Mk agarfa mkagarfa is aimed to create awareness on holy of orthodox tewahdo church. it will enable us to transfer informations

የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ወደ ከበረ ወደ ገነነ ወደ እግዚአብሔር ጌትነትም ከሚያገቡ ከከበሩ ከሰባት አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ አላቸው።          መጽሐፈ ጦቢት ምዕራፍ 12...
08/09/2022

የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ወደ ከበረ ወደ ገነነ ወደ እግዚአብሔር ጌትነትም ከሚያገቡ ከከበሩ ከሰባት አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ አላቸው።
መጽሐፈ ጦቢት ምዕራፍ 12:6
በሰው ነፍስ የተሾመ ከከበሩ ከመላእክት አንዱ ሩፋኤል ነው
መጽሐፈ ሄኖክ ምዕራፍ 6:3
ሩፋኤል ማለት የስሙ ትርጓሜ
ሩፋ ማለት ጤና፣ፈውስ መድኃኒት ማለት ነው
ኤል ማለት አምላክ ማለት ነው
በጥምረት ,የእግዚአብሔር ሐኪም ማለት ነው ።
ሩፋኤል ከሦስቱ ሊቀነመላዕክት ሦስተኛው ሊቀ መላዕክት ነው,
ቅዱስ ሚካኤል
ቅዱስ ገብርኤል
ቅዲስ ሩፋኤል
ጳጉሜ ሦስት የቅዱስ ሩፋኤል በዓለ ሲመቱ ነው
በዚህ ቀን ሐዋርያቱ ክርስቶስን ፣ጌታ ሆይ የከበረ መልአከ የቅዱስ ሩፋኤልን ክብር ታስረዳን ዘንድ እንለምንሐለን አሉት
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም ያን ጊዜ ሦስቱን የመላአክት አለቆች ቅዱስ ሚካኤል ፣ቅዱስ ገብርኤል ፣ ቅዱስ ሩፋኤልን ከሦስተኛይቱ ሰማይ ይመጡ ዘንድ አዘዛቸው
እነሱም ደስ እያላቸው መጡ
ጌታችንም ሩፋኤልንም የክብርህን ታላቅነት ያውቁ ዘንድ ስምህን ለሐዋርያት ነገራቸው አለው
የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሩፋኤልም ለሐዋርያት እንዲህ አላቸው ፣እኔ ሩፋኤል እባላለሁ የዋህ ነኝ ከመላእክት አለቆች ሦስተኛው ነኝ ፣ ልቦናን ደስ የሚያሰኝ የዋህ ቸር ለኃጥአን የምራራ ነኝ ፣በማለት ለሐዋርያቱ ብዙ ነገር ነገራቸው
ድርሳነ ሚካኤል ዘ ጳጉሜ
የመላዕክት አለቃ ቅዱስ ሩፋኤል ሆይ፣ በዓሳ ሐሞት ኩለህ የጦቢት አይን እንዳበራህ ሁሉ የእኛንም አይነ ልቦና አብራልን አሜን .። ከሐብተ ረድኤትህም ተሳታፊ አድርገን አሜን.።
አቤቱ የቅዱስ ሩፋኤል አምላክ ሆይ ከመከራ ነፍስ ከመከራ ስጋ ሰውረን ጠብቀን አሜን ።

https://www.facebook.com/490069727707457/posts/3232340740146995/?app=fbl
03/10/2020

https://www.facebook.com/490069727707457/posts/3232340740146995/?app=fbl

+ አባቶቻችን እንዲህ አሉ +

"እሳትና ውኃን ማዋሐድ እንደማይቻል በሌሎች ኃጢአት መፍረድም በራስ ኃጢአት ከመጸጸት ጋር አብሮ አይሔድም" ቅዱስ ዮሐንስ ዘሰዋስው

"የማያማትብ እጅ ቀኙም ግራውም አንድ ነው" አባ ፓስዮስ ዘደብረ አቶስ

"እግዚአብሔር ለኃጢአተኛ ሰው ያለው ፍቅር
ጻድቅ ሰው ለእግዚአብሔር ካለው ፍቅር ይበልጣል"
አባ አርሳኒ

"ሕፃን ልጅ እናቱ ስታጥበው ያለቅሳል:: ሕፃን እምነት (ትንሽ እምነት) ያላቸው ሰዎችም ነፍሳቸውን የሚያጥብ መከራ ሲመጣባቸው እግዚአብሔርን ያማርራሉ" አባ ስምዖን

"ዕለትን የሠጠህ እርሱ ለእለት የሚበቃህንም ይሠጥሃል" ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ

"እጅግ ምርጡ ጸሎት "ጌታ ሆይ አንተ ሁሉን ታውቃለህ የፈቀድከውን አድርግልኝ" ማለት ነው"
ባሕታዊ ቴዎፋን

"ሲያመነዝር ያየኸውን ሰው አንተ ንጹሕ ብትሆንም አትናቀው:: ምክንያቱም አታመንዝር ያለው ጌታ አትፍረድም ብሏል" አባ ቴዎዶር

"አንድ ሰው ኃጢአት ሲሠራ ብታይ እንኳን አትፍረድበት:: አንዳንዴ ዓይንህም ሊሳሳት ይችላል"
ቅዱስ ዮሐንስ ዘሰዋስው

"ለኃጢአተኛው ክንፍህን ዘርጋለት:: ኃጢአቱን ልትሸከምለት ባትችል እንኳን ሸፍንለት"
ቅዱስ ይስሐቅ ሶርያዊ

ከአበው አንዱን ትሕትና ምንድርን ነው? ብለው ጠየቁት:: እርሱም "ትሕትና ማለት ወንድምህ በበደለህ ጊዜ እርሱ ይቅርታ ሳይጠይቅህ በፊት ቀድመህ ይቅር ማለት ነው" አለ::

"ይቅር ካላልክ ገነትም ይቅርብህ" አባ ኤፍሬም አረጋዊ [ If you don’t forgive, forget heaven]

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
መስከረም 22 2013 ዓ ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ዘንድ ጸልዩ! ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like እና Share ያድርጉ
FB: https://www.facebook.com/officialHenokhaile/
Telegram: https://t.me/deaconhenokhaile
Instagram: https://www.instagram.com/p/CBnMF0nnhcQ/?igshid=549jvl607bv4
Youtube: https://www.youtube.com/channel/UCOaVsWC05aUjeqIEW3fWj7g

07/04/2020
07/09/2019

ዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው;
የሙከራ ሥርጭቱ ተጀመረ
ዐዲሱ የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቭዥን የሙከራ ሥርጭት እነሆ ተጀመረ።
ሥርጭቱን ከዛሬ ጀምሮ መከታተል ትችላላችሁ።
SATELITE: NILESA TKU ወይም EUTELSA W3
FREQUENC: 11555
SYMBOL RATE: 27500
POLARIZATION: V
ስያሜ፦ EOTCMK
ጣቢያዉን ከላይ በተጠቀሰው አድራሻ ታገኙታላችሁ።
ትከታተሉት ዘንድ ማኅበሩ መንፈሳዊ ግብዣዉን አቅርቦላችኋል።
ማስገንዘቢያ፡- EOTC TVንም ተከታተሉ፡፡
‹‹የምናወቀዉን እንናገራለን፤ ያየነዉንም እንመሰክራለን፤›› (ዮሐ. ፫፥፲፩)።

"...እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ሐላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡" ቅዱስ ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ"ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት...
30/07/2019

"...እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ሐላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡" ቅዱስ ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ

"ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት" / ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን/

"አዬ፣ ምነው እመ ብርሃን ? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?
ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?
እስከመቼ ድረስ እንዲህ፣ መቀነትሽን ታጠብቂባት?
ልቦናሽን ታዞሪባት?
ፈተናዋን፣ ሰቀቀኗን፣ ጣሯን ይበቃል ሳትያት?
አላንቺ እኮ ማንም የላት….

•••
አውሮጳ እንዲሁ ትናጋዋን፣ በፋሽስታዊ ነቀርሳ
ታርሳ፣ ተምሳ፣ በስብሳ
ሂትለራዊ እባጭ ጫንቃዋን፣ እንደኮረብታ ተጭኗት
ቀና ብላ እውነት እንዳታይ፣ አንገቷን ቁልቁል ጠምዝዟት
ነፍሷን ድጦ ያስበረከካት
ሥልጡን፣ ብኩን፣ መፃጉዕ ናት፤ ….
እና ፈርቼ እንዳልባክን፣ ሲርቀኝ የኃይልሽ ውጋገን
አንቺ ካጠገቤ አትራቂ፣ በርታ በይኝ እመ ብርሃን
ቃል ኪዳኔን እንዳልረሳት፣ እንዳልዘነጋት ኢትዮጵያን፡፡

•••
አዎን፣ ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እሸሸግበት ጥግ አጣሁ
እምፀናበት ልብ አጣሁ
እማማ ኢትዮጵያን መንፈሴ፣ ተፈትቶ እንዳይከዳት ሠጋሁ …
አዋጅ፣ የምሥራች ብዬ፣ የትብት ምግቤን ገድፌ
ከእናቴ ማኅፀን አርፌ
ከአፈርዋ አጥንቴን ቀፍፌ
ደሜን ከደሟ አጠንፍፌ
ከወዟ ወዜን ቀፍፌ

•••
በሕፃን እግሬ ድሄባት፣ በህልም አክናፌ ከንፌ
እረኝነቴን በሰብሏ፣ በምድሯ ላብ አሳልፌ
ከጫጩት እና ከጥጃ፣ ከግልገል ጋር ተቃቅፌ፤
በጋው የእረኛ አደባባይ፣ ክረምት እንደወንዙ ፍሳሽ
በገጠር የደመና ዳስ፣ በገደል ሸለቆ አዳራሽ
ከቆቅ እና ከሚዳቋ፣ ከዥግራ ጠረን ስተሻሽ
በወንዝ አፋፍ ሐረግ ዝላይ፣ መወርወር መንጠልጠል ጥሎሽ
ከፍልፈል ጋር ሩጫ ስገጥም፣ ከቀበሮ ድብብቆሽ
ከናዳ ጫፍ ሣር አጨዳ፣ ለግት ላሜ ትንሽ ግጦሽ
ለጥጃዬ የሌት ግርዶሽ
ለጥማድ በሬዎች ራት፣ ለማታቸው ትንሽ ድርቆሽ
ለግልገሌ ካውሬ ከለል
እማሳው ሥር ጎጆ መትከል
ለፀሐይ የሾላ ጠለል፣ ለዝናብ የገሳ ጠለል

•••
ውሎ የንብ ቀፎ ማሰስ፣ ያበባ እምቡጥ ሲፈነዳ
የግጦሽ ሣር ሲለመልም፣ ሲሰማሩ ሰደድ ሜዳ
አዝመራው ጣል ከንበል ሲል፣ ከብቱ ለሆራ ሲነዳ
ፈረስ ግልቢያ ስሸመጥጥ፣ ከወፎች ዜማ ስቀዳ
ልቤ በንፋስ ተንሳፎ፣ በዋሽንት ዋይታ ሲከዳ …..

ያቺን ነው ኢትዮጵያ የምላት
እመ ብርሃን እረሳሻት?

•••
ያቺን የልጅነት የምሥራች? የሕፃንነት ብሥራት
የሣቅ የፍንደቃ ዘመን፣ የምኞት የተስፋ ብፅአት
ያቺን የልጅነት እናት?
አዛኚቱ እንዴት ብለሽ፣ ጥርሶችሽን ትነክሺባት?
ሥሜን በሥምሽ ሰይሜ፣ ባገልግሎትሽ ስዋትት
ከዜማ ቤት እቅኔ ቤት፣ ከድጓ ቤት እመጻሕፍት
ካንቺ ተቆራኝታ ዕድሌ፣ ካንቺ ተቆራኝታ ነፍሴ
ከቀፈፋ ደጀሰላም፣ ከቤተልሔም ቅዳሴ
እኰ፣ ቀፎ ዳባ ለብሶ
ቅኔ ዘርፎ ግስ ገሦ
መቅደስ አጥኖ ማኅሌት ቆሞ
በልብስ ተክህኖ አጊጦ፣ በብር አክሊል ተሸልሞ
እመ ብርሃን ያንች ጽላት፣ ነፍስ ላይ በእሳት ታትሞ
የመናኒው ያባ ተድላ፣ ረድ ሆኜ፣ አብሮኝ ታድሞ
ሕይወቴ እምነትሽን ጸንሶ
ሥጋ ፈቃዴ ተድሶ
ለሕንፃሽ መዲና ቆሞ፣ ለክብርሽ ድባብ ምሰሶ
ሥሜን በሥምሽ ሰይሜ፣ ሆነሺኝ የእምነቴ ፋኖስ
ለዋዜማሽ ግሸን ማርያም፣ ለክብርሽ ደብረ ሊባኖስ
ስሮጥ፣ በወንበሩ አኖርሺኝ፣ በአንበሳው በቅዱስ ማርቆስ
ታዲያ ዛሬ ኢትዮጵያ ስትወድቅ፣ ከምትሰጪኝ የፍርሃት ጦስ
ምነው በረኝነት እድሜ፣ ዓይኔን በጓጎጣት የሎስ
የጋኔል ጥንብ አንሳ ከንፎ፣ ወርዶ በጨለማ በርኖስ

•••
ባክሽ እመ ብርሃን ይብቃሽ፣ ባክሽ ምስለ ፍቁር ወልዳ
ጽናት ስጪኝ እንድካፈል፣ የእናቴን የኢትዮጵያን ፍዳ፣
ከነከሳት መርዝ እንድቀምስ፣ ከነደደችበት እቶን
የሷን ሞት እኔ እንድሞታት፣ ገላዋ ገላዬ እንዲሆን፡፡

*አባታችን አቡነ ጴጥሮስ ዛሬ 83ኛ የሰማዕትነት ቀናቸው ነው ።

Image may contain: 1 person, cloud, sky and outdoor

03/04/2019

ከ Tewodros Belete Meistu
‹ # የዳግም_መምጣቱ_ነገር › (ነገረ ምጽአት)
ተዝካሮ ግበሩ ባሕታውያን ደቂቁ፤
ለምውት ጾም እስመ ደብረ ዘይት መንፈቁ። ( ከቀደሙት የተገኘ ጉባኤ ቃና)
አሕማላት (የለመለሙ ዕፀዋት) ካሉባቸው ሥፍራዎች ጌታችን ከ"ዐጸደ
ሐምል" ተራራ ዐጸደ ዘይትም ወደበዛበት ሥፍራ አስጠግቶ ነገረ ምጽአቱን
ያስተማረበት መታሰቢያ ለኹዳዴ እኩለ ፆም ነው!
እኛንም ከመፍቀሬ ሁከት ሰይጣን ጠብቆ በመፍቀርያነ ምሕረት መላእክቱ ይባቤ
የመንግሥቱ ዜጎች የርስቱ ተካፋይ ያድርገን።
ተከታዩን በቋዒ (እጅግ ጠቃሚና አድራሻ ጠቋሚ) ጽሑፍ እነሆ ፦
‹ # ዳግም_ምጽአት › ╭⊕∽∝⇨ (በቀሲስ ኅብረት የሺጥላ ⇄ Hibret Yesh*tila )
ዳግም ምጽአት ‹‹ደገመ›› እና ‹‹መጽአ›› ከሚሉ ሁለት የግዕዝ ግሦች
የተዋቀረ ሐረግ ነው፡፡ የጌታችንንና የአምላካችንን ለሁለተኛ ጊዜ ወደዚህች
ዓለም መምጣት ያመለክታል፡፡ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ዳግምነቱ ለልደቱ
ነው፡፡ ማለትም ልደቱን ‹‹ቀዳማዊ ምጽአት›› ካልን ዘንድ ለፍርድ መምጣቱን
‹‹ዳግም ምጽአት›› እንላለን፡፡
‹‹ዳግም›› የሚለውን ቃል አንድ ነገር ያለ ምንም ለውጥ ወይም ልዩነት
ሲደገም የምንጠቀምበት ከሆነ ‹‹የተካከለ ዳግም›› እንለዋለን፡፡ ያ ነገር
መሠረታዊ ጭብጡን ሳይለቅ ነገር ግን በበርካታ ለውጦች ታጅቦ ከተደገመ
ወይም ከቀደመው ጋር ሲነጻጸር ተደገመ የሚያሰኝ ምሥጢራዊ አካሄድ ካለው
‹‹ያልተካከለ ዳግም›› ይባላል፡፡ ፍጹም የሆነ መመሳሰል የሌለው መደገም
እንደማለት ነው፡፡ ዳግም ምጽአት፣ ዳግም ልደት፣ ዳግም ትንሣኤ ወዘተ
‹‹ያልተካከለ ዳግም›› ላልነው እንደ ምሳሌ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ቀደም ሲል ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚች ዓለም ሰው በመሆን መጥቷል፡፡ ለሁለተኛ
ጊዜ ደግሞ ለፍርድ እንደሚመጣ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የቀድሞ አመጣጡንና
ወደፊት ለፍርድ መመጣቱን ስናስተያያቸው በዓላማቸውም ሆነ በይዘታቸው
በጣም ከፍተኛ ልዩነት አላቸው፡፡ የሚመሳሰሉት ወደዚህ ዓለም መምጣት
በሚለው ጽንሰ ሐሳብ ብቻ ነው፡፡ ሰው ለመሆንም ሆነ ለፍርድ ቢመጣ ሁለቱም
ጊዜ መምጣት ነውና፡፡
‹‹ምጽአት›› መጣ የሚል ፍቺ ካለውና ‹‹መጽአ›› ከሚለው ግሥ የተገኘ ሲሆን
ትርጉሙ ‹‹መምጣት፤ አመጣጥ›› የሚል ነው፡፡ ‹‹መምጣት›› የሚለውን ቃል
እንኳን ለእግዚአብሔር ይቅርና ለሰው ስንጠቀምበትም የተለያየ አገባብና
ትርጉም የሚሰጥ ነው፡፡ ለምሳሌ ‹‹እገሌ ሄደ ወይም መጣ›› ብንል
የተጠቀሰው ሰው በአካል መሄድና መምጣቱን ያሳያል፡፡ ይህ አንዱ ዓይነት
አገባብ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ሰው በሐሳብ፣ በፈቃድ፣ በልብና በመንፈስ ሄደ፤
መጣ ሊባል ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ የቃሉ አገባብ በአካል ወዲህና ወዲያ ማለትን
አያመለክትም፡፡
ስለ እግዚአብሔር ወልድ ስለኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህች ዓለም መምጣት
ስንናገር ከላይ ስለተጠቀሰው ዓይነት የቃሉ ፍቺና አገባብ በትኩረት ማሰብና
ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ክብር ይግባውና ፈጣሪን
ሳናውቅ ልንሰድበው እንችላለን፡፡ እንዴት ቢባል ፈጣሪን እንደፍጡር ወዲህና
ወዲያ ይላል ማለት መስደብ ነውና፡፡ ታዲያ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውነት
መጥቷል፤ ዳግመኛም ለፍርድ ይመጣል ሲባል እንዴት ነው?
ከሁሉ አስቀድሞ እግዚአብሔር በሁሉም ቦታ መልቶ የሚገኝ ምሉዕ በኩለሄ
መሆኑን ማወቅና ማመን ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በቦታ ተወስነው እንደሚሩ
እንደፍጡራን ሄደ፤ መጣ እየተባለ ለባሕርይው አይነገርም፡፡ ስለእግዚአብሔር
መምጣት ስንናገር ሦስት ዓይነት መንገዶችን ለይተን ማወቅ አለብን፡፡ እነርሱም
በግብር መምጣት፣ በዘፈቀደ መገለጥ (መምጣት)፣ በኩነት መምጣት የሚሉት
ናቸው፡፡
1ኛ. በግብር መምጣት፡-ማለት በሥራ መምጣት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር
ሥራ ሲሠራ መጣ ይባላል፡፡ በቦታ መልቶ የሚገኝ ነፋስ ሲነፍስና ሣር ቅጠሉን
ሲያነዋውጽ ‹‹ነፋስ መጣ›› እንደሚባል ሁሉ እግዚአብሔርም አምላካዊ
ሥራውን በመሥራት ሲገለጥ ‹‹መጣ›› ይባላል፡፡ በግብር መምጣት በሌላ
መንገድ የ‹‹ረድኤት አመጣጥ›› ይባላል፡፡
‹‹መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል›› የሚለው ዐረፍተ ነገር እግዚአብሔር
ሥራ ሲሠራ መጣ እንደሚባል ማስረጃ ነው፡፡ ቀድሞም ቢሆን መንፈስ ቅዱስ
ድንግል ማርያምን ርቋት አያውቅም፡፡ ነገር ግን በታላቅ ሥራ በእርሷ ሲገለጥ
‹‹መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል›› ተብሎ እንደ አዲስ ተነገረ፡፡ ይህን
የመሰለ በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ፡- ‹‹በኤልሳቤጥም
መንፈስ ቅዱስ ሞላባት››… ወዘተ፡፡ (ሉቃ1.35፤ 1.42)
እግዚአብሔር እንደ ሦስትነቱ በአብርሃም ቤት ተገኝቶ ለአብርሃም ‹‹የዛሬ ዓመት
እንደዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ልጅን
ታገኛለች›› ብሎታል፡፡ ነገር ግን በተስፋው መሠረት ፈጣሪ ተመልሶ ወደ
አብርሃም ሲመጣ አናነብም፡፡ ከዚህ ይልቅ የምናነበው ‹‹እግዚአብሔርም
እንደተናገረው ሣራን አሰበ፤ እግዚአብሔርም እንደተናገረው ለሣራ አደረገላት፡፡
ሣራም ጸነሰች፡፡›› የሚል ነው፡፡ (ዘፍ18.10፤ 21.1) ምእመናን! እግዚአብሔር
ለሣራ የሚያደርግላትን ለመግለጽ ‹‹ወደ ቤትህ እመለሳለሁ›› ማለቱን
አያችሁን? ለሣራ ማድረጉ ወደ አብርሃም ቤት ተመልሶ እንደ መምጣት
ይቆጠራልና፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የእግዚአብሔር መምጣት የ‹‹ግብር ምጽአት››
ወይም የእግዚአብሔር በሥራ መምጣት ይባላል፡፡
2ኛ. በዘፈቀደ መምጣት፡- እግዚአብሔር በወደደው ጊዜ በወደደው ኅብርና
አምሳል ለሰዎች ራሱን ይገለጣል፡፡ ይህን ሲያደርግ ‹‹መጣ›› ይባላል፡፡
አመጣጡም የ‹‹በዘፈቀደ አመጣጥ›› ይባላል፡፡ እንደ ወደደው መገለጥና
መምጣት ማለት ነው፡፡
የሰው ልጅ ሊያየው ሊሰማውና በአጠቃላይ ሊረደው በሚችለው መጠንና
አምሳል ፈጣሪ ራሱን ይገልጣል፡፡ ይህም በሥጋዊና በደማዊ ወይም በሌላ
ፍጡር አምሳል ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ፡- መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል
ተገልጧል፡፡ እግዚአብሔር በእሳት፣ በብሩኅ ደመና፣ በጨለማ፣ በጭጋግ፣
በጢስና በብርሃን አምሳል ሊገለጥ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር መጣ
ይባላል፡፡ (ማቴ3.16፤ ዘጸ19.9) ይሁን እንጂ በእነዚህ ነገሮች አምሳል
ስለመጣ የተጠቀሱት ነገሮች እግዚአብሔር ናቸው ወይም እርሱ እነርሱን ሆኗል
ማለት አይደለም፡፡ ለጊዜው በእነርሱ አምሳል ተገለጠ እንጂ፡፡
3ኛ. የኩነት አመጣጥ፡- ሐዋርያው ‹‹ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ›› እንዳለው
በመምሰል ብቻ ሳይሆን በመሆን መምጣት አለ፡፡ የኩነት አመጣጥ በመሆን
መምጣት ማለት ሲሆን ከዘፈቀደ አመጣጥ የሚለየውም በዚህ ነው፡፡
እግዚአበሔር ለጊዜው በሰው አምሳል ተገለጠ ማለትና ሰው ሆነ ማለት በጣም
የተራራቁ ነገሮች ናቸው፡፡ ቀድሞ በሰው አምሳል ለአበው በዘፈቀደ ይገለጥ
የነበረ እግዚአብሔር በማዕከለ ዘመን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆነ፡፡
ማለትም በኩነተ ሥጋ ወደዚህች ዓለም መጣ፡፡ ስለዚህ ለኩነት አመጣጥ
የሚቀርበው ዋና ምሳሌ የክርስቶስ ልደት ነው፡፡ ልደቱ ምጽአት ሲሆን ነገር ግን
የኩነት ምጽአት ነው፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ከላይ ከተጠቀሱት ሦስት ዓይነት ምጽአቶች
የሚለይበት ነገር አለ፡፡ ከግብር ወይም ከረድኤት አመጣጥ የሚለየው በረቂቅ
ሳይሆን በግልጥ በመምጣቱ ነው፡፡ ከድንግል ማርያም በነሣው ሥጋ፣ በክበበ
ትሥብዕት፣ በግርማ መለኮት ተገልጦ ዓለም ሁሉ ስለሚመለከተው በዘፈቀደ
ከመገለጥም ይለያል፡፡ ክርስቶስ ሰው የሆነ አምላክ በመሆኑ ዳግም ምጽአት
ለኩነት ከመጣበት አመጣጥ ማለትም ከልደቱም የተለየ አመጣጥ ነው፡፡
የሚመጣው ለፍርድ እንጂ ሰው ለመሆን አይደለምና፡፡
ቃል ሥጋ የሆነው በተዐቅቦ ነው፡፡ ይህም ሥጋ ሥጋነቱን እንደጠበቀ ግዙፍ
የነበረው ወደ ረቂቅነት ሳይለወጥ፤ ውሱን የነበረው ወደ ምሉዕነት ሳይለወጥ
ማለት ነው፡፡ እንደዚሁም ቃልም ረቂቅነቱንና ምሉዕነቱን ሳይተው ሥጋና ቃል
ተዋሐዱ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ክርስቶስ ስንል ሥግው ቃል ማለታችን ነው፡፡
ክርስቶስ ይመጣል ስንልም ሥጋን የተዋሐደው ቃል ለፍርድ ይመጣል እያልን
ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ እግዚአብሔር ቃል ግዙፍና ውሱን ሥጋን ባለበት ሁኔታ
ሳይለውጠው ተዋሕዷል ብለን እስካመንን ድረስ ‹‹መጣ፣ ሄደ(ዐረገ)፣
ይመጣል›› ማለት በተዋሕዶተ ቃል ለሚያምኑ ሁሉ የሚስማማ ንግግር ነው፡፡
ለፍርድ የሚመጣው ከሦስቱ አካል አንዱ ወልድ ነው፡፡ የሚመጣውም ለፍርድ
ስለሆነ እጅግ በጣም በሚስፈራ ግርማ ነው፡፡ እንደ ሐኪም መምጣትና እንደ ዳኛ
መምጣት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ አምላካችን ክርስቶስ አስቀድሞ የመጣው
እንደ ሐኪም ነበር፡፡ ስለሆነም ሰዎች ብዙ የማይገባ ነገር ሲናገሩበትና
ሲያደርጉበት ባለመድኃኒት (ሐኪም) የበሽተኛውን ቁጣና ስድብ እንደሚታገሥ
እስከ መስቀል ሞት ድረስ ታግሦ አሳልፏል፡፡ ለፍርድ ሲመጣ ግን እንደዚያ ዓይነት
ትሕትናና ትዕግሥት መጠበቅ የለብንም፡፡ የዳኛ ሥራ እንደ ሕጉ መዳኘት ነው
እንጂ ማባበል፣ መምከርና ማስተማር አይደለምና፡፡ ስለዚህ ሀብታሙ፣ ደሀው፣
ወንዱ፣ ሴቷ፣ ሕፃኑ ሽማግሌው፣ ጳጳሱ ምእመኑ ሁሉ በፊቱ ይቆማል፡፡ የሁሉም
ሥራ ይገለጣል፡፡ ሁሉም ስለ ክፉ ሥራው በፊቱ ዋይ ይላል! የማይጠቅም
ዋይታ ነው፡፡
የፍርድ ቤት ቀጠሮ ያለበት ሰው ምን ማድረግ እንዳለበት አስቅድሞ ያስባል
እንጂ ችላ ብሎ አይቀመጥም፡፡ እኛም እንዲሁ እንድናስብበትና ተዘጋጅተን
እንድንጠብቀው ዕለተ ፍትሕ፣ ዕለተ ኩነኔ (ዳግም ምጽአት) እንዳለ አምላካችን
አስቀድሞ ነግሮናል፡፡ ቅዱስ ወንጌል ‹‹እንዳትሰናከሉ ይህን አስቀድሜ
ነገርኳችሁ››፤ ‹‹ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ፡፡›› ይለናል፡፡ ቀኑ መቅረቡን የምናውቅበት
ምልክቶችንም ዘርዝሮልናል፡፡ አብዛኞቹ ምልክቶች ተፈጽመዋል፡፡ ሌሎቹም
እየተፈጸሙ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹም ጥቂቶች ምልክቶች ከደጅ መድረሳቸው
የኮቴአቸው ድምጽ ይጠቁማል፡፡ (ማቴ24.1-51) የምጽአት ዋዜማ
ምልክቶችን ዝርዝርና ምሥጢር በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን፡፡
የክርስቶስ መምጣት ለሙታን ትንሣኤ እንደ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ሙታን የሚነሡት
እርሱ ሲመጣ ነውና፡፡ ስለዚህ ዳግም ምጽአት ከአምስቱ ምሥጢራተ ቤተ
ክርስቲያን ውስጥ ዋነኛ በሆነው በምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ትምህርት ውስጥ
ሰፊ ቦታ ተሰጥቶት ይብራራል፡፡ ይቆየን!
☞ (๓αrςh 22, 2011 ካጋሩት የተወሰደ☞ [email protected])

27/09/2018

በቅድሚያ እንኳን ለብርሐነ መስቀሉ አደረሣችሁ!!!
“ # ወይንሳዕ_መስቀለ_ሞቱ_ወይትልወኒ – # የሞቱን_መስቀል_ተሸክሞ_
ይከተለኝ ” (ማቴ ፲፮፥፳፬)
↣∽┄┉┉✽» ✧†✧ «✽┉┉┄∽↢
ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና በቃል መነገሩ፣ በኅሊና መዘከሩ፣ በሰው ልብ
መታሰቡ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት መዘገቡ ከፍ ይበልና፣ ጌታችንንና አምላካችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ ልጆቹ ፈቃዱን እያደረግን እንድንኖርና
እርሱም ከመልካም ምግባራችንና ከበጎ ትሩፋታችን ብቻ የተነሳ ፍጹማን
እንደማንሆን ያውቃልና፣ ከማያልቅ ልግስናው ከማይጓደል ምሕረቱ ዘመናትን
እየመጸወተን ደስ የሚሰኝበትን ለእኛ እያደረገ በቸርነቱ ያኖረናል::
ከእርሱና ከዓላማው ጋር ጸንተን እንድንኖርም እንዲህ ሲል በቅዱስ ወንጌል
አዝዞናል:: “ዘይፈቅድ ይትልወኒ ይጽላዕ ነፍሶ ያጥብዕ ወይንሳዕ መስቀለ ሞቱ
ወይትልወኒ (እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ
ይከተለኝ) ወምንተ ይበቁዖ ለሰብእ ለእመ ኩሎ ዓለመ ረብሐ ወነፍሶ ኃጉለ
(ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን
ይጠቅመዋል?)” (ማቴ. 16:24-26)።
ጥንቱንም ቢሆን እኛ የተፈጠርነው በሕይወት እንድንኖር ነው። ትንሳኤና ሕይወት
ክርስቶስ ግን የተወለደው ስለኛ እንዲሞት ነው:: በዚህም ሁላችን ለእርሱ
እንድንኖር እርሱ ስለ ሁላችን ሞተ “በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና
ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ። “(1ቆሮ፣
5:15)። ይህ ግን መስቀል የገደለው ያይደለ ይልቁንም በመስቀሉ ሞትን
ገደለበት እንጂ:: “በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም
ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።” (ፊል. 2:8) እንዲል::
ሊከተለኝ የሚወድ ነፍሱን ይጥላ አለ፣ ይህም ነፍሱንና ሥጋውን የሚለይ መከራ
ለመቀበል ይጨክን ሲል ነው። ሰውስ ለክርስትና ፍኖቱ ለነፍሱ ሥምረት እያደረ
የሥጋውን ፈቃድ እየገፋና እየጠላ ሊኖር ይገባዋል። ለዚህም ጌታችን ተከታዩን
ሃሳብ እንዲህ ሲል አስፍሮታል “ወምንተ ይበቁዖ ለሰብእ ለእመ ኩሎ ዓለመ
ረብሐ ወነፍሶ ኃጉለ …ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን
ይጠቅመዋል?” መከተሉም ቢሆን ሌጣውን ያይደለ የሞቱን መስቀል ተሸክሞ
ይለናል::
መስቀል ምንድር ነው ?
┈┈◦◎✧◎◦ ┈┈
መስቀል በቀደመው ዘመን ለኃጢአተኞች እግዚአብሔርን ለበደሉ መቅጫ የነበረ
“በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ
ነውና” (ዘዳ፣21:23)። ነገር ግን በአዲስ ኪዳን ለክርስቲያኖች ኃይል፣ ጽንዕ፣
ቤዛና መድኃኒተ ነፍስ ሆኖ የሚያገለግል አርማ ነው::
ወደዚህ ክብር እንዴት ሊሻገር እንደቻለ ሊያስረዱ የሚችሉ በመስቀሉ ከተፈጸሙ
ድንቅ መንክራት እፁብ ተዓምራት መካከል ተከታዮቹን ሦስት ዓበይት ነጥቦች
እንደእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ እንመለከታለን::
+ ጠላት የራቀበት ነው።
┈┈◦◎✧◎◦ ┈┈
መስቀል የቀደመው እባብ የዲያቢሎስ ራስ የተቀጠቀጠበት እኛም ድል
መንሳትን በግልጥ ያየንበት እጸ መድኃኒት ነው:: “በእኛ ላይ የነበረውን
የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም
በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል።አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል
በመንሣት በእርሱ (በመስቀል) እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው።” (ቆላ፣
2:14) እንዲል።
+ እኛ የቀረብንበት ነው።
┈┈◦◎✧◎◦ ┈┈
ተመልከቱ ራሱን ወደኛ ያቀረበበት ነው አላልንም “አመ ተለአልኩ እምድር
እስህብ ኩሎ ኃቤየ፤ እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ
እስባለሁ።” (ዮሐ፣12:32) እንዳለ እኛን ወደራሱ አቀረበበት፣ ምክንያቱም ሰው
በድሎ ራቀው እንጂ እርሱ ከሰው የተለየበት ጊዜ አልነበረምና። “እኔ የቅርብ
አምላክ ነኝ እንጂ የሩቅ አምላክ አይደለሁም።” (ኤር፣23:23) እንዳለን።
ይበልጡንም ለተዛምዶ ረቂቅ ቅርበቱ ያይደለ ሥጋችንን ነስቶ አማኑኤል
ተሰኝቷል። “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ።” ይህም በኩነት ታዲያ ዓላማው
ወደእኛ መቅረብ ብቻ ቢሆን ይህ ልደቱ በበቃው ነበር። መስቀሉ ግን ወደኛ
መምጣቱን ባንቀበል ወደራሱ ሊወስደን ወደ ሰማይ ቤታችን ሊስበን በቀራንዮ
ተተከለ። ለዚህም ሊቁ ማር ኤፍሬም “አቅረበነ ኃቤሁ ዘዚአነ ሞተ ነሳ ወእንቲአሁ
ሕይወተ ወኃበነ- ወደራሱ አቀረበን የእኛን ሞት ወስዶ የእርሱን ሕይወት ለእኛ
ሰጠን” ሲል መነሻችንን ያስረዋል።
+ የጥል ግድግዳ የፈረሰበት
┈┈◦◎✧◎◦ ┈┈
ሰው የሞትን እጽ ቆርጦ ቢበላ አምላኩን በደለ። በዚህም የጸብ ግድግዳ
ተተከለ። ሰው ከአምላኩ ተለየ ልዑለ ቃል ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “ነገር
ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፥ እንዳይሰማም
ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል።” (ኢሳ፣59:2) ሲል እንደገለጸው፣ ታዲያ
ከህገ ልቡና ወደ ህገ ኦሪት መሻገሩ ፍጻሜ ያለው ድኅነት ሊያመጣ ባለመቻሉ
የሚበልጥና የሚሻል አዲስ ኪዳን የሚሰጥበት አዲስ መስዋዕት የሚሰዋበት
አዲስ ድንኳን አስፈለገ (ዕብ፣ 9:11)።
ለዚህም የሀዲስ ኪዳን ሥርዓት ክቡር ደሙ የፈሰሰበት የሕይወት ህብስት ቅዱስ
ሥጋው የተቆረሰበት ዐረፍተ ማእከል የተናደበት እጸ መድኃኒት ቅዱስ መስቀሉ
ተሰጠን። “እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም
የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤
ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ
ዘንድ፥ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል
ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።” (ኤፌ፣ 2:15)።
እንግዲህ በጠቅላላው መስቀል የምንለው፣ በቁሙ ከቤተክርስቲያን ጉልላት
እስከ ምዕመናን ንቅሳት የሚታይ የድል ምልክት፣ በሰሌዳ ተስሎ በጣት
ተመሳቅሎ የሚገኝ የድኅነት አርማ፣ ካህናት በእጃቸው ይዘው የሚፈቱበት፣
ክርስቲያኖች በአንገታቸው አስረው ማንነታቸውን የሚመሰክሩበት መገለጫ
ሲሆን. በሌላ አገባብ መከራ የተጋድሎ ፍኖት ማለት ነው።
እግዚአብሔር ወልድ ክርስቶስ ስለሁላችን መዳን መከራን ተቀብሎልናል።
እናስተውል፣ እያንዳንዳችን በመዳን ኑሮ ሐሳባችን፣ እቅድ ምኞታችን በመከራው
ልንካፈለው፣ በሞቱ ልንመስለው ፈለጋውን ልንከተለው ይገባናል።
“ስለዚህ ኢየሱስ ደግሞ በገዛ ደሙ ሕዝቡን እንዲቀድስ ከበር ውጭ መከራን
ተቀበለ። “(ዕብ፣13:12) እንደተባለ፤ ከበር ውጪ አለ በቀራንዮ ኮረብታ የራስ
ቅል በተባለ ጎልጎታ ሊቀድሰን ተሰቀለ። እኛ ክርስቶስ በደረሰበት መከራ
ከድቅድቁ ጨለማ ድንቁርና ወደሚደነቀው ብርሃን እውቀት የተሻገርነው፣ ስለ
አዳም በደል መከሰስን ጥለን ስለራሳችን ጽድቅ መከራን በመቀበል
እንድንከተለው ነው::
ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ
ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና።
“(1ኛ፣ጴጥ.2:21) ሲል እንዳስረዳን። በዚህም ኅሩይ ነዋይ ቅዱስ ጳውሎስ
“እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ
ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ።
“(ፊል.3:10-11)። ሲል ምኞቱን አስረዳን ምን ይጠቅማል? የሚል ቢኖር ልሳነ
ዕፍረት እንዲህ ያስረዳዋል “ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን
ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን።” (ሮሜ.
6:5)።
# ሁሉ_የራሱ_መስቀል_አለው ሸክሙን የሚሸከምበት
“ለሁሉም እንዲህ አላቸው፦ በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ
መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ።” (ሉቃ፣9:23) ሁሉ የራሱን ሸክም
ይሸከማልና
“ወኩሉ ያመክር ምግባሮ (ሁሉ ሥራውን ይመርምር ለሌላው ሳይሆን ለራሱ
የሚመካበትን) እስመ ኩሉ ፆሮ ይፀውር (እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም
ነውና)” (ገላ6:5) እንዲል።ስለዚህ # የምንሸከመው_መስቀላችን_
የምንሰቀልበት_ሳይሆን_ሸክማችንን_የምንሰቅልበት_ነው ::”የክርስቶስ
ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ።” (ገላ፣ 5:24)
እንደተባለ።
እስኪ አእምሮአችንን ከመባከን ሰብስበን ነፍሳችንን የሚያሳርፍ አንድ ታሪክ
እናንብብ
“እርሱም በመንገድ ሲወጣ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ ተንበረከከለትና። ቸር
መምህር ሆይ፥ የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? ብሎ
ጠየቀው።ኢየሱስም፦ ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር
ቸር ማንም የለም። ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥
በሐሰት አትመስክር፥ አታታልል፥ አባትህንና እናትህን አክብር አለው።እርሱም
መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ
አለው።ኢየሱስም ወደ እርሱ ተመልክቶ ወደደውና። አንድ ነገር ጐደለህ፤ ሂድ፥
ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፥ መስቀሉንም
ተሸክመህ ና፥ ተከተለኝ አለው።ነገር ግን ስለዚህ ነገር ፊቱ ጠቈረ፥ ብዙ ንብረት
ነበረውና እያዘነም ሄደ።” (ማር 10:17)።
አይገርማችሁም በምድራችን ላይ ገንዘብን መውደድ የከበደ ሸክም እየሆነባቸው
“ገፋኤ-ነዳይ መፍቀሬ- ነዋይ” መጠርያቸው የሆኑ ብዙዎች አሉ:: ፍቅረ ነዋይ
(ገንዘብን መውደድ) ለኃጢዓት ሥርና ራስ ነው …… ጌታችን ተርቦ ሳይሳሳ፣
ተፈትኖ ድል ሳይሆን፣ ለሁላችን አርአያ በሆነበት ገዳመ ቆሮንቶስ ጠላታችንን ድል
ከነሳባቸው መንገዶች አንዱ ፍቅረ ነዋይን በጸሊዓ ነዋይ ነበር። ይህም ፍቅረ
ነዋይ ርዕሰ-ኃጣውእ ከስስትና ከትዕቢት ጋር አርዕስተ ኃጥውእ እየተባለ
ይጠራል። ይሁንና ግን ከአስራ ሁለቱ አንዱ በሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ ልብ ገብቶ
ተሳካለት። በዚህ ሥፍራ ደግም የኃጢዓት ሥር ተብሎ ተጠራ “ገንዘብን
መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት
ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።” (1ኛ.ጢሞ.6:10) እንዲል።
እንግዲህ ይህን የመሰለው ኃጢዓት ሁሉ ክቡድ ሸክም ይባላል። የምሕረት
አምላክ ግን በፍቅር ልሳን እንዲህ እያለ ይጠራናል “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ
የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ
ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት
ታገኛላችሁ፤ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።” (ማቴ.11:28-30)።
ቀሊል የሆነውን የእርሱን ሸክም እንሸከም ዘንድ እሱ የኛን ክቡድ ሸክም
በመስቀል ላይ ተሸከመ:: እንግዲህ ተመልከቱ በዚህ መንገድ እኛም
ሕይወታችንን እንድንሰጠው ሕይወቱን ሰጠን ለምን? የሚል ቢኖር እርሱ
የብዙዎችን ኃጢዓት በእንጨት ላይ የተሸከመው ብዙዎች የእርሱን ሕይወት
በዘመናቸው እንዲሸከሙ ነውና:: ነቢዩ አስቀድሞ በትንቢት እንዲህ እንዳለ
“ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥
ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።” (ኢሳ 53:12) ሊቀሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስም
የቃሉን መፈስጸም እንዲህ ሲል እንዳስረዳ “ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥
እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ
ተሸከመ፤” (1ኛ.ጴጥ፣2:24)።
# መከራን_መቀበል ( # መስቀላችንን_መሸከም )፦
+ ኃጢዓትን (አርእስተ ኃጣውእ) ያስተዋል።
┈┈◦◎✧◎◦ ┈┈
“በሥጋ መከራን የተቀበለ ኃጢአትን ትቶአልና።” (1ጴጥ፣ 4:2)።
+ ወደ እግዚአብሔር ያስገባል። ┈┈◦◎✧◎◦ ┈┈
“ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል” (ሐዋ
14:22) እንደተባለ ለብዙዎች ዘለፋ የሆነው ይህ የቅዱሳን ሐዋርያት
ምስክርነት “በጸጋ ድነናል” እያሉ ባልተገባ ፍካሬ ቃሉን እየጠቃቀሱ፤ ለመብልና
መጠጥ ይህን ለመሰለው የሥጋ ፈቃድ ራሳቸውን ለሚያስገዙ ጅራፍ
ይሆንባቸዋል፤ ምክንያቱም “የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ
ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ
አይደለችምና።” (ሮሜ.14:17) ይለናልና:: # ማጠቃለያ
┈┈◦◎✧◎◦ ┈┈
ቅዱስ አባታችን ብጹዕ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ በአንድ መጽሐፋቸው “ፈተና ያለው
ትምህርት ቤት አይደለም፣ ይልቁንም ትምህርት ቤት ያለው በፈተና ውስጥ ነው”
ብለዋል። እኛም እንዲህ እንላለን “ሕይወት በመከራ የተሞላ ነው ለሚል፣ የለም
ለክርስቲያንስ መከራ በህይወት የተመላ ነው እንጂ”፤ ሊቁ “መከራ ኢርኅቀ
እምርዕሰ ጻድቃን ወርዕሰ ጻድቃን ኢርኅቀ እምነ መከራ ግሩም.” ሲል ቅኔውን
ይጀምራል። የማይጠፋ ስምና የሕይወትን አክሊል ገንዘብ ሊያደርጉ ሲሹ መከራ
አይርቃቸውም። ቢርቃቸውም እንኳ እነርሱ ከመከራ መች ይርቁና።
መክበርያቸውን ሽተው ራሳቸው ላይ ተጋድሎ ያጸናሉ ሌላውም ሊቅ የጸናውን
ሰማዕት ተመለከተና “ኦ ጊዮርጊስ ስቃየ ኮንከ ለሥቃይከ” ሲል አደነቀ እንዴት
ባለ መከራ እንዲገድሉት ይጨንቃቸው የነበሩ አላውያን ቢፈጩት፣ ቢያቃጥሉት፣
አመድ አድርገው ቢበትኑት “እነሆኝ የክርስቶስ ባርያ” እያለ ሞትን ድል ቢነሳና
ከመካከላቸው ቢገኝ ለስቃዩ ስቃይ ሆነበት ወይግሩም! ታዲያ የቀደሙ
ምስክሮች ሕይወት ይህ ከነበረ የእኛ ተጋድሎ ወዴት ይሆን? “ጻድቅም በጭንቅ
የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ
አለው?” (1ኛ.ጴጥ.4:18)።
እንግዲህ በሁሉ እናመስግን በፈተናችን ዋጋ በመከራችን ጸጋ እንድንቀበል
እያሰብን ይህን እንጸልይ “ኦ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ አአኩተከ በእንተ ኩሉ
ግብር ዘአምጻእከ ላዕሌየ እመሂ ረኃበ አው ጽጋበ እመሂ ጥኢና አው ደዌ እመሂ
ፍሰሐ አው ኃዘነ…ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በእኔ ላይ ስላመጣህብኝ ነገር
ሁሉ አመሰግናለሁ ረሃብ ቢሆን፣ ጥጋብ ጤንነት ቢሆን፣ ደዌ ደስታም ቢሆን
ኃዘን”( ሰይፈ ሥላሴ ዘሐሙስ)።
መስቀሉን የሚሸከም ምረረ ገኃነምን ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን እየተዘከረ
በመከራው ይደሰታል እንጂ አይማረርም። የጌታችን ወንድም የተሰኘ ራሱን
የክርስቶስ ባርያ እያለ የጠራ ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ የመጀመርያ ምዕራፍ
ቁጥር 2 እና 3 ላይ “ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን
እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ
ቍጠሩት” ይለናል እኛም ከሐዋርያው ጋር እንዲህ እንላለን “ለእኛም ይገለጥ
ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ
አስባለሁ።” (ሮሜ፣ 8:18)።
✧†✧ ከፍኖተ መስቀሉ ከህያው ቅዱስ ቃሉ በረከት ይክፈለን። ✧†✧
( ከቴዎድሮስ በለጠ የተወሰደ )

11/09/2018

ማኅበረ ቅዱሳን ከJTV ጋር በመተባበር የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ልዩ የበዓል መርሐ ግብር አዘጋጅቷል
ማኅበረ ቅዱሳን ከJTV ጋር በመተባበር የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ልዩ የበዓል መርሐ ግብር አዘጋጅቷል
መርሐ ግብሩ ዻጉሜ ፭ ቀን ፳፻ወ፲ ዓ.ም ከምሽቱ 2:00-3:00 እና መስከረም ፩ ቀን2011 ዓ.ም ከጠዋቱ 3:00-4:00 ሰዓት
ይተላለፋል፡፡

11/09/2018

ከአሜሪካ ማእከል
በማኅበረ ቅዱሳን በአሜሪካ የዲሲ ንዑስ ማእከል አቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤት ነሐሴ ፲፪ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም ለሰባት ወራት ያስተማራቸውን 64 ተማሪዎችን የተማሪ ወላጆችና የማኅበሩ አመራር አባላት
በተገኙበት በሜሪላንድ ግዛት አስመረቀ፡፡
በምረቃው መርሐ ግብር ላይ የትምህርት ቤቱ አስተባባሪ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃይለ ማርያም የማኅበሩን መልእክትና የአቡነ ጎርጎርዮስ
ትምህርት ቤትን የ፳፻፲ ዓ.ም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
ዲ/ን ሙሉጌታ ኃይለ ማርያም “ከማኅበረ ቅዱሳን ዓላማዎች ልጆች
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት፣ ሥርዓትና
ትውፊት በመማር፣ ለአባቶቹ ተተኪ እንደሆን ማድረግ በመሆኑ ላለፉት ዓመታት ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በገቡ ወጣቶች ላይ ልዩ
ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ ቆይቷል፤አሁንም እየሠራ ይገኛል” ብለዋል፡፡
አያይዘውም “ሥራው ብዙ ውጤት ያስገኘ ቢሆንም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ከሚገኘው ወጣት የተተኪ ትውልድ ቊጥር አንጻር ሲታይ እጅግ በጣም አነስተኛ በመሆኑ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና
ሰንበት ትምህርት ቤቶች ከሕፃናት በመጀመር ሲያስተምር ቆይቷል፡፡
ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ ማስተማር አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ
ከ፲፱፻፺፩ ዓ.ም ጀምሮ ሕፃናትና ወጣቶችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ
ይገኛል፡፡ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትም ትምህርት ቤት በመክፈት
በማኅበሩ የሥርዓተ ትምህርትና የሙያ እገዛ እየተደረገላቸው
በማስተማር ላይ ይገኛሉ” በማለት የማኅበሩን አገልግሎት
ገልጠዋል፡፡
“በዲሲ ንዑስ ማእከልም ከ፳፻፲ ዓ.ም በመጀመር አሁን ያለንበት ደረጃ
ደርሰናል፡፡ 64 ተማሪዎችን ተቀብለን በሳምንት አንድ ቀን ቅዳሜ
ለሰባት ወራት በማስተማር ቆይተናል” ብለዋል፡፡ በቋንቋ ክፍል
ስድስት በቃል ትምህርት አንድ፣ ሦስት ረዳት፣ እንዲሁም በመጽሐፍ
ቅዱስ ጥናት አንድና አንድ ተጨማሪ በአጠቃላይ 11 መምህራን
ተሳታፊ እንደነበሩ ገልጠዋል፡፡
በምረቃው የተማሪ ወላጆች ማእከሉ ተማሪ የመቀበል አቅሙን
ማሳደግ እንዳለበትና ያለውን ልምድ ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት
ማካፈል የሚችልበትን መንገድ እንዲያመቻች ጠቁመዋል፡፡

07/09/2018

መልካም አዲስ አመት አትበሉን!!!!!!!
የ ፳፻፲፩ (2011) ዓ.ም የመልካም ምኞት መግለጫ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን
እንዲሁም ማኅበራዊ ሚዲያዎች 'መልካም አዲስ አመት' ሲሉ "መልካም
አዲስ ገረድ' ማለታቸው መሆኑን ያውቃሉ......
"አመት" ተብሎ በአልፋው "አ" ሲጻፍ ሴት አገልጋይ ገረድን ይገልጻል።
ለምሳሌ፦
"ተፈሥሒ ኦ አመት ወእም ድንግል ወሰማይ ሰማያዌ..." /ውዳሴ ማርያም
ዘረቡዕ/ ሲል ገረድ(ሴት አገልጋይ) ና እናት፤ ድንግልና ሰማይ ሆይ ደስ ይበልሽ
ማለት ነው።
"ዓመት" ሲሆን ዘመን ይሆናል። "...ርእሰ ዐውደ ዓመት ዮሐንስ ወላዴ
መጥቅዕ ወአበቅቴ።..."/መልክአ ዮሐንስ መጥምቅ፤ ለሥእርተ ርእስከ(ለራስ
ጸጉርህ)/ ሲል ደግሞ "የመጥቅዕና የአበቅቴ መጀመሪያ ርእሰ ዓመት ዮሐንስ
ሆይ..." ማለት ነው።
አመት የሚለው በብዙ ቁጥር አእማት ይሆናል። በዕብራይስጥ አማህ፤
በሱሪስት አምታ፤ በዐረብኛ ደግሞ አመት ይለዋል። ትርጓሜውም ሴት ባሪያ፤
ገረድ፤ ደንገጥር ማለት ነው። "...በወፍጮ እግር እስካለችው እስከ ባሪያይቱ..."
ዘፀ.11፥5 የሚለውን ግዕዙ "አመት እንተ ትነብር ዲበ ማሕረጽ።" ይለዋል።
በዚህ አገባብ አማርኛው "ባሪያይቱ" የሚለውን ግዕዙ "አመት" ይላታል።
ወንዶች ባሪያዎችን "አግብርት" ሲላቸው ሴቶች ባሪያዎችን ደግሞ
"አእማት" ይላቸዋል። [ዘፍ.32፥5 ግዕዙን ንባብ ተመልከት]
ዓመት የሚለው ደግሞ በብዙ ቁጥር "ዓመታት" ሲባል ዘመን፥ ዘመናት፥
ብዙ ቀን፥ የዕለታት ድምር ማለት ነው። "በባቢሎን ንጉሥ በብልጣሶር
በመጀመሪያው ዓመት" ዳን.7፥1 የሚለውን ግዕዙ "በቀዳሚ ዓመተ
መንግሥቱ።" ይለዋል። "የዕድሜህም ቁጥር ብዙ ነውና፥" ኢዮ.38፥21
የሚለውን ግዕዙ "ኊልቆ ዓመታቲከ፥" ይለዋል።
ስለሆነም አንድ ሰው 'እንኳን ለአዲሱ አመት አደረሰን' ሲል 'እንኳን ለአዲሷ
ገረድ አደረሰን' አለ ማለት ነው። ይኼ ደሞ ጸያፍ ነው።
"እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሰን" ሲል "እንኳን ለአዲሱ ዘመን አደረሰን
ማለቱ ነው። ይኸውም የተገባ ነው።
መልካም ምኞታችሁን የገለጻችሁ መስሏችሁ 'መልካም አዲስ አመት'
አትበሉን!!!!!
ከዘማርያም ዘለቀ

Adresse

Democratic Republic Of The

Site Web

Notifications

Soyez le premier à savoir et laissez-nous vous envoyer un courriel lorsque Mk agarfa publie des nouvelles et des promotions. Votre adresse e-mail ne sera pas utilisée à d'autres fins, et vous pouvez vous désabonner à tout moment.

Partager