07/02/2023
በጸሎትም በችሎትም
~የእግድ ውሳኔውን ለመስማት የፊታችን ረቡዕ ተቀጥሯል
የፍርድ ቤቱን ውሎ ጠበቆች በዝርዝር አስረድተዋል
ክስ ከመመስረቱ አስቀድሞ የሰው ሕይወትና የንብረት ውድመትን ለመታደግ ይቻል ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በውግዘት ከሕብረቱ የለያቸው ግለሰቦች እና ቡድኖች የቤተክርሲያኒቱን ህጋዊ ይዞታዎችን በኃይል ለመንጠቅ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እገዳ እንዲጣልበት ለፍርድ ቤቱ በዝርዝር ማስረዳታቸውን ገልጸዋል።
የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አሟልቶ ክሱን ለመመስረት ከሶስት ወር የማያንስ ጊዜ የሚጠይቅ መኾኑን ለፍርድ ቤቱ ያብራሩት ጠበቆቹ፤ በዚህ የጊዜ ሂደት ውስጥ በእየአንዳንዱ ቀን የሰው ሕይወት እየጠፋ እንዳይሔድ በውግዘት የተለዩት ግለሰቦች ላይ ጊዜያዊ እግድ እንዲጣል እና በተከሳሽነት ስሙ የተጠቀሰው መንግስት ህግ የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውን አብራርተዋል።
ፍርድ ቤቱ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ችሎቶች በተሻለ መልኩ አፋጣኝ የኾኑ አገልግሎቶችን እንደሰጣቸው እና በዛሬው የችሎት ውሎ የፍርድ ቤቱ ቀልጣፋ አገልግሎት ምስጋና ሊቸረው የሚገባ መኾኑን ጠበቆቹ ገልጸዋል።
ፍርድ ቤቱ የእግድ ጥያቄውን አስመልክቶ በርካታ ማብራሪያዎች ጠይቆ ምላሾችን መስጠታቸውን በዝርዝር አብራርተዋል።
ከ1፣30 ሰዓት በላይ የዘለቀ ማብራሪያቸውን ያደመጠው ፍርድ ቤቱ የችሎት ውሎው ቅጂ በጽሑፍ ተገልብጦ ነገ ከእኩለ ቀን አስቀድሞ እንዲደርሰው ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ በአስቸኳይ እግዱ ላይ ውሳኔ ለመስጠት የፊታችን ረቡዕ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ/ም ከቀኑ 8፣00 ሰዓት ላይ ቀጠሮ ሰጥቶ የዕለቱ የችሎት ውሎ ማጠናቀቁን አብራርተዋል።
ከፍርድ ቤቱ ውሎ ገለጻ ባሻገር የሕግ ባለሙያዎች ቡድን አባል የኾኑት የቤተክርስቲያኒቱ ጠበቃ አቶ አያሌው ቢታኒ የቤተክርስቲያኒቱ የበላይ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ባሰተላለፈው የምሕላ አዋጅ መሰረት በጾመ ነነዌ ሶስቱ ቀናት ከቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች የተላለፈው ትዕዛዝ የጾም የጸሎት የምህላ እና ጥቁር የመልበስ ትዕዛዛት ብቻ መኾኑን አስታውሰው፤ ከዚህ ውጪ ምንም አይነት የተለየ መልዕክቶችን የማስተላለፍ ትዕዛዝ እንዳልተሰጠ አስረግጠው በማስታወስ ምዕመናኑ በታዘዘው ብቻ እንዲጸኑ ጥሪ አቅርበዋል።
ከጥቁር መልበስ ትዕዛዝ ጋር በተያያዘ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት በህጋዊ ደብዳቤ ጭምር እገዳ ለመጣል የተሞከረው እንቅስቃሴ የእምነቱን ነጻነት እና የ
ግለሰቦች ያሻቸውን የመልበስ መብት የሚጋፋ እንቅስቃሴ መኾኑን እንደ ሕግ ባለሙያነታቸው የሚታዘቡት መኾኑን ገልጸው በቀጣይ በክስ ዝርዝር ውስጥ መካተት አለመካተት ይገባዋል በሚለው ቀሪ ስራዎችን እንደሚኖሯቸው ገልጸው መግለጫውን አጠናቀዋል።
(በወፍ በረር የለቀምኳቸው በመኾኑ ቃል በቃል አልተጻፈም)