13/08/2026
"መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ላይ ናቸው፤ ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወዳቸዋል።" (መዝ. ፹፮፥፩-፪)
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነትና ሥርዓት መሠረት ነሐሴ ፯ ቀን የሚከበረው "ጽንሰታ ለማርያም" ከእመቤታችን ከ፴፫ቱ በዓላት አንዱና ዋነኛው ነው። ይህ በዓል የሰው ልጅ የመዳን ተስፋ የተጀመረበት፣ ለአዳም የተሰጠው የ፭ ሺሕ ፭ መቶ ዘመን የተስፋ ቃል መሠረት የተጣለበት ታላቅ የመንፈሳዊ ደስታ ቀን ነው።
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላጆች ቅዱስ ኢያቄም (ከነገደ ይሁዳ/ቤተ መንግሥት) እና ቅድስት ሐና እግዚአብሔርን የሚወዱ፣ በሕጉ የሚኖሩ ደጋጎች ነበሩ። ነገር ግን ልጅ አጥተው ይኑሩ ስለነበር፣ ዕለት ዕለት ወደ ቤተ እግዚአብሔር እየሄዱ ለዓይናቸው ማረፊያ፣ ለልባቸው ተስፋ የሚሆን ልጅ እንዲሰጣቸው ይለምኑ ነበር።
አንድ ቀን አዝነው ሲጸልዩ ውለው ሲመለሱ፣ ርግቦች ከልጆቻቸው ጋር ሲጫወቱ አይተው ቅድስት ሐና፦ "አቤቱ ጌታዬ ግዕዛን ለሌላት እንስሳ ልጅ የሰጠህ አምላክ ምነው ለእኔ ልጅ ነሣኸኝ?" ብላ ምርር ብላ በማልቀስ ከባሏ ከቅዱስ ኢያቄም ጋር ወደ ሱባኤ ገቡ።
ሐምሌ ፴ ቀን በሱባኤያቸው ፍጻሜ ሁለቱም ድንቅ ራእይ አይተው ተነጋገሩ፦
• የቅዱስ ኢያቄም ራእይ፦"ሰባቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ" አለ።
◦ ትርጓሜው፦ ወፍ የተባለው አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን፤ ነጭነቱ ንጽሐ ባሕርዩ ነው። በራሱ ላይ መቀመጡ የሰውን ባሕርይ ባሕርይ እንደሚያደርግ ያመለክታል።
• የቅድስት ሐና ራእይ፦"ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ፣ ከራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማሕፀኔ ስትተኛ አየሁ" አለች።
◦ ትርጓሜው፦ ርግብ የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስትሆን፤ ነጭነቷ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋና ዘላለማዊ ድንግልናዋ ነው። በጆሮዋ ገብታ በማሕፀኗ መተኛቷ ደግሞ የብሥራተ ገብርኤልን ቃል በጆሮዋ ሰምታ አምላክን የምትፀንሰውን ንጽሕት ርግብ (ድንግል ማርያምን) የምትወልድ መሆኑን ያበስራል።
ራእዩን ካዩ በኋላ ወንድ ልጅ ቢወልዱ ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ እንዲሆን፣ ሴት ልጅም ቢወልዱ ማይ ቀድታ፣ መሶበ ወርቅ ሰፍታ፣ መጋረጃ ፈትላ ካህናትን እንድታገለግል ስእለት ተሳሉ። ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስም ስእለታቸውን አሳረገላቸው።
ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና ከራእዩ በኋላ አልጋ ምንጣፍ ለይተው እስከ ሰባት ቀን ድረስ ለየብቻቸው ሰነበቱ። ነሐሴ በባተ በሰባተኛው ቀን (ነሐሴ ፯) መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል፦ "ከሰው የበለጠች፣ ከመላእክት ሁሉ የከበረች ልጅ ትወልዳላችሁ" ብሎ አበሰራቸው። እመቤታችንም በፈቃደ እግዚአብሔር፣ በብሥራተ መልአክ ነሐሴ ፯ ቀን ተፀነሰች።
የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት የእመቤታችንን መፀነስ በተለየ ቅድስና ይገልጹታል፦
"ድንግል ሆይ! በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለሽም፤ በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ።" — አባ ሕርያቆስ (ቅዳሴ ማርያም)
አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ (በመጽሐፈ አርጋኖን)፦"የእግዚአብሔር የጸጋ ልጆችና የቅድስት ቤተክርስቲያን ማኅበሮች ሆይ! ይህቺን የተባረከችና የተመረጠች ሙሽራ የወለዱልንን ኢያቄምንና ሐናን እናመስግናቸው" ብሏል።
አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም (በማኅሌተ ጽጌ)፦"ሐና አንቺን የፀነሰችባት የደስታ ቀን ምን ያህል የተባረከችና የተቀደሰች ናት! ሟች ኢያቄምም ለሕይወት አንቺን ያፈራባት ቀን ምን ያህል የተቀደሰች ናት!" በማለት አድንቀውታል።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተፀነሰችበት ቀን (ነሐሴ ፯) ጀምሮ በዘጠኝ ወር ከነሐሴ ፭ ቀን በኋላ ግንቦት ፩ ቀን ተወልዳለች። የጽንሰቷ በዓል የሰው ልጅ የመዳን ተስፋ ማዶ የታየበት፣ የምሕረት ደመና የተዘረጋበት ታላቅ በዓላችን ነው።
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከትና ረድኤት፣ የአባቶቻችን የቅዱስ ኢያቄምና የቅድስት ሐና ጸሎት ከሁላችን ጋር ይሁን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
#እመቤታችን #ተዋሕዶ #ቤተክርስቲያን