ በዚያ ሰዓት ነው ቅዱሳት መጻሕፍት ይነበቡ የነበሩት፡፡ ዛሬ ይኼ ቤተሰብ ስለጠፋ ነው ብዙዎቻችን እያወቅነው፣ ፍቅሩ እያለን፣ እየወደድን መልስ ያጣነው፡፡ እመቤታችንን ማመን፣ ስለ እመቤታችን መቆርቆር፣ የእመቤታችን ስም ሲነሣ ደማችን እንዴት እንደሚሞቅ ኹላችንም እናውቋለን፡፡ ይኼንን የሚቃወሙ ሰዎች ኹለትና ሦስት ነገር ይዘው ሲመጡ ግን የሚኾን መልስ ያጣነው ፍቅሩ ጠፍቶብን አይደለም፡፡ ይኼ የቤተሰብ ማለትም ኢየሩሳሌም ውስጥ መሰጠት የነበረበት የወንጌል አገልግሎት ስለተቋረጠ ነው፡፡
ይህቺ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሳ 40 እና 50 ሚልዮን ሕዝብ የሰበሰበችው እንዲህ እኛ እንደምናደርገው ዓይነት ጉባኤ አዘጋጅታ አይደለም፡፡ በቤተሰብ የሚያስተምሩ መምህራን ስለነበሯት ነው፡፡ የሌሎች ቅዱሳንንም ታሪክ ብናይ እንደዚህ ነው፡፡
(ጸጋ ዘአብ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን) እስከ 15 ዓመታቸው ድረስ ለ8 ዓመታት ያህል ቅዱሳት መጻሕፍትን አስተምረው ነው ወደ ሊቀ ጳጳሱ የወሰዷቸው፡፡ “አሁን አውቀሃል፤ አሁን ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል አለብህ” ብለው የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ያፈሩት ራሳቸው ጸጋ ዘአብ ናቸው፡፡ ዛሬ ለቤተ ክርስቲያን ይህን የሚያፈራ ቤተሰብ አለን ወይ? “ልጄ መማር አለበት፤ ማወቅ አለበት፤ ነገ ወጥተህ መድረክ ላይ ወንጌል የምታስተምረው አንተ ነህ፤ ነገ ዲያቆን ካህን ጳጳስ ኾነህ የምታገለግለው አንተ ነህ፤ ነገ በገዳማት ገብተህ መናኝ መነኮሴ የምትኾነው አንተ ነህ፤ ነገ በየመሥሪያ ቤትህ ቁጭ ብለህ የቢሮ ሥራህን ስትሠራ የሃይማኖት ጉዳይ ሲመጣ ልክ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የምትመሰክረው አንተ ነህ” የምንል አለን ወይ?
ቅዱስ ጊዮርጊስኮ አባቱ ከልጅነቱ አንሥቶ አስተምሮ ስላሳደገው ነው የአባቱን መንግሥት ልረከብ ብሎ ሲሔድ ሰባዎቹ ነገሥታት እግዚአብሔር ላይ ሲያላግጡና ጣዖታትን ሲያመልኩ ሲያይ “አይ! ይኼን መንግሥት ተቀብዬ’ማ ሃይማኖቴን አልተውም” ብሎ ምስክርነትን መስጠት የጀመረው፡፡ ለምንድነው ዛሬ የቢሮ ሠራተኛው፣ የጥበቃ ሠራተኛው፣ ፖሊሱ፣ ዳኛው፣ ሹፌሩ፣ ፓይለቱ፣ ራዳቱ፣ ነጋዴው ምስክር መኾን ያቃተን? ፍላጎቱ ስለሌለን ነውን? አይደለም፡፡ ፍቅሩ ስለሌለን ነውን? አይደለም፡፡ ግን አልሠለጠንም፡፡
“አይ እዚ ጋር እንኳን ቀይ መስመር አለ” ነው ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ፡፡ “እዚህ ድረስ የአባቴን መንግሥት ለመውሰድ መጥቻለሁ፡፡ ከዚህ በላይ ግን ቀይ መስመር ይሰመራል፡፡” ክርስትና ይኼ ነው የሚፈልገው፤ ከዚህም በላይ፡፡ (ይህን) የሚል ነጋዴ፣ የሚል ባለሥልጣን፣ የሚል ምሁር፣ የሚል ሳይንቲስት ማፍራት የሚቻለው በቤተሰብ ውስጥ በሚሰጥ ትምህርት ነው፡፡ እኛ ቢያልፈን እንኳን፣ ዛሬ ይህን ጽሑፍ የምናነብ ሰዎች አልፎናል ብለን ብንጸጸት እንኳን ብዙዎቻችን ግን እንዳያልፋቸው ማድረግ አያቅተንም፡፡
ከዛ ነው መጀመር ያለበት፡፡ ሕፃናት ላይ ይበልጥ መሠረታችንን መመሥራት ያለብን፡፡ ሕፃናትን ነው ማነፅ ያለብን፡፡ እነርሱ በሚገባ ከተማሩ ጉባኤያት ባይደረግ እንኳን፣ ማይክሮፎን ባይተከል እንኳን፣ አዳራሾች ባይዘጋጁ እንኳን ምንም ጉዳት የለውም፡፡ ምንም ጉዳት የለውም!!!
እስኪ አስቡት! ሰንበቴው፣ ጽዋው፣ የቅዳሴ ሥነ ሥርዓቱ፣ የንግሥ ሥነ ሥርዓቱ ባይኖር ኖሮ በእኛ ስንፍና ምንድን ነበር የምንኾነው? የበእንተ ወንጌል ወይም የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ለማዘጋጀት ስንት ጊዜ ነው ማስታወቂያ የሚነገረው? ቁልቢ ገብርኤል ለመሔድ ግን ማስታወቂያ ያስፈልጋል? በነሐሴ 24 የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ንግሥ ለመሔድ ምንም ማስታወቂያ አያስፈልግም፡፡ መስከረም 21 ላይ ግሸን ለመሔድ ምንም ማስታወቂያ አያስፈልግም፡፡ ባይኾን “በዚህ ቦታ ተመዝገቡ” ለማለት ካልኾነ በስተቀር እንጂ ያን ቀን የግሸን በዓል እንደኾነ ኹሉም ያውቃል፡፡ ይህንን መሠረት ባይመሠርቱና በደማችን ውስጥ ባይተከል ኖሮ በየትኛው ኔትወርክ ነበር የምናመጣው? በየትኛው ማስታወቂያ ነበር ሰውን የምንሰበስበው? በየትኛው አሠራራችን ነበር ይህን የምናመጣው? ይህን ከታች ስለሠሩት ነው፡፡
በኢየሩሳሌም ማለት ይኼ ነው፡፡ ቤተሰብ ውስጥ ባልና ሚስት ሐዋርያ ኾነው ሲያስተምሩ ማለት ነው፡፡ እናትና አባት ለልጆቻቸው ሐዋርያ ሲኾኑ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለልጁ ለጢሞቴዎስ በጻፋቸው ኹለቱም መልእክቶቹ እየደጋገመ የሚናገረው ቃል አለ፡፡ የጢሞቴዎስ አያቱንና እናቱን ያነሣል፡፡ “ይህም እመነት ቀድሞ በኤትህ በሎይድ እናትህም በኤውንቄ ነበረባቸው፤ በአንተም ደግሞ እንዳለ ተረድቻለሁ” ብሎታል /2ኛ ጢሞ.1፡5/፡፡ ይኼስ ምንድነው የሚነግረን ቅዱስ ጢሞቴዎስ እንዲሁ የመጣ አይደለም፡፡ አያቱም እናቱም ያስተማሩት ትምህርት፣ በሕይወት አርአያ ኾነው ያሳዩት ሕይወት ነው በልቡ ውስጥ ያለው፡፡
ወላጆች መጾም ያለባቸው ለራሳቸው ብቻ አይደለም፡፡ የሚጾሙ ልጆች ማፍራት ከፈለግን የሚጾሙ ወላጆች መኖር አለባቸው፡፡ ወላጆች ቤት ውስጥ መጸለይ ያለባቸው ለራሳቸው ብቻ አይደለም፡፡ የሚጸልዩ ልጆች ማፍራት ከፈለግን የሚጸልዩ ወላጆች ማፍራት አለብን፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ልጆቹ አብረው የሚጾሙት፡፡ ከካህኑ በፊት እናትና አባታቸውን ነዋ ያወቁት! ከሰባኪው በፊት እናትና አባታቸውን ነዋ ያወቁት! ስለዚህ እናታቸው ስትጾም ይጾማሉ፡፡
ለምን ይመስላችኋል ብዙ ወጣቶች 14 እና 15 ዓመት ሲሞላቸው በልጅነታቸው በፍልሰታም በምንም ስናቆርባቸው የነበረውን ቁርባን የሚተዉት? ልጆች ኾነው እናመጣቸዋለን፡፡ 15 ዓመት ሲሞላቸው ግን እምቢ ይላሉ፡፡ ለምን? እኛ ስንቆርብ አላዩማ! ስለዚህ የማደግ ምልክቱ የሚመስላቸው ቁርባንን ማቆም ነው፡፡ ሰው ቁርባን ተወ ማለት አደገ ማለት ነው፡፡ ወላጆቻቸው ስላደጉ ነዋ የማይቆርቡት፡፡ እንደዉም በብዙ ቤተ ክርስቲያን “ቅዳሴ ማለት የማይቆርቡ ወላጆች የሚቆርቡ ልጆች የሚያቆርቡበት ነው፡፡” ወላጆች አይቆርቡም፤ ልጆች ግን ይቆርባሉ፡፡ ቅዳሴው ያልተማረ የሚያስተምርበት፤ ያልቆረበ የሚያቆርብበት ብቸኛ ቦታ ነው፡፡ እየቆረብን ቢኾን እነርሱም አብረው ይመጡና ይቆርቡ ነበር፡፡
ይኼ ነው የመጀመሪያው መሔድ ማለት፡፡ በቤተሰብ ውስጥ ነው መሔድ የሚጀመረው፡፡ ሰው’ኮ ዝም ብሎ ከኾነ ቦታ አይሔድም፡፡ አንድ ሰው ሒድ ቢባል ካለበት ነው የሚነሣው፡፡ መነሻችን ቤተሰብ ስለፈረሰ ነው ትልቁ ችግር፡፡ አሁን መመለስ ያለብን ወደዚህ ነው፡፡ በስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር ውስጥ መካተት ያለበት ይኸው ነው፡፡ ይህንን ጽሑፍ የምታነቡ የጽዋ ማኅበራት አላችሁ፤ ጉዞ ማኅበራት ውስጥ ያላችሁ አላችሁ፤ ሰንበቴው ውስጥ ያላችሁ አላችሁ፤ በተለያየ ማኅበራት ውስጥ ያላችሁ ሰዎች አላችሁ፡፡ ይህን ጽሑፍ አንብበን ስንጨርስ ማሰብ ያለብን ቤተሰብ ውስጥስ ምን እንሥራ? የሚል መኾን አለበት፡፡ እናት’ኮ ወደ ጉባኤ ትሔዳለች፤ ልጅ ግን አይሔድም፡፡ ባሎች ለብቻ ይሰበሰባሉ፤ ሚስቶች የሉም፡፡ አባቱ “ገብርኤል ነው” ብሎት ሲሔድ ነው እንጂ የሚያውቀው የት እንደሚሔድ አያውቅም፡፡ ለብቻው ነዋ የሔደው፡፡ እነርሱም ቤት ጽዋው ሲደረግ ለምን እየተደረገ እንደኾነ የሚነግረው ሰው የለም፡፡ እንደዉም ብዙ ልጆች ከቤታቸው ውስጥ የጽዋ መርሐ ግብር ሲደረግ፡- “እንግዶች ስለሚመጡ እንዳትበጠብጡ፤ ከዚህ ከመኝታ ቤት እንዳትወጡ፤ ውጭ ከኾናችሁም እንዳትገቡ፤ ድምጻችሁን እንዳታወጡ” ነው የሚባሉት፡፡ ቁጣው ነው የሚተርፋቸው፡፡ ስለዚህ ሌላ ነገር የተፈጠረ ነው የሚመስላቸው፡፡ “ዛሬ ቅዱስ ገብርኤልን ነው የምዘክረው፡፡ ዛሬ ተክለ ሃይማኖት ነው የምዘክረው፡፡ ዛሬ እመቤታችንን የምዘክርበት ምክንያት ይኼ ነው፡፡ አንተም ስታድግ ከእኔ ቀጥለህ ነው የምትሔደው፡፡ እንዲህ ብታደርጊ እንዲህ ነው” ብሎ የሚነግራቸው ሰው የለም፡፡
የብዙዎቹ በአዲስ አበባ ሰንበቴዎች ላይ የተደረገ ጥናት የሚነግረን ይኼ ነው፡፡ ከአጼ ምንሊክ ጀምሮ የተመሠረቱ ሰንበቴዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሥላሴ ካቴድራል አጠገብ ያለው የበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው ሰንበቴ ከ100 ዓመት በላይ ኾኖታል፡፡ እነዚህ ሰንበቴዎች ከፊታቸው የተጋረጠው አደጋ ሰንበቴውን የመሠረቱት ወላጆች ልጆቸ እየተተኩ አይደለም፡፡ በረከታቸው ይደርብንና ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልእ ይህን በተመለከተ ያስተማሩት ትልቁ ትምህርት፡- “ወደ ሰንበቴውና ወደ ጽዋው ጠላውን፣ ዳቦውን፣ ቆሎውን ይዛችሁ ስትሔዱ እናንተ አትያዙት፡፡ ጠላውን አንድ ልጅ፣ ዳቦውን አንድ ልጅ፣ቆሎውን አንድ ልጅ ተሸክሞ ይሒድ፡፡ ይግባ፤ ይይ፡፡ ይኼ የአንተ ሰንበቴ ነው፡፡ ነገ ትወርሷለህ በሉት” የሚል ነው፡፡ ይኼን ያደረገ ሰው ስለሌለ የሚወርሰው ታጣ፡፡
እኛ እንኳን ማንበብ ባንችል መጻሕፍቱን ገዝተንላቸው እንዲያነቡ የማናደርጋቸው ለምንድነው? በውድ ዋጋ ከፍለን ትምህርት ቤቶች ውስጥ የምናስተምራቸው ይኼንን ጭምር እንዲያነቡ አይደለም እንዴ? ፊዚክስና ኬሚስትሪ ብቻ እንዲያነቡ ነውን? ይኼንንም ጭምር እንዲያነቡ’ኮ ነው፡፡ ቆመው ማንበብ መልመድ አለባቸው፡፡ “ዛሬ አንተ ነህ ተረኛ፤ ዛሬ አንቺ ነሽ ተረኛ” ልንላቸው ይገባል፡፡ ኹለት፣ ሦስት ልጆች ባሉበት ቤት “አንተ የቅዱስ ሚካኤልን ትዘክራለህ፤ አንቺ ደግሞ እመቤታችንን ትዘክሪያለሽ፤ አንተ ደግሞ ተክለ ሃይማኖትን ትዘክራለህ፤ እኔ ደግሞ እገሌን እዘክራለሁ” ብለን ተካፍለን ካደረግን ልጆች ከልጅነታቸው አንሥቶ ፍቅረ ቅዱሳን ያድርባቸዋል፡፡ ይጠይቃሉ፡፡ “ለምንድነው በ24 ተክለ ሃይማኖት የኾነው?” ይላሉ፡፡ ይረዳሉ፡፡ “ለምንድነው ግን የቅዱስ ሚካኤል በዓል በ12 የሚውለው?” ይላሉ፡፡ ይረዳሉ፡፡ ማስረዳት ከቻልን ማስረዳት፡፡ ማስረዳት ካልቻልን ደግሞ “ይኼው መጽሐፉ አንብብ፤ እንደውም አንብብና ለኹላችንም ትነግረናለህ” እያልን ልናሳድጋቸው ይገባል፡፡ ሃይማኖታቸውን መመስከር፣ ስለ ቅዱሳን መናገር፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን መናገር በእናትና በአባታቸው ፊት ይለምዳሉ፡፡ ነገ ትምህርት ቤት ቢሔዱ፣ ሌላ ትልቅ ቦታም ቢሔዱ ስለ ሃይማኖታቸው በየጉባኤው፣ በየወርክሾፑ፣ በየሚድያው የማይኾን ነገር ሲነገራቸው ዝም አይሉም፡፡ “አይ! እዚህ ጋር ሐሳብ አለኝ፡፡ ይኼ ትክክል አይደለም፡፡ ይኼ ሥርዓት አይደለም፡፡ በእኛ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ አይደለም፡፡ አንተ እንደምትለው አይደለም!” ብለው የሚከራከሩ ሰዎች ይኾናሉ፡፡

ይኼ ስለጠፋ ነው ዛሬ ብዙ ቦታ ላይ የቤተ ክርስቲያን ስም ሲጠፋ እንኳን እያወቅነው፣ እየተናደድን፣ ፀጉራችንን እየነጨን ዝም የምንለው፡፡ “እንደው እግዚአብሔር ያሳይህ” እያልን እየረገምን ዝም የምንውለው ለዚሁ ነው፡፡
ኢየሩሳሌም ማለት ግን ይኼ ነው፡፡ በምታውቁት ቦታ፣ ስለ እኔ መናገር በማይቸግራችሁ ቦታ ጀምሩ ማለት ነው፡፡ ለሐዋርያት ከይሁዳ፣ ከሰማርያ፣ ከዓለም ዳርቻ ይልቅ በኢየሩሳሌም መመስከር ቀላል ነበር፡፡ ምስክር አለ፤ ማስረጃ አለ፤ ቦታው እዛው ነው፤ ሌላም ብዙ ምስክር መጥራት ይቻላል፡፡ እኛም በቤተሰባችን ውስጥ መመስከር ቀላል ነው፡፡ እንዲህ በአደባባይ ከመውጣታችን በፊት ከቤተሰባችን ውስጥ ነው ሃይማኖት ገንዘብ መደረግ ያለበት፡፡ ጸሎት እዛ ነው መለመድ ያለበት፡፡ ጾም እዛ ነው መለመድ ያለበት፡፡ ምጽዋቱ’ኮ እዛ ነው መለመድ ያለበት፡፡ በየቤታችን ሙዳዬ ምጽዋት አስቀምጠን ልጆች ከጸሎት በኋላ ገንዘብ እያስቀመጡ፥ ያንን የሙዳዬ ምጽዋት ገንዘብ ይዘው ነው እሑድ ዕለት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጡ የሚመጸውቱት፡፡ እንዲህ ከኾነ የሚሰጡ ልጆች እናፈራለን፡፡ እንዲህ ካልኾነ ግን ሙዳዬ ምጽዋትን የሚሰብሩ ልጆችን እናፈራለን፡፡ ከየት ያምጡት ታዲያ? ዛሬ’ኮ “ሙዳዬ ምጽዋት ምንድነው?” ቢባል “ገንዘብ በውስጡ ያለበት፤ ተሰብሮም ያ ገንዘብ የሚወሰድበት፤ እንደዉም ምንዛሪ ያለበት” ነው የሚመስላቸው፡፡ የሚሰጥ ነው የሚለውን እኛ ነን ማስተማር ያለብን፡፡ የጥንት ክርስቲያኖች እንደሚያደርጉት ዐቢይ ጾምና ፍልሰታ ላይ ቤተሰብ የማይጠቀሙበትን ልብስ ይሰበስቡና ኪዳነ ምሕረት በዓል ሲኾን ወይም ደግሞ የትንሣኤ በዓል ከመኾኑ በፊት ወስደው ለነዳያን ይሰጡ ነበር፡፡ ልጆቻችን ይህንን ነው በኢየሩሳሌም ማስተማር ያለብን፡፡ እንዲህ የምናደርግ ከኾነ ለሌላው ማዘን፣ ለሌላው መራራት ለምደው ያድጋሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ልጆች ካፈራን ቤታችን ውስጥ ሳንቲም የሚሰርቅ የሚነካ የለም፤ ቤታችን ውስጥ ርህራሄ ይኖራል፡፡ ይኼ ነው በኢየሩሳሌም የተባለው፡፡ የፈረሰውም ይኼ ነው፡፡
በይሁዳ እንቀጥላለን...

27/03/2013

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
ዘለዓለም አሜን

ውድ የፌስቡክ ገጻችን ምዕመናን ለሳምንቱ እንደምን ሰነበታችሁ እያልን ከባለፈው ሳምንት የቀጠለ ክፍል 2 ፅሁፋችንን እንደሚከተለው እናቀርባለን ፡፡

ኦርቶዶክስ ማለት ምን ማለት ነው?

ኦርቶዶክስ የሚለውን ቃል ኦርቶ/ortho/ ና ዶክሲ/doxy/ ከተባሉት ሁለት የግሪክ ቃላት የተወሰደ ሲሆን ኦርቶ ማለት /ርቱእ/ ቀጥተኛ /direct/ ማለት ሲሆን ዶክስ ማለት ደግሞ እምነት /አስተሳሰብ /ማለት ነው ፡፡ ስለዚህ ኦርቶዶክስ ማለት ቀጥተኛ እምነት ማለት ነው፡፡
በክርስቶስ ደም የተመሰረተችው ቤ/ክ ኦርቶዶክስ የሚለውን ስያሜ ያገኘችው በ325 ዓ.ም በጉባኤ ኒቂያ ነው፡፡ /synod of Nicene/ ምክንያቱ ደግሞ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

ቅድስት ቤ/ክ በክርስቶስ ደም ተመስርታ ምዕመናን በእርሷ ጥላ ውስጥ ማረፍ ከጀመሩ በኋላ ነገሮች ሙዝ የመላጥ ያህል ቀላል አልነበሩም ፡፡ መስራቹን ክርስቶስን ወደ መቃብር ያወረዱት አይሁዶች ክርስትናንም ግብዓት መሬቱን የፈጸሙላት መስሏቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ ሞትን ድል ነስቶ ሲነሳ ክርስትናም አብሮ ነበር የተነሳው፡፡ ባረገ በ10ኛው ቀን ኃይል መንፈስ ቅዱስን ከአርያም ልኮላቸው ቅዱስን ሐዋርያቱና ሌሎቹ የክርስቶስ ቤተሰቦች ከእርጅናቸው ታድሰው፣ ከፍርሀታቸው ታክመው፣ ድኑዓን ሆነው፣ የክርስትናን ሠንደቅ ዓላማ ያለምንም መረበሽ በአይሁድ ሰፈሮች ውስጥ እያውለበለቡ መሄድ ጀመሩ፡፡ በዚህም ድርጊታቸው ዛቻን፣ ማስፈራሪያ፣ ግርፋትና ፣መታሰር ዘወትር ሽልማታቸው ሆነ፡፡ ነገር ግን ይሄ ነገር አጥንትና ደማቸው የሆነውን ክርስቶስን ሊያስተዋቸው አልቻለም፡፡ ይልቁንም ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባናል እያሉ ምስክርነታቸውን ሰጡ ፡፡ ሥራ 5÷29

አብዝተው በገረፏቸው መጠን የእግዚአብሔር ቃል በዚያው መጠን እየሰፋ መጣ፡፡ በኢየሩሳሌምም የደቀመዛሙርት ቁጥር እጅግ እየበዛ ሄደ፡፡ ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖቱ የታዘዙ ሆኑ፡፡ የአገልግሎቱም መንኮራኩር ለማፋጠን በመልካም የተመሰከረላቸውን፣ መንፈስ ቅዱስና ጥበብ የሞላባቸውን፣ ሰባት ሰዎች ተመርጠው በእጅ መጫን ህብተ ክህናት ከተሰጣቸው በኋላ እስጢፋኖስን ሊቀ ዲያቆናት አድርገው ሾሙት፡፡ እርሱም ጸጋንና ሀይልን ተሞልቶ በህዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር ፡፡ታዲያ ከቀሬናና ከእስክንድርያ ከኪልቅያና ከእስያ የነበሩ የአይሁድ ሰዎች መጥተው ሊከራከሩት ይወዱ ነበር፡፡ነገር ግን ይናገርበት የነበረውን ጥበብና መንፈስ ይቃወም ዘንድ አልቻሉም ፡፡ በዚያን ጊዜ በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የሰድብና ነገር ሲናገር ስምተነዋል የሚሉ የሀሰት ምስክር አስነሱ፡፡ ወደ ሽንጎም አመጡት፤፤ ያዩት ሰዎችም በንዴትና በእልህ ጥረሳቸውን አፋጩበት፡፡ እርሱ ግን ፊቱን እንደመልአክ በጸዳል ያጥለቀለቀውን መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ከጠራራ ፀሐይ ይልቅ የበራውን እውነት እርሱን ለመስማት ግድ ለሌላቸው ጆሮዎች አፈሰሰ፡፡ በዚህ ጊዜ የበፊቱ ሳውል የኋላው ጳውሎስ እስጢፋኖስ በድንጋይ በሚወገርበት ጊዜ የወጋሪዎችን ልብስ ይዞ ቆሞ ይመለከት ነበር ፡፡ ሥራ 6÷1-15 ሥራ 7÷1-60
እዚህ ላይ ሁለት ታሪኮች ይነሳሉ፣ አይሁድ እስጢፋኖስን ሲገድሉ የክርስትናው መንኮራኩርን ፍሬም እንይዛለን፡፡ ፍጥነቱንም እንገታለን ብለው ነበር፡፡ የሆነው ግን ይሄ አልነበረም፡፡ ይልቁንም በእስጢፋኖስ ምክንያት በቤ/ክ ላይ ታላቅ ስደት ሆነ፡፡ ወደ ይሁዳና ወደ ሰማርያ አገሮች ተበተኑ፣ታዲያ እነዚህ ወደ ተለያዩ ሀገሮች የተበተኑት ክርስቲያኖች በሄዱበትና በደረሱበት ቦታ ሁሉ ክርስትናን ሰበኩ፡፡ ቁጥራቸው በዛ፡፡ ስለዚህ የአይሁድ ሴራ ከሸፋ፡፡

ሌላኛው ታሪክ ደግሞ ሳውል ለሚኖርበት የአይሁድ እምነት ተቆርቁሮ ክርስቲያኖችን ከምድረ ገፅ ለመደምሰስ ከሊቀ ካህናቱ የፈቃድ ደብዳቤ አውጥቶ ወደ ደማስቆ( ሶርያ) ተመመ ፡፡ ወደ ደማስቆ ሲቀርብ ከሰማይ ባንፀባረቀ ታላቅ ብርሃን ተመትቶ ወደ ምድር ወደቀ ፡፡ ‹‹ሳወል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ?” ሥራ 9÷4 የሚል ድምጽን ሰማ፡፡ ‹‹አንተ ማነህ የማሳድድህ አለው?››፡፡ ክርስቶስም ‹‹አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፡፡ የመውጊያው ብረት ብታቃወም ላንተ ይብስብሃል›› ፡፡ አለው በዚህ ቃል ሳውል ያሳድድው የነበረውን እምነት ወደ ድንኳን ለመመለስ በነገስታትና በእስራኤል ልጆች ፊት የጌታን ስም የሚሸከም ምርጥ ዕቃ ለመሆን ቆርጦ ተነሳ፡፡
ምንም እንኳ አይሁዳውያኑ ክርስትናን ከወለል በታች ለማድረግ ቢሯሯጡም ትናንት ከእነሱ ጋር ይሯሯጥ የነበረው ጳውሎስ የክርስትናን ዕቃ ይዞ ከየትኞቹም አገልጋዮች በላይ መፋጠንን ስራው አደረገው፡፡ አንድ ጊዜ አንድ ንጉስ ‹‹የተወጋነው ከኛው ክንፍ በተወሰዱ ላባዎች ነው’’ እንዳለ በአንድ ወቅት ከእነርሱ ጋር ስለ ኦሪትና ግዝረት ስሌሎችም በክርስቶስ አካልነት ምክንያት ስላለፉት ጥላዎች ቋሚነታቸውን ደግፎ ይከራከር የነበረው ጳውሎስ ዛሬ ግን እውነቱን ተረድቶ ያለፈውን ህይወቱን እየገረመው በሥጋ የአብርሃም ልጆች ሆነው ነገር ግን ከመንግስት ሰማይ በአፍኣ/ በወጭ/ ይጣሉ ዘንድ ስላላቸው ለእስራኤል ዘሥጋ ድህነት አዲሲቱን ህግ ወንጌልን ያውቁ ዘንድ የብርታትን ዝናር ታጥቆ ተነሳ፡፡ ፊትህን ካላየን ማደር አይሆንልንም እያሉ ይናፍቁት የነበሩት ረበናተ አይሁድ /መምህራን አይሁድ/ ቅዱስ ጳውሎስ ከየትኛውም ጊዜ በላይ የሚጠሉት፣ ሊገድሉት የሚፈልጉት ጠላታቸው ሆነ፡፡ እርሱ ግን ‹‹ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለው›› እያለ በምድረ ፍልስጥኤም የተጀመረችውን ክርስትናን ወደ አህዛብ ሀገር በሚገርም ፍጥነት አደረሰ፡፡ ክርስቲያኖችም ቁጥራቸው እየበዛ ሄደ፡፡

ነገር ግን ቁጥራቸው በበዛው ልክ ፈታኛቸውም እንደ አሸን እየፈሉ ነበር፡፡ በተለይም በአህዛብ ሀገር ጣኦታቱን የማያገለግሉ ካህናት ጣኦታት በጣኦታቱ ስም ከህዝብ የሚያገኙት ገቢ ስለተቋረጠባቸው ክርስትናን ድራሹን ለማጥፋት ተነሱ፡፡ ይህንን በተመለከተ የመጀመሪያውን ትልቁን ስደት ያወጀው ከ54-68 ዓ.ም በሮም የነገሰው ኔሮን ቄሳር ነው፡፡ ይህ ሰው ፍፁም ጨካኝ ነበር፡፡ በሮማ መንበር ላይ በነገሰ በዓመቱ የአባቱን ልጅ አስገደለ፡፡ ቆይቶ ደግሞ እናቱን በመርዝ ገደለ፡፡ በዘመነ መንግስቱ መገባደጃ ላይ ሚስቱን ፣እያስተማረ ያሳደገውን መምህሩን አስገድሏል፡፡ ኔሮን ቄሳር ክርስቲያኖችን ለመፍጀት መነሻ ያደረገው የሮማን ከተማ መቃጠልን ተከትሎ ነው፡፡ ለከተማይቱ መቃጠል ዋናው ምክንያት የሮማ አማልክት በክርስቲያኖቹ ተቆጥተው በከተማይቱ ላይ ወረዳ መቅሰፍት ነው ብለው ካህናት ጣኦታቱ ማስወራት ጀመሩ ፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኖች ሥጋቸው እንደሽንኩርት ተቀረደደ ፣ በፈላ ዘይት ተቀቀሉ፡፡ ብዙ ግፍና መከራ ደረሰረባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ቅዱስ ጴጥሮስ ቁልቁል ተሰቅሎ . ቅዱስ ጳውሎስ አንገቱን ተሠይፎ በሰማዕትነት ያለፉት፡፡ ይህ እልቂት ከኔሮን ቀጥሎ በተነሱት በዶሚኒያን (81-96 ዓ.ም)፣ትራጃን /98-117ዓ.ም/ ፣ዲዮቅልጥያኖስ /250-305ዓ.ም/ በከፍተኛው ሁኔታ ቀጥሎ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ክርስቲያኖች በካታከምብ/ የምድር ጉድጓድ / እየኖሩ አንድነታቸውን ግን እየጠበቁ ኖረዋል፡፡ ከደረሰባቸው ጭፍጨፋ በተጨማሪ በሲሞን መሠርይ የተጀመረው ምንፍቅና በግኖስቲኮችም ቢቀጥልም ቤተ ክርስቲያን ግን አንድነቷን እየጠበቀች ክርስትና የሚለውን ስም ይዛ ቀጥላ ነበር፡፡
በኔሮን ቄሳር የተጀመረው ክርስቲያኖችን የመጨፍጨፍ አባዜ 312 ዓ.ም ላይ በነገሰው በንጉስ ቆስጠንጢኖስ ዕረፍት አገኘች፡፡ ቤ/ክ መብቷ ተከበረላት፡፡ ታዲያ ቤ/ክ ከወራሪ ጠላቶች አርፉ የሰላም አየር መተንፈስ በጀመረችበት ወቅት በረጅሙ የቤ/ክ ተጋድሎ ዘመን ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የኖረው ኑፋቄ ትምህርት በአርዮስ አማካኝነት በይፋ ወደ አደባባይ ወጣ፡፡

በ257 ዓ.ም ወደ ዚህች ምድር የመጣው የሊቢያው ተወላጅ አርዮስ በ3ኛው መ/ክ/ዘመን አካባቢ በተመሠረተው በአንጾኪያ ት/ቤት ሉቅያኖስ ከተባለው መናፍቅ ዘንድ ተምሯል፡፡ከአንጾኪያ ት/ርቱን ጨርሶ ያቀናው ወደ ግብጽ እስክንድርያ ነበር፡፡ በወቅቱም የእስክንድርያ 17ኛው ፓትርያርክ ከነበሩት ከአባ ጴጥሮስ ዲቁና ተቀበሎ ማገልገል ጀመረ፡፡ ‹‹ወልድ ፍጡር ነው’’ የሚለውን በአንጾኪያ ሉቅያኖስ ጭኖ የላከውን ክህደት በእስክንድርያ ቤ/ክ ለማራገፍ ሲውተረተር ቅዱስ ጴጥሮስ ደርሶበት ትህትናን በተመላበት አነጋገር ‘’ልጄ ሆይ ይህንን ነገር ከእኔ አልሰማኸው፡፡ ከመጽሀፍም አላገኘኸው፡፡ አስበኸው እንደሆነ አትናገረው፡፡ ተናግረኸውም እንደሆነ አትድገመው!!’’ ሲል መከረው፡፡አርዮስ ግን ክህደቱን በልቡ ቆጥሮ ከላይ ግን ለይምሰል የቅዱስ ጴጥሮስን ተግሳጽ የተቀበለ መስሎ ክህደቱን ግን ውስጥ ውስጡን ያሰራጭ ነበር፡፡

አንድ ቀን ሌሊትም ቅዱስ ጴጥሮስ በራእይ ‹‹ ቀሚሱ ለሁለት በተቀደደ ሕጻን አምሳል ክርስቶስ ታየው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ደንግጦ ‹‹አንተ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ አይደለህምን›› ሲል ጠየቀው፡፡ ጌታም ‹‹አዎን›› ሲል ይመልስለታል፡፡ ታዲያ ‹‹ልብስህን ማን ቀደደብህ›› ብሎ ሲጠይቀው ‹‹አርዮስ ልብሴን ቀደደብኝ›› በማለት ይመልስለታል፡፡ ይህንን ራዕይ ካየ በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ አኪላስና እለ እስክንድሮስ የተባሉትን ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ ያየውን ራእይ ገልጾላቸው አርዮስን ፈጽመው እዳያስጠጉት አስጠነቀቃቸው፡፤ እርሱንም አውግዞ ከቤ/ክ አንድነት ለየው፡፡
ከቅዱስ ጴጥሮስ ዕረፍት በኋላ አኪለስ 18ኛው የእስክንድርያ ቤ/ክ ፓትርያርክ ሆኖ ተሾመ ፡፡ በነገራችን ላይ በቤ/ክ ዘመነ ሰማዕታት እየተባለ በሚጠራው ወቅት የዘመነ ሰማዕታት የመጨረሻው ሰማእት እየተባለ የሚጠራ በመሆኑ ተፍጻሜት ሰማእት ቅዱስ ጴጥሮስ እተባለ ይጠራል፡፡አኪላስ ፓትርያርክ ሆኖ ከተሾመ በኋላ አርዮስ ባልጀራነቱን ተገን አድርጎ በመቅረብ አኪለስን የውዳሲ ካንቱ ጨው አላሰው፡፡ አኪለስም በውዳሴ ከንቱ መረብ ተጠልፎ ወድቀ፡፡
የመምህሩን ቃል ጥሶ አርዮስን ከግዘቱ ፈትቶ ወደ ቤ/ክ መለሰው አኪላስም በመንበረ ማርቆስ ላይ ለአንድ ዓመት ያህል እንኳን አልቆየም ሞተ፡፡ አኪላስም ከሞተ በኋላ በ303 ዓ.ም አለ እስክንድሮስ በመንበር ማርቆስ ላይ ተሾመ ፣የአርዮስ ክህደትም እንደ ሰደድ እሳት እየተዘመተ በመሆኑ አርዮስን አስጠርቶ የክህደት ትምህርቱን እንዲያቆም ነገረው፡፡ አርዮስ በእምቢታው ጸና፡፡ ይባስ ብሎ የግጥም ጸጋውን በመጠቀም ለእንጨት ሰባሪው፣ ለውሃ ቀጅው ፣ለሱቅ ነጋዴው ሁሉ ማደል ጀመረ፣

በዚህም ምክንያት ቤ/ክ በጣም እታወከች ስትመጣ በንጉስ ቆስጠንጢኖስ ትዕዛዝ መሠረት በ325 ዓ.ም በታናሿ እስያ ውስጥ በጥቁር ባህር ወደብ አካባቢ በምትገኝ ኒቂያ በተባለች ከተማ ጉባኤ ተደረገ፡፡ ጉባኤው ‹‹ወልድ ፍጡር ነው›› በማለት አርዮስ ያቀረባቸውን ጥቅሶች መረመረ፡፡ ወልድ በባህርይ ፍጡር ከሆነ በመዳን ምሥጢር ላይ ስለሚያመጣው አደጋ ፣ሌሎችም ሀሳቦች በስፉት ተነስተው ተብራሩ፡፡
በተለይ ወጣቱ ሊቀ ዲያቆናት አትናቴዎስ የጉባኤው ፈርጥ ሆኖ ነበር የዋለው፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ መልስ ሲሰጥ በማቴዎስ ወንጌል የተማርነው የጠፋው በግ ምሳሌ የሰው ዘርን የሚመለከት ነው፡፡ ፈላጊውም አካላዊ ቃል የእግዚአብሔር ልጅ ወልድ ነው፡፡‹‹ቃል ፍጡር›› ከተባለ የጠፈው እርሱ ራሱ ነዋ!! ብሎ አትናቴዎስ ለጉባኤው ሲያሰማ አርቶዶክሳውያኑ በደስታ ተዋጡ፡፡ እራሱ የጠፋ ከሆነ ደግሞ ራሱ ሌላ ፈላጊ ያስፈልገው ነበር፡፡ ሌሎችም ብዙ ጥያቄዎቹ ፉርሽ ተደረጉበት፡፡ 318 ቱ ሊቃወንትም አንድ ልብ ሆነው አርዮስ አልመለስ ቢል ገዝተው ለዩት፡፡ ሊቃውንቱም ከሀዋርያት አባቶቻችን የቀበልነውን እምነት ሳንበርዝ፣ ሳንከልስ ሳናጣምም ቀጥ እንዳለ እናምናለን ሲሉ ኦርቶዶክሳውያን ተባሉ፡፡ ስለዚህ ኦርቶዶክስ ማለት ከሐዋርያት ቀጥ ብሎ የወረደውን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ ነው የሚለውን ትምህርት ያመነ ማለት ነው፡፡

አንዳንዶች ይህንን ቃል ባለመረዳት ሲተቹ ሲሸረድዱ ይስተዋላሉ፡፤ እኛ ግን ይሄ ስም ዋጋ የተከፈለበት ስም እንደሆነ እናምናለን፡፡ አርዮስና አርዮሳውያን ክርስቶስን የባህርይ አምላክነት ቀሚስን ለመቅደድ ሲነሱ እውነተኞቹ ግን ቀሚሱን ሰፍተው የባህርይ አምላክነቱን አምነው ኦርቶዶክስ የሚለውን ካባ ደረቡ፡፡
በዚህ ስም ክርስቶስ ይከበራል፡፡ በዚህ ቤት የክርስቶስ የባህርይ አምላክነቱ እስከ ሙሉ ክብሩ ይመለክበታል፡፡ ስለዚህ ስም ብለው ብዙዎች በቀስቱ ፈት አለፉ፤ ብዙዎች ወደ ስለት፤ ወደ ጉድጓድ ገቡ ፡፡ ለአንበሶች ተሰጡ፡፡ የማይሆኑትን እየሆኑ ይህንን ስም እዚህ አደረሱ፡፤
አርዮስና አርየሳውያን ግን ለእስልምናና ለጀሆቫ ዊትነስ /የይዋሃ ምስክሮች / መሠረት ሆኑ፡፡
ፅሑፋችንን የምንዘጋው ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ በተናገሩት ቃል ይሆናል፡፡

‹‹ከእነርሱም /እስራኤላውያን/ ክርስቶስ በስጋ መጣ፡፡ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፡፡አሜን›› ሮሜ 9÷5

‹‹የእግዚአብሔር ልጅ እንደመጣ፣ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደሰጠን እናውቃለን፡፡ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፡፡እርሱም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡እርሱም እውነተኛ አምላክና የዘላለም ህይወት ነው፡፡ ልጆች ሆይ ከጣኦት ራሳቸውን ጠብቁ ›› 1ኛዮሐ 5÷20-2

‹‹ተዋህዶ›› የሚለውን ቃል በሚቀጥለው ፅሁፍ እንደእግዚአብሔር ፈቃድ ይቀርባል፡፡

መልካም ሳምንት
ወስብሐት ለእግዚአብሄር

18/03/2013

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና

ከሁሉም በማስቀደም “Let us Discuss what Orthodox Christianity is” በሚል የfacebook ገጻችን ላይ በጊዜው እንለጥፋለን ብለን ባለመለጠፋችን ይቅርታ እየጠየቅን ከዚህ በኃላ በየሳምንቱ ወቅቱን የጠበቀ መንፈሳዊ ጽሑፎችን ለማቅረብ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ቃል እየገባን የመጀመሪያውን ጽሑፋችንን የፌስ ቡኩ መጠሪያ የሆነው “Let us Discuss what orthodox Christianity is” ተብሎ የተሰየመበት ምክንያት በማብራራት እንጀምራለን፡፡

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና ምን ማለት እንደሆነ እንወያይ!!!!

በመጀመሪያ ክርስትና የሚለውን ቃል እንመልከት
ክርስቲያን ማለት የክርስቶስ ተከታይ ፣ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ማለት ሲሆን ምዕመናን/አማኞች/ መጅመሪያ በአንጾኪያ ክርቲያን ተባሉ፡፡ ሥራ11፣26 ክርስትና ማለት ደግሞ ያመኑ ክርስቲያኖች የሚከተሉት እምነት ነው፡፡ መስራቹ ደግሞ በገዛ ደሙ ፈሳሽነት ያጸናት ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ከተመሰረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠረት አይቻልምና፡፡ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ‘እንዳለ 1ኛ ቆሮ፣11 ኤ.ፊ 2፣20’
እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ የተመሠረተችው ክርስትና የአዳምና ልጆቹን የዘመናት እንቆቅልሽ የፈታች፣ የዓመተ ፍዳ መዝገብን የዘጋች ፣መስቀል የእርግማን መልክት መሆኑ ቀርቶ ከቀስቱ የምናመልጥበት ምክንያቶች ሆኖ የተሰጠባት፣ አባ አባት ብለን የምጮህበት የልጅነት መንፈስ የተቀበልንባት ፣የበዛ ትርፋችን የበረከተ መክሊታችን ሆኖልን ዕረፍት ያገኝባት መንገድ ሆናለች፡፡
እርግጥ ነው ከክርስትና በፊትም በኃላ ወደ ፈጣሪ መድረሻ ናቸው ተብለው የተቀየሱ “መንገዶች“ ነበሩ ፡፡አሁንም ቀያሹ እግዚአብሔር ባይሆንም በንስር ፍጥነት ብዙ መንገዶች በመቀየስ ፣ብዙ መሰረቶች በመመስረት ላይ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ክርስትና ከነዚህ ሁሉ መንገዶች ወይም እምነቶች በምንድው የሚለው ሰው ቢኖር ልዩነቱ ክርስትና

1.የመገለጥ እምነት ነው፡፡

ክርስትና የመገለጥ እምነት ነው ሲባል በራዕይ በህልም ወይም በትንቢት ለሆነ ነቢይ ተነግሮት በዚያ ነቢይ አነሳሽነት የተመሰረተ እምነት አይደለም፡፡ ለምሳሌ የእስልምና እምነት ለነቢዩ መሐመድ መልአኩ ጅብሪል ከአላህ በተላከው ቃል መሰረት የተመሰረተ እምነት ነው፡፡ የአይሁድም እምነት እግዚአብሔር ለነቢዩ ሙሴ በሲና ተራራ ላይ በሰጠው ዐሠርቱ ትእዛዛት መሰረት ለሕዝበ እስራኤል የተሰራች እምነት ነው፡፡
ክርስትና የመገለጥ እምነት ነው ሲባል ግን ከዚህ በተለየ መልኩ ነው፡፡ ይኸውም ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከቅድስት ድንግል በነሳው ሥጋ ሰው ሆኖ ተገልጦ የሰራት እምነት ናት፡፡ ክርስትና በራእይ አልመጣችም፡፡ በሕልም ላይም አልተመሰረተችም፡፡ ነገር ግን ራሱ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ተገልጦ በቤተ ልሔም ተወልዶ ፣ ወደ ግብጽ ተሰዶ ፣ በናዝሬት አድጎ፣ በባሕረ ዮርዳኖስ ተጠምቆ፣ በገዳመ ቆሮንቶስ ጾሞ ፣ በኪደተ እግሩ ዓለምን እየቀደሰ ፣ ትምህርቱን በስራው እየገለጠ ፣ሁሉን እያሳየ ክርስትና እንዲህ ናት እያለ ክርስትናን መሰረታት፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ክርስትና የመገለጥ እምነት መሆኗን ሲመሰክር ‹‹ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለው፡፡ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሰረት ነው፡፡ እግዚአብሔርን የመምሰል ምስጢር ታላቅ ነው፡፡ በሥጋ የተገለጠ፣ በመንፈስ የጸደቀ ፣ ለመላእክት የታየ ፣ በአህዛብ የተሰበከ ፣ በዓለም የታመነ ፣ በክብር ያረገ›› 1ኛ ጢሞ 3÷16
ስለዚህ ክርስትና የማይታየው እግዚአብሔር በሚታይ ሥጋ ፣ የማይዳሰሰው ፈጣሪ በሚዳሰስ ሥጋ ተገልጦ ፣ የባዘኑትን በጎች ወደ በረቱ የመለሰበትን አውነት ይሰብካልና ልዩ ነው፡፡ ይህንን እውነት ከክርስትና ሃይማኖት ውጭ የሚሰብክ የለም፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹ የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደመጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፡፡ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፡፡›› 1ኛ ዮሐ 4÷12 በወንጌሉ ላይም ‹‹ ቃልም እግዚአብሔር ነበር፡፡ . . . ቃልም ሥጋ ነው፡፡›› እንዲል ዮሐ 1-1÷14

2. ልዩ ነው፡፡

ሁለተኛውና ትልቁ ነጥብ ደግሞ ከስነ መለኮት ትምህርት አንጻር ከሌሎች ሃይማኖት ክርስትና ልዩ ነው፡፡
ለምሳሌ፡- የአይሁድ ፣የእስልምና ፣የአፖስቶሊኮች ፣የጂሆቫ ዊትነሶችን ወ.ዘ.ተ እግዜአብሔር አንድነቱን እንጂ ሦስትነቱ አይቀበሉም ፡፡አንዳንድ እምነቶች ደግሞ ወደ ሚሊዮን የሚቆጠሩ አማልክት ያሏቸው አሉ ፡፡ ለምሳሌ፡ ጥንታውያን ግሪኮች በታላቁ የግሪክ ተራራ አሊምፐስ /Olympus/ ይኖራሉ ተብለው የሚታመኑ ብዙ አማልክት አሏቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል፡ ጁፒተር /የአማልክት ንጉስ/ ፣ጂኖ /የሰማይ ንግስት/፣ አፖሎ/የፀሐይ ፣የመድኃኒትት፣የሙዚቃ ና የግጥም አምላክ ፣ቬኑስ /የቁንጅና የሣቅ፣ የጋብቻ አምላክ/ ፣ኔፕቱን/የውኃዎች አምላክ /፣ ፕላቶ/የሲኦል አምላክ/ ፣አፍሮዳይት /የፍቅር አምላክ/…ወ.ዘ.ተ እየተባሉ የሚጠሩ አማልክት አሏቸው፡፡
ክርስትና ግን ከእነዚህ ከላይ ከተጠቀሱት እምነቶች በተለየ መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት አድርጋ እግዚአብሔር አንድም ሦስትም ነው ብላ ታስተምራለች፡፡ አንድነቱ በመፍጠር ፣በመግዛት /መለኮት/፣በፈቃድ ፣በስልጣን ብሎም በአንድ ልብ በማሰብ ፣በአንድ ቃል በመናገር፣በአንድ እስትንፋስ በመተንፈስ አንድነቱ ይገለጻል ፡፡ ስለዚህ “እስራኤል ሆይ ስማ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው ፡፡” ዘጸ 6÷5 ሲል ከዚህ አንጻር መጽሐፍ ቅዱስ እየገለጸ መሆኑ ግልጽ ነው ፡፡ በ ሌላም ቦታ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔና አብ አንድ ነን” ዮሐ 10÷30 ፣ “እኔን ያየ አብን አይቷል ፡፡ …እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ “ ዮሐ 14 ÷10-11
“የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፡፡…እርሱ ያከብረኛል ፡፡ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና፡፡ ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፡፡ስለዚህ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ፡፡ “ ዮሐ16÷14
ይኼን አንድነት ቅዱስ ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮ 8÷5-6 እና በ1ኛ ቆሮ 12÷4 ላይ እንዲህ አድርጎ አስቀምጦታል፡፡
‹መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፡፡ነገር ግን በሰማያት ሆነ በምድር ሆነ አማልክት የተባሉ ምንም ቢኖሩ ለእኛስ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን፡፡›› 1ቆሮ 8÷5-6
‹‹መንፈስ ግን አንድነው፡፡›› 1ቆሮ 12፡4
ቅዱስ ጳውሎስ እንግዲህ አብንም፣ወልድንም፣መንፈስ ቅዱስንም አንድ እያለ በመግለጽ ፍጹም አንድነታቸውን በረቀቀ ምስጢር ገለጸ፡፡ስለዚህ ሶስት አማልክት አንልም:: አንድ አምላክ እንላለን እንጂ፡፡ አንድ አምላክ ስንልም በመፍጠር ፣በአገዛዝ ፣ በስልጣን፣ በአንድ ልብ አስቦ፣ በአንድ ቃል ተናግሮ፣በአንድ እስትንፋስ ተንፍሶ፣ በመኖር ይገለጻል፡፡ ይህን ምስጢር በተለይ በዩሐንስ 16፡14 ላይ በሚገርም ሁኔታ ተገልጻል ፡፡ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስን ‹‹ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል›› በማለት መንፈስ ቅዱስ ከወልድ ቃልነትን ገንዘብ አድርጎ በእርሱ ቃልነት የሚናገር መሆኑን ሲገልጽ ‹‹ ለአብ ያለው ሁሉ የኔ ነው››በማለቱ ደግሞ ወልድ ከአብ ልብነትን ገንዘብ አድርጎ በአብ ልብነት የሚያስብ መሆኑን ይገልጻል፡፡‹‹ እኔና አብ አንድ ነን›› ዩሐ 10፡30 በማለቱ ደግሞ አንድነታቸውን በሚገባ ገልጾል፡፡
ሦስትነታቸውን ደግሞ በስም፣ በአካልና በግብር ይገለጻል፡፡ ለምሳሌ፡-‹‹ እንግዲህ ሂዱና አህዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው›› ማቴ 24፡19 አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ብሎ ሶስትነታቸውን÷ስም ብሎ አንድነታቸውን ገለጸ፡፡ እዚህ ላይ አስተውል፡፡ ስሞች አላለም፡፡ ስም እንጂ፡፡ የተቀረውን ምስጢር በሌላ ጽሁፍ ላይ ይዳሰሳል፡፡ ይህውም ከምስጢሩ ጥልቅት፣ ስፋትአንጻር ነው፡፡
ስለዚህ ክርስትና ልዩ ነው ሲባል ባለብዙ አማልክት አስተሳሰብ(Polytheism) አይሰብክም፡እንደሌሎችም አንድነው ብቻ ብሎ ሶስትነቱን ገሸሽ አያደርግም:: ነገር ግን አንድነቱን ሶስትነቱ ሳይጠቀልለው፣ አንድነቱ ሶስትነን ሳይከፋፍለው ለዘላለም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ እግዚአብሔር ተብለው ይጠራሉ እንጂ፡፡

3. በር ነው

ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችንና አምላካችን መዳኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እኔ የበጎች በር ነኝ፡፡ ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦች እና ወንበዴዎች ናቸው፡፡ ዳሩ ግን በጎቼ አልሰሟቸውም፡፡ በሩ እኔ ነኝ፡፡ በኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፡፡ ይገባልም ይወጣልም፡፡ መሰማሪያ ያገኛል፡፡›› ዩሐ 7፡10 እንዳለ ክርስትና ወደ ፈጣሪ መግቢያ ብቸኛ በር ናት፡፡ ያለዚህ በር የሚገባ ቢኖር መሰማሪያ አያገኝም፡፡ለምሳሌ፡- ራሳቸውን የጽድቅ በር አድርገው የመጡ ነበሩ፡፡ይህንን ነገር የከበረው የህግ መምህር ገማልያል በሐዋ 5፡35 ላይ ‹‹የስራኤል ሰዎች ሆይ ስለነዚህ ሰዎች ተጠንቀቁ::ከዚህ ወራት አስቀድሞ ቴዎዳስ እኔ ታላቅ ሰው ነኝ ብሎ ተነስቶ ነበርና፡፡ 400 የሚያክሉ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተባበሩ::እርሱም ጠፋ፤የሰሙትም ሁሉ ተበተኑ፡፡ እንደምናምንም ሆኑ፡፡ ከዚህ በኋላ ሰዎች በተጻፉበት ዘምን የገሊላው ይሁዳ ተነሳ፡፡ ብዙ ሰዎችንም አሸፍቶ አስከተለ፡፡ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበተኑ፡፡›› እንዳለ ራሳቸውን የፈጣሪ እንደራሴ፣መልእክተኛ አድርገው ከእርሱ በፊትም ከእርሱም በኋላ የመጡ አሉ ፡፡እውነቱ ግን በር አለመሆናቸው ነው፡፡ ጌታ ራሱን በመልካም እረኛ ልጆቹን ደግሞ በበጎች መስሎ ባስተማረበት 10ኛ የዩሐንስ ወንጌል ም ዕራፍ ላይ እንደዚህ ሰዎችን መንጋውን ለነጣቂ ተኩላ አሳልፈው በሚሰጡ ሞያተኛ መስሎቸዋል፡፡ በማቴዎስ 7፡13 ‹‹ በጠባው ደጅ ግቡ፡፡ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጁ ሰፊ መንገዱም ትልቅ ነውና፡፡ ወደ እሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው ወደህይወት የሚወስደው ደጁ የጠበበ መንገዱም የቀጠነ ነውና፡፡ የሚያገኙት ጥቂቶች ናቸው›› እንዳለ ክርስትና ባለጠጋው ጹም'ደሀውን መጽውት፣አንድም ቀኝህን ለመታህ ግራህን መልስለት፣ አንድ ምዕራፍ እንድትሸኘው ቢጠይቅህ ሁለት ምዕራፍ ሂድለት፣ ጠላትህን ውደድ የሚረግምህን መርቅ፣ ለሚያሳድድህ ጸልይለት የምትል ፍጽምት ትርፍት ህግ ነችና የጠበበች ደጅ ነች፡፡
እናም ክርስትና በር ናትና ወደ ጽዮን ተራራ' ወደ ህያው እግዚአብሔር ከተማ ይገባባታል ፡፡ ክርስትና ደጅ ናትና ወደ በኩራት ማህበር' በደስታም ወደተሰበሰቡበት ወደ አእላፋት መላእክት' ፍጹማንም ወደሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች ይገባባታል፡፡
በክርስትና በርነት መሰማሪያ ይገኛል ፡፡በሩ ደግሞ ክርስቶስ ነው ፡፡በዚህ በር ሲታመን ብቻ ወደ አብ ይመጣል፡፡ በዚህ በር ሲታመን ብቻ ወደ መንፈስ ቅዱስ ይቀረባል፡፡ በዚህ በር አንድነቱ ሶስትነቱ ይመሰጠራል፡፡ ይህን በር ያሳወቀን ጌታ ስሙ ከፍ ከፍ ይበል፡፡ በሩን የጠፋባቸውንም ሆነ የተዘጋባቸውን እግዚአብሔር ያስብልን፡፡
ኦርቶዶክስና ተዋህዶ የሚሉትን ቃላት ሰፊ ምስጢራቸውን በቀጣዩ ጊዜ እናቀርባለን፡፡
መልካም ሳምንት
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Address

Assela
442

Telephone

+251913779651

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Let us discuss what Orthodox Christianity is posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Place Of Worship

Send a message to Let us discuss what Orthodox Christianity is:

Share