09/02/2025
በሀገረ ጀርመን የሚገኙ ካቶሊካውያን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ስጦታ አበረከቱ !
የካቲት 2 ቀን 2017 ዓ.ም(ተ.ሚ.ማ/አዲስ አበባ)
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተከርስቲያን የጀርመን እና አካባቢው ሀገረ ስብከት የዱስልዶርፍ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ፤ ከካቶሊካውያን የሕንጻ ቤተክርስቲያን ስጦታ ተበርክቶለታል።
ላለፉት 10 ዓመታት የደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ካህናት እና ምእመናን ሲገለገሉበት የቆዩት እና የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ንብረት የነበረው የሴንት ኖርበርት ቤተ ክርስቲያን በጋራትህ ከተማ ከሚገኙ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አንዱ ሲሆን ባሳለፍነው ጥር 18 ቀን 2017 ዓ.ም (Jan 26, 2025) ሙሉ በሙሉ ለደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን በስጦታ ተሰጥቷል።
ከ 60 ዓመታት በፊት በተሠራው በዚህ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን የስጦታ መርሐ ግብር ላይ የሁለቱም የሃይማኖት ተከታዮች ካህናት እና ምእመናን በተገኙበት የጋራ ጸሎት ተደርጓል እንዲሁም መዝሙሮች እና የተለያዩ መርሐ ግብሮች ቀርበዋል። የሁለቱ አብያተክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ቤዛ መንግሥቱ እና ቄስ ማርቲን ሩስተር በዝግጅቱ ለታደሙ ምእመናን ስለሁለቱም ሃይማኖቶች ገለጻ አድርገዋል።
በአካባቢው የሚነበበው ራይኒሸፖስት የተባለ ጋዜጣ እንደዘገበው ቄስ ማርቲን ሩስተር የስጦታውን ምክንያት ሲያስረዱ “በአካባቢው ያሉ ምእመናን ቁጥር እየቀነሰ በመምጣቱ እኛ ለረጅም ግዜ ልንሰጠው የማንችለውን ሃይማኖታዊ አገልግሎት መስጠት ይችላሉ እና ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካህናት እና ምእመናን ለመስጠት ወስነናል” ብለዋል።
ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ቤዛ መንግሥቱ በበኩላቸው በውጭ ሀገር የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በውጭ ሀገር ለሚኖሩ የእምነቱ ተከታዮች የእምነት ቦታ ከመሆንም ውጭ ትንሿ ኢትዮጵያ እንደሆነች ገልጸዋል። አክለውም ስለተደረገው ስጦታ ለአስተዳዳሪው ካህንና ለካቶሊክ እምነት ተከታዮች በራሳቸውና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ስም ከታላቅ አክብሮት ጋር ምሰጋናን አቅርበዋል።
በመርሐ ግብሩም የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን ስጦታ የሚያረጋግጥ የስጦታ ውል ቄስ ማርቲን ሩስተር ለሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ቤዛ መንግሥቱ በአክብሮት አስረክበዋል። በቦታው ታድመው የነበሩ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን እና ምእመናት በእንባ የታጀበ ደስታቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ቄስ ማርቲን ሩስተርን ጨምሮ በቤተክርስቲያኑ የስጦታ ሂደት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉት ለካቶሊክ እምነት ተከታዮች ከኢትዮጵያ ተዘጋጅተው የመጡ የመስቀል ቅርጽ ምስል ፣ የአንገት ልብስ አንዲሁም የአበባ እቅፍ ከታላቅ አክብሮትና ምስጋና ጋር በሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ቤዛ መንግሥቱ አማካይነት ተበርክቶላቸዋል።
ዘገባው የጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሚድያ ነው