21/08/2026
ጌታ ኢየሱስ በዮሐንስ 21:19 ላይ ለጴጥሮስ «ተከተለኝ» የሚል ጥሪ ሲያቀርብለት፤ ከፊቱ የሚጠብቀውን መራራ መስዋዕትነት እና የሞቱን መንገድ ቁልጭ አድርጎ ከነገረው በኋላ ነበር። ይህ የክርስቶስ ጥሪ፤ ዛሬ እኛ የምንኖርበት የዲጂታል ዓለም ከሚሰብከው እውነታ ጋር ሲነጻጸር እጅግ ጥልቅ የሆነ ተቃርኖን ያሳያል።
በአሁኑ የሶሻል ሚዲያ እና የዘመናዊው ባህል እሽክርክሪት ውስጥ ሰዎችን ለመሳብ እና «ተከታይ» (Followers) ለማፍራት የሚኬድበት መንገድ በፍጹም የተለየ ነው። ዛሬ ብዙዎች ተከታይ የሚያበዙት የሰዎችን ስሜት የሚያስደስት፣ ምቾት የሚሰጥ እና ፍላጎታቸውን ብቻ የሚያረካ ነገር በመናገር ነው።
የሰዎችን ስሜት የሚደግፍ እና መስማት የሚፈልጉትን ብቻ የሚያበስር አካልን መከተል እጅግ ቀላል ነው፤ የሰው ልጅ ተፈጥሮም ወደዚህ ያደላል። እንዲህ ያለው መንገድ ምንም ዓይነት ዋጋ መክፈልን፣ መስዋዕትነትን ወይንም ራስን መካድን አይጠይቅም። የዛሬው የዲጂታል ዓለምም የሚያበረታታው ይህንኑ የቅጽበታዊ ደስታ እና የእራስን ስሜት የማርካት አቋራጭ መንገድ ነው።
በሌላ በኩል ግን... የጌታ ኢየሱስ ጥሪ ሙሉ በሙሉ ተቃራኒ ነበር!
ክርስቶስ ሰዎችን የጠራው ጊዜያዊ ምቾትን፣ ቁሳቁሳዊ ሀብትን ወይም ሰዎችን ለሙገሳ ቃል በመግባት አይደለም። ይልቁንም እውነትን እና የእውነተኛ ደቀ መዝሙርነትን ዋጋ በግልጽ ጠረጴዛው ላይ በማስቀመጥ ነበር!
ኢየሱስ ለጴጥሮስ ከፊቱ የሚጠብቀውን የበረታ ፈተና እና አሰቃቂ ሞት ሳይደብቅ «ተከተለኝ» ማለቱ፤ የእሱ ጥሪ በጊዜያዊ ስሜት ሳይሆን፣ በጥልቅ እምነት እና በመስዋዕትነት ዐለት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያበስራል።
በጊዜያዊ ስሜትና በይስሙላ ደስታ ላይ የተመሠረተ ተከታይነት የጥዋት ጤዛ ነው፤ ሁኔታዎች ሲቀየሩ ወይም ፈተናዎች ሲደቅኑ ያ ጥረት አየር ላይ በኖ ይቀራል! ዋጋውን አውቆ፣ እውነቱን ተቀብሎ እና መስቀሉን ተሸክሞ መከተል ግን የጸና እና የማይናወጥ የህይወት መሠረት ይፈጥራል።
አዎ! በስሜታችን የሚያስደስቱንን ነገሮች መከተል ይቀል ይሆናል፤ ነገር ግን በህይወታችንም ሆነ በትውልድ ላይ እውነተኛ እና ዘላቂ ለውጥ የሚያመጣው ዋጋ የሚያስከፍለውን የእውነት መንገድ መከተል ብቻ ነው።
Jo Yoseph