Micah Alaye - ሚካ አላዬ

Micah Alaye - ሚካ አላዬ ሃይማኖተ አበዉ

ጷግሜ ፩ የማዕተብ ቀን!ማዕተብ አለማሰር ዘመናዊነት ነውን?ስለምን ማዕተብ እናስራለን??ዛሬ ዛሬ ማዕተብ አለማሰር ዘመናዊነት የሚመስላቸው ሰዎችን እያየን ነው፡፡ሰይጣን እጅግ ጥበበኛ ከመሆኑ ...
06/09/2021

ጷግሜ ፩ የማዕተብ ቀን!
ማዕተብ አለማሰር ዘመናዊነት ነውን?
ስለምን ማዕተብ እናስራለን??
ዛሬ ዛሬ ማዕተብ አለማሰር ዘመናዊነት የሚመስላቸው ሰዎችን እያየን ነው፡፡
ሰይጣን እጅግ ጥበበኛ ከመሆኑ የተነሳ የሰውን ድክመት እያየ የሚያሸንፍበትን የሚያስክድበትን ስልት እንደ ጊዜው ይቀያይራል በዚህ በዘመናችን ደግሞ ዲያቢሎስ በዘመናዊነት ሽፋን ስለሱ ተገርፎ ተጠምቶ ተሰድቦ ሀሞትን ጠጥቶ ተሰዶ ፊቱ ላይ ተተፍቶ ፊቱን ተመቶ ራቁቱን ቀራኒዮ ላይ ተሰቅሎ የተከፈለለትን ያ... ያ... ያን የመስቀሉን ፍቅር ያን የማይከፈል ውለታን ያን ዲያቢሎስ ያፈረበትን እኛ ደግሞ ሞት ሆይ መውጊያህ የታለ? ሲኦል ሆይ ድል መንሳትህ የታለ? ብለን በሞት የዘበትንበትን የጥል ግድግዳ የፈረሰበትን እኛና አምላካችን ሥላሴ የታረቅንበትን መስቀል ጥልን የገደለበት መስቀል "ብርሀናችሁ በሰው ሁሉ ፊት ይብራ" እንዲል መጽሐፍ በኩራት በደስታ አንገታችን ላይ አስረን በሰው ሁሉ ፊት የአምላካችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር እንዳንገልጽ ዲያቢሎስ በአንድም በሌላም መንገድ ማዕተቡን መስቀልኑ እያስበጠሰ ከጎኑ እያሰለፋቸው ነው፡፡
ወዳጄ ሆይ አትሸወድ ባሰርከው መስቀል ላይ የምታፍር ከሆነ በክርስቶስ አፍረሀል በክርስቶስ ካፈርክ
‹‹በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ
እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ ፣
በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው
በአባቴ ፊት…..........›› ማቴ 10፡33 እንግዲህ በማዕተባችን ስለ አምላካችን ስለ ቀናች እምነታችን
መመስከር ካልቻልንና ካፈርን እንዴት ነው ለእኛስ ሊመሰክርልን
የሚቻለው? ስላመንበት ነገር ምንጊዜም ከመመስከር አንመለስ፡፡
በእምነት ቆመን ሁል ጊዜም እንደ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ
እንበል ሁል ጊዜዘም በቃል በስራ የተሰቀለውን ክርስቶስን
እሰብካለሁ ‹‹በወንጌል አላፍርምና›› ሮሜ 1፡16
የሚገርመው ሰይጣን አንገትህ መስቀል በማሰርህ እንደሚያሳፍርና ማሰር እንደለለብህ ሲነግርህ ሌላ የilluminati አርማ ባለ አምስት ኮከብ ወይም ምላጭ ወይም ሰንሰለት ወይም ሌላ ነገር ማሰርህ ግን እንደሚያሳፍር አለመንገሩ ነው፡፡ ወይም ዛሬ ጸሎት ስታደርግ ለማደር ብትፈልግ ጸሎት እያደረክ ያለ እንቅልፍ ማደሩ ለጤናህ ጎጂ እንደሆነ ሲነግርህ ፓሪ እየጨፈርክና እየጠጣህ ማደርህ ግን ለጤናህ ጥሩ እንዳይደለ አለመንገሩ ነው፡፡
እናቶቻችን መስቀልን ግንባሮቻው ላይ አንገታቸው ላይ ሲነቀሱ ያሾፈ ወጣት እጁላይ እባብና ድራጎን ይነቀሳል፡፡ ዲያቢሎስ ሁሌ ለማሳት ዘዴ አያጣም፡፡
እኔግን እንደ ሐዋርያው በማዕተቤ በመስቀል በወንጌል በክስስትናዬ በኦርቶዶክስነቴ አላፍርምና ማዕተቤን መበጠስ ከፈለጉ ከእናንገቴ ይውሰዷት፡፡
ዘመናዊነት ለዲያቢሎስ መወገን ለእርሱም መስገድ መገዛት በክርስትና ማፈር ከሆነ ይቅርብኝና ፋራ ልሁን እኔ ግን እላለሁ እርድና (አራድነት) ዘመናዊነት ስልጣኔ በእምነት(በሃይማኖት) ነው፡፡
ሰው ስጋውን ቢጠቅም በሥጋው ቢዘምን በነፍሱ በመንፈስ ግን ባዶ ከሆነ ምን ይጠቅመዋል????፡፡
ስለምን ማዕተብ እናስራለን????????
ማዕተብ: የክርስትናችን ዓርማ የነፍሳችን ሰንደቅ ዓላማ
ሦስት ቀለማት ያላቸው ክሮች የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሲኾኑ አንድ ላይ መፈተላቸው ወይም አንድ መኾናቸው ቅድስት ሥላሴ ማለት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በመለኰት በህልውና አንድ አምላክ መኾናቸውን ያመለክታል፡፡ ጥቁሩ፡- ክርስቲያን ስለ ሃይማኖት የሚቀበለው መከራ የሚሸከመው መስቀል፣ ቀዩ ፡- በሰማዕትነት ደም የማፍሰስ ሲኾን ቢጫው ደግሞ የክርስቲያን ተስፋ የሃይማኖት ምልክት ነው፡፡
ክርስቲያን ለክርስቶስ ታማኝ በመኾኑ በነፍሱ ሞግዚት በቄሱ እጅ ከሕፃንነቱ ጀምሮ የድኅነቱ ምልክት በሚኾን አንገቱ በማዕተበ ክርስትና ይታሰራል፡፡ ማዕተብ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ ስለ እኛ ቤዛ ለመኾን የብረት ሀብል /የብረት ገመድ/ በአንገቱ ታስሮ በአይሁድ መጎተቱን ስለሚያስታውሰን ለታማኝነታችንና ለክርስቲያንነታችን ምልክትነቱ ማረጋገጫ ስለኾነ አናፍርበትም፡፡
ይልቅስ እንኮራበታለን እንጂ፡፡
አንዲት ሀገር ነፃና ሉዓላዊ መኾኗ የሚታወቀው ወይም ራሷን የቻለች መንግሥት ያላት ከባዕድ ቀንበር ቅኝ ግዛት ነፃ የወጣች መኾኗ በቀዳሚነት የሚለየው በባንዴራዋ ምልክትነት እንደኾነ እንደዚኹም አንድ ክርስቲያን በክርስቶስ አምኖ በጥምቀት ከዲያብሎስ ቁራኝነት ነፃ መውጣቱ፣ ነፃነት ያለው አማኝ መኾኑ የሚታወቀው በማተቡ ምልክት ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች የማዕተብ ሥርዐትን ለመቃወምና ዘመናውያን መስለው ለመታየት ‹‹እምነት በልብ ነው›› ይላሉ፤ ተሳስተዋል! ሃይማኖት የልብ ብቻ አይደለም፤ የጠቅላላው ሕዋሳት ኹሉ ናት ፡፡
አጋንንት የለከፏቸው ሰዎች ማተብና መስቀል አይወዱም፡፡ የሰፈረባቸው ርኩስ መንፈስ ማተብ እንዲበጥሱ መስቀል እንዲጥሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ማተብ በሰይጣን ዘንድ ከተጠላ በአጋንንት ላለመለከፍ የማዕተቡ መኖር ይጠቅማል ማለት ነው፡፡
የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያኖች በአንገታቸው ላይ ክር ያስራሉ፤ ለሕፃኖቻቸውም ክርስትና ሲነሡ ክር ያስሩላቸዋል፡፡ በሕፃናቱም ኾነ በዐዋቂዎቹ ክርስቲያኖች አንገት ላይ የሚታሰረው ክር በግእዝ
ማዕተብ በአማርኛ ማተብ ይባላል፡፡ ቃሉ የወጣው
ዐተበ ካለው ግእዛዊ ግስ ነው፡፡ ዐተበ ፍቺው አመለከተ፣ ባረከ ማለት ነው፤ ማዕተብ ፍቺው ከዚኽ ይወጣል፡፡ ምልክት ማለት ነው፡፡
ለተጠመቁ ክርስቲያኖች የክር ማተብ ለሃይማኖት ምልክትነት ወይም መታወቂያ ከመኾኑ በፊት፣ በብሉይ ኪዳን ዘመን የሃይማኖት አባቶች ከጣዖት አምላኪዎች ተለይተው የሚታወቁበት ምልክት ነበራቸው፡፡ ስለ ታላቁ የሃይማኖት አባት ስለ ጻድቁ አብርሃም የሃይማኖት ማኅተም(ምልክት) ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሳይገረዝም በነበረው እምነት ያገኘው የጽድቅ ማኅተም የኾነ የመገረዝን ምልክት ተቀበለ፡፡›› (ሮሜ ፪÷፲፩፤ ዘፍጥ.፲፯÷፱ – ፲፬)
በሥርዐተ ኦሪት ብኵርና ከጥንት ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ገንዘብ ኾኖ ስለሚቆጠር ብኵርና ላለው ኹሉ የአባት በረከት ከሌሎች ይልቅ በይበልጥ ምርቃት ዕጥፍ ድርብ ኾኖ ስለሚሰጠው ብኵርና ይወደዳል፤ ይፈቀራል፡፡ ብኵርና ማቃለል ዋጋ የሌለው ጸጸትን ያስከትል ነበር፡፡ ብኵርና ለዘመነ ሐዲስ ክርስትና ምሳሌ እንደኾነ ይታመናል፡፡ ክርስትናውን ንቆ አቃሎ ዓለምን መስሎ የሚኖር ሰው፣ ለጊዜያዊ መብል ፍለጋ ብኵርናውን በሸጠው በያዕቆብ ወንድም ዔሳው ተመስሏል፤ ‹‹. . .ስለ አንድ መብል በኵርነቱን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ለዚኽ ዓለም የሚመች ሰው እንዳይኾን ተጠንቀቁ፡፡ ከዚያ በኋላ እንኳ በረከቱን ሊወርስ በወደደ ጊዜ እንደተጣለ ታውቃላችኹና በእንባ ተግቶ ምንም ቢፈልገው ለንስሐ ስፍራ አላገኘምና፡፡›› (ዕብ.፲፪÷፲፮፤ ዘፍጥ.
፳፭÷፳፱ – ፴፬፤ ፳፯÷፴ – ፵)
ብኵርና ለክርስትና ምሳሌ መኾኑ ከላይ ተገልጧል፡፡ ትዕማር ከይሁዳ መንትያ ልጆችን ፀንሳ በምትወልድበት ጊዜ በኵሩ እጆቹን ሲያወጣ አዋላጅቱ ቀይ ፈትል ለምልክት አስራበታለች፡፡ ይህ ምሳሌያዊ ድርጊት በሐዲስ ኪዳን ሲተረጎም ከትዕማር የተወለደው በኵሩ ዛራ ለክርስቲያን ምሳሌ ሲኾን ቀዩ ፈትል ለክርስትናው ምልክት፤ ለማዕተብ ምሳሌ ኾኗል፡፡
አዋላጅቱ ለአጥማቂው ቄስ ምሳሌ ናት፡፡ ትዕማር የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ስትኾን በኋላ የመጣው ፋሬስ በኵሩን ጥሶ ቀድሞ መወለዱና ከቀይ ፈትል አልባ መኾኑ በምሳሌያዊ ትንቢትነት፣ ከቤተ ክርስቲያን በጥምቀት ከተወለዱ በኋላ ክርስትናቸውንና ጥምቀታቸውን ክደው የእውነተኞቹ ክርስቲያኖች ተቃዋሚዎች በመኾን ፊት ከተፈጠረ ጆሮ እንደ ቀንድ ብቅ ያሉ የመናፍቃንና የኢጥሙቃን (ኢአማንያን) ምሳሌ እንደኾኑ ያስረዳል፡፡ (ማቴ.፩÷፫፤ ዘፍጥ.፴፰÷ ፳፮ – ፴)
በዛራ ልማድ ጌታችን ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ እመቤታችን አውራ ጣቱን በክር አስራዋለች፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ለኖሎት ተገልጦ ምልክቱን እንዲህ ሲል ነግሯቸዋል፡- ‹‹ወከመዝ ትእምርቱ ለክሙ ትረክቡ ሕፃነ እሱረ መንኮብያቲኹ፤ ምልክቱ ይህ ነው፡፡ ሕፃኑ አውራ ጣቱን ታስሮ ታገኙታላችኹ፡፡›› (ሉቃ.፪÷፲፪) እመቤታችን አውራ ጣቱን በክር እንዳሰረችው ‹‹ወወለደት ወልደ ዘበኵራ ወአሰርቶ መንኮብያቲኹ፤ የበኵር ልጅዋን ወለደች፤ አውራ ጣቱን አሰረችው፡፡›› ( ሉቃ.፪÷፯፤ የግእዝና አማርኛ ነጠላ ትርጉም አማርኛ ሒዲስ ኪዳን ይመልከቱ)
ድንግል እመቤታችን አውራ ጣት ማሰሯ ለክርስቲያኖች ማዕተብ ማሰር አብነት ኾኗል፡፡ ጣቱን ማሰሯ ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ይኸውም፡- ፩ኛ/
ሕፃን ስለኾነ እንዲያጸናው፤ ፪ኛ/ ጣቱን ባይታሰር ምትሀት ነው፤ ሰው አልኾነም ለሚሉ መናፍቃን ለክሕደታቸው ምክንያት ባገኙ ነበርና ምክንያት ለማሳጣት፤ ፫ኛ/ ቀደም ብለን እንደገለጽነው ልማዳችንን አስቀረብን እንዳይሉ በዛራ ልማድ፤ ፬ኛ/
ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በዕለተ ዓርብ ከመስቀል አውርደው እንዲኽ አድርገው ይገንዙሃል ለሰው ቤዛ ለመኾን ልትታሰር መጣኽን፣ ስትል ነው በማለት መምህራነ ቤተ ክርስቲያን በአንድምታ ትርጓሜያቸው ያትታሉ፡፡
በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ዘንድ ክርስቲያን የኾነ ኹሉ ማተብ የማሰር ልምድ የጀመረው በሃይማኖተ አበው በ ድርሳነ ያዕቆብ እንደተገለጸው፣ ከልደተ ክርስቶስ በኋላ በእስክንድርያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአምስተኛው ምእት ዓመት ያስተምር በነበረው በሊቀ ጳጳሱ በያዕቆብ ዘእልበረዳኢ ዘመነ ስብከት ነበር፡፡
ያዕቆብ ዘእልበረዳኢ የሶርያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባት ነው፡፡ መምህሩ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ስለ ተዋሕዶ ሃይማኖት ሲመሰክር በመለካውያን (ልዮናውያንና ንስጥሮሳውያን) ግፊትና ተቃውሞ መከራ ሲቀበል ጽሕሙ ተነጭቶ ጥርሶቹ ረግፈው ስለነበር የተነጨ ጽሕሙን የረገፉ ጥርሶቹን በመሐረም ቋጥሮ ‹‹ዝንቱ ፍሬ ሃይማኖቱ ለእግዚአብሔር፤ ለእግዚአብሔር የምናቀርብለት የሃይማኖት ፍሬ ይህ ነው›› በማለት ለእስክንድርያ በያዕቆብ ዘእልበረዳኢ እጅ ልኮላታል፡፡ እርሱም ስለ ሃይማኖት በደሴተ ጋግራ ታስሮ ሰማዕት ኾኗል፡፡
ደቀ መዝሙሩ ቅዱስ ያዕቆብ አልባሌ መስሎ በሶርያ ብቻ ሳይኾን በእስክንድርያ የሴት ቀሚስ ሳይቀር ለብሶ ሲያስተምር ንስጥሮሳውያን ከጉባኤው እየገቡ ስላስቸገሩት ኦርቶዶክሳውያንን ከመናፍቃን ለመለየት ከእግዚአብሔር ባገኘው ምልክት ጥቁር ቀይ ቢጫ ክሮች አንድ ላይ ፈትሎ በአንገታቸው ላይ ያስርላቸው ጀመር፡፡ ሌሊት ሌሊት ሲያስተምርና ሲጸልይ የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ጥርሶቹ እንደ ፋና ያበሩለት ነበር፡፡ ይህም በተኣምራት የተፈጸመ ነው፡፡
ሦስት ቀለማት ያላቸው ክሮች የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሲኾኑ አንድ ላይ መፈተላቸው ወይም አንድ መኾናቸው ቅድስት ሥላሴ ማለት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በመለኰት በህልውና አንድ አምላክ መኾናቸውን ያመለክታል፡፡ ጥቁሩ፡- ክርስቲያን ስለ ሃይማኖት የሚቀበለው መከራ የሚሸከመው መስቀል፣ ቀዩ፡- በሰማዕትነት ደም የማፍሰስ ሲኾን ቢጫው ደግሞ የክርስቲያን ተስፋ የሃይማኖት ምልክት ነው፡፡
ቆይቶ ግን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሕፃናት ክርስትና ሲነሡ፣ ኢአማንያን አምነው ሲጠመቁ ቀይ፣ ነጭና ሰማያዊ ፈትሎች በአንድ ላይ ተገምደው መታሰር ጀመረ፤ ትርጓሜውም የሦስቱ አንድ ላይ መገመድ የሥላሴን አንድነት ሦስትነት የሚያመለክት ምሳሌ ነው፡፡
ይኽንንም ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲያስረዱ፡-
ሥላሴ ማዕተበ ብርሃን ኃይለ ሃይማኖቶሙ ለክርስቲያን፤ ሥላሴ ለክርስቲያን ኹሉ የሃይማኖታቸው ጉልበት መታወቂያ የብርሃን ማዕተብ (ምልክት) ናቸው፤ ብለዋል፡፡
ቀለሞቹ ደግሞ ቀይ፡- ክርስቶስ ደሙን አፍስሶ አድኖናል፤ ስለ ስሙም በሰማዕትነት ደማችንን ማፍሰስ ይገባናል የማለት፤ ነጩ፡ – የጥምቀት በጥምቀትም የሚገኝ ስርየተ ኃጢአት፤ ሰማያዊ፡-
በጸጋ ልጅነት አግኝቻለኹ፤ ሰማያዊ አባት አለኝ፤ ሰማያዊ ርስት መንግሥተ ሰማይ ይቆየኛል፤ ስለዚኽም በሰማያዊ ግብር ጸንቼ መኖር በሰማያዊት ሕግ ሕገ ክርስቶስ ወንጌል ተመርቼ መኖር ይገባኛል እንደማለት ነው፡፡
በኢትዮጵያ ክርስትና የገባው በዘመነ ሐዋርያት በመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ ይኹንና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ጵጵስና ከሌሎች ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያን ጋራ የዕኩልነት ማዕርግ ያገኘችው በአራተኛው ምእት ዓመት በቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን እንደኾነ ተረጋግጧል፡፡ በዚኽ ዘመን አቡነ ሰላማ ሕዝቡን አጥምቀው ወደ ክርስትና ሲመልሱ ለክርስትናቸው ምልክት ከግንባራቸው ላይ እየበጡ መስቀለኛ ምልክት ያደርጉላቸው እንደነበር ይተረካል፡፡
ከአቡነ ሰላማ የጀመረው ማዕተብ የማሰር ትውፊት በዘጠኙ ቅዱሳን ዘመንም እየተስፋፋ ሔዶ በቤተ ክርስቲያን ክርስትና ለሚነሡ ኹሉ ሥርዐተ እምነታችን ኾኖ ቆይቷል፡፡ እስከ አኹንም በተለይ በሰሜናውያን ዘንድ በመበጣትም ኾነ በንቅሳት ለክርስትናቸው ምልክት መስቀል ከግንባራቸው ማድረግ የጸና ልምድ ኾኖ ይታያል፡፡
ማዕተብ ያላሰረ ኦርቶዶክሳዊ የአባቶቹን የተቀደሰ ክርስቲያናዊ ትውፊት እንዳልተቀበለ ያስቆጥረዋል፡፡ በምሳሌያዊ አነጋገርም ሃይማኖት አልባውን ማለትም ክርስቲያን ያልኾነውን ማተብ የለሽ፣ ያልተጠመቀ፣ አረሚ ይሉታል፡፡ ክርስቲያን በማተቡ መነኵሴ በቆቡ እንዲታወቅ ማተብ አልባ መኾን ደግሞ ክርስቲያን ይኹን ያልተጠመቀ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ በመለዮዋቸው ሌሎች እንዲታወቁ ክርስቲያን በማተቡ ክርስትናውን ሲያሳውቅ ኖሯል፡፡
በተለመደው አነጋገር÷ እገሌ ማተብ አለው፤ ባለማተብ ነው ሲባል እገሌ ታማኝ ክርስቲያን ነው፤ እውነተኛ ሐቀኛ ነው የማለትን ትርጉም ይሰጣል፡፡
ባለማተቢቱ ሲባል ከአሚን ባሏ የረጋች ከባሏ ሌላ የማታውቅ እውነተኛ ታማኝ ክርስቲያን የማለት ፍች አለው፡፡ በዚኽ ምክንያት በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ የማተብ ትርጉም ከፍተኛ ቁምነገርን አዝሎ ይገኛል ፡፡
አንዲት ሀገር ነፃና ሉዓላዊ መኾኗ የሚታወቀው ወይም ራሷን የቻለች መንግሥት ያላት ከባዕድ ቀንበር ቅኝ ግዛት ነፃ የወጣች መኾኗ በቀዳሚነት የሚለየው በባንዴራዋ ምልክትነት እንደኾነ እንደዚኹም አንድ ክርስቲያን በክርስቶስ አምኖ በጥምቀት ከዲያብሎስ ቁራኝነት ነፃ መውጣቱ፣ ነፃነት ያለው አማኝ መኾኑ የሚታወቀው በማተቡ ምልክት ነው፡፡ ለደብዳቤ፣ ለጽሑፍ ዓርማ ማኅተም ፊርማ እንደሚያስፈልገው ያም ለመተማመኛ እንደሚያገለግል ጥቅሙ ታውቆ ይሠራበታል፡፡
በዚኹ አንፃር የክርስቲያን ማዕተቡም ሃይማኖታዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ በቅድሚያ፣ በልቡ የሚያምነው ሃይማኖት ክርስትናን ሳያፍርበት በአንገቱ ባለው ማተብ መግለጹ በክርስትናው አለማፈሩን፣
ክርስትናኽን ካድ ማተብኽን በጥስ የሚል ዐላዊ ቢመጣና ያን ምልክት አይቶ ቢሠዋው የሰማዕትነት ክብር ያገኘበታል፡፡ ያም ባይኾን በማተቡ ምልክትነት በመናፍቃንና በኢአማንያን የሚቀበለው ዘለፋ ስለ ክርስቶስ መስቀል እንደተሸከመ ያስቆጥረዋል፡፡
ኹለተኛው፣ ያለጥርጥር ክርስቲያን መኾኑ ታውቆለት ከክርስቲያን ወገኖች ጋራ ተሳትፎውን ማከናወን ይችላል፡፡ ማተብ ከሌለው ግን ክርስቲያን ይኹን ያልተጠመቀ ስለማይታወቅ በሃይማኖት ዜጎች ዘንድ በቀላሉ ተቀባይነት ማግኘት አይችልም፡፡ ሦስተኛ፣ ከማይታወቅበት አገር እንደወጣ በበሽታም ይኹን በአደጋ ሕይወቱ ቢያልፍ በማተቡ መታወቂያነት የክርስቲያን ሥርዐት ተፈጽሞለት በቤተ ክርስቲያን ሊቀበር ይችላል፡፡
አራተኛ፣ ማተብና መስቀል ያለው ክርስቲያን በውኃ ዋና ወይም በበረሓ ጎዳና በውኃ የሚኖሩ ወይም በበረሓ ያሉ አጋንንት በቀላሉ ሊለክፉት አይችሉም፡፡ ይህም በየጠበሉ ስፍራ በተኣምራት ተረጋግጧል፡፡ አጋንንት የለከፏቸው ሰዎች ማተብና መስቀል አይወዱም፡፡ የሰፈረባቸው ርኩስ መንፈስ ማተብ እንዲበጥሱ መስቀል እንዲጥሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ማተብ በሰይጣን ዘንድ ከተጠላ በአጋንንት ላለመለከፍ የማዕተቡ መኖር ይጠቅማል ማለት ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች የማዕተብ ሥርዐትን ለመቃወምና ዘመናውያን መስለው ለመታየት ‹‹እምነት በልብ ነው›› ይላሉ፤ ተሳስተዋል! ሃይማኖት የልብ ብቻ አይደለም፤ የጠቅላላው ሕዋሳት ኹሉ ናት፡፡ እግዚአብሔርን ስንወደውና ስናመልከው በልባችን ብቻ ሳይኾን በአፋችንም በአንገታችንም በጠቅላላው ሰብአዊ ተፈጥሯችን ኹሉ መኾን ይገባዋል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር የጠቅላላው ሰውነታችን አምላክና ፈጣሪ ስለኾነ ነው፡፡ ‹‹ስለዚኽ በሰው ፊት የሚመሰክርልኝ ኹሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለኹ፤ በሰው ፊትም የሚክደኝን ኹሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለኹ፡፡›› (ማቴ.፲÷፴፪÷፴፫)
በዚኽ ቃለ ወንጌል መሠረት በኢአማንያን ዘንድ ክርስቲያን መኾናችንን የምንገልጸው በልባችን ብቻ ሳይኾን በቃላችንና በሥራችንም ጭምር ነው፡፡ በአንገታችንስ እንዳንመሰክርለት ማን ያግደናል? በአንገታችን ባለው ማዕተብም ለእግዚአብሔር እንመሰክራለን፡፡ የስሙን ምልክት በአንገታችን እናኖራለን፤ አናፍርበትም!! የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ በጥምቀታችን እንደምንመሰክር የጥምቀታችንንም ዓርማ በማተባችን እናረጋግጣለን፡፡ (ሮሜ ፲፮÷፲፫፤ ኢዩኤ. ፪÷፴፪፤ ሮሜ ፮÷፩-፭፤ ማቴ.፭÷፲፩-፲፪፤ ፩ኛጴጥ.፫÷፳፩-፳፪፤ ፬÷፲፪-፲፮)
ከወንጌል የተለየች ትምህርት እንዳንቀበል ሐዋርያት አስጠንቅቀውናል፡፡ መላእክት በራእይ ገልጸውልናል፤ ከእግዚአብሔር አግኝቻለኹ ብለው የሚመጡትን መናፍስት እንድንመረምራቸው በቅዱሳት መጻሕፍት ታዝዘናል፡፡ ማተብ የማሰር የተቀደሰ ክርስቲያናዊ ትውፊታችንን የሚቃወሙ በክርስቶስና ሞትና ትንሣኤ የማያምኑ ተረፈ አይሁድ ስለኾኑ ተቃውሞውን ዋጋ ሳንሰጠው ማተባችንን እናጠብቃለን፡፡ ‹እንደ ውሻ በአንገታችኹ ገመድ አስራችኹ› ተብለን በመነቀፋችንም እንደሰትበታለን እንጂ አንሠቀቅም፡፡ ውሻ ለጌታው ታማኝ ነው፡፡ ሌሎች የተለከፉ ያበዱ ዘላን ውሾች እንዳይለክፉትና ከሞት እንዳያደርሱት ወይም ወንበዴዎች በሥጋ መርዝ ቀብተው ለሥጋው ሲሣሣ እንዳይገድሉት ትንሽ ጎጆ ሠርቶለት ቢያስረው ለውሻው ሕይወት አስፈላጊ እንደኾነ በኹሉም የታወቀ ነው፡፡
በዚኹ አንፃር ክርስቲያን ለክርስቶስ ታማኝ በመኾኑ በነፍሱ ሞግዚት በቄሱ እጅ ከሕፃንነቱ ጀምሮ የድኅነቱ ምልክት በሚኾን አንገቱ በማዕተበ ክርስትና ይታሰራል፡፡ ማዕተብ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ ስለ እኛ ቤዛ ለመኾን የብረት ሀብል /የብረት ገመድ/ በአንገቱ ታስሮ በአይሁድ መጎተቱን ስለሚያስታውሰን ለታማኝነታችንና ለክርስቲያንነታችን ምልክትነቱ ማረጋገጫ ስለኾነ አናፍርበትም፡፡ በ ድርሳነ ሰንበት ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ የውሻን ታማኝነት ለክርስቲያን ታማኝነት ምሳሌ አድርጎ ገልጾታል –
‹‹ከልብሰ የአምር እግዚኡ፤ ውሻ ጌታውን ያውቃል›› ፡፡ ጌታችንም በቅዱስ ወንጌል በውሻ የተመሰለችውን ከነናዊቷን ሴት ስለ ታማኝነቷ አድንቋታል፤ ልጅዋንም ፈውሶላታል፡፡(ማቴ.፲፭÷፳፩-፳፰)
ማዕተብን ከሚቃወሙ አንዳንዶች ‹‹ጽዳት ያጎድላል›› በማለት ያመካኛሉ፡፡ በርግጥ የጠንቋይ ክታብ የቃልቻ ግሣንግሥ መሰብሰቢያ ካደረጉት የሥጋ ንጽሕናን ብቻ ሳይኾን የሚያጎድለው የነፍስንም ጽዳት የሚያጎድል መኾኑ ዕውቅ ነው፡፡ ማተብ እና መስቀሉ ግን ጽዳት ያጎደለበት ጊዜ ስለሌለ ሰበብ አያዋጣም፡፡ ስለዚኽ
የክርስትናችንን ዓርማ የነፍሳችንን ሰንደቅ ዓላማ
በነፃነት ስናውለበልብ ለመኖር ያብቃን፡፡ አሜን፡፡
ምንጭ፡- መለከት መጽሔት
Micah Alaye
ወስብሀት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር!!!

ከቶ ምን ሊረባኝ?                          ከኃጢአት ርቄበጽድቅ ካልተጓዝኩሐሰትን ጠልቼእውነትን ካልናፈኩለበደልኩት ክሼቅሚያዬን መልሼንስሀ ገብቼበቁርባን ካልታተምኩከቶ ምን ሊረ...
06/09/2021

ከቶ ምን ሊረባኝ?


ከኃጢአት ርቄ
በጽድቅ ካልተጓዝኩ
ሐሰትን ጠልቼ
እውነትን ካልናፈኩ
ለበደልኩት ክሼ
ቅሚያዬን መልሼ
ንስሀ ገብቼ
በቁርባን ካልታተምኩ
ከቶ ምን ሊረባኝ?
ዛሬም አዲስ ዓመት
አዲስ ቀን መመኘት፡፡
ዘመን ሁሌ አዲስ ነው
መልካምን ለሰራ
በጽድቅ ለተጓዘ
በቃል የሰማውን
በተግባር አውሎ
ለአምላክ ለታዘዘ
ዘመን ሁሌ አዲስ ነው
በቃሉ ተተመርቶ
በአምላክ ቤት ለኖረ፡፡

እውነትን አትግፈፏት
መንፈሳዊ የግጥም መድብል!!
ወስብሀት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር፡፡

ጳጉሜን 7የያዝነውን አመት ልንሰናበት ጥቂት ቀናት ሲቀሩን የያዝነውሣምንት ደግሞ ጳጉሜን ይባላል። ስለዚህች ልዩ የሆነች ወር (ጳጉሜን) መጠነኛዕውቀት ይኖረን ዘንድ የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ...
05/09/2021

ጳጉሜን 7
የያዝነውን አመት ልንሰናበት ጥቂት ቀናት ሲቀሩን የያዝነው
ሣምንት ደግሞ ጳጉሜን ይባላል። ስለዚህች ልዩ የሆነች ወር (ጳጉሜን) መጠነኛ
ዕውቀት ይኖረን ዘንድ የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጽሁፍ የሆነውን፥
ጳጉሜን'ን' የሚመለከት መረጃ ታነቡት ዘንድ እጋብዛለው።
ጳጉሜን በ600 ዓመታት አንድ ጊዜ 7ቀን እንደምትሆንም
ይረዳሉ።
መልካም ንባብ
ጳጉሜን - አምስት፣ ስድስት፣ ሰባት
(ዲያቆን ዳንኤል ክብረት)
የመግቢያ ማስታወሻ
በጽሑፉ ውስጥ በግእዝ ቁጥሮች በቅንፍ ውስጥ የተጻፉት
ሐሳቡን እንዲወክሉ ብቻ ነው፡፡ በኋላ (ቁጥር ፭ ተመልከት ቢል
ያንን ሐሳብ መልሶ ለማየት እንዲረዳ ነው፡፡
የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ
ጳጉሜ የምትባል አሥራ ሦስተኛ ወር ስላለችን ነው፡፡ የቤት
ኪራይና የወር ደመወዝ የማንከፍልባትና የማንቀበልባት፤
መብራትና ውኃ ግን ከነሐሴ ወር ጋር ጨምረው
የሚያስከፍሉባት፤ ሲሻት አምስት፣ ሲያስፈልጋት ስድስት፣
ስትፈልግ ደግሞ ሰባት የምትሆን ወር ናት፡፡ እንዲያውም ከአሥራ
ሁለቱ የኢትዮጵያ ወሮች ጳጉሜ በብዙ መንገድ የተለየች ናት፡፡
በአንድ በኩል በጣም ትንሿ ወር ናት፡፡ ሲቀጥልም ወርኃዊ በዓላት
የማይውሉባት ወር ናት፡፡ እንዲያም ሲል ደግሞ ከሌሎች ወሮች
በተለየ የቀኖቿ መጠን የሚቀያየሩ ብቸኛ ወር ናት፡፡ ከሌሎች
የኢትዮጵያ ወሮች በተለየም ስሟ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ወር ናት፡፡
በሁለት ዘመናት መካከልም እንደ መሸጋገሪያ የምትታይ ወርም
ናት፡፡
ጳጉሜ ማለት በግሪክ ‹ጭማሪ› ማለት ሲሆን ዓመቱን በሠላሳ
ቀናት ስንከፍለው የሚተርፉትን ዕለታት ሰብስበው የሰየሟት
ተጨማሪ ወር ናት፡፡ ወይም በየዕለቱ በፀሐይና በጨረቃ
አቆጣጠር መካከል የሚፈጠረውን ልዩነት ሰብስበው ያከማቹባት ወር ትባላለች፡፡
ዓመቱ በዐውደ ፀሐይ ሲለካ 365 ቀናት ከ15
ኬክሮስ 6 ካልዒት ሲሆን በጨረቃ ሲለካ ደግሞ 354 ቀናት
ከ22 ኬክሮስ፣ 1 ካልዒት፣ 36 ሣልሲት፣ 52 ራብዒት፣ 48
ኀምሲት ነው፡፡
(60 ኬክሮስ አንድ ቀን ነው)በሁለቱ መካከል
(በፀሐይና በጨረቃ) በዓመት ውስጥ ያለው ልዩነት 11 ቀናት ከ7
ኬክሮስ ይሆናል፡፡[በነገራችን ላይ በዘመን አቆጣጠራችን ውስጥ
ከዕለት በታች የምንቆጥርባቸው ስድስት መለኪያዎች አሉ፡፡
ኬክሮስ፣ ካልዒት፣ ሣልሲት፣ ራብዒት፣ ኀምሲትና ሳድሲት፡፡
60 ሳድሲት አንድ ኀምሲት፣
60 ኀምሲት አንድ ራብዒት፣
60 ራብዒት
አንድ ሣልሲት፣
60 ሳልሲት አንድ ካልዒት፣
60 ካልዒት ደግሞ 1
ኬክሮስ ይሆናል፡፡
60 ኬክሮስ ደግሞ 1 ዕለት፡፡
1 ኬክሮስ 24
ደቂቃ ነው]
ጳጉሜን ለማግኘት የሚጠቅመን የየዕለቱን ልዩነታቸውን
መመልከቱ ነው፡፡
በየዕለቱ በጨረቃና በፀሐይ መካከል 1 ኬክሮስ
52 ካልዒት(60 ካልዒት አንድ ኬክሮስ ነው)፣ ከ 31 ሣልሲት(60
ሣልሲት አንድ ካልዒት ነው) ይሆናል፡፡[ይህም ማለት 5 ሰዓት
ከ48 ደቂቃ ከ46 ካልዒት(ሴኮንድ?)] ይህ ልዩነት በአንድ ወር
ምን እንደሚደርስ ለማወቅ በ30 እናባዛው፡፡ 30 ኬክሮስ፣ 1560
ካልዒት፣ ከ930 ሣልሲት ይሆናል፡፡ የዓመቱን ለማግኘት ደግሞ
በ12 እናባዛው፡፡ 360 ኬክሮስ(፩)፣ 18720 ካልዒት(፪)፣
11160 ሣልሲት(፫) ይመጣል፡፡
ቀደም ብለን 60 ኬክሮስ አንድ ዕለት ይሆናል ባልነው መሠረት
360 ኬክሮስ ለ60 ሲካፈል 6 ዕለታትን ይሰጠናል(፩)፡፡ 18720
ካልዒትን(፪) በስድሳ በማካፈል 312 ኬክሮስን እናገኛለን፡፡ ያም
ማለት ትርፉን 12 ኬክሮስ ትተን 300ውን ኬክሮስ ለ60
በማካፈል 5 ዕለት እናገኛለን፡፡ ይኼም ማለት 5 ዕለት ከ12
ኬክሮስ(፬) ይሆናል፡፡ 11160 ሣልሲትን(፫)ለ60 ብናካፍለው
186 ካልዒት ወይም ደግሞ 3 ኬክሮስና 6 ካልዒት(፭) ይሆናል
ማለት ነው፡፡
ከላይ ኬክሮስን በዓመቱ ቀናት አባዝተን ያገኘነው(፩) 6 ዕለት
አለ፡፡ ይኼ ዕለት ሕጸጽ ይባላል፡፡ ፀሐይና ጨረቃን እኩል
መስከረም አንድ ላይ ዓመቱን ብናስጀምራቸው ፀሐይ የወሯ
መጠን ምንጊዜም ሠላሳ ሲሆን ጨረቃ ግን በአንደኛው ወር 29
በሌላኛው ወር ግን 30 ስለምትሆን ዓመቱ እኩል አያልቅም
የጨረቃ ዓመት ነሐሴ 24 ቀን ያልቃል፡፡ ይህም ማለት ጨረቃ
በሁለት ወር አንድ ጉድለት ታመጣለች፡፡ ያንን ነው ሊቃውንቱ
ሕጸጽ(ጉድለት) ያሉት፡፡ በዚህም መሠረት ከላይ ኬክሮሱን(፩)
በዓመቱ ቀናት አባዝተን ያገኘነውን 6 ዕለት ለጨረቃ ሕጸጽ
ስንሰጠው የመስከረም/ ጥቅምት (1)፣ የጥቅምት/ ኅዳር(2)፣
የጥር/ የካቲት(3)፣ የመጋቢት/ ሚያዝያ(4)፣ የግንቦት/ ሰኔ
(5)፣ የሐምሌ ነሐሴ (6) ሆነው ተካፍለው ያልቃሉ፡፡
በሌላም በኩል ደግሞ በጨረቃና በፀሐይ ዑደት መካከል በዓመት
ያለው ልዩነት 11 ቀናት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልዒት) ይሆናል፡፡
ስድስቱን ዕለታት ጨረቃ ለምታጎልበት (ሕጸጽ) ብንሰጠው ቀሪ 5
ዕለት ይኖረናል፡፡ ጳጉሜ ማለት እነዚህ 5 ቀናት ናቸው፡፡ አሁን
የአሥራ አንዱን ዕለታት ከፈጸምን ሽርፍራፊዎቹን (15 ኬክሮስና
6 ካልዒት) እንይ፡፡
ከላይ እንዳየነው በፀሐይና ጨረቃ ዓመታት መካከል የተፈጠሩትን
11 ቀናት ስድስቱ ለሕጸጽ ማሟያ ሲገቡ የቀሩት 5 ዕለታት ናቸው
ጳጉሜ የምትባለውን ወር በመሠረታዊነት የፈጠሯት፡፡
በጎርጎርዮሳውያኑ አቆጣጠር እነዚህ 5 ተጨማሪ ዕለታት
በጃንዋሪ፣ ማርች፣ ሜይ፣ ጁላይና ኦገስት ላይ ስለተጨመሩ
እነዚህ ወራት 31 ለመሆን ተገድደዋል፡፡ (ይህንን የከፈለው በ46
ቅልክ የነበረው ዩልየስ ቄሣር ነው፡፡ ለአራቱ ወሮች 30 ቀን፣
ለአንዱ 28/29 (በየአራት ዓመቱ)፣ ለቀሩት ሰባት ወሮች ደግሞ
31 ሰጥቷቸዋል፤ ለአምስቱ ወሮች 31 ያደረጋቸው ከጳጉሜ
ወስዶ ሲሆን ለሁለቱ ወሮች አንዳንድ ቀን የጨመረላቸው
ከፌቡርዋሪ 2 ቀናት ወስዶና ወሩን 28 አድርጎ ነው)፡፡
ከእንግዲህ የሚቀሩን ከላይ የየዕለቱን ልዩነት ለዓመት ስናባዛ
(ቁጥር ፪ና ፫ ተመልከት) የቀሩን 15 ኬክሮስና 6 ካልዒት
ናቸው፡፡ ሁለቱን ከላይ ያየናቸውን (፬ና፭) ስንደምራቸው (12
ኬክሮስ + 3 ኬክሮስ ከ6 ካልዒት) 15 ኬክሮስ ከ 6 ካልዒት
ይመጣሉ፡፡
ቀደም ብለን አንድ ዕለት 60 ኬክሮስ ነው ብለናል፡፡ ስለዚህም
አንድ ዕለት (60 ኬክሮስ) ለማግኘት ከላይ ያገኘነውን 15
ኬክሮስ በ 4 ማባዛት አለብን፡፡ በአራት ዓመት አንዴ ጳጉሜ 6
የምትሆነው እነዚህ በየዓመቱ የተጠራቀሙት 15 ኬክሮሶች አንድ
ላይ መጥተው በአራት ዓመት አንድ ጊዜ አንድ ዕለት ስለሚሆኑ
ነው፡፡ እርሷም ሠግር(leap year)ትባላለች፡፡ ጎርጎርዮሳውያኑ
ይህቺን ሠግር በፌቡርዋሪ ወር ላይ ጨምረው ወሩን በየአራት
ዓመቱ አንድ ጊዜ 29 ቀን ያደርጉታል፡፡
15ቱ ኬክሮስ በአራት ዓመት ተደምረው አንድ ዕለት መጡና
በአራት ዓመት አንዴ ጳጉሜን ስድስት አደረጓት፡፡ የቀረችው 6
ካልዒትስ (ቁጥር ፭) የት ትግባ?
ካልዒት አንዲት ዕለት ትሆን ዘንድ 3600 ካልዒት ያስፈልጋሉ፡፡
ይህንን ያህል ካልዒት ለማግኘት 600 ዓመታት ያስፈልጉናል፡፡
ለዚህ ነው ጳጉሜ በየስድስት መቶ ዓመታት ሰባት የምትሆነው፡፡
እስካን የጠየቅኳቸው የባሕረ ሐሳብና የታሪክ ሊቃውንት
በታሪካችን ውስጥ ጳጉሜን 7 የሆነችበትን ዘመን እንደማያውቁ
ነግረውኛል፡፡ ሒሳቡ ሲሰላ በየ 600 ዓመቱ ሰባት ትሆናለች
ቢባልም አስቦ በስድስት መቶኛው ዓመት ሰባት የሚያደርጋት
እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ በፈረንጆቹ ብሂል ‹ፌብሩዋሪ 30› ማለት
የመሆን ዕድል ያለው ነገር ግን ሆኖሞ የማያውቅ ሊሆንም
የማይችል(possible but never happen)› ተደርጎ
እንደተወሰደው ሁሉ ምናልባት በኛም ጳጉሜን 7 ማለት
እንደዚያው ይሆን ይሆናል፡፡
በነገራችን ላይ ጳጉሜን 5 ቀን በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ
‹ዕለተ ምሪያ› ወይም የተመረጠች ቀን ትባላለች፡፡ የጌታችን ልደት
ለመጠበቅ ሊቃውንቱ ሲያሰሉባት የቆየችው ዕለት በመሆኗ ነው
ይህንን ስያሜ ያገኘችው፡፡ የጌታችንን ልደት ቀን የምትወስነው
ጳጉሜ 5 ቀን ናት፡፡ ልደት የሚውለው ጳጉሜ 5 በዋለበት ቀን
ነው፡፡ ለምሳሌ ዘንድሮ ጳጉሜን 5 ቀን ረቡዕ ነው የምትውለው፤
ስለዚህም በ2007 ዓም ልደት የሚውለው ረቡዕ ነው፡፡ በየአራት
ዓመቱ አንድ ጊዜ ጳጉሜን 6 ስትሆን ልደት በ28 የሚከበረው
ዕለተ ምሪያን ስለማይለቅ ነው፡፡ ስድስተኛዋ ቀን ልደትን በአንድ
ቀን ስታዘልለው እኛ በ28 እናከብረዋለን፡፡ ልደት ጳጉሜ 5 ቀንን
(ዕለተ ምሪያን) ስለማይለቅ፡፡ ታድያ ምነው እነ ጥምቀትና ግዝረት
አይለወጡም? ቢሉ፡፡ ሊቃውንቱ የሚሰጡት መልስ ‹ትውልድ
ሱባኤ እየቆጠረ በተስፋ የጠበቃት ዕለተ ልደትን ስለሆነ ነው፤
ሌሎቹ የመጡት በልደቱ ምክንያት ነው›› የሚል ነው፡፡
በጎርጎርዮሳውያንም ቢሆን በአራት ዓመት አንዴ ልደት ዝቅ
ትላለች፡፡ የእነርሱ የማይታወቀን ጭማሪዋ ፌብርዋሪ ላይ
ስለሆነች ነው፡፡ ያ ደግሞ አዲሱን ዓመት ካከበሩ በኋላ
ስለሚመጣ ነው፡፡ የእኛ ግን የምትወድቀው ጳጉሜን መጨረሻ
ላይ በመሆኗ ከአዲስ ዓመት በፊት ስለምትጨመር ጎልቶ
ይታወቃል፡፡
እንግዲህ ጳጉሜ የምትባለው አስገራሚ ትንሷ ወራችን እንዲህ
በስሌት የተሞላች፣ አምስት ሆና ቆይታ በየአራት ዓመቱ አንዴ
ስድስት፣ በየስድስት መቶ ዓመቱ ደግሞ ሰባት የምትሆን ናት፡፡
ታላላቆቹ ወሮች ምንም ሳይፈጥሩ የልደትን ቀን የምትወስን፣
የዓመቱን ሠግር የምታመጣ፣ ታሪከኛ ወር ናት፡፡ የትንሽ ትልቅ
ማለት እንዲህ ነው፡፡

የኢትዮጵያውያን አቆጣጠርና የአውሮፓውያን አቆጣጠር ልዩነትየዘመናት ባለቤት እግዚአብሔር አምላክ ቀናትን በወራትዓመታትን እያፈራረቀ እድሜ ለንስሓ ዘመን ለፍስሐ ሰጥቶ ለዚህስላደረሰን ክብር ይግ...
04/09/2021

የኢትዮጵያውያን አቆጣጠርና የአውሮፓውያን አቆጣጠር ልዩነት
የዘመናት ባለቤት እግዚአብሔር አምላክ ቀናትን በወራት
ዓመታትን እያፈራረቀ እድሜ ለንስሓ ዘመን ለፍስሐ ሰጥቶ ለዚህ
ስላደረሰን ክብር ይግባውና በኢትዮጵያውያንና በአውሮፓውያን
ዘመን አቆጣጠር መካከል በርካታ መሠረታዊ የሚባሉ ልዩነቶች
ይታያሉ፡፤ ለዚህም ይመስላል ብዙዎች ዘመን መለወጫ በመጣ
ቁጥር ጥያቄ ያነሳሉ፡፡
ኢትዮጵያዊያን ዕለተ ቀመርን ወይንም ዘመን መለወጫን
የምናደርገው በመስከረም ሲሆን የአውሮፓውያን የዘመን
መለወጫ ፤ ታህሳስ /December/ 29 ልደትን አክብረው ጥር /
January/ 1ቀን ዘመን መለወጫቸው ነው፡፡
በኢትዮጵያውያን ዓመተ ምህረታችን 2005 ሲሆን የነሱ
2013/2014 ይሆናል፡፡ ይህም የሰባት ዓመት ከስምንት ወር
ልዩነት ይኖረናል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ሁሉንም ወራት በሠላሳ ቀናት ከፍለን አስራ
ሁለት ወር ከ 5 ቀን ጳጉሜ አድርገን ስንቆጥር ፤ አውሮፓውያን
ግን 28፣ 30፣ 31 በማድረግ 365 ቀኑን አስራ ሁለት ወር ብቻ
በማድረግ ይቆጥራሉ፡፡
ከላይ የተመለከትናቸው ዋና ዋና ልዩነቶች ሲሆኑ ከዚህ
ቀጥለን እነዚህ ልዩነቶች ለምን እንደተፈጠሩ ባጭሩ
እንመለከታልን፡፡
7.1. የዘመን መለወጫ ልዩነት
ኢትዮጵያዊያን ዘመን የምንለውጠው መስከረም አንድ ቀን /
ዕለተ ቀመር/ ነው፡፡ መስከረም የዘመን መለዋጫ የሆነበት
ምክንያት፡- በዚህ ወር ቀኑና ሌሊቱን እኩል የሚሆኑበት ነው፡፡
ቀኑ ሙሉ 12 ሰዓት ሌሊቱም ሙሉ 12 ሰዓት ይሆናል፡፡
ምክንያቱም ከመስከረም 26 እስከ ታህሳስ 26 ድረስ ፀሓይ
በምድር ወገብ አካባቢ ስለምትሆን የቀኑን ርዝማኔ እኩል
ይሆናል፡፡
በሀገራችን ይህ በዓል ለመከበሩ የሚቀመጡ እውነታዎች ሲኖሩ
ይኸውም
በዚህ ወር ንግሥት ሳባ ኢየሩሳሌም ደርሳ የጠቢብ ሰሎሞንን
ጥበብ አድንቃ ስትመለስ ዕንቍ ለጣትሽ ብሎው በርካታ የከበሩ
ዕንቍ በስጦታ የተበረከተላት በዚህ ወር በመሆኑ የዘመን
መለወጫ በመስከረም አንድም እናደርጋለን፡፡ በዚህም የተነሳ
መስከረም አንድ ቀን እንቁጣጣሽ በመባል ይታወቃል፡፡ መሳ10÷1
ፀሓይ የ365 ቀናትና ጉዞዋን ፈፅማ አንድ ብላ የምትጀምረው
በዚህ ወር ነው፡፡
አንድም፡- የክረምቱ /የጨለማው/ ወራት የሚያበቃበትና ወርሃ
ጽጌ የሚጀምርበት ወር በመሆኑና
አንድም፡- ኖህና ቤተሰቡ ከጥፋት ውኃ ድነው ምድር መድረቋን /
አበባና ፍሬ መስጠቷን/ የተመለከተው በዚህ ወር ነበር፡፡ ዘፍ.
8÷8 በዓመቱም /ከ12 ወር በኋላ/ የዘመን መባቻ መጀመሪያ
ወይም የዘመን መለወጫ አድርጎ አክብሯል፡፡ ኩፋሌ 24÷7
‹‹በመጀመሪያ ወር መባቻ ለራሱ መርከብ ይሠራ ዘንድ ታዘዘ
በእርሷም ምድር ደረቀች፡፡›› እንዲሁም እግዚአብሔር በዚህ ወር
ለሙሴ የዘመን መለወጫ ይሆን ዘንድ አዞታል፡፡ ዘሌ 23÷53
እግዚአብሔር ለእስራኤል በአዘዘው ሥርዓት መሠረት ከግብፅ
በወጡበት በሰባተኛው ወር የሚከበር በዓል ነው፡፡ በክርስትናው
ዘመን እስከ ዐሥራ አንደኛው ክ/ዘመን ድረስ ዓለም በአንድነት
በዚህ ወር በመጀመሪያው ዕለት ያከብር ነበር፡፡ ነገር ግን
ጎርጎርዮስ ሰባተኛ /1073-1035/ የዘመን መለወጫ ከልደት
በዓል ጋር እንዲያያዝ በማለት ወደ ጥር አዞረው በዚሁ መሠረት
የምዕራቡ ዓለም በጥር ወር ሲያከብር የምሥራቅ ግን እስካሁን
መስከረምን አለቀቁም በዚህ ወር አዲስ ዓመታችን ከሚጀምሩ
መካከል ግሪክ፣ ሩስያና ሮማንያ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያና
ለእስክንድሪያ ቤተ ክርስቲያንም ይኸው መስከረም ወር አዲስ
ዓመታቸው መባቻ /መግቢያ/ ነው፡፡ በዚህም መሠረት
ቤተክርስቲያናችን ዕለቱን እስከዚህ ያደረስን በማለት
እግዚአብሔርን የምታመሰግንበት የአጽዋማትና የበዓላትን /
የዐዋድያቱን/ የምታውጅበት ፍሬ ምድርን ባረካ የአዲሱ ዓመት
አገልግሎት አሐዱ ብላ የምትጀምርበት ታላቅ በዓል ነው፡፡
7.2 የሰባት ዓመት ከስምንት ወር ልዩነት ለምን ተገኘ?
የጎርጎርዮሳዊያን አቆጣጠር ስንመለከት ብዙው ነገር የተዘበራረቀ
ወጥነት የሌለው እንደሆነ እንመለከታልን፡፡ በወራቱ ውስጥ ያሉት
ቀናት የተለያዩ መሆን እና የጌታን ልደት ለማክበር መነሻ ያደረጉት
ታሪክን እንጂ ቅዱሳን መጻሕፍትን አለመሆኑ ነው፡፡ የጌታን ልደት
ሊያከብሩ የተጠቀሙት ሮም ከተመሠረተች ስንት ዓመት አንደሆነ
በማስላት ነው፡፡ ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ ሮም
ከተመሠረተች 753 ዓመቷ ነው በማለት ከዚህ ጊዜ ጀምሮ
ቆጥረዋለወ፡፡ ይህም ማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ
5508 ዓመተ ዓለም ነበር ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ቤተክርስቲያን
የጌታ (ጽንሰት) የቆጠረችው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ 5500
ዓመተ ዓለም ዓመተ ፍዳ ከተፈፀመ በኋላ ያለውን አድኖናል
በማለት ነው፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ ያለውን ዓመት ምህረት በማለት
የጌታ(ጽንሰት) መሆኑን ታስተምራለች፡፡ ለዚህም መሠረት
ያደረገችው ቅዱሳን መጻሕፍት ነው፡፡
‹‹በሀሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ
ወእድሕክ ውስተ መርኀብከ- 5 ቀን ተኩል ሲፈፀም
አድንሃለሁ፡፡›› አንዲት ቀን ለእግዚአብሔር እንደ አንድ ሺህ ዘመን
ነው፡፡ መዝ 89÷4፤ 2ጴጥ 3÷8 ይህም ማለት 5ሺህ 5 መቶ
ዘመን ሲፈፀም አድንሃለው የሚለውን አምላካዊ ቃሉን መሠረት
በማድረግ ልደተ ክርስቶስን እናከብራለን፡፡ ይህ ቀን መድኃኒታችን
ከድንግል ማርያም የተፀነሰበት ቀን ቀኑም መጋቢት 29 በዘመነ
ዮሐንስ በዕለተ እሑድ ነው፡፡ ይህ ቀን እንዲሁ በዋዛ የተደረገ
ሳይሆን ሐዋርያው ቀዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው በጽኑ ቀጠሮ
ነው፡፡ ወአመ በፅሐ ዕድሜሁ ፈነወ እግዚአብሔር ወልዶ
ወተወልደ እምብእሲት - የዘመኑ ፍፃሜ በደረሰ ጊዜ
እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ልጁን ላከ ገላ 4÷4 በማለት
የገባው ቃል በተፈፀመ ጊዜ መጥቶ እንዳዳነን ተናግሯለል፡፡
እንደ ቤተክርስቲያን ይህ ዓይነት ልዩነት የተገኘው በዓመተ
ምህረት ብቻ ሳይሆን ከጥንት ማለትም ከጌታችን ልደት በፊት
ጀምሮ የመጣ ነው፡፡ ልዩነቱም በኦሪት አማካኝነት የተከሰተ ሲሆን
ኦሪት አራት ጊዜ ተፅፏል፡፡ የመጀመሪያው ሙሴ የፃፈው ሲሆን
ኦሪት ዘሌዋውያን ይባላል፡፡ ሁለተኛው ኦሪት ዘሊቃውንት ሲሆን
ይኸውም በጥሊሞስ 70 ሊቃውንት ሰብስቦ የብሉይ ኪዳን
ሊቃውንት የብሉይ ኪዳን መጽሓፍትን ከዕብራይስጥ ወደ
ቅብጥ /ግሪክ/ ሲያስተረጉም የተፃፈ ስለሆነ ኦሪት ዘሊቃውንት
ተብሏል፡፡ ስልምናሶር የተባለ ንጉሥ 10 ነገድ ማርኮ በሰማሪያ
አስፍሯቸው መቅሰፍት ሲጨርሳቸው ምክንያቱን ሲጠይቁ ያዕቆብ
አቡነ እግዚአብሔር አምላክነ የማይል በሰማሪያ አይኖርም ሲሉት
ምናሴ ካህን ልኮላቸው አስተምሯቸዋል፡፡
አንተኑ ተዐቢ እምያዕቆብ አቡነ ዘወሀበነ ዘንተ ዐዘቅተ አንተ
ከያዕቆብ አባታችን ትበልጣለች ብላ ሳምራዊቷ ሴት ጌታን
የጠየቀችው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ዮሐ 4÷1 ካህኑ ምናሴም
ኦሪትን የፃፈላቸው ኦሪት ዘአይሁድ ነው፡፡ አይሁድ የክርስቶስ ሰው
መሆን በፅኑ ተቃውመው ጌታን ሰቅለውታል፡፡ ከእሱ በኋላ
የተነሳው ቀዳሚ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ ስለ ክርስቶስ ሰው
መሆን ሲያስተምር ጊዜው ሳይደርስ ደረሰ ፣ ሥጋ ሳይለብስ ለበሰ
ትላለህ ብለው በእስጢፋኖስ ላይ ተነሱበት፡፡ እሱም መጽሐፈ
ብሉይን አውጥቶ ሱባዔ አበውን ቆጥሮ /በትንቢተ ÷ያለውን
ተርጉሞ/ ረታቸው፡፡ በዚህም ጊዜ የዘመናት አቆጣጠር ዝብርቅርቁ
ወጥቷል፡፡ የኛይቱ ቤተክርስቲያን ትምህርተ እስጢፋኖስን ተቀብላ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ 5500 ዘመን ሲፈፀም መጥቶ አዳነን
በማለት ታስተምራለች፡፡
7.3 የአስር ቀን ልዩነት ለምን ተገኘ?
ሌላው የዘመን ልዩነት ያመጣው በጎርጎርዮሳዊያን አቆጣጠር
ፀሐይ የምትዞረው 365 ቀን ከአምስት ሰዓት ነው ይላሉ፡፡ ቤተ
ክስቲያናችን ደግሞ 365 ቀን ከ6 ሰዓት ወይንም ከ15 ኬክሮስ
ነው ትላለች፡፡ ስለዚህ በየዓመቱ እነዚህ አንድ አንድ ሰዓታት
አጠራቅመው የቀን ልዩነት እንዲኖር አድርገዋል፡፡ ለምሳሌ
በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር መስከረም አንድ ቀን ነው፡፡ ስለዚህ
የቀናት ልዩነት የተከሰተው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
7.4 የወራት መዛባት
ጎርጎርዮሳዎያን ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ወራቶቻቸው
ዝብርቅርቅ ያለ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ወራት ውስጥ ያሉ የቀናት
ብዛት የተለያዩ ናቸው፡፡ በየካቲት /February/ ወር 28 ቀናት
ሲኖሩት ሌላውን ሰባቱን ወራት 31 ቀን የቀሩትን አራት ወራት 30
ቀን በማድረግ 365 ቀናቱን ይፈጽማሉ፡፡
ኢትዮጵያዊያን ግን 12ቱን ወራት ሙሉ ሰላሳ ቀን አድርገን
የተቀረውን ጳጉሜን 5 ቀን በማድረግ 13ኛ ወር ትሆናለች፡፡
ፀሓይ የምትዞረው 365 ቀን ከ6 ሰዓት /15 ኬክሮስ/ ስለሆነ
እነዚህን 6 ሰዓታት ወይንም 15 ኬክሮስ በአራት ስናባዛው አንድ
ቀን /24 ሰዓት/ ይሆንና በ4 ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ሉቃስ
ጳጉሜ ስድስት ትሆናለች፡፡ ይህም ሁኔታ እንደ አውሮፓውያኑ
የተዘበራረቀ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡
የአውሮፓውያን የወራት ስያሜ መሠረት ያደረጉት ያመልኳቸው
የነበረውን ጣዖታት (አማልክት) እንዲሁም የታዋቂ ሰዎችን ስም
በመጠቀም ነው፡፡
1. በአውሮፓውያን መጀመሪያ ወር ጃንዋሪ /January/
በኢትዮጵያውያን ጥር ይባላል፡፡ ጃኑስ /Janus/ በሚባለው
የሮማውያን ጣዖት ስም የተሰየመ ነው፡፡
2. ሁለተኛው ፌብሩዋሪ /February/ በእኛ የካቲት ሲሆን ቃሉ
የተወሰደው ፌብሩዋሬ /Februare/ ከሚለው የላቲን ቃል ሲሆን
መንፃት /መዘጋጀት/ ማለት ነው፡፡ ይህም ስያሜ የተሰጠው
በጁሊየስ ቄሳር ዘመነ ነበር፡፡ በጁሊያን አቆጣጠር ዘመን
መለወጫ በመጋቢት /Marhc/ ስለሆነ በዚህ ወር ለአዲስ
ዓመት የሚዘጋጁበት ነው፡፡ ስለዚህ ፌብሩዋሬ ወይንም መዘጋጀት
ብለውታል፡፡
3. ሦስተኛው ወር ማርች /Marhc/ በእኛ መጋቢት ይባላል፡፡
ማርቲቭ /MARTIVE/ ወይንም የማርስ ጌታ / honor of
mars / ከሚል ቃል የወሰዱት ሲሆን ይህም የጦርነት
አምላካቸውን /gods of war/ ለማስታወስ የሰየሙት ነው፡፡
4. አራተኛው ወር አፕሪል/April/ በእኛ ሚያዝያ ሲሆን አፍሮዳይት
ማስታወሻ ይሆን ዘንድ የሰየት ነው፡፡
ሰባተኛ ወር ኦክቶበር /Aphrodite/ ስምንተኛ፣ ኖቨምበር /
May/ ዘጠነኛ፣ ዴሴምበር /Maria/ አስረኛ ወር ይሆናል፡፡
ከዚህ የምንረዳው የወራት ስያሜ የተሰጠው በጁሊያን
አቆጣጠር ጊዜ መሆኑን ያሳየናል፡፡
7.6 የዕለታት ስያሜ ልዩነት
ኢትዮጵያውያን ቀኖቻችንን የሰየምነው በሥነ ፍጥረት ላይ
ተመስርተን ነው፡፡
1. እሑድ አሐደ ከሚለው ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም አንድ
አደረገ የመጀመሪያ ሆነ ማለት ነው፡፡ በዚህ ቀን ፍጥረታት
መፈጠር ስለጀመሩ እሑድ ተብሏል፡፡
2. ሠኑይ /ሰኞ/ ሠነየ ከሚል ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ሁለት
አደረገ ማለት ነው፡፡ ለሥነ ፍጥረት ሁለተኛ ስለሆነ ሰኑይ /ሰኞ/
ተብሏል፡፡
3. ሠሉስ/ማግሰኞ/ ሠለሰ ከሚል ግስ የተገኘ ሲሆን ሦስት አደረገ
ማለት ነው፡፡ ማግሰኞ የሚለው የሰኞ ማግስት ማለት ነው፡፡
4. ረቡዕ ረብዐ /አራት አደረገ/ ከሚል ግስ የተገኘ ሲሆን ለሥነ-
ፍጥረት አራተኛ ቀን ማለት ነው፡፡
5. ሐሙስ ሀመሰ /አምስት አደረገ/ ከሚል ግስ የተገኘ ሲሆን
ለሥነ-ፍጥረት አምስተኛ ቀን ማለት ነው፡፡
6. ዓርብ ዓረበ ከሚል ግስ የተገኛ ሲሆን ተካተተ ማለት ነው፡፡
ፍጥረት እሑድ መፈጠር ጀምረው ዓርብ ስለተካተቱ /ተፈጥረው
ስለተፈፀሙ/ ዓርብ ተብሏል፡፡
7. ቅዳሜ ቀዳሚትሲሆን ሰንበተ ክርስቲያን ከሆነችው ከዕለተ እሑድ
ቀድማ ስለምትገኝ ቀዳሚት ሰንበት /ቅዳሜ/ ተብላለች፡፡
አውሮፓውያን ግን ቀኖቻቸውን የሰየሙት ልክ እንደ
ወራቶቻቸው ሁሉ በጣዖቶቻቸውና በአማልክቶቻቸው ስም ነው፡፡
1. ሰንዴይ /Sunday/ ማለት የፀሓይ ቀን ማለት ነው፡፡ በፀሓይ
ያመልኩ ስለነበር የፀሓይ ቀን ማለት ብለውታል፡፡
2. መንዴይ /Mon-day/ የጨረቃ ቀን ማለት ሲሆን በጨረቃ
ስለሚያመልኩ የሰየሙት ነው፡፡
3. ቲዮስዴይ /tues-day/ ቲዮ የሚባል የጦርነት አምላክ
ስለነበራቸው ለሱ ማስታወሻ የሰየሙት ነው፡፡
4. ዌድንስዴይ /Wednes-day/ የታላቁ አምላክ የዎደን ቀን
በማለት ሰይመውታል፡፡
5. ተርስዴይ /Thurs-day/ ቶር በሚባለው የነጎድጓድ አምላክ ስም
ደይመውታል፡፡
6. ፍራይዴይ / Fri-day / የታላቁ አምላክ የዎደን ሚስት ስሟ
ፍሪግስ ይባል ስለነበር ለሷ መታሰቢያ እንዲሆን ፍራይደይ
ብለውታል፡፡
7. ሳተርዴይ /Satur-day/ የሰማይ ኮከብ የሳተርን የከዋክብት ቀን
ማለት ሲሆን በከዋክብት ያመልኩ ስለነበር ሳተርዴይ ብለውታል፡፡
7.7 የሰዓታት ልዩነት
ጎርጎርዮውያን 365 ቀን ከ5 ሰዓት ከማድረጋቸውም
በተጨማሪ ከፀሓይ ዙሪያ ጋር በተያያዘ በቀኑ ውስጥ ያሉት ሰዓታት
ወጥነት የላቸውም፡፡ አውሮፓውያን በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ /
ከምድር ወገብ/ ከላይ ስለሚገኙ ፀሓይ በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ
ስትሆን ቀኑ በመርዘም ሌሊቱ ያጥራል፤ በደቡባዊ ንፍቅ ክበብ
ስትሆን ቀኑ በመርዘም ሌሊቱ ረዝሞ፤ ቀኑ ያጥራል፡፡ እኩል 12
ሰዓት ቀን 12 ሰዓት ሌሊት የሚሆንበት ጊዜ በጣም ትንሽ ነው፤
ይህም ፀሓይ በምድር ወገብ አካባቢ በምትሆንበት ጊዜ ብቻ
ነው፡፡
የኢትዮጵያውያን ሰዓት ግን ሁልጊዜም በ12 ሰዓት የተከፈለ ነው፡፡
ቀኑ ሙሉ 12 ሰዓት ሌሊቱን ሙሉ 12 ሰዓት ነው፡፡ ምክንያቱም
ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትገኘው በምድር ወገብ አካባቢ በመሆን
ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሰዓት የሚጀምረው ከሣልሲት /ከቅጽበት ነው/
60 ሣልሲት= 1ካልዒት /150ው ካልዒት አንድ ነው/
60 ካልዒት = 1 ኬክሮስ ነው
60 ኬክሮስ = 1 ዕለት ወይም 24 ሰዓት ይሆናል፡፡
60 ደቂቃ = 1 ሰዓት ነው
ወስብሀት ለእግዚአብሔር!!!
ጥያቄ አለኝ????
ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ልደትን
(የጌታችንን ልደት) በ29 ከኛጋ ለምን ያከብራሉ?
የዘመን መለወጫ መስከረም አንድ መሆኑን በምን
አወቃችሁ??? ዘመኑስ በአራቱ ወንጌላውያን መሰየሙ
ለምን እንደሆነ ታውቁት ይሆን????
ጥምቀትንም ጥር 11 ለምን ያከብራሉ?
በሠጀመሪያ ልደት ታህሳስ 29 መሆኑን እንዴት
አወቃችሁ???
ጥምቀትም ጥር11 መሆኑን እንዴት አወቃችሁ??
ይቀጥላል፡፡
ባህረ ጥበባት የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ
ቤተክርስቲያን ይህን የዘመን ቀመር ስትሰራ አምልኮቷን
ወንጌልን ልትሰብክበት ነው፡፡
ዘመናትን በአራቱ ወንጌላዊያን ከፍላ በደሙ የመሰረታትን
ክርስቶስን ትሰብካለች፡፡
ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን አይ ልደትን እናከብራለን ካሉ
መጀመሪያ ጾመ ነቢያትን መጾም ግድ ነው ከጾሙ በኀላ
ከኛጋ ያክብሩ፡፡
የዘመን ቆጠራችን ኦርቶዶክስን የሚሰብክ ነው
የዘመን ቆጠራችን እጅግ የሚረቅ የሚደንቅ ምስጢር
ጥበብን የያዘ ነው
የዘመን ቆጠራችን መጽሀፍ ቅዱስን የሚሰብክ ነው፡፡
እነ ኢሳያስን አስበን የነቢያትን ጾም ከጾምንን በኀላ ልደትን
እናከብራለን
ልደትን ካከበርን በኀላስ?
ጥምቀትን እናከብራለን ቃል እግዚአብሔር ከተወለደና
ከአደገበኀላ ተጠምቋልና
ከዛ ደሞ ሆሳዕና ስቅለትን ተንሳኤውን እርገቱን
ጰራቅሊጦስን ፋሲካን እናከብራለን ከዛም ዳግማዊ
ተንሳኤ ምጽአቱን እናከብራለን ይህን ሁሉ ባህረ ጥበባት
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በጾም ጀምራ በምስጢር በጥበብ
ታከብራለች ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንም ግጻዊውን
ከስንክሳሩ ስንክሳሩን ከሃይማኖተ አበው ሃይማኖተ አበውን
ከቅዳሴው ቅዳሴውን ከማህሌቱ በምስጢር በጥበብ
አያይዘው ይህን ቃለ እግዚአብሔር ከዘመን ቆጠራችን
አያይዘው የየቀኑን የየሳምንቱን የየወሩን የየአመቱን ቀናት
መጽሀፍ ቅዱስን ይሰብኩበታል ወንጌልን ይሰብኩበታል፡፡፡
ታዲያ ምንም የማይመለከታቸው ፕሮቴስታንቶች እኛ
በመሰረትነው ጥበብና አምልኮ ላይ ምስጢሩ ሳይገባቸው
ጥልቅ ማለታቸው ለምን ይሆን ጾመን ማህሌቱን ቆመን
ቅዳሴውን ቀድሰን ምስባኩን ሰብከን መጨረሻላይ በዓሉን
ልናከብር ስንል ብቻ እኛም እናከብረዋለንኮ ማለት ተገቢ
ነው????
ደሞ ሆሆሆ ይቺ ፖለቲካ የሚሏት ነገር አለች ደምብ ነው
አሉ በኛ በዓል ሃይማኖታዊ መግለጫ መስጠት......
ፓስተር ቶሚ ስለ ገና ልደት በአል ምን አስተያየት አለህ?
EBS tv
መጋቢ ሊሊ ስለ ዘመን መለወጫ በዓል ብትገልጺልን? EBC
ፒር bla bla bla........................
እኔ ከኛጋ ለምን አከበሩ አይደለም ማክበራቸው የእውነት
ደስ ይለኛል ግን አላይደል ለባለቤቱ ክሬዲት መሰጠት
አለበታ.........
ወዳጄ ፕሮቴስታንትን ባንድ ቃል ብቻ ግለጸው ብትባል የትኛው ቃል ባሕሪውን የሚገልጽ
( የሚመጥን ) ይመስልሃል ?
ፕሮቴስታንትን ባዶ የሚለው ቃል በሚገባ የሚገልጸው ይመስለኛል ፦
ባዶ ታሪክ
ባዶ እምነት
ባዶ ሥርዓት
ባዶ እውቀት
ባዶ መልስ
ባዶ ሕይወት
ባዶ አዳራሽ ጥቂቶቹ የባሕሪው መገለጫዎቹ ናቸው ።
ፕሮቴስታንት ብጠይቀው ምንም የማይመልስ ዲዳ ፣ ብታስረዳው ምንም የማይገባው ድንዙዝ ነው ።
ፕሮቴስታንት ከዲያቢሎስ የተጎናጸፋቸው ሰባት ሐብታት ( ፀጋዎች ) አሉት
1 . ክህደት
2 .ትዕቢት
3 .ጥላቻ
4 .ምቀኝነት
5 .ስድብ
6 .ማጭበርበር
7 .ማስመሰል ናቸው
ይሄን ተዝቆ የማያልቅ ሐብቱን እየዘረዘረ እየመነዘረ ይጠቀማል ይዋጋል ይቃወማል ።
ሐዋርያው ይሁዳ ፦ ከተናገረው በላይ ስለነሱ ማለት ይከብዳል
" በነፋስ የተወሰዱ ውኃ የሌለባቸው ደመናዎች፥ ፍሬ የማያፈሩ ሁለት ጊዜ የሞቱ ከነሥራቸው የተነቀሉ በበጋ የደረቁ ዛፎች "
ነበር ያለው (የይሁዳ መልእክት 1:12)
የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፦
፨ የራሷ ፊደል
፨ የራሷ የግዕዝ ቋንቋ
፨ የራሷ መጽሐፍ ቅዱስ ( ከዕብራይስጡና . ከግሪኩ ቀጥታ የተተረጎመ )
፨ የራሷ የዘመን አቆጣጠር
፨ የራሷ ያሬዳዊ ዜማ
፨ የራሷ የዜማ መሳሪያ ( ጸናጽል ከበሮ በገና ...)
፨ የራሷ የጥንታዊ ገዳማትና አድባራት ባለቤት ነች ።
፨ በዓለም ላይ የጠፉ ቢፈለጎ እንኳን በባለቤቶቹ በእስራኤላውያን ዘንድ እንኳን የማይገኙ (ለምሳሌ መጽሐፈ ሄኖክን ) የመሳሰሉ ቅዱሳት መጻሕፍትን ብትፈልግ የምታገኝው በዚህች ቤተ ክርስቲያን ነው
፨ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውን ታቦተ ፅዮንን ብትፈልግ የምታገኝው በዚህች ቤተ ክርስቲያን ነው
፨ ክርስቶስ የተሰቀለበትን ግማደ መስቀል በዓለም ላይ እግርህ እስኪነቃ ብትዞር የምታገኝው በዚህች ቤተ ክርስቲያን ነው ።
ወዳጄ እስቲ በዓለም ላይ ይህን ሁሉ መንፈሳዊ ሐብት አማልቶ ይዛል ( አለው ) የምትለውን አንድ የእምነት ተቋም ስሙን ጥራልኝ ? የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለምን የፀጋው ግምጃ ቤት እንደምትባል አሁን ገባህ ?
ባዶ የሆነው የፖሮቴስታንቱ ድርጅት
፨ የሷን መጽሐፍ ቅዱሰ ወስዶ ለገዛ ፍላጎቱ እንደሚመችው እየጨመረና እየቀነሰ አሻሽሎ ይጠቀማል ፤ ከሷ ወስዶ መልሶ እሷን ለማስተማር ይዳዳዋል ፤ ከሷ መውሰዱን ሸምጥጦ ይክዳል ፤ከሷ ለመውሰዱ ማስረጃ ካስፈለገህ በቀላሉ የያዘውን መጽሐፍ ቅዱስ ብታየው ከግዕዙ ቋንቋ የተቀዳ መሆኑን ትደርስበታለህ
ለምሳሌ ፦
፨ እግዚአብሔር የሚለው ቃል የግዕዝ ቃል ሲሆን እግዚእ ማለት ጌታ( ገዢ ) ፣ ብሔር ማለት ዓለም ሲሆን እግዚአብሔር ማለት ወደ አማርኛ ሲመለስ የዓለም ጌታ(የዓለም ገዢ ) ማለት ነው ።
፨ ኦሪት (የጥነት )
፨ ዘፀአት ( መውጣት )
፨ ዘሁልቁ ( መቁጠር )
፨ ማህልየ ማህልይ ዘሰሎሞን (ከመዝሙራት ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር )
፨ ወልደ ዕጓለመህያው ( የሰው ልጅ ) ማለት ሲሆን እንዳሉ በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ የግዕዝ ቃላትና ሐረጎች ናቸው እነዚህና ሌሎችም የሚነግሩህ መጸሐፍቱ ከየት እንደመጡና ምንጫቸውን ጭምር ነው ።
ባዶ የሆነው የፕሮቴስታንቱ ድርጅት
የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በምታወጣው የዘመን ቀመር ነው ዘመኑን የሚቆጥረው ፤ እሷ ላይ ተለጥፎና የሷ ጥገኛ ሆኖ የተነገረውን ዘመን እየቆጠረ ይኖራል እንጂ ልቁጠርስ ቢል ምኑን ይቆጥራል ? ምን አለውና ?
ይሄ ባዶ ጅርጅት እንኳን የራሱ የሆነ ዘመን አቆጣጠር ሊኖረው ቀርቶ የሚቀጥለው የጌታ ልደትና ትንሣኤ መቼ እንደሚከበር እንኳን አያውቅም ፤ ለተከታዮቹ የሚነግራቸው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የምታወጣውን ካላንደር እያየ ነው ፤ ስለ ዘመን ቀመር ብታስረዳው የማይረባ የማይጠቅም ነው ይልሃል ፤ አንተ የጌታን ልደትና ትንሣኤ ስታከብር ደግሞ አብሮ ተመሳስሎ ካንተ ጋር ሲያከብርና ከኔ ወዲያ ላሳር ሲል ታየዋለህ ፤ ቀን መቁጠርና በዓላትን ማክበር የማይረባ የማይጠቅም ከሆነ ለምን አንተ የጌታን ልደት የጌታን ትንሣኤ ታከብራለህ ? ለምን ሌላውን ትነቅፋለህ ? ብትለው ወዳጄ እሱ ዲዳ ነው ምንም አይመልስልህም ፤ ጌታ ለዘላለም ፍሬ አይገኝብስሽ ብሎ እንደረገማት ዛፍ ፤ፍሬ ያለው መልስ የማታገኝበት በዚህ ፈንታ የማይረባ የማይጠቅም ፍሬ ከርስኪ ሲቀባጥር ታገኝዋለህ
ወዳጄ ከውጭ አገር ቱሪስት መጥቶ የሚጎበኝው ፤ ቱሪስቱ ባየው ነገር ተገርሞ ፣ተደንቆ ፣ ተደሞ የሚሄደው በማነው ? በኦርቶዶክስ ገዳማት ፣ አድባራትና በዓላት አይደለምን ? የፕሮቴስታንቱ ድርጅት ይጓብኝ ቢባል እንኳን ምኑ ይጓበኛል ? ምን አለውና ? ቃሉ " ምድር ባዶ ነበረች አንዳችም አልነበረባትም " እንደሚል ዘፍ 1 : 2 ምንም የሌለው ባዶ አይደለምን ? ገና ዘፍጥረት 1 : 2 ላይ ያለ ምስኪን ድርጅት ምን አፍ አለውና ያውራ ?
ወዳጄ አንተ የመስቀል ፣ የጥምቀትና የቅዱሳን በዓላትን ስታከብር ፤ ነጭ ለብሰህ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስትጎርፍ ፤ ስታስቀድስ ፣ ስትጾም ስትጸልይ ፣ ስትሰግድ የሚበሽቀው የሚቃጠለው
ወዲያው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ በዚሁ አንተ በዓላትን በምታከብርበት ፣ አጽዋማትን በምትጀምርበት ቀን እየጠበቀ አንዴ ኮንፍረስ አንዴ የአዳር ፕሮግራም ለማዘጋጀት የሚራወጠው ፤ እንዳበደ ውሻ ያገኝሁትን ሁሉ ካልነከስኩ የሚለው ለምን ይመስልሐል ? ባዶነቱ የሚፈጥርበት ቅናት አይደለምን ?
ወዳጄ እግዚአብሔር ስድስቱን ቀን ሥራ ሰርቶ በሰባተኛው ቀን ከሥራ ሁሉ አረፈ ይላል ቃሉ ነገር ግን ዲያቢሎስና መናፍቃኑ እጅና ጓንት ሆነው ያንተን ፤ ክርስቶስ በደሙ የዋጃትንና የመሰረታትን ቤተ ክርስቲያን ለማፍረስ አይደለም የአንድ ቀን የአንድ ደቂቃ እረፍት እንደሌላቸው እወቅ ።
ወዳጄ አንተ ያለህ መንፈሳዊ ሐብትና ፀጋ ላይታይህና ላታስተውለው ትችላለህ ፤ ምናልባት በዚህ መንፈሳዊ ሐብትህ ብትጠቀምበት ሰይጣን ምን አይነት ፀጋና ክብር
እንደምታገኝ ጠንቅቆ ያውቃል ስለዚህ በእባብ ተሰውሮ አዳምና ሔዋንን ዋሽቶ ፀጋቸውን ያሳጣቸው ጠላት ዛሬ ደሞ ላንተ በተራህ በፕሮቴስታንቱ ተሰውሮ መጥቶ ይዋሽሃል ይቃወምሃል ይዋጋሀሃል ፀጋህን ያሳጣህ ዘንድ።
ፕሮቴስታንቱ ሳያቁት ከባዶነት በሚመነጭ ቅንአት አንተን ይቃወማሉ ይዋጋሉ ይቺን ቀዳዳ ያገኝ ሰይጣን ደግሞ እነሱን እንደፈለገ እንደ ጋሪ ፈረስ እየጋለበ ግዳጁን ይፈጽማል ።
ወዳጄ ያንተ ቤተ ክርስቲያን
የረጅም ዘመን የታሪክ ባለቤት ፤
የብዙ ቅዱሳት መጻሕፍት ማህደር ፤
የብዙ ሊቃውንት መፍለቂያ ፣
የፀጋው ግምጃ ቤት ነችና ሰይጣን እየተበሳጨ የሚያወራውን አትስማ ፤ እግዚአብሔር የሚሰጠውን ፀጋና ክብር ታገኝ ዘንድ ዝም ብለህ ሥራህን ሥራ

“በዚህች ዓመት ደግሞ ተዋት” ሉቃ.13÷6-9ወልድ /ኢየሱስ ክርስቶስ/ በመዋዕለ ሥጋዌው በምሳሌ አድርጐወንጌልን አስተምሯል፡፡ በምሳሌ ማስተማር ሊተላለፍ የተፈለገውንመልእክት ሲያስተላልፉት ም...
03/09/2021

“በዚህች ዓመት ደግሞ ተዋት” ሉቃ.13÷6-9
ወልድ /ኢየሱስ ክርስቶስ/ በመዋዕለ ሥጋዌው በምሳሌ አድርጐ
ወንጌልን አስተምሯል፡፡ በምሳሌ ማስተማር ሊተላለፍ የተፈለገውን
መልእክት ሲያስተላልፉት ምግብን በጣፈጠ መረቅ ፈትፍቶ
እንደማጉረስ ያህል ይሆናልና፤ እንዲሁም አንድ መልእከት
በምሳሌ ጣፍጦ በቋንቋ ዘይቤ ተውቦ ሲቀርብ ምሥጢሩ ልብን
ይማርካል፡፡ ስለዚህ የሰው አእምሮ በሃይማኖት ልጓም ተስቦ
ለምግባረ ጽድቅ እንዲዘጋጅ ጌታችን ለነጋዴው በወርቅ በዕንቁ፣
ለገበሬው በእርሻ በዘር፣ ለባልትና ባለሙያዎች በእርሾ በቡሆ፣…..
ወዘተ እየመሰለ ያስተምር ነበር፡፡ ማቴ.4÷30፡፡
እኛም ጌታ በምሳሌ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል ለወቅቱ
የሚስማማውን መርጠን እንመለከታለን
በሉቃ.13÷6-9 ላይ
ይህንንም ምሳሌ መሰለ “ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት አጠገብ
የተተከለች በለስ ነበረች ግን ፍሬ ሊፈልግባት ቢመጣ ምንም
አላገኘም፡፡ ስለዚህ የወይን አትክልት ጠባቂዋን እነሆ ከዚህች
በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁምና
ቁረጣት፤ ስለምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳሉቁላለች? አለው፡፡” እርሱ
ግን መልሶ ጌታ ሆይ ዙሪያዋን እስክኮተኩትላትና ፋንድያ
እስካፈስላት ድረስ በዚህች ዓመት ደግሞ ተዋት፡፡ ወደ ፊት ግን
ብታፈራ ደህና ነው፤ ያለዚያ ግን ትቆርጣታለህ አለው፡፡” ተብሎ
ተጽፏል፡፡
ይህ ከላይ የተገለጸው ምሳሌ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን
ሲተረጐም /ሲመሰጠር/ እንዲህ ነው፤ የወይን አትክልት
የተባለች ኢየሩሳሌም ናት፣ አንድ ሰው የተባለ እግዚአብሔር ነው፣
በለስ የተባሉ ደግሞ ቤተ እስራኤል ናቸው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ
“እግዚአብሔር ለዘለዓለም አይራብም” ይላል ኢሳ.46÷25፡፡
ራሱ ጌታችንም “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ
ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው፡፡” ብሏል ዮሐ.4÷35 ፡፡ ስለዚህ
ሰማያዊያን መላእክትን እንዳይራቡ ያደረገ አምላክ እስራኤል
ዘሥጋን ገበሬ በማያርስበት ዘር በሌለበት ዝናብ በማይጥልበት
ምድረ በዳ መና ከሰማይ አውርዶ የመገበ ጌታ ተራበ ሲባል
ያስገርማል! ግን ፍጹም አምላክ እንደመሆኑ ፍጹም ሰው ሆኗልና
አልተራበም አንልም፤ በሥጋ ተርቧልና የዕፀ በለስ ፍሬን ፈለገ፡፡
ይኸውም የበለስ ውክልና ከተሰጣቸው ቤተ እስራኤል
የሃይማኖትና የምግባር ፍሬን እንደፈለገ ያመለክታል፡፡ “በለስ
ዘይቤ ቤተ እስራኤል እሙንቱ” ተብሏልና እግዚአብሔር አምላክ
በብሉይ ኪዳን በቅዱሳን ነቢያት አድሮ የሃይማኖት /የምግባር/
ፍሬ ባገኝባቸው ብሎ ወደ እስራኤል ሔደ፤ ግን ምንም አላገኘም፡፡
እንዲያውም ሕዝቡ ቅዱሳን ነቢያትን በመጋዝ እየሰነጠቁ፣
በምሳር እየፈለጡ በማጥፋት ከዘመን ዘመን ወደተለያየ አዳዲስ
ባዕድ አምልኮአቸው ሲገቡ አየ፡፡ ስለዚህ የበለስዋን ጠባቂ
“ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም ፍሬ አላገኘሁባትምና ቁረጣት”
አለው፡፡ ሦስት ዓመት ያለው ዘመነ መሳፍንት፣ ዘመነ ነገሥታትና
ዘመነ ካህናትን ነው፡፡ በዚህን ጊዜ የወይን ጠባቂዋ የተባለ
መጋቤ ብሉይ ቅዱስ ሚካኤል “ተራድቼ ሥራ እስካሠራቸው
ድረስ የዘንድሮን ይቅር በላቸው” እያለ መለመኑን ያጠይቃል፡፡
አንድም ሰው የተባለ አብ ቢሉ በልጁ ህልው ሆኖ፣ ወልድ ቢሉ
ሰው ሆኖ ሃይማኖት፣ ምግባር ፍለጋ ወደ እስራኤል ሄደ፡፡ ሦስት
ዓመት በመዋዕለ ስብከቱ እየተመላለሰ ሲያስተምራቸውም ምንም
ፍሬ አላፈሩምና “ይህችን ዕፀ በለስ ቁረጣት” አለው፡፡ መጋቤ
ሐዲስ ቅዱስ ገብርኤል ግን “ተራድቼ ሥራ እስካሠራቸው ድረስ
ይቅር በላቸው፡፡” ብሎ ለመነ የጌታን ትምህርት ያልተቀበሉ
አይሁድ ግን የንስሐን ፍሬ ለማፍራት በጄ የሚሉ አልሆኑም፡፡
በአንደበታቸው የአብርሃም ልጆች ነን ይላሉ፤ ነገር ግን
የአብርሃምን ሥራ ሊሠሩ አልቻሉም፡፡ “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ
ያከብረኛል ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው” እንዲል፡፡
ስለዚህ ጌታ ከዕፀ በለሷ ዛፍ ምንም የሚበላ ፍሬ ስላላገኘ
ረገማት፡፡ አንድም ጌታችን የፈለገውን ባለማግኘቱ ጉባኤ
አይሁድን ረገመ፡፡ “በአንጻረ በለስ ረገማ ለኃጢአት” እንዲል፡፡
ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለዚህ ጉዳይ እስራኤል ከበረከት
ይልቅ እርግማን እንዳገኛቸው አሕዛብ ደግሞ የእግዚአብሔርን
ጸጋ እንዳገኙ ሲገልጽ “አሕዛብ በእግዚአብሔር ቸርነት አበባ
ሰበሰቡ፤ በአይሁድ ዘንድ ግን እሾህ ተረፈ፡፡ ይኸውም የሃይማኖት
ጉድለት ነው፡፡” ብሏል፡፡
ዛሬም ገበሬ ዘርን ዘርቶ አርሞና ኮትኩቶ ከአሳደገ በኋላ የድካሙን
ፍሬ እንደሚጠብቅ ሁሉ፤ እግዚአብሔር አምላካችንም በድንቅ
መግቦቱ ከአሳደገን ልጆቹ የምግባርና የሃይማኖት ፍሬን
ይፈልግብናል፡፡ ግን ጌታ ወደ በለስ ሕይወታችን ቢመጣ ምን
ያገኝ ይሆን? ፍሬ ወይስ ቅጠል?
የእግዚአብሔር ቃል ግን ለንስሐ
የሚገባውን ፍሬ እንድናፈራ ያዘናልና መንፈሳዊ ሕይወታችን
እንዳይደክም፣ እንዳይጠወልግ፣ እንዳይደርቅና አላስፈላጊ ሆኖ
ሲገኝ ደግሞ ወደ እሳት እንዳይጣል የንስሐን ፍሬ ልናፈራ
ይገባናል፡፡ ሕይወት ያለ ንስሓ ክንፍ እንደሌላት ወፍ ናትና፡፡
በንስሓ ወደ እግዚአብሔር የሚመለሱ ሰዎች ግን ይቅርታን /
ምሕረትን/ ያገኛሉ፡፡ እግዚአብሔር የሚመለከተው ያለፈ
ማንነታችንን ሳይሆን የዛሬውንና የወደፊቱን ሕይወታችንን ነውና፡፡
ቅዱስ ያሬድ “ኢተዘኪሮ አበሳ ዚአነ ኢኃደገነ ፍጹመ ንማስን ኄር
እግዚአብሔር ኃጢአታችንን በማሰብ እንጠፋ ዘንድ ከቶ
አልተወንም ቸር አምላክ ነውና” እንዲል፡፡ አዎ! እኛ በንስሓ
ከተመለስን አምላካችን በኃጢአታችን ላይ አያስኬደንም፤ እርሱ
የኃጢአታችንን አድራሻ ክረምት በፈለቀው ባሕር ውስጥ
ይጥለዋልና፡፡ ሚክ.7÷18፡፡
እኛ ሰዎች ልብ ካልን በአዲሱ የዘመን መለወጫ ከተፈጥሮ እንኳ
ብዙ ነገር መማር እንችላለን፡፡ አዝርእት፣ እፅዋት፣ ታድሰው፣
ቅጠላቸው ለምልሞ በአበባ ተንቆጥቁጠው እናያለን፡፡ ጋራ
ሸንተረሩ አረንጓዴ ለብሶ፣ አፍላጋት በየቦታው እየተንፎለፎሉ፤
አዕዋፍ በዝማሬ፣ እንስሳት በቡረቃ ሰማይ ምድሩን ልዩ
ያደርጉታል፡፡ ታዲያ ግዑዛኑ ፍጥረታት ጽጌ መዓዛቸውን የአዲስ
ዓመት መሥዋዕት አድርገው ሲያቀርቡ እኛስ ምን ይዘናል?
ሰው ሠራሽ ሆኖ መዓዛ የሌለውን፣ ፍሬ የማያፈራውንና አበባ
መሰሉን ሳይሆን፣ እግዚአብሔር የፈጠረውን፣ ያለመለመውንና
አብቦ መልካም መዓዛ የሚሰጠውን የተፈጥሮ አበባን እንሁን፡፡ ያን
ጊዜ ዝንቦች ሳይሆኑ ንቦች ማርን ለማዘጋጀት ይቀስሙናል፡፡
ስለዚህ በሃይማኖት ብቻ ያይደለ በምግባርም እናብብ፡፡ ያን ጊዜ
ከዘማሪው ክቡር ዳዊት ጋር “በቸርነትህ ዓመታትን ታቀዳጃለህ
ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል የምድረ በዳ ተራራሮችም
ይረካሉ” ብለን ለመዘመር እንበቃለን፡፡ መዝ.64÷11-13፡፡
በአጠቃላይ አዲስ ዘመን የአምላክ ስጦታ /በረከት/ ነው፡፡
ስለዚህ በምድር ላይ የሚኖር ማንኛውም ሰው ዘመኑ በፈጣሪ
ምልጣን የተያዘና የተገደበ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት “አቤቱ እኛ አፈር
እንደሆንን አስብ፤ ሰው ዘመኑ እንደ ሣር ነው፡፡ እንደ ዱር አበባም
ያብባል ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ግን ያልፋል” በማለት ሰው ካደገ
በኋላ በሕመም ፀሐይነት ይደርቅና በሞት ነፋስነት ይወለዳል፡፡
ባለፈው ዓመት ብዙዎች ወደሞት መንደር ደርሰዋል፤ እኛም
እንደነርሱ መንገደኞች መሆናችንን እንርሳ፡፡
ባለቅኔው፡-
“በሉ እናንተም ሒዱ የእኛም ወደዚያው ነው ወትሮም መንገደኛ
ፊትና ኋላ ነው” እንዲል፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስም በበኩሉ “ሣሩ ይደርቃል፤
አበባውም ይረግፋል፤ የአምላካችን የእግዚአብሔር ቃል ግን
ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል” በማለት የሰው ሁሉ ክብሩ ሥጋዊ
ሕይወቱና ተድላ ደስታው አንድ ጊዜ፣ አንድ ወቅት ለምልሞና
አምሮ የሚታይ ሆኖ ሳለ ያው ደግሞ ሳይቆይ የሚጠፋ መሆኑን
ያመለክታል፡፡ ኢሳ.40÷8፡፡ ስለዚህ በአዲሱ ዘመን ራሳቸውን
ለከፍተኛ ግብ የሚያዘጋጁ ሁሉ ወደ ተቀደሰ መንፈሳዊ ሕይወት
ሊሸጋገሩ ይገባል፡፡ ከእግዚአብሔር የተሰጠን እድሜም የአጭር
ጊዜ እንግዳ መሆናችንን ስለሚያስገነዝበን የምንሸኘውም እንዲሁ
ባልታወቀ ጊዜ ውስጥ መሆኑን በመረዳት እውነተኛ ሃሳባችንና
ሥራችንን ለተተኪው ትውልድ የማይረሳ አስመስጋኝ ቅርስ መሆን
አለበት፡፡
እንዲህ ዓይነቱ መልካምነት ደግሞ ለክርስቲያን በአዲሱ ዘመን
እንደሎተሪ ዕጣ የሚደርሰው ሳይሆን ራሱ ፈልጐ የሚሆነው ነው፡፡
ስለዚህ ይልቁንም በአሁኑ ዘመን በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ሁሉ
ፍጻሜ እያገኘ ባለበት ዘመን ፍቅር በጠፋበት ዘመን አብዛኛው
ሕዝብ ለማይረባ ነገር ብሎ ደገኛ ሃይማኖቱን እየለቀቀ ወደ
አልባሌ ቦታ ሲገባ የሕይወት ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ እኛ
በአዲሱ ዓመት የሕይወት ለውጥን ካሳየን የእግዚአብሔር ጸጋ
በውስጣችን ሥራውን በመጀመር በአንድ ሰንሰለት ላይ በርካታ
የሕይወት ለውጥን ያመጣልናል፡፡ ይህ የሕይወት ለውጥ በአዲሱ
ዘመን ውስጥ ለመኖሩ ተግባራዊ መለኪያው ደግሞ ቀጣይነቱ፣
ፍጹም ተጋድሎውና ግልጽ መሆኑ ነውና ራሳችንን እንመርምር፡፡
1ጢሞ.4÷7፡፡
ባለቅኔው፡-
“አዲስ ሰው ስትሆን ጽድቅን ሳታፈራ እንዲያው እንደታጠርክ
በክፋት ወጋግራ አሮጌውን ሳትጥል አዲስ መደረቱ የዘመን ቅበላ
ይቅር ምናባቱ!” እንዲል፡፡
የዚያች የወይን ጠባቂ “ወደፊት ብታፈራ ደህና ነው ያለበለዚያ
ግን ትቆርጣታለህ” እንዳለ ለነፍሳችን አንድ ነገር ሳንይዝ፣
ዘመናችን እንዳያረጅና እንዳይቆረጥ ዛሬ ለበጐ ሥራ እነነሣ፡፡
መጥመቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አሁንም “ምሳር በዛፎች ሥር
ተቀምጧል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ
ይቆረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል” ይላልና፡፡ ማቴ.3÷10 እነሆ !
ዛሬ ግን እንደ እግዚአብሔር ቸርነት አሮጌውን ዓመት አሳልፈን
ለአዲሱ ዓመት በቅተናል፡፡ ስለዚህ አዲሱን ዓመት በመንፈሳዊ
ሕይወታችን ጐልምሰን፣ ሁላችንም ለተቀደሰ ዓላማ ተሰልፈን፣
ከክፉ ምግባራችንም ተመልሰን የምንቀደስበት የምንባረክበት
የሰላም፣ የጤናና የደስታ ዘመን ያድርግልን አሜን!!
ማህበረ ቅዱሳን
ወስብሀት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር

Address

Addis Ababa

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Micah Alaye - ሚካ አላዬ posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share