28/07/2026
👉እባካችሁን በትዕግስት ጨርሱት
እግዚአብሔር የሚፈልገው እረኛ ማን ነው?
ቲቶ 1:5፤ ስለዚህ ምክንያት የቀረውን እንድታደራጅ በየከተማውም፥ እኔ አንተን እንዳዘዝሁ፥ ሽማግሌዎችን እንድትሾም በቀርጤስ ተውሁህ፤
በአዲስ ኪዳን ውስጥ ካሉት የጳውሎስ መልእክቶች መካከል ወደ ቲቶ የተጻፈው መልእክት የእውነተኛ እረኝነትን፣ የቤተ ክርስቲያን አመራርን እና የጤናማ ትምህርትን እጅግ በግልጽ የሚያሳይ መጽሐፍ ነው። ይህን መልእክት በትክክል ለመረዳት ግን አንድ ዋና ጥያቄ መመለስ አለብን፦ ጳውሎስ ቲቶን ለምን ወደ ቀርጤስ ላከው? በቀርጤስ ምን ችግር አለ በዛስ ያሉት አማኞች እና ቤተክርስቲያንስ ችግራቸው ምን ይሆን ?
በቲቶ መጽሐፍ ላይ የምናነበው የጳውሎስ መልእክት የተጻፈው በሰላም ዘመን አልነበረም፤ ቤተ ክርስቲያን በውስጥና በውጭ ከባድ መናወጥ ባጋጠማት ጊዜ ነበር። የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ቤተ ክርስቲያን በሮማ ግዛት ውስጥ በፍጥነት እየተስፋፋች ነበር፤ ነገር ግን የወንጌል መስፋፋት ከሐሰተኛ ትምህርት፣ ከዓለማዊ ባህል እና ከመንፈሳዊ ጥቃት የተለየ አልነበረም። ጳውሎስ በየከተማው የተተከሉት አብያተ ክርስቲያናት በጤናማ ትምህርትና በቅድስና እንዲቆሙ ያለማቋረጥ ይጨነቅ ነበር።
በዚያ ዘመን ቀርጤስ በሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ ያለች ትልቅ ደሴት ነበረች። በንግድ መንገዶች መሀል ስለነበረች የብዙ ባህሎች፣ የብዙ ሃይማኖቶችና የብዙ ፍልስፍናዎች መገናኛ ሆና ነበር። ነገር ግን በሀብቷ የታወቀችው ያህል በሥነ ምግባሯ አልታወቀችም፤ በግሪክ ዓለም የቀርጤስ ሰዎች በውሸት፣ በማታለል፣ በስግብግብነትና በራስ ወዳድነት የታወቁ ነበሩ። እንዲያውም በግሪክ ቋንቋ “ክሬቲዜይን” የሚለው ቃል “እንደ ቀርጤሳዊ መዋሸት” የሚል ትርጉም እስኪኖረው ድረስ ስማቸው ከውሸት ጋር ተያይዞ ነበር።
ይህን የሚያሳየው ጳውሎስ ራሱ የተናገረው ብቻ አይደለም። ከክርስቶስ ልደት በፊት በስድስተኛው ክፍለ ዘመን የኖረው የቀርጤስ ታዋቂ ነቢይና ገጣሚ ኤፒሜኒዴስ ራሱ ስለ ሕዝቡ እንዲህ ብሎ ጽፎ ነበር፤ “የቀርጤስ ሰዎች ሁልጊዜ ውሸታሞች፣ ክፉ አራዊት፣ ሰነፍ ሆዳሞች ናቸው።” ጳውሎስም ይህንን በቲቶ 1፥12 ሲጠቅስ፣ “ከእነርሱ መካከል የገዛ ነቢያቸው አንዱ…” በማለት ነው የሚናገረው የውጭ ሰው ሳይሆን የራሳቸው ሰው ችግሩን ምን ያክል አስከፊ እንደነበር ያሳያል።
የሚያሳዝነው ግን ይህ የውጭ ማኅበረሰብ ችግር እና ስም በውጭ ብቻ አልቀረም፤ ወደ ቤተ ክርስቲያንም ገባ። የክርስቶስ ስም የተጠራባቸው ሰዎች ገና በእምነት አልበሰሉም፤ የቤተ ክርስቲያን አመራር አልተደራጀም፤ በየከተማው የተሾሙ ሽማግሌዎች አልነበሩም፤ እና ወደቤተክርስቲያን እና ወደ ህዝበ ክርስቲያኑ ዘልቆ በመግባቱ ይህንንም ክፍተት እንደ ትልቅ እድል በመቁጠር ሐሰተኛ አስተማሪዎች የክርስቲያኑን ቤተሰቦችን በትምህርታቸው ያፈርሱ ነበር። ለአስነዋሪ ትርፍ ሲሉ ማስተማር የማይገባቸውን ያስተምሩ ነበር፤ የአይሁድ ተረቶችንና የሰው ትእዛዞችን ከወንጌል ጋር ያቀላቅሉ ነበር። ከዚህ የተነሳ ብዙዎች በአፋቸው እግዚአብሔርን እናውቃለን ቢሉም፣ በሥራቸው ግን በድርጊቶቻቸው ይክዱት ነበር።
እንግዲህ እዚህ ላይ ነው የዚህ የእግዚአብሔር ሰው ሚና ይህን ሁሉ ያየ ጳውሎስ ስለ ራሱ ዝና አልተጨነቀም፤ ስለ ክርስቶስ መንጋ ተጨነቀ። በቲክቶክ ቢስድቡኝ አብረህ በላህ ቢሉኝ ዩቱብ ላይ ቢሰድቡኝ ስለ ስሙ ስለ ማንነቱ ሳይጨነቅ እየተበከለ ስላለው እና እየተበተነ ስለሚመለከተው የእግዚአብሔር ህዝብ ስለዚህም ምክንያት ለማስተካከል ቲቶን ወደ ቀርጤስ ላከው፤ እንዲሸሽ ሳይሆን እንዲቆም፣ እንዲያስተካክል፣ እንዲያቋቁም እና የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን በጤናማ ትምህርት እንደገና እንዲያንጽ።
ይህ ታሪክ የቀርጤስ ብቻ አይደለም፤ በየትውልዱ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ነው። ጌታ ዛሬም የሚፈልገው ከችግር የሚሸሽ አገልጋይ ሳይሆን፣ እንደ ቲቶ ወደ ተናወጠው ወደሕዝብ ገብቶ የቀሩትን ነገሮች የሚያስተካክል ታማኝ እረኛ ነው።
ይህ ጥያቄ ስለ አንድ ሰው ጉዞ ብቻ አይደለም፤ ስለ እግዚአብሔር የአገልግሎት ልብ ነው። ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ባሪያዎቹን የሚልካቸው ሰላም ወዳለበት አይደለም፤ ሰላም ወደጠፋበት ነው። ሥርዓት ወዳለበት ሳይሆን ሥርዓት ወደፈረሰበት ነው። እውነት ወደቆመበት ሳይሆን ሐሰት ወደበዛበት ነው።
ቀርጤስ በዚያን ዘመን በሥነ ምግባር የወደቀች፣ በውሸት፣ በማታለልና በራስ ወዳድነት የታወቀች ደሴት ነበረች። ከዚያ የበለጠ የሚያሳዝነው ግን ያ መንፈሳዊ በሽታ ወደ ቤተ ክርስቲያንም መግባቱ ነበር። ሐሰተኛ አስተማሪዎች ተነስተው ቤተሰቦችን ያደናግሩ ነበር፤ የቤተ ክርስቲያን አመራር ገና አልተደራጀም ነበር፤ ብዙዎችም ስለ እግዚአብሔርን በአፋቸው ቢመሰክሩም በኑሯቸው ይክዱት ነበር (ቲቶ 1፥10–16)።
በዚህ ሁኔታ ጳውሎስ ዝም ብሎ አልተመለከተም። ቤተ ክርስቲያን ስትናወጥ እረኛ ዝም ብሎ አይቆምም፤ የተልእኮ ሰው ይልካል። ስለዚህ ቲቶን የላከው ወደ ምቹ አገልግሎት ሳይሆን፣ ወደ መንፈሳዊ ጦርነት ነበር፤ የቀሩትን እንዲያስተካክል፣ ሽማግሌዎችን እንዲሾም፣ ሐሰተኛ ትምህርትን እንዲገሥጽ፣ በጤናማ ትምህርትም የክርስቶስን መንጋ እንዲያጸና ነበር።
ይህ የታሪክ ታሪክ ብቻ አይደለም፤ የዛሬም ጥሪ ነው። ዛሬም ጌታ የሚፈልገው ዝናን የሚያሳድድ አገልጋይ ሳይሆን፣ የተሰበረውን የሚያቀና፣ የተበተነውን የሚሰበስብ፣ በእውነትና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ቤቱን የሚያንጽ እረኛ ነው። ቲቶ ወደ ቀርጤስ የተላከበት ምክንያት ይህ ነበር፤ ይህም ዛሬም ለክርስቶስ እያንዳንዱ ታማኝ አገልጋይ የተሰጠ ጥሪ ነው።
ወንድሞቼ እህቶቼ ሆይ፣ ሰዎች “ገንዘብ ተቀብለዋል” ይሉ ይሆናል፤ “ለምን ወደዚያ ሄዱ?” ብለው ይወቅሱ ይሆናል፤ ስማችሁንም ሊያጠፉ ይሞክሩ ይሆናል። ጌታ ግን አንድ ጥያቄ ብቻ ይጠይቃል፤ ስለ እኔ ወይስ ስለ ስማቹህ ? “መንጋዬን ወደድክን?” ወይስ የራስህን ክብር ቀረህ ወይስ ሄደህ አስተካከልክ
በእናንተ መሄድ ምክንያት አንድ ኃጢአተኛ ወደ ንስሐ ቢመጣ፣ አንድ የተበተነ ቤተሰብ ቢታረቅ፣ አንዲት የደከመች ቤተ ክርስቲያን ብትጠነክር፣ አንድ የጠፋች ነፍስ ክርስቶስን ብትቀበል፣ አልያም ያቺ ቤተክርስቲያን ትምህርቷን ብታርም ብታቀና መንጋዎቿን በአግባቡ ብታሰማራ ያ ከሰዎች ነቀፋ ሁሉ ይልቅ የሚበልጥ ሽልማት አይደለምን? አንተ ታማኝ የሚያስብል ተሸላሚ አያደርግምን ?
አንዳንዶች “መልካም ስሜ ይጠፋል” ብለው ይፈራሉ። በእርግጥ ጌታ የሚታዘዙትን ያዛል ልብ አድርግ አንተ አገልጋይ ይህን ከማን ተማርከው ምሳሌህ ማን ነው
ኢየሱስ ካልክ እንግዲያውስ ልንገርህ ጌታ ኢየሱስ ስሙን ለመጠበቅ አልመጣም፤ ራሱን ለመስጠት መጣ (ማርቆስ 10፥45)። ጳውሎስም ቲቶን ወደ ቀርጤስ የላከው ዝናውን እንዲጠብቅ ሳይሆን፣ የፈረሰውን እንዲያቀና፣ የተበተነውን እንዲሰበስብ እና በእውነት እንዲያቆም ነበር።
እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው የማይነቀፍ ስም አይደለም፤ ታማኝ ልብ ነው። ከሰዎች ዘንድ ያለንን ክብር ከክርስቶስ በጎች በላይ ካስቀመጥን፣ ዝናችንን ከወንጌል በላይ ካደረግን፣ ስማችን እንዳይነካ ብለን የተበተነውን መንጋ ችላ ካልን፣ የመልካሙን እረኛ ልብ አንከተልም።
ክርስቶስ በዮሐንስ 10 እንደተናገረው ቅጥረኛው ተኩላውን ሲያይ ይሸሻል፤ እውነተኛው እረኛ ግን ሕይወቱን ለበጎቹ ያኖራል። በሕዝቅኤል 34 ደግሞ እግዚአብሔር እረኞችን፣ “ደካሞችን አበረታታችሁ? የተበተኑትን ሰበሰባችሁ? የጠፉትን ፈለጋችሁ?” ብሎ ይጠይቃቸዋል። ጌታ የሚጠይቀው ስለ ዲግሪያችሁ፣ ስለ ማዕረጋችሁ፣ ስለ ተከታዮቻችሁ ወይም ስለ ዝናችሁ አይደለም፤ ስለ መንጋው ታማኝነታችሁ ነው።
ስለዚህ ከስንፍና እረኝነት እንውጣ። በሩቅ ቆመን ከመተቸት ይልቅ ወደ ተሰበረው እንሂድ። ከማኅበራዊ ሚዲያ ክርክር ይልቅ የተበተነውን መንጋ እንሰብስብ። ከታላቅ ስም ይልቅ ታማኝ አገልግሎትን እንምረጥ።
ምክንያቱም በመጨረሻ ጌታ “ስንት ተከታይ ነበረህ?” አይልም፤ “የሰጠሁህን መንጋ በታማኝነት ጠበቅህን?” ብሎ ይጠይቃል። በዚያ ቀን የሚከበረው ታላቅ ስም ያለው ሰው ሳይሆን፣ ለመልካሙ እረኛ ታማኝ ሆኖ የኖረው አገልጋይ ይሆናል።
“እንግዲህ ታማኝና መልካም ባሪያ፣ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ።” (ማቴዎስ 25፥21)
ስለዚህ እመርቃችኋለሁ…አሜን በሉኝ
ሐዋርያው ጳውሎስ በቲቶ እንደተማመነ፣ እግዚአብሔርም በእናንተ እንዲታመን እመርቃችኋለሁ።
እንደ ቲቶ የምትሄዱበት ሁሉ የደከመች ቤተ ክርስቲያን ትበርታ፤ የተሰበረ ልብ ይፈወስ፤ የጠፋ ነፍስ ወደ ክርስቶስ ትመለስ።
የምትሰብኩት ወንጌል በቃል ብቻ ሳይሆን በኃይል፣ በመንፈስ ቅዱስና በተለወጠ ሕይወት ይገለጥ።
የምትናገሩት እውነት የተኙትን ያንቃ፣ የተሳሳቱትን ይመልስ፣ የደከሙትን ያበርታ፣ የተስፋ ቆራጮችን እንደገና በክርስቶስ ተስፋ ይሙላ።
እንደ ቲቶ የተበላሸውን ሥርዓት የምታቀኑ፣ ብቁ መሪዎችን የምታስነሱ፣ ጤናማ ትምህርትን የምታጸኑ፣ ቅዱሳንን ለመልካም ሥራ የምታዘጋጁ ይሁኑ።
በምትሄዱበት ሁሉ የጨለማ ሥራ ይፍረስ፤ የክርስቶስ ብርሃን ይብራ፤ ቤተ ክርስቲያን በእምነት፣ በፍቅርና በቅድስና ትታነጽ።
እንደ ቲቶ የምትተክሉት አገልግሎት ከእናንተ በኋላም ፍሬ የሚያፈራ ይሁን፤ የምታፈሩት ፍሬ ለአንድ ዘመን ሳይሆን ለትውልድ ይኑር።
👉በመጨረሻም፣ እንደ ቲቶ ስትጨርሱ የምትተዉት ሕንፃ ሳይሆን የተገነባ ቤተ ክርስቲያን፣ ስም ሳይሆን የተለወጠ ሕይወት፣ ዝና ሳይሆን የሚኖር ፍሬ፣ ክብርም ለእናንተ ሳይሆን ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይሁን።
በመጨረሻዬም አሜን ካላችሁኝ እንደ ቃሉ መሰረት
🙏የጳውሎስ ራእይ፣ የቲቶ ታማኝነት፣ የመንፈስ ቅዱስ ቅባት እና የክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሜን።