27/09/2022
መስቀል አደባባይን የመስቀል አደባባይ ማድረግ አለብን - (ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ)
እንደሚታወቀው መስቀል የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ በዓልዋ መሆኑ የታመነ ነው፡፡ ሆኖም የመስቀል በዓል ከመንፈሳዊ በዓልነቱ ይልቅ ፌስቲቫላዊ ቅርፁ በጣም የሚያይል አከባበር ያለው በዓል ነው፡፡
እንደሚታወቀው በበዓሉ ዕለት ቤተ ክርስቲያን ከምትጠቀምበት ሰዓት ይልቅ የተለያዩ የፖለቲካ ሰዎችና ተጋባዥ እንግዶች ርዝመቱ የማይገመት ንግግር የሚያደርጉበት ሰዓት ይበዛል፡፡ የቤተ ክርስቲያንዋም አካላትም ከመንፈሳዊ ስብከት ይልቅ መንግሥትንና ተጋባዥ ዲፕሎማቶችን ማእከል ያደረገ ‘የተከበሩ አቶ እገሌ’ የሚበዛው ንግግር ሲያደርጉበት ይስተዋላል፡፡ በዓለ መስቀልም ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ለመዳሰስ ሰበብ ሆኖ ያገለግላል እንጂ ወደ አደባባዩ መጥቶ ስለ ጌታችን መስቀል ምንም ዓይነት ነገር ሰምቶ የሚሔድ ምእመን የለም፡፡
በደርግ ዘመን እንኳን ከብዙ ችግር ጋር እነ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የሰበኩት ‘ዮም መስቀል ተሰብሐ’ የሚል ስብከት ተጠቃሽ ነበር፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ግን መስቀል አደባባይ ላይ የሚተላለፉ መልእክቶች እንዴት በዓሉን ከወቅታዊ ትኩሳት ጋር እናስተሳስረው በሚለው ላይ ብቻ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ከዚያ ውጪ መስቀል አደባባይ በአግባቡ ምሕላ እንኳን ደርሶበት አያውቅም፡፡ ሐቁን ለመናገር እንደ መስቀል በዓል አከባበርም መስቀሉን የሚቀብር ተራራ የለም፡፡
የምእመናን በዓል እንደመሆኑ ከውጪ የሚመጡ እንግዶች ሕዝቡ በዓሉን ሲያከብር መመልከት ሲገባቸው በመስቀል አደባባይ ግን ሕዝቡ የውጪ እንግዶች በዓሉን ሲያከብሩ ከሩቅ ሆኖ ይመለከታል፡፡ ነፋስ የሚያማታውን የስፒከር ድምፅ እየተከተለ ጭብጨባ ሲሰማ ያጨበጭባል፡፡ የአደባባዩ መርሐ ግብር አስተዋዋቂ አሁን እንዲህ እየተከናወነ ነው ሲል እየሰማ ሥፍራው ላይ ያለው ሕዝብ በቤቱ በቴሌቪዥን ከሚመለከተው ሰው ያነሰ መረጃ ኖሮት ተደናብሮ ይመለሳል፡፡ አንዳንዴም ደመራው ቶሎ አልበራ ሲለው በፉጨትና በጭብጨባ ፍጠኑ ይልና ሕዝቡ ራሱ ጧፍ በመለኮስ በዓሉን ያስጀምራል፡፡
አንድ ስብከት ሳይሰበክ ፣ አንድ መዝሙር በወጉ ሳይሰማ ሊቃውንቱ ፣ መዘምራኑ የኦሎምፒክ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት እንደሚታዩት አትሌቶች ምንም ሰዓት ሳያገኙ በጥድፊያ አልፈው እንዲያልፉ ይደረጋል፡፡ አብዛኛው የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣትና የማኅበራት መዘምራን መስቀል ሲመጣ እንደ ትልቅ አገልግሎት የሚያዩት ከበዓሉ ዕለት ይልቅ ለበዓሉ ሲዘጋጁ የሚያቀርቡትን ዝማሬና ወደ አደባባዩ እስከሚደርሱ ድረስ በመንገድ ላይ የሚዘምሩትን ዝማሬ ነው፡፡ የልዩ ልዩ ሚዲያ ጋዜጠኞችም መስቀሉን መቅበራቸው የተለመደ ነው፡፡ ‘የዘንድሮን የመስቀል በዓል ካለፈው ዓመት የተለየ የሚያደርገው ግድቡ በተገባደደበት ማግስት ላይ በመሆናችን ሲሆን’ የሚል ዘገባ ያቀርባሉ፡፡
አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ለቃለ መጠይቅ ያቀርቡና ‘መስቀል ከሃይማኖታዊነቱ ባሻገር ለሀገር የሚያበረክታቸው እሴቶች ምን ምን ናቸው?’ ‘የመስቀል በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡ ያለው ጠቀሜታ ምንድን ነው?’ የሚሉ በየዓመቱ እንደ ችቦው የማይቀሩ ችክ ምንችክ ያሉ ጥያቄዎችን ያቀርባሉ፡፡ በማግስቱም የመንግሥት ሚዲያዎች ስለ ክትፎ አሠራርና ስለ ቆጮ አዘገጃጀት ቀኑን ሙሉ ሲያብራሩና ዘፈን ሲጋብዙ ይውላሉ፡፡ ታሪኩን የማያውቅ ሰው ንግሥት እሌኒን የጉራጌ ንግሥት ፣ መስቀሉም ከክትፎ ውስጥ ተቆፍሮ የተገኘ ሊመስለው ይችላል፡፡
ብቻ በአጭሩ መስቀልን ሲያስታውስ አንድ ነገር ጨበጥሁ የሚል ሰው ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ደመራው የሚለኮስበት ውብ ሰዓት ላይ ብቻ ሕዝቡ በእልልታና በጧፍ እያጀበ ሰውነትን የሚነዝር ዝማሬ ያቀርባል፡፡ አሁን አሁን ቀረ እንጂ ደመራው የወደቀበትን አቅጣጫ እንደ ሀገሪቱ ፖለቲካ ኮምፓስ ቆጥሮ ወዴት ወደቀ ብሎ በጭንቀት የሚጠይቅም ብዙ ሰው አለ፡፡ ከዚያ በኋላ መስቀል አደባባይ ለሰዓታት ብቻ መስቀሉን አክብሮ አገልግሎቱ ያበቃል፡፡
ይህንን በማድረግ ፈንታ ቢያንስ ከዋዜማው ጀምሮ እንኳን ቤተ ክርስቲያን አደባባዩን መጠቀም መቻል አለባት፡፡ ዓለምን ያስደመሙት የኢትዮጵያ መስቀል ዓይነቶች ለሀገር ውስጥና ለውጪ ጎብኚዎች በዐውደ ርእይ የሚታዩበትና ለሽያጭ የሚቀርቡበት ፣ የኢትዮጵያ የመስቀል ዐውደ ጥናት የሚካሔድበትና በዘርፉ ላይ ጥናት የሠሩ ባለሙያዎች ጥናት የሚያቀርቡበት ፣ የቤተ ክርስቲያንዋ የያሬዳዊ ዜማ ሀብታት በአደባባይ የሚታዩበት ፣ በዕለቱ ተካልበው የሚያልፉት የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በዋዜማው ምሽት አደባባዩን ሞልተው ዋዜማውን በዝማሬ የሚያሳልፉበት ፣ በዕለቱ የሚቀርበውም ትርዒት የተመጥነና ለሕዝቡ ትደራሽ እንዲሆን በባለሙያዎች የታገዘ ቢሆን ፣ ቤተ ክርስቲያንዋ በበዓሉ ላይ ለሚገኘው ሕዝብ አንዳንድ የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራዎችን የምትሠራበት ሁኔታ ቢመቻች መስቀል አደባባይ እውነትም መስቀል አደባባይ መሆን ይችላል፡፡
ስለመስቀል አደባባይ ከጻፈው የተወሰደ - ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ