25/08/2026
አምላክን በድንግልና ጸንሳ በድንግልና የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያም ከአዳም ዘር የተላለፈ ኃጢአት (ጥንተ-አብሶ) ያላገኛት መርገመ ሥጋ ፣ መርገመ ነፍስ የሌለባት ገና ከመወለዷ አስቀድሞ በአምላክ ሕሊና ታስባ ትኖር የነበረች ፣ በሰው ልማድና ጠባይ ከሚደርሰው ሥጋዊ ሀሳብና ፈቃድ ሁሉ የተጠበቀች ከተለዩ የተለየች ንጽሕት ቅድስተ ቅዱሳን ናት። (መኃ 4፡7) ። እመቤታችን በውስጥ፣ በአፍኣ ፣ በነፍስ ፣ በሥጋ ቅድስት ስለሆነች እግዚአብሔር ለልጁ ማደሪያ መርጧታል። ማኅደረ መለኮት እንድትሆን አድርጓታል። አምላክን ለመውለድ ያስመረጣትና ያበቃት ድንግልናዋ ፣ ንጽሕናዋ ነው። (አባ ሕርያቆስ፣ መዝ 132፡13)። ንጽሐ ሥጋ ፣ ንጽሐ ነፍስ ፣ ንጽሐ ልቡና ለእመቤታችን ገንዘቦቿ ናቸው።