28/07/2023
✝ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ✝
✝ #ሐምሌ ፳፪ (22) ቀን።
❤ እንኳን ለታላቁ ለሆኑት ለእውነተኛ ለኢትዮጲያዊው ጻድቅ ቀን መታሰቢያ በዓልና ዝዋይ ቅዱስ ገብርኤል የካህናት ማሰልጠኛን ለመሰረቱን ካልዕ ዕረፍት ቀን መታሰቢያ በሰላም አደረሰን።
✝ ✝ ✝
✝ ኢትዮጵያዊው ሰማዕት ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ፦ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ ሰማዕት የሆኑት አቡነ ጴጥሮስ በ1875 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ ተወለዱ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ በሰማዕትነት እንደሚሞቱ አስቀድመው መምህራቸው በትንቢት ነግረዋቸው ነበር፡፡ "አለቃ ተጠምቀ" የተባሉ ቅድስናን ከሊቅነት ጋራ አስተባብረው የያዙ የቅኔ መምህራቸው አንድ ቀን አቡነ ጴጥሮስን ጠርተው "ኀይለ ማርያም አንተ ወደፊት ጳጳስ ትሆናለህ፤ በወቅቱም አረመኔ በዚህች ሀገር ይሠለጥናል፡፡ ታዲያ ያኔ አንተ ለነፍስህ ሳትሳቀቅ በሰማዕትነት እለፍ፤ ሰማዕትነት ክፍልህ ነው፣ አደራ" ብለዋቸው ነበር፡፡ ይኸውም ትንቢት ደርሶ አቡነ ጴጥሮስ በሰማዕትነት ለማረፍ በቅተዋል፡፡
✝ ብፁዕ አባታችን የጵጵስና ስማቸውን ከማግኘታቸው በፊት መመህር ኀይለ ማርያም ይባሉ ነበር፡፡ በልጅነታቸው ወላጆቻቸው ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመውሰድ በሃይማኖትና በምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ አድርገዋቸዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓተ ትምህርት ከንባብ እስከ ቅኔ ያሉትን ትምህርቶች በሚያስገርም ፍጥነት ከተማሩ በኋላ ወደ ቅኔው አውድማ ጎጃም በመሄድ በሸዋራ የቅኔ ትምህርታቸውን ፈጽመው መምህር ሆነዋል፡፡ የዜማውንም ትምህርት ወደ ጎንደር ሄደው ተምረዋል፡፡ በመቀጠልም ወሎ ቦሩ ሜዳ ላይ ወንበር ዘርግተው የመጻሕፍትን ምሥጢር ይመግቡ ወደነበሩት ወደ ሊቁ አካለ ወልድ ዘንድ በመሄድ ዋና ዋናዎቹን የመጻሕፍት ትርጓሜ ማለትም ብሉያትን፣ ሐዲሳትንና ሊቃውንትን በሚገባ አሒዱ፡፡
✝ ከዚህ በኋላ በ1900 ዓ.ም ወሎ አምሐራ ሳይንት ሄደው በምስካበ ቅዱሳን ገዳም ገብተው ወንበር ዘርግተው ለ9 ዓመታት ቅኔንና መጻሕፍትን አስተማሩ፡፡ በ1910 ዓ.ም ወደ ደብረ ሊባኖስ መጥተው ሥርዓተ ምንኩስናን ፈጸሙ፡፡ ከዚያም መምህርነት ተሹመው ደብረ መንክራት ምሁር ኢየሱስ ገዳም ሄደው ለ6 ዓመታት ካስተማሩ በኋላ በ1916 ዓ.ም እንደገና በዝዋይ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም በመምህርነት ተሹመው ለ3 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በ1919 ዓ.ም ወደ አ.አ በመምጣት የመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ መምህርና በቤተ መንግሥት የግርማዊ ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ የንስሓ አባት ሆኑ፡፡
✝ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ በራሷ ተወላጅ ጳጳሳት ልጆቿ እንድትመራ ከ1600 ዓመታት በኋላ ስለተፈቀደላት ከዚህ በኋላ በሃይማኖታቸውና በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው አምስት ደጋግ አባቶች ሲመረጡ አንዱ አቡነ ጴጥሮስ ነበሩ፡፡ በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የራሷን ጳጳስ ስትሾም አቡነ ጴጥሮስ ግንቦት 18 ቀን 1921 ዓ.ም ጵጵስና ተሾሙ፡፡ ከዚህም በኋላ ብፁዕ አባታችን "አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምሥራቀ ኢትዮጵያ ተላዌ አሠሩ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዐ" ተብለው በያኔው መንዝና ወሎ ሀገረ ስብከት ተሾሙ፡፡
✝ ብፁዕ አባታችንም ቅድስት ቤተ ክርስቲያንንና ቅድስት ሀገራችን በጸሎታቸው፣ ሕዝቡን በትምህርታቸው እየጠበቁ በተጋድሎ እየኖሩ ሳለ አረመኔው የኢጣሊያ ፋሺስት በ1928 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ጦርነትን አውጆ ሕዝቡን በግፍ ይገድል ቤተ ክርስቲያንን ያቃጥል ጀመር፡፡ በየገዳማቱ እጅግ በርካታ ካህናትና መነኮሳት ተገደሉ፣ ብርቅዬ የቤተ ክርስቲያን ቅርሶች ተዘረፉ፡፡ አቡነ ጴጥሮስም ይህንን ግፍ በማየታቸው ከሀገራችን አርበኞች ጋር በመሆን በጸሎታቸው ሊዋጉት ተነሡ፡፡ አባታችን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ተከትለው ወደ ሰሜን ጦር ግንባር ማይጨው ዘምተዋል፡፡ ፋሺስቱ በማይጨው በመርዝ የተደገፈ ጦርነት ከማድረጉ የተነሣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሲበታተንም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ወደ አ.አ የተመለሱት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደው ለአገርና ለነፃነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን ለሠላሌ አርበኞች በሚገባ አስተምረዋል፡፡
✝ በደብረ ሊባኖስ ጫካዎች ውስጥ መሽጎ የነበረው የእነ ደጃዝማች አበራ ካሣ አርበኛ ጦር እና በሸንኮራ በኩል መሽጎ የነበረው የእነ ፍቅረ ማርያም አርበኛ ጦር እንደሁም በምዕራብ ይመራ ከነበረው የእነ ደጃዝማች አባ ነፍሶ ጦር ሦስቱም በአንድ ጊዜ ወደ መሐል አ.አ በመግት አ.አ ላይ መሽጎ የነበረውን ፋሽስትን ለመውጋት ታቅዶ የነበረው ዕቅድ በመረጃ ክፍተት ምክንያት ውጤታማ ሳይሆን ቀረ፡፡ በተለያየ ጊዜ መሐል አ.አ እየደረሱ ማለትም በመጀመሪያ የእነ ፍቅረ ማርያም አርበኛ ጦር ለብቻው በኮተቤ አድጎ የካ ሚካኤል ላይ ሲድርስ ተመቶ ተመለሰ፤ ይሄኛው እንዳለቀ ቀጥሎ የእነ አባ ነፍሶ ጦር በባቡር ጣቢያ መጣሁ ቢልም በጠላት ጦር ድካሚ ተመቶ ተመለሰ፤ መጨረሻ ላይ የእነ ደጃዝማች አበራ ካሣ አርበኛ ጦር በእንጦጦ በኩል ቢመጣም እርሱም በጠላት ጦር ተመቶ ተመለሰ፡፡
✝ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ሦስቱም የአርበኞች ጦር በመረጃ ክፍተት ምክንያት እየተመታ ወደመጣበት ሲመለስ አቡነ ጴጥሮስ አብረው ከአርበኛው ጦር ጋር መመለሱን አልፈለጉትም ይልቁንም "ብችል ጠላት በኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ በቅርብ ርቀት ሆኖ የሚመለከተውን ሕዝብ በማትጋት በጠላት ላይ እንዲነሣ አደርገዋለሁ ካልሆነም ደግሞ እዚሁ እሞታለሁ" በማለት አባታችን ከአርበኞቹ ተነጥለው አ.አ ቀሩ፡፡ ይሁን እንጂ ጠላት በመላዋ ከተማ ያሰማራቸው ባንዳዎች አባታችንን እንዳሰቡት ሊያነቀሳቅሷቸው አልቻሉም ነበር፡፡ በመሆኑም አባታችን "የሀገሬን ሕዝብ ለጠላት እንዳይገዛ በአደባባይ አውግዤ ጠላትን ረግሜ በሰማዕትነት ባልፍ ይሻለኛል" ብለው ራሳቸውን ለጠላት አሳልፈው ለመስጠት ወሰኑና የፋሺስት ኢጣሊያ እንደራሴ ለሆነው ለራስ ኀይሉ ሄደው እጃቸውን ሰጡት፡፡ እርሱም ብፁዕ አባታችንን ወስዶ ለግራዚያኒ ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም አሳልፎ ሰጧቸው፡፡ ግራዚያኒም ግማሽ ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዲገደሉ ወሰነባቸው፡፡ አቡነ ጴጥሮስ በፈቃዳቸው እጃቸውን አሳልፈው ከሰጡበት ጊዜ ጀምሮ በጠላት የጥይት እሩምታ በሰማዕትነት እስካለፉበት ጊዜ ድረስ የነበረውን ሒደት ኮርየሬ ዴላሴራ የተባለው ጋዜጣ ወኪልና የምሥራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረው ፖጃሌ የተባለው ጋዜጠኛ እ.ኤ.አ ሰኔ 15 ቀን 1936 ዓ.ም በአዲስ አበባ በነበረ ጊዜ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ የተሰጠውን ፍርድና የተፈጸመውን የግፍ ግድያ ባየውና በተመለከተው መንገድ እንደሚከተለው ጽፎ ነበር።
✝ "ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም አቡነ ጴጥሮስ ተይዘው ወደ ግራዚያኒ ቀረቡ፡፡ በዚህ ጊዜ አቡነ ቄርሎስ የተባሉት ግብፃዊ ጳጳስ ቀርበው "ለእስክንድርያው መንበረ ፓትርያርክ ምክር ቤት ሳታሰማ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ እንዳች ነገር ማድረግ አይገባህም" ሲሉ ለግራዚያኒ ነገሩት፡፡ አቡነ ቄርሎስ ይህን ማለታቸው በዲፕሎማቲክ ደረጃ ለዓለም ለማሰማትና የአቡነ ጴጥሮስን ሕይወት ለማትረፍ አስበው ነበር፡፡ ነገር ግን ግራዚያኒ የአቡነ ጴጥሮስ የሞት ፍርድ እንኳንስ እስከ ግብጽ ከአ.አ ውጭ እንኳ ከመሰማቱ በፊት በግማሽ ቀን እንዲፈጸም መመሪያ አስተላላፈ፡፡