01/08/2026
ከሀገራዊ ምክክር መድረክ የተገፋው ሙስሊም ማህበረሰብ
•••••••••••••••••••••••••••••
የኢትዮጵያ ሙስሊም ታሪክ ባለቤት የሆነ፣ ሀገር ስትሰራ አብሮ የሰራ፣ በአራቱም አቅጣጫ ታሪክ እሴት ያለው፣ ለሀገር ሰላም እና ልማት ቅድሚያ ሰጥቶ መስዋእትነት ሲከፍል የኖረው ነባሩ ሙስሊም ሱፍይ ማህበረሰብ ሀገራዊ ኮሚሽን ከተቋቋመበት ቀን ጀምሮ ለበርካታ ጊዜያት እንደ ሀገር እንደ ሙስሊም ማህበረሰብ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ያላቸውን ጥያቄዎች ለኮሚሽኑ በደብዳቤ በአካላዊ ውይይትም አቅርቧል።
ሀገራዊ ምክክር መድረክ ሲጀመር በዋናነት ተሳታፊ እንዲሆን ማድረግ ግዴታ መሆን የነበረበት ሙስሊም ማህበረሰብ ስልታዊ በሆነ መንገድ ከመድረኩ ተገፍቷል። በአንፃሩ በኢትዮጵያ ሙስሊም ታሪክ ከ40 አመት የዘለለ ሚና የሌላቸው፣ ነባር የሙስሊሙ ማህበረሰብ ታሪክ እና እሴቶች ለፖለቲካዊ ፍጆታ ካልሆነ የኔ ነው ብለው የማያምኑ፣ መጅሊሱን በመጠቀም ነባሩን ታሪክ እና እሴት ለማጥፋት ሌት ተቀን የሚሰሩ፣ የብዙሃኑ ሙስሊም ማህበራዊ ውክልና የሌላቸው እስር እና ሚድያ ያገነናቸው ሰዎች በሙስሊሙ ወካይነት ከመድረኩ ተሰይመዋል።
ያለፈውን የሚረሳ የወደፊቱን ይረሳል እንደሚባለው የታሪክ ባለቤት የሆነው ነባሩ ሱፍይ ሙስሊም ማህበረሰብ ያገለለ የምክክር መድረክ ስንኩል እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህ ዋናው እና የኢትዮጵያን ሙስሊም በቅጡ የሚወክል ህዝብ ከምክክር መድረኩ ገለል እንዲል የተፈለገው ለምንድነው? ይህ ህዝብ ለሰላም ዘብ ከመሆን ለሀገር ቅድሚያ ሰጥቶ ህመሙን ታቅፎ ከመኖር የዘለለ ምን በደል ፈፅሞ ነው የተገፋው? እውን በዚህ ልክ የታሪክ ባለቤት የሆነውን ሙስሊም ማህበረሰብ ገፍቶ ሀገራዊ አንድነት ማምጣት ይቻላል?
የምክክር ኮሚሽኑ ከሃይማኖት ተቋማት ማህበረሰብን የሚወክሉ ሰዎች የመረጠው ሰላም Ministry of Peace የሰላም ሚኒስቴር ነው ቢልም ኮሚሽኑ ነፃ እና ገለልተኛ እንደመሆኑ ተገፍተናል ብዙ መከራ እና ስቃይ እየተፈፀመብን ነው ችግራችንን እወቁልን ብሎ በመድረኩ አሳትፉን ብሎ በተደጋጋሚ የጠየቀውን ማህበረሰብ መርሳት እና ጉዳዩን ወደ ሌላ መንግስታዊ ተቋም ማላከክ ተገገቢም ፍትሃዊም አይደለም።
ሰላም ሚኒስትር ሐይማኖታዊ ጉዳዮችን በሚመለከት ትኩረት
ስለሚሰጥ ነባሩ ሙስሊም ሱፍይ ማህበረሰብ እየደረሰበት ያለውን መገፋት እና ስቃይ ከተገቢው በላይ በቂ መረጃ እና ማስረጃ ያለው ቢሆንም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሙስሊም ሹመኞች አፍቃሪ ወሀብያ በመሆናቸው የሱፍዩ ማህበረሰብ ጥያቄ ወደ ላይኛው የመንግስት አካል እንዳይቀርብ አፍነው ከጠረጴዛቸው ሥር በማስቀመጥ በአንፃሩ የተሳሳቱ እና የተዛቡ መረጃዎችን ለበላይ አለቆቻቸው በማቅረብ ሱፍይ ሙስሊሙ እየበደሉ እንደሆነ እናውቃለን። እንደ አንድ መንግስታዊ ተቋም መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ለበላይ የመንግስት አካላት ማሳወቅ ሲገባቸው ሙስሊም ሹመኞቹ ከመጅሊሱ ጋር እጅና ጓንት በመሆን የመጅሊሱን በደል መሰወር መርጠዋል።
ነባሩ ሙስሊም ማህበረሰብ እየተፈፀመበት ያለውን የተቀናጀ በደል እና ጭቆና ተገንዝቦ ትግሉን ከዚሁ አንፃር ማስኬድ ይጠበቅበታል። እውነት ትቀጥናለች እንጂ አትበጠስም ዛሬ
ቀኑ ቢጨልም ነገ ብርሃን ይሆናል። ዝንተ ዓለም የዘለቀ የጭቆና ቀንበር የለም በደል ፈፃሚውን ይቀብራል።
የአዲስ አበባ ሙስሊም ወጣቶች ማሕበር