22/08/2026
‹‹...በቀናች ሃይማኖት ሆኖ ስሟን መጥራት ወድቆ የሚፍገመገመውን ያነሣል፣ ኀጥኡንም ጻድቅ ያደርጋልና፡፡ አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች የዓለም ሁሉ መድኃኒት የምትሆን የክብርት እመቤታችንን ስም የሚጠራ አንደበት ምንኛ የተባረከ ነው፡፡ እንደምን ያመልጥ! እንደምንስ ከመከራ ሁሉ ይድን ዘንድ ምንኛ ዕድለኛ ይሆን! እንደምን ከፍ ከፍ ይል! ይህ ስም ከሁሉ ይልቅ እንደምን የተከበረ ነው፡፡ በቃልኪዳን ውኃ ያነጻን ዘንድ ጻድቃንም ለመሆን ወደ እርሷ ለሚገቡ ኀጥአን አማላጅ ይሆን ይሆን ዘንድ በቃልኪዳን ቀለም በመንግሥተ ሰማያት በር የተጻፈ ነውና፡፡
አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች የክብርት እመቤታችን ቃልኪዳን የተጀመረ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኋላ አይደለም፡፡ አዳም ከገነት ከወጣና ከከብሩም ከተለየ ጀምሮ ነው እንጂ፡፡ ፈጽሞ ባለቀሰ ጊዜ ጌታችን አለኝታ ባለው ቃልኪዳን ‹ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ተሰቅዬ ሙቼ አድንሃለሁ› ብሎታልና፡፡ እመቤታችንን የዓለሙ ሁሉ መድኀኒት አድርጎ እንደፈጠራት ልብ አድርጋችሁ እነሆ ዕወቁ፡፡
ሁለተኛም ከሁሉ ይልቅ ከቸር ፈጣሪያችን በተሰጧት ኪዳናት ሁሉ ለእስራኤል ደኅንነት ትሆን ዘንድ ለሙሴ የተሰጠው ሕጉ የተጻፈበት ጽላት ያለበት መጠጊያ ብሎ ስም እንዳወጣለት ዕወቁ፡፡ የተወደዳችሁ የክርስቶስ ወገኖች ሆይ! አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች የክብርት እመቤታችን ስም አጠራር የማዳኑን ኃይል እንነግራችሁ ዘንድ ስሙ፡፡
አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት እመቤታችን ለነቢያት፣ ለሐዋርያት፣ ለጻድቃንና ለሰማዕታትም ሁሉ እመቤታቸው ናት-የእርሷ ቃልኪዳን ፍጻሜያቸው ነውና፡፡ በእርሷ ሥጋ መስቀልን አሳስቦ ከመናገሩ የተነሣ ምንም ለእነዚህ ክቡራን ሁሉ ቃልኪዳን ቢሰጣቸው የቃልኪዳን መመኪያ አክሊል እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ ይህን ቃልኪዳን በመስማት አምነው አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች የክብርት እመቤታችንን ስም በመጥራት የዳኑትን ስንቱን እንነግራችኋለን፡፡ የተአምራቷ ኃይል ከሰማይ ከዋክብት ከባሕር አሸዋ እጅግ የበዛ ነውና፡፡ ልመናዋ ክብሯ ለዘለዓለሙ በዕውነት በሁላችን በተዋሕዶ ልጆች ላይ አድሮብን ይኑር››
"የገነት ዛፍ ማርያም ሆይ፤ ልጅሽ በክንዱ ዐቅፎ በአፉ እየሳመ በቀኙ ሊያሳርፍሽ ባሳረገሽ ጊዜ፤ አንቺን ለመቀበል ክንፍ ለክንፍ እየተጋጩ እልፍ አእላፋት መላእክት ወረዱ፡፡ መላእክት በየነገድ በየነገድ ኾነው በመባርቅት ክንፎች እንደ ጋሻ ጋርደው ከኤዶም ገነት በተቀበሉሽ ጊዜ የሚያስደንቅ ክብር ለተገለጸባት ለክብርት ዕርገትሽ ሰላምታ ይገባል!!!
እንኳን ለእመቤታችን የዕርገት በዓል አደረሳችሁ አደረሰን!!!