ተዋሕዶ ሚዲያ ኔትዎርክ-Tewahedo Media Network

ተዋሕዶ ሚዲያ ኔትዎርክ-Tewahedo Media Network Contact information, map and directions, contact form, opening hours, services, ratings, photos, videos and announcements from ተዋሕዶ ሚዲያ ኔትዎርክ-Tewahedo Media Network, Religious organisation, Addis Ababa.
(1)

ዛሬ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናቸን ከቀናት በፊት ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉ ሁለት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን በክብር የምትሸኝበት  ከባድ ቀኗ ነው። የብፁዕ አቡነ ባስልዮስ እና የብፁዕ ዶ/ር  አቡነ...
25/03/2023

ዛሬ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናቸን ከቀናት በፊት ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉ ሁለት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን በክብር የምትሸኝበት ከባድ ቀኗ ነው።

የብፁዕ አቡነ ባስልዮስ እና የብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ የሽኝት ስነ ስርዓት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ቤተሰቦቻቸው እና ምእመናን በተገኙበት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም እየተከናወነ ይገኛል።

የአባቶቻችን በረከት ይደርብን።

ፎቶ፦ የኢኦቴቤ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ

ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ

መጋቢት 1/2015 ዓ.ም በሥጋ እረፍት የተለዩንና ዛሬ መጋቢት 16/2015 ዓ.ም አስከሬናቸው ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በክብር አቀባበል የሚደረግለት የብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ሣልሳይ የሮቸስተር ቅድስት ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን የበላይ ጠባቂ የሕይወት ታሪክ ይህንን ይመስላል።

“መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ ሩጫዬንም ጨርሻለሁ፣ ሃይማኖቴን ጠብቄአለሁ፣ ከእንግዲህ ወዲህ የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶ ይጠብቀኛል” 2ኛጢሞ. 4፥6-8
ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ፡ በቀድሞ ስማቸው መ/ር ሐረገ ወይን በቀለ መሸሻ ከአባታቸው ከግራዝማች በቀለ መሸሻና ከእናታቻው ከወ/ሮ ደብሬ እንግዳ በ1939 ዓ/ም በቀድሞ አጠራር በጐጃም ጠቅላይ ግዛት በእንጅባራ ወረዳ ዳንጊያ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ ተወለዱ። ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በአካባቢያቸው በሚገኙ የአብነት ትምህርት ቤቶች በመግባት ፊደል፣ ንባብና የቃል ትምህርት እንዲሁም ከመሪጌታ ዴንሳ ወንድምሁነኝ፣ ጾመ ድጓ፣ ድጓ፣ መዋሥዕትና ዝማሬ በሰከላ ወረዳ ባሕር ዛፋ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አጥቢያ ተምረዋል።

መ/ር ሐረገ ወይን በቀለ የጾመ ድጓና የድጓ ትምህርታቸውን ወደ መምህርነት ደረጃ ለማሳደግ ስለፈለጉ ወደ ደጋ ዳሞት በመሄድ ከመሪጌታ ብርሃኑ ደግመው ከልሰዋል። መ/ር ሐረገ ወይን በቀለ ሁሉንም የአብነት ትምህርቶች ለመማር ባላቸው ጽኑዕ ፍልጎት ወደ ሰከላ ወረዳ ሮቢት ጽዮን በመሄድ ከመሪጌታ መሠረት ቅኔ ከነአገባቡ ተምረው አጠናቀዋል። በመቀጠልም የአቋቋም ትምህርታቸውን በባሕርዳር ከተማ ከሊቀ ኅሩያን ተስፋ ዳኘው በኋላም ወደ ጎንደር ደብረ ኃይል ወደብረ ጥብብ በዓታ ለማርያም ገዳም በመሄድ ከየኔታ ወላዴ አእላፍ ሔኖክ ወልደ ሚካኤል የአቋቋም ትምህርታቸውን በሚገባ አጠናቀዋል።

ከዚያም ወደ ባሕርዳር በመመለስ በወቅቱ የፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የደብሩ አስተዳዳሪ ከነበሩት ከታላቁ አባት መምህር አባ ኃይለማርያም አየለ ቅዳሴና ባሕረ-ሐሳብ ተምረዋል።

መምህር ሐረገ ወይን በቀለ ፍላጎታቸው ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል በመሆኑ የአብነት ትምህርታቸውን ካጠናከሩ በኋላ በ1959 ዓ/ም በባሕር ዳር ጣና ሐይቅ ክብራን ገብርኤል ገዳም በመምህር አባ ኃይለማርያም ምንኩስናን ተቀብለዋል።
መምህር አባ ሐረገ ወይን በቀለ ቤተ ክርስቲያንንና ምእመኖቿን በይበልጥ ለማገልገል ይችሉ ዘንድ በማሳብ ወደ ደብረ ማርቆስ በመሄድ ሥልጣነ ክህነት ከሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ ተቀብለዋል።

መምህር አባ ሐረገ ወይን በቀለ የአብነት ትምህርታቸውን ከተለያዩ መምህራን ካጠናቀቁ በኋላ ብስለታቸውንና እውቀታቸውን የተገነዘቡት የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው የሽንብጥ ሚካኤል አስተዳዳሪ አድርገው ሾመዋቸዋል።

መምህር አባ ሐረገ ወይን በቀለ የጊዜውን ትውልድ በሰፊው ለማገልገል ከአብነት ትምህርት በተጨማሪ በጊዜው እንደ እንግዳ ነገር የሚታየውን ዘመናዊ ትምህርት መቅሰም አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ቤተክርስቲያንን እያገለገሉ ጎን ለጎን የአስኳላ ትምህርት ቤት በመግባት ከ1ኛ እስከ 8ተኛ ክፍል ትምህርታቸውን በፋሲሎ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ ከ9 እስከ 12ኛ ደግሞ በጣና ሀይቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሚሰጠውን መደበኛ ትምህርት ተከታትለው ተመርቀዋል፡፡

መምህር አባ ሐረገ ወይን በቀለ የአብነት ትምህርትን ከዘመናዊ ትምህርት ጋር ማዛመዳቸውን የተገነዘቡትና በጊዜው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ለከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ወደ ጀርመን ልከዋቸው በጀርመን የሚጠበቅባቸውን የነገረ መለኮት ትምህርት ከጨረሱ በኋላ ለአገልግሎት ወደ ሀገር ቤት በመመለስ በተለያዩ ገዳማትና አድባራት በአስተዳዳሪነት አገልግለዋል።

ጥቂቶችን ለመጥቀስ ያህል፦ መልአከ ምሕረት በተባሉበት በድሬድዋ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን፣ በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሶዶሬ መድኃኔዓለም ገዳም፣ በምዕራብ ሸዋ መናገሻ ማርያምና በጋራው መድኃኔዓለም አንድነት ገዳም፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በኮተቤ ካራ አሎ መድኃኔዓለም እና ጻድቁ አቡነ ገሪማ ገዳም እንዲሁም የጉለሌ ጽርሐ አርያም ቅዱስ ሩፋኤል ደብር ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

መልአከ ምሕረት አባ ሐረገ ወይን በቀለ በተለያዩ አድባራት በአስተዳዳሪነት ካገለገሉ በኋላ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ተሹመው በሰሜን አሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ በሚገኘው ቅድስት ሥላሴና ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በአስተዳዳሪነት ለብዙ ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በተጫማሪም በባፍሎ መድኃኔዓለምና በሮቸስተር ቅድስት ኪዳነ ምሕረት አብያተ ክርስቲያናት አገልግለዋል።

መልአከ ምሕረት አባ ሐረገ ወይን በቀለ በኒውዮርክ ክፍለ ሀገር አገልግሎት ላይ እንዳሉ ቅን አገልግሎታቸው፣ መንፈሳዊነታቸውና የቤተክርስቲያን ዕውቀታቸው ታይቶ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ 4ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ጥር 11/ 1999 ዓ/ም ከሌሎች አባቶች ጋር በአንብሮተ ዕድ ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ተብለው ኤጲስ ቆጶስ ሆነው ተሹመዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ሣልሳይ ኤጲስ ቆጶስ ሆነው ከተሾሙ በኋላም የኒውዮርክ፣ ኒውጀርሲ፣ ቦስተንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በመሆን ለብዙ ዓመታት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በትጋትና በአባትነት ክብር ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
በዚህ የአገልግሎት ዘመናቸውም፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት፣ ዲቁናንና ቅስናን በመስጠት አገልጋዮች እንዲበዙ በማድረግ ፣ በሀገረ ስብከታቸው አብያተ ክርስቲያናትን በማቋቋም፣ ምእመናንን በማጽናናት መንፈሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በማከናወን ላይ እንዳሉ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሰሜን አሜሪካ ኒዮርክ ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ76 ዓመታቸው መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተዋል።

የብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ የሕይወት ታሪክ

#ውልደት
የቀድሞው አባ ኃይለ ማርያም መለሰ የኋላው ብፁዕ አቡነ አረጋዊ (ዶ/ር) ከአባታቸው ከሊቀ መዘምር መለስ አየነው ደስታና ከእናታቸው ከወ/ሮ ፀሐይ ገብረ አብ በሰሜን ጎንደር ደብረ ሰላም ሎዛ ማርያም አካባቢ በ1961 ዓ.ም ተወለዱ።

#ትምህርት
• ፊደል፥ ንባብ፥ ዳዊትና ቅዳሴ ከመርጌታ ሙሴ ብፅዐ ጊዮርጊስ ተምረዋል።
• ቅኔ፥ ከግጨው መንከር ምንዝሮ ተክለ ሃይማኖት፥ ሐዲሳት፥ ከመጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት ግምጃ ቤት ማርያም ተምረዋል።
• 1ኛና 2ኛ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዐፄ ፋሲል፡ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በዳግማይ ደብረ ሊባኖስ አዘዞ ተክለ ሃይማኖት ት/ቤቶች ተምረዋል።
• ከሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ በቴዎሎጂ ዲፕሎማ፥
• ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በቴዎሎጂ ዲግሪ፥
• ከኖርዌይ ስታቫንገር ስፔሻላይዝድ ዪኒቨርስቲ የማስተርስ ዲግሪ፥
• ከፕሪቶርያ ዩኒቨርስቲ በፍልስፍና የፒኤችዲ ዲግሪ አግኝተዋል።

#ቋንቋ
• ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ የኖርዌይ፥ የስዊድንና የዴንማርክ ቋንቋዎችን ይችላሉ፡፡


• ዲቁና - በ1968 ዓ.ም. ከብፁዕ አቡነ እንድርያስ (ቀዳማዊ) በወቅቱ የሰሜን ጎንደር ሊቀ ጳጳስ ተቀብለዋል፥
• ምንኵስና - በ1984 ዓ.ም. በታዋቂውና ጥንታዊው ገዳም ጎንድ ተከለ ሃይማኖት ተቀብለዋል፥
• ቅስና - ከብፁዕ አቡነ ያዕቆብ (ኤርትራዊ) በወቅቱ የሰሜን ጎንደር ሊቀ ጳጳስ ተቀበለዋል፥
• ቁምስና - ከብፁዕ አቡነ ገብርኤል በወቅቱ የምዕራብ ሸዋ ሊቀ ጳጳስ ተቀብለዋል።

#አገልግሎት
• በሆለታ ደብረ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት፥ በሆለታ ገነት ደብረ ኤዶም ቅዱስ ገብርኤል፥ በሆለታ ገነት ደብረ ሣህል መድኃኔ ዓለም፥ በወሊሶ ጻድቁ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አብያተ ክርስቲያናት በአስተዳዳሪነት ሠርተዋል።
• የወልመራ ወረዳ ቤተ ክህነት ምክትል ሊቀ ካህናት ሆነው በቅንንነት አገልግለዋል።

• በኖርዌይ ስታሻንገር መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪና የሕፃናትና ቤተሰብ መምሪያ የቦርድ ምክትል ሰብሳቢ በመሆን መርተዋል።

• የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የቦርድ አባል፡ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት የቦርድ አባል በመሆን እያገለገሉ አገልግለዋል።
• በቤተ ከህነት ጠቅላይ ጽ/ቤት ሲል በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ኃላፊ፥
• በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በመጀመሪያ የሪሰርችና ምርምር ኃላፊና አካዳሚክ ዲን፥ ም/ዋና ዲን በመሆን አገልግሎት ሰጥተዋል።
• የቅድስት ልደታ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የቦርድ አባል በመሆንም ሠርተዋል።
• በዓለም አቀፍ ተሳትፎ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ከርስቲያንን በመወከል የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማእከላዊ ኮሚቴ አባል፥ የመላው ኦርየንታል ኦርቶዶስ አብያተ ከርስቲያናትን በመወከል የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል በመሆን ተሳትፈዋል፡፡

• የመንበረ ፓትርያርከ ጠቅላይ ጽ/ቤት ምክትል ሥራአስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል።

«በጎ ነገር የሆነው ሁሉ ያለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ፍጻሜ ሊያገኝ አይችልም ተብሎ በተጻፈው መሠረት ምንም እንኳን ሁሉም ተመራጮች ቆሞሳት ከዕጩ ተወዳዳሪዎቻቸው ጋር የድምፅ ብልጫ በማግኘት ሊመረጡ የቻሉት በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ መሆኑ ቢታመንበትም ቅሉ ቆሞስ ዶ/ር ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ግን ከእጩ ተወዳዳሪያቸው ጋር እኩል ድምፅ አግኝተው የተመረጠት በዕጣ ስለሆነ በእሳቸው ምርጫ በይበልጥ እደ መንፈስ ቅዱስ እንዳለበት ያሳያል፡፡

ብፁዕነታቸው ከሹመታቸው በኋላ የቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት እና የውጪ ግንኙነት መምሪያ የበላይ ኃላፊ እና የድሬደዋና ጅቡቲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን ቅድስት ቤተክርስቲያን ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።

ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ያለፈውን ዓመት በሕመም ምክንያት በሀገር ውስጥ እና በውጪ ሀገር በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ትናንት መጋቢት 12 /2015 ዓ.ም በተወለዱ በ54 ዓመታቸው ከእዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል ።

የብፁዕ አባታችን በረከታቸው ይደርብን ።

ፎቶ:- መልአከ ሰላም አባ ኪሮስ ወልደ አብ
(የፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት)

+ ጊዮርጊስ ሆይ ከእኛ ወገን ነህን? + ወደ አድዋ ከዘመተው ሕዝብ አብዛኛው ባዶ እግሩን ነበር:: ዳዊት ጎልያድን ሊዋጋ ሲወጣ ከያዛት በትር በቀር አብዛኛው ሰው መሣሪያ አልታጠቀም:: አብዛ...
02/03/2023

+ ጊዮርጊስ ሆይ ከእኛ ወገን ነህን? +

ወደ አድዋ ከዘመተው ሕዝብ አብዛኛው ባዶ እግሩን ነበር:: ዳዊት ጎልያድን ሊዋጋ ሲወጣ ከያዛት በትር በቀር አብዛኛው ሰው መሣሪያ አልታጠቀም:: አብዛኛው ዘማች ባዶ እጁን የዘመተው ሁለት ነገር አስቦ ነው:: መሣሪያ ባይኖረውም በውጊያው መካከል ከጠላት ጦር መሣሪያ ነጥቄ እዋጋለሁ አለዚያም ከሚወድቁት ላይ መሣሪያ አንሥቼ እዋጋለሁ ብሎ ነበር:: በውጊያው መድፍ በጎራዴ እስከመማረክ ያደረሳቸውም ይህ ቆራጥነታቸው ነበር::

ለመንፈሳዊ ጥንካሬያቸው ደግሞ ምሥጢሩ አብራ የዘመተችው የቤተ ክርስቲያን ጸሎት እና ንጉሡ በድንግል ማርያም ስም ምለው የሠጡት አደራ ነበር:: ለተገፉ የሚቆመው ሰማዕቱ ጊዮርጊስም በግፍ ባሕር አቁዋርጠው በደሃ ሕዝብ ላይ እሳት ከሚያዘንቡት ከአባቱ ዘመዶች ከሮማዊያን ጋር ሳይሆን እንደ ዳዊት በትር ይዘው በእግዚአብሔር ስም ከወጡት ባለማተቦች ጋር በምልጃው ተሰልፎ ዋለ::

በዚያች ዕለት አንድ ጣሊያናዊ ቅዱስ ጊዮርጊስን አግኝቶ ኢያሱ ቅዱስ ሚካኤልን እንደጠየቀው "ከእኛ ወገን ነህ ወይንስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ? " ብሎ ቢጠይቀው ኖሮ "እኔ አሁን ከእግዚአብሔር ተልኬ መጥቻለሁ ይልቅስ የቆምክባት መሬት ኢትዮጵያ የተቀደሰች ናትና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ" ባለው ነበር::

የዐድዋ ዘማቾች ጾመኞች ነበሩ:: እንግሊዝም ጣሊያንም ሰይጣን ይመስል ኢትዮጵያን የተዋጉአት በዐቢይ ጾም ነበር:: "ወድቀህ ብትሰግድልኝ መንገድና ፎቅ እሰራልሃለሁ" ያለንን ጣሊያን አባቶቻችን "ሒድ አንተ ጣሊያን የራስህን እንጂ የእኔን አታስብምና" ብለው ድል ነሡት::

ዘማቾቹ የምግብ እጥረት ቢኖርም እንኩዋን ጾሙን ትተን ካልበላን አላሉም:: ድንገት መሞቴ አይቀር ብበላ ይሻለኛል ሳይሉ ተዋግተው ድል ተቀዳጁ:: እኛ በሰላም ጊዜ የምንተወውን ጾም እነርሱ በጦርነት ላይም ሆነው አልተዉትም:: በዚያ ድል ሀገሪቱ ለዐርባ ዓመት ከጦርነት ስታርፍ ለዕድሜ ዘመንዋ ደግሞ ከቅኝ ግዛት ዐረፈች::

ቅኝ ግዛት ብንገዛ ኖሮ ደሃ አንሆንም ነበር የሚል ሰው አይጠፋም:: ይህንን አሳብ የብዙ አፍሪካውያን ሀገራት ጆሮ አይስማው:: ዛሬ ነጻ ከወጡም በኁዋላ በባርነት ሕሊና የሚሰቃዩ ብዙ ናቸው::

ብዙ በፈረንሳይ የተገዙ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ዛሬም ድረስ በአደራ አስተዳደር በፈረንሳይ በእጅ አዙር ይተዳደራሉ:: በተባበሩት መንግሥታት ሳይቀር ቅኝ ገዢዎቻቸውን ተወካይ ሁነኝ ብለው የሚልኩ ሀገራት አሉ::

ዛሬም ድረስ በአንዳንድ አፍሪካ ሀገራት ጥቁሮች ሊስተናገዱ በተሰለፉበት ሱፐር ማርኬት አንድ ነጭ ከመጣ ሰልፍ ሳይይዝ ቅድሚያ ይስተናገዳል:: (በዓይኔ ያየሁት ነው)

ዛሬም ድረስ ብዙ አፍሪካዊያን ጥቁር በአስተሳሰብ ከነጭ በታች ነው ብለው ያምናሉ:: በዜኖ ፎቢያ የገዛ ወንድሞቻቸው አፍሪካውያንን የሚያሰቃዩ ደቡብ አፍሪካውያን ነጭ ሰፈር ግን ዝር አይሉም:: ሂሳብ ስታሰላ ሲያዩህ እንኩዋን አንተ ጥቁር ሆነህ እንዴት ያለ ካልኩሌተር መደመር ቻልክ የሚሉ ሰዎች ተፈጥረዋል::

በአውሮፓ በአሜሪካ ተወልደው አድገው ስኬታማ የሆኑት ጥቁሮች እንኩዋን የቤተሰብ ስማቸው ላይ አያቶቻቸውን በባርነት የገዛው ነጭ ገዥ ስም አብሮ ስለሚለጠፍ የዕድሜ ልክ የበታችነት ይሰማቸዋል:: አባቶቻችን ከብዙ ጣጣ አድነውናል አሁን ራሳችን የምንፈጥረውን ችግር ቢያዩ ለማመን የሚቸገሩ የሚሆኑትም ዘር ሳይለዩ አብረው የተዋደቁት ጀግኖች ናቸው:: ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬም ቤሩታዊት ኢትዮጵያን ከዘረኝነትና ጥላቻ ከመጨካከን ደራጎን ይታደጋት ዘንድ የምንማጸንበት ጊዜ ነው::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
የካቲት 23 2012 ዓ ም
ወላይታ ሶዶ ኢትዮጵያ

ፎቶ :- ሊባኖስ ቤሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤሩታዊትዋን ያዳነበትን ሥፍራ ተሳልሜ የተነሣሁት ነው::

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ!

ዜና ዕረፍት ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመቀሌ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ በዛሬው ዕለት የካቲት 21...
01/03/2023

ዜና ዕረፍት
ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመቀሌ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ በዛሬው ዕለት የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል በረከታቸው ይደርብን።

የብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የሕይወት ታሪክ

ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በክልል ትግራይ በማዕከላዊ ዞን በዓድዋ ወረዳ ልዩ ስሙ የሐ ደብረ ሐመልማል (መዝብር) በተባለው ቀበሌ ሚያዝያ 20 ቀን 1928 ዓ.ም ከአባታቸው ከአለቃ
ኃይሉ ወልደ ማርያምና ከእናታቸው እመት ዘነበች ወልደ ማርያም ተወለዱ፡፡

ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ ከአጎታቸው ከቄስ ገብረ ሕይወት ወ/ማር ያም ትምህርት ጀምረው ትምህርቱ እየገባቸው ሲሄድ ወላጆቻቸው መሪ ጌታ ተክለ ጊዮርጊስ ከሚባሉ መምህር አስገብተዋቸው ንባብና የቃል ትምህርት በማጠናቀቅ የግብረ ዲቁናን ትምህርት ተማሩ፡፡

ሆኖም የትምህርት ፍላጐታቸው እየ ተጠናከረ በመሄዱ የፈለጉትን ትምህርት ለመከታተል ከትውልድ አገራቸው ወጥተው ደብረ ዓባይ ወደሚባለው የመዝገበ ቅዳሴ ማስመስከሪያ የአብነት ቦታ ገዳም በመሄድ ምስክር ከሆኑት ሊቅ ከመምህር የኋላሸት መንገሻ ምዕራፍ ጾመ ድጓ፣ ባሕረ ሐሳብና የመዝገበ ቅዳሴን የዜማ ትምህርት ልኩን፣ አመሉንና ተቃራኒውን ለይተው ለመምህርነት በሚያበቃ ደረጃ ስለወሰነት በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡

ከዚያም በኋላ በዚሁ ገዳም ቅዳሴ እያስተማሩ ከመሪጌታ መጽሔት ቅኔ ተምረዋል፡፡ በዚህም ሳይወሰኑ የቅኔ ሞያቸውን ለማዳበር ከደብረ ዓባይ ተነሥተው ወደ ጎንደር ክፍለ ሀገር በመሄድ በሊቅነታቸው ከታወቁት ከመምህር አክሊሉ ገ/ሥላሴ ዘንድ ቅኔ ቤት ገብተው ለአምስት ዓመት ያህል ቅኔ ከነአገባቡ ከመማራቸውም በላይ የዳዊትንና የፍትሐ ነገሥትን ትርጓሜንም ከርሳቸው አሂደዋል፡፡

ከዚያም ወደነበሩበት ገዳም ወደ ደብረ ዓባይ ተመልሰው በዚያው ቅዳሴ እያስተማሩ ለ7 ዓመታት ያህል ከየኔታ የኋላሸት ጉባኤ መጻሕፍት ሐዲሳትን አሄደዋል፡፡ በዚህም ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው አቡነ መዝራዕተ ክርስቶስ ገዳም ወንበር ዘርግተው ጉባኤ አስፍተው ለ12 ዓመታት ያህል በአፍለኛው ጉባኤያቸው ጠንክረው በማስተማር ብዙ ዲያቆናትን፣ ቀሳውስትንና መምህራንን አፍርተዋል፡፡

ቀጥሎም መምህራቸው የኔታ የኋላሸት በ1962 ዓ.ም ታኅሣሥ 13 ቀን ስለ ዐረፉ በእሳቸው እግር ተተክተው ሲያስተምሩ ከቆዩ በኋላ የትግራይ ክፍለ ሀገር ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በመቀሌ ከተማ ያሠሩት ከፍተኛ መንፈሳዊ ኮሌጅ የካህናት ማሠልጠኛ አዳሪ ቤት ስለሆነ ለቤተ ክርስቲያናችን ብዙ ፍሬ የሚያፈሩ መሆናቸውን በመግለጽ ደጋግመው ስለጻፉላቸው፣ አስጠርተውም ስለነገሩዋቸው ቀደም ሲል ከቦታው አብረዋቸው ከየኔታ የኋላሸት የተማሩ አባት ቄሰ ገበዝ ገብረ ሊባኖስን ተክተው በ1963 ዓ.ም ወደ መቀሌ መጡ፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጉባኤ አስፍተው በከሳቴ ብርሃን ሰላማ መንፈሳዊ ኮሌጅና በደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል በማስተማር ላይ እንዳሉ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በ1975 ዓ.ም አገልግሎታቸውንና ትጋታቸውን ተመልክተው መልአከ ሰላም በማለት የመዐርግ ስም ሰጥተው በመምህርነታቸው ላይ በተደራቢነት የደብረ ሰላም ቅ/ሚካኤል ካቴድራል አስተዳዳሪ አድርገው ሾመዋቸዋል፡፡

በዚህ ካቴድራልም ለ22 ዓመታት በሰላም የኖሩ ሲሆን የማስተማሩ ሥራ እንደተጠበቀ በሳቸው አመራር በርካታ የልማት ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡

ጥቂቶቹንም ለመግለጽ የደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የተሠራ ቢሆንም ብዙ ነገር ይጎድለው ስለነበር
• አጥሩ በሚገባ እንዲታጠር፣
• በብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የተጀመረው ትልቁ ደወል ቤት ከፍጻሜ እንዲደርስ፣
• ትልቅ የሰንበት ት/ቤት አዳራሽ፣
• የብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ሙዝየም (ቤተ መዘክር)፣
• የቅዱስ ፓትርያርክና የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ ቤት፣
• የቤተ ክርስቲያኑ ቆርቆሮ እንዲቀየር፣ ምንጣፍ እንዲነጠፍ አድርገዋል፤ ሌሎችንም አስፈላጊ እድሳቶች አሳድሰዋል፤ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋይ ካህናትን መኖርያ ቤት አሠርተዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ልክ እንደስማቸው ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሰላም አባት በመሆን ለ22 ዓመት ሲያስተዳድሩ በካቴድራሉ አገልጋይ ካህናት ዘንድ እንዳያጥዋቸው ከመጨነቅ በቀር ምንም ዓይነት እክል ገጥሟቸው አያውቅም፤ የሰላም አባት የመሆናቸውን ያህል ሁሉም አባታዊ ፍቅር በተላበሰ መልኩ ያከብራቸዋል፤ ትእዛዛቸውን ያከብራል፤ ምክራቸውን ይቀበላል፣ በብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ዘንድ እንደ አስተዳዳሪ ማዘዝ ብቻ አይታሰብም፣ ‹‹ዘይከውን ሊቀ ይኩንክሙ ላእከ›› የሚለውን አምላካዊ ቃል በመከተል

• በልማት ሥራ፣
• በማኅሌት፣ በሰዓታት፣
• በቅዳሴ፣
• በስብከተ ወንጌልና በማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ከተራው አገልጋይ ቀድሞ መገኘት የዘወትር ተግባራቸው ነው፡፡

ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ከላይ እንደተጠቀሰው ሞያቸው የቅዳሴ ትምህርት ብቻ አይደለም፤ የመጻሕፍተ ሐዲሳት ሞያም ስላላቸው ለ33 ዓመታት ከሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ካሣ ጋር በመሆን የመዝሙረ ዳዊትን፣ የመጻሕፍተ ሐዲሳትን፣ የፍትሐ ነገሥትን እንዲሁም የውዳሴ ማርያምን፣ የቅዳሴ ማርያምን ጉባኤ በመምራት አንድ ቀን ሳይለዩ ትሕትናቸውን፣ ትዕግሥታቸው ንና መልካም ምሳሌነታቸውን ያሳዩ ተወዳጅ አባት መምህር ናቸው፡፡ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስም እጅግ አብልጠውና አልቀው ይወዱዋቸው ስለነበር ሁሉ ጊዜ ይጐበኛቸው ነበር፡፡

ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በታወቀው የመዝገበ ቅዳሴ ሞያቸው በተሰጣቸው የመዓዛ ክህነት ሀብት ልዩ ተሰጥዎ ያላቸው ድምፃዊ ከመሆናቸው የተነሣ ከጥንት ከአበው ሲያያዝ የመጣውን የደብረ ዓባይ ባሕል የቅዳሴ ዜማ አብነት ግእዙና ዕዝሉ እንዲሁም አራራዩና አንቀጹ ሳይቀር በሙሉ በዘመናዊ መሣሪያ የድምፅ መቅረጫ ቴፕ ተቀርጾ በቅርስነት ለትውልድ ይተላለፍ ዘንድ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ባዘዙት መሠረት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ድምፃቸው ተቀርጾ ተሰራጭቷል ፤ በዚህም ከፍተኛ አገልግሎት ለቤተ ክርስቲያን ማበርከታቸውን በመረዳት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የመታሰቢያ ስጦታ የአንገት አይከል ዕፀ መስቀል ሸልመዋቸዋል፡

ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በ1940 ዓ.ም ማዕርገ ዲቁናን ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ ጳጳስ ዘኤርትራ፤ በ1946 ዓ.ም መዐርገ ምንኵስናን ከመምህር ዘሚካኤል ዘደብረ ዓባይ ገዳም መምህር፣ (አበምኔት) በ1949 ዓ.ም መዐርገ ቅስናን ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል ዘጎንደር በ1969 ዓ.ም መዐርገ ቁምስናን ከብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ዘትግራይ ተቀብለው በእነዚህ ሁሉ የክህነት መዐርጋት መንፈሳዊውን አገልግሎት እየሰጡ በንጽሕና በድንግልና የኖሩ አባት ናቸው፡፡

ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ትሕትናን፣ አፍቅሮ ቢጽን፣ አክብሮ ሰብእን ዓላማ አድርገው የሚኖሩ በካህናት፣ በምእመናንና በተማሪዎቻቸው ዘንድ ተወዳጅነት ያላቸው፣ በአባትነታቸው ብዙ ፍቅርን ያተረፉ በአጠቃላይ በአርአያነታቸውና በገብረ ገብነታቸው በሁሉም ዘንድ ክብር ያገኙ ደግ አባት ናቸው፡፡

ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ይህን በመሰለው ቅድስናቸው፣ በቤተ ክርስቲያን ትምህርት እውቀታቸው፣ በተለይም በመዝገበ ቅዳሴ የአብነት መምህርነታቸው አያሌ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን በማፍራታቸውና ባበረከቱት የረዥም ዘመን ቅድስናን የተመላ አገልግሎት ፍጹም አባትነታቸው ተመዝኖ ብቁ ሆነው በመገኘታቸው ሐምሌ 9 ቀን 1997 ዓ.ም በተደረገው የጳጳሳት ምርጫ ከሌሎች ዕጩ ቆሞሳት ጋር ተወዳድረው ባገኙት የድምፅ ብልጫ የመቀሌ ደብረ ሰላም ቅ/ሚካኤል ካቴድራልና የከሣቴ ብርሃን ሰላማ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ ጳጳስ ሆነው እንዲሠሩ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ተመርጠው ሐምሌ 22 ቀን 1997 ዓ.ም በብፁዕ ቅዱስ አቡነ ጳውሎስ (ዶ/ር) ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዕጅ ተሹመዋል።

ብፁዕነታቸው በተመደቡበት ኃላፊነት በቅንነት ሲያገለግሉ ቆይተው ዛሬ የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።

የብፁዕነታቸው በረከት ይደርብን!

ምንጭ፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት

የብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ሥርዓተ ቀብር በአድዋ ደብረ ሐመልማል አቡነ አፍጺ ገዳም እንደሚፈጸም ተገለጸ።

የቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ሥርዓተቀብር በአድዋ ደብረ ሐመልማል አቡነ አፍጺ ገዳም የካቲት 22 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚፈጸም ተገልጿል።

በመቀሌ ከተማ በሚደረገው የሽኝት መርሐ ግብርም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እንደሚገኙም መንፈሳዊ ኮሌጅ በአወጣው መርሐ ግብር ጠቁሟል።

❤ ማርያም ሆይ ስለዚህ እንወድሻለን ❤" ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዐብየኪ እስመ ወልዲኪ ለነ መብልዐ ጽድቅ ዘበአማን ውስ ቴ ሕይወት ዘበአማን" (ማርያም ሆይ ስለዚህ እንወድሻለን ፣ ...
28/02/2023

❤ ማርያም ሆይ ስለዚህ እንወድሻለን ❤

" ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዐብየኪ እስመ ወልዲኪ ለነ መብልዐ ጽድቅ ዘበአማን ውስ ቴ ሕይወት ዘበአማን"

(ማርያም ሆይ ስለዚህ እንወድሻለን ፣ ከፍ ከፍም እናደርግሻለን ፣ እውነተኛ የጽድቅ መብልንና እውነተኛ የሕይወት መጠጥን ወልደሽልናልና ::)

✝️ የብህንሳ ኤጲስቆጶስ አባ ሕርያቆስ አምላክን ስለ ወለደች ስለ እመቤታችን ድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ የደረሰው የቁርባን ምስጋና።

+ ረሀብ ስንት ቀን ይፈጃል? +"ከረሃብ ሰይፍ ይሻላል" የሚል የአበው ብሂል ቢኖርም አሁን ሁለቱም እሳቶች ወገናችንን እየፈጁ ነው:: ከጦርነት እሳት ያመለጠውን የረሃብ እሳት ይቀበለዋል:: ...
24/02/2023

+ ረሀብ ስንት ቀን ይፈጃል? +

"ከረሃብ ሰይፍ ይሻላል" የሚል የአበው ብሂል ቢኖርም አሁን ሁለቱም እሳቶች ወገናችንን እየፈጁ ነው:: ከጦርነት እሳት ያመለጠውን የረሃብ እሳት ይቀበለዋል:: ረሃብን በምን ቃል እንግለጸው? በዚህች ደቂቃ ውስጥ አንተ ይሄን ጽሑፍ ስታነብ በረሃብ አለንጋ ክፉኛ ተገርፎ እያሸለበ ያለ ብዙ ወገን አለ::

ረሃብን ለመግለጽ ምን ቃል አለ?? ነፍሳቸውን ይማርና ሁለቱ ዕንቁ ደራስያን ጋሽ ጸጋዬ እና ጋሽ ስብሐት እንዲህ ብለው ነበር :-

ረሃብ ቀጠሮ ይሰጣል?
ወይስ ቀን ቆጥሮ ይፈጃል?
“የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል”
ይባላል፣ ድሮም ይባላል
ይዘለዝላል ይከትፋል
ብቻ እስከሚጨርስ ድረስ ሆድ ለሆድ ጊዜ ይሰጣል?

ወተት አንጀት ነጥፎ ሲላብ
ሆድ ዕቃ ደርቆ ሆድ ሲራብ
ተሟጦ አንጀት በአንጀት ሲሳብ …

የጣር ቀጠሮው ስንት ነው?
ለሰው ልጅ ሰው ለምንለው?
ላይችል ሰጥቶ ለሚያስችለው?
ስንት ቀን ነው? ስንት ሌት ነው?
(ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን)

"የተራቡ ልጆች አባት ምሬት :-

አበላቸው እህል ከልክለህ አምስት ልጆች የሠጠኸኝ ምነው?

አምስት ልጅ ተሰብስቦ አንድ ላይ ሲውል አንዲት ሳቅ ብቅ ሳትል መምሸቱ ምነው?

ልጆቼ አንዲት ቀን እንኳን አኩኩሉ ሳይጫወቱ ማለቃቸው ምነው?

ልጆቼን በአንድ ቀን ስቀብር ዝም ብለህ ማየትህ ምነው?"

(ጋሽ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር)

በያለንበት ለምግብ በተቀመጥን ጊዜ እያንዳንዱ ጉርሻ የሆነን ሰው ዕድሜ ሊያራዝም ይችል እንደነበረ እናስብ::
ጠጥተን የምንታጠብበትን ውኃ አጥቶ በዚህች ቅጽበት የሚያሸልብ ወገናችንን አንርሳ:: ደግመን እንላለን ጦርነት ክፉ ነው:: ረሃብ ደግሞ የባሰ ነው:: ሀገራችንን ከሁለቱም ዕረፍት ትፈልጋለች:: እስከዚያው ግን ለወገኖቻችን በየአቅጣጫው እንረባረብ!

በቦረና በረሃብ ወገኖቻችን እያለቁ ነው:: ከሰኞ ጀምሮ የእርዳታ ዘመቻ ይጀመራል::

Haile




Check this page 👇👇👇
Yared Shumete - ያሬድ ሹመቴ

አስተብፅዕዋ ወይቤልዋ ኀጥአን እለ ይነብሩ ፈለገ እሳት ፤ ሰዓሊ ለነ ማርያም ቅድስቱ ለእግዚአብሔር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቃል ኪዳን ለተቀበለችበት ዓመታዊ በዓል እንኳን በሰላምና...
23/02/2023

አስተብፅዕዋ ወይቤልዋ ኀጥአን እለ ይነብሩ ፈለገ እሳት ፤ ሰዓሊ ለነ ማርያም ቅድስቱ ለእግዚአብሔር

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቃል ኪዳን ለተቀበለችበት ዓመታዊ በዓል እንኳን በሰላምና በጤና አደረሰን !

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ !

Kabaja waggaa waggaadhaan waadaa Giiftii keenya Qulqulleettii Dubroo Maariyaamtiif illee nagaa fi fayyaan nu fidde!

Waaqni Itoophiyaa fi ummata ishee haa eebbisu

18/02/2023
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ፓትርያርክ የአቢይ ጾምን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃ...
17/02/2023

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ፓትርያርክ የአቢይ ጾምን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እነሆ፦

መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፤

• በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት እንዲሁም ኢትዮጵውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ!
እንደ ስሑትና ደካማ ሰብአዊ ባሕርያችን ሳይሆን እንደ አባታዊ ቸርነቱ ሁል ጊዜ በምሕረቱ የሚጐበኘን አምላካችን እግዚአብሔር እንኳን ለጾመ ኢየሱስ አደረሰን፤ አደረሳችሁ!
• “ንጹም ጾመ፣ ወናፍቅር ቢጸነ፣ እስመ ከማሁ አዘዘነ፡- ጾምን እንጹም፣ ባልንጀራችንንም እንውደድ፣ እንዲህ አዞናልና” (ቅዱስ ያሬድ)
እግዚአብሔር በዚህ ዓለም ስንኖር፣ እንድናደርገው ያዘዘን ዓቢይ ነገር ቢኖር ፍቅር ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረታትን ፈጥሮ እየመገበ የሚገኘው በፍቅር ነው፡፡ እኛንም ከፍዳ ኃጢአት ያዳነን በፍቅር ነው፡፡ ሕይወታችንና ንብረታችን ተጠብቆ የሚኖረው ፍቅር ሲኖር ነው፡፡

ግላዊና ማኅበራዊ ኑሮአችን እንዲሁም ሃይማኖታዊ አምልኮአችንና የተግባር እንቅስቃሴአችን በሙሉ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ፍቅር ሲኖር ነው፡፡
በፍቅር ውስጥ በረከት እንጂ ጉድለት የለም፤ በፍቅር ውስጥ ጤና እንጂ በሽታ የለም፤ በፍቅር ውስጥ ጽድቅ እንጂ ኃጢአት የለም፤ በፍቅር ውስጥ እግዚአብሔር እንጂ ዲያብሎስ የለም፡፡ ይህም በመሆኑ ቅዱስ መጸሐፍ ፍቅርን ‹‹የሁሉም ነገር ማሰሪያ ነች›› በማለት ይገልጻታል፡፡
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከሁሉም የምትበልጠው ታላቋ ትእዛዝ ‹‹ፍቅር›› እንደሆነች ከመግለፁም በላይ ኦሪትና ነቢያት ሁሉ በእሷ እንደሚጠቃለሉ አስተምሮናል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
ፍቅርን እንደ ዓይን ብሌን ስንጠብቃት በእጅጉ የምትጠቅመንን ያህል ጣል ጣል ስናደርጋት ደግሞ በእጅጉ ትጎዳናለች፡፡ በፍቅር እጦት የሚደርሰው ጉዳት በተወሰነ ነገር ብቻ ሳይሆን በነፍስም ሆነ በሥጋ፣ በምድርም ሆነ በሰማይ እጅግ በጣም የገዘፈና የሰፋ ነው፡፡

በሀገራችን የሆነውና እየሆነ ያለውም ይኸው ነው፡፡ ፍቅርን ባጣንባቸው ዓመታት ከየት ወዴት እንደደረስን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚገነዘበው ነው፡፡ ያተረፍነው ነገርም ምን እንደሆነ የምናውቀው ነው፡፡

ይሁንና የፍቅር እጦት ምን ያህል እንደጎዳን ራሳችን ተገንዝበን ወደ ሰላሙ መንገድ መመለሳችን የተሻለ አማራጭ መሆኑን ሳንመሰክር አናልፍም፡፡ የተጀመረው የፍቅርና የሰላም ጉዞም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ልባዊ ምኞታችንና ጸሎታችን ነው፡፡

ይህንን ሰላም እንዲመጣ ያደረጉ ወገኖችም ሁላቸውን ሳናመሰግን አናልፍም፡፡ ምክንያቱም በሰዎች መካከል ፍቅርንና ሰላምን የሚያደርጉ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉ ብሎ ጌታ እንደ አስተማረን ብፅዕና ይገባቸዋልና ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
የፍጹም ፍቅር መገኛ የሆነው ቅዱስ ወንጌል የሚያስተምረው ፍቅር፣ ራስን ማፍቀር ወይም መውደድ ሳይሆን ራስን መጥላት ባልንጀራን ግን መውደድ ነው፡፡ ወንጌላዊ-ፍቅር ፍጹም ነው የሚያሰኘውም ቅሉ ይህ ነው፡፡

ለሁለት ሺሕ ዘመናት ያህል በቅዱስ ወንጌል አስተምህሮ ላይ የተገነባው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ባህልም ይህን ፍቅር ጠብቆ የሚጓዝ ነው፡፡
ይህም በመሆኑ የኢትዮጵያ አበው መነኮሳት ከነበራቸው ፍቅርና ትሕትና የተነሣ፣ የሹመት ሽሚያ አያውቁም ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር ትልቁን ሥልጣን ይቅርና የአንድ ገዳም መሪ ለመሆንም በእግር ብረት ታስረው በግድ ካልሆነ በቀር እሺ ብለው በፈቃደኝነት ሹመትን አይቀበሉም ነበር፡፡
ራሱን በራሱ መሾም ወይም እኔን ሹሙኝ ብሎ መናገርና የሌላን ድጋፍ መጠየቅ ለኢትዮጵያውያን መነኮሳት ጭራሽ ነውርና ጸያፍም ነበር፡፡

ያም በመሆኑ ነው ከዘመነ ብሉይ ጀምሮ ለሦስት ሺሕ ዘመናት የዘለቀው ሃይማኖታችን ምንም ዓይነት መለያየት ሳያጋጥመው አንድ ሆኖ ሊዘልቅ የቻለው፡፡
ይህ የቤተ ክርስቲያናችን ጠንካራ አንድነት ለሕዝቡም በመትረፉ የሀገሪቱን አንድነትና ነጻነት አስጠብቆ እስከ ዘመናችን ሊደርስ ችሎአል፡፡ በዚህም ቤተ ክርስቲያናችን የሕዝብንና የሀገርን አንድነትና ነጻነት ለማስጠበቅ ያደረገችውና የምታደርገው ጥረት ሊያስመሰግናት እንጂ ሊያስወቅሳት አይገባም፡፡


የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
ከቅርብ ቀናት ወዲህ በቤተ ክርስቲያናችን ተከሥስቶ የነበረውን ሕጋዊ ያልሆነ ድርጊት የቤተ ክርስቲያናችንን ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና ባሕላዊ መርሕን የናደ፣ እንደዚሁም በኢትዮጵያ ይቅርና በዓለም ታሪክ ተደርጎ የማያውቅ ድርጊት እንደሆነ ቤተ ክርስቲያናችን በአጽንዖት ስትገልጽ ቆይታለች፡፡
ይህንን የቤተ ክርስቲያን ድምፅ በመስማትና በመቀበል ሕዝበ ክርስቲያንና ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለእግዚአብሔር ባቀረቡት ኃዘንና ጸሎት እንደዚሁም ባደረጉት መጠነ ሰፊና ዙርያ መለስ የሆነ የድጋፍ ርብርብ ስሕተቱ ሊታረም ችሏል፡፡

ለተገኘው መንፈሳዊ ውጤትም ክቡር ጠቅላይ ሚንስትርና መንግሥታቸውን፣ የቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሉዓላዊነት እንዲከበር ከፍተኛ መሥዋዕትነት ለከፈለው መላው ሕዝበ ክርስቲያን እንዲሁም ይህ ስሕተት እንዲታረም ከቤተ ክርስቲያናችን ጎን ተሰልፈው ድምፃቸውን ላሰሙ ኢትዮጵያውያንና የውጭ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በቤተ ክርስቲያናችን ስም ከፍ ያለ ምስጋና እናቀርብላቸዋለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን ግልፅ ማድረግ የምንፈልገው ከቤተ ክርስቲያናችን ዶግማ፣ ቀኖና እና ሥርዓት መከበር እንደዚሁም ከሉዓላዊ አንድነቷ መጠበቅ በመለስ ያለው ጥያቄ ለማስናገድ ቤተ ክርስቲያናችን ዝግጁ መሆኗን ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ሕዝቦች በቋንቋቸው የመማር፣ የማስተማርና የማምለክ እንዲሁም የመተዳደር መብትን ካሁን በፊትም፣ አሁንም፣ ካሁን በኋላም የምትነፍግበት መሠረት እንደሌለም ሁሉም ሊያውቀው ይገባል፡፡
ይህም በመሆኑ በቋንቋ የመጠቀም መብት በሕገ ቤተ ክርስቲያናችን ምዕራፍ 2 አንቀጽ 5 ከቁጥር 1-3 ባለው አንቀጽ በሚገባ ተቀምጦ ይገኛል፡፡ ስለሆነም በቋንቋ የመጠቀም ጥያቄ በሕግ ደረጃ ተመልሶ በተግባር እየተሰራበት የሚገኝ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል፡፡

የተወዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤
ዛሬ ታላቁን ጾማችን በፍቅር ሆነን የምንጾምበት ወቅት ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው ጾም ማለት ስጋዊ ፈቃድን በመግታት ከእግዚአብሔር ጋር ጥብቅ ግንኙነት ለማድረግ የሚካሄድ መንፈሳዊ ተጋድሎ ነው፡፡
በጌታችን ጾም በተግባር እንዳየነው ጾም ማለት ዲያብሎስ የሚሸነፍበት በአንጻሩ ደግሞ የእግዚአብሔር ሕዝብ አሸናፊዎች የሚሆኑበት ኃይል ነው፡፡
ስለሆነም ጾም የተጋድሎና የሙዓት ሜዳ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የምንታገለውም ልቡሰ ሥጋ ሰውን ሳይሆን ረቂቅ ፍጡር የሆነው ሰይጣን በሰው አድሮ የሚነዛውን አጥፊ ሐሳቡንና ድርጊቱን ነው፡፡

ከዚህም ጋር ሰውነታችን ለዚህ ክፉ መንፈስ ታዛዥ እንዲሆን የሚገፋፉ ጥሉላት መባልዕትን መተው፤ ኃይለ ሥጋን መቈጣጠር፤ ኃይለ መንፈስን ደግሞ ማጎልበት ያስፈልጋል፡፡ በጾም ወቅት የተራቡትን ማጉረስ የታረዙትን ማልበስ የተበደሉትን መካስ፣ ፍትሕና ርትዕ በማኅበረ ሰብ ውስጥ ማንገሥ ያስፈልጋል፡፡

በጾም ወቅት ኅሊናችን ማሰላሰል ያለበት ሰው ምን አለ? ወይም ምን አደረገ? በሚለው ሳይሆን እግዚአብሔር በፊቱ ምን ዓይነት ሰው እንድንሆንለት ይፈልጋል? በሚለው ላይ ነው፡፡

ስለዚህ ጾማችን በዚህ መንፈስ የተቃኘ ፍቅረ፣ እግዚአብሔርንና ፍቅረ ቢጽን ማእከል ያደረገ፣ መጠራጠርንና አለመተመማንን ያስቀረ፣ የተለያዩትን ያቀራረበ፣ የተሳሳቱትን ያረመ በአንጻሩ ደግሞ ሁላችንን በሰላምና በፍቅር አንድ አድርጎ ያስተሳሰረ ይሆን ዘንድ በዚህ መንፈስ ተነቃቅተን እንድንጾመው አባታዊ ጥሪያችንን ለሕዝበ ክርስቲያኑ እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም፤
በሀገራችን እየታየ ያለው የሰላም ጭላንጭልና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ዝንባሌ በእጅጉ ጠቃሚና ለሁለንተና ልማታችንና ለዕድገታችን እንደዚሁም ለተሟላ አንድነታችን ጠቃሚነቱ የጎላ ስለሆነ እግዚአብሔር ለዘለቄታው እንዲያሳካልን ከልብ እንድናዝንና ወደ አምላካችን በተመሥጦ እንድንጸልይ በአጽንዖት በማሳሰብ አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
መልካም የጾም ወራት ያድርግልን!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር! አሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስምወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
የካቲት ፲፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

Address

Addis Ababa

Telephone

+251912739138

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when ተዋሕዶ ሚዲያ ኔትዎርክ-Tewahedo Media Network posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Place Of Worship

Send a message to ተዋሕዶ ሚዲያ ኔትዎርክ-Tewahedo Media Network:

Share