የቅድስት ድንግል ማርያም ልጆች

የቅድስት ድንግል ማርያም ልጆች *የድንግል ማርያም የአስራት ልጆች ሰላማቹህ ይብዛ *

♡†♡
ድንግል እመቤቴ ማርያም ሆይ ባማረ በተወደደ ነገር ሁሉ መሰልሁሽ ምስጋናሽን ግን ለመፈፀም አልቻልኩም፡፡እግዚአብሔርን ባመሰገንሁ ጊዜ ባንቺ ለስሙ ምስጋና አቀርባለሁ ፤ በስምሽም ፀሎቴን በፀለይሁ ጊዜ ፀሎቴን ለልጅሽ አቀረብሁ፤ዳግመኛም ውዳሴሽን ወደማወቅ ባህር ልዋኝ ወደድሁ ፡ ወደ ክብርሽ ገናንነት ወደብ እደርስ ዘንድ ደከምሁ ፡ ያንዲቷን ማእበል ሞገድ ያህል ስንኳን አላለፍሁም፡፡ ወደ ፅርሀ አርያም ጠፈር ለመድረስ የሚቻለው ማነው? ከምድር በታች ወዳለው ባህር መሰረትስ መዋኘት ማን ይችላል? ድንግል ሆይ ክብርሽን ገናንነትሽን ጠንቅቆ መናገር የሚቻለው ማነው?
ድንግል ማርያም ሆይ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን አ

ሜን።
†♥†
ድንግል እመቤቴ ማርያም ሆይ ከፀሎትሽ ረዳትነት በቀር ሊረዳኝ የሚችል እንደሌለ አወቅሁ፡፡ ከልመናሽም በቀር የሚያድን እንደሌለ ያለበኩርሽም የሚበጀኝ እንደሌለ አወቅሁ፡፡ ድንግል እመቤቴ ሆይ ፦ ወዳንቺ ተጠጋሁ በልጅሽም አመንሁ እርሱንም አመለክሁ ቸርነቱንም ተስፋ አደረግሁ፡፡
♥†♥
በእብራይስጥ ማሪሃም የተባልሽ እመቤታችን ድንግል ማርያም ሆይ ሁሉ ላንቺ ሆነ ፡ ሁሉም ስላንቺ ተፈጠረ ፤አዳም ከህቱም ምድር ተፈጠረ አንቺን ያፈራ ዘንድ ነው ። ሔዋንም ከአዳም ከግራ ጎኑ ተፈጠረች አንቺን ትወልድ ዘንድ ፤ ምድርም ተፈጠረች አዳም አባትሽን ታስገኝ ዘንድ ፡፡ ለምግቡም ቡቃያውን ታወጣ ዘንድ ሰማይም ስለርሱ ተሰቀለ ፤ ፀሃይና ጨረቃም ከዋክብትም እንዲያበሩለት በመውጣትና በመግባታቸው የዘመኑ ቁጥር እንዲታወቅ ተፈጠረ ፤ መላእክትም እንዲያገለግሉት ተፈጠሩ ፤ ድንግል ሆይ ክብርሽን ገናንነትሽን ለመናገር የሚቻለው ማነው? ምስጋናሽን መናገር ማን ይችላል? ድንግል ማርያም ሆይ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን አሜን።

28/05/2026

🥰❤

❤🙏❤
24/08/2024

❤🙏❤

*ቀዳም_ሥዑር (የተሻረች ቅዳሜ)*_*🌿ቀዳም_ሥዑር ይባላል፡-*__♦በዚች ዕለች ከድሮው በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረችው ቅዳሜ ትባላለች፡፡ የማትጾመዋ...
04/05/2024

*ቀዳም_ሥዑር (የተሻረች ቅዳሜ)*

_*🌿ቀዳም_ሥዑር ይባላል፡-*_

_♦በዚች ዕለች ከድሮው በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረችው ቅዳሜ ትባላለች፡፡ የማትጾመዋ ቅዳሜ ስለምትጾም ስዑር /የተሻረች/ ተብላለች በዓል መሻርን አይመለከትም በቀዳም ሥዑር ሌሊት ሥርዓቱ የሚጀመረው በመኀልየ ሰሎሞን ምንባብ ነው፡፡ ማኀሌቱም እዝሉ እየተቃኘ እየተመጠነ፣ እየተዘመመ እየተመረገደ እየተጸፋ ያድራል፡፡ ጥዋት አቡን መዋሥዕት ውዳሴ ማርያም ዜማ ተደርሶ ወለመልአከ ሕይወትሰ ሰቀልዎ በሚለው ሰላም ይጠናቀቃል፡፡በዚህ ዕለት ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲያቆናት ቄጤማ ተሸክመው ቃጭል ሲያቃጨሉ መታየታቸው ዕለተ ትንሣኤውን ለሚናፍቅ ምእመን ትልቅ ብስራት ነው፡፡_

_*🌿ለምለም_ቅዳሜ ይባላል፡-*_

_♦ካህናቱ ለምእመናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት ስለሆነ በዚህ ተሰይሟል፡፡ ቀጤማውንም ምእመናን እስከ ትንሣኤ ሌሊት በራሳቸው ላይ ያስሩታል፡፡ በቀዳም ስዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለዓዋዲ/ እየመቱ ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሃደ የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር፤ ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደሰጠን እና ትንሣኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር፤ ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመናኑም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ፡፡ ቄጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሠሩበትን ድርጊት የሚያስታውስ ነው፡፡_

_♦(የቀጤማው አመጣጥና ምስጢርም ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ምድር በማየ አይኅ /በጥፋት ውኃ/ በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሰረችው ቀጤማ ይዛ በመግባት ነው፡፡ ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች የኃጢአት ውኃ ጐደለ፣ የኃጢአት ውኃ ጠፋ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻነት ተሰበከ ታወጀ በማለት ካህናት ቄጠማ ይዘው ምእመናንን ያበሥሩበታል፡፡)_

_*🌿ቅዱስ_ቅዳሜ ይባላል፡-*_

_♦ቅዱስ ቅዳሜ መባሉ ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ በዚህ ቀን ከሥራው ሁሉ ያረፈበት ነው፡፡ በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ሥራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ፣ በነፍሱ ሲዖልን በርብሮ ባዶዋን አስቀርቷታል፡፡ በዚያ ለነበሩት ነፍሳትም የዘለዓለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ከሌሎቹ ዕለታት የተለየ ዕለት ለማለት ቅዱስ ቅዳሜ ተብሏል፡፡_

_*(ስምዐ ተዋሕዶ የስምዐ ጽድቅ ልዩ እትም ዘሰሙነ ሕማማት*_

ታኅሣሥ 3አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ታኅሣሥ ሦስት በዚህች ቀን አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ነው፣ የሊቀ መላ...
13/12/2023

ታኅሣሥ 3

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ታኅሣሥ ሦስት በዚህች ቀን አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ነው፣ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ፋኑኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፣ የጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ ዕረፍታቸው ነው።

በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም

ታኅሣሥ ሦስት በዚህች ቀን አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሦስት ዓመት ሲሆናት ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ነው ። እርሷ ለእግዚአብሔር የስእለት ልጅ ነበረችና።

እናቷ ቅድስት ሐና ልጅ የሌላት ስለሆነች በቤተ እግዚአብሔር ውስጥ ከሴቶች ተለይታ ርቃ ትኖር ነበር ሽማግሌ ከሆነ ከኢያቄም ከባሏ ጋርም እጅግ የምታዝን ሆነች ። እግዚአብሔርም ኀዘናቸውን ሰማ ቅድስት ሐናም እንዲህ ብላ ለእግዚአብሔር ተሳለች የሰጠህኝን ፍሬ ለእግዚአብሔር አገልጋይ አደርገዋለሁ ።

ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያምንም በወለደቻት ጊዜ ሦስት ዓመት በቤቷ ውስጥ አሳደገቻት ከዚህም በኋላ ከደናግል ጋር ትኖር ዘንድ ወደ ቤተ መቅደስ ወሰደቻት በቤተ መቅደስም ምግቧን ከመላእክት እጅ እየተቀበለች ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረች ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም መጥቶ ከእርሷ ሥጋን እስከ ነሣ ድረስ።

ከሴቶች ሁሉ የተመረጠች ይቺ ናት በቤተ መቅደስም በመኖር ዐሥራ ሁለት ዓመት ሲፈጸምላት እርሷ ለእግዚአብሔር የተሰጠች የስዕለት ልጅ ናትና ለሚጠብቃት ይሰጧት ዘንድ ካህናት እርስበርሳቸው ተማከሩ በሴቶች ላይ የሚደርስ በርሷ ላይም ይደርስባታል ብለው ስለፈሩ በቤተ መቅደስ ውስጥ ይተዋት ዘንድ ለእርሱ ትክክል መስሎ አልታያቸውም ስለዚህም ሊጠብቃት ለሚገባው በእርሷ ላይ እጮኛ ሊአኖሩ ወደዱ።

ከዚህም አስቀድሞ ሊቀ ካህናት ዘካርያስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ልጄ ማርያም ሆይ አንቺ እንዳደግሽና ለአካለ መጠን እንደደረስሽ ዕወቂ ልትታጪ ትወጃለሽን እግዚአብሔርን የሚፈራ መልካም የሆነ የተባረከ ጐልማሳ እንፈልግልሽን ወይም በሕይወትሽ ዘመን ሁሉ በቤተ መቅደስ ተቀምጠሽ እግዚአብሔርን ልታገለግዪው የምትሺ ከሆነ በሴቶች ላይ የሚደርሰው በሚደርስብሽ ወራት ወደ ቤተ መቅደስ ደጅ ከመግባት ትጠበቂ ዘንድ በኦሪቱ የተጸፈውን የርግማን ሥርዓት በአንቺ ላይ እንሠራለን አላት ።

ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያምም እነሆ እኔ የእግዚአብሔር አገልጋዩ በፊታችሁ ነኝ አባትና እናት የሉኝም ስሙ ቡሩክ ምስጉን ከሆነ ከእግዚአብሔር በታች በእናትና አባት ፈንታ እናንት ናችሁና የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንደምታውቁ አድርጉ ብላ መለሰች።

ካህናቱና ማኅበሩም ሁሉ ዘካርያስን ወደ ቤተ መቅደስ ገብተህ ስለዚች ብላቴና ማርያም ወደ እግዚአብሔር ጸልይ አሉት ዘካርያስም ገብቶ ሲጸልይ በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና እንዲህ አለው። ዘካርያስ ሆይ ወጥተህ ከዳዊት ወገን ሚስቶቻቸው የሞቱባቸውን ሁሉ ወንዶች ሰብስብ የየአንዳንዱንም በትር ከስሙ ጋር ውሰድ ወደ ቤተ መቅደስም በምሽት አግብተህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይበት በነጋ ጊዜም በትሮቻቸውን አውጣ እግዚአብሔርም በበትሩ ላይ ምልክት ለገለጠልህ ለዚያ ሰው ማርያምን ተቀብሎ ሊጠብቃት ይገባዋል።

ካህኑ ዘካርያስም ወጥቶ አንድነት ለተሰበሰቡት ሕዝብ የእግዚአብሔር መልአክ የነገረውን ነገራቸው በዚያንም ጊዜ ከዳዊት ወገን ጐልማሳም ቢሆን ሽማግሌም ቢሆን ሚስቱ የሞተችበት ሁሉ በኢየሩሳሌም ወደአለ ቤተ መቅደስ ይሒድ እያሉ ዓዋጅን ዙረው የሚናገሩ በእስራኤል አገር ሁሉ ላከ ።

ከዳዊት ወገን የሆነ ጠራቢው ዮሴፍም በሰማ ጊዜ በትሩን ይዞ ከናዝሬት ወደ ኢየሩሳሌም ሔደ ካህኑ ዘካርያስም የሁሉንም በትሮች ተቀብሎ ስማቸውን በላያቸው ጻፈ ቁጥራቸውም አንድ ሽህ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ አምስት ሆነ ዘካርያስም በትሮችን ወደ ቤተ መቅደስ አስገብቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ እንዲሁም ሰዎች ሁሉ ከቤተ መቅደስ ውጭ ቁመው ይጸልዩ ነበር ዘካርያስም ጸሎቱን በፈፀመ ጊዜ ለየአንዳንዱ በትራቸውን አውጥቶ ሰጠ ጠራቢው ዮሴፍም በትሩን ሊቀበል በቀረበ ጊዜ ከእርሷ ነጭ ርግብ የመሰለች ተገለጠች እየበረረችም ሒዳ በጠራቢው ዮሴፍ ራስ ላይ ተቀመጠች ካህናቱና ሕዝቡ ሁሉ አይተው እጅግ አደነቁ ምስጉን የሆነ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።

ዘካርያስም ዮሴፍን ዮሴፍ ሆይ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ እንደ ተናገረ ድንግል ማርያምን ወደ ቤትህ ወስደህ ጠብቃት አለው ዮሴፍም ቅድስት ድንግል ማርያምን ከካህናት እጅ ተቀበላት በእርሱም ዘንድ ኖረች ። ከዚህም በኋላ የመላእክት አለቃ ገብርኤል ስለ እግዚአብሔር ልጅ ከእርሷ ሰው ሁኖ ስለመወለዱ በዮሴፍ ቤት አበሠራት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

💒  ዘወረደ)፤ የአቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት⬇⬇⬇⬇⬇⬇⬇⬇⬇⬇⬇⬇የአብይ ጾም ሳምንታት 8 ናቸው፤1.     ዘወረደ2.    ቅድስት3.    ምኩራብ4.    መጻጉዕ5.    ደብረዘይት6.    ...
08/03/2021

💒
ዘወረደ)፤ የአቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት
⬇⬇⬇⬇⬇⬇⬇⬇⬇⬇⬇⬇

የአብይ ጾም ሳምንታት 8 ናቸው፤

1. ዘወረደ

2. ቅድስት

3. ምኩራብ

4. መጻጉዕ

5. ደብረዘይት

6. ገብርሔር

7. ኒቆዲሞስ

8. ሆሣዕና

ስያሜአቸውና ትርጉማቸውም ፤

የአቢይ ጾም ሦስቱ ክፍሎች

1. ዘወረደ (ጾመ ሕርቃል)፤ ይህም ጾሙ ከሚገባበት ሰኞ ጀምሮ እስከ እሑድ ድረስ ያለው 7 ቀን ነው።

2. የጌታ ጾም፤ ይህም ከቅድስት ሰኞ እስከ ሆሣዕና ዋዜማ ዓርብ ድረስ ያለው 40 ቀን ነው።

3. ሕማማት፤ ይህም ጌታችን በአልዓዛር ቤት ለማዕድ ከተቀመጠበት የሆሳዕና ቅዳሜ ጀምሮ እስከ ሥዑር ቅዳሜ ያለው መከራን የተቀበለበት 8 ቀን ሕማማት ነው።

ይህም 7+40+8 = 55 ቀን ማለት ነው።

«ዘወረደ» ማለት «የወረደ» ማለት ነው፡፡ አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰው አምላክ ሆነ ማለት ነው። ይህም ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስክርስቶስ እኛን ለማዳንና ፍቅሩን ሊገልጽልንከሰማያት መውረዱን ከድንግል ማርያም የእኛን ሥጋ መዋሐዱን የሚዘክር፤ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን የሚያመላክት፣ የሚታወስበት፣የሚነገርበት የዐቢይ ጾም አንደኛው ሳምንት ነው፡፡ዮሐ.3-13፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም በገባዉ ቃልኪዳን መሰረት “ የዘመኑፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ልጁን ላከ” እንዳለ ሐዋርያዉቅዱስ ጳዉሎስ የጠፋዉን አዳም ፍለጋ ከአባቱእሪና ሳይጎድል ሳይለይ ከሰማይ መዉረዱን የምናዘክርበት በዓል ነዉ። ይህ ጾም የጾምመግቢያ የመጀመሪያ ሳምንት የምንጾመው ጾም ሲሆን ሕርቃል የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም“ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ (አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ አመት ሲፈፀም) ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅየ አድንኃለሁ” ብሎ ለአዳም ቃል ገባለት ፡፡ ዘፍ. ፫ ፥ ፲፭ ይህ ኪዳነ አዳም ይባላል ፡፡ የቃል ኪዳን ሁሉ መሠረት ነው ፡፡ ሁለቱን ኪዳናት (ብሉይ ወሐዲስ) በፅኑዕ ተስፋ ያስተሳሰረ የረጅም ዘመናት የድኅነት ሰንሰለት ነው ፡፡ ዘወረደ እርቀ አዳም ፤ ተስፋ አበው ፤ ትንቢተ ነቢያት ፤ ሱባኤ ካህናት መፈፀሙ ፤ ኪዳነ አዳም መሲህ መወለዱ የሚነገርበት የፍቅር አዋጅ ነው ፡፡

ዘወረደ ማለት?

▶️ የምስጢረ ሥጋዌ ትምህርት ነው

▶️ ዘወረደ ስንል አምላክ መጣ ፤

▶️ ወረደ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ ፤

▶️ በፍጹም ተዋሕዶ ሰው ሆነ ማለታችን ነው ፡፡

▶️ ዘወረደ በአምላክ ትህትና ክብረ አዳም የሚነገርበት ነው ፡፡

▶️ አምላክ ሰው በመሆኑ ሰው አምላክ ሆነ ፤ ከበረ ፤ ገነነ ፤ ነገሠ ፡፡

▶️ ሕያው አምላክ ክርስቶስ በቅድስት ሞቱ ሟቹን አዳም ዘላለማዊ ሕያው አደረገው ፡፡

▶️ አምላክ ወልደ አምላክ በመስቀል ላይ በፈቃዱ ሞቶ ለአዳም ያለውን ታላቅ ፍቅር ገለጸ ፡፡

▶️ የተጣላውን አዳምን በፈቃዱ ታረቀው፡፡

▶️ ጠላቶቹ ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን ፥ ይልቁንም ከታረቅን በኃላ በሕይወቱ እንድናለን ፡፡ ሮሜ. 5 ፥ ፲ ፡፡ በዚህም ትህትናን ፍቅርን አስተማረን ፡፡

የዲያብሎስን ሥራ ሊያፈርስ የተገለጠው የእግዚአብሔር ልጅም በፆም ድል ማድረግን ለእኛ አስተምሮናል። እኛም በዚህ በአብይ ፆም የለመነውና የጠየቅነው ነገር ሁሉ ከኃጢአት በስተቀር እንዲከናወንልን ፆምን ገንዘባችን እናድርግ።
- በፆም የተጠቀሙ ቅዱሳን አባቶችና ቅዱሳንእናቶች እንዳሉን እናስተውል። በተለይ አሁን በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰበሚታየው አስቸጋሪ ፈተና እያንዳንዳችን ልባዊ ፆም በመፆም ልዑል እግዚአብሔር የፀሎታችንን ምላሽ እንዲሰጠን እንማፀን።

ጾም ጸሎታችን የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይቀበልልን አሜን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር🙏🏽🙏🏽🙏🏽

ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከፍርድ ወደ ምሕረት፣ ከድቅድቅ ጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን ያሸጋግረን ዘንድ አምላክ ሰው ሆነ፡፡ ባሕርያችንን ተዋሕዶ በእኛ መልክ ተገለጠ፡፡ የተዘጋው የገነት በር ሊከፈት፣...
07/01/2021

ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከፍርድ ወደ ምሕረት፣ ከድቅድቅ ጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን ያሸጋግረን ዘንድ አምላክ ሰው ሆነ፡፡ ባሕርያችንን ተዋሕዶ በእኛ መልክ ተገለጠ፡፡ የተዘጋው የገነት በር ሊከፈት፣ የአዳም እርግማን ሊፋቅ፣ የዲያብሎስ መንግሥት ሊናወጥ፣ ምርኮና ብዝበዛ በወህኒው ሲኦል ሊሆን... ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ተወለደ...!

እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ...!

ቀና ሲሉ ----
ሰማዩ ሞት አርግዞ
የሞት ጭጋግ
ከአድማስ አድማስ ተንጠርዞ
ጎንበስ ቢሉ
ምድር በኃጢአት ተጀቡኖ
ፍጥረት በግፍ ተሸፍኖ
ቅዱስ በርኩስ ተኮንኖ
ዝብርቅርቁን የዓለም ጣጣ
አስተካካይ መላ ታጥቶ
ቤዛ ሆኖ የሚታደግ
ከሰው ወገን መድኅን ጠፍቶ...

ነቢያቱ አለቀሱ
የቤዛው ቀን ርቋቸው
ሰማያትን ቀደህ ብትወርድ
ምናለበት? አሰኛቸው
ና ተገለጥ አዶናይ ሆይ
አሁን አድን አሁን አቅና
የምሳሌህ ክቡር ፍጥረት
በኃጢአት ጦስ ጠፍቷልና
ክንድህን ላክ ኤልሻዳይ ሆይ
ፅድቅህ ይምጣ ከሰማያት
የአዳም ቀዬ ምድሪቷን
የግፍ ቁና አስጨነቃት
ሲሉ ጮሁ ቅዱሳኑ
የትንቢት ቃል የገባቸው
የአባታቸው የተሥፋ ቀን
ሩቅ ሆኖ ቢታያቸው
እንደ ሰይጣን ከንቱ ምኞት
ያ ብሩክ ቀን አልዘገየም
እንደ ሰው ልጅ መዳን ጉጉት
ያ ድንቅ ቀን አልቸኮለም
በዘመኑ በወራቱ
በዕለቱ በሰዓቱ
ቃል ተከብሮ ንግርት ሰምሮ
ሕፃን ታየ ከእነ እናቱ..!

ክብር ይሉት ሞገስ ዝና
በሰማይ ላይ ተወውና
በውርደቱ ፍርድ ሊያርቅ
ሰው ሊፈጥር እንደገና
ተገለጠ አማኑኤል
ከሰው ወገን እንደ ባሪያ
ጎጆ ቢጤ ማረፊያ አጥቶ
ተወለደ በማጎሪያ...!!!

እነሆ ከዋነኞቹ አለቆቹ አንዱሚካኤል ሊረዳኝ መጣ!!ትንቢተ ዳንኤል 10 ፤13እንኻን አደረሠን ቅዱስ ሚካኤል ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቀን🙏🙏🙏
22/09/2020

እነሆ ከዋነኞቹ አለቆቹ አንዱ
ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ!!
ትንቢተ ዳንኤል 10 ፤13
እንኻን አደረሠን ቅዱስ ሚካኤል
ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቀን🙏🙏🙏

✝️ ፯ ስላሴ ❤️                                  የቅድስት ስላሴ ቸርነት ና ምህረት ከሁላችን ጋር ይሁን! ለሃገራችን ሠላም ለህዝባችን ፍቅርን ይስጡልን።          ...
17/09/2020

✝️ ፯ ስላሴ ❤️
የቅድስት ስላሴ ቸርነት ና ምህረት ከሁላችን ጋር ይሁን! ለሃገራችን ሠላም ለህዝባችን ፍቅርን ይስጡልን። የአብርሃምን ቤት የባረኩ ስላሴ የእኛንም ቤት በበረከት
ይሙሉልን🤲🏻💚💛❤️🤲🏻

❖የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤና ዕርገት ነሐሴ 16✍ በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ ❤🍁ነሐሴ 16 ቀን አስደናቂውን የእመቤታችንን የዕርገቷን በዓል ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ...
21/08/2020

❖የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤና ዕርገት ነሐሴ 16
✍ በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
❤🍁ነሐሴ 16 ቀን አስደናቂውን የእመቤታችንን የዕርገቷን በዓል ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በታላቅ ድምቀት ታከብራለች፤ የቅድስት ድንግል ማርያም መላ ዕድሜዋ 64 ሲኾን ይኸውም በእናት ባባቷ ቤት 3 ዓመት፤ በቤተ መቅደስ 12 ዓመት፤ ጌታን ፀንሳ በቤተ ዮሴፍ 9ወር ከ5 ቀን፤ ከልጇ ጋር 33 ዓመት ከ3 ወር ከቆየች በኋላ፤ ዓለምን ለማዳን በዕለተ ዓርብ በመስቀል በተሰቀለ ጊዜም የሚወድዳት እናቱን ለሚወድደው ደቀ መዝሙር ለዮሐንስ “እነኋት እናትኽ” በማለት አደራ በመስጠት በዮሐንስ በኩል ለሚወድደን ለእኛ የአደራ ልጆቿ እንድንኾንና የአደራ እናታችን እንድትኾን ታላቅ ስጦታን በቀራንዮ በእግረ መስቀል ሥር ሰጠን (ዮሐ ፲፱፥፳፮‐፳፯)፡፡

❖✔ በዚኽም መሠረት ሐዋርያትም ከአምላካቸው የተሰጠቻቸው የአምላካቸውን እናት ይዘው ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስ ወርዶ 72ት ቋንቋ ገልጾላቸው ታላቅ መንፈሳዊ ኀይልን ሰጣቸው (የሐዋ 1፥14)፤ ዮሐንስም በእናትነት የተቀበላት ቅድስት ድንግል ማርያምን በቤቱ 15 ዓመት አኑሯታል፡፡

❖✔ በነገረ ማርያም በብራናው ላይ እንደተጻፈ 64 ዓመት ሲመላት ልጇ ክርስቶስ ለእናቱ ተገልጾ ከኀላፊው ዓለም ወደ ማያልፈው ሰማያዊዉ ዓለም ሊወስዳት እንደኾነ ነገራት፤ ርሷም ይኽነን ለሐዋርያት ነገረቻቸው፤ እነርሱም “አይቴ ተሐውሪ እግዝእትነ” (እመቤታችን ወዴት ትኼጃለሽ) ብለው ሲጠይቋት “ኀበ ጸውአኒ ወልድየ” (ልጄ ወደ ጠራኝ) በማለት ወደዚያኛው ዓለም የመኼጃዋ ጊዜ እንደደረሰ ነገረቻቸው፤ ይኽነን ሰምተው “ወበከዩ ኲሎሙ ሐዋርያት” ይላል ሐዋርያት በእጅጉ ዐዘኑ አለቀሱ፡፡ ያን ጊዜ ቅዱሳን መላእክት ተገልጸው ሐዋርያትን ማዕጠንታቸውን ይዘው ደስ አሰኝተው እንዲሸኝዋት እንጂ እንዳያዝኑ እንዳያለቅሱ በመንገር አረጋጓቸው፡፡

❖✔ ጌታም እናቱን “እኔ ኹሉን መጋቢ የኾንኹትን ያጠቡ ጡቶሽን የተባረኩ ናቸው፡፡ እንዲኹም በከፍታ ቦታዎች ወደሚገኙ ሰማያዊ ስፍራዎች ወስጄሽ በአባቴ በመልካም ነገሮች እመግብሻለኊ፡፡ እስከዚያው በጉልበትሽ ላይ ያስቀመጥሺኝ ድንግል እናቴ ማርያም ሆይ በኪሩቤል ሠረገላ ላይ በማኖር ከእኔና ከቸሩ አባቴ ጋር ወደ ሰማያት እወስድሻለኊ፡፡

❖✔ በመጠቅለያ ጨርቆች እንደጠቀለልሽኝ ኹሉ የእኔ ድንግል እናት ማርያም ሆይ በወለድሽኝ ዕለት በከብቶች በረት ከላም እና አህያ ጋር በአንድ ላይ ከብበውኝ እንዳኖርሽኝ ኹሉ (ኢሳ ፩፥፫፤ ሉቃ ፪፥፯)፤ እኔ ደግሞ ዛሬ ከእኔ ጋር ከሰማያት ባመጣዋቸው በሰማይ መጐናጸፊያ ሰውነትሽን እጠቀልለዋለኊ፤ ከዚያም ከሕይወት ዛፍ ሥር አስቀምጠዋለኊ፣ ኪሩቤልም በሰይፈ ነበልባላቸው እንዲጠብቁት አደርጋለኊ (ዘፍ ፫፥፳፬)፡፡

❖✔ የተባረከችውን ነፍስሽን የሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም መንበር በተሸፈነችበት መሸፈኛዎች እንድትሸፈን አደርጋለኊ፡፡ እኔን በሚያሳድድበት ጊዜ ሥርዓት አልባውን ሄሮድስ በመፍራት ወደ ግብጽ ምድር እንደተሰደድሽው ኹሉ (ማቴ ፪፥፲፫-፲፰)፤ መላእክቶቼ ኹልጊዜም በክንፎቻቸው እያጠሉብሽ እና መልካም ዝማሬያቸውን እንዲዘምሩልሽ አደርጋለኊ” አላት፡፡

❖✔ ይኽነንም ልጇ እያላት ጥር 21 እሑድ ዕለት በልጇ ፈቃድ በመዐዛ ገነት፣ በመዝሙረ ዳዊት፣ በይባቤ መላእክት የእመቤታችን ነፍሷ ከሥጋዋ ተለየች፤ ጌታም እንደ በረዶ ጸዐዳ የኾነውን የድንግል ማርያምን ነፍስ በዕቅፉ ውስጥ እንደያዘ ለነፍሷ የከበረ ሰላምታውን ሰጥቶ ባማረው ሸማ ጠቅልሏት ለሊቀ መልአኩ ለቅዱስ ሚካኤል በብርሃናማ ክንፎቹ እንዲሸከማት ሰጠው፡፡

❖✔ ሊቁ ቅዱስ ያሬድም ይኽነን ይዞ በድጓው ላይ “ፃኢ እምሊባኖስ ሥነ ሕይወት ርቱዕ አፍቅሮትኪ ቡርክት አንቲ እምአንስት ማኅደረ መለኮት ሰላም ለኪ፤ ማርያም እመ አምላክ ወልድኪ ይጼውዐኪ ውስተ ሕይወት ወመንግሥተ ክብር” (የሕይወት ደም ግባት የአምላክ እናት ከሊባኖስ ውጪ፤ ፍቅርሽ የቀና ነው፤ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ፤ የመለኮት ማደሪያ ሰላምታ ላንቺ ይገባል፤ የአምላክ እናት ማርያም ሆይ ልጅሽ ወደ ዘላለማዊ ሕይወትና ወደ ክብር መንግሥት ይጠራሻል) በማለት አመስጥሮታል፡፡

❖✔ ቅዱሳን ሐዋርያትም ሥጋዋን በክብር ገነዘዋል፤ ከኢትዮጵያ ሊቃውንት መኻከል ስለዚኽ በቅዱሳን ሐዋርያት ስለተደረገው የከበረ የሥጋዋ ግንዘት ቅዱስ ያሬድ አምልቶ አስፍቶ የጻፈ ሲኾን፤ በነሐሴ ፲፭ በአጫብሩ ድጓ ውስጥ በአስደናቂ መልኩ እንዲኽ ተጽፈዋል፡-

╬ “ሐዋርያት አመድበሉ
ሥጋ ድንግል ጠብለሉ
በሰንዱነ ብርሃን ዘላዕሉ
ልብሳ ተካፈሉ”
(ሐዋርያት ተሰበሰቡ፤ ከላይ በመጣ በፍታ (መጐናጸፊያ) የድንግል ሥጋን ጠቀለሉ፤ ልብሷንም ተካፈሉ)

╬ “በደመና ተጋቢኦሙ ሐዋርያት ለድንግል ንጽሕት
ገነዝዋ በክብር ወበስብሐት
ለቀበላሃ ወረዱ ኀይላት
ወቀበርዋ ውስተ ገነት”
(ሐዋርያት በደመና ተሰብስበው ንጽሕት ድንግልን በክብር በምስጋና ገነዟት፤ ለአቀባበሏ ኀይላት ወረዱ፤ በገነት ውስጥም ቀበሯት)

╬ “ተጋቢኦሙ ሐዋርያት እምኲለሄ
በደመናት ዘምሉእ ሡራኄ
ገነዙ በክብር ወበስባሔ
ሥጋ ድንግል ዘይምዕዝ እምርሔ”
(ብርሃንን የተመላ በኾነ በደመናት ሐዋርያት ከአራቱ ማእዝን ተሰብስበው ልብን ከሚመስጥ ሽቱ ይልቅ የሚሸትት የድንግልን ሥጋ በክብርና በምስጋና ገነዙ)

╬ “ተጋቢኦሙ በደመና ሰማይ
ሐዋርያት ሥርግዋን በዕበይ
ገነዝዋ ለድንግል በብዙኅ ግናይ
ዳዊት ዘመራ በመሓልይ”
(በገናንነት የተጌጡ ሐዋርያት በሰማይ ደመና ተሰብስበው ድንግልን በብዙ ምስጋና ገነዟት፤ ዳዊትም በምስጋና አመሰገናት፡፡)

╬“ተጋቢኦሙ አርድዕተ ወልዳ
በደመና ብርሃን ጸዐዳ
ገነዝዋ በስብሐት ለጽርሕ ሳይዳ”
(ጸዐዳ በኾነ በብርሃን ደመና የልጇ ደቀ መዛሙርት ተሰብስበው፤ ውቢቱ አዳራሽን በምስጋና ገነዟት)

╬ “ተጋብኡ በቅጽበት ለግንዘተ እሙ ቅድስት
ብፁዓን ሐዋርያት
ቦኡ ኀቤሃ በሰላም አምኁ ኪያሃ
በስብሐት ገነዙ ሥጋሃ”
(ንኡዳን ክቡራን ሐዋርያት ቅድስት የምትኾን የጌታ እናቱን ለመገነዝ በቅጽበት ተሰበሰቡ፤ ወደ ርሷ ገብተው በሰላምታ ርሷን እጅ ነሧት፤ ሥጋዋንም በምስጋና ገነዙ) በማለት ሊቁ ማሕሌታይ በሐዋርያት እጅ የተደረገ የሥጋዋን ግንዘት አምልቶ አስፍቶ ጽፏል፡፡

❖✔ ሐዋርያት በታላቅ ግርማ በአምላክ እናት ሥጋ ፊት ምስጋናን እያሰሙ ዝማሬን እየዘመሩ ሥጋዋን እጅ እየነሡ ጌቴሴማኒ ሊቀብሯት ሲኼዱ አይሁድ አይተው ለምቀኝነት አያርፉምና ቀድሞ ልጇ ሞተ፣ ተነሣ፣ ዐረገ እያሉ እያስተማሩ ኖሩ ከመቃብሩም ተአምራት ይደረጋል፤ አሁን ደግሞ ርሷ ሞተች፣ ተነሣች፣ ዐረገች ብለው ሊያስተምሩ አይደል፤ “ንዑ ናውዒ ሥጋሃ ለማርያም ምስለ ዓራታ” በማለት እናቃጥላለን ብለው በምቀኝነት ተነሡባቸው፤ ታውፋንያ የሚባል ከአይሁድ ወገን በድፍረት የአልጋዋን አጎበር ሊነካ ሲሞክር ቅዱስ ገብርኤል በሰይፈ እሳት ቀጣው፡፡

❖✔ ያን ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ በዕለተ ዐርብ ከአምላኩ በስጦታ የተሰጠችውን የአምላክ እናትን ሥጋዋን በድፍረት ሊነኩ መምጣታቸውን አይቶ “ይቤ ዮሐንስ ወኢይገድፍ ምዕቅብናየ ወዘንተ ብሂሎ ወድቀ በላዕሌሃ” ይላል (ዐደራዬን አላፈርስም፤ ከርሷ ጋር እሞታለኊ በማለት ይኽነን ተናግሮ በላይዋ ላይ ወደቀ፡፡ ከዚያም “ወወረዱ ሚካኤል ወገብርኤል እምሰማይ በዐቢይ ግርማ” ይላል ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል በታላቅ ግርማ ወርደው የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥጋዋንና ቅዱስ ዮሐንስን በደመና ነጥቀው በገነት በሕይወት ዛፍ ሥር አኖሯት፡፡

❖✔ ወዲያውኑ “ወአምጽኡ ሎቱ ማዕጠንተ ወርቅ” ይላል የወርቅ ማዕጠንት ለዮሐንስ አምጥተውለት፤ “ወዕጥን ሥጋሃ ለማርያም መዓልተ ወሌሊተ” ይላል የቅድስት ድንግል የከበረ ሥጋዋን በመዓልትና በሌሊት ዕጠን አሉት፤ ዮሐንስም ይኽነን ክብር በመቀበሉ ደስ ብሎት ሥጋዋን እያጠነ “ወፍና ሠርክ ያመጽዕ ሎቱ ራጉኤል መልአክ ኅብስተ ሰማይ” ይላል ሰርክ ሲኾን ራጉኤል መልአክ ሰማያዊ ኅብስት ሰማያዊ መጠጥ እያመጣለት ያን እየተመገበ በገነት ቆይቷል፡፡

❖✔ ኋላም በጌታ ፈቃድ ከተቀሩት ሐዋርያት ጋር ተገናኘ፤ ሐዋርያትም የእመቤታችንን ነገር እንደምን እንደኾነ ሲጠይቁት ርሱም በገነት ያየውን ነገር ነገራቸው፤ እነሱም ይኽነን ታላቅ ምስጢር ዮሐንስ አይቶ እኛ ሳናይ ብለው ሱባኤ ነሐሴ 1 ዠመሩ ነሐሴ 14 ቀን በኹለተኛው ሱባኤ ጌታ የእናቱን ሥጋ አምጥቶ ሰጥቷቸው በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል፡፡

❖✔ በተወደደች ዕለት ነሐሴ 16 “ወአዘዞሙ እግዚእነ ለሰብአቱ ሊቃነ መላእክት ከመ ይጸውዕዋ ለምድር” (ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት ምድርን ይጠሯት ዘንድ አዘዛቸው) እነርሱም ምድርን “ይኤዝዘኪ እግዚእነ ከመ ታውጽኢ ሥጋሃ ለእሙ ቅድስት” (ጌታችን የንጽሕት እናቱን ሥጋ ታወጪ ዘንድ ያዝሻል) አሏት፤ ያን ጊዜ ልጇ “ንዒ ኀቤየ ወላዲትየ ከመ አዕርጊ ውስተ መንግሥተ ሰማያት” (ወደ መንግሥተ ሰማያት አሳርግሽ ዘንድ እናቴ ወደኔ ነዪ) አላት፤ ያን ጊዜ በልጇ ሥልጣን የቅድስት ድንግል ማርያም ነፍሷና ሥጋዋ ተዋሐዱ፤ ነሐሴ 16 ዕለትም ከሞት ተነሣች፡፡

❖✔ ያን ጊዜ “ወረዱ መላእክት ወሊቃነ መላእክት” ይላል ቅዱሳን መላእክት ከሰማይ በታላቅ ግርማ ወረዱ፤ ነቢዩ ዳዊትም “ወትቀውም ንግሥት በየማንከ” (ንግሥቲቱ ወርቀ ዘቦ ግምጃ ደርባ ደራርባ በቀኝኽ ትቆማለች) እያለ ይዘምርላት ነበር፤ አየሩ ኹሉ በቅዱሳን መላእክት ተመላ፤ እጅግ የሚያስደንቅ መዐዛ አካባቢን ዐወደው፡፡

❖✔ ስለ አካላዊ ዕርገቷ አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፋቸው በቊ ፹፪ ላይ፡-
“አመ ነሥኡኪ እምኤዶም አዕላፈ ማሕሌት ጾታ
እንዘ ይጼልሉኪ ድንግል በአክናፈ መባርቅት ከመ ወልታ
ሰራዊተ ሰማይ ይቤሉ ለክብረ ፍልሰትኪ ግርማ ትርሲታ
መኑ ይእቲ ዛቲ ዘገዳመ ጽጌ ዕጥነታ
ወከመ ሠርጸ ጢስ ዘስኂን ይምዕዝ ዕጥነታ”

(ድንግል ወገኖች አመስጋኞች መላእክት በየነገድ በየነገድ ኾነው በመባርቅት ክንፎች እንደ ጋሻ ጋርደው ከኤዶም ገነት በተቀበሉሽ ጊዜ የሚያስደንቅ ክብር ለተገለጸባት ለዕርገትሽ የሰማይ ሰራዊት አበባ ካለበት በረሓ የምትወጣ መዐዛዋም ከነጭ ዕጣን ይልቅ የሚሸትት አወጣጧም እንደ ጢስ አወጣጥ የኾነችይኽቺ ማናት? ይኽቺ ማን ናት ይላሉ (መሓ ፫፥፲፮)) በማለት በአስደናቂ መልኩ ዕርገቷን ገልጸዋል፡፡

❖✔ ቅዱስ ያሬድም በዝማሬው ላይ “ፈለሰት ማርያም በስብሐት ውስተ ሰማያት መላእክት ወሊቃነ መላእክት ወረዱ ለተቀብሎታ” (እመቤታችን በምስጋና ወደዚያኛው ዓለም በተለየች ጊዜ ለአቀባበሏ መላእክትና ሊቃነ መላእክት ወረዱ) ይለዋል፡፡

❖✔ ያን ጊዜ በታላቅ ክብር በመላእክት ታጅባ ወደ ሰማይ ስታርግ፤ ሐዋርያው ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ሲመጣ ሰማዩ ኹሉ በቅዱሳን መላእክት ተመልቶ የአምላክ እናት በክብር ስታርግ ተመለከተ፤ ያን ጊዜ ነገሩ ረቆበት ምን ይኾን እያለ ሲል ቅዱሳን መላእክት የእመቤታችን ዕርገት እንደኾነና እጅ እንዲነሣ ነገሩት፡፡

❖✔ ርሱም “ከቶ ምን አርጌ ይኾን፤ ቀድሞ የልጇን ትንሣኤ ሳላይ ቀረኊ ዛሬ ደግሞ የርሷን ትንሣኤ ሳላይ ልቅር” ብሎ “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ” ይላል ተበጻብጾ ሊወድቅ ወደደ፤ እመቤታችንም “አይዞኽ አትዘን እነሱ ሞቴን አይተዋል እንጂ ዕርገቴን አላዩም አኹንም እመቤታችን ተነሣች ዐረገች ብለኽ ንገራቸው” ብላ ለበረከት ሰበኗን ሰጠችው፡፡

❖✔ ርሱም በደስታ ተመልቶ ሐዋርያት ያሉበት በመኼድ የእመቤታችን ነገር እንደምን ኾነ ብሎ ጠየቃቸው፤ እመቤታችን ሞተች ቀበርናት አሉት፤ “መቼ ሞተች?” አላቸው በጥር አሉት፤ “መቼ ቀበራችኋት?” አላቸው በነሐሴ አሉ፤ ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር ተዉ ይኽ ነገር እንዴት ይኾናል አላቸው፤ ቅዱስ ጴጥሮስም ቶማስን ቀድሞ የልጇን ትንሣኤ አላምን ብለኽ የጌታን ጐን የዳሰሰ እጅኽ ተቃጥሎ ነበር፤ አኹን ደግሞ እኛ ብንነግርኽ አላምን ትላለኽ ብሎ፤ “ወነሥአ መክርየ” ይላል መቆፈሪያ ይዞ ኼዶ ይቆፍር ጀመር።

❖✔ ርሱም የያዘውን ይዟልና ጸጥ ብሎ ይሰማቸዋል፤ ቈፍረው ሲያጧት ደነገጡ፤ ቶማስም አይዟችኊ አትደንግጡ እመቤታችን እኮ በመላእክት ምስጋና ወደ ሰማይ አረገች ብሎ ሰበኑን አሳያቸው፤ እነርሱም ለበረከት ሰበኑን ተካፍለውታል፡፡ ዛሬም ሐዋርያዊት የኾነችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ይኽነን በማሰብ በመስቀል ሥር የሰበኗ ምሳሌ የሚኾን ሰፊ ጨርቅ ታደርጋለች፡፡

❖✔ ባመቱ ቶማስ አይቶ እኛ ሳናይ ብለው በድጋሚ ሐዋርያት ሱባኤ ሲገቡ ክብር ይግባውና ጌታችን በደመና ነጥቆ ወስዶ ሥርዓተ ቊርባንን ፈጽሞላቸው፤ ስለ እናቱ ዕርገት በዓለሙ ኹሉ ዙረው እንዲያስተምሩ አዝዟቸዋል፡፡ እነርሱም ዓለምን ዞረው ወንጌልን ሲያስተምሩ የቅድስት ድንግል ማርያምን ዕርገት ሰብከዋል አስተምረዋል፡፡

❖✔አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፋቸው ላይ ወደ ምጡቅ ሰማይ ስለተደረገው ዕርገቷ ፡-
“እንዘ ይፀውረኪ በሐቂፍ ወይስዕመኪ በአፍ
አመ አፍለሰኪ ወልድ ውስተ የማኑ ለዐሪፍ
ጽጌ ዕፀ ገነት ማርያም ዘትጼንዊ ለአንፍ
እንዘ ይትጓድዑ አክናፈ በክንፍ
ለቀበላኪ ወረዱ አእላፍ”

(ለአፍንጫ መዐዛን የምትሰጪ የገነት ዛፍ ማርያም ሆይ፤ ልጅሽ በክንዱ ዐቅፎ በአፉ እየሳመ በቀኙ ሊያሳርፍሽ ባሳረገሽ ጊዜ፤ አንቺን ለመቀበል ክንፍ ለክንፍ እየተጋጩ እልፍ አእላፋት መላእክት ወረዱ) በማለት አስተምረዋል፡፡

❖✔ በተመሳሳይ መልኩ ዳግመኛ አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፋቸው በቊ፹፬ ላይ፡-
“ትእምርተ ፍልሰትኪ እምድረ ጽጌ ድንግል በክልኤ
በደመና ሰማይ አርአየ ዘሐዋርያት ጉባኤ
ወእለ ሞቱ አንቅሐ እምከርሠ መቃብር ቀርነ ጽዋዔ
ለነሰ እንዘ ይብሉ ሶበ ሰማዕነ ውዋዔ
መሰለነ ዘበጽሐ ትንሣኤ”

(በኹለት ወገን ድንግል የኾንሽ ማርያም ሆይ አበባ ካለበት ምድር ወደ ሰማይ የማረግሽ ተአምር በሰማይ ደመና የሐዋርያት ጉባኤን አሳየ፤ የሞቱትንም ከመቃብር ውስጥ በተአምር ነጋሪት ድምፅ አስነሣ፤ ለእኛስ የምስጋና ከፍተኛ ድምፅን በሰማን ጊዜ የሙታን መነሣት የደረሰ መሰለን እስኪሉ ድረስ) በማለት ሐዋርያትን ተሰብስበው ሳሉ ዕርገቷን እንዲያዩ እንዳደረጋቸው ጽፈዋል፡፡

❖✔ የአምላክ ታቦት ስለኾነች ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም አካላዊ ዕርገቷ አስቀድሞ ትንቢት እንዲኽ ተነግሮላታል፡-

💥 “አቤቱ፥ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት።” መዝሙረ ዳዊት 131 (132)፡8
💥 “መዓዛም እንደ ከርቤና እንደ ዕጣን የሆነችው፥ ከልዩ ከነጋዴ ቅመም ሁሉ የሆነችው፥ ይህች ከምድረ በዳ እንደ ጢስ ምሰሶ የወጣችው ማን ናት?” (መሓ 3፡6)

❤ ከሞት ተነሥታ በንጉሥ ክርስቶስ ቀኝ ስለመቆሟ፡-
💥 “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” (መዝ 44፡9) ይላል፡፡

❤💥 የአማናዊት ታቦት የቅድስት ድንግልን ወደ ሰማይ ማረግ በዐይኑ የተመለከተው ዮሐንስም “በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ” በማለት መስክሮላታል (ራእ ፲፩፥፲፱)፡፡

❤💥 በመቀጠልም አሕዛብንም ኹሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ጌታን የወለደች እመቤታችን በታላቅ ክብር በሰማይ ናትና ዮሐንስ በራእ ፲፪፥፩ ላይ:- “ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሓይን ተጐናጽፋ ከእግሮቿ በታችም ጨረቃ ያላት በራሷም ላይ የዐሥራ ኹለት ከዋክብት አክሊል የኾነላት” በማለት ይመሰክርላታል፡፡

💥❤💥 ቅዱሳት መጻሕፍትን ስናጠና እንደምናገኘው በመቃብር ውስጥ መፍረስ መበስበስ የኀጢአት ውጤት ሲኾን ትእዛዝን የጣሰውን አዳምን “ዐፈር ነኽና ወደ ዐፈርም ትመለሳለኽና” በማለት ተረግሞ ነበር (ዘፍ ፫፥፲፱)፤ በዚኽም ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሥጋዊ ደማዊ የኾነው ኹሉ ወደ መቃብር ሲወድቅ፤ ርሷ ግን ከእናቷ ማሕፀን ዠምራ በመንፈስ ቅዱስ የተጠበቀች አዳማዊ ኀጢአት ያላገኛት፣ ኀጢአት አልባ የኾነች እንዲያውም አዳምና ሔዋን ይኽነን መርገም ከመስማታቸው በፊት ከነበራቸው ንጽሕና የበለጠ ንጽሕናን ገንዘብ ያደረገች ናትና በመቃብር አልቀረችም ልጇ ሞትን ድል አድርጎ እንደተነሣ የመቅደሱ ታቦት ቅድስት ድንግልም በልጇ ሥልጣን ከሞት ተነሥታ በሰማይ አለች፡፡

✔❖ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በነሐሴ ፲፮ የቅድስት ድንግል ማርያም የዕርገት በዓል ብሔራዊ በዓል ተደርጎ በተለያዩ ሀገራት ሲከበር ዕርገቷ ይታሰብባቸው ከነበሩ ሀገራት ውስጥም ኦስትሪያ፣ ቤልጂየም፣ አንዶራ፣ ቺሊ፣ ኮሎምቢያ፣ ክሮሺያ፣ ኢኳዶር፣ ፈረንሳይ፣ ግሪክ፣ ሊባኖስ፣ ጣሊያን፣ ማልታ፣ ስሎቬኒያ፣ ፖላንድ፣ ፖርቹጋል፣ ሩማኒያ፣ ቺሊ፣ ሳይፕረስ፣ ሀይቲ፣ ሴኔጋል፣ ስሎቬኒያ፣ ስፔን፣ ካሜሩን፣ ጋቦን፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ሴኔጋል፣ ቶጎ፣ ኮትዲቭዋር፣ ማዳጋስካር እና ሌሎች በርካቶች የዓለም ሀገራት ይገኛሉ (Columbus World Travel Guide, 25th Edition, The Assumption of the Blessed Virgin Mary into Heaven, the free encyclopedia) ተመልከቱ፡፡

★ ምንጭ፡- ነገረ ማርያም በሐዲስ ኪዳን መጽሐፍ፤ በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ የተጻፈ
✔ነገረ ማርያም በሊቃውንት ክፍል አንድ መጽሐፍ፤ በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ የተጻፈ
✔ መልክአ ማርያም ንባቡና ትርጓሜው በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ የተጻፈ፡፡
የእመቤታችን በረከት በዝቶ ተትረፍርፎ ይደርብን፡፡ መልካም በዓል፡፡

እንኳን ለሐያሉ መላዕክ ቅዱስ ሚካኤል የመታሰቢያ በዓል አደረሳችሁ አደረሰን  የመላዕኩ ረዴት በረከት በሁላችን  ይደርብን፣ ጥበቃው አይለየን!
18/08/2020

እንኳን ለሐያሉ መላዕክ ቅዱስ ሚካኤል የመታሰቢያ በዓል አደረሳችሁ አደረሰን የመላዕኩ ረዴት በረከት በሁላችን ይደርብን፣ ጥበቃው አይለየን!

Address

Addis Ababa

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when የቅድስት ድንግል ማርያም ልጆች posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share