Cairo Mission for Nation International Church Egypt

  • Home
  • Egypt
  • Cairo
  • Cairo Mission for Nation International Church Egypt

Cairo Mission for Nation International Church Egypt Cairo Mission for Nation Int'l Church is the branch of East & Central Africa Command Sudan / Khartoum . Now Pastor Biniam Kidie is z main pastor.

05/07/2022


ዛሬ ማክሰኞ ምሽት
ልዩ ፀጋ የመካፈልና የአምልኮ ጊዜ

በአዲስ አበባ ተልዕኮ ለትውልድ አፖስትሊክ ሴንተር

አድራሻ:- ከቄራ ወደ ጎተራ በሚወስደው መንገድ ንስር መኪና መሸጫ ፊት ለፊት

05/07/2022

ምዕራፍ - 38
በሌሎች ላይ ቶሎ በክፉ መፍረድን ለምን አቆምኩ?!
➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖
መንፈሳዊ ነገር ብዙም ባልገባኝ የልጅነት ወራቶቼ ከነበሩኝ ባህሪዎች አንዱ ሰዎች ላይ ቶሎ በክፉ የመፍረድ ባህሪ ነበር። ይህ ማለት ገና እንዳየሁ "ይህ ሰው ማለት እንዲህ ነው" ብሎ የመፈረጅ ክፉ አባዜ ማለት ነው። የሰውን ውጫዊ ገፅታ አይቶ ለፍርድ መቸኮል እንኳን በእኔ በታላቁ የእግዚአብሔር ሰው ነብይ ሳሙኤል ላይ የነበረ ትልቅ ችግር እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ በግልፅ ይናገራል። ይገርማችኋል! በሳሙኤል እይታ ቢሆን ኖሮ ትንሹ ዳዊት በፍፁም ሊቀባ አይችልም ነበር። ለዚህ ነው መጽሐፍ " ሰው ፊትን ያያል እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል።" የሚለው። ለዚህም ይመስለኛል እግዚአብሔር ስትፆሙ አለ "ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ።" ያለው። በሌላ ስፍራ ላይ " ይህ ህዝብ በከንፈሩ ብቻ ወደእኔ ይቀርባል ፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው። " ይላል። ውድ ወዳጆቼ! በጣም ብዙ ጊዜ ሰውን ገና እንዳየሁ አእምሮዬ በመፍረድ ተታልዬ አውቃለሁ። በውጫዊ ገፅታ ማለትም በአለባበስ፣ ወይም በፀጉር አቆራረጥ፣ ወይም በአረማመድ ስታይል (እየነጠረ ስለሚሄድ) ፣ ወይም በአነጋገር ስታይል አይቼ "ይሄ ዱርዬ ነው" ብዬ ስፈርጅ ጌታ ብዙ ጊዜ አስተካክሎኛል። እውነትም እኔ እንዳልኩት ዱርዬ ሳይሆን እጅግ መልካምና ትሁት ሰዎች ሆነው ያገኘኋቸው ብዙ ናቸው። በአንፃሩ "ትሁት ፣ መልካም እና ቀና ናቸው" ብዬ ያሰብኳቸው ሰዎች እጅግ ተንኮለኞች ፣ አስመሳዮች እና አታላዮች ሆነው ያገኘኋቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። ይህ ሲባል ሁልጊዜ እንደዚህ ነው ማለት አይደለም። ትልቁ ነገር ሰው በውጪው አይተን ወዲያው እንደምንፈርጀው አይደለም። ቀርበን ካላየነው እና ካላዳመጥነው በፍፁም ልናውቀው አንችልም። ከዚህም የበለጠ እግዚአብሔር ስለዚያ ሰው የሚላችሁ ነገር በጣም ወሳኝ ነው። እግዚአብሔር ጣልቃ ባይገባ ዳዊት በምን መመዘኛ ለንግስና ይታጫል?! የሚሆን ነገር አልነበረም ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ካለ ለሰው ባይመስል እንኳን መቀባትህ /ሽ አይቀርም። እግዚአብሔር ይመስገን!!

ውድ ወዳጆቼ! በመንፈሳዊ ነገር እያደግሁ ስመጣ በሰዎች ላይ ቶሎ መፍረድ እንዴት እንዳቆምኩ ታውቃላችሁ? እንዲህ ነው ነገሩ። መጽሐፍ ሲናገር “ወንድሞች ሆይ፥ እርስ በርሳችሁ አትተማሙ። ወንድሙን የሚያማ በወንድሙም የሚፈርድ ሕግን ያማል በሕግም ይፈርዳል፤ በሕግም ብትፈርድ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም።” (ያዕቆብ 4፥11) ይላል። ለካስ ወንድሜን ለማማት እና ወንድሜ ለመፍረድ ውስጤ ላይ ህግ (ሚዛን) ያስፈልገኛል። ለካስ በራሴ ሚዛን እየመዘንኩት ነው ወንድሜ ላይ የፈረድኩበት እና ያማሁት። ልክ ሚዛኑን መጣል ስጀምር ወንድሜን ከማማት ወይም በወንድሜ ላይ ከመፍረድ ይልቅ መውደድ ጀመርኩ ።

የሰው ሁሉ ችግር አእምሮው ውስጥ ስለሌላው ሰው መለኪያ ሚዛን ወይም ህግ አለው። ለምሳሌ፦ "ንጉስ መሆን ያለበት ቁመቱ ዘለግ ያለ ፤ ደረቱ ሰፋ ያለ ሰው ነው" የሚል መለኪያ ነብዩ ሳሙኤል ውስጥ ነበር። ይህ ግን የእግዚአብሔር መለኪያ አልነበረም ፤ የእግዚአብሔር መለኪያ የልብ ሁኔታ ነበር። ልክ እንደዚሁ ሰዎችን በራሳችን ግምት ፣ ወይም ባህሉ በሰጠን ፣ ወይም ከቤተሰብ በወረስነው ፣ ወይም በትምህርት ቤት በቀሰምነው ዕውቀት ተነስተን ሰው ላይ ፈጥነን እንፈርዳለን። ከእነኚህ መለኪያዎች ተነስተን ያለርህራሄ ሰውን እንገድላለን ፣ ሌላውን እናጠፋለን ፣ እናሳዳለን ፣ እናፈናቅላለን ፣ ከስራ እናባራለን ፣ እንጨክናለን ፣ እናማለን ፣ እንጠላለን ፣ ወዘተ... ሳናውቀው በተዛባ መለኪያ ሰዎችን መዝነን እናጠቃቸዋለን ፤ የተገለሉ እናደርጋቸዋለን። ለዚህ ነው ጌታ ኢየሱስ ሲናገር " በሰው ፊት የከበረ አለ ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት የተናቀ ነው።" አለ። ምናልባትም እኛ እዚህ የናቅናቸው ፣ ክብር ያልሰጠናቸው ፣ ያዋረድናቸው ፣ ዱርዬ ናቸው ያልናቸው ፣ ኃጢአተኛ ናቸው ፣ ትዕቢተኛ ናቸው ያልናቸው ፣ በተለያየ መለኪያ የጣልናቸው ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት እጅግ የከበሩ ሊሆኑ ይችላሉ። እግዚአብሔር ብቻ ይቅር ይበለን። እስከዛሬ ጌታ የተቀበላቸውን ስንቱን አሳደን ይሆን? ስንቱን አምተን ይሆን? ስንቱስ ላይ አላግጠን ይሆን? አስባችሁታል ከሰማይ የወረደውን የእግዚአብሔርን ልጅ ኢየሱስን አይተውት በእነርሱ መለኪያ "አጋንንት አለበት" አሉት። ምናልባትም "አጋንንት አለባቸው" ያላችኋቸው ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ከእናንተ በእጅጉ የተሻሉ ሊሆኑ ቢችሉስ?

ውድ ወዳጆቼ! ይህ ሲገባኝ ነው ከአእምሮዬ ላይ ሚዛኑን አውልቄ የጣልኩት። ሰውየው ላይ ከመፍረዴ በፊት ሰውየውን መውደድና በሰውየው ጫማ ውስጥ ሆኖ ነገሩን ማየት የጀመርኩት። በጣም የሚገርመኝ ሌላው ላይ በፈረድኩበት ጉዳይ ብዙ ጊዜ እኔ ራሴ ስወድቅ ራሴን አግኝቼዋለሁ። ለዚህ ነው የፍርድ መለኪያዬን መጣል ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም መራራት ፣ ነገ እኔም በዚያ ድካም ውስጥ ላልፍ እንደምችል መረዳት እንዳለብኝ የገባኝ ። ትላንት እከሌ በድሎኛል ብለህ ዛሬ አንተ መበደል ከጀመርክ በምን ተሻልክ? በሌላው በፈረድክበት ጉዳይ አንተ አልተገኘህም? ሌላውን ኃጢአተኛ ብለህ ድንጋይ ወርውረህ ልትገድል ያለኸው ሰውዬ ራስህ በእውነተኛው ዳኛ ፊት ቀርበህ " ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት የመጀመሪያውን ድንጋይ አንስቶ ይውገራት " ሲል ከትልቅ እስከ ትንሽህ ድንጋይን ጥለህ የሄድከው እንዴት ይረሳሃል? ግመል የሚያክል የራስህን ኃጢአት ውጠህ ትንኝ የምታክለውን የሌላውን ኃጢአት ለማጥራት ስንቴ ሄድክ? በራስህ አይን ላይ ምሰሶ የሚያክል በደል አስቀምጠህ ስንት ጊዜ በወንድምህ ውስጥ ያለችውን ትንሽዬ ጉድፍ ካላጠራሁ አልክ? ይህ በእርግጥ ግብዝነት አይደለምን? እንደዚህ ከሆንን ማን ማንን ይረዳዋል? ማን ማንን ያሳዋል? ማንስ ለማን ይደርስለታል? እናስተውል።

ውድ ወዳጆቼ! የፅሑፌ አላማ ሁሉን ሰው አግበስብሰን ወደ ህይወታችኝ ፣ ወይም ወደ ስራችን ወይም ወደ አገልግሎታችን እናስገባ ማለት አይደለም። አላማዬ በሌሎች ላይ ፈጥነን ከመፍረዳችን በፊት

1. መለኪያችንን (ሚዛናችንን) ምንድነው? የሚለውን እንድንመለከት ፣
2. ከፍርድ በፊት ፍቅርን እንድናስቀድም ፣
3. ሌላውን ሰው ቀርቦ ለመረዳት የሚሆን የልብ ቅንነት እንዲኖረን ፣
4. "እግዚአብሔርስ ስለዚያ ሰው ምን እያለን ነው?" የሚለውን አውቀን ለጌታ ድምፅ እንድንታዘዝ ፣
5. ምናልባትም በምንፈርድበት ጉዳይ እኛ ራሳችን የባስን ሆነን እንዳንገኝ ፣
6. ምናልባትም አላስፈላጊ የጌታን ፍርድ በላያችን ላይ እንዳናጠራቅም እና
7. ከሰዎች ሁሉ ጋር በአግባቡ በሰላም የምንኖርበትን ፀጋ እያዳበርን እንድንሄድ ወይም ልበ-ሰፊዎች እንድንሆን በማሰብ ነው።

ተባረኩልኝ ፤ እወዳችኋለሁ!!

ፓስተር ተስፋጽዮን ዳዊት
ማክሰኞ ሰኔ 28/2014 ዓ.ም
July 05/2022 G. C.

መልዕክቱ ከጠቀመዎት ለሌሎች ሼር ያድርጉ ፤ አስተያየትዎንም ይፃፉ።

29/06/2022

ምዕራፍ - 36
በህይወቴ ላይ ለውጥ (Change) ስፈልግ ከምን እጀምራለሁ?!
➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖
በመጣሁባቸው የህይወት ጉዞዎቼ ውስጥ በጣም ከምጠላው ነገር አንዱ የተደጋገመ አንድ ዓይነት የህይወት ስርዓት መኖር ነው። ይህ በጣም አሰልቺና የሞትኩ ያህል እንዲሰማኝ የሚያደርገኝ ነገር ነው። እኔ በህይወት ኖርኩ ብዬ የማስበው መብላትን ፣ መጠጣትን ፣ መዝናናትን ፣ ገንዘብ ማግኘትን ወይም ሚስት አግብቶ ልጆች መውለድን ወይም ተምሮ ስራ መቀጠርን አይደለም። አውቃለሁ እነዚህ ነገሮች በጣም አስፈላጊ ናቸው ፤ እኔ ግን የማስበው እነኚህ ነገሮች ወደምድር የመጣሁበትን ዋነኛ አጀንዳ ማስፈፀሚያ መሳሪያዎች እንጂ የህይወቴ ዋና ግቦች እንዳይደሉ ነው ። ለምንድነው እዚህ ምድር ላይ የመጣሁት? የመጣሁበትን ዋና አጀንዳ በርግጥ እየፈፀምኩ ነው? እየፈፀምኩ መሆኔንስ በምን አውቃለሁ? ውድ ወዳጆቼ! እነኚህ የዘወትር ጥያቄዎቼ ነበሩ ። ተስፋዬ የሚለመልመው የተጠራሁበትን (እዚህ ምድር ያለሁበትን አጀንዳ) በፈፀምኩ ቁጥር እንደሆነ ጠንቅቄ አውቃለሁ ። ዋጋ ቢያስከፍለኝ እንኳን እየከፈልኩ በመቀጠሌ ደስ የሚለኝ ለዚያ ነው። የሚገርመው ግን የመጣሁበትን ታላቁን አጀንዳ በመስራቴ ወድቄ ወይም ከስሬ አላውቅም ፤ እግዚአብሔር ባርኮኛል። ጌታ ይመስገን!

ውድ ወዳጆቼ! የህይወት አጀንዳዬን በምፈፅምበት ጊዜ ሌላው የሚያሳስበኝ ዋናው ጉዳዬ በርግጥ እየተለወጥኩ ነው ወይ? ወይስ ባለሁበት ነው ያለሁት? የሚለው ነው። አንዳንድ ጊዜ የተለወጥኩ እየመሰለኝ አንድ አይነት ቦታ ደጋግሜ ስረግጥ ራሴን አገኛለሁ። መንፈስ ቅዱስ ሲያነቃኝ እንደገና ከቆምኩበት እቀጥላለሁ። ለዚህ ነው በህይወታችን ላይ ፀሎት አስፈላጊ የሚሆነው።

ውድ ወዳጆቼ! ከዚህ በፊት ገና ታዳጊ እያለሁ ላለመለወጤ ምክንያት አድርጌ የማስበው ዙሪያዬ ያሉ ነገሮችን ነበር። ይህ ማለት እኔ ያልተለወጥኩት በቤተሰቤ ምክንያት እንደሆነ ፣ ወይም በምኖረው ዝቅተኛ ኑሮ ምክንያት ፣ ወይም የተመቻቸ ኑሮና አካባቢ ላይ አለመወለዴን ፣ አንዳንድ ጊዜ ኢትዮጵያዊ መሆኔ ራሱ ችግር ያለበት ይመስለኝ ነበር። አብዛኛዎቻችንም ላለመለወጣችን የምንደረድራቸው ብዙ ምክንያቶች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ ። የሚገርመው ግን ከእነዚያ ምክንያቶች ተላቀን የለውጣችንን ጉዞ ወስነን ካልጀመርን ሁሌም እንዳማረርን ባለንበት እንቀራለን እንጂ አንለወጥም ። አለቆቻችንን እያሳበብን ፣ ያለንበትን ድርጅት ወይም ተቋም ሰበብ እያደረግን ፣ መንግስትን እያሳበብን ፣ እናትና አባታችንን እየወቀስን ፣ አካላዊ ገፅታችንን ምክንያት አድርገን ፣ አለመማራችንን ሰበብ አድርገን አእምሯችንን ዝግ አድርገን ከተቀመጥን መቼም አንለወጥም።

ውድ ወዳጆቼ! ልክ በመንፈሳዊ ነገር እያደግሁ ስመጣ የገባኝ ምስጢር ለካስ የህይወት መውጫ ከእኔው ልብ እንጂ ከየትም አይደለም። መጽሐፍም የሚለው "የህይወትህ መውጫ ልብህ ናት" ነው። "ስለዚህ የእኔ ለውጥ በማንም እጅ አይደለም ያለው ፤ ለውጤ በራሴ እጅ ነው ያለው" ብዬ ማሰብ ጀመርኩኝ ። ስለዚህ ማንም ላይ ማሳበብ ፤ ማንንም መውቀስ አቆምኩኝ ።ለመለወጥ ሳስብ ከፍተኛው ጦርነት ከራሴ ጋር ሆነ። ራሴን ማሳመን ፣ ስንፍናዬን መዋጋት ፣ አላስፈላጊ ባህሪዎቼን በተቻለኝ መጠን መቅረፍ ፣ ጠቃሚ ባህሪዎችን እየገነባሁ መምጣት ፣ ሁልጊዜም ለመማር የተዘጋጀ ልብ መያዝ ፣ እንደጨረሰ ሰው ሳይሆን የኋላውን እየረሳ ከፊቱ ያለውን ለመያዝ እንደሚዘረጋ ሰው መሆን ፣ አንዳንድ ጓደኞቼን ከህይወቴ ላይ መቁረጥ ፣ አንዳንድ ቦታዎች መሄድ ማቆም ፣ አንዳንድ ጊዜ የሚበሉብኝ ጌሞችን ማቆም ፣ ባህሪዬን የማይገነቡ ቪድዮዎችን ማየት ማቆም ፣ ወዘተ... ነበረብኝ። በአንፃሩ ደግሞ ብዙ ጊዜዬን ለለውጥ የሚያነሳሱኝ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ እና ለብቻዬ ማሰላሰል ግዴታዬ አደረኩኝ። እንደዚህ አይነት ውሳኔዎች እንደምናወራቸው ቀላል አይደሉም ፤ ቆራጥነት ይጠይቃሉ። ውስጣቸው ላይ ህመም (Pain) አላቸው። አንዳንዴም ተስፋ ቆርጠን ወደነበርንበት ልንመለስም እንችላለን። እኔም ብዙ ጊዜ ወደነበርኩበት ስንፍናና ጥሩ ያልሆኑ ባህሪዎች ተመልሼ አውቃለሁ። ነገር ግን እንደገና ተነስቶ ወደፊት በመሮጥ አምናለሁ። ደክሞኝም ቢሆን ፣ ጉልበቴም ዝሎ ቢሆን ስለመለወጤ ለደቂቃም ብትሆን ላስብ እፈልጋለሁ።

ውድ ወዳጆቼ! ለእኔ መለወጥ ማንንም ተጠያቂ አላደርግም ፤ ራሴን ነው የምጠይቀው። ለመለወጥ ምን እያደረኩ ነው? እየተማርኩ ነው? እያሰላሰልኩ ነው? ምንም ዓይነት ስራ ሳልንቅ በደስታ እየሰራሁ ነው? እየፀለይኩ ነው? መንፈሳዊ መልዕክቶችን እያዳመጥኩ ነው? የህይወት ዘመን አሰልጣኞችን ወይም አማካሪዎችን እያማከርኩ ነው? ከሌሎች ልምድ ለመቅሰም ሙከራ አድርጌያለሁ? ዝቅ ብሎ ለመነሳት የሚሆን ትሁት ባህሪስ አለኝ? ወይስ እንዲሁ በባዶ ራሴን እቆልላለሁ? ሰዎችን እንደየባህሪያቸው ለመሸከም ዝግጁ ነኝ? ወይስ ቶሎ ቁጡ እሆናለሁ? ከትንሽ ለመጀመር ዝግጁ ነኝ ወይስ ትንሿን ነገር እንቃለሁ? የሌሎች ስኬት አበሳጭቶኝ ተስፋ ያስቆርጠኛል? ወይስ በስኬታቸው በመደሰት ነገ እኔም እነርሱ የደረሱበት እንደምደርስ ተስፋ አደርጋለሁ? አለቆቼን አከብራለሁ ወይስ እንቃቸዋለሁ (እሰድባቸዋለሁ ) ? ወዘተ... እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ።

ውድ ወዳጆቼ! ከእግዚአብሔር ጋር የለውጣችሁ ባለቤት እናንተው ራሳችሁ ናችሁ። ለእናንተ ማንም አይለወጥላችሁም ። ማንም ያዝንልኛል ብላችሁ አታስቡ ፤ ማንም አያዝንላችሁም ። የሆነ ሰው ይሸከመኛል ብላችሁ አታስቡ ፤ ማንም አይሸከማችሁም ፤ ሁሉም ከትንሽ ጊዜ በኋላ ይሰለቻችኋል ። ይልቅ ራሳችሁን ለመሸከም ተዘጋጁ ። "ለምን አያስቡልኝም?" አትበሉ ። ከእግዚአብሔር በቀር ማንም አያስብላችሁም ፤ ለራሳችሁ ቁጭ ብላችሁ ብታስቡ ይሻላችኋል ። እውነቱን ልንገራችሁ ። ይህ ዓለም ከጥቅም ጋር የተሳሰረ ነው። ካልጠቀማችሁት አውጥቶ ይጥላችኋል ። እዚህ ዓለም ላይ ያየሁት ነገር ማንም ሰው ከአሸናፊ ወገን ነው መሆን የሚፈልገው። አሸናፊ መሆንህን ሲያረጋግጡ ይከተሉሃል ፤ ወዳቂ መሆንህን ሲያዩ ይሸሹሃል። ውድ ወዳጆቼ! ቁጭ ብላችሁ አታልቅሱ ተነስታችሁ አሸናፊነታችሁን እያረጋገጣችሁ ቀጥሉ ።

በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን ተብሎ እንደተፃፈ የአሸናፊነትና የለውጥ መንፈስ በኢየሱስ ስም ያግኛችሁ ። አሜን!!

ተባረኩልኝ ፤ እወዳችኋለሁ!!

ፓስተር ተስፋጽዮን ዳዊት
ረቡዕ ሰኔ 22/2014 ዓ.ም
June 29/2022 G. C.

መልዕክቱ ከጠቀመዎት ለሌሎች ሼር ያድርጉ ፤ አስተያየትዎንም ይፃፉ።

25/06/2022

ምዕራፍ - 35
እጅ መጫን በህይወቴ ላይ ምን ጠቀመኝ ?! ምንስ ጎዳኝ?!
➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖
በህይወቴ እጅግ በጣም ከምወዳቸው ነገር ግን ከምጠነቀቅባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ እጅ መጫን ነው። እጅ መጫን በመጽሐፍ ቅዱስ በግልፅ ከተቀመጡ አስተምህሮዎች መካከል አንዱ እንደሆነ አምናለሁ። እጅ በመጫን ውስጥ የሚተላለፉ መንፈሳዊ ምስጢሮችም እንዳሉ አውቃለሁ። ለምሳሌ:- ሙሴ ኢያሱ ላይ እጅ በመጫኑ ምክንያት የተካፈለውን የአመራር ጥበብ አውቃለሁ ፤ እንዲሁም ወጣቱ አገልጋይ ጢሞቲዎስም በሽማግሌዎች እጅ መጫን የተካፈለው ስጦታ እንደነበር ሐዋርያው ጳውሎስ በግልፅ ፅፎልናል። በአንፃሩ ደግሞ እጅ የሚጭኑብን ሰዎች የክፉ መንፈስ ተጠቂ ከሆኑ ያንኑ መንፈስ ሊያካፍሉን ይችላሉ። ለምሳሌ :- የዝሙት መንፈስ ያለበት አገልጋይ እጁን ሲጭንብን ያንኑ የዝሙት መንፈስ ነው የሚያካፍለን። ውድ ወዳጆቼ! ማንም ሰው ያለውን ያንኑ ነው የሚያካፍለን ፤ የሌለውን ሊያካፍለን አይችልም።

ውድ ወዳጆቼ! እስከዛሬ ለደረስኩበት መንፈሳዊ እድገቴ ፣ ለአገልግሎቴ ፣ ለበረከቴ ፣ ለቤተሰቤ መሳካት ፣ ለፈውሴ ፣ ለተከፈቱልኝ በሮች ፣ ለሚገለጡብኝ የፀጋ ስጦታዎችና ላለኝ ጥንካሬ የረዳኝ እጃቸውን የጫኑብኝ ታላላቅ የእግዚአብሔር ሰዎች አስተዋፅኦ ነው ብዬ አምናለሁ። 'ታላላቅ' ስል የግድ አለም ላይ ታዋቂ የሆኑ ማለት አይደለም ፤ ይልቁኑ በእኔ ህይወት ትልቅ ስፍራ ያላቸው ማለት ነው። የሚገርማችሁ በአንፃሩ ደግሞ ጥቂት የሚሆኑ እጃቸውን የጫኑብኝ ሰዎች ከጫኑብኝ በኋላ ህይወቴ የተበላሸባቸው ፣ ባህሪዬ ላይ ደስ የማይሉ ነገሮችን እንድለማመድ የሆንኩባቸው ፣ በህልሜ የተሰቃየሁባቸው በኋላ ግን ሌሎች የማከብራቸው የእግዚአብሔር ሰዎች እጅ ጭነው ፀልየውልኝ ነፃ የወጣሁባቸው ጉዳዮች አሉ። እውነት ለመናገር አንዳንዱ አገልጋይ እንኳን ጭኖብኝ ይቅርና ዝም ብሎ ሲያወራኝ ራሱ ክፉ ሃሳብ ገብቶብኝ ያውቃል። ወዳጆቼ ይህንን ጉዳይ ቀላል አድርጋችሁ እንዳታስቡት ፤ ለረዥም አመታት ተቸግሬ አውቃለሁ ፤ ጌታ ረድቶኝ ነው የወጣሁት። ከዚህ የተነሳ እጅ መጫንን በተመለከተ ያዳበርኳቸው አመለካከቶች አሉ። ምን አልባት እነኚህ አመለካከቶቼ ሊጠቅሟችሁ ይችላሉ ፤ ነገር ግን እንደማይጠቅማችሁ ካሰባችሁ ልትተዉት ትችላላችሁ። እነኚህ አመለካከቶቼ ምንድናቸው?

1. እጅ በመጫን እጅግ በጣም አምናለሁ። በየጊዜው እጅ ይጫንልኛል ፤ እኔም እጅ እጭናለሁ ፤

2. ያገኘሁት የእግዚአብሔር ሰው ሁሉ ጋር ግን እጅ አላስጭንም ፤ መጀመሪያ የሰውየውን የህይወት ደረጃ በመንፈስ ለመለየት ጥረት አደርጋለሁ ፤

3. መንፈሴ ላይ ስለ ሰውየው ጥሩ ስሜት ካልተሰማኝ በፍፁም እጅ አላስጭንም ፤ ቢቀርብኝ ይሻለኛል ፤

4. አንዳንድ ጊዜ ድንገት ውስጤ ደስ ሳይለው ነገር ግን እንዳይጫንብኝ ማድረግ የማልችልበት ሁኔታ ከገጠመኝ የማደርገው ከዚያ ሰው መልካም የሆነው ነገር ብቻ ወደ እኔ እንዲሻገር ክፉው ግን እንዳይሻገርብኝ በኢየሱስ ደም ራሴን እየሸፈንኩ እፀልያለሁ ፤

5. እጅ በመጫን ባምንም መጽሐፍ እንደሚል ግን ፈጥኜ በማንም ላይ እጅ አልጭንም ፤ ምክንያቱም በዚያ ሰው ኃጢአት መተባበር (ወይም ያንን ሰው empower ማድረግ) አልፈልግም ፤ ስለዚህ የመንፈስን ምሪት እከተላለሁ፤

6. ቤተክርስቲያን ላይ መድረክ ላይ ያለ የእግዚአብሔር ሰው "አጠገባችሁ ባለው ሰው ላይ እጅ ጭናችሁ ፀልዩ" ሲባል በቅንነት እታዘዛለሁ ፤ በዚያ ሰዓት እኔ የማምነው አጠገቤ ያለው ሰውዬ ነገር ያልፍብኛል ብዬ ሳይሆን መድረኩን የያዘውና መንፈሳዊ ትዕዛዙን ያዘዘው የእግዚአብሔር ሰው ቅባት ያልፋል ብዬ ነው ፤

7. እጅ በእኔ ላይ የመጫን መብት የሰጠኋቸው የእግዚአብሔር ሰዎች አሉ። እነርሱም :-
7.1. መንፈሳዊ መሪዎቼ ወይም አለቆቼ
7.2. በእኔ ህይወት መንፈሳዊ ተካፍሎት ያላቸው ማለትም ለረዥም ጊዜ ያስተማሩኝ ፣ የመከሩኝ ፣ የገሰፁኝ እና ለደረስኩበት ህይወት አስተዋፅኦ ያላቸው
7.3. ባላቸው የህይወትና የአገልግሎት ፍሬ ምስክርነት ያላቸው የእግዚአብሔር ሰዎች
7.4. በመንፈስ ቅዱስ ተመርቼ እጅ እንዲጭኑልኝ ጌታ የነገረኝ የእግዚአብሔር ሰዎች
7.5. ከፍ ያለ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ልምምድ ያላቸው እና አለምአቀፋዊ ተፅእኖ ያላቸው የእግዚአብሔር ሰዎች
7.6. ረዥም የታማኝነት እና ዋጋ መክፈል አገልግሎት ጉዞ የመጡ የተመሰከረላቸው አባቶችና እናቶች
7.7. አብረውኝ የሚያገለግሉ የማምናቸው አገልጋዮች

8. እኔ ደግሞ ቢለምኑኝ እንኳን እጅ የማልጭንባቸው ሰዎች አሉ። እነዚህም :-
8.1. መንፈሳዊ አባቶቼ (አስተማሪዎቼ) ላይ በፍፁም አይሆንም
8.2. መንፈሳዊ አለቆቼ ላይ እጅ አልጭንም
8.3. ፀጋን ለመካፈል እግሩ ስር ለተቀመጥኩለት የእግዚአብሔር ሰው እጅ አልጭንም
8.4. ፈቃደኛ ላልሆነ ሰው እጅ አልጭንም
8.5. መንፈሴ ላልፈቀደለት ወይም ውስጤን ደስ ላላለው ሰው እጄን አልጭንም
8.6. ሚስጥራዊ የኃጢአት ልምምድ ውስጥ ሆኜ እጄን በማንም ላይ አልጭንም
8.7. እምነት ሳይኖረኝ በማንም ላይ እጄን አልጭንም

9. በህይወቴ ፈቅጄ እጁን የጫነልኝን ሰው አላማውም (ሀሜት ማለት ነው) ፣ ሲታማም መስማት አልፈልግም ፣ አልቃወመውም ፣ ከሚቃወሙትም ሰዎች ወገን ሆኜ አልሰራም ።

- እንኳንና እጁን ጭኖ ፀጋ ላካፈለኝ የእግዚአብሔር ሰው ይቅርና በህይወቴ አንዲት ቀን ለረዳኝ ማንኛውም ሰው ትልቅ ክብር አለኝ።

10. እጁን የጫነብኝ ሰው እንደበደለኝ ከተሰማኝ ይቅር እለዋለሁ ፤ በተደጋጋሚ የሚበድለኝ ከሆነ አሁንም ይቅር እለዋለሁ ነገር ግን ከጌታ ጋር ተነጋግሬ "ታገሰው" ካለኝ እታገሰዋለሁ ፤ ተለየው ካለኝ ያንን የእግዚአብሔር ሰው ምንም ሳላሳዝን እለየዋለሁ። ከተለየሁት በኋላ ያ የእግዚአብሔር ሰው ስሜን ቢያጠፋ እንኳን እርሱን የሚጎዳ ነገር በፍፁም አላደርግም። ይህ እስከዛሬ የመጣሁበት ጉዞ ነው።

ውድ ወዳጆቼ! እጅ በመጫን ውስጥ ከተጎዳሁት ይልቅ በህይወቴ የተጠቀምኩት እጅግ ይበልጣል። ለዚህ ነው በልዩ ልዩ ጊዜዎች ኃይልን ለመቀበል ፤ ፀጋን ለመካፈል እጅ ለማስጫን የእግዚአብሔር ሰዎች ጋር እመጣለሁ። ስመጣ በጣም በአክብሮት ፣ በፍፁም ትህትና እና ፍቅር ነው በፊታቸው የምቀርበው ።

ይህንን ለምታነቡ ወዳጆቼ እፀልያለሁ እጅ የሚጭኑላችሁ መልካም የሆኑ ልባችሁ የሚያርፍባቸውን የእግዚአብሔር ሰዎች በኢየሱስ ስም ይሰጧችሁ! አሜን።

ተባረኩልኝ ፤ እወዳችኋለሁ!!

ፓስተር ተስፋጽዮን ዳዊት
ቅዳሜ ሰኔ 18/2014 ዓ.ም
June 25/2022 G. C.

የቴሌግራም ቻናሌን መቀላቀል አይርሱ!!

መልዕክቱ ከጠቀመዎት ለሌሎች ሼር ያድርጉ ፤ አስተያየትዎንም ይፃፉ።

16/06/2022

በወንጌል አንደራደርም ፤ አብረን እንሰብካለን!!

እርስዎም ይገኙ ፤ ሼርም ያድርጉ!!
🔥🔥🔥🔥🔥🔥🔥
Glory of God TV / Prophet Zekariyas

16/06/2022


ልዩ የኃይል ኮንፍራንስ በስዊድን ስቶኮልም
ከሐዋርያ ዳንኤል ጌታቸው ጋር.............................................
የኮንፍራንስ ቀናት፡
ከ June 29 - June 30/2022
July 1፣ 2፣ እና July 3/2022
ሰዓት፡- 16፡00 – 21፡00 ሰዓት
አድራሻ፡- T-Centrale ለምትመጡ Hjulsta ወይም Akalla ባቡር የኃለኛውን ቫገን በመያዝ StadsHagen በመውረድ ወደላይ ትወጡና ከ3ደቂቃ የእግር ጉዞ በኃላ የቤ/ክን ህንጻ ያገኙታል፡፡

ከ Akalla ወይም Hjulsta ለምትመጡ ደግሞ የባቡሩን የፊተኛውን ቫገን በመያዝ StadsHagen ወርዳችሁ ወደላይ በመውጣት የቤ/ክን ህንጻ ያገኙታል፡፡

የቤተክርስቲያኑ ስም፡
SOS Church Stockholm
Warfvings vag 26 StadsHagen

ለበለጠ መረጃ፡ 073-892-4688/073-768-3803

አዘጋጅ - ተልዕኮ ለትውልድ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ስዊዲን ስቶክሆልም

12/06/2022

ምዕራፍ - 31
ስለ ነብያት እና ስለሚመጡልኝ የግል ትንቢቶች የእኔ አቋም ምንድነው?!
➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖
እስከ አሁን በመጣሁባቸው የህይወትና የአገልግሎት መንገዴ ከትንቢት ጋር ተያይዞ ያዳበርኳቸው አቋሞች አሉ።ባሳለፍኳቸው ዓመታት ብዙ እውነተኛ ነብያት ገጥመውኝ ያውቃሉ ፤ ደግሞም ሐሰተኛ ነብያት ገጥመውኝ ያውቃሉ ፤ ብዙ እውነተኛ ትንቢቶች መጥተውልኝ ያውቃሉ ፤ ደግሞም ሐሰተኛ ትንቢቶች መጥተውልኝ ያውቃሉ። በመጣሁበት መንገድ በድፍረት የሐሰት ትንቢት አምጥተውልኝ ፊት ለፊት ትክክል አለመሆናቸውን የነገርኳቸውም አሉ። ውድ ወዳጆቼ! እኔ "በአዲስ ኪዳን ነብያት የሉም " ከሚሉ ወገን አይደለሁም። ለቤተክርስቲያን ከተሰጡ አምስቱ የፀጋ ቢሮዎች (5 Fold Offices) መካከል አንዱ የነብይነት ፀጋ እንደሆነ አምናለሁ (ኤፌሶን 4፤11) ፤ እስከ ክርስቶስ ዳግም ምፅአት እነኚህ ፀጋዎች በሙሉ ይሰራሉ ብዬ አምናለሁ። ያም ብቻ ሳይሆን ትንቢትን በመናቅ ሳይሆን በመመርመር ፤ ከዚያም ትክክለኛ የሆነውን በመቀበል እና ትክክለኛ ያልሆነውን በመጣል አምናለሁ።

ታዲያ ስለ ትንቢት እና ስለ ነብያት ያሉኝ አቋሞች ምን አይነት ናቸው? ውድ ወዳጆቼ! እነኚህ በመጣሁባቸው መንገዶቼ እና ባለችኝ ጥቂት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዕውቀት ያዳበርኳቸው የእኔ የግል አቋሞቼ ናቸው። ማንም ላይ ለመጫን አይደለም ፤ ማንም የመቀበልም ያለ መቀበልም መብት አለው። ስለዚህ መቀጠል እንችላለን :-

1. እውነተኛ የአዲስ ኪዳን ነብይ የትንቢቱ ዋና ዓላማ ህዝቡን በክርስቶስ መስቀል ወደ ተሰራው ስራ ማምጣት ነው ብዬ አምናለሁ ፤

2. ትንቢት የሚመጣው ለማነፅ፣ ለመምከር እና ለማፅናናት ነው የሚል አቋም አለኝ ፤ ከዚህ ውጪ መቀበል አልችልም ፤

3. የትኛውም ትንቢትም ሆነ መንፈሳዊ ልምምዶች የእግዚአብሔር ቃልን በፍፁም ሊተኩ አይችሉም ፤ ስለዚህ ህዝቡ በእግዚአብሔር ቃል ላይ በዋነኝነት መመስረት ይገባዋል ብዬ አምናለሁ ፤

4. በእውነተኛ የነብይነት ፀጋ ውስጥ ስህተት የለም ብዬ አምናለሁ ፤ ነገር ግን የነብዩ የመንፈሳዊ እድገት ትንቢቱን በተሳሳተ መንገድ እንዲያመጣ ሊያደርገው ይችላል ብዬ አስባለሁ። ለዚህ ደግሞ በእግዚአብሔር ቃልና በፀጋው ውስጥ ስር ሰደው ነብያት ሊያድጉ ይገባል ብዬ አምናለሁ ፤

5. በየትኛውም ነብይ ላይ በፍፁም አልፈርድም ፤ ይልቅስ ትንቢቱን በመንፈስ እመረምራለሁ ፤ በእግዚአብሔር ቃል እመዝናለሁ ፤ የውስጤን ድምፅ እሰማለሁ ፤ ውስጤን ሰላም ካልተሰማኝ እና ከተረበሽኩ ትንቢቱን አልቀበልም ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር የሰላም እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም ብዬ አምናለሁ ፤

6. በሁለት ጉዳዮች ላይ በተለይ ትንቢት አልሰማም። የመጀመሪያ ፤ በራዕዬ ጉዳይ የትኛውም "ታዋቂ" ነብይ እንኳን ቢሆን ትንቢት አልሰማም ፤ በዚህ ጉዳይ እግዚአብሔር ለእኔ ለራሴ ይናገረኝ ፤ እንደውም ለእኔ የነገረኝን ለአባቴም ይንገረው የሚል አቋም አለኝ። ምክንያቱም ራዕይ እዚህ ምድር በስጋ የመኖሬ ምክንያት ነው። ሁለተኛ ፤ በትዳሬ ጉዳይ ምንም አይነት ትንቢት አልሰማም። ይህ ሲባል ከማግባቴም በፊት ሆነ አግብቼም ቢሆን ትንቢት አልሰማም። ከፈለገ እግዚአብሔር ለእኔ ለራሴ ይናገረኝ። የትኛውም ነብይ ስለ ትዳሬ በሚለኝ መቼም አልመራም። ሚስቴን ሳገባም በትንቢት አላገባኋትም ፤ ያገባኋት ወድጃት ነው። አሁን 9 ዓመት ሆኖናል ፤ ሁለት ድንቅ ልጆች አፍርተናል። አንድም ቀን እኔም ሆንኩ ውድ ባለቤቴ በትዳራችን ጉዳይ ትንቢት ተቀብለን አናውቅም። ይኸው በሰላምና በፍቅር እየኖርን ነው።

7. ትንቢት ሁሉ ይፈፀማል የሚል እምነት የለኝም። አንዳንዱ ሊፈፀም ይችላል ፤ አንዳንዱ ላይፈፀም ይችላል ብዬ አምናለሁ። ይህ ግን የነብዩ ወይም የእግዚአብሔር ችግር ነው ብዬ አስቤ አላውቅም። ትንቢቶች የማይፈፀሙበት የተለያዩ ምክንያቶች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ። ለምሳሌ :- በራሴ ጥፋት ምክንያት ላይፈፀም ይችላል። ከእግዚአብሔር ፈቃድ ይልቅ የራሴን ፈቃድ የምከተል ከሆነ ትንቢቱ አይፈፀምም።

8. ትንቢቶች የመፈፀሚያ ጊዜያቸው ሊፈጥንም ሊዘገይም ይችላል ብዬ አምናለሁ። በእግዚአብሔር ፈቃድና ሃሳብ ላይ ስፀና ብዙ ትንቢቶች በጊዜ ሂደት ተፈፅመው አይቼ አውቃለሁ። አንዳንዱን በራሴ ምክንያቶች የዘገዩብኝ ይኖራሉ።

9. ነብይነትን ለዘመናዊ ቢዝነስ የሚጠቀሙ አገልጋዮችን ነፍሴ ትፀየፋለች። እግዚአብሔር በገንዘብ የሚባርክ አምላክ እንደሆነ ፤ የፀጋውም ባህሪ ደሃ የሚያደርግ እንዳልሆነ አምናለሁ። ያም ብቻ ሳይሆን ሰዎች ደስ ብሏቸው እንደ እግዚአብሔር ሰዎች አምነው በሚሰጡት የፍቅር (የደስታ) ስጦታ አምናለሁ። ከዚያ ውጭ ግን ለመቀበል እቸገራለሁ ፤ ያም ሆኖ እነኚያን ሰዎች በፍፁም ለመኮነን አልሯሯጥም ፤ ከእኔ መጀመሪያ የሚጠበቀውን ለማድረግ እጥራለሁ።

10. በባህሪዬ ትንቢት ለመስማት ብዬ በየቦታው የመሄድ ተነሳሽነቱ (አፒታይቱ) የለኝም። ትንቢት ለመስማት እስከዛሬ የሄድኩባቸው 3 ቦታዎች ናቸው ፤ የሚገርመው 3ቱም ቦታ ትንቢት አልመጣልኝም (😂)። ይልቁኑ ያለሁበት ድረስ የእግዚአብሔር ሰዎች እየመጡ ብዙ ትክክለኛና የተፈፀሙ ትንቢቶችን አምጥተውልኛል። ጌታ ይመስገን። ውድ ወዳጆቼ! ትንቢት ለመስማት መሄድ መጥፎ ነው እያልኩ አይደለም ፤ የእኔ ሃሳብ ለትንቢት ብሎ ከመዞር ይልቅ በእግዚአብሔር ቃል የታነፀ ስብዕና መያዝ እጅግ ወሳኝ ነው ማለቴ ነው።

ይህ ሲባል ፀጋን ለመካፈል ሲባል ብዙ ቦታዎች እና አገሮች በመሄድ አምናለሁ ፤ አሁንም እሄዳለሁ። ስሄድ ግን መንፈሴ ያረፈበትና የማምነው የእግዚአብሔር ሰው ጋር እንጂ ያገኘሁት ሁሉ ጋር አልሄድም።

ውድ ወዳጆቼ! ለዛሬ የተወሰኑ ጉዳዮችን አካፍያችኋለሁ። ትልቁ መልዕክቴ ግን ከምንም በላይ በእግዚአብሔር ቃል ላይ እና በክርስቶስ የመስቀሉ ስራ ላይ የተመሰረተ ህይወት ይብዛላችሁ። በግላችሁ እግዚአብሔር እንዲናገራችሁ ፀልዩ። እግዚአብሔር መንፈሳዊ ጆሮአችሁን ከፍቶ ይናገራችኋል። ሌላው የክርስቶስን መልክ ከልባችሁ የሚያጠፋባችሁን ፣ እምነታችሁን የሚመታባችሁን ፣ ከቤተክርስቲያን እንድትጠፉ የሚያደርጋችሁን ፣ ትዳራችሁን የሚያፈርስን ፣ መለያየትን (ሁከትን) የሚዘራን ፣ ከሰማችሁት ደቂቃ ጀምሮ ጭንቀት የፈጠረባችሁን ፣ በመሪዎቻችሁ ላይ እንድትነሱ የሚያደርጋችሁን ፣ ለወሲብ እና ለገንዘብ ባሪያ የሚያደርጋችሁን ትንቢትም ሆነ ፣ ራዕይም ሆነ ህልም አትስሙ። የእግዚአብሔር ቃል ላይ ተመስረቱ።

እወዳችኋለሁ ፤ ተባረኩልኝ!!

ፓስተር ተስፋጽዮን ዳዊት
እሁድ ሰኔ 05/2014 ዓ.ም
June 12/2022 G. C.

መልዕክቱ ከጠቀመዎት ለሌሎች ሼር ያድርጉ ፤ አስተያየትዎንም ይፃፉ።

06/06/2022


#ሰላም የተወደዳችሁ እንዴት ናችሁ? በጣም በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ጊዜ የተሰኘው መጽሐፍ ሊመረቅ #6 ቀን ብቻ ቀረው በዚህ ድንቅ ምርቃት እንድትገኙ በታላቅ ትህትና ተጋብዛችኋል #መጽሐፉ ውስን ቁጥር ስለሆነ በቀኑ ምርቃት ስነስርዓት ላይ የተገኙ ሁሉ 1ኛ እትሙን እንድታገኙት እመክራለሁ። #ምርቃቱ የሚካሄደው በኦንላይን ፌስቡክ ሰኔ 5 ከሰዓት 9:00 ላይ evangelist eyu በተሰኘው ቻናል ላይ ነው ወይንም Evangelist Eyu ላይ እንድትገኙ በአክብሮት ተጋብዛችኋል። #ከኢዩ የጌታ ሠራዊት ለበለጠ መረጃ whats up 0970752729

Evangelist Eyu

Address

Al Mahdi
Cairo

Telephone

+201122766905

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Cairo Mission for Nation International Church Egypt posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share