Officia Tsion Mariam Catholic Church ጽዮን ማሪያም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን

  • Home
  • Ethiopia
  • Addis Ababa
  • Officia Tsion Mariam Catholic Church ጽዮን ማሪያም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን

Officia Tsion Mariam Catholic Church ጽዮን ማሪያም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን Catholic church

14/09/2026

As our Holy Father celebrates his birthday, we pray for his intentions, good health and that he may be strengthened in his singular mission as leader of the Catholic Church.

የጽዮን ማርያም ቁምስና ቆሞስ ክቡር አባ አማኑኤል እናት እና አባት የሆኑት አቶ ተክለማርያም ደምስ እና ወ/ሮ አልማዝ ፈርሻ የጋብቻ 50ኛ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ!
13/09/2026

የጽዮን ማርያም ቁምስና ቆሞስ ክቡር አባ አማኑኤል እናት እና አባት የሆኑት አቶ ተክለማርያም ደምስ እና ወ/ሮ አልማዝ ፈርሻ የጋብቻ 50ኛ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ!

መስከረም 1/2019 ዓ.ምብፁዕ አባታችን አቡነ ተስፋሥላሴ እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ በሰላም አደረስዎት አዲሱ ዓመት በእግዚአብሔር ጸጋ በምሕረቱ ብዛትና በእመቤታችን በድንግል ...
11/09/2026

መስከረም 1/2019 ዓ.ም
ብፁዕ አባታችን አቡነ ተስፋሥላሴ እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ በሰላም አደረስዎት
አዲሱ ዓመት በእግዚአብሔር ጸጋ በምሕረቱ ብዛትና በእመቤታችን በድንግል ማርያም አማላጅነት ለእርስዎ ለቤተሰብዎ እና ለመላው የካቶሊክ እምነት ተከታዮች የሰላም የጤና የበረከትና የተስፋ ዓመት እንዲሆን የጽዮን ማርያም ማኅበራዊ ድረ-ገጽ ልባዊ ምኞቱን ይገልፃል።

ጳጉሜን 1 ቀን 2018 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ብርሃነኢየሱስ ጋር የመንበረ ጵጵስና ርክክብ በማድረግ የተሰጠዎትን የእረኝነት አገልግሎት በትሕትና በጥበብና በፍቅር ለመወጣት በጸሎት ላይ ሆነው የሚጓዙበት ይህ አዲስ ዓመት ለእርስዎም ሆነ ለመላው ካቶሊካውያን አዲስ ተስፋና አዲስ ጸጋ የሚያመጣ ይሁን።

እግዚአብሔር በጵጵስና አገልግሎትዎ የተሰጠዎትን ቅዱስ አደራ በጥበብና በብርታት እንዲወጡ ጸጋውን ያብዛልዎት በሚመሩት መንጋ መካከል የእምነት የፍቅር የአንድነትና የሰላም ፍሬ ይብዛ።

በዚህ አዲስ ዓመት እግዚአብሔር ጉዞዎን ይምራ እጆችዎን ይባርክ ልብዎን በጥበቡ ይሙላ በአገልግሎትዎም ለቤተክርስቲያን ለሕዝብና ለሰላም የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ በብዙ መልካም ፍሬ ይባረክ።

እንኳን ለአዲሱ ዓመት እና ለአዲሱ የጵጵስና አገልግሎት ዘመን በሰላም አደረስዎት!

እግዚአብሔር ይጠብቅዎት ያበርታዎት ይባርክዎት
የእመቤታችን ማርያም አማላጅነትና ጥበቃ ሁልጊዜ ከእርስዎ ጋር ይሁን! 🙏
ጽዮን ማርያም ማኅበራዊ ድረ-ገጽ
የቴሌግራም ገፃችንን ለመቀላቀል ማስፈንጠርያውን ይጫኑ ቤተሰብ ይሁኑ
https://t.me/tsion_marian
https://t.me/TsionMariamCatholicChurc

የአዲስ ዓመት መጀመሪያ የምስጋና መስዋዕተ ቅዳሴ መስከረም 1/2019 ዓ.ም በጽዮን ማርያም ቁምስና ተደረገ።
11/09/2026

የአዲስ ዓመት መጀመሪያ የምስጋና መስዋዕተ ቅዳሴ መስከረም 1/2019 ዓ.ም በጽዮን ማርያም ቁምስና ተደረገ።

ከሆሣዕና ሀገረ ስብከት ከብፁዕ ጳጳስ አቡነ ስዩም ፍራንሷ የ2019 ዓ.ም. የአዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ የተላለፈ መልዕክትመግቢያ ከእግዚአብሔር አባታችንና ከጌታችን...
10/09/2026

ከሆሣዕና ሀገረ ስብከት ከብፁዕ ጳጳስ አቡነ ስዩም ፍራንሷ የ2019 ዓ.ም. የአዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ የተላለፈ መልዕክት

መግቢያ ከእግዚአብሔር አባታችንና ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን” (ሮሜ 1፥7)።
ክቡራን ካህናት! ገዳማውያንና ገዳማዊያት፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ምእመናን ሁላችሁ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያና በተለያዩ የውጭ ሀገራት የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊት፣ በተለይም የሀገረ ስብከቱ ተወላጆች ሁላችሁ፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የ2019 ዓ.ም. የተባረከ፣ በተስፋ የተሞላና በመንፈስ ቅዱስ የታደሰ ዓመት ይሆን ዘንድ እመኝላችኋለሁ።
አዲስ ዓመት የዘመን መቁጠሪያ መቀየር ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔር የሚያድሰንና አዲስ የምስክርነት ጉዞ የሚጠራን የጸጋ ጊዜ ነው። እያንዳንዱ ዓመት ያለፈውን ለማረም፣ ዛሬን በታማኝነት ለመኖርና የነገን ተስፋ በክርስቶስ ለመገንባት አዲስ ዕድል ነው።
2019 ዓ.ም. አዲስ ዓመትን ስንቀበል በመጀመሪያ ላለፈው ዓመት ሁሉ ከእኛ ጋር ሆኖ ስለጠበቀን፣ ስለደገፈንና ስለመራን እግዚአብሔርን በምስጋና ልብ እናስብ። በደስታና በብዛት፣ በበረከትና በችግር ጊዜ ሁሉ እርሱ አልተወንም።
እንዲሁም በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ለሆሣዕና ሀገረ ስብከት ምእመናን፣ ካህናት፣ ገዳማውያን፣ ካቴኪስቶች፣ ወጣቶች፣ ቤተሰቦች፣ የሰበካችን ተቋማት ሠራተኞች፣ ለጋሽ ደጋፊዎች፣ የመንግሥት ተቋማት፣ በውጭ አገራት የሚኖሩ የሰበካችን ልጆችና የተለያዩ ተቋማትን ሁሉ ለቤተ ክርስቲያናችን በጸሎት፣ በአገልግሎትና በልግስና ላበረከታችሁት ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
በችግርና በፈተና መካከል ያሳያችሁት ታማኝነት ራሱ ለክርስቶስ ታላቅ ምስክርነት ነው። “ጌታን አመስግኑ ቸር ነውና! ፍቅሩም ለዘላለም ነውና” (መዝ. 118፥1) እንደሚለው፣ የእግዚአብሔር ምሕረት እስከ ዛሬ አቁሞናል።
ስለዚህ አዲሱን ዓመት በምስጋና፣ በእምነትና በተስፋ እንጀምር። “የሚመጣውን ሁሉ ባናውቅም” ከእኛ ጋር የሚጓዘውን ጌታ እናውቃለን። በዚህም ዓመት እንደ ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን በኅብረት፣ በተሳትፎና በተልእኮ አብረን እንድንጓዝ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
1. የአዲሱ ዓመት የእግዚአብሔር ጥሪ፦ “ምስክሮቹ ትሆናላችሁ”
የ2019 ዓ.ም. መሪ ቃል፦ “... ምስክሮቹም ትሆናላችሁ” (ሐዋ. 1፥8) የሚል ነው። ስለዚህም እያንዳንዱ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተጠናክሮ የክርስቶስ ምስክር እንዲሆን ነው።
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በድክመታቸው ሳይሆን በሚቀበሉት የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተመልክቶ ወደ ምስክርነት ጠራቸው። ዛሬም እግዚአብሔር በድክመታችን ላይ ሳይሆን በጸጋው እንድንታመን ይጠራናል። ምክንያቱም “ከእርሱ የጸጋ ሙላት በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀብለናል” (ዮሐ. 1፥16)።
እግዚአብሔር ታሪክን የለወጠው በታላላቅ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በእምነት፣ በታማኝነትና በታዛዥነት የሚኖሩ ሰዎችን በመጠቀም ነው። አብርሃም፣ ሙሴ፣ ዳዊት፣ የኢየሱስ እናት ማርያምና ሐዋርያት የዚህ ምሳሌዎች ናቸው።
“ምስክሮቹ ትሆናላችሁ” የሚለው ጥሪ ለካህናትና ለገዳማውያን ብቻ ሳይሆን ለተጠመቀ ክርስቲያን ሁሉ ነው። ስለዚህም በአብሮነት፣ በኅብረት፣ በተሳትፎና በተልእኮ ወንጌልን እንመስክር።
ምስክርነትም በአንደበት ከመናገር በፊት በሕይወት መገለጥ አለበት። ስለዚህ “እኔ በክርስቶስ ይበልጥ እንዴት እለወጣለሁ?” ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይገባናል።
ስለዚህ በአዲሱ ዓመት በድክመታችን ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጸጋና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ታምነን፣ ሕይወታችንን በክርስቶስ እንድንለውጥና በታማኝነት ምስክሮቹ እንድንሆን ነው። የግል ለውጥ ቤተሰብን፣ ማኅበረሰብንና አገርን ወደ አዲስ ለውጥ ይመራል።
2. ምስክርነት የሚጀምረው ከልብ መታደስ ነው
እውነተኛ ምስክርነት ከውስጥ ሕይወት መታደስ ይጀምራል። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ዓለም ከመላኩ በፊት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንዲሞሉ አዘዛቸው። ይህም እውነተኛ ምስክርነት በመጀመሪያ ከራስ ሕይወት ለውጥ እንደሚጀምር ያሳያል።
ራሱ ያልተለወጠ ሰው ሌሎችን ለመለወጥ ይቸገራል! የክርስቶስን ፍቅር በልቡ ያልተቀበለ ሰውም ያንን ፍቅር ለሌሎች ማሳየት አይችልም። ስለዚህ የዚህ ዓመት የመጀመሪያ ጥሪያችን የውስጥ መታደስ ነው።
ቅዱስ ጳውሎስ፦ “አሮጌውን አውልቃችሁ ጣሉ፤ ነገር ግን በአእምሮአችሁና በመንፈስ ታደሱ” (ኤፌ. 4፥22-23) በማለት ያስተምረናል።
የክርስቲያን ሕይወት የአንድ ቀን ውሳኔ ሳይሆን በየዕለቱ ከክርስቶስ ጋር የምንጓዝበት የለውጥ ጉዞ ነው። ስለዚህ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት፣ ጸሎት በሕይወታችን ያለውን ስፍራ፣ በቤተሰባችን የክርስቶስ ፍቅር መኖሩን፣ እንዲሁም በቃላችንና በተግባራችን ሰዎችን ወደ ክርስቶስ እየመራን መሆናችንን በየጊዜው ልንመረምር ይገባል።
3. በኢትዮጵያ ሁኔታ ውስጥ የተስፋ ምስክሮች እንሁን
በክርስቶስ ወንድሞችና እህቶች፣ እግዚአብሔር የጠራን በተስፋ የተሞላ ተልእኮ ለመፈጸም ነው።
ክርስቲያን የሚኖረው ከዓለም ችግር ለመሸሽ አይደለም፤ በዓለም መካከል የክርስቶስ ብርሃን ለመሆን ነው።
ዛሬ በኢትዮጵያ ብዙ የሚያስመሰግኑና ተስፋ ሰጪ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸው የሚታወቅ ቢሆንም፣ አገራችን ብዙ ፈተናዎችን እየተጋፈጠች እንደሆነም ይታወቃል።
በተለያዩ አካባቢዎች የሰላም እጦት፣ መፈናቀል፣ ድህነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የወጣቶች ተስፋ መቁረጥ፣ የቤተሰብ ችግሮችና የመከፋፈል መንፈስ ይታያሉ።
በዚህ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያናችን የተስፋ ድምፅ ልትሆን ይገባታል። ስለዚህ ሁላችንም የጥላቻ ሰዎች ላንሆን የእርቅ ሰዎች እንድንሆን፣ የመከፋፈል ወኪሎች ላንሆን የአንድነት ገንቢዎች፣ የፍርሃት ተሸካሚዎች ላንሆን የተስፋ አስተላላፊዎች መሆን ይገባናል።
ጌታ ኢየሱስ፦ “በዓለም ላይ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” (ዮሐ. 16፥33) ይለናል።
ይህ ቃል ዛሬ ለእያንዳንዳችን፣ እንዲያውም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ የሚያስፈልግ ቃል ነው። ችግር መኖሩን ብናውቅም፣ ችግሩ እንዲቆጣጠረን መፍቀድ የለብንም። የተለያየ ስብራት፣ ሕመምና ስቃይ ቢገጥመንም የምናምነው የፈውስ ኃይል ያለው ክርስቶስ መሆኑን ሁሌም መዘንጋት የለብንም።
4. የሰላምና የእርቅ ምስክሮች እንሁን
የተወደዳችሁ ወንድሞችና እህቶች፣ በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያን በጣም የምትፈለግበት ተልእኮ የሰላምና የእርቅ አገልግሎት ነው።
ምክንያቱም የሰው ልብ በፍርሃት፣ በጥርጣሬና በመከፋፈል በተጎዳበት ጊዜ የክርስቶስ የፍቅር መልእክት የበለጠ ያስፈልጋል።
ጌታ ኢየሱስ የመጣው ለማዳን፣ የተሰበረውን ለመጠገን፣ የተራራቀውን ለማቀራረብ፣ ኃጢአተኛን ወደ ምሕረት ለመጥራት ነው።
ቅዱስ ጳውሎስ፦ “ይህ ሁሉ የሆነው በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን፣ የማስታረቅንም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው” (2ቆሮ. 5፥18) ይለናል።
ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን የሰላም ተመልካች ሳትሆን የሰላም ግንባታ ተዋናይ ነች።
ለዚህም ቤተሰብ የመጀመሪያው የእምነትና የፍቅር ትምህርት ቤት ስለሆነ፣ ልጆች ስለ እግዚአብሔር በመጀመሪያ የሚማሩት በቤተ ክርስቲያን ብቻ አይደለም፤ በቤታቸው ውስጥ በሚያዩት የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የሰላም፣ የአብሮነት፣ የጸሎትና የመከባበር ሕይወት ነው።
ይህ ለሰላም ትልቅ መሠረት ነው። ሰላም በልብ ይጀምራል፣ ከዚያም በቤተሰብና በማኅበረሰብ ያድጋል።
ጥላቻን፣ በቀልን፣ መድሎንና መከፋፈልን የሚያባብሱ ንግግሮችን እንከላከል። ሁላችንም የሚለያይ ግድግዳ ከሚገነቡ ይልቅ በፍቅር የሰላም ድልድይ የሚገነቡ ሰዎች እንሁን።
ኢየሱስ፦ “ሰላም የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው፣ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና” (ማቴ. 5፥9) ይላናል።
በተለይም ለአገራችን ሕዝብ ኃላፊነት የተሰጣቸውን መሪዎች እናስብ። እግዚአብሔር ጥበብን፣ ድፍረትን፣ ትሕትናንና ሕዝብን በእውነትና በፍትህ የማገልገል ፍላጎትን ይስጣቸው።

የብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ የቀድሞ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳትና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባዔ ፕሬዜዳንት የ2019 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከ...
10/09/2026

የብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ የቀድሞ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳትና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባዔ ፕሬዜዳንት የ2019 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
"ጌታን አመስግኑ ቸር ነውና" (መዝ 136፤1)

በክርስቶስ የተወደዳችሁ ብፁዓን ጳጳሳት

ክቡራን ካህናት

ገዳማውያንና ገዳማውያት

መላው ምዕመናንና ምዕመናት

እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ከአገራችሁ ውጭ የምትገኙ ኢትዮጵያውናና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በጎ ፍቃድ ያላችሁ የኢትዮጵያ ወዳጆች በሙሉ



እንኳን ለ2019 ዓመተ ምህረት የዘመን መለወጫ በዓል አደረሳችሁ! እንኳን ከዘመነ ቅዱስ ማርቆስ ወደ ዘመነ ቅዱስ ሉቃስ በሰላም አደረሳችሁ፡፡

የዘመናት ባለቤት እግዚአብሔር እነሆ ከዘመን ወደ ዘመን አሸጋገረን፤ አዲስ ዓመት መጣልን፤ ክብርና ምስጋና ለእርሱ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይሁን! ዳዊት በመዝሙሩ 136፤26 እንደሚለን የሰማይን አምላክ ልናመሰግን ያስፈልጋል።

ያለፈውን ስናስብ የምናመሰግንባቸው ወቅቶች እነሆ ብዙ ናቸው፡፡ በመሆኑም በግልም ሆነ በጋራ በቤተሰብም ውስጥ ሆነ በማኅበረሰብ ለተከናወኑ ቁም ነገሮች ምስጋናን እናቅርብ፡፡

ማመስገን አመስጋኙን ያሳድገዋል፡፡ ማመስገን ትሕትናን ገልጾ በረከትን ያመጣል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ 1ኛ ቆሮ 4፤7 "ሁሉንም ከአምላክ ተቀብለህ ለምን ምንም እንዳልተቀበልክ ትሆናለህ?" የሚል ያቀርባል፡፡ በእርግጥም ምስጋናና ውዳሴን መርሳት በ2018 ዓ/ም ውስጥ የተቀበልነውንና የተደረገልንን ችላ ማለት ነው፡፡ ራሳችንን ስንመረምር ንሰሐ የምንገባባቸውም ጊዜያት አያሌ ናቸው፡፡ ከአምላካችንም ጋር ሆነ ከወንድም እህቶቻችን ጋር ግንኙነታችን እንዴት ነበረ? ባልንጀራችንንም እንደ ራሳችን ያልወደድንበት ወቅቶች ብዙ አልነበሩምን? እግዚአብሔርን በፍፁም ልባችን፤ በፍፁም ኃይላችን፤ በፍፁም ነፍሳችን ያልወደድንባቸው ወቅቶችስ አልነበሩምን? ይህንንስ ትዕዛዝ ሁልጊዜ ፈጽሜያለሁ በማለት ደፍሮ መናገር የሚችልስ ማነው?

ይህንን ለማለት እንደማንችል ማስተዋል ከፈለግን የቅዱሳንና የጻድቃንን ንግግር መስማት ይበቃናል፡፡ ቅዱሳንና ጻድቃን ትላልቅ ኃጢአተኞች እንደሆኑ በድፍረት ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱም ምናልባት ለብዙዎቻችን የማይታየው ይታያቸዋልና ነው፡፡ በጣም ንፁህ በሆነ ቤት ውስጥ ብጣሽ ወረቀት ወይንም ትንሽ ቆሻሻ እንደሚታየው ማለት ነው፡፡ ቅዱሳን እና ጻድቃን አዘውትረው "እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ" ካሉ እኛም የበለጠ "ጌታ ሆይ ማረኝ ! ጌታ ሆይ ማረን!" ልንል ይገባናል፡፡

​በብሉይ ኪዳን ነቢያት ዘወትር የእግዚአብሔርን ምህረት ለሕዝባቸው ይለምናሉ፡፡ እኛም ላለፈው ኃጢያቶቻችን ምህረትን ልንለምን ይገባናል፡፡ በፍፁም አልተሳሳትኩም የሚባል ስህተት የለምና፡፡ ኃጢአትን መካድ በራሱ ኃጢአት ነውና። በሉቃስ ወንጌል ምዕ.18፣9-14 ላይ እንደምናነበው ጽድቅን አግኝቶ የተመለሰውን ቀራጭ ማስታወስ እጅጉን ይጠቅማል፡፡ ምክንያቱም በትህትናውና ምህረትን በመለመኑ ጽድቅን አግኝቶ ሲመለስ በአንጻሩ እራሱን እንደመልካም ሰው ብቻ እየቆጠረ የተመጻደቀው ፈሪሳዊ ከበረከት ሸሸ፡፡

አዲሱን ዓመት ስንቀበል ለወደፊት እንዲሻሻሉ ወይንም እንዲለወጡ የእግዚአብሔርን ፀጋ የምንጠይቅበት ወቅት ነው፡፡ የሰላምና የዕርቅ ዘመን እንዲሆንልን፤ የእግዚአብሔር ምሕረትና ፍቅር እንዲገዛንና የአምላክን ፀጋ በመምረጥ ሕይወታችን ትርጉም የሚያገኝበት ሁኔታ እንዲመጣልን ተስፋ በማድረግ አዲሱን ዓመት እንጀምረው፡፡

​ ዘመናችን የማኅበራዊ ግንኙነት ዘመን ነው፡፡ ብዙ ድምፆችን እንሰማለን፡፡ ነገር ግን የሚሻለውንና የሚያስፈልገውን የምንለይበትን ፀጋ ከእግዚአብሔር መቀበልን አንዘንጋ፡፡ መልካሙን ለማስተናገድ ፈቃደኛ እንሁን፡፡ ነገር ግን ጎጂውንና አፍራሹን ለመሸሽ አናመንታ፡፡ እግዚአብሔር የሚወደውን የሰው ልጅን ክብር የሚያስጠብቀውን ለመቀበል አንፍራ፡፡ በአንጸሩ ፈጣሪ የሚወደውን፣ ከፈሪሃ እግዚአብሔር የራቀውን ጥበብ የሌለበትን ከመሸሽ ወደ ኋላ አንበል፡፡

​ከዚሁ ጋር በተያያዘ ብፁዕ ወቅዱስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዎ 14ኛ በቅርብ ጊዜ ለዓለም ሁሉ ስለ ሰው ልጅ ክብር በተጻፈው የቤተክርስቲያን ሐዋሪያዊ መልዕክታቸው የሚከተለውን አስተላልፈዋል፡፡ "በታላቅነቱ ሁሉ በእግዚአብሔር የተፈጠረው የሰው ልጅ ዛሬ ወሳኝ በሆነ ምርጫ ላይ ይገኛል፤ አዲስ የባቢሎን ግንብ መገንባት ወይም እግዚአብሔርና የሰው ልጅ አብረው የሚኖሩባትን ከተማ መገንባት"፡፡

​የመልዕክቱ ፍሬ ሐሳብ የሰው ልጅ የደረሰበትን ቴክኖሎጂና አስተውሎት መሰል መሳሪያ ለሰው ልጅ ክብርና ለፍትህ እንዲጠቀምበት ይጋብዛል፡፡ በሌላ አነጋገር የሰው ልጅ እራሱ በሰራው መሣሪያ ሰውን ዝቅ ካደረገ ፈጣሪንም ከደፈረ የባቢሎን ግንብ ታሪክ ተደገመ ማለት ነው፡፡ የዚያን ዘመን ሰዎች በትምክህታቸው ረጣሪን ለመቆጣጠር ፈለጉ፡፡ እርሱ ድረስ የሚደርስ ግንብ የሠሩ መስላቸው፡፡

ነገር ግን በኦሪት ዘፍጥረት ምዕ. 11 እንደምናስተውለው ሰዎች እንኳን እግዚአብሔር ላይ ሊደርሱ፣ ይልቁንም እግዚአብሔር እነርሱን ለማግኘት እንደወረደ እናነባለን፡፡ በእነርሱ አመለካከት ወደ ከፍተኛ ስፍራ ደርሰዋል ነገር ግን ቅዠት ነበር፡፡

ታዲያ የሰው ልጅ የሚከብረው በእግዚአብሔር የተሰጠውን መልክ በፍቅር ሲጠብቅ መሆኑን ከረሳና ይህንን መልክ ወደ ባርነት የሚወስድ መንገድ ከተከተለ ዕጣ ፈንታው የባቢሎን ግንብ ሰዎችን ዓይነት ሲሆን ነው ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ ግልጽ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ቤተክርስቲያን ቴክኖሎጂን አትቃወምም፡፡ ሆኖም ቤተክርስቲያን አደራ የምትለው ግን ሰው በዚች ምድር ላይ ልዩ ጥሪ፤ ልዩ ሃላፊነት፤ ልዩ ክብር አለውና ይህንን የሚረሳ ወይንም የሚያጠፋ መሣሪያ መሥራት ስህተት ነው የሚል ነው፡፡

​እያንዳንዱ ትውልድ የራሱን ዘመን የመቅረፅ እንዲሁም ታሪክ የእያንዳንዱ ሰው ክብር የሚጠበቅበት፤ ፍትህ የሚሰፍንበትና የሚስፋፋበት፤ ወንድማማችነትና እህትማማችነት በግልጽ የሚታይበት ስፍራ እንዲሆን የመምራት ሃላፊነት መውረስ አለበት፡፡ ሆኖም እያንዳንዱ ዘመን ሰብዓዊነት የጎደለውና የበለጠ ፍትህ የሌለው ዓለም የመፍጠር አደጋ ተደቅኖበታል፡፡ የሰው ልጅ እውነተኛ ማንነቱን የማበላሸት አደጋ በሚረጋገጥበት ጊዜ ሁሉ እና ክርስቲያኖች የሰው ልጅ ሚስጥር እውነት ሆኖ የሚገለፀው በእግዚአብሔር ቃል አማካይነት መሆኑን በማወቅ ኣይኖቻችንን ወደ እርሱ እናንሣለን፡፡ እውነትና ሕይወት በሆነው በክርስቶስ እያንዳንዳችን ወደ ሙላት እናድጋለን፡፡

​በመጨረሻም ሁላችንም በዚህ አዲስ ዓመት እውነተኛ ሰላምን እግዚአብሔር እንዲሰጠን እንፈልጋለን፡፡ ከእርስ በርስ ጦርነት ወጥተን፣ ሁሉም ጠግቦ የሚኖርበት የእውቀት ጮራ ለሁሉም የሚደርስበት፣ ስደትና መፈናቀል የሚያበቃበት፤ የተጣሉ እንዲታረቁ፤ ያልተማሩ እንዲማሩ፤ በበጎ ፈቃድ ተባብሮ በመጣር በአገራችን የተስተካከለና ፍፁም የሆነ ሰላም እንዲሰጠን በሙሉ ልባችን እንፀልይ እንመኝ፡፡

ይህን የዘመን መለወጫ በዓል ስናከብር በችግረኞች መካከል በመገኘትና ችግራቸውን በማቃለል የችግራቸው ተሳታፊዎች በመሆን ክርስቲያናዊ ተግባራችንን እንፈጽም፡፡

​አዲሱ ዓመት ለታመሙት ምህረትን፤ ላዘኑት መጽናናትን፤ ለታሰሩት መፈታትን፤ በጭንቀት በችግርና በመከራ ውስጥ የሚገኙትን ወገኖችንንን እግዚአብሔር ሰላሙንና ፍቅሩን ፀጋውን የሚሰጣቸው የምህረት ዓመት ያድርግልን፡፡

​ልዑል እግዚአብሔር አዲሱን ዓመት ይባርክልን፣ ይቀድስልን፣ ሰላሙን ያውርድልን፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ብርሃን በጥበብ እንድንመራ ያድርገን፡፡


በድጋሚ ሁላችሁንም እንኳን ለ2019 ዓ/ም በሰላም አደረሳችሁ፡፡

እግዚአብሔር አዲሱን ዘመናችንን ይባርክልን

ለመላው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉየጽዮን ማርያም ማኅበራዊ ድረ-ገጽ እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ በሰላም አሸጋገራችሁ እያለ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና በዓለም ዙ...
10/09/2026

ለመላው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ

የጽዮን ማርያም ማኅበራዊ ድረ-ገጽ እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ በሰላም አሸጋገራችሁ እያለ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና በዓለም ዙሪያ ለምትገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የአዲሱን ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክቱን በደስታ ያስተላልፋል።

አዲሱ ዓመት በተስፋ፣ በፍቅርና በሰላም የተሞላ እንዲሆን በቤተሰቦቻችን ደስታና መተሳሰብ ለማኅበረሰባችን አንድነትና ለሀገራችን ሰላም እንዲበዛ ይመኛል።

አዲሱ ዘመን ለሁላችንም የጤና፣ የሰላም፣ የፍቅር፣ የተስፋና የአንድነት ዓመት ይሁንልን።
እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ!
መልካም አዲስ ዓመት!

  በእግዚአብሔር የተወደዳችሁ፣ በእምድብር ሀገረ ስብከት የምትገኙ ካህናት፣ ደናግል፣ ምዕመናን፣ እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁላችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች፦የጊዜ ባለቤት፣ የዘመን ባለቤት እ...
10/09/2026



በእግዚአብሔር የተወደዳችሁ፣ በእምድብር ሀገረ ስብከት የምትገኙ ካህናት፣ ደናግል፣ ምዕመናን፣ እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁላችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች፦

የጊዜ ባለቤት፣ የዘመን ባለቤት እግዚአብሔር ነው። ዘመናትን የሚባርክ፣ ዘመናትን የሚቀያይር እርሱ ነው። 2018 ዓመተ ምህረትን በፍቅሩ ጠብቆ፣ ለ2019 ዓመት በሰላም ስላሻገረንና ስላደረሰን የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን።

እግዚአብሔርን ስናመሰግን በደስታና በተስፋ በተሞላ ልብ ሆነን ነው። «ሁሉን ነገር አዲስ አደርጋለሁ» ይላልና እግዚአብሔር።

ዓመታትን ሲያሻግር ሲቀያይር አዲስ ዓመት ብለን ደግሞ ስናከብር፦

ባለፈው ዓመት እግዚአብሔር የሰጠንን በረከት እየቆጠርንና እያመሰገንን፣
በጎደለብንና ባጎደልነው ነገር ደግሞ በዘንድሮው ዓመት እግዚአብሔር ሙሉ እንዲያደርግልን እኛም የጎደለውን ለመሙላት ጥረት እያደረግን፣
በተለይ ደግሞ ከምንም በላይ እግዚአብሔርን የበለጠ የምንፈራበት፣ የምናከብርበት ለእግዚአብሔር የምንታዘዝበት
ወንድሞቻችንን እንደ ራሳችን አድርገን የምንወድበት፣
ፍጥረትን የምንከባከብበት፣
በተሰጠን ኃላፊነት ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂነት እንዳለብን በመረዳት በመታመን፣
መልካሙን ገድል እንደሚጋደሉ መልካም ክርስቲያኖች መልካም ሥራን እየሠራን የምንኖርበት፣

በእምነት የምንጸናበት፣ በፍቅር የምንቆምበት፣ ስለ ሰላምና ስለ እርቅ የምንጸልይበት፣ የምናውጅበትና የምንሰራበት ዘመን እንዲሆን እግዚአብሔር ዕድል ሰጥቶናል።

እንደ ካቶሊካውያን ምዕመናን፣ እንደ ካቶሊካውያን ወገነ ክህነት፣ እንደ ካቶሊካውያን መነኮሳት፣ በሀገረ ስብከታችን እግዚአብሔር የሰጠንን ታላቁን የስብከተ ወንጌል ተልዕኮ በጽድቅና በቅድስና መፈጸም እንድንችል እግዚአብሔር እንዲያግዘን የምንጸልይበትና የበለጠ የምንተጋበት ጊዜ ነው።

«ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፣ ወንጌልንም አስተምሩ፤ በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው» ብሎ ያዘዘውን ቃል በመከተል፦
ወንጌልን በእውነትና በፍቅር በመስበክ፣
ሥርዓተ አምልኮን በክብር፣ ለቅድስናና ለጽድቅ በመፈጸም፣
በመልካም እረኝነት በመምራት፣
በፍቅር ሌሎችን ወንድሞችና እህቶችን በማገልገል፣
የምንተጋበት ዓመት እንዲሆን ቁርጥ ፍቃድ እንድናደርግና በሲኖዶሳዊነት መንፈስ አብረን ወደ ጌታ መንግሥት እንድንጓዝ ሁላችንም የበኩላችንን ጥረት እንድናደርግ እግዚአብሔር አዲስ ዓመት ሰጥቶናልና። ዘመንን የሚባርክ፣ ዘመንን የሚቀድስ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችንን፣ ሕዝባችንንና ሀገራችንን እንዲባርክ እንጸልያለን።

2019 ዓመት የቅዱስ ሉቃስ ዘመን፦
የበረከት፣የጽድቅ፣የቅድስና፣የእምነት ያድርግልን።

ሁላችንንም በፍቅር አስተሳስሮ፣ በአንድነትና በአብሮነት፣ እንደ ወንድማማቾች በእግዚአብሔር እንደሚያምኑ ሰዎች በመልካም ሥነ ምግባር እንዲያቆመን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ይሁንልን።

የተባረከ፣ የተቀደሰ 2019 ዓመት ለሁላችንም ይሁን። አሜን!

Address

Addis Ababa
321

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Officia Tsion Mariam Catholic Church ጽዮን ማሪያም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Place Of Worship

Send a message to Officia Tsion Mariam Catholic Church ጽዮን ማሪያም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን:

Shortcuts

Share