13/08/2026
ነሐሴ ሰባት በዚች አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያምን ፅንስቷ ነው፣ የሐዋርያት አለቃ የከበረ ሐዋርያው ጴጥሮስ በዓል ነው፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ጢሞቴዎስ አረፈ፣ የራኄል ልጅ ቅዱስ ዮሴፍ ተወለደ።
በዓለ ጽንሰታ ለእግዝእትነ ማርያም
ነሐሴ ሰባት በዚች ቀን እግዚአብሔር የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤልን ወደ ከበረና ከፍ ከፍ ወዳለ ጻድቅ ኢያቄም ላከው አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያምን ፅንስቷንና ልደቷን በእርሷም ለዓለሙ ሁሉ ድኅነትና ተድላ ደስታ እንደሚሆን ነገረው።
ይህ ጻድቅም ሰው ኢያቄምና የከበረች ሚስቱ ሐና ልጅ ሳይወልዱ ሸመገሉ የከበረች ሐና መካን ሁናለችና ስለዚህም እጅግ ያዝኑ ነበር የእስራኤል ልጆች ልጅ ያልወለደውን ከእግዚአብሔር በረከትን ያጣ ነው እያሉ ያቃልሉት ነበርና። እነርሱም ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ዘወትር ፈጽሞ ይለምኑ ነበር። ከዚህም በኋላ ወንድ ልጅን ወይም ሴት ልጅን ቢወልዱ ለእግዚአብሔር ቤት አገልጋይ ሊያደርጉ ስለትን ተሳሉ።
የከበረ ኢያቄምም በተራራ ላይ ሳለ ሲጸልይና ሲማልድ እነሆ በላዩ እንቅልፍ እንቅልፍ ብሎት አሸለበ ያን ጊዜ ከእግዚአብሔር የተላከ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ተገለጸለት እንዲህም አለው ሚስትህ ሐና ትፀንሳለች ዓለሙ ሁሉ ደስ የሚሰኝባትን የብዙዎችም ዐይነ ልቡ ናቸው በእርሷ የሚበራላችውን በእርሷም ድኅነት የሚሆንባትን ሴት ልጅን ትወልድልሃለች።
በነቃ ጊዜም ወደ ቤቱ ሒዶ ለሚስቱ ለቅድስት ሐና ነገራት ራእይዋን እውነት እንደሆነች አመኑዋት ከዚህም በኋላ ነሐሴ ሰባት በዚች ቀን የከበረች ሐና ፀነሰች ለዓለም ሁሉ መመኪያ የሆነች በሁለት ወገን ድንግል የሆነች የአምላክ እናት እመቤታችንን ማርያምን ወለደቻት።
ቅዱስ ጴጥሮስ ሐዋርያ
በዚህችም ቀን የሐዋርያት አለቃ የከበረ ሐዋርያ ጴጥሮስ በዓል ነው። በዚች ቀን ጌታችን የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ እርሱ እንደሆነ በሐዋርያት መካከል ታምኗልና።
በከበረ ወንጌል እንደተባለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል ብሎ ጠየቃቸው እርሱ ልብን ኲላሊትን የሚመረምር ሰዎች የሚያስቡትን ሁሉ የሚያውቅ ሲሆን።
ያን ጊዜ ሐዋርያት ተጠራጣሪዎች ስለነበሩ ስለዚህ ያሰቡትን በልባቸው ያለውን እንዲናገሩ ከከተማ ውጭ አወጣቸው። ከእርሳቸውም ኤልያስ እንደሆነ የሚአስቡ አሉ ወይም ከቀደሙት ነቢያት አንዱ እንደሆነ የሚሉም ነበሩ። ጴጥሮስም በእነርሱ ላይ ተቆጥቶ ለምን እንዲህ ታስባላችሁ እርሱ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነው እንጂ አላቸው።
ስለዚህም የጴጥሮስን ሃይማኖት በመካከላቸው ይገልጥ ዘንድና ግልጥ ሊያደርግ ወደ ውጭ አወጣቸው። እንዲሁም በጠየቃቸው ጊዜ ኤልያስ እንደሆንክ ወይም ከቀደሙት ነቢያት አንዱ እንደሆንክ ሰዎች ይናገራሉ በማለት እነርሱ የልባቸውን ተናገሩት። ጴጥሮስ ግን አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ ብሎ በእውነት ምስክርን ሆነ።
ስለዚህም ጌታችን አመሰገነው የመንግሥተ ሰማያትንም ቊልፍ ሰጠው ። ከዚያች ቀን ወዲህ የሐዋርያት ሁሉ አለቃ ሆነ በእርሱም የሊቃነ ጳጳሳት የኤጲስቆጶሳት የቀሳውስትና የዲያቆናት ሹመት ተሰጠ። የቤተ ክርስቲያንም መሠረት ተባለ።
አባ ጢሞቴዎስ ሊቀ ዻዻሳት
በዚህችም ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሃያ ስድስተኛ የሆነ የከበረ አባት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ጢሞቴዎስ አረፈ። ይህንንም ቅዱስ በእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ይሆን ዘንድ የክብር ባለቤት ጌታችን መርጦት ተጋዳይ የነበረ አባ ዲዮስቆሮስ በደሴተ ጋግራ ከአረፈ በኋላ ሊቀ ጵጵስና ተሾመ።
ይህም አባት ጢሞቴዎስ ብዙ መከራ ደርሶበታል። ንጉሥ መርቅያን ለእስክንድርያ አገር ሌላ መናፍቅ ሊቀ ጳጳሳት ሹሞ አባት ጢሞቴዎስን አስቀድሞ አባ ዲዮስቆሮስ ተሰዶባት ወደ ነበረች ደሴተ ጋግራ አጋዘው። መርቅያንም ከሞተ በኋላ የእስክንድርያ ሰዎች ተነሥተው መርቅያን የሾመውን ሊቀ ጳጳሳት ገደሉት አባት ዲዮስቆሮስ እንዳዘዘ አባ ጢሞቴዎስን መልሰው ሾሙት።
ከዚህም በኋላ የመርቅያን ልጅ ልዮን ነገሠ ያን ጊዜ አባ ጢሞቴዎስን ሁለተኛ ወደ ደሴተ ጋግራ አጋዘው በዚያም ዐሥር ዓመት ኖረ ልዮን እስከ ሞተ ድረስ ከእርሱም ኋላ ዘይኑን ነገሠ። ያን ጊዜም አባ ጢሞቴዎስን ወደ መንበረ ሢመቱ በታላቅ ክብር መለሰው ሕዝቡንም እያስተማራቸውና እየመከራቸው በቀናች ሃይማኖትም እያጸናቸው ኖረ።
በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበርም ሃያ ሁለት ዓመት ኖረ እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።
ቅዱስ ዮሴፍ ጻድቅ
በዚህችም ቀን የራኄል ልጅ ዮሴፍ ተወለደ።
(ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 7 ና ከገድላት አንደበት)
🗓 የነሐሴ 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.በዓለ ጽንሰታ ለእግዝእትነ ማርያም
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱስ ገብርኤል መበሥር
4.ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
5.አፄ ናዖድ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
6.ቅዱስ ዮሴፍ ጻድቅ (ወልደ ያዕቆብ-ልደቱ)
7.አባ ጢሞቴዎስ ሊቀ ጳጳሳት
🗓ወርሐዊ በዓላት
1.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)
2.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
3.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
4.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
5.አባ ባውላ ገዳማዊ
6.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
7.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)
የነሐሴ 7 ቀን የእለቱ ግጻዌ
መልእታት
👇
ዕብራ 9÷1-11
1ጴጥ 2 ÷6-18
ሐዋርያት 10፥ 1-30
ምስባክ 👇
"ብጹዕ ብእሲ ዘእንተ ገሠጽኮ እግዚኦ። ወዘመርሀኮ ሕገከ። ከመ ይትገኅሥ እመዋዕለ እኩያት። መዝ.93÷12-13
ትርጉም➣"ለኃጢአተኛ ጕድጓድ እስኪቈፈር ድረስ ከክፉዎች ዘመናት ይወገድ ዘንድ፥ አቤቱ፥ አንተ የገሠጽኸው ሕግህንም ያስተማርኸው ሰው ምስጉን ነው።" መዝ.93÷12-13
የእለቱ ወንጌል📖
👇
ማቴዎስ 16÷13-24
የሚቀደሰው ቅዳሴ
👇
ቅዳሴ ዘእግዝእትነ ነው።
የነሐሴ 7 ቀን ወንጌል ሙሉ ንባብ📖
ማቴዎስ 16
¹³ ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፦ ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ።
¹⁴ እነርሱም፦ አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት።
¹⁵ እርሱም፦ እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው።
¹⁶ ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፦ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ።
¹⁷ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ።
¹⁸ እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።
¹⁹ የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።
²⁰ ያን ጊዜም እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለማንም እንዳይነግሩ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው።
²¹ ከዚያን ቀን ጀምሮ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ ከሽማግሎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጥላቸው ጀመር።
²² ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ፦ አይሁንብህ ጌታ ሆይ፤ ይህ ከቶ አይደርስብህም ብሎ ሊገሥጸው ጀመረ።
²³ እርሱ ግን ዘወር ብሎ ጴጥሮስን፦ ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው።