13/03/2024
በሃገራችን የሚገኙ የአብነት ትምህርት ቤቶችን የመደገፍ ፣የማቋቋም የግንባታ ዘመቻ"በእንተ ስማ ለማሪያም ለእኔ ተማሪ" በሚል መሪ ቃል ተጀመረ።
ይህ ዘመቻ ለአብነት ተማሪዎች የምግብ ፣የመጽሀፍ ፣የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ፣የህክምና አገልግሎት ፣መኖሪያ እስከ ማንበቢያ ቤተመጻሕፍት ለማቅረብ የተነደፈ የንቅናቄ ፕሮጀክት ነው።
ፕሮጀክቱ በተለያዩ የሀገሪቱ ገጠራማ ስፍራዎች ላይ ከረሃብ ከእርዛት ጋር በመተጋል ለዕውቀት ዋጋ እየከፈሉ ለሚገኙ በ20 የአብነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚገኙ 1 ሺህ 2 መቶ የአብነት ተማሪዎች መሆኑን ቁስቋም የበጎ አድራጎት ማህበረ በዛሬው እለት ለመገናኛ ባለሙያዎች በተሰጠ መግለጫ ላይ ተነግሯል።
ማህበረ ቁስቋም የተለያዩ መንፈሳዊና ሐገራዊ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ በሱስ ዉስጥ የሚገኙ ወጣቶችን በዕውቀት በክህሎት ማብቃት ፤ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናትን በማስከፈት ፣ ገዳማትን የሚደግፍ ማህበር ነው።
በተጨማሪም በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ በሆኑ አደጋዎች ምክንያት በተለያዩ ችግሮቸ ውስጥ የሚገኙ ገዳማትንና አድባራትን የኢኮኖሚ ነጻነት እንዲኖራቸው በማድረግ፣ ለሴት መነኮሳትና ለአቅመ ደካማ አረጋዊ መነኮሳት የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ሟሟላት የህክምና አገልግሎት የመስጠት ስራዎችን እየሰራ የቆየ ማህበር መሆኑንም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶኮስ ተዋህዶ በተክርስቲያን የኢትዮ ሱማሌ ሀገረ ስብከት ሊቃነ ጳጳስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ "የአብነት ት/ቤትን መደገፍ በወጀብ የማይናድ በድንጋይ የተገነባን የዕውቀት መንደር መፍጠር ነው "ብለዋል።
የማህበረ ቁስቋም የህዝብ ግንኙት ክፍል ሃላፊ የሆኑት ሲስተር ቤዛዊት በቀለ፣ለዕውቀት ቤቷ የዬኔታ ደጅ መሆኑን በማመን ፤ጥናት በማድረግ ለባለሙያዎች ጉዳዩን በማስመልከት በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በማስተቸት የመፍትሄ ሃሳብን በመያዝ ይህን የንቅናቄ መረሃግብር እንዲዘጋጅ ተደርጓል ብለዋል።
ሊቀ ህሩያን ደረጄ ግርማ የአብነት ትምህርት በ1901 ዓ.ም ዘመናዊ ትምሀርት ቤት ከመግባቱ በፊት የነበረ ትምህርት ቤት ሲሆን፣ አለም አሁን የሚደነቅበትን የሥነ-ዜማ፣ የሥነ-ጽሁፍ፣ የሥነ-ፈለግ፣ ፣የሥነ-ህንፃ፣ የሥነ-ህክምና፣ የሥነ-ሂሳብ ጥበቦችንና ሌላም ብዙ ትምህርቶችን ለአለም ያስተዋወቀች የሀገር ባለውለታ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ሊቀ ህሩያን ደረጄ ግርማ የአብነት ትምህርት ቤትን መደገፍ የሃይማኖት ጉዳይ ብቻም ሳይሆን የሀገርን ህልውና የመቀጠልና ያለመቀጠል ጉዳይ በመሆኑ፤ ሀገሬ ታሪኳ ሳይጠፋ ቤተክርስቲያን ዕሴቷ ሳይጓደል ለልጄ የሚል ኢትዮጵያዊ ሁሉ እጁን ይዘርጋ፤ የባለታሪክ ልጆች ነንና ጥቂት በማድረግ ታሪክ እንስራ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በልዑል ወልዴ
መጋቢት 04 ቀን 2016 ዓ.ም
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ወቅታዊ አዳዲስ መረጃዎችና ፕሮግራሞችን ለማግኘት ከታች ያሉትን ገፆቻንን ይጎብኙ ቤተሰብ ይሁኑ ።
Telegram https://t.me/ethiofm107dot8
Twitter https://twitter.com/EthioFM
YouTube https://www.youtube.com//videos
Facebook https://www.facebook.com/onelovebroadcast
በፍቅር ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊነት እንዳይላላ ከልቡ የሚተጋ፣ መከባበርና መተሳሰብን የሚያስቀድም ኤፍ ኤም ሬዲዮ ነው!!!