Tewahido Haymanote ተዋህዶ ሃይማኖቴ

Tewahido Haymanote ተዋህዶ ሃይማኖቴ “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።”
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች ፥ምዕራፍ 1 ቁር 18

03/08/2022

ፈሪሳውያን ፣ሰዱቃውያን እና ጻፎች ምንድን ናቸው?
1. ፈሪሳውያን
• እነዚህ የተመረጡ ቡድኖች ወግ አጥባቂ ሆነው የሙሴን
ሕግን እና ባሕላችንን እንጠብቃለን የሚሉ ነበሩ፡፡
•ፈሪሳውያን በትንሳኤ ሙታን ያምናሉ፡፡
“ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም
ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፥ እንዲህ ሲል፦ ሁለት ሰዎች
ሊጸልዩ ወደ መቅደስ ወጡ፥ አንዱ ፈሪሳዊ ሁለተኛውም ቀራጭ።
ፈሪሳዊም ቆሞ በልቡ ይህን ሲጸልይ።
እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፥ ቀማኞችና ዓመፀኞች
አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ
አመሰግንሃለሁ፤ በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጦማለሁ፥ ከማገኘውም
ሁሉ አሥራት አወጣለሁ አለ። ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ
ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም፥ ነገር ግን።
አምላክ ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር።
እላችኋለሁ፥ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤
ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥
ራሱን ግን የሚያዋርድ ከፍ ይላል።” ሉቃ 18፡9-14፡፡
2. ሰዱቃውያን:-
• በመሠዊያው ከሁሉ በላይ ሥልጣን የነበራቸውና ከመሠዊያው
ከሚገኘው ስጦታ ይካፈሉ የነበሩ ቡድኖች ናቸው፡፡
• በጣም ሀብታሞች፣ በገንዘብና ቁሳዊ ነገር ብቻ ላይ Aትኩሮት
የነበራቸው የፈሪሳውያን ጠላቶች ነበሩ፡፡
• ሰዱቃውያን በትንሳኤ ሙታን አያምኑም፡፡
• ሰዱቃውያን በመላዕክት ወይም በመንፈስም መኖር አያምኑም፡፡
“ጳውሎስ ግን እኵሌቶቹ ሰዱቃውያን እኵሌቶቹም ፈሪሳውያን
መሆናቸውን አይቶ። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ፈሪሳዊ የፈሪሳዊም ልጅ
ነኝ፤ ስለ ተስፋና ስለ ሙታን
መነሣት ይፈርዱብኛል ብሎ በሸንጎው ጮኸ። ይህንም ባለ ጊዜ
በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ጥል ሆነ ሸንጎውም
ተለያየ።ሰዱቃውያን። ትንሣኤም መልአክም መንፈስም የለም
የሚሉ ናቸውና፤ ፈሪሳውያን ግን ሁለቱን ያምናሉ። ታላቅ ጩኸትም
ሆነ፥
ከፈሪሳውያንም ወገን የሆኑት ጻፎች ተነሥተው። በዚህ ሰው ላይ
ምንም ክፉ ነገር አላገኘንበትም፤ መንፈስ ወይስ መልአክ ተናግሮት
ይሆን? ብለው ተከራከሩ።” የሐ. ሥራ 23፡1-9፡፡
• ጌታችን “ኢየሱስም፦ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ
ተጠንቀቁና ተጠበቁ አላቸው። ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ
እንድትጠበቁ ብዬ ስለ እንጀራ እንዳልተናገርኋችሁ እንዴት
አታስተውሉምን? እነርሱም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት
እንጂ
ከእንጀራ እርሾ እንዲጠበቁ እንዳላላቸው ያን ጊዜ አስተዋሉ። ”
ማቴ 16፡6፣ 16፡11-12፡፡
3. ጻፎች
• እነዚህም ከፈሪሳውያን ጋር ተጠቅሰዋል፡፡ “በዚያን ጊዜ ኢየሱስ
ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሎ ነገራቸው።ጻፎችና
ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል።” ማቴ 23፡2፡፡
“እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ሰዎች ሳያውቁ በላዩ
የሚሄዱበት የተሰወረ መቃብር ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ።” ሉቃ
11፡44፡፡
• ጻፎች ከፈሪሳውያን ጋር ሆነው መጻሕፍትን የሚጽፉ እና
የሚያስተምሩ ፈሪሳውያን እንጂ የተለዩ የሃይማኖት ቡድኖች
አልነበሩም፡፡
• ጻፎች በዚህ መልክ የታወቁት ከእዝራ ዘመን አንስቶ ነው፡፡
“በያቤጽም የተቀመጡ የጸሐፊዎች ወገኖች
ቲርዓውያን፥ሺምዓታውያን፥ ሡካታውያን ነበሩ እነዚህ ከሬካብ ቤት
አባት ከሐማት የወጡ ቄናውያን ናቸው።” ቀዳ ዜና 2፡55፡፡
• ጻፎች በሕዝቡ ዘንድ ክብር ይሰጣቸው ነበር፡፡
• ጌታችን ስለጻፎችና ፈሪሳውያን ከተናገራቸው የሚከተሉት
ይገኛሉ፡፡ “ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ፥
ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም።” ማቴ 5፡20፡፡
“እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ መንግሥተ ሰማያትን
በሰው ፊት ስለምትዘጉ፥ ወዮላችሁ እናንተ አትገቡም
የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ። ” ማቴ 23፡13

12/02/2021

+ ኦርቶዶክሳውያን ለቅዱሳን ለምን ይዘምራሉ? +

ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ካሏት ብዙ መገለጫዎች አንዱና ዋነኛው ‹ምስጋና የሚገባውን› እግዚአብሔርን ሳታቋርጥ የማመስገን አገልግሎትዋ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ለማመስገን ለዓመታት የዜማ ስልት ተምረው የተመረቁ የስብሐተ እግዚአብሔር ሊቃውንት ያሏት ይህች ቤተ ክርስቲያን ዝማሬዋ ፣ ማሕሌትዋና ቅዳሴዋ የሃያ አራት ሰዓታት ጊዜ የማይበቃው ፣ ለሰዓት ሲባል በንባብ እየተባለ ፣ ዜማው እያጠረ የሚተው በመሆኑ ፀሐይ በማይጠልቅበት በዘላለማዊው መንግሥት ለማመስገን ዝግጁ ሆና የምትጠባበቅ ቤተ ክርስቲያን ያሰኛታል፡፡ ከዚህ እንደ ባሕር ጥልቅ ከሆነው ስብሐተ እግዚአብሔር ጋር የእግዚአብሔር ቅዱሳንንም በሰፊው ታመሰግናቸዋለች፡፡

በዚህች አጭር ጽሑፍ ምስጋና የባሕርይ ገንዘቡ የሆነው እግዚአብሔር ከሆነ ፍጡራን ለሆኑ ለቅዱሳን ሰዎች ፣ ለቅዱሳን መላእክትና ለድንግል ማርያም የሚዘመረው መዝሙርና የሚቀርበው ውዳሴ ምን ያህል ተገቢ ነው? ለቅዱሳን መዘመር ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ተገቢ ነው ወይ? የሚለውን እንመለከታለን፡፡

ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ሳስብ በመጽሐፍ ቅዱስ ወደር ያልተገኘለትን ዘማሪ ለመጠየቅ ወደድኩ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ በስሙ መቶ አምሳ መዝሙራት የተጻፉለት ፣ ራሱ ሰማኒያ ሰባት መዝሙራትን የዘመረና በሥሩ ያሉ መዘምራን ደግሞ አብረውት ብዙ መዝሙራትን የዘመሩበት የዝማሬ ባለ ጠጋ ንጉሥ ዳዊትን ‹‹እውነት ለፍጡራን ምስጋና ይገባል ወይ?›› ብዬ ልጠይቀው አስቤ ወደ መዝሙረ ዳዊት ገሰገስኩ፡፡

ፈጣሪ እንደ ልቤ ያለው ዳዊት የልቤን ማን እንደነገረው እንጃ የእኔን ጥያቄ ለመመለስ ቸኩሎ ጠበቀኝ፡፡ ገና የመጀመሪያው መዝሙሩን ‹‹ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሔደ ፣ በኃጢአተኞች መንገድ ያልቆመ ፣ በዋዘኞች ወንበር ያልተቀመጠ›› ብሎ ጀምሮት አገኘሁት፡፡ (መዝ. 1፡1) ዳዊት በዚህ ዝማሬው ‹ምስጉን ነው› ያለው ፈጣሪን ነው ወይንስ ፍጡርን? እግዚአብሔርን ነው እንዳልል ‹በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል› ይላል፡፡ ስለዚህ ዳዊት ዝማሬውን የጀመረው ‹በክፉዎች ምክር ያልሔደ ፣ በኃጢአተኞች መንገድ ያልቆመ ፣ በዋዘኞች ወንበር ያልተቀመጠ›ን ሰው በማመስገን ነው፡፡

ወደ መዝሙሩ ስገባ ዳዊት ምስጋናውን ሰፋ አድርጎ ‹ለቅኖች ምስጋና ይገባቸዋል› ‹ለችግረኛ የሚያስብ ምስጉን ነው› ‹አንተ የመረጥከው በአደባባዮችህም ለማደር የተቀበልከው ምስጉን ነው› ‹እግዚአብሔር አምላኩ የሆነ ሕዝብ ምስጉን ነው› ‹እልልታን የሚያውቅ ሕዝብ ምስጉን ነው› ብሎ ከግለሰቦች አልፎ ሕዝብን ሲያመሰግን አገኘሁት፡፡ ከሁሉ ያስደነቀኝ ግን ‹‹መተላለፉ የቀረችለት ፣ ኃጢአቱ የተከደነችለት ሰው ምስጉን ነው›› የሚለው ዝማሬው ነው፡፡ ኃጢአቱን እግዚአብሔር ይቅር ያለውና በደሉን ፈጣሪ የሸፈነለት ሰው በታላቁ ዘማሪ በዳዊት አንደበት መዝሙር ከተዘመረለት በሃሳብዋ እንኳን ኃጢአትን ስላልሠራችው ድንግል ምን ዓይነት መዝሙር ይዘመርላት ይሆን?

ንጉሥ ዳዊት ሕይወት ላላቸው ሰዎች ብቻ ዘምሮ አላቆመም ፤ ለማትናገረውና ከእንጨት ከድንጋይ በሰው እጅ ለተሠራችው ከተማው ለጽዮን የእግዚአብሔር ማደሪያ በመሆንዋ ዝማሬን አዝንሞላታል፡፡
‹‹እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታል ፤ ማደሪያው ትሆነው ዘንድ ወድዷታል፡፡ እንዲህ ሲል ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት ፣ መርጫታለሁና በእርስዋ አድራለሁ››
‹‹እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወድዳቸዋል ፤ የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ በአንቺ የከበረ ነገር ይባላል››
‹‹በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ ተቀመጥን ፤ ጽዮንን ባሰብናት ጊዜ አለቀስን ፤ የማረኩን በዚያ የዝማሬን ቃል ፈለጉብን ፤ የእግዚአብሔርን ዝማሬ እንዴት በባዕድ ምድር እንዘምራለን? ኢየሩሳሌም ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ፤ ባላስብሽ ምላሴ ከጉሮሮዬ ጋር ይጣበቅ ፤ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድድ›› ብሎ ስለ ቅድስቲቱ ከተማ ሲዘምር አገኘሁት፡፡ ከራሱ አልፎም በዙሪያው ላሉት በመዝሙሩ እንዲህ ሲል ጥሪ አቀረበ ‹‹ጽዮንን ክበቧት በዙሪያዋም ተመላለሱ ፤ ግንቦችዋን ቁጠሩ ፤ በብርታትዋ ልባችሁን አኑሩ ፤ ለሚመጣው ትውልድ ትነግሩ ዘንድ›› የእግዚአብሔር ከተማ ጽዮንን ለማይወድዱ ደግሞ በመዝሙሩ ‹‹ጽዮንን የሚጠሉ ሁሉ ይፈሩ ወደ ኋላቸውም ይመለሱ›› ብሎ ዘምሮአል፡፡

ዳዊት ስንት ኃጢአተኛ ሲራኮት ለሚውልና ለሚያድርባት ከተማ የእግዚአብሔር ማደሪያው እንድትሆን እንደ መረጣት አውቆ እንዲህ ሲዘምር ማየቴ ‹መንፈስ ቅዱስ ይጸልልሻል የልዑል ኃይልም ያድርብሻል› ለተባለችዋ ቅድስት ድንግል ማርያም ‹የጌታዬ እናት ፣ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ፣ የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ› ብዬ ለመዘመር እንድችል ኃይል የሚሠጥ ሆነልኝ፡፡ ባቢሎን በተባለ በኃጢአት ሥፍራ ሆኜ ድንግልን ባሰብኳት ጊዜ እንዳለቅስና ‹‹ድንግል ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ባላስብሽም ምላሴ ከጉሮሮዬ ይጣበቅ›› ብዬ እንድዘምርላት ድፍረት ሠጠኝ፡፡

የዳዊት ሲደንቀኝ ልጁ ሰሎሞን ደግሞ ‹ከመዝሙራት ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር› (መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን) በተባለ ውብ ድርሰቱ ከአባቱ የባሰ የመዝሙር ቅኔን ሲቀኝ አገኘሁት፡፡ በዚህ ዝማሬው ላይ በፍቅረኛሞች መካከል የሚደረግን የፍቅር ቃል ልውውጥ ሰበብ አድርጎ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ሙሽራው ስላደረጋትና እርስዋም ‹ውዴ› ብላ ስለምትጠራው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውብ ስንኞችን ጽፎ አገኘሁት፡፡

በዚህ ዝማሬው ላይ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውድዋ የሆነውንና ነፍስዋ የወደደችውን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስን ስትፈልገው ፣ በከተማ የሚጠብቁ ጠባቂዎች የተባሉ መላእክትን ስትጠይቅ ፣ ቤተ ክርስቲያን በቀዳም ስዑር የምትዘምረው ‹እርሱ እስኪፈልግ ድረስ ፍቅርን እንዳታስነሡት› ብላ አልጋ በተባለ መቃብር ስለ ሰው ልጅ ፍቅር የተኛውን ክርስቶስን እርሱ ወድዶ ሞትን ድል አድርጎ እስከሚነሣ በእምነት እንዲጠብቁ ስትናገር ፣ ውዴ ወደ ገነቱ ወረደ ብላ ነፍሳትን ይዞ ወደ ገነት ስለ መውጣቱ ስትዘምር በሰሎሞን ዝማሬ ውስጥ አገኘሁ፡፡ በዚህ ዝማሬ ላይ ሙሽራው ስለ ሙሽራዪቱ ቤተ ክርስቲያን ቅድስናና ውበት ፣ ጡቶችዋ ስለተባሉ የቃሉ ወተት ስለሚፈስስባቸው ብሉይና ሐዲስ ኪዳን ማማር ፣ ድንቅ ቅኔ ሲዘምር አገኘሁት፡፡

በሰሎሞን መዝሙር ላይ ‹ወዳጄ ሆይ ነይ ውበቴ ሆይ ተነሽ› ‹ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው ነውርም የለብሽም› የሚሉት ውብ ዝማሬዎች ለፍጡር እንጂ ለፈጣሪ የቀረቡ ምስጋናዎች አይደሉም፡፡ ለዚህም ነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን ውብ ዝማሬ ሁለተናዋ በቅድስና ለተዋበችው ድንግል ማርያም መዝሙር አድርጋ የምትዘምረው፡፡ አባቱ ዳዊት ‹ልጄ ሆይ ስሚ እዪም ጆሮሽን አዘንብዪ› ብሎ ለጠራት ድንግል ልጁ ሰሎሞን ‹እኅቴ ሙሽራ ሆይ› ብሎ መዘመሩን የምንቀበለውም ከዚህ ተነሥተን ነው፡፡

ቅዱሳንን ማመስገን በዳዊትና በሰሎሞን አላበቃም ፤ መላእክትም ለቅዱሳን ሲዘምሩ ታይተዋል፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ‹ጸጋ የሞላብሽ ሆይ ደስ ይበልሽ አንቺ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ› ብሎ ለድንግል ማርያም ያቀረበው ሰላምታ ‹ከእንዴት ውለሻል› ሰላምታ ያለፈ ምስጋና አይደለምን? ለዘካርያስ ‹አንተ ከካህናት ተለይተህ የተባረክህ ነህ› ያላለው ይህ መልአክ ለድንግል ለይቶ ያቀረበው በእርግጥም ምስጋና ነበር፡፡ ስለሆነም የገብርኤልን ሰላምታ ተውሰን ድንግሊቱን ለዘወትር እናመሰግናታለን፡፡ ገብርኤል ያቀረበውን እኛ ማቅረብ አያስፈልገንም የሚሉ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ሆኖም ድንግሊቱ ‹ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ያመሰግኑኛል› ብላ መናገርዋ ለማመስገናችን ምክንያት ነው፡፡ ‹ትውልድ ሁሉ› አለች እንጂ ሰው ሁሉ አላለችምና ከየትውልዱ የማያመሰግኗት ቢገኙ አይደንቅም ፤ ከእኛ የሚጠበቅብን እንደ ኖህ ‹በትውልዳችን ጻድቅ› ሆኖ መገኘት ብቻ ነው፡፡ መልአኩ ገብርኤል ‹ደስ ይበልሽ› ቢላትም እኛ ‹ደስ ይበልሽ› አንላትም የሚሉ ሰዎች መላእክት ‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ› የሚሉትን እግዚአብሔርም ‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ› ለማለት እንዴት ፈቃደኞች ሊሆኑ ይችላሉ?

ለቅዱሳን የሚቀርበው ምስጋና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው መሆኑን የምንደመድመው መድኃኔዓለም ክርስቶስ ራሱ ለመጥምቁ ዮሐንስ የተናገረው ምስጋና ነው፡፡ ‹‹ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ ከነቢይም የሚበልጠውን … እላችኋለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም›› (ሉቃ. 7፡26-28) ከዚህ በላይ ምስጋና ከየት ይመጣል? በዜማ መሆኑ ከሆነ ችግሩ በንባብ እንለዋለን።

የመጥምቁ ምስጋና በቅዱስ ገብርኤልም አንደበት ተነግሮ ነበር፡፡ ቅዱስ ገብርኤል የዮሐንስን ልደት ሲገልጥ ‹‹በመወለዱ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል›› ብሎ ነበር ፤ ወደ መዝሙር ሲለወጥ ‹ዮም ፍስሓ ኮነ በእንተ ልደቱ ለዮሐንስ› እንደማለት ነው፡፡

አባቱ ዘካርያስ ደግሞ ‹‹አንተ ሕፃን ሆይ የልዑል ነቢይ ትባላለህ›› ብሎ ነበር ይህም ‹ወአንተኒ ሕፃን ነቢየ ልዑል ትሰመይ ፤ አርኩ ለመርአዊ ትሰመይ›› የሚለው መዝሙር ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ለቅዱሳን ስትዘምር ቃላትና ግጥም የምትዋሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡

‹‹ሐውፅ እምሰማይ ተክለ ሃይማኖት ፀሐይ›› (ፀሐይ ተክለ ሃይማኖት ሆይ ከሰማይ ሆነህ ጎብኝ)
የሚል መዝሙር ቢዘመር ‹‹ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ›› የሚለውን የተስፋ ቃል ይዞ ነው፡፡ (ማቴ. ፲፫፥፵፫)

‹‹ጊዮርጊስ ኃያል ኮከበ ክብር›› ተብሎ ቢዘመር ‹‹ብዙዎችን ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ›› የሚለውን ይዞ ነው፡፡ (ዳን. 12፡3)

‹‹አቡነ አረጋዊ ሆይ ነፍሴ ዛሬ በአንተ ፊት የከበረች ትሁን!›› ‹‹ትክበር ነፍስየ በቅድሜከ ዮም ፤ ወባርከኒ አባ አረጋዊ›› ተብሎ ሲዘመር ብንሰማ አንድ የመቶ አለቃ በነቢዩ ኤልያስ ፊት ተንበርክኮ ‹‹የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ነፍሴ አሁን በፊትህ የከበረች ትሁን›› ብሎ ካቀረበው ልመና ተወስዶ ነው፡፡ (2ነገሥ. 1፡13)

በአንዳንድ ሥፍራ ለቅዱሳን በሚቀርቡ ምስጋናዎች ላይ ለፈጣሪ የቀረቡ የምስጋና ቃላት ተወስደው ለቅዱሳን ሲቀርቡ ይታያል፡፡ ይህንን የሚያዩ ሰዎች ቅዱሳን የተመለኩ ፣ የፈጣሪ የባሕርይ ክብሩ ለቅዱሳን የተሠጠ መስሏቸው ይተቻሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ለቅዱሳን በሚዘመሩ መዝሙራት ሁሉ ላይ የሚታረም ነገር አያጡም፡፡ ሆኖም ይህንን ዓይነት እርማት ላድርግ ብሎ የሚነሣ ሰው መጽሐፍ ቅዱስንም ማረም ሊኖርበት ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ለእግዚአብሔር የተነገረን ቃል ለቅዱሳን ሲሠጥ በተደጋጋሚ እናገኘዋለን፡፡

ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት ፡-

‹‹ገብረ መንፈስ ቅዱስ የዓለም ብርሃን ናቸው›› ሲባል ‹‹የዓለም ብርሃን ክርስቶስ ብቻ ነው›› ብሎ የሚቃወም ቢኖር ራሱ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ ‹‹እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ ፤ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ›› ብሏል፡፡ የእርሱ ብርሃንነት የባሕርይው የቅዱሳን ብርሃንነት ግን ከእርሱ የተሠጠ ነው ብለን እንከፍለዋለን እንጂ የቅዱሳንን ብርሃንነት አንክድም፡፡ (ማቴ. 5፡14)

አንዳንድ ምእመናን ስለ ድንግል ማርያም አማላጅነት ሲመሰክሩ ‹‹ለእመቤቴ የሚሳናት ነገር የለም›› ሲሉ የሚሰማ ሰው ራሱን እየነቀነቀ ‹የእኛ ሰው Bible ላይ ብዙ ይቀረዋል› ብሎ ሊመጻደቅ ይችላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያውቅ ከሆነ ግን ‹‹እምነት ቢኖራችሁ የሚሳናችሁ ነገር የለም›› የሚለውን የጌታ ቃል ፣ ‹‹ኃይልን በሚሠጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ›› የሚለውን የጳውሎስ ቃል በሰማበት ጆሮው ‹ያመነችው ብፅዕት› ‹የልዑል ኃይል ያደረባት› ድንግል ‹የሚሳናት የለም ሲባል ከመቆጣት ይልቅ ለምእመናን የተሠጠውን እምነትና ማስተዋል ያደንቃል፡፡ (ማቴ. 17፡20 ፣ ፊል. 4፡13 ፣ ሉቃ.1፡35፣45)

ለእግዚአብሔር የተነገሩ ቃላት ለቅዱሳን ተደግመው ብናገኛቸው እንኳን ትርጉሙን እንረዳለን እንጂ የእግዚአብሔርን ክብር ቅዱሳን ወሰዱ አንልም፡፡ ለምሳሌ ጌታ መጥምቁ ዮሐንስን ‹የሚያበራ መብራት ነበር ፤ በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ› ሲለው ወንጌላዊው ደግሞ ‹‹እርሱ ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ ብርሃን አልነበረም›› ብሎታል፡፡ የማንን እንቀበል? የጌታችንን ንግግር ወይስ የወንጌላዊውን? ዮሐንስ ብርሃን ነው ወይንስ አይደለም? መልሱ ግልጥ ነው ዮሐንስ ብርሃን ነው ፤ የዮሐንስ ብርሃንነት ግን ከክርስቶስ ብርሃንነት ጋር ሲተያይ የሻማና የፀሐይ ብርሃን ያህል ነውና ብርሃን አልነበረም ተብሏል ብለን እንረዳዋለን፡፡(ዮሐ. 1፡8 ፤ 5፡35)

የእግዚአብሔርን ክብር አስጠብቃለሁ ብሎ የትርጉም ልዩነቱን ሳይረዳ ለቅዱሳን የሚቀርብን ምስጋና የመተቸት ዝንባሌ ያለው ሰው ግን ይህ አካሔዱ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚያጣላው ነው፡፡ ሰሞኑን አንዳንድ ሰዎች ‹የአዳም ፋሲካው ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ› የሚለውን ቃል በመጥቀስ እንዴት ድንግል ማርያም ፋሲካ ትባላለች ‹ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአል› ይል የለምን እንዳሉ ሰማን፡፡ ስለ እንክርዳድ ማውራት እንክርዳድን ዝነኛ እንጂ ስንዴ ስለማያደርገው ተናጋሪዎቹን ትተን ጉዳዩን እናስተውለው፡፡

ወደ ሌላ ዝርዝር ሳንገባ አንድ ጥያቄ እናንሣ ፤ ክርስቶስ ፋሲካ ነው ወይንስ የፋሲካ በግ? ፋሲካ የሚባለው በዓሉ ነው? ወይንስ በጉ ነው? የታረደው በዓሉ ነው? ቢባል ምን ይመለሳል? "ፋሲካን እረድ" ሲል በጉን ነው (2ዜና 35:5)፣ "ይህ ፋሲካ ለእግዚአብሔር ተፈሰከ" ሲል በዓሉን ነው። (2ነገሥ 23:23)

ፋሲካ ሲል በዓሉን ከሆነ መሻገሪያ ፣ ደስታ ማለት ነውና ለድንግል ማርያምም ሊነገር ይችላል፡፡ ‹ታርዶአል› የተባለው ግን በጉን ነውና እመቤታችንን እመ በግዑ (የበጉ እናት) እንጂ የታረደችው በግ ብለናት እንደማናውቅ ግልጥ ነው፡፡ ጨርሶ ለክርስቶስ የተነገረ ቃል ለእርስዋ ለምን ይደገማል? ከሆነ ደግሞ እስቲ የቅዱስ ጳውሎስን ንግግር እንመልከት፡-

ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ 2:20 ላይ ፡- ‹‹ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ›› ብሏል፡፡ አልፎ ተርፎም ‹‹እኔ ለዓለም ከተሰቀልሁበት ከክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ›› ብሏል፡፡ (ገላ. 6፡14)

የዚህ ንግግር ትርጉም ምንድን ነው? ቅዱስ ጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር ተሰቅሎ ነበር ማለት ነው? የተሰቀለው በቀኙ ነው የግራው?"ለዓለም ተሰቀልኩ" እንዴት አለ? እውን ለዓለም የተሰቀለው ጳውሎስ ነውን? ክርስቶስ አይደለምን? የፋሲካው ሲገርምህ ለዓለም ተሰቅዬአለሁ ያለ መጣ? ጳውሎስ የተሰቀለውን የክርስቶስን ክብር መሸፈኑ ነውን?

እንደዚያ እንዳንል ደግሞ ራሱ ጳውሎስ ‹‹ጳውሎስ ስለ እናንተ ተሰቅሎአልን? እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን›› ብሎ አሳርፎናል፡፡ (1ቆሮ 1፡13) ስለዚህ መተርጎም መብራራት አለበት እንጂ ቃሉ ተመሳሰለ ተብሎ አይብጠለጠልም። ጫማ ይስተካከላል እንጂ እግር አይስተካከልም እንደሚባለው መስተካከል ያለበት የእኛ አረዳድ እንጂ የመጽሐፉ ቃል አይደለም።

ሐዋርያው ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ ሲል የክርስቶስን የመከራ መንገድ ተከትያለሁ ፣ የመከራው ተሳታፊ በመሆን የክብሩ ተካፋይ እሆናለሁ ሲል ነው። "ለዓለም ተሰቅልኩ" ያለው ደግሞ በክርስቶስ መከራ በማመኔ ለዓለማዊ የኃጢአት ሥራ ሙት ሆኜአለሁ ማለቱ ነው ብለን እናብራራለን እንጂ ጳውሎስ የጌታን ክብር ተጋፋ አንልም፡፡

ቅዱሳንን የምናመሰግናቸው የእግዚአብሔር ስለሆኑና ነቢዩ እንዳለው "እግዚአብሔርም በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ስለሆነ ነው" ሥዕሉ ሲደነቅለት የሚበሳጭ ሠዓሊ እንደሌለ ሁሉ የእርሱ ድንቅ ሥራዎች ሆነው ፣ እርሱን አገልግለው ሲወደሱ ፈጣሪን ደስ ይለዋል እንጂ አያዝንም። ጠርሙስ ሰብራ ሽቱን በእግሩ ላይ ላፈሰሰለች ሴት "ወንጌል በሚነገርበት ሥፍራ ሁሉ ያደረገችው ነገር ለእርስዋ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል" ብሎ የተናገረ ጌታ አንገታቸው ተሰብሮ ደማቸውን ስለ ስሙ ስላፈሰሱ ቅዱሳን በዓለም ሁሉ ቢነገርና ቢዘመር የሚከለክል አይደለም። (ማቴ 26:13)

ምስጋና እንኳን ለቅዱሳን በሃይማኖታችን ከጸናን ለእኛም ለደካሞቹም አልተከለከልንም ፣ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና :–

"ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥ ምስጋናም ይብዛላችሁ" ቆላስ 2: 7

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ሚያዝያ 19 2010 ዓ ም
አዲስ አበባ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ዘንድ ጸልዩ! ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like እና Share ያድርጉ
FB: https://www.facebook.com/officialHenokhaile/
Telegram: https://t.me/deaconhenokhaile
Instagram: https://www.instagram.com/p/CBnMF0nnhcQ/?igshid=549jvl607bv4
Youtube: https://www.youtube.com/channel/UCOaVsWC05aUjeqIEW3fWj7g

27/11/2020

+ ስሞት ዓይኔን የሚከድንልኝ ማን ይሆን? +

አንድ ሁልጊዜም መማር የማይታክታቸው አባት ነበሩ:: በጣም የተማሩ ቅኔ አዋቂ መጻሕፍት የመረመሩ ሊቅ ቢሆኑም ሁሌም ከአትሮንስ ሥር የማይጠፉ ተማሪ ነበሩ:: ይህንን ልምዳቸውን ያየ አንድ ሰው "እርስዎ ብዙ የተማሩና ያነበቡ ሰው ነዎት ከዚህ በኁዋላ ማረፍ ሲገባዎት ለምን ጊዜዎን በትምህርት ያጠፋሉ?" አላቸው:: እርሳቸውም "መልአከ ሞት መጥቶ ወደ ፈጣሪ በወሰደኝ ጊዜ 'የት አግኝተህ አመጣኸው?' ሲባል ከአትሮንስ ሥር ቁጭ ብሎ የአንተን ቃል ሲሰማ አገኘሁት ብሎ እንዲነግርልኝ ነው" አሉ::

መልአከ ሞት አሁን በዚህ ሰሞን መጥቶ ቢወስድህ ምን ሲያደርግ አገኘሁት የሚል ይመስልሃል? ሲጸልይ? ሲመጸውት? ሲመርቅ? ሰዎችን በፍቅር ቃል ሲናገር? ሲያማ? ሲሳደብ? ሲያስታርቅ? ሲያጣላ? እውነትም የእኚህ አባት ጭንቀት እጅግ ተገቢ ጭንቀት ነበር::

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን "እስከ መጨረሻይቱ ሕቅታ ድረስ አንድነት ሦስትነትህን በማመን አጽናን" ብላ በቅዳሴዋ የምትጸልየው በሞት የምወሰድበት ወቅት ምናልባትም ክፉ የምንሠራበትና ፈጣሪን የምንክድበት ጊዜ እንዳይሆን ነው:: "ሽሽታችሁ በክረምትና በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ" እንዲል እንደ ክረምትና ሰንበት ሥራ አቁመን ከበጎ ምግባር በራቅንበትና በሰነፍንበት ሰዓት እንዳንሞት እንጸልያለን::

ሌላው ቅዱስ አባት ነባቤ መለኮት ቅዱስ ጎርጎርዮስ ደግሞ ከሞቱ በኃላ ስለሚከሰተው የመጀመሪያ ክስተት ሲናገር
"ስሞት ዓይኔን በጣቶቹ የሚከድልኝ ማን ይሆን?" (Who will lay his fingers upon my eyes when I die?) ብሎአል:: (On His own life 43)

ምናልባት "ስሞት ዓይኔን ማንስ ቢከድነው ምን ለውጥ አለው?" ብለን እናስብ ይሆናል:: ሆኖም የመጨረሻዋን ቅጽበት የዓይናችን መከደን ጉዳይና የሚከድነው ሰው ማንነት ትልቅ ዋጋ ያለው ነው::

እግዚአብሔር በበጎነታቸው ለወደዳቸው ቅዱሳን ከሚመርቀው ምርቃት አንዱ "ልጆችህ ዓይንህን ይከድናሉ" የሚል ነበር::

ያዕቆብን እንዲህ ሲል መረቀው
"ወደ ግብፅ አብሬህ እወርዳለሁ : ከዚያም አወጣሃለሁ
ልጅህ ዮሴፍም እጁን በዓይኖችህ ላይ ያኖራል"
ዘፍ 46:4

የምንወደውን ሰው ዓይን ከድኖ መሰናበት "ሲቀብር ይቆርጥለታል" ከሚባለው ልማዳዊ ብሂል በላይ ፍጹም ዕረፍት የሚሰጥ ስንብት ነው:: ምንም ስቃዩና ኀዘኑ ጥልቅ ቢሆንም የመጨረሻዋን ሕቅታ ሰምቶ የምንወደውን ሰው ዓይን ከድኖ የመሸኘትን ያህል የሕሊና ዕረፍት የለም::

ለአባት "ልጆችህ ዓይንህን ይከድናሉ" መባል ምርቃት የመሆኑን ያህል ለወላጆች የልጅን ዓይን መክደን ግን እጅግ ከባድ ኀዘን ነው:: ሆኖም ምንም ኀዘኑ ጥልቅ ቢሆን ልጅን ዓይን ከድኖ መሰናበት ኀዘንን የሚያቀልል ስንብት ነው:: ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በአንድ ልጃቸው ሞቶ በኀዘን በተሰበሩ ወላጆች ቤት ገብቶ ይህንን የማጽናኛ ቃል ተናግሮ ነበር :-
"ጻድቁ ኢዮብ የልጆቹን ዓይን ለመክደንና አፋቸውን ለመግጠም ሰውነታቸውንም ለማስተካከል እንክዋን አልታደለም ነበር:: እናንተ ግን ቢያንስ የልጃችሁን የመጨረሻ ቃል ሰምታችኃል ዓይኖቹንም ከድናችኃል አፉንም ገጥማችኃል:: እናንተ ዐሥር ልጆቹን ካጣው ኢዮብ በላይ ስለምን ታዝናላችሁ?"

ቅዱስ ጎርጎርዮስ "ዓይኔን የሚከድንልኝ ማን ይሆን?" አለ:: ይህንን አስበነው እናውቅ ይሆን? ማን እንዲሸኘን እናስብ ይሆን? ቅድስት መቅሪና ስትሞት ወንድምዋ ጎርጎርዮስ ዓይንዋን እንዲከድንላት ትመኝ ነበር:: ሆኖም በሞተችበት ዕለት ሳትሞት በፊት በወሰዳት እንቅልፍ ምክንያት ዓይንዋ ተከድኖ ነበር:: (St.Gregory of Nyssa, On the life of St Makrina)

ቅዱስ ፍላብያኖስ ዘአንጾኪያም እኅቱ ዓይንዋን እንዲከድንላት ስትመኝ ኖራ በሞተች ዕለት እርሱ ለጸሎት ወደ ቁስጥንጥንያ ሔዶ እንደነበረ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ተናግሮአል::

ለአንዳንድ ቅዱሳን ደግሞ ማን መጥቶ ዓይናቸውን እንደሚከድን አስቀድሞ ፈጣሪ ይገልጥላቸው ነበር:: ከሃያኛው ክፍለ ዘመን ቅዱሳን አንዱ የሆኑት ፓትርያርክ ቅዱስ ቄርሎስ ሳድሳዊ ለአንድ ወጣት ጦቢት የሚል ቅጽል ስም አውጥተው ይጠሩት ነበር:: ለምን ጦቢት እንደሚሉት ባያውቅም ስሙን ግን አውቆ በጠሩት ቁጥር አቤት ይል ነበር:: ፓትርያርኩ በሞቱበት ዕለት ይህ ወጣት እግር ጥሎት ቀድሞ የደረሰው እርሱ ነበር:: ዓይናቸውን የከደነና አፋቸውን የገጠመው የዕረፍታቸውን ዜናም ለሌሎች ያሳወቀው ቀብሩንም ያስፈጸመው እርሱ ነበር:: ይህ ከሆነ በኁዋላ "ጦቢት" ብለው የሚጠሩበትን ምክንያት አስታውሶ መጽሐፈ ጦቢትን ሲያነብ ይህንን ጥቅስ አገኘ :-
"ጦቢትም እንዲህ አለ :- በነነዌ አደባባይ የሞተ ሰው ሳገኝ እቀብረው ነበር" ጦቢ 1:4
ጻድቁ ይህ ወጣት እንደሚቀብራቸው አውቀው ራሱን ለአደጋ አጋልጦ ድሆችን ይቀብር በነበረው በጦቢት ስም ይጠሩት ነበር::
እኔና አንተ ግን የማናውቅ ስለሆንን እንዲህ እንላለን
"ስሞት ዓይኔን የሚከድንልኝ ማን ይሆን?"

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ታኅሣሥ 29 2012 ዓ ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ዘንድ ጸልዩ! ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like እና Share ያድርጉ
FB: https://www.facebook.com/officialHenokhaile/
Telegram: https://t.me/deaconhenokhaile
Instagram: https://www.instagram.com/p/CBnMF0nnhcQ/?igshid=549jvl607bv4
Youtube: https://www.youtube.com/channel/UCOaVsWC05aUjeqIEW3fWj7g

25/11/2020

+ ሁለቴ የወጣ ስም +

መቼም ባል ሚስቱን የሚጠራበት ስም ቁጥሩ ባይበዛ እንኳን ቢያንስ ሁለት ስም መሆኑ አይቀርም፡፡ የመጀመሪያው ስም ያው ስትወለድ በወላጆችዋ የወጣላት ስም ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ወደ ትዳር ገብተው ሦስት ጉልቻ ሠርተው የፍቅርን እሳት ‘እፍ ሲሉ’ ፍቅሩን ለመግለጽ የሚጠራበት ስም ማውጣቱ አይቀርም፡፡ ፍቅራቸው በጸና መጠን ታዲያ የሚጠራበት ስም ሁሉ አልበቃት አልመጥናት እያለ ይቸገራል፡፡ ‘አካሌ’ ‘እናቴ’ ‘እኅቴ’ ‘ውዴ’ ወዘተ ይላታል፡፡ በፍቅር መካከል ጠብ አይቀርምና ደግሞ ሲጣሉ የሚጠራበት ስም በፊት ለፊትም በጀርባም መቀየሩ አይቀርም፡፡

አዳምና ሔዋን የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ናቸው፡፡ ከእርሱ አካል በመገኘትዋ ‘አካሌ’ ፤ አብረው በመፈጠራቸው ‘እኅቴ’ ፤ ከጎኑ ተወስዳ በመገኘትዋ ሕመሜ ፣ እርሱ በተኛ ሰዓት በመፈጠርዋ ሕልሜ ሊላት የሚገባ ብቸኛዋ ረዳቱ እርስዋ ነበረች፡፡ ረዳቱ ናት ሲባል አገልጋዩ ናት ማለት አለመሆኑን ‘እግዚአብሔር ረዳቴ ነው’’ የምንልበት የዳዊት መዝሙር ምስክር ነው፡፡ አዳም እርስዋን ባየ ጊዜ ደስ ብሎት ወደዳት፡፡ ስለዚህም የመጀመሪያውን ስም አወጣላት፡፡ ‘ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል’ አለ፡፡

በእርግጥ ሴት የሚለው ስም አሁን እርስዋን በጾታ ለሚመስሉ ሁሉ መጠሪያ ነው፡፡ በዓለም ላይ አንዲት ሴት ብቻ በነበረችበት ሰዓት ግን ሴት ስም ነበር፡፡ እንደ ዕብራይስጡ ከሆነ እንዲያውም ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል የሚለው ዐረፍተ ነገር ‘ከ‘Ishah’ ተገኝታለችና ‘Ish’ ትባል’ የሚል ሲሆን ከጾታ ይልቅ ሴት የወንድ አካል መሆንዋን በቃላቱ ድምፀትም የሚያጎላ ስም ነበር፡፡

ይህች ሴት ግን ለአዳም ውድቀት መነሻ የሆነ መታለልን ተታለለች፡፡ ሰይጣን በዕባብ ሥጋ ተሰውሮ ያለውን ሰምታ አምና ተቀበለች፡፡ ‘ከዛፉ ብትበሉ ዓይናችሁ ይከፈታል ክፉና መልካሙን ታውቃላችሁ’’ የሚለውን የዕባብ ምክር ያለ ጥርጣሬ ሰማች’’ እንደ ጎመን እርሻ የዘሩባትን የምታበቅል የዋሂት ሆና ነው እንጂ ‘ዛፍ ተበልቶ አምላክ መሆን ከተቻለ ምነው አንተ በልተህ አልሆንህም?’ ብላ በጥያቄ ማፋጠጥ በቻለች ነበር፡፡

ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ እንዲህ ይላል፦ ‘ዕባብ ‘ከዛፉ ብትበሉ ዓይናችሁ ይከፈታል ፣ ክፉና መልካሙን ታውቃላችሁ’ ሲላት ‘ቀድሞውኑ ያልተዘጋ ዓይኔ እንዴት ሊከፈት ይችላል ትለኛለህ? ዓይኖቼ ካልተከፈቱ አንተን እንዴት ለማየት ቻልሁ? የማያቸው ነገሮች ሁሉስ እንዴት ሊታዩኝ ቻሉ? መልካሙንና ክፉን መለየት የማልችል ከሆንሁ የአንተስ ምክር ክፉ ይሁን ደግ በምን አውቃለሁ?’ አላለችም፡፡ ባሪያ ነህ ነጻ? ሰማያዊ መልአክ ነህ ወይንስ አውሬ? አላለችም’ አምና ተቀበለች እንጂ’’ ይላል፡፡ እናም ከዛፉ ፍሬ እርስዋ በልታ ባልዋንም አበላችው፡፡ ሁለቱም ጸጋቸው ተገፈፈ፡፡ በዚህ ምክን ያት በባልና ሚስቱ ላይ ታላቅ እርግማን ወረደባቸው፡፡ በእርስዋ ላይ ምጥና መከራን ፣ በአዳም ላይ ደግሞ የተረገመ መሬት ገበሬነትን ፈረደበት ፣ ‘አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ’ የሚል ከባድ ርግማንን ፈረደበት፡፡ ሁለቱም ከገነት ተባረሩ፡፡

እስቲ ሁኔታውን ልብ እንበለው! አብረው ከገነት ሲወጡ አዳም ሚስቱን እንዴት የሚያናግራት ይመስላችኋል? በዚህ ዘመን በሚስቱ ምክንያት እንደ ገነት ካለ ቦታና ክብር የተዋረደ ባል ሚስቱን እንዴት ብሎ የሚያናግራት ይመስላችኋል? እንደቀድሞው ‘አካሌ ሥጋዬ አጥንቴ’ ይላት ይሆን? በፍጹም አያደርገውም! ካልገደልሁ ካላለም ተመስገን ነው! በእርግጠኝነት ይጣላሉ፡፡ ሚስቱን እንኳን በስምዋ ሊጠራት ከተባረረበት ገነት ብዙ ሳይርቅ እዚያው ሲኦል መፍጠሩ አይቀርም፡፡ አዳም ግን ያደረገው ለማመን የሚከብድ ነገር ነበር፡፡

ክብሩን አጥቶ ፣ ከፈጣሪው ተጣልቶ ፣ እርግማኑን ሰምቶ ፣ ጸጋውን ተነሥቶ ከእርስዋ ጋር ሲወጣ የመጀመሪያ ሥራው ለሚስቱ ስም ማውጣት ነበረ፡፡ ‘ሴት ትባል’ ብሎ ያወጣላትን ስም ቀይሮ በአዲስ ስም ሊጠራት ወሰነ፡፡ ከነበረበት ሁኔታ አንጻር ኀዘን የተቀላቀለበት ፣ ቂም ያዘለ ፣ ወቀሳ ያረገዘ ስም ቢያወጣ ትርጉም ይሠጥ ነበር፡፡ አዳም ግን ለሚስቱ ያወጣው ስም በፍቅር የሚነድዱ አዲስ ሙሽሮች የሚጠራሩበት የሚመስል ስም ነበር፡፡ ሚስቱን ያላት ሕይወቴ ፤ የሕይወትም ሁሉ እናት! ነው፡፡

ሞት አከናንባው እየወጣ ሕይወት ብሎ መጥራት እንዴት ያለ ነው? ‘ረዳት ትሁንህ ብለህ የሰጠኸኝ ሴት ከዛፉ ሠጠችኝና በላሁ’’ የሚለው ክስ የት ሔዶ ነው? ካላችሁ አዳም የሚናገረው አጠገቡ ስላለችው ሔዋን ሳይሆን ደግማ ስለምትወልደውና ሕይወትን ወልዳ ስለምሠጠው ስለ ሁለተኛዋ ሔዋን ስለ ድንግል ማርያም ነበር፡፡ ስለዚህ ‘አዳም እመቤታችን ማርያም ከእርሱ አብራክ እንድትከፈል ከሔዋንም ማኅፀን እንድትወለድ አውቆ ሔዋንን ሕይወቴ ነሽ ይላት ነበር’ እንዲል /መቅድመ ተአምረ ማርያም/

ሕይወቴ / የሕያዋን ሁሉም እናት ያላት ሁለተኛይቱ ሔዋን ድንግል ማርያም ናት፡፡ ይህችኛዋ ሔዋን የተለየች ሔዋን ናት፡፡ ሞትን ያመጣች ሳትሆን ሕይወትን የወለደች ሔዋን ፣ ከአዳም የተገኘች ሳይሆን አዳምን ያስገኘች ሔዋን ፣ አዳም ስም ያወጣላት ሳትሆን ለሁለተኛው አዳም ‘ኢየሱስ’ ብላ ስም ያወጣች ሔዋን ፣ ከአዳም ሥጋን የወሰደች ሳትሆን አዳም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነሥቶ የተገኘባት ሔዋን ናት፡፡

ይህች ሔዋን የዚያችኛዋ ሔዋን መድኃኒት የሆነች ሔዋን ናት፡፡ በምጥ ትወልጃለሽ የተባለች ሳትሆን ሳታምጥ የወለደች ሔዋን ፣ አዝዛለሁ ብላ ታዛዥነት የተፈረደባትና ‘ፈቃድሽ ወደ አዳም ይሆናል’ የተባለችዋ ሔዋን ሳትሆን ‘እነሆኝ ባሪያው’ ብላ ልትታዝ ቀርባ ሁለተኛው አዳም ‘ይታዘዛት ነበር’ የተባለላት ሔዋን ናት፡፡ ያችኛዋ ሔዋን በዕፀ በለስ ዛፍ ላይ የተሰቀለውን የዛፉን ፍሬ አይታ የተመኘች በልታ ባልዋን ያበላች ፣ ዕርቃን ሆና ባልዋንም ዕርቃን ያደረገች ሔዋን ነበረች፡፡ ይህችኛይቱ ሔዋን ድንግል ማርያም ግን በመስቀሉ ዛፍ ላይ የተሰቀለውን የማኅፀንዋን ፍሬ መልካም እንደሆነ አይታ ለእርሱ ሆድዋን ማደሪያ አድርጋ ሠጥታ ለሁላችንም አበላችን፡፡ የሁላችንም ዓይኖች ያን ጊዜ ተከፈቱ ፣ ያን ጊዜም ዕርቃናችንን እንዳልሆንን አወቅን ፤ የተጠመቅን ሁላችን ልጅዋን ለበሰናልና ቅጠል ሰፍቶ ማገልደም አላስፈለገንም፡፡

የቀደመችዋን ሔዋን የገዛ ባልዋ አዳም በፈጣሪ ፊት ‘‘ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት እርስዋ ከዛፉ ሠጠችኝና በላሁ’’ ብሎ ከስሷት ነበር፡፡ እኛ ግን ስለ ድንግል ማርያም ምንም ክስ የለንም:: ስለእርስዋም እግዚአብሔርን እንዲህ ስንል እናመሰግነዋለን ‘ከእኛ ጋር እንድትሆን ‘እነኋት’ ብለህ የሰጠኸን ሴት የማኅፀንዋን ፍሬ አንተን ሠጠችንና በላን ፤ ከዕጸ ሕይወትም እንበላ ዘንድ አደልከን ይኸውም የከበረ ሥጋና ደምህ ነው’’ እያልን እናመሰግነዋለን፡፡ እኛ ግን ሁለተኛዪቱን ሔዋን ድንግል ማርያምን እንኳን እንደ ቀደመችው ሔዋን ልንወቅሳት ይቅርና እንዲህ አመስግነናትም አንጠግብም፡-

‘‘እንደ እመቤታችን ማርያም የአብ ማረፊያ የሆነ ማን ነው? እንደ እመቤታችን ማርያም የወልድ ማደሪያ የሆነ ማን ነው? እንደ እመቤታችን ማርያም የመንፈስ ቅዱስ ንጹሕ አዳራሽ የሆነ ማን ነው? ለሰው ኃጢአት ሳይሠራ መኖር ይቻለዋልን? ... እመቤታችን ማርያም ንጽሕት በመሆንዋ አምላክ እንዲያድርባት አደረገችው ...

እመቤታችን ማርያም ከአዳም ጀምሮ በነቢያት ትነገር ነበር ... አዳም እመቤታችን ማርያም ከእርሱ አብራክ እንድትከፈል ከሔዋንም ማኅፀን እንድትወለድ አውቆ ሔዋንን ሕይወቴ ነሽ ይላት ነበር .. የሔዋን የሚጎዳ ማሠሪያዋ በአንቺ የተቆረጠላት እመቤቴ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ ... እግዚአብሔር በብሩሕ ደመና ተጭኖ በማኅፀንሽ ያደረ እመቤቴ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ ... እኔ ለምእመናን ወንጌልን የማስተምርለት የጌታዬ እናቱ እመቤቴ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ ... እኛ ከምንወደው እርሱም ከሚወድደን ከልጅሽ ዘንድ ኃጢአታችንን ያስተሰርይልን ዘንድ ለምኚልን’ /መቅድመ ተአምረ ማርያም/

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጥር 21 2012 ዓ ም
አቃቂ ፤ አዲስ አበባ
ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ!

ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like, Subscribe እና Share ያድርጉ :-

የፌስቡክ ገጽ :- https://www.facebook.com/officialHenokhaile/
የቴሌግራም ቻናል : https://t.me/deaconhenokhaile
የዩቲዩብ ገጽ: https://www.youtube.com/channel/UCOaVsWC05aUjeqIEW3fWj7g

20/01/2020

Address

Addis
Addis Ababa
0001

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Tewahido Haymanote ተዋህዶ ሃይማኖቴ posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share