04/08/2026
ለ180 የቲሞችና አረጋውያን ከ1.1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ተደረገ!
• ሀሩን ሚዲያ | ሐምሌ 28 ቀን 2018 ዓ.ል
በቄራ ሰላም መስጂድ የሚገኘው 'ሰላም የየቲም ህጻናትና አረጋውያን የልማትና መረዳጃ ተቋም' ከ1.1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለ180 የቲሞች፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ድጋፍ አድርጓል።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳዳም ሀሰን እንደገለጹት፤ በዕለቱ ከ1.1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የዱቄት፣ የዘይትና የሳሙና ድጋፍ ለ180 የቲሞች፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኛ ግለሰቦች ተሰጥቷል። ይህ ድጋፍም በየሁለት ወሩ በቋሚነት እየተካሄደ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ተቋሙ ከምግብና ከመሠረታዊ ቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ፣ በትምህርት፣ በህክምና፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና በአስቤዛ ድጋፍ ከ20 ዓመታት በላይ ለየቲሞችና ለአረጋውያን ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱንም አቶ ሳዳም ገልጸዋል።
የቄራ ሰላም መስጂድ ኢማምና የቂርቆስ ክፍለ ከተማ መጅሊስ የሥራ አስፈጻሚ አባል ኡስታዝ ሰኢድ አሊ በበኩላቸው፤ መስጂዶች ከመንፈሳዊ አገልግሎታቸው ባሻገር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በማስተባበር ሁለንተናዊ አገልግሎት ሊሰጡ እንደሚገባ ገልጸው፣ በመስጂዱ ቅጥር ግቢ ውስጥ በቋሚነት እየተካሄደ ላለው የድጋፍ ሥራ የተቋሙን ድጋፍ ሰጪ አባላት አመስግነዋል።
የቄራ ሰላም መስጂድ የሥራ አስፈጻሚ አባል ቶፊቅ ዳሪ በበኩላቸው፣ ለረጅም ዓመታት እየተደረገ ያለው ድጋፍ የቲሞች የብቸኝነት ስሜት እንዳይበረታባቸውና አረጋውያንም በችግር እንዳይወድቁ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
"የቲምነት ስሜቱ ከባድ ነው" ያሉት ቶፊቅ ዳሪ፤ ወላጅ የሌላቸው ህጻናትን መደገፍ የአካላዊ ፍላጎታቸውን ከማሟላት ባለፈ የስሜት ቁስላቸውን ለማቃለል እንደሚረዳ ጠቅሰው፣ መሰል ተቋማትን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል። በመሆኑም መላው ማህበረሰብ ከተቋሙ ጎን በመቆም ለየቲም ህጻናትና አረጋውያን የሚደረገውን ድጋፍ እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
በ1994 ዓ.ል በበጎ ፈቃደኞች የተመሠረተው 'ሰላም የየቲም ህጻናትና አረጋውያን መርጃ ድርጅት'፣ በአሁኑ ወቅት 500 የየቲም ቤተሰቦችን በቋሚነት ከመደገፉ በተጨማሪ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ዲናዊ ሀላፊነቶችን እየተወጣ መሆኑ በድጋፍ መርሃ ግብሩ ላይ ተገልጿል።
📅 ሰፈር 21 ቀን 1448 ዓ.ሂ
© ሀሩን ሚዲያ