Evangelical Churches Fellowship of Ethiopia

Evangelical Churches Fellowship of Ethiopia ECFE is an umbrella organization with a view to increasing coordination of member church activities for the promotion of fellowship & cooperation in Ethiopia
(1)

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት ኅብረት፥ ፕሮፌሰር ክሬግ ኪነር የለገሱትን የመጻሕፍት ስጦታ ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ግንቦት26 ቀን 2018 ዓ.ም አበረከተ።የኢትዮጵያ ወንጌላዊያ...
03/06/2026

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት ኅብረት፥ ፕሮፌሰር ክሬግ ኪነር የለገሱትን የመጻሕፍት ስጦታ ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ግንቦት26 ቀን 2018 ዓ.ም አበረከተ።
የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስትያናት ኅብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ደረጀ ታፈሰ፥ በፕሮፌሰር ክሬግ ኪነር የተጻፉ፥ ፕሮፌሰሩም ለኢትዮጵያ መልካሙን የተመኙበት ጽሑፍና ፊርማቸው ያረፈበትን መጻሕፍት ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት በስጦታ ባበረከቱበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፥
በአሜሪካን አገር ከሚገኙ ወዳጆች የተገኙት እነዚህን የመጻሕፍት ስጦታዎች በአገር ውስጥ በግዥ ለማግኘት እንደሚያስቸግር፥ መጻሕፍቱ በአንድ ሥፍራ ከሚሆኑ በአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ቢቀመጡ በርካታ አጥኚዎችንና አንባቢያንን ሊጠቅሙ እንደሚችሉ ገልጸው፥ ትውልድ እውቀት አልባ ሊሆን እንደማይገባ፥ በመልካም እውቀት የተገነባ ትውልድ ደግሞ ለአገር እድገት ሁነኛ አስተዋጽዖ ማድረግ እንደሚችል፥ ይህ እንዲሆን ደግሞ ኅብረቱ የበኩሉን ድርሻ እያበረከተ መሆኑን ገልጸው ፥ ስጦታውን ከአሜሪካን ድረስ ያመጡትን ዶክተር ፈቃዱ አመኑን አመስግነዋል።
መጻሕፍቱን ከፕሮፌሰር ክሬግ ተረክበው ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት እንዲሰጥ መነሻውን የወጠኑት ዶክተር ፈቃደ አመኑ፥ በታዋቂው የነገረ መለኮት ሊቅ የተጻፉት እነዚህ መጻሕፍት፥ የተለያየ የእምነት አመለካከት ያላቸውን ሰዎች ለምርምር ተግባር ሊያግዝ የሚችል፥ ወደየ ቤተ እምነቱ ሄደው ለማንበብ ለሚከብዳቸው አጥኚዎችም አብርሆት አማካይና አመቺ ከመሆኑ አንጻር መመረጡን ገልጸው፥ እነዚህን ውድ መጻሕፍት የለገሱትን ፕሮፌሰርና ሌሎች ወዳጆቻቸውን ከልብ አመስግነዋል። አክለውም፥ የመጻሕፍቱ ስጦታዎች በዚህ እንደማይገደቡና ተጨማሪ መጻሕፍትን ለቤተ መጻሕፍቱ ለማበርከት ቃል ገብተዋል።
በመጨረሻም የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ታሪኩ፥ ስለተደረገው የመጻሕፍት ስጦታ ከልብ አመስግነው፥ በቤተ መጻሕፍቱ ስም ለኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት ኅብረት እና ለፕሮፌሰር ክሬግ ኪነር የምስጋና ምስክር ወረቀት አበርክተዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት ኅብረት ከባርናባስ ኤይድ ጋር በመተባበር በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉና በሽረ እንዳ ሥላሴ መጠለያዎች ለሚገኙ 2700 የቤተሰብ ሃላፊዎች የጤፍ እህ...
25/05/2026

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት ኅብረት ከባርናባስ ኤይድ ጋር በመተባበር በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉና በሽረ እንዳ ሥላሴ መጠለያዎች ለሚገኙ 2700 የቤተሰብ ሃላፊዎች የጤፍ እህልና የሽሮ ዱቄት ድጋፍ አደረገ።

ሰኞ ግንቦት 17 ቀን 2018 ዓ.ም በተከናወነው በዚህ የድጋፍ መርሐ ግብር የትግራይ ሴቶች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ አበባ ኃይለሥላሴ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት ኅብረት ተወካይ አቶ የኔነህ ታደሰና የምዕራብ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ግደይ አዘናው ንግግር አድርገዋል።

በዕለቱ ወ/ሮ አበባ ኃ/ሥላሴ ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት ኅብረት ከዚህ ቀደም አድርጎት የነበረውን ተመሳሳይ ድጋፍ አስታውሰው፣ በዚህ ሳምንትም 27 ሚሊዮን ብር ሊያወጣ የሚችል ድጋፍ በማደረጉ ምስጋናቸውን በተፈናቃዮች ስም አቅርበዋል።

አስከትለውም ከእርዳታው ጎን ለጎን ተፈናቃዮቹን በሰላማዊ መንገድ ወደ ቀዬአቸው መመለሱ ዘላቂ ወደሆነ መፍትሄ ያደርሳል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረትን በመወከል ንግግር ያደረጉት የኅብረቱ ሚሽንና ቲዮሎጂ መምሪያ ሃላፊ አቶ የኔነህ ታደሰ፣ ኅብረቱ ድጋፍ ለማድረግ ወደ ሽሬ ሲመጣ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሆነ አስታውሰው፣ ከቀዬው ተሰዶ ወደዚህ ስፍራ የመጣው ሕዝብ በአንድ ዘመን እጁን ለሌሎች የሚዘረጋ፣ የተራቡትን የሚመገብ፣ የታረዙትን የሚያለብስና የተጠሙትን የሚያጠጣ እንደነበር ገልጸው፣ ሆኖም ይህን ሕዝብ በዚህ መከራ ውስጥ የማይተው፣ መልሶ ለጋሽ፣ አጉራሽና አልባሽ የሚያደርግ ፈጣሪ እንዳለ፣ ወደዚህ ተስፋ ለመድረስ ግን፣ ሁኔታዎችን መለወጥ በሚችል እግዚአብሔር መታመን፣ እርሱን ተስፋ ማድረግ፣ ተስፋ ሳይቆርጡም ወደ እርሱ መጮህና በጽናት መራመድ እንደሚገባ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅሰው ተፈናቃዮችን የሚያጽናናና ተስፋ የሚሰጥ መልእክት አስተላልፈዋል። አያይዘውም፣ ሥራውን በማሳለጥ በማስተባበርና ድጋፍ በማድረግ የተሳተፉትን፣ የባርናባስ ፈንድን፣ የትግራይ ሴቶች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ አበባ ኃ/ሥላሴን፣ የዋናው ቢሮ ሠራተኞችን፣ የሽሬ ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት ዋና ጸሐፊ መጋቢ ተስፉ ብርሃኔንና ባልደረቦቻቸውን በህዝቡ ፊት አመስግነዋል።

በመቀጠል የምዕራብ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ግደይ አዘናው ስለተደረገው ርዳታ አመስግነው፣ ሕዝቡንም አጽናንተውና አበረታተው ሁኔታዎችም በዚህ መልኩ እንደማይቀጥሉ ጠቅሰው ንግግራቸውን አጠናቀዋል።

በመጨረሻውም፣ የሽረ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ዋና ጸሐፊ መጋቢ ተስፉ ብርሃኔ ቃለ እግዚአብሔርን በመጥቀስ ሕዝቡን የሚያጽናና እና ልብ የሚደግፍ መልእክት አስተላልፈዋል ።

የኅብረቱ ተወካዮች እንዳስረዱት፣ በነገው እለት ስድስት መቶ እሽግ አልሚ ምግብና ዳይፐር፣ እንዲሁም ለሰባት መቶ ሃምሳ እንስቶች የሚሆን የንጽህና መጠበቂያ ፓድ እደላ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ከበርናባስ ኤይድ ጋር በመተባበር በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉና በመቐሌ መጠለያዎች ለሚገኙ ህፃናት የሚሆን 400 እሽግ አልሚ ምግብ፣ 40...
22/05/2026

የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ከበርናባስ ኤይድ ጋር በመተባበር በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉና በመቐሌ መጠለያዎች ለሚገኙ ህፃናት የሚሆን 400 እሽግ አልሚ ምግብ፣ 400 ፓኬት የልጆች ዳይፐርና ለ300 ሴቶች የሚያገለግል የንጽህና መጠበቂያ ቁሶችን አበረከተ።

ግንቦት 14 ቀን 2018 ዓ.ም በተደረገው በዚህ የድጋፍ መርሐ ግብር፣ የኀብረቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ፓስተር ሰንበቶ ባሼ፣ ክርስቶስ በዚህ ስፍራ ቢሆን በእንዲህ ዓይነት እጦትና ጉዳት ላሉ ሰዎች ልብን የሚያጽናና የፍቅር የርህራሄና የአብሮነትን መንፈስ እንደሚያኖር ጥርጥር የለኝም ካሉ በኋላ፣ ሕዝበ እስራኤል መከራ በደረሰበት እና ተስፋ በቆረጠ ጊዜ ወደ እርሱ በመጮሁ ምክንያት እግዚአብሔር ተዓምራትን እንዳደረገ ዛሬም እንዲሁ ተስፋ ቆርጠው ላዘኑና ወደ እርሱ ለሚጣሩ ሁሉ የተስፋ በር ይሆናል በማለት ተናግረዋል

አስከትለውም ዛሬ በኅብረቱ በኩል ወደ እናንተ እንዲደርስ የተደረገው ጥቂትድጋፍ የፍቅራችንና የአብሮነታችንን ስሜት ለመግለጽ እንጂ ችግሩን የሚፈታ እንዳልሆነ እንረዳለን፤ ከዚያ በላይ ግን እግዚአብሔር አምላክ የተሰደዱትን የሚደግፍ፣ ያዘኑትንም የሚያጽናና አምላክ በመሆኑ መልካም ተስፋ ከፊታችሁ አለ በማለት ንግግራቸውን በጸሎት አጠቃለዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት ኅብረት ከ፣ barnabasaid ጋር በመተባበር በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉና በመቀሌ መጠለያዎች ለሚገኙ 1800 የቤተሰብ ሃላፊዎች የጤፍ እህልና ...
22/05/2026

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት ኅብረት ከ፣ barnabasaid ጋር በመተባበር በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉና በመቀሌ መጠለያዎች ለሚገኙ 1800 የቤተሰብ ሃላፊዎች የጤፍ እህልና የሽሮ ዱቄት ድጋፍ አደረገ።

ግንቦት 13 ቀን 2018 ዓ.ም በተከናወነው በዚህ የድጋፍ መርሐ ግብር የትግራይ ሴቶች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ አበባ ኃይለሥላሴ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት ኅብረት ስላደረገው ተደጋጋሚ ድጋፍ አመስግነው፣ ሌሎችም ተቋማት ድጋፍ ከማድረግ ጋር ተፈናቃዮቹ ዘላቂ ወደሆነው ኑሮአቸው በሚመለሱበት ሁኔታ ላይ አጥብቀው እንዲሰሩ ጥሪ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት ፕሬዚዳንት ፓስተር ደረጀ ታፈሰ ባደረጉት ንግግርም፥ በስፍራው መገኘታቸው ለደስታና ለጭብጨባ ሳይሆን፣ በልባቸው ውስጥ ጥልቅ የሆነ ሐዘንና ቁጭትን ይዘው መሆኑ፥ ከፊታቸው የሚያይዋቸው ወገኖች—እናቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን—በጦርነትና በተለያዩ ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው፣ ሜዳ ላይ ወድቀውና በየካምፑ ተጠልለው መታየቱ የማንንም ሕሊና የሚነካ እውነታ እንደሆነ ገልጸው፥ የሕዝባችን መከራና እንባ የእኛም መከራና እንባ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር በመመደብ የምግብና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ይዞ መቅረቡን። ድጋፉም ተቋማዊ ግዴታ ብቻ ሳይሆን፣ ከፈጣሪ የተቀበልነው የፍቅርና የወንድማማችነትን አደራ ለመወጣት የሚደረግ ጥረት እንደሆነ ገልጸዋል።
በማስከተልም፥ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት፣ ከተለያዩ ርዕዮተ-ዓለማዊ ፍልስፍናዎችም ሆነ ከአክቲቪዝም ፍጹም ገለልተኛ የሆነ መንፈሳዊ ተቋም መሆኑን። ወገንተኝነቱም ለሰው ልጅ ክብር፣ ለሕይወት መትረፍና ለሰላም ብቻ እንደ ሆነ፣ የሰውን ልጅ ሕይወት የሚቀጥፍ፣ ሰብአዊነትን የሚያረክስ፥ የሰው ልጆችን ለእንዲህ ዓይነቱ ስደትና እንግልት የሚዳርግ ማንኛውንም የጦርነትና የግጭት አጀንዳ አጥብቆ እንደሚጸየፍ አሳውቀዋል።

አያይዘውም ጦርነት አሸናፊ እንደሌለው፥ የጦርነት ትርፉና ውጤቱ ዛሬ ከፊታችን የሚታየው እንባ፣ ረሃብ፣ ስደትና የትውልድ መፈናቀል ብቻ እንደሆነ ገልጸው፣ የሀገራችን መሪዎች፣ የፖለቲካ ኃይሎችና በየደረጃው የሚገኙ ውሳኔ ሰጪ አካላት የሕዝብን እንባና ስቃይ እንዲመለከቱ፤ ሰውን ከሚጎዱ እንቅስቃሴዎች እንዲቆጠቡ፤ የታሪክና የሕሊና ተጠያቂነትን እንዲያስታውሱ ማሳሰብ እንደሚወዱ ገልጸዋል።
ኅብረቱ እንደ መንፈሳዊ ተቋም፥ ለሀገራችን ሰላም ሌሊትና ቀን እንደሚጸልይ፤ የቆሰሉትን ለመጠገንና የተራቡትን ለመመገብ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ እንደሚያደርግ፥ ዘላቂው መፍትሔ ግን እርዳታ ማደል ሳይሆን፣ እርዳታ ፈላጊ እንዳይኖር ግጭትን በዘላቂነት ማስወገድ እንደሆነ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

አጠቃላይ የሆነውን ርዳታ አስመልክተውም፥ በሳምንቱ ቀናት መቀሌን ጨምሮ በሌሎችም የትግራይ አካባቢዎች 5160 አባወራዎችን አብሮም ከ15480 በላይ ቤተሰቦችን ሊመግብ የሚችል 1275 ኩንታል ጤፍ፥ 145 ኩንታል ሽሮ፥ ለ3500 ሰዎች ምጥን (ፋፋ)፥ ለ2500 እንስቶች የንፅህና መጠበቂያ፥ ለ1500 ህፃናት የዳይፐር ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቅሰው፥ በድጋፍ ሂደቱም አስተዋፆ ላደረጉ፥ ለትግራይ ክልል ሴቶች ማኅበር፥ በተለይም፥ ለወ/ሮ አበባ እና የሥራ ባልደረቦቻቸው፥ ለኅብረቱ ሰላምና አድቮኬሲ ዳይሬክተር ለአቶ ደቻሳ ሂረጰሳ እና የሥራ ባልደረቦቻቸው፥ ለበርናባስ ፈንድ ዩኬ፥ ለትግራይ ክልል ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ዋና ጸሐፊ ለፓስተር አብርሃም እና የሥራ ባልደረቦቻቸው፥ እንዲሁም ለባለ ድርሻ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በመጨረሻም ከ መዝ 34:18 ጠቅሰው፥ “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፥ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።” የሚለውን ቃል ካነበቡ በኋላ፥ ለተፈናቃዮች ተከታዩን መልእክት አስተላልፈዋል፤

በጦርነት ምክንያት ያጣችሁት ንብረት፣ ከቀያችሁ መፈናቀልና በስጋችሁ ላይ የደረሰው አካላዊ ጉዳት፥ ከባድና ጥልቅ ጠባሳ እንዳሳደረባችሁ እናውቃለን። ነገር ግን ዛሬ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እንድታውቁት የምንፈልገው ትልቅ እውነት፥ እግዚአብሔር እንዳልረሳችሁ፥ የሰው ልጅ መጠለያንና ሰላምን ቢነሳችሁም፣ የማይናወጠው ፍቅሩ ከእናንተ ጋር እንደሆነ፥ ስብራታችሁን እንደሚጠግን፣ አካላዊና መንፈሳዊ ቁስላችሁን እንደሚያክም፥ ዛሬ በምድር ላይ ያለውን መከራ ዓይታችሁ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለባችሁ፥ እግዚአብሔር ካላችሁበት ሁኔታ ውስጥ አውጥቶ አዲስ ተስፋና የተሻለ ነገን የመስጠት ኃይል እንዳለው ልነግራችሁ እወዳለሁ። እናንተ የክብር ሥራዎቹ ናችሁ፤ ነገ ይለወጣል፣ ቁስላችሁ ይፈወሳል፣ የፈረሰውም ሕይወታችሁ እንደገና ይታደሳል። እግዚአብሔር ብርታትንና ፍጹም ሰላሙን ይስጣችሁ! በማለት አጠናቀዋል።

በአስቸጋሪ የጉዞ መስመሮችና ምቹ ባልሆኑ ከባቢያዊ ዐውዶች ስኬታማ ሥራዎችን አከናውነናል።ኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ሰላምና አድቮኬሲ መምሪያ የሩብ ዓመት ተግባሩን  ገ...
09/05/2026

በአስቸጋሪ የጉዞ መስመሮችና ምቹ ባልሆኑ ከባቢያዊ ዐውዶች ስኬታማ ሥራዎችን አከናውነናል።

ኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ሰላምና አድቮኬሲ መምሪያ የሩብ ዓመት ተግባሩን ገመገመ

ሚያዚያ 29 ቀን 2018 ዓ.ም በማዶ ሆቴል በተካሄደው በዚህ መርሐ ግብር የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ምክትል ፕሬዚዳንት ፓስተር ሰንበቶ ባሼ ከማቴዎስ 6፥25 በማንበብ፥ ኢኮኖሚያዊና ሥነ-ልቦናዊ ጫናዎች በሚፈጥሩት የድባቴ ዐውድ ውስጥ ከሚፈጠረው የጭንቀት በሽታ ተላቀን፥ በምንም ነገር እንዳንጨነቅ በቃሉ የመከረንን ጌታ መስማት ይጠቅመናል በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

አስከትሎም፥ የሰላምና አድቮኬሲ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ደቻሳ ሂርጰሳ፥ ባለፉት አራት ወራት የተከናወኑ ሥራዎች፥ የታለሙ እቅዶችና በሥራው ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ከመስኩ ባለሙያዎች የሚሰማበት ጊዜ እንደሆነ ከገለጹ በኋላ፥ በተለያዩ ክልሎች የተሰማሩ የመስኩ ባለሙያዎች ስኬቶቻቸውንና ተግዳሮቶቻቸውን ተንትነዋል፤ በዚህም፥

• በወጣት ተማሪዎች መካከል ስለተሠሩት የሰላም ተግባራት፤
• በማህበራዊ ሥነ ልቦና ዙርያ ስለተሰጡ ሥልጠናዎች፤
• ስለ ራስ አገዝ ቡድኖችና በስራቸው ስለተገኙት ውጤቶች፤
• በሴቶች፥ በሃይማኖት መሪዎችና በወጣቶች ላይ ስለተሰጠ ትኩረት፤
• ጾታዊ ጥቃትን አስመልክቶ ስለተከናወኑ ሥራዎች፤
• ግጭት በነበረባቸው አንዳንድ አካባቢዎች በሁለት ባላንጣዎች መካከል ስለተፈጠረው መተማመን፤
• በግጭት ምክንያት የጉዳት ሰለባ የሆኑ ሕፃናትን በመለየት ስለተሰጠው ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ፤
• ሰላምን አስመልክቶ ውይይቶች በተደጋጋሚ ስለመደረጋቸው፤
• በራስ አገዝ ቡድን ውስጥ ከታቀፉ ግለሰቦች ሰለተገኙ አነቃቂ የስኬት ምስክርነቶች፤
• ግጭት ታይተውባቸውና መቃቃር ተከስቶባቸው በነበሩ አንዳንድ አካባቢዎች የታዩ ተስፋ ሰጪ የማኅበረሰብ መስተጋብሮች፤
• በተለያየ ቦታ የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶች የንግድ ክህሎት ሥልጠና የተሰጣቸዉ ሲሆን፥ የሥራ ማስጀመሪያ ገንዘብ ከቀረበላቸው በኋላ ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል። በወጣቶቹ ዘንድ የታየውን እድገት የመከታተልና የማበረታታት ተግባር በመከናወን ላይ ያለ ሲሆን፥ ወጣቶቹ ለእድሜ እኩዮቻቸው የተግባር አርአያና የሰላም አምባሳደር በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። በማለት አውስተዋል።

ባለሙያዎቹ ችግሮች በተከሰቱበት አካባቢዎች ተገኝተው ተግባራቶቻቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት ስለገጠማቸው ልዩ ልዩ ተግዳሮቶች ሲያወሱ፥

• የጸጥታ ችግር ባሉባቸው ስፍራዎች በሚደረጉ የሥራ እንቅስቃሴዎች ላይ ስላሉ ስጋቶች፤
• በታቀደው መሠረት ተግባራቶቻቸውን ማከናወን እንዳይችሉና የሥራ መስተጓጉል እንዲፈጠር ምክንያት ስለሆነ የዋጋ ግሽበት፤
• ግጭት በተከሰተባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ከተለያየ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ አካላት ጋር በተደረጉ ውይይቶችና ንግግሮች ነባራዊውን እውነት በመግለጽ ረገድ ማኅበረሰቡ ስላለበት ስጋት ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል።

ምክትል ፕሬዚዳንቱ ስለተከናወኑ ተግባራት አድናቆታቸውን በመግለጽ፥ ተግዳሮቶች የሚፈቱበትን መንገድ ከቢሮ ሃላፊዎች ጋር እንደሚመክሩበት አሳውቀዋል። አስከትሎም የመምሪያው ዲሬክተር፥ በአስቸጋሪ የጉዞ መስመሮችና ምቹ ባልሆኑ ዐውዶች ውስጥ ስኬታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸው፥ እነዚህ ተግባራት ሰላምን በማስፈን ረገድ አስተዋጽኦ እንዳደረጉና ቀጣይ የሆኑ አገልግሎቶችም ሰላምን ግብ ባደረገ መንገድ ሊከናወኑ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የሸገርና አካባቢው ክልል ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ምሥረታ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ጽሕፈት ቤት...
21/04/2026

በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የሸገርና አካባቢው ክልል ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ምሥረታ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ጽሕፈት ቤት ተካሄደ።
ሚያዚያ 12 ቀን 2018 ዓ.ም የሸገርና አካባቢው ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት መሪዎች በተገኙበት በተካሄደው በዚህ የምሥረታ ጉባዔ መክፈቻ፥ የኅብረቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ፓስተር ሰንበቶ ባሼ ጉባኤው ታሪካዊ መሆኑን በመግለጽ፥ የፕሬዚዳንቱን ሰላምታና የደስታ መልእክት ካስተላለፉ በኋላ፥ ከሁለተኛ ነገሥስት ምዕራፍ ዐራት በመጥቀስ፥ ኪዳን ጠባቂ የሆነው እግዚአብሔር ድካማችንን ፈጽሞ እንደማይዘነጋ፥ ለእግዚአብሔር ቤት የምንሰጠውንም አገልግሎት ከቶም እንደማይረሳ ተናግረዋል።
የሸገርና አካባቢው ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናትን ከፅንሰቱ ጀምሮ ሲያደራጅ የነበረው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ዋና ጸሐፊ ፓስተር ሳሙኤል ብርሃኑ፥ የሸገርና አካባቢው ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ሂደትና መነሻን አስረድተው፥ ሸገርና አካባቢው ሰፊ ቦታ ከመያዙ ባሻገር የኢኮኖሚ፥ የፖለቲካና የማኅበራዊ ስበት ማዕከል እየሆነ መምጣቱ፥ የዞን ኅብረቶች በክልል ማዕቀፍ ይያዙ ዘንድ አስገድዷል በማለት ተናግረዋል። በማጠቃለያቸውም ክልሉን በማደራጀት ለደከሙ መሪዎችንና አገልጋዮች ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ፥ ክልሉን በጸሎት በአሳብ እና በገንዘብ መደገፍ ቸል ሊባል እንደማይገባ አሳስበዋል።
የክልሉን የመተዳደሪያ ደንብ ካረቀቁት አባላት አንዱ ፓስተር ፈቃዱ ጫንያለው መተዳደሪያ ደንቡን በንባብ አሰምተው፥ ከጉባኤው ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሽ ከሰጡ በኋላ ደምቡ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል። በመጨረሻ ጠቅላላ ጉባኤው ሥራ አመራር ቦርድ መርጦና ለሥራቸውም መሳካት ጸሎት ካደረገ በኋላ የክልሉን መመሥረት ይፋ አድርጓል።
በዕለቱ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ሚሽን እና ቲዎሎጂ መምሪያ ኃላፊ፥ ወንድም የኔነህ ታደሰ የምርጫ ሂደቱን የመሩ ሲሆን፥ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ፓስተር ሰንበቶ ባሼም ሸገር እና አካባቢው በኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ኅብረት ውስጥ 18ኛ ክልል ሆኖ የክርስቶስን ወንጌል በስፋት ለማገልገል አብሮን በመሰለፉ ደስታ ይሰማናል በማለት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የ2018 ዓ.ም የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ መታሰቢያ በዓልን አስመልክቶ በአዲስ አበባ ስታዲየም ያዘጋጀው መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት ተካሂዷ...
12/04/2026

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የ2018 ዓ.ም የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ መታሰቢያ በዓልን አስመልክቶ በአዲስ አበባ ስታዲየም ያዘጋጀው መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ ላይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ከንቲባ ክብርት ዶክተር አዳነች አብቤ፣ ክብርት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች ካውንስል ጠቅላይ ጸሐፊ ፓስተር ዶክተር ጌትነት ለማ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ፣ ፓስተር ደሳለኝ አበበ እንዲሁም የሰሜን አሜሪካ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የቦርድ ሰብሳቢ ፓስተር ሄኖክ ጸጋዬ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።

የተለያዩ መንፈሳዊ መርሐ ግብሮች በተካሄዱበት በዚህ ፕሮግራም ፓስተር ጻድቁ አብዶና ፓስተር ዘሪሁን ደጉ የመግቢያ ጸሎት ያደረጉ ሲሆን፣ በማስከተል፣የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ፓስተር ደሳለኝ አበበ፣ ለተለያዩ ተቋማት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ካቀረቡ በኋላ በዚህ ዓመት እያከበርን ያለነው የትንሳኤ በዓል በኅብረቱ ሃምሳኛ ዓመት ምሥረታ ማግስት መዋሉ ታሪካዊ ያሰኘዋል ብለዋል። አክለውም፣ የበዓሉ ዋነኛ እንብርት ከሆነው ከክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ፣ ሌሎች ያደረጉብንን ማሰላሰል ሳይሆን፣ የተደረገልንን ማሰብ እንደሆነ አመላክተዋል። ክርስቶስ ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለወዳጆቹ ያሳየው የተወጋው ጎኖን እንጂ የሰቀሉትን ሰዎች አለመሆኑን፣ ሰላምን እንጂ ጠላትነትን አለመስበኩን፣ በክህደት የሸሸውን ሰው የትንሳኤው ምስክር ማድረግን እንጂ በክህደት ተግባሩ አለማሸማቀቁን አስታውሰው፣ የትንሳኤው ዐውድ መቁረስን ሳይሆን መቆረስን፣ መቀበልን ሳይሆን መስጠትን፣ ክብር መፈለግን ሳይሆን ማክበርን አሳይቶናል፤ የመኖሪያ አድራሻችን በክርስቶስ ውስጥ፣ ዜግነታችንም ሰማያዊ እንዲሆን መሥዋዕትነትን ከፍሏል ብለዋል።

በማስከተል የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ደረጀ ታፈሰ፣ ለክብር እንግዶችና ለፕሮግራሙ መሳካት ሁነኛ አስተዋፅዖ ላደረጉ ሁሉ ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ፣ ከማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 16 ከቁጥር 1-5 በማንበብ፣ የክርስቶስን አስከሬን ሽቱ ለመቀባት በማለዳ ወደ መቃብሩ የሄዱ እህቶች ትልቅ ጭንቀት የሆነው መቃብሩ ላይ የተገጠመውን ድንጋይ ማን ያንከባልልልናል የሚል ቢሆንም፣ ወደ መቃብሩ በቀረቡ ጊዜ ግን ድንጋዩ ተንከባሎ እንዳገኙት፣ሮ በመንገዳችን ላይ የተጋረጠው የተስፋ መቁረጥ ድንጋይ እንዲሁ በጌታ ኃይል እንደሚከባለል ገልጸዋል፣

አስከትለውም፣ ክርስቶስ ባልንጀራን ስለ መውደድ አስተማረን እንጂ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረውን ሰው ስለመግፋት አልነገረንምና ህዝባችንን በሃይማኖትም ሆነ በዘር ለማጣላት እና ለማጋጨት የሚደረገውን ማናቸውንም ተግባር ኅብረቱ በጽኑ የሚቃወም መሆኑን ገልጸዋል።

መጋቢት 8 ቀን 20015 ዓ.ም የፓስተሮች ኮንፍራንስ በተካሄደበትና ግብረሰዶማዊነትን አስመልክቶ ኅብረቱ አቋሙን ባሳየበት መግለጫ፥ "ምንም ዓይነት ዲሞክራሲያዊ ይኹንታን ይዞ ቢመጣ ግብረሰዶማዊነት ኃጢአት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚነግረን እኛም ይህን ቃል እውነት እንደሆነ እናምናለን። ይሁንና በዚህ የኃጢአት ልምምድ ውስጥ የወደቁ ወገኖቻችን ተፈጥሮአዊ ወደ ሆነው የጾታ ሥርዓት እንዲመለሱ እናስተምራለን፣ ወደ እግዚአብሔር እውነት እንዲመለሱ እንጸልያለን፣ በፍቅርም እንሠራለን" የሚለው መግለጫ ዛሬም እንዳልተለወጠ አሳውቀዋል።

በማስከተል ክርስቶስ ስለመወለዱ፣ ስለሞቱና ስለትንሳኤው የተናገረው ትንቢት እንደተከናወነ፣ እንዲሁ ስለምፅአቱ የተናገረው ትንቢት ይፈጸማልና ጌታችን ተመልሶ ይመጣል። እኛም የወንጌሉን አገልግሎት በማጽናት ምፅአቱን መጠባበቅ ይገባናል ሲሉ ተናግረዋል። በመጨረሻም በፊታችን ያለው አገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ የመጸለይ ኃላፊነት እንዳለብን፣ እንደ ዜጋም የመምረጥ መብታችን እንድንጠቀም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

አስከትሎ የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች ካውንስል ጠቅላይ ጸሐፊ ፓስተር ዶክተር ጌትነት ለማ፣ ባተላለፉት መልእክት፣ በዚህ ስፍራ መሰብሰባችን ሞትን ድል አድርጎ የተነሳውንና በአብ ቀኝ በክብር የተቀመጠውን የክርስቶስን ትንሳኤ ለማሰብ እንጂ ለሌላ ዓላማ እንዳይደለ አስገንዝበው፣ በዚህ ባለንበት ወቅት እንደ አንድ አባት ልጆች በአንድ መንፈስ ልንያዝና ልንቆም ይገባናል ሲሉ ተናግረዋል።

በሰሜን አሜሪካ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ቦርድ ሰብሳቢ ፓስተር ሄኖክ ጸጋዬ ቃለ እግዚአብሔርን ያቀረቡ ሲሆን፣ በስብከታቸውም በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ በአንድ ሐረግ የተገለጡ ሁለት ቃላት፣ አሉታዊ ነገሮችን ወደ አዎንታ የለወጡ መሆናቸውን ገልጸው፣ በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ የተጠቀሰውና፣ "እግዚአብሔር ግን" የተሰኘው ሐረግ አሉታዊ ዓረፍተ ነገርን አስከትሎ የመጣ እንደሆነ፣ ሞትን ወደ ሕይወት፣ ዝለትን ወደ ብርታት፣ ተስፋ መቁረጥን ወደ ባለተስፈኝነት እንደሚቀይር ተናግረዋል። አያይዘውም፣ በተለይ የተቆረጠን ተስፋ የሚቀጥል አምላክ በዚህ አሠራሩ ዳግመኛ ዕድል እንድናገኝ ካደረገ፣ ይህ ሁለተኛ ዕድል ከእኛ እንዳይወሰድ፣ ከክፋት እና ከኃጢአት በራቀ መንገድ ህዝቡን ልንመራና የእግዚአብሔርን አሳብ ልናገለግል ያስፈልጋል ብለዋል።

በማጠቃለያው ፓስተር ደረጀ ታፈሰና ዘማሪ አውታሩ ከበደ የጸሎት ፕሮግራሙን የመሩ ሲሆን፣ በዚህም ለአገራችን ኢትዮጵያ አጥብቆ ጸሎት ተደርጓል። አስከትሎም የትንሳኤውን ጌታ የራሳቸው ጌታ ላላደረጉ ሰዎች የንስሀ ጥሪ ተደርጎ፣ በርካቶች ይህን የሕይወት ጥሪ በመቀበል በክርስቶስ የመሥዋዕትነት ሥራ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ፣ ዘማሪ አውታሩ ከበደ፣ ዘማሪት ቤተልሔም ወልዴ፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ ዘማሪ ዮሴፍ አያሌውና ዘማሪ ድንበሩ ባይለየኝ ዝማሬዎቻቸውን ሲያቀረቡ፣ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የአዲስ አበባ ክልል ዋና ጸሐፊ ፓስተር ሙላቱ ኤርምያስ ደግሞ መድረኩን በማስተናበር አገልግለዋል።

ሚያዝያ 4 ቀን 2018 ዓ.ም

11/04/2026
ዓርብ ሚያዝያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም በማለዳው ክፍለ ጊዜ ፓስተር ጻድቁ አብዶ፣ ፓስተር   ዶ/ር አሳየኸኝ በርኸና ፓስተር አሹ መልእክቶቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ "አገልጋይና ትህትና፣ አገልጋይ...
25/04/2025

ዓርብ ሚያዝያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

በማለዳው ክፍለ ጊዜ ፓስተር ጻድቁ አብዶ፣ ፓስተር ዶ/ር አሳየኸኝ በርኸና ፓስተር አሹ መልእክቶቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ "አገልጋይና ትህትና፣ አገልጋይና ባለአደራነት፣ እንዲሁም ሚሽን ዋነኛው ጉዳይ፤" የተሰኙ ነጥቦች ዋና ትኩረት አግኝተዋል።

የተሰኘውን የቴሌግራም ቻናል ቤተኛ በማድረግ የጉባኤውን መረጃዎች ይጋሩ።

Address

Addis Ababa
8783

Telephone

+251113717777

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Evangelical Churches Fellowship of Ethiopia posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share