ኪዳነምህረት እናቴ

ኪዳነምህረት እናቴ ኪዳነምህረት እናታችን

26/04/2025
29/01/2025

“ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ”
እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ዕረፍት አደረሰን፤አደረሳችሁ!!!
በመ/ር ጌታቸው በቀለ
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት በመዝሙር፣ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ፣ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ፣ አባ ጊዮርጊስ በሰዓታት እንዳመሰገኗት ሁሉ፤ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በመደነቅ “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ፣ ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኵሉ” በማለት ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዕረፍት ገልጿል /ድጓ ዘአስተርእዮ ማርያም/ ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ምድር ፷፬ ዓመት ኖራ ያረፈችው ጥር ፳፩ ቀን ነው፤ በዚህ ዕለትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ዕረፍት በማሰብ በዓሉን በታላቅ ድምቀት ታከብራለች፡፡
የቤተክርስቲያን ታሪክ ስናጠና ከአንደኛው እስከ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ነገረ ክርስቶስን (Christology) ከነገረ ማርያም (Mariology) ጋር ያለውን ጥልቅ ምስጢር በመረዳታቸው ምሥጢረ ሥጋዌን ከማስተማራቸው አስቀድሞ ነገረ ማርያምን በጥልቀት ይማሩን ያስተምሩ እንደነበር እናስተውላለን፡፡ ሊቃውንቱ በትምህርታቸው ሁሉ ነገረ ማርያም የሃይማኖት ክፍል (Dogma) መሆኑን አብራርተው ገልጠውታል፡፡ ምክንያቱ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት የተወለደው አካላዊ ቃል 5500 ዘመን ሲፈጸም ያለ አባት ከቅድስት ድንግል ማርያም በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና ተወለደ፡፡ እርሱ በእውነት የባሕርይ አምላክ ነው፤ እርሷም በእውነት የአምላክ እናት ናት ብሎ መመስከር ሃይማኖት ነው፡፡
ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ይህን ይዛ በዘወትር ሥርዐተ አምልኮቷ ጊዜ በምትገለገልባቸው የተለያዩ የጸሎትና የቅዳስያት መጻሕፍት ሁሉ የነገረ ማርያም አስተምህሮዋን በስፋትና በጥልቀት ትመሰክራለች፡፡ በዚህም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ሁለንተናዊ ሕይወት ከእግዚአብሔር የማዳን ሥራ (Soteriology) ጋር በእጅጉ የተዋሐደና በቀጥታ የተገናኘ መሆኑን እናስተውላለን፡፡
የእመቤታችን ክብሯ ከመላእክትና ከደቂቀ አዳም ከፍ ከፍ ያለ መሆኑ፤ የባሕርይ አምላክ አካላዊ ቃል ክርስቶስን በኅቱም ድንግልና ፀንሳ በኅቱም ድንግልና የወለደች በመሆኗ ወላዲተ አምላክ (Theotokos – Mother of God)፣ እመ እግዚአብሔር ጸባኦት፣ እመ ብርሃን፣ ማኅደረ መለኮት እያለች ታስተምራለች፡፡ በሥጋዋ በኅሊናዋ ድንግል በክልኤ የተባለች ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድመ ፀኒስ ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ፀኒስ ጊዜ ወሊድ፣ ድኅረ ፀኒስ ድኅረ ወሊድ ጽንዕት ናት፡፡ በመሆኑም አምላክን ስትወልደው ማኅተመ ድንግልናዋ አለመለወጡ አምላክም ሰው ሲሆን ባሕርየ መለኮቱ ላለመለወጡ፣ ዳግመኛም ድንግል ወእም ስትባል መኖሯ አምላክ ወሰብእ ሲባል የመኖሩን ይህን ታላቅ የሥጋዌ ምሥጢር ያወቅንባት የተረዳንባት መሆኗን ቅድስት ቤተክርስቲያን ታስተምረናለች፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሦስት ዓመት በእናት በአባቷ ቤት፣ ዐሥራ ሁለት ዓመት በቤተመቅደስ፣ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከልጇ ጋር፣ ዐሥራ አምስት ዓመት በዮሐንስ ቤት፣ በአጠቃላይ ስድሳ አራት ዓመት በዚህ ምድር ላይ ኖራ ዐርፋለች፡፡ለዚህም በህይወተ ሥጋ በኖረችበት ዘመን ልክ ቅዱስ ኤፍሬም ውዳሴ ማርያምን በ፷፬ አንቀጽ ከፍሎ ፷፬ ጊዜ ሰአሊ ለነ ቅድስት ብለን እንድናመሰግናት አድርጓል፡፡
በጥር ፳፩ ቀን እመቤታችን ጌታችን አየሱስ ክርስቶስ፣ ቅዱሳን መላእክትና ደጋግ ቅዱሳን አባቶች በተገኙበት እጅግ ታላቅ በሆነ ክብር ባረፈችበት ዕለት ሐዋርያት በጌቴሴማኒ ሊቀብሯት ሲሉ አይሁድ የክርስቶስ የሆኑትን ማሳደድ ልማዳቸው ነበርና “እርሷንም እንደ ልጇ ተነሳች አረገች እንዳይሉ፣ ሥጋዋን እናቃጥል” ብለው በክፋት ተነሱባቸው፡፡ ከአይሁድም ወገን የሆነ ታውፋንያ የሚባል ሰው የከበረ ሥጋዋን ለማቃጠል ሲታገል፣ በተዓምራት ተቀጣ፤ ሥጋዋ ከጌቴሴማኒ ተነጥቆ በገነት በዕፀ ሕይወት ስር እስከ ነሐሴ ፲፬ ቀን ቆይቷል፡፡ ኋላም በልጇ ኃይልና ስልጣን ከሞት እንድትነሳና እንድታርግ አድርጓታል፡፡ዕረፍቷም በመልክአ ማርያም “ያለመጨነቅና ያለፃእር ከሥጋዋ ለተለየች ነፍስሽ ሰላምታ ይገባል›› እንደተባለው ያለመጨነቅና ያለፃእር ነበር፡፡

እመቤታችን ሕይወቷ ከሕፃንነቷ ጀምሮ በብዙ ፈተና የተሞላ ነበር፡፡ በተለይም ስምኦን አረጋዊ በቤተመቅደስ “በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል” ብሎ እንደተነበየላት /ሉቃ.፪፥፴፭/ በግብፅ ስደት፣ በቀራንዮ ስቅለት፣ በአይሁድ ክፋት የደረሰባት መከራና ኃዘን አብቅቶ ወደ ዘላለም ደስታ ትገባ ዘንድ ሞትን ቀምሳለች፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን “ወዳጄ ሆይ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ ነዪ፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ፤ ዝናሙም አልፎ ሔደ፡፡ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፤ የዜማም ጊዜ ደረሰ፡፡ የቍርዬም ቃል በምድር ላይ ተሰማ” /መኃ.፪፥፲-፲፬/ እንዳለ ኀዘኗ ያልፍ ዘንድ ወደ ዘላለም ደስታም ትገባ ዘንድ ዐርፋለች፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከክፉ ዓለም ወደ በጎ ዓለም አሸጋግሯታልና” ያለውም ይህንን ያመለክታል፡፡

እንደማጠቃለያ
በዚህ ዓለም በአካለ ሥጋ ያሉ ሰዎችን ልደት በባህላዊ መንገድ ስናከብር በመወለዳቸው ደስ ይላቸው ዘንድ አብረን በመደሰት ነው፡፡ በሕይወተ ሥጋ የተለዩንን ዘመዶቻችንን ስናስብ ደግሞ “ነፍስ ይማር” እያልን በመጸለይ ነው፡፡ የቅዱሳንን እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ልደትንና ዕረፍትን ስናስብ ግን እነርሱን እያመሰገንን፣ ተጋድሏቸውን እያሰብን፣ ያከበራቸውን አምላክ እያከበርን፣ ክብራቸውንም እያደነቅን፣ በረከታቸው፣ ረድኤታቸው፣ አማላጅነታቸው ይደርሰን ዘንድ እየተማጸንን ነው፡፡ የእመቤታችንንም ዕረፍት ስናከብር ይህንን እያስተዋልን ሊሆን ይገባል፡፡
የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
ዋቤ መጻሕፍት፡-
✍️ መጽሐፍ ቅዱስ
✍️ ነገረ መርያም
✍️ መልክአ ማርያም
✍️ መጽሐፈ ስንክሳር ጥር 21
✍️ ወላዲተ አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ

18/08/2024

Address

Addis Ababa

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when ኪዳነምህረት እናቴ posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share