30/01/2024
ጊዜ ዕረፍታ ለሶልያና
ወረደ ወልድ እምዲበ ልዕልና
ጠሊሳነ ንግሥ ሶቤሃ ከደና
በሶልያና (ማርያም) ዕረፍት ጊዜ ወልድ ከልዕልና ወረደ።
የንግሥና መጐናጸፊያን በዚያን ጊዜ ሸፈናት። (ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ )
የዘንድሮው አስተርእዮ ለማርያም — የእመቤታችን 1967ኛ ዓመት የዕረፍቷ መታሰቢያ ነው። አስተርአየ ተገለጠ ሲሆን፤ አስተርእዮ
ደግሞ መገለጥ ነው። አስተርእዮን በግሪክ ‹‹ኤጲፋኒ›› ይሉታል፡፡ የእኛም ሊቃውንት ቃሉን በቀጥታ በመውሰድ ‹‹ኤጲፋኒያ›› እያሉ በዜማ መጻሕፍቶቻቸው ይጠሩታል፡፡ ትርጕሙም መታየት፣ መገለጥ ገሃድ ማለት ነው፡፡ አስተርእዮ የሚለው ቃል ‹‹አስተርአየ›› ከሚለው ግሥ ራሱን ችሎ ሳይለወጥ በአምስቱ አዕማድ የሚፈታ ብቸኛ ግሥ ነው፡፡ ይህም ማለት፡- አስተርአየ፤ ታየ፤ ተያየ፤ አሳየ፤ አስተያየ፤ አየ ተብሎ ይፈታል ማለት ነው፡፡
ዘመነ አስተርእዮ (የመገለጥ ዘመን) ከክርስቶስ ልደት (ከተገለጠበት) እስከ ዐቢይ ጾም መዳረሻ ባለው ጊዜ የሚከበር ነው። ዘመነ አስተርእዮ በውስጡ ዐራት ዓበይት በዓላትን ይዟል። እነሱም የጌታችን ልደት፣ የጌታችን ጥምቀት፣ የቃና ዘገሊላ ተዓምርና የእመቤታችን ዕረፍት ያጠቃልላል፡፡ ዘመን የማይቆጠርለት፣ ይህን ያህላል፣ ይህን ይመስላል የማይባል ጌታ ከድንግል በሥጋ ተወልዶ ስለተገለጠ፣ ለዘመናት በእምነት ካልበሰሉ ምዕመናን አዕምሮ ተሰውሮ የነበረ የሥላሴ ኀልወት (ምስጢረ ሥላሴ) በጌታ ጥምቀት በዮርዳኖስ ወንዝ በገሃድ ስለታየ፣ በሥጋ ማርያም የተገለጠ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለ30 ዓመታት በግልጥ ሳያስተምር በየጥቂቱ አድጎ በቃና ዘገሊላ አምላክነቱን ስለገለጠ፣ ቤተክርስቲያናችን ይህንን ወቅት ዘመነ አስተርእዮ ትለዋለች፡፡ አስተርእዮ ማርያም የእመቤታችን የዕረፍት በዓል መታሰቢያ ነው። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በድጓው፦
ለምንት ይዜኃር ኃያል በኃይሉ
ወባዕል በብዝኅ ብዕሉ
ኢያድለወ ሞተ ክርስቶስ ለሥጋ አባሉ
ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ
ሞታ ለማርያም የአፅብ ለኩሉ ። ይላል።
‹‹ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐፅብ ለኵሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው፤ የቅድስት ማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል›› በማለት የመሠከረው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዕረፍት ነው፡፡ አባ ጽጌ ብርሃን ደግሞ በማኅሌተ ጽጌ ‹‹እግዚአብሔር ጽጌ ትንቢት ለቢሶ ሥጋኪ ሥጋ ዚአነ፤
አመ አስተርአየ በምድር ወተአምረ ለነ፤
ንዌድሰኪ እንዘ ንብል ምክሐ ዘመድነ፤
ዮም በፍሥሓ ለማርያም እምነ፤
አስተርእዮ በሰማይ ኮነ፤
የትንቢት አበባ እግዚአብሔር እኛን ሥጋ የሆነውን የአንቺን ሥጋ ለብሶ በምድር እንደተገለጠ ለእኛም እንዲታወቅ ድንግል ሆይ የወገናችን መመኪያ ዛሬ ለእናታችን ለቅድስት ማርያም በሰማይ ፍጹም በደስታ መገለጥ ሆነ እያልን እናመሰግናለን›› ብሏል፡፡ ዳዊትም እንዲህ አለ ‹‹በከመ ሰማዕነ ከማሁ ርኢነ፤
በሀገረ እግዚእ ኃያላን በሀገረ አምላክነ
እግዚአብሔር ሣረራ ለዓለም ።
እንደ ሰማን እንዲሁ አየን። በሠራዊት ጌታ ከተማ በአምላካችን ከተማ እግዚአብሔር ለዘላለም ያጸናታል››፡፡ (መዝ. ፵፯፥፰) በነቢያት ይወለዳል ሲባል የሰማነው በበረት ተጥሎ፤ በጨርቅ ተጠቅልሎ በግዕዘ ሕፃናት ሲያለቅስ ሰማነው እንዲሁም በዮርዳኖስ ሲጠመቅ አየነው ብሏል።
እመቤታችን በምድር ላይ በአይሁድ ክፋት ብዙ መከራና ኃዘን ካሳለፈች በኋላ በ49 ዓመተ ምሕረት፣ በዘመነ ሉቃስ፣ ጥር ሃያ አንድ ቀን፣ በዕለተ እሑድ በስድሳ ዐራት ዓመቷ ወደ ዘለዓለም ደስታ ትገባ ዘንድ ዐርፋለችና፡፡
እመቤታችን በ5485 ዓ.ዓ ከአባቷ ከቅዱስ ኢያቄም ከእናቷ ከቅድስት ሐና “እም ሊባኖስ ትወጽዕ መርዓት" ከሊባኖስ ሙሽራ ትወጣለች ተብሎ በተነገረው መሠረት ነሐሴ 7 ቀን ተጸነሰች፡፡
ግንቦት አንድ ቀን ሊባኖስ በምትባል ቦታ በብጽዓት ተወለደች።
በጾም በጸሎት በአስተብቁዖት ተገኘች።
ንጽሕት በመሆኗም ማኅደረ ወልድ ሆነች።
ከእናትና ከአባቷ ዘንድ ሦስት ዓመት፣
በቤተ መቅደስ 12 ዓመት፣
መድኃኔዓለምን በማኀጸንዋ ጸንሳ ዘጠኝ ወር ፤
ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ 33 ዓመት ከሦስት ወር፣
ከዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ ዘንድ 14 ዓመት ከዘጠኝ ወር
ጠቅላላ ድምር 64 ዓመት ሲሆናት ጥር 21 ቀን በ49 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡
ሰላም ለፍልሰተ ሥጋኪ መካነ ፍሥሓ ምጡቀ ፤
በአእባነ ባሕርይ ዘተነድቀ ፤
ማርያም ደብተራ እንተ ኢትትከደኒ ሠቀ።
( እመቤቴ ማርያም ሆይ ምጡቅና ሩቅ ወደሚሆን የደስታ ቦታ ላረገ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል፡፡)
እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ የዕረፍት በዓል (አስተርእዮ ማርያም) በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ ‼