24/06/2026
ድካምና አገልግሎት
አንዳንድ ጊዜ በብዙ እያገለገልን እየመሰለን ነገር ግን በውስጣችን ደክመን እንገኛለን:: በመጽሐፍ ቅዱሳችን ማርታ በብዙ አገልግሎት ባክና ትክክለኛውንና የሚያስፈልጋትን ነገር ዘንግታ ነበር ፤ ከእግሩ ስር ሆና ከእርሱ ማዳመጥ። በሽርጉዱ ሌሎችን አያገለገለች ነገር ግን እራሷን በእርሱ ስር አቆይታ ከእርሱ መቀበልን ስለረሳችም ጌታችን የሚያስፈልገው ግን ጥቂት እንደሆነ ስያስታውሳት እናያለን ::
"ማርታ ግን አገልግሎት ስለ በዛባት ባከነች፤... ኢየሱስም መልሶ፡— ማርታ፥ ማርታ፥ በብዙ ነገር ትጨነቂአለሽ ትታወኪማለሽ፥ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው ፥ ...”
ሉቃ 10:40
እንደ አንድ የካምፓስ ክርስቲያን ተማሪ አገልግሎት ቅድሚያ ከምንሰጣቸው ነገሮች መካከል መሆኑ ጤናማ ውሳኔ ቢሆንም ፣ በአገልግሎት ለምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ከግል ጊዜያችን በላይ ቅድሚያ ስንሰጥ ግን ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን የግል ጊዜ ቀስ በቀስ እየተሻማ፤ ምንም እንኳን በሕብረት ውስጥ በብዙ የምንሳተፍና በብዙ ስናገለግል ብንታይም በውስጥ ማንነታችን ግን ለድካም ያጋልጠናል::
ስለዚህ ወደ መፍሔውም ስንሻገር የመጀመሪያ እርምጃ ድካማችንን በእግዚአብሔር ፊት ማቅረብ ይሆናል ፤ እርሱ ሸክማችንን ይዘን በፊቱ እንድናኖርና ልያሳርፈን በቃሉ ተናግሯልና:: ሌላኛው ነገር እግዚአብሔር በሰጠን በዚህ ውድ ጊዜ ቆም ብለን ልናስብና ምን ላይ እንዳለን እራሳችንን በመመርመር ከእግዚአብሔር ጋር ስላለን ጊዜ ተገቢ ውሳኔ ላይ መድረስ ያስፈልጋል::
በአጠቃላይ እንደ ክርስቲያን አገልግሎት ተገቢ እና በትጋት ልናደርገው የሚገባ ነገር ቢሆንም የአገልግሎታችን መሠረት የሆነውን ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን የግል ጊዜ ቸል ልንል አይገባም። አገልግሎት ከእግዚአብሔር ከሰማነውና ካስተማረን ለሌሎች ጥቅም የምንውልበት ነውና።