ደብረ ሰዋሰዉ አደሬ ኪዳነምህረት ገዳም

ደብረ ሰዋሰዉ አደሬ ኪዳነምህረት ገዳም ገዳም

22/06/2024

" #በዓለ ጰራቅሊጦስ

በላእከ ወንጌል በእደ ማርያም ይትባረክ /ቀሲስ/
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ትምህርትሥርጭት ኃላፊ

“ኢየኀድገክሙ ዕጓለ ማውታ ትኩኑ”
“ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም”
/ዮሐ.14÷18/
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከምታከብራቸው ዘጠኝ ዐበይት (ታላላቅ) በዓላት መካከል አንዱ የጰራቅሊጦስ በዓል ነው፡፡

ጰራቅሊጦስ፡- ቃሉ ግሪክ ነው፡፡ ጰራቅሊጦስ ማለት መጽንዒ በእምነት የሚያጸና፣ መንጽሒ ከኃጢአት የሚያነጻ፣ ናዛዚ ያዘኑትን የሚያረጋጋ፣ መስተፍሥሒ፣ ያዘኑትን የሚያስደስት፣ ከሣቲ ምስጢርን የሚገልጽ ማለት ነው፡፡
ጰራቅሊጦስ፡- መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ የጰራቅሊጦስ በዓል ታሪክ እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም የሚሠራውን ሥራ ከጨረሰ በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያትን ወደ አባቴ እሄዳለሁ (አርጋለሁ) ሲላቸው ደነገጡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም መደንገጣቸውን አይቶ “ኢይደንግጽክሙ ልብክሙ እመኑ በአግዚአብሔር ወእመኑ ብየ እስመ ውስተ ቤተ አቡየ ብዙኅ ማኅደር ወምዕራፍ ቦቱ” (ልባችሁ አይደንግጥባችሁ በእግዚአብሔር እመኑ በእኔም እመኑ በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ ማለት፡- በአባቴ ቤት በመንግሥተ ሰማያት ብዙ ማዕርገ ሀብታት አለ) (ዮሐ.14÷1) እንዲሁም /በዚሁ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14÷18/ “ኢየኀድገክሙ ዕጓለ ማውታ ትኩኑ” (ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም) ሲል መድኃኒታችን ኢየሱሰ ክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያትን አጽናንቷቸዋል፡፡
/በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 24 ቁጥር 49/ ላይ እንደተጻፈውም የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያርግ ሲል ቅዱሳን ሐዋርያትን “አንትሙሰ ንበሩ ሀገረ ኢየሩሳሌም እስከ ትለብሱ ኃይለ እምአርያም” (እናንተ ግን ከላይ ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ተቀመጡ) አላቸውና ዐረገ በሐዋ.ሥራ ምዕራፍ 2- ከቁጥር 1 ጀምሮ እንደተጻፈው እነርሱም ይህን አምላካዊ ቃል መሠረት በማድረግ በኢየሩሳሌም በጽርሐ ጽዮን በማርቆስ እናት በማርያም ቤት ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው ተሰብስበው ሳሉ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዐረገ በአሥረኛው ቀን በተነሣ በሃምሳኛው ቀን ጧት በሦስት ሰዓት ለቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል ወረደላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ፍርሃት ከውስጣቸው ወጣ መንፈሳዊ ድፍረት አገኙ፡፡ አንድ የዕብራይስጥ ቋንቋ ብቻ ነበር የሚያውቁት ሰባ አንድ ዓይነት ቋንቋ (የአገሩ ሁሉ ቋንቋ) ተገለጸላቸው፡፡ ከእነርሱ ቋንቋ ጋር በሰባ ሁለት ዓይነት ቋንቋ ተናገሩ፡፡ የአገሩ ሁሉ ቋንቋ የተገለጸላቸውም ሁሉንም በአገሩ ቋንቋ እንዲያስተምሩ ነው፡፡ ከተለያየ ክፍለ ዓለም የመጡ ሰዎች ነበሩና እነዚህ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? እንዴት የእኛን አገር ቋንቋ ሊናገሩ ቻሉ? በማለት ተገረሙና አመንትተው እርስ በርሳቸው እንጃ ይህ ምን ይሆን? አሉ፡፡ ሌሎች ግን ጉሽ የወይን ጠጅ ጠጥተው ሰክረው ነው አሉ፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፡-የይሁዳ ሰዎች በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ፡- ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን ቃሎቼንም አድምጡ፡፡ ለእናንተ እንደመሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም ከቀኑ ገና ሦስተኛ ሰዓት ነውና፡፡ ነገር ግን ይህ በነቢዩ ኢዩኤል የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው፡- ይህም “እግዚአብሔር ይላል፡- በኋለኛይቱ ቀን እንዲህ ይሆናል ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፣ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፣ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፡፡ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች አገልጋዮች ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ፡፡ ድንቆችንም በላይ በሰማይ ተአምራትን፤ በታች በምድርም ምልክቶችን፤ ደምን እሳትንና ጢስንም እሰጣለሁ፡፡ የምትገለጠው ታላቅዋ የእግዚአብሔር ቀን ሳትመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል፡፡ የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” /ኢዩ.2÷28-32/ ይህን መሠረት በማድረግ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ልብን የሚነካ ትምህርት ሰጠ፡፡ ሕዝቡም ቅዱስ ጴጥሮስ በሰጠው ትምህርት ልባቸው ተከፈተ ቅዱስ ጴጥሮስንና ሌሎቹንም ሐዋርያት ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ? አሉአቸው፡፡ “ቅዱስ ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው ንስሓ ግቡ ሁላችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ ኃጢአታችሁም ይሰረይላችኋል የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፡፡ የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነው፡፡ ስለዚህ ራሳችሁን ከዚህ ክፉ ዓለም አድኑ” ብሎ መከራቸው፡፡ በዚችም ዕለት ቅዱስ ጴጥሮስ በሰጠው ትምህርት ሦስት ሺህ ሰዎች አምነው ተጠመቁ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የሞቱና የትንሣኤው ምስክሮች ሆኑ፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በነሱ ላይ ሲያድር ለቤተክርስቲያን ጉዞ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ፡፡ ይህ የጰራቅሊጦስ በዓል በግሪኮች ቋንቋ ጰንጠቆስጤ ይባላል፡፡

ጰንጠቆስጤ ማለት ሃምሳኛ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ከተነሣ በኋላ ሃምሳኛው ቀን ነው፡፡ ይህም ዕለት በዓለ ሃምሳ፣ በዓለ ጰራቅሊጦስ ነው፡፡

እንዲሁም ታላቁ ሊቅ ቅ/ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን በዓል በሚገባ አነጋገር “የቤተክርስቲያን የልደት ቀን” ብሎታል፡፡ ይህ በዓል በብሉይ ኪዳን የእሸት በዓል (በዓለ ሰዊት) ይባላል፡፡ እስራኤል የነጻነት በዓላቸውን ከሚያከብሩበት ከበዓለ ፋሲካ ጀምረው ሃምሳውን ቀን በዓል አድርገው ይሰነብታሉ፡፡ በሃምሳኛው ቀን በዓለ ሰዊትን (የእሸት በዓላቸውን) ያከብራሉ፡፡ በሀገራቸው ከመጋቢት እስከ ግንቦት ያለው ወቅት በሀገራችን ከመስከረም እስከ ኅዳር እንዳለው የእሸት ወራት (የጸደይ ወራት) ነውና የእሸት በዓላቸውን የሚያከብሩት በኦሪት ዘሌዋውያን /ምዕራፍ 23÷10-17/ በታዘዘው መሠረት ማንኛውም እስራኤላዊ ገበሬ ከዘራው ሁሉ በየአይነቱ እሸቱን ቆርጦ ተሸክሞ ወደ ምኵራቡ ይመጣል፡፡ በቤተ መቅደስ የሚያገለግለው ካህን ተቀብሎ ባርኮ ጸልዮ የሚጠበሰው እየተጠበሰ የሚታሸው እየታሸ በማኅበር አንድነት ይበላል፡፡ ይህም “ቀዳምያት” ይባላል፡፡ የመጀመሪያው ማለት ነው፡፡ ከማንኛውም በረከት የመጀመሪያው በእግዚአብሔር ፊት መቅረብ፣ ለእግዚአብሔር መሰጠት እንዳለበት ታዟልና፡፡

በዚህ መሠረት ከበዓለ ጰራቅሊጦስ የምንማረው፡- ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያትን “እናንተ ግን ከላይ ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ተቀመጡ” ባላቸው መሠረት በኢየሩሳሌም ተቀምጠው ተስፋውን ሲጠባበቁ መንፈስ ቅዱስ ወርዶላቸዋል፡፡ ዛሬም መንፈስ ቅዱስ የሚወርድባት ኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን ናት “ሚ መጠን ግርምት ዛቲ ዕለት ወዕፅብት ዛቲ ሰዓት እንተ ባቲ ይወርድ መንፈስ ቅዱስ እመልዕልተ ሰማያት (ይህች ቀን ምን ያህል የምታስፈራ ናት? ይህች ሰዓት ምን ያህል የምታስጨንቅ ናት? መንፈስ ቅዱስ ከሰማየ ሰማያት የሚወርድባት) /ሥርዓተ ቅዳሴ/ ለቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ እንደ ወረደላቸው ለእኛም ሁል ጊዜ ይወርድልናል እንዲወርድልንም ሁል ጊዜ ወደ ቤተክርስቲያን መሄድ ይገባል፡፡ ከቤተክርስቲያን ተለይቶ ጽድቅ የለም፡፡”
ቤተ ክርስቲያን፡- የመንግሥተ ሰማያት በር ናት “ዛቲ ይእቲ ኆኅታ ለሰማይ (ይህች የሰማይ ደጅ ናት) /ዘፍ 28÷17/”
በዚህ መሠረት ለእኛም በ40 ቀንና በ80 ቀን የተሰጠን ጸጋመንፈስ ቅዱስ እንዳይለየን ሕጉን ትእዛዙን መጠበቅና ጧት ማታ ወደ ቤተ ክርስቲየን መገስገስ ይገባል፡፡
ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት" የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትና የቅዱሳን ተራዳኢነት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤
ወለወላዲቱ ድንግል፤
ወለመስቀሉ ክቡር

#ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን
በአማን ተንሥአ እሙታን

#የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ

🎚🎚🎚🎚🎚🎚🎚🎚🎚🎚🎚🎚🎚🎚
#ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
#መረጃ ጥቆማ
[email protected] ይጠቀሙ።
በፌስቡክ https://www.facebook.com/AddisAbabaDiocese?mibextid=2JQ9oc

ከዚህ በተጨማሪ በሌሎች የበይነ መረብ አማራጮች ለመከታታል
በቴሌግራም: https://t.me/AddisAbabaDiocese
በዋትስ አፕ: https://whatsapp.com/channel/0029VaJznc90rGiNUScgwn3U
በዩቱዩብ: http://www.youtube.com/
በቲውተር: https://twitter.com/AADioceseMedia/media
በቲክቶክ:http://tiktok.com/
መጠቀም ይችላሉ።

12/05/2024

ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጋላችሁ?
(ሉቃ.24:5)

(በላእከ ወንጌል በእደ ማርያም ይትባረክ /ቀሲስ/
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ትምህርት ስርጭት ኃላፊ)

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን እንደሚነሣ ቅዱሳን ነቢያት አስቀድመው ትንቢት ተናግረዋል፡፡ ከትንቢቶቹም አንዱ ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃሕ እምንዋም፡፡ ወከመ ኃይል ወኅዳገ ወይን፡፡ ወቀተለ ጸሮ በድኅሬሁ /የተኛ ሰው ከእንቅልፍ እንደሚነቃ እግዚአብሔር ከሙታን ተነሣ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያልም ሰው፤ በኋላው በተተከለ መስቀል ጠላቱን ድል አደረገ/ /መዝ. 77፡65/
ስለ ጌታችን ትንሣኤ አራቱም ወንጌላውያን ጽፈዋል፡፡ ይህም /ማቴ. 28፡1-15/ ማር. 16፡1-18/ /ሉቃ. 24፡ 1-12/ ዮሐ. 20፡ 1-18/ ይህን መሠረት በማድረግ የትንሣኤው ታሪክ እንደሚከተለው ተገልጻል፡፡
ትንሣኤ፡- ቃሉ ግእዝ ሲሆን ትርጉሙ መነሣት ማለት ነው፡፡ የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ መጀመሪያ ትንሣኤውን የገለጠው ለማርያም መግደላዊትና ለያዕቆብ እናት ማርያም፤ ለሰሎሜ እንዲሁም ለሌሎች ቅዱሳት አንስት ነው፡፡
ማርያም መግደላዊት አገሯ መግደሎን ስለሆነ በአገሯ መግደላዊት ተብላለች ሰባት አጋንንት አድረውባት ሰባት ዓይነት ኃጢአት ያሠሯት ነበር፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰባቱንም አጋንንት አወጣላት፡፡ ይህን ከባድ ውለታ በማሰብ ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን እጅግ ማልዳ ከላይ ከተጠቀሱት ቅዱሳት አንስት ጋር ሽቶ ይዛ ወደ መቃብሩ ሄደች ይህም በአገራቸው በእስራኤል ልማድ ነው፡፡ በእስራኤል ሰው በተቀበረ በሦስተኛው ቀን በመቃብሩ ላይ ሽቶ ያርከፈክፉበታል፡፡ ወደ መቃብሩ በደረሱ ጊዜ መቃብሩ ተከፍቶ ሁለት መላእክት ነጭ ልብስ ለብሰው አንዱ መልአክ በመቃብሩ በራስጌ ሌላው በግርጌ ሆነው ታዩአቸው፡፡ እነርሱም እጅግ ፈሩ፣ መፍራታቸውን አይተው ሁለቱ መላእክት “አትፍሩ አይዟችሁ ሕያዉን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጋላችሁ? እርሱ ተነሥቷል በዚህ የለም በኃጢአተኞች እጅ አልፎ እንደሚሰጥና እንደሚሰቀል፣ በሦስተኛውም ቀን እንደሚነሣ አስቀድሞ በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደተናገረ አስቡ፡፡ መነሣቱንም ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ፈጥናችሁ ንገሯቸው” በማለት ሁለቱ መላእክት አጽናንተዋቸዋል፡፡ እነርሱም ሄደው መነሣቱን ለደቀ መዛሙርቱ ነግረዋል፡፡ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራ 20፡ ቁ. 19-31 እንደተጻፈው በትንሣኤ ዕለት ማታ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን ስለፈሩ በዝግ ቤት ተሰብስበው ሳሉ የሰላም ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ መጣ፡፡ ተሰብስበው በነበሩበት ቤት ገባ፡፡ በመካከላቸው ቆሞ ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው ይህንንም ብሎ እጆቹንም ጎኑንም አሳያቸው፡፡ እነርሱም በጣም ደስ አላቸው፡፡ እርሱም ዳግመኛ ሰላም ለእናንተ ይሁን አብ እንደላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው፡፡ ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፡፡ ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል የያዛችሁባቸው ግን ይያዝባቸዋል አላቸው፡፡ ነገር ግን ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ በዚሁ ቀን አልነበረም ሌሎች ደቀ መዛሙርት ጌታን አይተነዋል አሉት፡፡ እርሱ ግን የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላገባሁ እጄንም በጎኑ ካላኖርሁ አላምንም አላቸው፡፡

ከስምንት ቀን በኋላም ደቀ መዛሙርቱ ደግመው በውስጥ ነበሩ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበር፡፡ ደጆችም ተዘግተው ሳሉ የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው፡፡ ከዚያም በኋላ ቶማስን ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን አለው፡፡ ቶማስም ጌታዬ፤ አምላኬም ብሎ መለሰለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቶማስን ስለአየኸኝ አምነሀል ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው፡፡ ይህ ቀን ጌታችን ለሁለተኛ ጊዜ ቶማስ ባለበት ለደቀ መዛሙርቱ የተገለጠበት ቀን ስለሆነ ዳግም ትንሣኤ ተብሏል፡፡

የጌታችን ትንሣኤ ለክርስትናው ትምህርት መሠረት ነው፡፡ የጌታችን ትንሣኤ የእኛም ትንሣኤ ነው፡፡ ለምን፡- በእርሱ ትንሣኤ የእኛ ትንሣኤ ተረጋግጧልና እኛ ሞተን ፈርሰን በስብሰን አንቀርም በትንሣኤ ዘጉባኤ እንነሣለን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የእኛን ትንሣኤ በዘርዕ ምሳሌ ተናግሯል፡፡ ይህም “አንተ ሰነፍ አንተ የምትዘራው እንኳን ካልፈረሰ አይበቅልም” /1ኛ. ቆሮ. 15፡36/ ይህም ማለት አንድ ገበሬ ዘርዕ ይዘራል፤ ያ ዘርዕ ከአፈር ጋር ይቀላቀላል፤ ይፈርሳል ከዚያም ይበቅላል እኛም ሞተን ፈርሰን በስብሰን አንቀርም እንነሳለን፡፡ መቃብራችን ላይ መስቀል መደረጉ የትንሣኤያችን ምልክት ነው፡፡

ስለዚህ ለእኛ ትንሣኤ መሠረቱ የጌታችን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ሁላችንም በትንሣኤ ዘጉባኤ እንነሣለን፡፡ ከዚያም በሕይወተ ሥጋ ሳሉ መልካም የሠሩ ተመስግነው ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት ወደ መንግሥተ ሰማያት ይገባሉ፡፡ በሕይወተ ሥጋ ሳሉ ክፉ የሠሩ ደግሞ ተወቅሰው ዘለዓለማዊ ፍዳ ወዳለበት ወደ ገሃነመ እሳት ይገባሉ፡፡ ይህንንም ጌታችን በቅዱስ ወንጌል እንዲህ ሲል ተናግሯል፡፡ “ስለዚህ ነገር አታድንቁ በመቃብር ያሉት ሙታን ሁሉ ቃሉን የሚሰሙባት ሰዓት ትመጣለች ሕጉን የፈጸሙ በሕይወት ለመኖር ይነሣሉ፡፡ ክፉ ሥራ የሠሩ ግን በፍዳና በጨለማ ለመኖር ይነሣሉ፡፡” /ዮሐ. 5፡29/

በዚህ መሠረት ሀገረ ሕይወት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ትንሣኤ ልቡና ያስፈልገናል፤ ትንሣኤ ልቡና ማለትም የልብ መነሣት ማለት ነው፤ ልባችን መልካም ሥራ ለመሥራት መነሣት አለበት፡፡ ይህንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፡፡ “አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል” /ኤፌ. 5፡14/
መሠረተ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ያሬድ “ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ” (ትንሣኤህን ላመንን ለእኛ ብርሃነ ረድኤትህን ላክ) ብሎ በተናገረው መሠረት ፈጣሪያችን ብርሃነ ረድኤቱን እንዲልክልን ትንሣኤውን ማመን ያስፈልጋል፡፡ ለመንፈሳዊ ጉዞ መሠረቱ እምነት ነውና፡፡

እምነተ ጠንካሮች መሆን እንደሚገባን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፡፡ “የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራ ከዚህ ተነሥተህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል” /ማቴ. 17፡20/ ይህንን ሊቃውንት ሲያመሰጥሩት በሰናፍጭ ፍሬ ላይ ትንሽ እንኳን የመሰንጠቅ ምልክት አይታይም በእምነታችሁ ትንሽ እንኳን ጥርጥር እንዳይኖር፣ ጥርጥርን አስወግዳችሁ ፍጹም እምነትን ገንዘብ ካደረጋችሁ ተራራ ታፈልሳላችሁ፡፡ እንዲሁም በተራራ የተመሰለው ሰይጣንን ታወጣላችሁ ማለት ነው፡፡
እምነታችንን ደግሞ በሥራ መግለጽ ያስፈልጋል ሰው በእምነት ብቻ አይድንም ከእምነት ጋር ግድ ሥራ ያስፈልጋል፡፡ “እምነት አለኝ የሚል ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን?” /ያዕ. 2፡14/ እምነትማ ብቻ ከሆነ አጋንንትም ያምናሉ፣ ይንቀጠቀጡማል፡፡ /ያዕ. 2፡19/

ቅዱስ ያዕቆብ በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 26 ላይ በእምነት ብቻ መዳን እንደማይቻል እጅግ በሚያስደንቅ ምሳሌ ተናግሯል፡፡ ይህም፡- “ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው፡፡”

በዚህ መሠረት ከመከራ ሥጋ፣ ከመከራ ነፍስ እንድንድን፤ በረከተ ሥጋ፣ በረከተ ነፍስ እንድናገኝ እምነታችንን በሥራ መግለጽ ያስፈልጋል፡፡

እምነታችንን በሥራ ገልጸን ሀገረ ሕይወት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲሁም የቅዱሳን አማላጅነት አይለየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር።

እንኳን አደረሳችሁ
መልካም በዓል ይሁንልን

08/02/2023

የራስን ኃጥያት እንደማየት የመሰለ መድኃኒት የለም።
በመንበረ ፀባዖት በእግዚአብሔር ፊት የሚደርስው ንስሃ፡ የራስህ ኃጥያትህ እስኪያሸማቅቅህ ድረስ እንዲሰማህ ተመኝ። እራሳችን ላይ መፍረድ፡ እርሷ መድኃኒታችን ናት። የተነጥቅነውን፡ ረድኤተ እግዚአብሔር በጠላት ፊትም ሞገስን ታሰጠናለች።
ኃጥያታችንን እንዳናይ ከሚያደርጉን ነገሮች አንዱ ግብዝነት ነው። ግብዝነት ደግሞ ኃጥያታችን ጭራሽ እንድንኮራበት ያደርገናል፡ ግድ የለሽ ያደርገናል፡ ይህ ልባችን ነው እግዚአብሔርን የምያሳዝነው።
በእውቀትህ ምትታበይ አንተ፤ ገንዘብህ ትምክትህ የሆነብህ አንተ፤ በዝሙት ጥማት፤ እግዚአብሔርን ከመፍራት ይልቅ ንቀህ ለእራስህ ስሜት የተገዛህ፤ እባክህ እወቀው እባክህ ተረዳው፤ እባክህ ኃጢያትህን ተጠየፈው፤ ተፀፀትባት፤ እስክትፀየፋት ድረስ ንስሃ ግባባት፤ የነነዌን ሰዎችን ሃዘን ስጠኝ ብለህ ተማፀነው።

ይህች ሃዘን፤
- ለነፍስህ እረፍት የምትሰጥህ መድኃኒት ነች
- ከእግዚአብሔር ዘንድ የምታስታርቀን
- ከአንተ አልፎ ለቤተሰብህ፡ አልፎም ለወገንህ፡ አልፎም ለአገር የሚተርፍ
- ከናቁን ጠላቶችህ ፊት ሞገስን የምታሰጥህ

ጥፋትህን፡ ኃጢያትህ፡ ተዕቢትህ፡ ክፋትህ፡ እማን!!! አዎ በድያለሁ፡ አዎ በድዬሃለሁ፡ አንተን ሳልፈራ በሰው ፊት ያንተ ሰዉ እንደሆንኩኝ የማስመስል። አቤቱ የልቤን የሰወርኩትን፡ እንዲሁም በግብዝነቴ የተሰወረብኝን ኃጢያቴን ይቅር በለኝ!

የመርከቧን በማእበል ተናውጻ ከመስጠም ያተረፋት፡ የነብዩ ዮናስ እራሱ ላይ መፍረድ ነውና፡ እንደነብዩ ዮናስ እራስህ ላይ ፈርደህ ለአገር የሚተርፈውን ንስሃ ግባ።

አቤቱ ይቅር በለን።
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።

የጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ነገረ መለኮት ተከታታይ ትምህርት በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ በዚህ በፆም ወቅት ሊሰማ የሚገባ ወቅታዊ ትምህርት
08/03/2022

የጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ነገረ መለኮት ተከታታይ ትምህርት በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ በዚህ በፆም ወቅት ሊሰማ የሚገባ ወቅታዊ ትምህርት

ሊታይ የሚገባው ትምህርት በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ። መልሶቹ ሁሉ እነሆ

ብትመጡ ከበረከቱ የምትካፈሉ፡ መምጣት ባትችሉ እንኳን ለሰው ሼር እያደረጋችሁ፡ የእምቤታችንን በረከት ለሌሎች እንዲያገኙ በማድራግ አገልግሉ፡፡ Kessis Fasil Tadesse kesis tew...
18/02/2022

ብትመጡ ከበረከቱ የምትካፈሉ፡ መምጣት ባትችሉ እንኳን ለሰው ሼር እያደረጋችሁ፡ የእምቤታችንን በረከት ለሌሎች እንዲያገኙ በማድራግ አገልግሉ፡፡
Kessis Fasil Tadesse kesis tewodros eshetu Rodas Tadese Abebe

መነሻ አራዳ ጊዮርጊስ ለበለጠ መረጃ 09110992220920244705 09114699980913884889ይደውሉ!
16/02/2022

መነሻ አራዳ ጊዮርጊስ ለበለጠ መረጃ

0911099222
0920244705
0911469998
0913884889

ይደውሉ!

ደብረሰዋሰዉ አደሬ ኪዳነምህረት ታሪክ /ምንጭ: በአድያመ ቅዱሳን የሚገኙ ገዳማት እና አድባራት _ ከደቀመዝሙር መለሰ ኃይሉ/የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርሰቲያን እስከመቼውም የማትረሳቸ...
21/12/2021

ደብረሰዋሰዉ አደሬ ኪዳነምህረት ታሪክ

/ምንጭ: በአድያመ ቅዱሳን የሚገኙ ገዳማት እና አድባራት _ ከደቀመዝሙር መለሰ ኃይሉ/

የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርሰቲያን እስከመቼውም የማትረሳቸውም የማትተካቸውም ብዙ ቅርሶቿን ያጣችው ከዮዲት ጉዲት ቀጥሎ በ16ኛው መ/ክ/ዘመን በአሕመድ ግራኝ ወረራ ነው፡፡ ግራኝ የሚለው ቅጽል ስም ያከሉበት ክርስትያኖች ናቸው ፡፡ ሙሉ ስሙ ግን አሕመድ ኢብን ኢብራሒም አልጋዚ ነው ፡፡

የአህመድ ግራኝ ጥቃቶች
አህመድ ግራኝ ከዮዲት ጉዲት ተርፈዉ የቀሩትንና ከሱዋ በኃላ የተተኩትን አብያተ ክርስትያናትና ቅርሶች በአጠቃላይ አወድሟቸዋል፡፡ ግራኝ ያቃጠላቸዉ ገዳማትና አድባራት ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነዉ፡፡ የግራኝ ችግር አጠቃላይ ብዙ አብያተ ክርስትያናት እንደጠፉ ቀርተዋል፡፡ አንዳንዶች ከብዙ ዘመን ከማለፉ የተነሳ ትክክለኛ ቦታቸዉን ማወቅ ያስቸግራል፡፡ ታዲያ በዚህ አስቸጋሪና ፈታኝ በሆነ የመከራ ዘመን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ለትውልድ አርቆ በማሰብ እና ውስጣቸው በኃይማኖታዊ ፍቅር በመቃጠል ብዙውን ፈታኝና የግራኝን አሰቃቂ መከራ እንደ ጸጋ በመቁጠር አባቶቻችን በቀደመው ዘመን ብዙ ቅርሶችን ከቦታ ቦታ በማዘዋወር በመደበቅ አብያተክርስቲያናቱንና ገዳማቱ ሲቃጠሉ ብዙ ታቦታትንና ቅርሶችን አሽሽተው በዱር በገደል ውስጥ እንዲቀመጡና ለትውልደ እንዲተላለፍ አድርገው አልፈዋል ፡፡

ከእነዚህም አንዷ አደሬ ቅ/ኪዳነምህረት ስትሆን ከላይ በጠቀስነው የመከራ ዘመን ቀደምት አባቶቻችን ከ 40 በላይ ታቦታትንና ቅርሶችን በመያዝ ከኤረር ፣ከዝቋላ ፣ከቱሉዴምቱ ከሚባል ቦታ በመሰደድ ወደታች 270 ሜትር በሚሆን ትንሽ ዋሻ ውስጥ ያስቀመጡ ሲሆን ይህችውም አድያመቅዱሳን /የቅዱሳን አውራጃ /እየተባለ በሚጠራው ቡልጋ ርዕስ ላይ የምትገኘው ከታለቁ ገዳም ከአቲሳ አቡነ ተክለኃይማኖት የተወለዱበት እና 99 ቅዱሳን የወጡበት እንዲሁም ዲያቢሎስን ከፈጣሪው ጋር ለማስታረቅ እና የሰው ልጆች በሰላም እንዲኖሩ የለመኑት እናት ቅድስት ክርስቶስ ሳምራን ያስገኙት እና የተወለደችበት ቡልጋ ዞረሬ አፋፍ ላይ ልዩ ስሟ አደሬ በተባለች ትንሽ ዋሻ ውስጥ የሀገርና የኃይማኖት አርበኞች አባቶቻችን ለመጪው ትውልድ አርቆ በማሰብ ከሃይማኖታዊ ግዴታቸውን የተወጡ አባቶቻችን ታሪክ እና ከዘመናት በኋላ ብዙ ገቢረ ተአምራት በቦታዋና በፀበሏ እየተደረገ የዛሬዋን ያለባትን የአደሬ ደብር ሰዋስው ቅድስት ኪዳነ ምህረት ገዳምን ታሪክ እነሆ ብለናል ፡፡

የአረቡ ፀሐፊ አብያተ ክርስቲያናቱን የተቃጠሉበትን መግለፅ እያቃተው በደፈናው የበደቄ ቤተክርሰቲያን ወይም አፄናኦድ የተባሉት ከማለት በቀር ትከከለኛውን ቦታና የቤተክርስቲያናቱን ስም ስላልጠቀሰው የአብዛኛው ገዳማት እና አድባራት ስም አልታወቀም እኛም ስለነዚህ ታቦታት አመጣጥ እንጂ እያንዳንዱ ታቦት ከየት ቤተ መቅደስ እንደመጣ መናገር ስለተቸገርን በጥቅሱ በውል የሚታወቀውን የመጡበትን አካባቢና ዘመኑን ብቻ ለመናገር ተገደናል ፡፡ምክንያቱም በህይወት ያሉ አባቶችን እንዳንጠይቅ እንኳን ዘመኑ እጅግ እሩቅ ከመሆኑም በላይ እስካሁን በህይወት የሚኖር ባለመኖሩ በትክክል መረጃ የተገኘውን አካባቢና ዘመኑን ፅፈነዋል፡፡ግራኝ ይከተለው የነበረውም ስልት አብያተክርስቲያናቱን የማውደም ብቻ ሳይሆን አብረው ያሉትን ድርሳናትን ጭምር ማውደም ስለነበር በዚህ የተነሳ ፡-

1ኛ.ብዙ ቅዱሳት መጽሐፍት ተቃጠሉ የታሪክ ሰነዶች የእሳት እራት ሆኑ፡፡

2ኛ.ካህናትና መነኮሳትም ገዳማቸው ሲቃጠል ሲያዩ በደም ፍላት እሳት ውስጥ እየገቡ አለቁ፡፡

3ኛ.ምእመናንን የሚያጠመቅ ሕፃናትን ክርስትና የሚያነሳ ካህን ተመናመነ፡፡

4ኛ.ከሞት የተረፉት ምእመናን በሰይፍ እየተገደዱ የእስልምና ዕምነትን እንዲቀበሉ ተደረጉ፡፡

5ኛ. ስብከተ ወንጌል ተዳከመ፡፡

ይህ ከሆነ ከ1534ዓ.መ በኋላ ግራኝ አህመድ በጎንደር ከተማ በተደረገዉ ጦርነት ተሸንፎ እርሱም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ኢትዩጵያም ከ15 አመት መከራ ተገላገለች፡፡ ከዚህ በኃላ አፄ ገላውዴዎስ አገሪቱን ከአረጋጉ በኃላ የፈረሱትን አብያተክርስቲያናትን ማደስና በመከራው ዘመን ወደ ተለያየ ቦታ የተሠደዱትን ታቦታትና ቅርሳ ቅርስ በእግዚአብሔር ፈቃድ ለአባቶች የተገለጡትን በዋሻ እና በተራራው ውስጥ የሚገኙትን እና ከጉዳት የተረፉትን አስመለሡ በራዕይ አባቶች ከአዩዋት ከተመለሱ ቦታ አንዷ አደሬ ስትሆን ለ15 አመታት 40 የሚሆኑ ታቦታትና ቅርሶች በጉያዋ ሸሽጋ አደራዋን በእምነት ከአባቶች ተቀብላ ለአባቶች ያስረከበች ለአደሬ ምድር 23 ታቦታት በፈቃደ እግዚአብሔር ወደመጡበት ከወሠዱ በኃላ 17 የሚሆኑትን ፅላቶች ግን ወዴትም እንደማይሄዱ እና በዚሁ ቦታ ታቦታቸው እንደሚወጣ እንደሚነግስ ዋናዋ ታቦት ግን የግራኝ እመቤት ኪዳነ ምህረት እንደምትተከል እና የዓለም ህዝብ ሁሉ ወደዚህች ቦታ መጥቶ ችግሩን የነገረ ሁሉ እንደሚፈታለት በችግር ቀን ሸሽጋ ብዙ ቅርሶችን ላስረከበች እና አደራዋን ለተወጣች ለአደሬ እና ለአካባቢዋ ቃል ኪዳንን በመሃላ አጽንተውለት ሔደዋል ፡፡
ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁን፡፡

ታቦታቱ ከዋሻ ሣይወጡና እንዴት እንደወጡ
በአባቶች የተነገረው ትንቢት ከዛሬ 96 ዓ.ም በፊት ተደገመ፡፡ ይኸውም ከተለያዩ ቦታዎች አባቶች ባሕታውያን በስውር እየመጡ በዚሁ ባለው ዋሻ አፋፍ ላይ ፀሎት እያደረጉ በወረቀት ፅፈው መልዕክት በመጣል ወደመጡበት ጥሔዱ ነበር የአተፌው ሕዝብም በዚሁ አካባቢ ከብቶች ስለሚጠብቅ ወረቀቱን ከማግኘታቸውም በላይ በአፋፉ ላይ ባለው ዋሻ ውስጥ የቅዳሴ፣ የከበሮና የፀናፅል እና የምስጋና ድም ይሰሙ እንደነበር በሕይወት ያሉ አባቶች ምስክሮች ናቸው፡፡

እንግዲህ የብዙ አባቶች መልዕክት የገባውና የምስጋናውን ቃል በተደጋጋሚ ከዋሻ ውስጥ የሠማው የአገሩ ሕዝብ እርስ በራስ መመካከር እናቶችን ቅዱስት ኪዳነ ምህረትን ማህበር እናቋቁምና በዚሁ ባለው ዘፍስር በወር በወር እንጠጣ ተባብለው ተማከሩ ተማክረውም አልቀሩም በኪዳነ ምህረት ስም ሠንበቴ መጠጣት ጀመሩ ቦታው የእምነት ቦታ መሆኑ የተረጋገጠው በዚያ ወቀት ነበር፡፡ ከዚህ በኃላ የአገሬው እናቶችና አባቶች ማህበር ለመጠጣት ሲሔዱ እጣን በነልእሣት አድረገው አፋፉ ላይ ባለው የወይራ ሰር ያጤሱ እንደነበር ታሪኩ ያስረዳል፡፡ በመቀጠልም ይህን ያዩ አባቶች ካህናት አፋፍ ላይ ትንሽ መቃኞ ለመስራት በአሠቡበት ወቅት ያልጠበቁት ፈተና ገጠማቸው፡፡

በዚህ አካባቢ መቃኛ መስራሠት እንደማይቻልና ታቦትም እንደ ሌላ ውስጥም እንደሆነና ይህንን ሀሣብ ያመጠትንም ካህናትና ምዕመናንን ክስ በመመስረት እስከ መናገሻ አውራጃ ድረስ በመሔድ ሙግት ገጠሙ፡፡ ይህን ሁኔታ አሁን ላይ ሆነው አባወልደ ሚካኤል የሚባሉ አሁን በሕይወት ያሉና በእርጅና ምክንያት እንኳን ቤተክርስቲያንን ማገልገል ያልተው አባት ሲያስታውሱት ግማሾቹ ካህናት ለክርክር ወደ መናገሻ ሲሔዱ ቆራጥ የሆኑ የአገሬው ካህናትና ምዕመናን በድፍረት ትንሽ የሳር መቃኞ ሠሩ እና በዚያች ውስጥ ኪዳን እናደርሳለን መቅድም ማንበብ ጀመርን በዚህ ሁኔታ ከቆየን በኋላ አሉ አንድ ቀን ሌሊት ስዓታት ቆመን እኔና አባ ተዘራ ኃይለ ሰንበት /ታቦቷን ከዋሻ ያወጧት አባት ማለት ነው/ ሣንተኛ በቁም ራዕይ አየን ራዕዩንም እንደሚከተለው ይገልፁታል ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሰዎች 6/ስድስት/ ሆነው ከልዝብ ድንጋይ ገብርኤልና ከአቲሣ ተክለ ሃይማኖት ከማርያም ገዳም መጥተው እዋሻ ውስጥ ሲገቡ ሁለታችንም አየን ብዙም ሣይቆይ አንድ ባህታዊ ከወላይታ መጥተው የወልድ እናት እመቤታችን ከዚህ ከዋሻ ውስጥ ከብዙ ታቦታት ጋር ትወጣለች ብለው ተናገሩ የሀገሬውን ሕዘብ ምኞትና እምነት የበለጠ አጠናከረው፡፡

ካህናቱም ህዝቡም ክርክሩን ገፉበት በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ የሌላው ደብር ካህናት እና ክስ የመሰረቱት ምእመናን ባህታዊውን አባረሯቸው እሳቸው ግን የላከኝ እግዚአብሔር ነው በማለት በሌላ ጊዜ መጥተው ሌላም ትንቢት ጨምረው ተናግረው ሄዱ ይላሉ :

በወቅቱ የነበሩ ቆሞስ አባ ወልደ ሚካኤል ራዕዩም ፡- እንደፀሐይና እንደጨረቃ የምታበራ ቤተክርስቲያን ይሰራል በፀበሏ ብዙ ህሙማን ይፈወሳሉ እውራን ያያሉ ለምፃሞች ይነፃሉ ብዙ ገብረታምር የሚፈፀምባት ታላቅ የመማፀኛ ቦታ ትሆናለች፡፡ ብዙዎች ከህመማቸው የሚድኑባት ብዙኃኑ የሚፅናናባት የድሆች መጠጊያ፣የደካሞች የተስፋ ቦታ ከአራቱም ማዕዘነ ዓለም ህዝብ ወደዚህ ይጎርፋል፡፡ ከታላላቆቹ ገዳማት አንዲቷ ትባላለች እያሉ ተናገሩና ወደ መጡበት ተመለሱ ከእኚህ ባህታዊ ትንቢት በኋላ ክርክር ተዘጋና ታቦቷ የአምላክ እናት በመሆን እራሷን ችላ እንድትተከል እና በራሷ አስተዳደር እንድትመራ ተወሰነ፡፡
(ይቀጥላል)

ምድረ ዞረሬ (ምንጭ: በአድያመ ቅዱሳን በምድረ ዞረሬ የሚገኙ ገዳማት እና አድባራት፣ በደቀመዝሙር መለስ ኃይሉ) ዞረሬ የተባለዉ ቦታ ከአዲስ አበባ በስተ ሰሜን በኩል ወደ ከ80 እስከ 85 ኪ...
20/12/2021

ምድረ ዞረሬ (ምንጭ: በአድያመ ቅዱሳን በምድረ ዞረሬ የሚገኙ ገዳማት እና አድ
ባራት፣ በደቀመዝሙር መለስ ኃይሉ)

ዞረሬ የተባለዉ ቦታ ከአዲስ አበባ በስተ ሰሜን በኩል ወደ ከ80 እስከ 85 ኪሜ ርቀት አሌልቱ በተባለ ወረዳ የሚገኝ ሃገር ሲሆን ታላቁ ፃድቅ አቡነ ተክለሃይማኖት የተወለዱበት ልዩ ስሙ ኢትሳ ተክለሃይማኖት የተባለዉ ታላቁ ደብርን ጨምሮ ብዙ ጥንታዉያንና ባለ ብዙ ታላላቅ ታሪክ የሚገኙበት ገዳማት እና አብያተ ክርስትያናት የሚገኙበት አገር ነዉ።

ዞረሬ የሚለውን ትርጉም እንዴት እንደተሰጠው ጥቂት ከታሪኩ እንጋብዝዎት፤
ዝጣ ማር ዘቀደምት አበው አባ አምሀ ኢየሱስ ዘሀገረ ዘምድር ዞረሬ መካነ ሙላዱ ለተክለኃማኖት ጥንት ሙላፉ ሐገረ ኢየሩሳሌም ፤ንጉሱ የኢየሩሳሌም ድንግዛን ይሄ ወደ ወንግዛን የተባለው ንጉስ ሸዋን በሐይማኖት ለማነፅ በእግዚአብሔር ስለታዘዘ እኔ በምገዛው ሀገር የምትኖሩ ምዕመናን ሁሉ የተማሩ ከበኩር/ከመጀመሪያ/ልጆቻችሁ አንዳንድ ምረጡ ብሎ አዘዘ። የተመረጡት ሕዝቦች ሌዋውያኖችም ቁጥራቸው መቶሃያ ሲሆኑ ለእነዚህ አለቃቸው ወይም መሪያቸው አቦ ይድላ ነበር ትርጓሜውም የሸዋን ምድር በሀይማኖት ያነፀ ማለት ነው፡፡ ሲመጡም ታቦታቱን ንዋየ ቅዱሳቱን የቤተክርስቲያን መገልገያ ንዋያትን ሁሉ ይዘው እንደመጡና ከገርማማ ወንዝ በፈረስ እስከ አሌግቱ ወንዝ ድረስ አፋፉን ስለዞሩ ምደረ ዞረሬ የሚለውን ስያሜ እንዳገኘ መፅሀፍ ይመሰክራል በመቀጠልም በዚሁ ቀፃላ ፅላልሽ/ኢቲሣ/ ሀገሩ ውስጥ ከገባ በኋላ ፅላልሽ የምትባለውን/አቲሣን/ ሀገር መርጦ አለቃው ተቀመጠባት ተቀምጦባትም ሳለ የሀገሩን ሰዎች እያስተማረ እያጠመቀ ብዙ አብያተክርስቲያናትን አነፀ ከሀገሩም የከበሩ ሽማግሌዎችን ልጆች መርጦ አግብቶ ልጅ ወልዶ ስሙንም ሀርበሽ አለው ካልዕ/ሁለተኛ/ ስሙ ህይወት ከነፅዮን ይባላል የህይወት ከነፅዩን ትውልድ ሲወርድ ሲዋረድ 99 ቅዱሳኖች ተወልደውበታል ከ99 ቅዱሳኖች መካከል 12 ንበረዕድ ተሸሞበታል ከነሡ መካከል ታዴዎስ የተባለው እና ሚዲያም የተወለደው ንቡረዕድ ዘደብረ ፅዛልሽ/የአቲሣ/ ድርሳዎለች እንዲሁም ማትያስ ፈጠጋር/ምንጃር ከንኮራ/ደርሳዋለች ቀውስጦስ ሀገር መሀግል ንቡረ ዕድ ሲሆን 4ኛ ሣሙኤል የሀገር ወገግ ንቡረዕድ ነው፡፡ ታዲዎስና ማትያስም ሆነው ወንጌልን ሲያስተምሩ አለውያን የሆኑህ ዝቦች ያሉበት ደርሶዋቸው የአለውያኑ ንጉስ መፅሐፍችሁ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ያልፋል ይላል እነዚህን አስራ ሁለት ግመሎች በመርፌቀዳዳ ካሣለፋችሁ እኔም ህዝቦቼም በፈጣሪያችሁ ስም እናምናለን አለቸው እና አሳልፈው የአሳዩት ቅዱሳኖች ሀገር እንደሆነች እና አደሬ የሚለው የሀገር ስም ዞረሬ ከሚለው የመጣ ሣይሆን አይቀርም የሚሉ አሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ አደሬ ሀደረ/አደረ ከሚለው የግዕዝ ቃል የመጣ እንደሆነ እና አቡነ ተክለሃይማኖት ወንጌል አስተምረው ሲመለሱ አድረውበት ሰለነበር ማደሪያዬ/ጉዶዶ/ እንዳሉትና ከዚያም ሳይመጣ እንዳልቀረ ይነገራል፡፡
(ይቀጥላል)

Address

በአሌልቱ ወረዳ በምድረ ዞረሬ ወደ ኢቲሳ ተክለሃይማኖት መዉረጃ
Aleltu
30303

Telephone

+251920244705

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when ደብረ ሰዋሰዉ አደሬ ኪዳነምህረት ገዳም posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share