Hamere Noah Kidist Kidanemihret EOTC - Calgary

Hamere Noah Kidist Kidanemihret EOTC - Calgary Contact information, map and directions, contact form, opening hours, services, ratings, photos, videos and announcements from Hamere Noah Kidist Kidanemihret EOTC - Calgary, Religious organisation, 2020 27 Avenue, Northeast Calgary, AB.

01/21/2024

እንኳን አደረሰን።

በቃና ዘገሊላ ወይም በገሊላዋ ቃና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈጸመውን ተአምር በማሰብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በዓል ታከብራለች፡፡ ይህም በጥምቀት በዓል ማግስት በጥር ፲፪ ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገሊላ ክፍል በምትሆን በቃና በተደረገ ሰርግ ላይ ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር ተገኝቶ ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በወንጌሉ ‹‹የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ እናት ድንግል ማርያምም በዚያ ነበረች›› እንዳለ እመቤታችን ለሠርገኞቹ ዘመድ ነበረችና ከልጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ በሠርጉ ላይ ተገኝታ ነበር፡፡ በተጨማሪ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ከጌታ ጋር በሠርጉ ተገኝተው ነበር፡፡ ሆኖም ግን የሠርጉ ሥነ ሥርዓት እየተከናወነ ባለበት ጊዜ ድንገት የወይን ጠጅ አለቀ፡፡ አሳላፊዎቹም በጭንቀት ግራ በገባቸው ጊዜ የጭንቅ አማላጅ አዛኝ እናታችን ድንግል ማርያም ጭንቀታቸውን ተረድታ ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወር ብላ ‹‹የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም›› አለችው፡፡

እርሱም መልሶ ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› ‹‹ጊዜዬ ገና አልደረሰም›› አላት፡፡ እመቤታችንም ለአሳላፊዎቹ ‹‹የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ›› አለቻቸው፡፡ ጌታም በቦታው የነበሩ ስድስት የድንጋይ ጋኖች ውኃ ሞልተው እንዲያመጡ አዘዛቸው፡፡ ሲያመጡለትም ውኃውንም ወደ ወይን ለውጦ ለአሳዳሪው እንዲሠጡት አዘዘ፡፡ አሳዳሪውም ወደ ወይን የተለወጠውን ውኃ በቀመሰ ጊዜ አደነቀ፡፡ ከወዴት እንደመጣ ስላላወቀ ሙሽራውን ‹‹ሰው ሁሉ መልካሙን የወይን ጠጅ አስቀድሞ ያመጣል፤ ከጠገቡ በኋላም ተርታውን ያመጣል፤ አንተ ግን መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆየህ›› አለው፡፡ (ዮሐ.፪፥፩-፲፩)

ይህንን ድንቅ ተአምርም በማሰብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን አስተምህሮ በጥምቀት በዓል ማግስት ቀን የቃና ዘገሊላ በዓል ይከበራል፡፡ የቃና ዘገሊላ ጥንተ ነገሩ የተፈጸመው የካቲት ፳፫ ቀን ነው፡፡ ነገር ግን አባቶቻችን የውኃን በዓል ከውኃ በዓል ጋር ለማክበር ብለው የካቲቱን በዓል ወደ ጥር ፲፪ አምጥተውታል፡፡ ይህም ውኃ ወደ ወይን የተለወጠበትን በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ለማከናወን ነው፡፡

ከበዓሉ ረድኤት ያሳትፈን፤ አሜን!

ፅንሰታ ለማርያም.
08/12/2023

ፅንሰታ ለማርያም.

ፅንሰታ ለማርያም

የብሕንሳ ኤጲስ ቆጶስ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ላይ የእመቤታችንን የፅንሰቷን ነገር "ኦ ድንግል አኮ በፍትወተጺነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ:- ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም ፤በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ" በማለት ተናግሯል፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከመወለዷ በፊት የአባቷ እና የእናቷ ታሪክ እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡ በኢየሩሳሌም አገር የሚኖሩ ኢያቄምና ሐና የተባሉ በጣም ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡ ልጅ ስላልነበራቸው እጅግ ያዝኑ ነበር፡፡ ወደ ቤተ እግዚአብሔር እየሄዱ እግዚአብሔር አምላክ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ አጥብቀው ይለምኑት ነበር፡፡ መባ ይዘውም ሒደው ለሊቀ ካህናት ሮቤል ሲሰጡት እረሱምሊቀ ካህኑ እንኳ ሳይቀር “እግዚአብሔር ብዙ ተባዙ ያለውን ሕግ በእናንተ ላይ እንዳይፈጸም አድርጎ ልጅ የከለከላችሁ ኃጢአተኛ ብትሆኑ ነውና መባችሁን አልቀበልም” ብሎ በእጅጉ አሳዝኗቸዋል። በሊቀ ካህናቱ እያዘኑና እየተከዙ ሲመለሱ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ ዛፍ ሥር ተቀምጠው ሳለ ርግቦች ከልጆቻቸው ጋር ሲጫወቱ ተመልክተው “ለእነዚህ ወፎች እንኳ ልጆችን የሰጠህ አምላክ ለእኛስ መች ይሆን ልጅ የምትሰጠን?” ብለው እጅግ አምርረው አለቀሱ፡፡

እንዲሁም ”ልጅ ያልወለደውን ከእግዚአብሔር በረከትን ያጣ ነው‘ እያሉ ያቃልሉት ነበርና በዚህም እያዘኑ እነርሱም ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ዘወትር ፈጽሞ ይለምኑ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ይኅን በሰሙ ጊዜ “ወንድ ልጅን ወይም ሴት ልጅን ቢወልዱ ለእግዚአብሔር ቤት አገልጋይ ሊያደርጉ” ስለትን ተሳሉ፡፡

እግዚአብሔር አምላክም ኃዘናቸውን ሰምቶ ሐምሌ ፴ እሷ ለእርሱ ግምጃ ሲያስታጥቁት መቋሚያው አፍርታ ፍጥረት ፍሬዋን ሲመገቡ፣ እሱ ለእሷ ነጭ ርግብ ሰባቱን ሰማያት ሰንጥቃ መጥታ በቀኝ ጆርዋ ገብታ በማኅፀንዋ ስታድር ራዕይ አሳያቸው። እነርሱም ሄደው ለመፈክረ ሕልም/ ሕልም ተርጓሚ/ ነገሩት፤ ሕልም ተርጓሚውም የከበረች ልጅ ትወላዳለችሁ” ሲል ተረጎመላቸው። እያቄም እና ሐናም ሕልማቸው እንዲፈጸምላቸው የእግዚአብሔርን ፈቃድ በጸሎት እየጠየቁ ኖሩ፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ አብርሃምን እና ሣራን የተመለከተ አምላክ በኢያቄምና ሐና አማካኝነት ለዓለም ድኅነት ምክንያት የሆነችውን እና ዓለም ሳይፈጠር በአምላክ ልቡና ታስባ ትኖር የነበረችው እመቤታችን ድንግል ማርያም በነሐሴ ሰባት ቀን ተፀነሰች፡፡

ሐና በእርጅናዋ ጊዜ መፅነሷን የሰሙት ዘመዶቿና ያገሯ ሰዎች ተገርሙው፤ እየመጡ ጠይየቋት፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያም በተሰነፀች ጊዜ ተአምራትን አድርጋለች። ከእነዚህም መካከል ዐይነ ስውር የነበረችው የአርሳባን ልጅ ወደ ሐና መጥታ እውነትም ሐና መፅነሷን ለማረጋገጥ መሕፀን ዳሰሰቻት፡፡ በአድናቆትም ዐይኗን ስትነካ ዐይኗ በራላት፡፡ በሌላ ጊዜም የአጎቷ ልጅ ሳምናስ በሕመም ምክንያት ይሞትና ሐና ትወደው ስለነበር አስክሬኑ በተቀመጠበት አልጋ ዙሪያ ስታለቅስ ድንገት ጥላዋ ቢያርፍበት የሞተው ተነሥቶ ሐና የአምላክ እናት የምትሆን እመቤታችንን እንደምትወልድና በዚህም ሐና እጅግ የከበረችና ምስጋና የሚገባት መሆኗን መሰከረ፡፡ ለዓለም ሁሉ የድኅነት መገኛ የሆነች ክብርት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተፀነሰችበት ዕለት ነሐሴ ሰባት የተባረከች እንደመሆኗ መላው ክርስቲያን በዓሏን ሊያከብር ይገባል፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ልጅሽ ወዳጅሽ ይቅርታውን፣ ቸርነቱን፣ ምሕረቱን በእኛ ላይ ያሳድርብን ዘንድ ለምኝልን፡ አሜን!!

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ነሐሴ እና መዝግበ ታሪክ

04/23/2023

የቅዱስ ጊዮርጊስ ሰማዕትነት በመጽሐፈ ስንክሳር

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አምላክ አመ ዕሥራ ወሠሉሱÂ ለሚያዝያ በዛቲ ዕለተ ኮነ ፍጻሜ ስምዑ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሰማዕት ዐቢይ ወክቡር ዘተሰምየ ፀሐየ ወኮከበ ጽባሕ፡፡

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሚያዝያ ሃያ ሦስት በዚች ቀን ፀሐይና የአጥቢያ ኮከብ የተባለ ታላቅና ክቡር የሆነ የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ የምስክርነት ፍጻሜ ሆነ፡፡

የዚህም ቅዱስ አባቱ መስፍን ነው፡፡ ስሙም አንስጣስዮስ ይባላል፡፡ ከቀጰዶቅያ አገር ነው፡፡ የእናቱም ስም ቴዎብስታ ይባላል ከፍልስጥዔም አገር ናት ታናሽ ሆኖ ሳለ አባቱ ዐረፈ፡፡

ሃያ ዓመትም በሆነው ጊዜ የአባቱን ሹመት ሊቀበል ወደ ንጉሥ ዱድያኖስ ዘንድ ሔደ፡፡ ንጉሡም ጣዖትን እንዲአመልኩ ሰዎችን ሁሉ ሲያስገድዳቸው አገኘው፡፡

ይህንንም አይቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ እጅግ አዘነ በእርሱ ዘንድ ያለውን ገንዘቡን ሁሉ ለድኆች፣ ለምስኪኖች ሰጠ ባሮቹንም ነፃ አወጣቸው፡፡

ከዚህ በኋላ በንጉሥ ፊት ቁሞ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ፡፡ ንጉሡም አባበለው ብዙ ቃል ኪዳንም ገባለት እርሱ ግን አልተቀበለውም፡፡

ለመስማት እንኳ የሚያስጨንቅ ሥቃይን አሠቃየው ጌታችን ግን ያጸናዋል ቍስሉንም ያድነዋል ሦስት ጊዜም እንደሚሞት እርሱም እንደሚአስነሣው በአራተኛውም የምስክርን አክሊልን እንደሚቀበል ነገረው፡፡ ቃል ኪዳንም ሰጠው ስሙ በዓለሙ ሁሉ የተገለጠ ይሆን ዘንድ በተጋድሎና መከራ በመቀበልም ጽኑዕ በሆነ ሥቃይም ሰባት ዓመት እንደሚኖር መላእክትም እንደሚአገለግሉት ነገረው፡፡

ንጉሡም ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለመታዘዙና ባለመመለሱ እጅግ አዘነ፡፡ ስለዚህም አትናስዮስ የሚባል ታላቅ ሥራየኛ አመጣ፡፡ እርሱም መርዝን ቀምሞ በጽዋ መልቶ አስማት ደግሞ እንዲጠጣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሰጠው፡፡ ወዲያውኑ የሚሞት መስሎት ነበር፡፡ ቅዱሱም ያንን ጽዋ ጠጣው ምንም ጉዳት አልደረሰበትም፡፡

ያ መሠርይም በክብር ባለቤት በጌታ በኢየሱስ አምኖ በሰማዕትነት ሞተ፡፡ ከእርሱም ጋር ሌሎች ብዙዎች ሰዎች በሰማዕትነት ሙተው የሕይወት አክሊል ተቀበሉ ቁጥራቸውም ሠላሳ ሺህ ሰባት መቶ ነፍስ ነው፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስም በዱድያኖስና በሰባ ነገሥታት ፊት በቆመ ጊዜ በዚያም የተቀመጡባቸው የዕንጨት ወንበሮች ነበሩ፡፡ ቅዱሱንም እሊህን የተቀመጥንባቸውን ወንበሮች እንዲበቅሉ እንዲአብቡና እንዲአፈሩ ታደርጋቸው ዘንድ ከአንተ እንሻለን አሉት፡፡ በዚያን ጊዜ ጸለየ እንዳሉትም አደረጋቸው ይህንንም ድንቅ ሥራ አይተው ቍጥር የሌላቸው ብዙ አሕዛብ በጌታችን አመኑ፡፡

ከዚህም በኋላ ቅዱሱን ወስደው በጐድጓዳ ብረት ምጣድ ውስጥ አበሰሉት፡፡ አቃጥለው አሳርረውም ሥጋውንና ዐጥንቱን ፈጭተው አመድ አድርገው ከረጅም ተራራ ላይ በተኑት፡፡ ጌታችንም ነፍሱን ወደ ሥጋው መልሷት ደግሞ አስነሣው፡፡ ወደ ነገሥታቱም ተመልሶ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ስም ሰበከ፡፡ ቍጥር የሌላቸው አሕዛብ አይተው አደነቁ በጌታችንም አምነው በሰማዕትነት ሞቱ፡፡

ነገሥታቱም ደግመው ሙታኖችን ብታሥነሣ አምላክህ ዕውነተኛ አምላክ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ በእርሱም እናምናለን አሉት፡፡ ቅዱሱም ጸለየ ከጒድጓድም ውስጥ ወንዶችና ሴቶችን ጐልማሶችንም አስነሣላቸው እነዚያም በክብር ባለቤት በጌታችን ስም አስተማሩ የገሀነምንም ወሬ ተናገሩ ጥምቀትንም ተቀብለው ተመልሰው ዐረፉ፡፡

ከሀድያን ነገሥታት ግን ሙታንን ያስነሣህ አይደለም የረቀቁ ሰይጣናትን አሳየህ እንጂ ብለው ተከራከሩ፡፡ ከዚያም ከጭንቀታቸው ብዛት የተነሣ ከአንዲት ድኃ ሴት ዘንድ አስጠበቁት እርሷም እንጀራ ልትለምንለት ወጣች የእግዚአብሔርም መልአክ በላዩ ከበጎ ነገር ሁሉ የተመላ ማዕድን አቀረበለት፡፡ የዚያች መበለትም የቤቷ ምሰሶ ቅርንጫፍን አበቀለ ታላቅ ዛፍም ሆነ፡፡

ያቺም መበለት በተመለሰች ጊዜ የቤቷ ምሰሶ ቅርንጫፍ አብቅሎ ታላቅ ዛፍ እንደሆነ ስለ ማዕዱም ይህን ታላቅ ምልክት አይታ የክርስቲያኖች አምላክ ሰው ተመስሎ ወደ እኔ መጣ አለች፡፡ ቅዱስም እኔ አምላክ አይደለሁም፡፡ የአምላክ ባሪያ ነኝ እንጂ አላት፡፡ እርሷም እንዲህ ብላ ለመነችው የአምላክ አገልጋይ ከሆንክ ቸርነትህ እንድትደርሰኝ እለምንሃለሁ፡፡ ዕውር ደንቆሮ ዲዳ ጐባጣ የሆነ ልጅ አለኝና ታድንልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ፡፡ ስለ ጌታችን እምነትም አስተማራትና በመስቀል ምልክት አማተበው ያን ጊዜም አየ፡፡ ቅዱሱም በሌላ ጊዜ እንዲሰማ እንዲናገርና እንዲሔድ እንዲአገለግለኝም እኔ እሻለሁ አላት፡፡

በዚያን ጊዜ ንጉሡ በአገሩ ሜዳ ውስጥ ሲዘዋወር ያቺን ዛፍ አይቶ አደነቀ ስለ እርሷም ጠየቀ ቅዱስ ጊዮርጊስ በእርሷ ዘንድ የተቀመጠባት የዚያች መበለት የቤቷ ምሰሶ እንደሆነ ነገሩት፡፡ ንጉሡም ተቆጣ ቅዱሱንም ከዚያ ወስዶ አስገረፈው በመንኰራኵርም አበራዩት ሙቶም ከከተማ ውጭ ጣሉት ጌታም ከሞት አስነሣው ወደ ነገሥታቱም ተመለከተ ንጉሡም አይቶ ደነገጠ ስለ ሕይወቱም አደነቀ፡፡

ከዚህም በኋላ ይሸነግለው ዘንድ ጀመረ በመንግሥቱ ላይም ሁለተኛ ያደርገው ዘንድ ቃል ገባለት ቅዱስ ጊዮርጊስም እየዘበተበት ነገ በጥዋት ለአማልክቶችህ መሥዋዕትን አቀርባለሁ አንተም ሕዝቡ እንዲሰበሰቡ እዘዝ እኔ ስሠዋ እንዲአዩ አለው፡፡ ንጉሡም ዕውነት የሚሠዋ መስሎት ደስ አለው ወደ ቤተ መንግሥቱም እልፍኝ አስገብቶ አሳደረው፡፡

ለጸሎትም ተነሣ የዳዊትንም መዝሙር አነበበ የዱድያኖስ ሚስቱ እለስክንድርያ ንግሥት ሰምታ ቃሉ ደስ አሰኛት የሚያነበውንም ይተረጒምላት ዘንድ ለመናቸው፡፡ እርሱም እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ሰው እስከሆነበት ጊዜ የሆነውን ሁሉ ሊያስረዳትና ሊያስገነዝባት ጀመረ፡፡ ትምህርቱም በልቡዋ ተቀርጾ በክብር ባለቤት በጌታችን አመነች፡፡

በማግሥቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአማልክት ሲሠዋ ለማየት ሰው ሁሉ እንዲሰበሰብ ዐዋጅ ነጋሪ ዞረ የቤቷን ምሰሶ ያበቀለላት ያቺ መበለት ሰምታ ዕውነት መስሏት እጅግ እያዘነች ልጅዋን ተሸክማ እያለቀሰችም ወጣች፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስም በአያት ጊዜ ፈገግ አለ ልጅሽን በምድር ላይ አኑሪው አላት፡፡ ከዚያም ልጅዋን ጠርቶ ወደ አጵሎን ሒድ ወደእኔም ይመጣ ዘንድ በክብር ባለቤት በጌታዬ ኢየሱስ ስም እዘዘው አለው፡፡ ያን ጊዜ ያ ልጅ ድኖ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዳዘዘው ወደ ጣዖቱ ቦታ ሒዶ አዘዘው፡፡ በጣዖቱ ያደረ ያ ርኵስ መንፈስም ከማደሪያው ወጥቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አለት መጥቶ እኔ ሰውን ሁሉ የማስት እንጂ አምላክ አይደለሁም ብሎ በሕዝቡ ሁሉ ፊት አመነ፡፡ ቅዱሱም ትውጠው ዘንድ ምድርን አዘዛትና ወዲያውኑ ዋጠችው ጣዖታቱንም ከአገልጋዮቻቸው ጋራ አጠፋቸው ንጉሡም ከወገኖቹ ጋር ዐፈረ፡፡

ብስጭትና ቁጣንም እንደተመላ ወደ ንግሥት ሚስቱ ዘንድ ገባ፡፡ እርሷም አምላካቸው ጽኑዕና ኃያል ነውና ክርስቲያኖችን አትጣላቸው አላልኩህምን አለችው፡፡ ይህንንም ከእርስዋ ሰምቶ በእርሷ ላይ እጅግ ተቆጣ ወደ ክብር ባለቤት ክርስቶስ እምነት የከበረ ጊዮርጊስ እንደአስገባት አወቀ፡፡

ከዚህም በኋላ ከከተማ ውጭ እንዲጐትቷትና በመጋዝም እንዲሰነጥቋት አዘዘ፡፡ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለች፡፡

በዚያም ጊዜ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሥራ ነገሥታቱ ሁሉም ደነገጡ ኀፍረት ደግሞ እንዳይጨምርባቸው ከእርሱም እንዲአርፍ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ እንዲጽፍ ንጉሥ ዱድያኖስን መከሩት፡፡

ያን ጊዜም የክቡር ጊዮርጊስን ራስ በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ፡፡ ድል አድራጊ ጊዮርጊስም እጅግ ደስ አለው፡፡ እሳት ከሰማይ አውርዶ ሰባውን ነገሥት ያቃጥላቸው ዘንድ መከራውም ከክርስቲያን ወገን ጸጥ ይል ዘንድ ጌታችንን ለመነው፡፡ ወዲያው እሳት ወርዶ ከሠራዊታቸው ጋር ሰባውን ነገሥታት አቃጠላቸው፡፡

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተገልጾ ብዙ ቃል ኪዳን ሰጠው፡፡ በምድር መታሰቢያህን ለሚያደርግ ሁሉ እኔ ኃጢአቱን ሁሉ እደመስሳለሁ በመከራም ውስጥ ሁኖ በባሕርም ሆነ በየብስ ወይም በደዌ በስምህ የሚለምነኝን እኔ ፈጥኜ ከመከራው አድነዋለሁ፡፡ ይህንንም ጌታችን ተናግሮ በክብር ወደ ሰማይ ወጣ፡፡

ከዚህ በኋላ ራሱን ዘንበል አድርጎ በሰይፍ ቆረጡት በመንግሥተ ሰማያት አክሊላትን ተቀበለ፡፡ ከአገልጋዮቹም የቀሩት ሥጋውን ወስደው በልብስ ጠቀለሉት ወደሀገሩ ልዳም ወሰዱት፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ሠርተው በውስጥዋ አኖሩት ከእርሱም ቍጥር የሌላቸው ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የቅዱስ ጊዮርጊስም በረከቱ ረድኤቱ ሁላችን የክርስቲያን ወገኖችን ከሥጋና ከነፍስ መከራ ይጠብቀን ለዘላለሙ አሜን፡፡

03/25/2023

ገብር ኄር

የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ገብር ኄር የተሰየመው በቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ በዚህ ሳምንት ለሰው ሁሉ የማገልገያ ጸጋ መሰጠቱን፣ ሰጪው እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን፣ ቅን አገልጋዮች ስለሚቀበሉት ዋጋ ፣ ሰነፍ አገልጋዮች ስለሚጠብቃቸው ፍርድ ይሰበካል፡፡ «ገብር ኄር ወገብር ምእመን ዘአሥመሮ ለእግዚኡ፤ ጌታውን ያስደሰተው አገልጋይ ታማኝና ቸር አገልጋይ ነው፤መኑ ውእቱ ገብር ኄር፤ ቸር አገልጋይ ማን ነው?» እያሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይዘምራሉ፤ በቅዳሴው ደግሞ የማቴዎስ ወንጌል ፳፭፤፲፬-፴ ይነበባል።

፩. የምሳሌው ትርጉም

የመክሊቱ ባለቤት አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ባለ አምስት፤ ባለ ሁለትና ባለ አንድ መክሊት የተቀበሉት በጥምቀት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ፤ተምረው የሚያስተምሩ መምህራን ናቸው፡፡ የስጦታው መለያየት መበላለጥን ለማሳየት ሳይሆን የአንዱ ጸጋ ከሌላው እንደሚለይ የሚያጠይቅ ነው፤ «መንፈስ ቅዱስ አንድ ሲሆን ስጦታው ልዩ ልዩ ነው፡፡ ጌታም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ» ፩ቆሮ ፲፪፥ ፬፡፡
ባለ አምስትና ባለ ሁለት መክሊት የተባሉት አገልጋዮች ቃለ እግዚአብሔርን ከተማሩ በኋላ መክረው አስተምረውና ራሳቸውን አስመስለው ያወጡ ናቸው፡፡ ባለ አንድ መክሊት የተባለው ዐላውያን ነገሥታት፤ ዐላውያን መኳንንት እሳት ስለት አሳይተው ቢያስክዱኝ፣መናፍቃን ተከራክረው ቢረቱኝ፣ ምላሽ ቢያሳጡኝ፣ ሃይማኖቴን ቢያስቱኝ ብሎ ከማገልገል ይልቅ ሃይማኖቱን የማያስተምርና የማይመሰክር ነው፡፡ «ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔም በሰማያት በአለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ በሰው ፊት የሚክደኝን ግን እኔም በሰማያት በአለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ» ብሏል፤ ማቴ ፲፤፴፪ ፡፡ ስለዚህ በተሰጠን መክሊት በተባለ ጸጋ በሰው ሁሉ ፊት በማገልገል ልንመሰክር ይገባል፡፡

፪ አምስትና ሁለት መክሊት የተቀበሉ አገልጋዮች ጠባይ

እነዚህ አገልጋዮች ለጌታቸው ታማኝ የነበሩ፤ በተቀበሉት መክሊት ወጥተው፤ ወርደውና አትርፈው የተገኙ ናቸው፡፡ መክሊታቸውን ከተቀበሉ በኋላ በእምነት ሊሰማሩ ወጡ እንጂ በሥጋት እጅና እግራቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም፡፡ እነርሱም በተሰጣቸው መክሊት መጠን በእምነት በማገልገላቸው ሁለቱም ገብር ኄር (ቸር አገልጋይ) የሚል የክብር ስም ተሰጣቸው፤ «ወደ ጌታህ ደስታ ግባ» የሚለውን የምሥራች ቃል ሰሙ፡፡

፫. አንድ መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ጠባይ

እምነት የጎደለው ተጠራጣሪ ነበረና ማትረፉን ሳይሆን መክሰሩን፣ ማግኘቱን ሳይሆን መድከሙን፣ ብቻ አሰበ፡፡ በተቀበለው መክሊት ባለማትረፉ ራሱን ከመውቀስ ይልቅ ሰጪውን ጌታ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፤ ካልበተንህበት የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው ብሎ የጽርፈት ንግግርን ተናገረ፡፡ ጌታው አስቀድሞ መክሊቱን ሲሰጠው አልቀበልም ሳይል ምን ሠራህና ምን አተረፍህ ሲባል ጌታውን ከሰሰ፡፡ ልቡ የደነደነ፣ጥፋቱን ለማመን የማይፈቅድ፣ለመመለስ የዘገየ ነበረና ወደ ውጭ ልቅሶ፤ ጥርስ ማፏጨት ወዳለበት አውጡት የሚለውን የፍርድ ቃል ሰማ፡፡ ዛሬ መልካም ሥራ ላለመሥራታቸው ምክንያት የሚያበዙ፣ ሃይማኖታቸውን ለመመስከር የሚያፍሩ፣ የሚፈሩና ኀጢአት ለመሥራት ግን የሚደፍሩ ሰዎች ባለ አንድ መክሊቱን አገልጋይ ይመስላሉ፡፡ እንግዲህ «በጎ ነገር ማድረግን የሚያውቅ፤ የማይሠራትም ኀጢአት ትሆንበታለች» ተብሏልና፤ያዕ ፬፥፲፯፡፡

፬ ለአገልግሎት ተፈጥረናል

እግዚአብሔር ሰውን በአርአያው ፈጥሮ፤ በልጅነት ጸጋ አክብሮ፤ ሁሉን አዘጋጅቶ ለአዳም አንድ ልጁን ለመስቀል ሞት ያዘዘው በዓላማ ነው፡፡ ይኸውም «እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ላዘጋጀው በጎ ሥራ በኢየሱስ ክርስቶስ የፈጠረን ፍጥረቱ ነንና» ኤፌ ፪፥፲፡፡ ለመልካሙ ሥራ ሁሉም ሰው ተጠርቷል፤ በጥምቀት ዳግም የወለደንና በመስቀሉ ያዳነን በመልካም ሥራ እንድናገለግል ነው፡፡

፭ እኛ በመክሊታችን ምን አተረፍን?

ጸጋችንን እናውቃለን? ለማወቅስ እንሻለን? በተሰጠን ጸጋ አትርፈናልን? ካላተረፍን ለምን? በእርግጥ አለማትረፋችን ግድ ይለናል? ከእግዚአብሔር ዘንድ ጸጋ ያልተቀበለ የለም፤ ሰው ጸጋውን አለማወቁ አልተቀበለም፤ ጸጋ የለውም አያሰኝም፡፡ ከሁሉ አስቀድመን ጸጋ እንደ ተሰጠን ማመን ይጠበቅብናል፡፡ የተሰጠንን ጸጋ ለማወቅ ለሕይወታችን በሚጠቅም አገልግሎት ራሳችንን መፈተን መሞከር ይጠበቅብናል፤ ሳንሰማራና ራሳችንን ሳንፈትን ጸጋችንን ማወቅም ሆነ ማትረፍ አይቻልም፡፡ ጸጋ እንደተሰጠን አምነን ስንረዳና ራሳችንን ለአገልግሎት ስናዘጋጅ ማትረፊያ አገልግሎቱን መመልከት እንችላለን፡፡ በምን ማገልገል እዳለብን አለማወቅ አገልግሎትን ውስን አድርጎ መመልከት፣ለአገልግሎት መዘግየትና እንዴት ማገልገል እንዳለብን አለመረዳት ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ፡-

ሀ) በምን እናገልግል?

አንዳንዶች ምን ጸጋ ኖሮኝ ነው የማገለግለው? ሲሉ ይሰማሉ፤ ነገር ግን ከጸጋ እግዚአብሔር የጎደለ ሰው የለም፡፡ «መንፈስ ግን አንድ ሲሆን ስጦታው ልዩ ልዩ ነው፤ ጌታም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ፡፡ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አሠራር አለ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የጥበብ ቃል የሚሰጠው አለ፡፡ በመንፈስ ቅዱስም የዕውቀት ቃል የሚሰጠው አለ፡፡ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፤ ለአንዱም ተኣምራትን ማድረግ፤ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፤ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፤ለአንዱም በልዩ አይነት ልሳን መናገር፤ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጐም ይሰጠዋል» ይላል፤፩ቆሮ ፲፪፥፬–፲፡፡ ስለዚህ በአለን ጸጋ ማገልገል ይገባናል፡፡

ለ) አገልግሎት ውስን ነውን?

አገልግሎት በቤተ ክርስቲያን፤ በበዓላትና በአጽዋማት ብቻ የሚመስላቸው፣ ካልቀደሱና ካላወደሱ፣ ካልዘመሩና ካላስተማሩ አገልግሎት የሌለ የሚመስላቸው ሰዎች አይጠፉም፡፡ ነገር ግን አገልግሎት በጊዜና በቦታ፤ በሁኔታም ሆነ በዓይነት አይወሰንም፡፡ «ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ፤ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ፤ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ» ፩ጴጥ ፪፥፭፡፡ የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ስንሆን ሕዋሳቶቻችን እግዚአብሔርን የምናገለግልባቸው ንዋየ ቅድሳት ናቸው፡፡ በዐይናችን ቅዱሳት መጻሕፍትን ስናነብ፣ በጆሮአችን የተገፉትንና የተቸገሩትን ሰዎች ጩኸት ስንሰማ፣አፋችንን ለጸሎት ለምስጋና ስንክፈት፣ እጆቻችን ለአሥራት በኩራት ለምጽዋት ሲዘረጉ፣እግሮቻችን ማልደው ወደ ቤተክርስትያን ለጸሎት ሲገሰግሱ፣መንፈሳዊ ቤት ለመሆን እየሠራን እያገለገልን ነው፡፡ በጊዜያችን የታመሙትንና የታሰሩትን ብንጠይቅ፣ በጉልበታችን ደካሞችን ብንረዳ፣ በዕውቀታችን ያላወቁትን ብናሳውቅ ፣ በገንዘባችን የተቸገሩትን ብንጎበኝ፤ በጸጋ ላይ ጸጋና በበረከት ላይ በረከት እናተርፋለን፡፡ ወደ ጌታ ደስታ ግቡ የሚለውን የምስራች ቃል እንሰማለን፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንሆናለን፡፡

ሐ) ለአገልግሎት ብንዘገይስ?

አንዳንድ ሰዎች ማገልገል እንዳለባቸው ቢያውቁም ለውሳኔ ይዘገያሉ፡፡ «ዛሬ ወይም ነገ ወደዚያች ከተማ እንሄዳለን ፤ በዚያችም ዓመት እንኖራለን፤ እንነግዳለንም፤ እናተርፋለንም፤ የምትሉ እናንተ ተመልከቱ፤ ነገ የሚሆነውን አታውቁምና» ያዕ ፬፥፲፫-፲፬፡፡ ዛሬ እንኑር ነገ ስለማናውቅ የኛ የሆነውን ተረድተን ልናገለግል ይገባል፡፡ «ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች» ዮሐ፤፱፥፬፡፡ ሌሊት የተባለው ዕለተ ሞትና ዕለተ ምጽአት ነው፤ በሞት ከተጠራን በኋላ ልማር ላስተምር፣ ልወድስ ልቀድስ፣ ላጉርስ ላልብስ ማለት የለምና ለአገልግሎት ልንፈጥን ይገባል፡፡

መ) እንዴት እናገልግል?

ማገልገል አንድ ነገር ሆኖ ሳለ እንዴት ማገልገል እዳለብን ካልተረዳን አገልግሎታችን ያለእምነት የተሟላ አይሆንም፡፡ «ያለ እምነትም እግዚአብሔርን ደስ ማሠኘት አይቻልም» ዕብ ፲፩፥፮፡፡ ሰማያዊ ዋጋን እያሰብን እናገልግል፤ «ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየኛል? መከራ ነውን? ኀዘን ነውን? ስደት ነውን? ራብ ነውን? ጭንቀት ነውን? ሾተል ነውን?» ሮሜ.፰፥፴፭፡፡ ሰማያዊውን ዋጋ ስናስብ በፈተና በመከራ እንጸናለን፤ በትሕትና ሆነን እናገልግል «ከእኔ ተማሩ፤ እኔ የዋህ ነኝና፤ ልቤም ትሑት ነውና» ብሏል፤ ማቴ ፲፩፡፳፱፡፡
እንግዲህ መክሊት የተቀበሉትን አገልጋዮች ስናስብ፤ አምስትና ሁለት መክሊት የተቀበሉ፤ ለጌታቸው ታማኝ የነበሩ፤ በተቀበሉት መክሊትም መከራን ታግሰውና በእምነት በማገልገላቸው ሁለቱም ገብር ኄር (ቸር አገልጋይ) ተባሉ፡፡ አንድ መክሊት የተቀበለው አገልጋይ እምነት የጎደለው ተጠራጣሪ ነበረና ማትረፉን ሳይሆን መክሰሩን ብቻ የሚያስብ ደካማ፤ የተፈጠረበትን ዓላማና የተሰጠውን ተልእኮውን ያልተረዳ ሰው ነበር። እኛም በጥምቀት ዳግም የተወለድነውና በመስቀሉም የዳንነው ተልእኳችንን ተረድተን በመልካም ሥራና በታማኝነት እንድናገለግል ነው፡፡ ቀደምት ቅዱሳን አባቶቻችንን አርአያ በማድረግ ለምን፤ በምንና እንዴት ማገልገል እዳለብን ልንረዳ ይገባል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ ወወላዲቱ ድንግል፤ ወመስቀሉ ክቡር!

ምንጭ፥ ማህበረ ቅዱሳን

03/18/2023

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

ደብረ ዘይት የወይራ መብቀያ፣ በወይራ ደን የተሸፈነ ተራራ ማለት ነው። «ደብር» ማለት «ተራራ» ማለት ሲሆን «ዘይት» ማለት ደግሞ «ወይራ» ማለት ነው። በዚህም «ደብረ ዘይት» ማለት የወይራ ዛፍ የሞላበት፣ የበዛበት፣ የወይራ ተራራ ማለት ይሆናል።
ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ የሚገኝ ቦታ የሚገኘው ተራራ በደብረ ዘይት በመካከል የቄድሮን ሸለቆ ብቻ አለ። ከግርጌው ጌቴ ሴማኒ የተባለው የአትክልት ስፍራ ይገኛል። የጸሎተ ሐሙስ ማታ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተያዘበትና በኋላም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ሥጋዋ ያረፈበት ወይም የድንግል መካነ መቃብር በዚህ ተራራ ግርጌ ይገኛል። ቤተ ፋጌ እና ቢታንያ በኮረብታው ጫፍ እና በምሥራቅ ዳገት ላይ ይገኛሉ። ይህ ተራራ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጸ ብዙ ድርጊቶች የተፈጸሙበት ቦታ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስ፣ ስለ ዓለም ፍጻሜና ስለ ዳግም ምጽአት በዚህ ተራራ ላይ ተናገሯል። (ማቴ.፳፬፥፫) በዚሁ ተራራ ላይ ወደ ሰማይ ዐርጓል። በዚሁ ተራራ ላይ ቀን በከተማና በገጠር ሲያስተምር ውሎ ሌሊት የሚያድርበት የኤሌዎን ዋሻ ይገኛል። በኋለኛው ምጽአቱ በዚሁ ቦታ እንደሚገለጥ ትንቢት ተነግሯል። (ሉቃ.፳፬፥፶፣ዘካ.፲፬፥፫-፭)

የዓቢይ ጾም እኩሌታ ላይ ያለው ሰንበት በዚህ ተራራ ተጠርቷል። ይህንን ዕለት የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ የዳግም ምጽአት አድርጎ መዝሙሩን ጽፏል። በዚህ ተራራ ላይ «እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፦ ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት» ተብሎ እንደተጻፈው ለደቀ መዛሙርቱ የዳግም ምጽአቱን፣ የዓለምን ፍጻሜና የትንሣኤ ሙታንን፣ ትምህርት በሰፊው ስላስተማረ በዓሉ በተራራው ስም ተሰይሟል።(ማቴ.፳፬፥፫)
ከዕለታት አንድ ቀን ደቀ መዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ሥነ ሕንፃ በትኩረት እያንዳንዱን ነገር በመመልከት አደነቁ። ጧት በጸሎት ጊዜ ጸሎታቸውን አድረሰው ሲጨርሱ የጧት ፀሐይ አርፎበት ያሸበረቀውን ቤተ መቅደስ ውበቱን አስተውለው የትኛው ጥበበኛ እንዳሠራው እየተነጋገሩ ጌታችንንም አብሮ እንዲያደንቅ ሲጠብቁ እርሱ ግን ያልጠበቁትን ነገር ተናጋረ። ቤተ መቅደሱ እንደሚፈርስ፣ አያይዞም ከሞት በኋላ ተነሥቶ እንደሚያርግና ነገር ግን ዓለምን ለማሳለፍ ዳግም እንደሚመጣ ወደፊት የሚሆኑ ምሥጢራትን እንዲሁም በቤተ መቅደሱና በሕዝቡ ላይ የሚደርሰውን ትንቢት ነገራቸው። ይህም ነገር ዕረፍት ስለነሣቸው ወደ ደብረ ዘይት ከተሻገሩ በኋላ በሰፊው እንዲገልጽላቸው ጠየቁት። በዚህ ክፍል እንደምናየው ጥያቄያቸው ዕለትና ምልክት ነው፤ ወይም «መቼ» እና «ምን» የሚል ነው። የቤተ መቅደሱ መፍረስ መቼ ይሆናል? የዓለም መጨረሻና የመምጣትህስ ምልክቱ ምንድን ነው? ጌታችንም በጥያቄያቸው ላይ ብቻ አተኩሮ ሰፊ መልስ ሰጥቷቸዋል።
መቼ ይሆናል ላሉት የመጀመሪያው ጥያቄ «ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም (ሰውም) ቢሆን የሚያውቅ የለም» ሲል አጭር መልስ ሲሰጥ፣ ስለ ሁለተኛው ጥያቄም መቀበል ቢከብዳቸውም በማስጠንቀቂያዎች፣ በምክሮች፣ በማጽናኛዎችና በምሳሌዎች አስተምሯቸዋል። (ማቴ.፳፬፥፴፮)

የዳግም ምጽአት ምልክቶቹ

፩.ሐሰተኞች ክርስቶሶች
ጌታችን ኢየሱስ በአንደኛ ደረጃ የተናገረው ምልክት በተለያዩ ወቅቶችና ሀገራት ብዙ ሐሰተኛ ክርስቶሶች እንደሚነሡ ነው። የጌታችን ቃል አይቀርምና ከዚህ ቀደም ብዙ ሰዎች «እኔ ክርስቶስ ነኝ» በማለት ተነሥተው ነበር። በዮሐንስ ራእይ ላይ ዋናው አውሬ ተብሎ የተጠቀሰውና በቅዱስ ጳውሎስ «የዐመፅ ሰው እርሱም የየጥፋት ልጅ» የተባለው ብዙ ጥፋትና መከራ የሚያደርሰው ባለ ፮፷፮ (ስድስት ስድሳ ስድስት) መለያ ምልክቱ ሐሳተኛ ክርስቶስ እስኪገለጥ ደረስ መንገድ ብዙ ሐሰተኞች ክርስቶሶች ተነሥተዋል። በእውነተኛው ንጉሥ ክርስቶስ ዳግም መምጣት የሚደመሰሰው ሐሳዊ መሲሕ የመጨረሻውና ለሦስት ዓመት ከመንፈቅ ቤተ ክርስቲያንን የሚወጋ የታላቁ መከራ ፈጻሚና አስፈጻሚ ይሆናል። ጌታችን እስኪመጣ ድረስ እንዳንሰናከል አስቀድሞ «ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ … በዚያን ጊዜ ማንም እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ» ሲል ያስጠነቀቀን ለዚህ ነው።(ራእ. ፲፫፥ ፭፣፳፫)

፪.ጦርነት
ጦርነት ቀደምት የነበረ፣ በአሁኑ ጊዜ ዘመን በብዛት የተከሰተ ነገር ግን በተለይ በዚህ ጊዜ በብዙ ሀገራት የተካሄድ ነው፡፡ ጦርነት በቀደምት ዘመናት ሴቶችን፣ አቅመ ደካማ ሺማግሌዎችንና ሕፃናትን ለእልቂት የማያጋልጥ ነበር። በዚህ ጊዜ ግን ጦርነት ማንንም የማይለይ፣ ለማንም የማይራራ፣ የሁሉን ደም የሚያፈስና እጅግ አስከፊ ሆኗል። ይህንንምም ጌታችን የዳግም ምጽአቱን ምልክት ለጠየቁት ለደቀ መዛሙርቱ ሁለተኛ ምልክት አድርጎ «ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና» ሲል ተናግሯል። (ማቴ.፳፬፥፮)

፫.ረኃብ
ረኃብ ሰዎችን በአስከፊና በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ የሚከት አሳዛኝ ክስተት ነው፤ ስለ ረኃብ ወሬ በሀገራችንም ኢትዮጵያ ጭምር የሰማነውና ያየነው በመሆኑ የገንዘብ አቅም ያለው ረኃብተኞችን ለማብላት እና ለማጠጣት የሌለው ደግሞ በጸሎት ለመርዳት ጥሯል፡፡ ነገር ግን ይህ ሰው ሰራሽ ችግር ለጠላቶቻችን መሳለቂያ አድርጎን ይኖራል። በተለይ የተፈጥሮ ችግር ሳያጋጥመን ሰዎች ባመጣነው ችግር በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ለአስቸኳይ ምግብ ርዳታ የተጋለጠበት ሁኔታ ያሳዝናል። ይህም ዓይነት በጥል፣ በተንኮልና በጭካኔ ሰዎች የሚፈጥሩት ችግር የምጽአት ሦስተኛ ምልክት ሆኖ በጌታችን ለደቀ መዛሙርት ተነግሯል፤ «ረሀብም ቸነፈርም በልዩ ልዩ ሥፍራ ይሆናል» እንዲል። (ማቴ.፳፬፥፯)
፬. የመሬት መንቀጥቀጥ
የመሬት መንቀጥቀጥ ባለፉት ዓመታት በርካታ ጉዳት በተለያዩ ሀገሮች እንዳደረሰ የሚዘንጋ አይደለም። በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዛሬ በዘመናት በተለያዩ ሀገሮች የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈና በርካቶችን ቤት ንብረት አልባ ያደረገ የመሬት መንቀጥቀጥ በሄይቲ፣ በታይዋን፣ በቱርክ፣ በፊልፕንስ፣ አንዲሁም በሌሎች ሀገራት ተከሥቷል። ይህም ለደቀ መዛሙርቱ የዓለም ፍጻሜ ምልክት የማግኘት ጥያቄ የተሰጠው «የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል» ተብሎ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ፍጻሜ ምልክት ተደርጎ የተነገረው ቃል አይቀርምና እየሆነ ነው። (ማቴ.፳፬፥፯)

፭. የክርስቲያኖች መከራ
የክርስቲያኖች መከራ እየጀመረ ይመስላል። ሰይጣን ኢቴስቶችን፣ እስላሞችንና አይሁድን በመጠቀም በክርስቲያኖች ላይ ከምንጊዜውም በላይ ችግር መፍጠር የጀመረበት ጊዜ ነው። በአውሮፓ የክርስቲያኖች ጥያቄ ቶሎ የማይመልስበት ጊዜ ሆኗል፤ የቤተ ክርስቲያንን ጥያቄ ለማስተናገድም መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ፈቃደኛነታችውን እያጡና ይህንን ወንጀላቸውን ለመሸፈንም በሕግ አንቀጽ እየፈጠሩለት ይታያሉ። «በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችሁማል፤ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ» ተብሎ እንደተጻፈው በሃይማኖት ጸንቶ መኖር እንደኋላ ቀርነት፣ ከሐዲነት እንደተራማጂነትና ሥልጡንነት የሚታይበት ዘመን ላይ እንዳለን ግልጽ ነው። ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተስፋፋ አመለካከት ክርስቲያኖችን ወደ ማግለልና ወደ መወንጀል የሚያድግ መሆኑ ከሚታዩት እኩይ ተግባራት መካከልም ይቆጠራል፡፡ (ማቴ.፳፬፥፱)

፮. ሐሰተኞች ነቢያት
በዲያብሎስ መንፈስ ምትሐታዊ አሠራርን እያሳዩ፣ አይቻላቸው እንጂ ቢቻላቸው የተመረጡትን ሳይቀር የሚያስቱ «ነቢያት ነን» የሚሉ ብዙዎች ደፋሮች እንዲመነሡ ጌታችን ስድስተኛ የዳግም ምጽአቱ ምልክት አድርጎ ጠቅሷቸዋል። በአሁኑ ዘመን በሀገራችንም «ነቢያት ነን» የሚሉ አጭበርባሪዎች እንደ አሸን ፈልተዋል።
እነዚህም በነቢይ ኤልያስ እንዲሁም በነቢዩ ኤልሣዕ ስም እያጭበረበሩና እየዋሹ በምትሐታዊ አሠርራር የሚያስቱ ሐሰተኞች እንደሚነሡ ሌላው የዳግም ምጽአቱ ምልክት ሆኖ ተነግሯል፤ «ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ …ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ … እንግዲህ፦ እነሆ፥ በበረሀ ነው ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ እነሆ፥ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ፥ አትመኑ» እንዲል። (ማቴ.፳፬፥፲፩፣፳፮) እንግዲህ በዘመናችን በሀገራችንም ሆነ በሌላው ዓለም በነቢይነትና በሰባኪነት ስም የሚደረገውን የንግድና የርኩሰት እንቅስቃሴ በማስተዋል መከታተልና መጠበቅ ያስፈልጋል።

፯. የፍቅር መጥፋት
ሌላውና አሳዛኙ ጉዳይ የፍቅር መቀዝቀዝ ነው፤ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነውና የሰው ልጅ ፍቅርን ማጣት የለበትም። አሁንም «ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች» የሚለው ትንቢት እንዳይፈጸምብን ፍቅርን መንከባከብ፣ ማልማትና ማስፈት ይገባል። (ማቴ.፳፬፥፲፪) ፍቅር የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው፤ ፍቅር የመልካምና በጎ ንገር ሁሉ መገኛና ምንጭ ነው። ስለዚህ ሰዎች በፍቅር መኖር አለብን፡፡

፰. የወንጌል መዳረስ
የወንጌል ለዓለም መዳረስ ለደቀ መዛሙርቱ የዳግም ምጽአቱ ምልክቶች ሁነው ከተሰጡት አንዱ ነው። በፍርድ ቀን በክርስቶስ አምኖ እና እምነቱን በሥራ ገልጾ ስለመኖር ሲጠየቅ «አልሰማሁም፤ አላየሁም፤ አላወኩም» የሚል ከኃጥአን ጋር ይፈረድበታል፤ «ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል» ተብሎ እንደተነገረው በሁሉም ቤት ወንጌል ይሰበካል፡፡ (ማቴ.፳፬፥፲፬)
በመሆኑም በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ዕለት «እናንተ የአባቴ ቡሩካን ኑ፥ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ» እንድንባል ቅዱስ ቃሉን ሰምተን፣ አምነንና ታምነን እስከ መጨረሻው በሕገ እግዚአብሔር መመራትና በበጎ ምግባር በቅድስና ሕይወት ልንኖር ይገባል፡፡ (ማቴ.፳፭፥፴፬)
ከላይ የተገለጹት እና ሌሎችም ምልክቶች በአሁኑ ዘመን በአብዛኛው የታዩ እና እየታዩ ያሉ ናቸው። ትንቢቱን የተናገረው ባለቤቱ ወልደ አምላክ ክርስቶስ በመሆኑ የበለጠ ትኩረት እንድናደርግበት ግድ ይለናል። ከዚህም ተነስተን የክፋት ትንቢት መፈጸሚያ እንዳንሆን መጠንቀቅ ይገባናል። ከምልክቶቹ ፍጻሜ አንጻር ግን እራሳችንን መታዘዝ በማስተማር ሕይወታችንን በንስሐ ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ ብቸኛ መፍትሄ ነው።

ምጽአት

ከብዙ የምጽአት ምልክቶች በኋላ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ይሆናል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ እንዳረገ እንዲሁ ተመልሶ ይመጣል። ስለዚህም ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ላይ «እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ ፥ እነሆነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሏቸው።» (ሐዋ ፩፥፱ ) በማለት ጽፎልናል። ከላይ «ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል» የሚለው ኃይለ ቃል የሚያስረዳው ጌታችን ባረገበት ኃይልና የመላእክት እልልታ እንዲሁ በቅዱሳን መላእክት ታጅቦ በክብር በደመና ለፍርድ እና ለእያንዳንዱ ዋጋውን ለመስጠት መምጣቱን እንደሆነ መገንዘብ ያስፈለጋል።

ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ(ማቴ ፳፭) ስለ ጌታችን ዳግም አመጣጥ እና በፍርድ ወንበር መቀመጥ ሲገልጽ «የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፤ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል።» በማለት ጻድቃንን በበጎች፣ ኃጥአንን በፍየሎች መስሎ ጻድቃንን ለክብር በቀኝ፣ ኃጥአንን ለሃሳር በግራ ለይቶ ያቆማቸዋል። ቀጥሎም ጌታችን ክርስቶስ በፍርድ ቃል በቀኙ ያሉትን «እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና።» ይላቸዋል። ነገር ግን ጻድቃን ብዙ መልካም ሥራ ሰርተው ሳለ ምንም እንዳልሰሩና እንዳላደረጉ ሆነው ከእግዚአብሔር ቸርነት የተነሳ ክብር እንደተሰጣቸው አውቀው በትህትና ቃል «ጌታ ሆይ፥ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን?» ይሉታል። እርሱም መልሶ በሕይወት ዘመናቸው ከእነርሱ ለሚያንሱት ያደረጉትን መልካም የቸርነትና ትህትና ሥራ እንደዋጋ ቆጥሮላቸው «እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት» ብሎ ጻድቃንን ወደ ዘለዓለም ሕይወት ይሰዳቸዋል።

ነገር ግን በኃጥአን ላይ ከዚህ በተቃራኒ ፍርዱም ሆነ የእነሱም ምላሽ የተለየ ይሆናል። ጌታም እርሱን ባላመለኩት መጠንና ከሰይጣናት በተስማማ ሁኔታ መንገዳቸውን ባደረጉ ልክ እንዲህ በማለት ይፈርድባቸዋል፤ «እናንተ ርጕማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘለዓለም እሳት ከእኔ ሂዱ። ተርቤ አላበላችሁኝምና፥ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፥ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፥ ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፥ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና።» እነርሱ ግን ፍርዱን በመቃወም እንዲህ እያሉ ይከራከራሉ። «ጌታ ሆይ፥ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን አላገለገልንህም?» ጌታችንም በምላሹ የርህራሄን ሥራ ለታናናሾቻችሁ አልሰራችሁም ፤ ያን አለመስራታችሁ ለኔ አለመስራታችሁ ነው ብሎ ወደ ዘለዓለም ቅጣት ይሰዳቸዋል።

ያቺ የፍርድ ቀን የዓለም ፍጻሜ ናት። በዛች ቀን መስማት እንጂ መመለስ መከራከር የለም። የዚያች ቀን የፍርድ ውሳኔ ዛሬ በምድር ላይ የምንፈጽመው የአምልኮና የመልካም ወይም የክፉ ምግባር ውጤት ነው። ዛሬ አካሄዳችንን ከእግዚአብሔር ጋር ካደረግን ከእግዚአብሔር ጋር በተስፋዪቱ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት እንሆናለን፤ዛሬ አካሄዳችንን ከዲያብሎስ ጋር ካደረግን ግን በግራ ከዲያብሎስ ጋር እንቆማለን፤ትሉ በማያንቀላፋ እሳቱ በማይጠፋ በገሃነም እሳት መኖር ግድ ይለናል። የዛሬ የአምልኮ አያያዛችን የፍጻሜውን ቀን ይወስነዋልና ዛሬ ሳናመነታ አኗኗራችንን እንወስን።

ተስፋ መንግሥተ ሰማያት

የደብረ ዘይት እለት ጻድቃን የሚናፍቋት የተስፋ መንግሥተ ሰማያት እለት ናት። ተስፋ ብርሃናዊ መገስገሻ መንገድ ናት።ተስፋ የማይታየውን አጉልታ፣ ሩቁን አቅርባ የምታሳይ መነጽር፣ መከራውን ደስታ የምታደርግ ሀሴት፣ደካማውን የምታበረታ ኃይል ናት። የሰው ልጅ የተስፋ መንግሥት ሰማያትን ፍጹም ደስታ፣ የቀቢጸ ተስፋ ገሀነመ እሳትን ፍጹም ሥቃይ ቢያውቅ፣ ቢረዳው ኖሮ በዚህ ዓለም ይድላኝ ሳይል ኑሮው በመንኖ ጥሪት ይሆን ነበር። «ወምንተ ይበቁዖ ለሰብእ ለእመ ኲሎ ዓለመ ረብሐ ወነፍሶ ሃጉለ። ወምንተ እምወሀበ ሰብእ ቤዛሀ ለነፍሱ። ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?» (ማቴ ፲፮ ፥ ፳፮ ) እንዲል።

ተስፋ የምናደርጋት መንግሥተ ሰማያት የእግዚአብሔር መንግሥት ናት። እርሷም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያዘጋጃት፣ የእግዚአብሔር ምሕረቱና ጥበቡ የሚገለጽባት፣ በትንሣኤ ዘጉባኤ ፍርድ ቀን በእርሱ ያመኑ የሚገቡባት የእግዚአብሔር ቤት ናት። «በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ … እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ፤ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ።» እንዳል ጌታ በወንጌሉ።

በአጠቃላይ ደብረ ዘይት ሁለት ተቃራኒ ነገሮች የሚፈጽሙበትን የነገረ ዳግም ምጽአት ሁኔታን ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምንማርበት የዓቢይ ጾም ሳምንት ነው። ይኸውም ትንሣኤ ዘለክብር እና ትንሳኤ ዘለሀሳር ነው። አንዱ ከእግዚአብሔር ጋር የሚሆንበት ሌላው ከሰይጣን ጋር ኑሮው የሚወሰንበት፣ አንዱ መንግሥተ ሰማያትን የሚወርስበት ሌላው ገሀነመ እሳት የሚገባበት፣ አንዱ የሚደሰትበት ፣ ሌላው ዋይታ የሚያሰማበት፣ የበረከትና የመርገም ቀን፣ የተስፋና ተስፋ የመቁረጥ ቀን፣ የደስታና የጭንቅ ቀን፣ የእልልታና የዋይታ ቀን፣ አንዱ ሌላውን የማያድንበት፣ እናት ልጄን የማትልበት፣ ልጅ እናቴን የማይልበት፣ ባልና ሚስት የሚለያዩበት፣ ጓደኞች ዳግም የማይገናኙበት፣ ኃጥእ ከጻድቅ መተያየት የሚያበቁበት የመጨረሻ እለት ዳግም ምጽአት ናት።

ሰሚ ከሆንን የደብረ ዘይትን ጩኸት ልንሰማ ይገባናል። የምትነግረንን የምጽአትን ምልክቶች፣ የምጽአትን ትንቢቶች፥ «እግዚአብሔርሰ ገሀደ ይመጽእ፣ ወአምላክነሂ ኢያረምም፣ እሳት ይነድድ ቅድሜሁ። እግዚአብሔር በግልጽ ይመጣል፤ አምላካችን ዝምም አይልም ከፊቱም እሳት ይነዳል» ፣ ወዘተ የሚለውን ፣ ጌታ በወንጌሉ በፍርድ ቀን ለእያንዳንዱ እከፍለው ዘንድ በቁጣ እመጣለሁ ያለውን ፣ ከደብረ ዘይት ልንማር ይገባናል። ያለዚያ ግን በመጨረሻው ቀን ዕጣ ፈንታችን ከዲያብሎስ ጋር እሳቱ በማይጠፋ እና ትሉ በማያንቀላፋ በገሃነመ እሳት ሥቃይ ይሆናል ።

በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለን ርስተ መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ የአምላችን እግዚአብሔር ርዳታ አይለየን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፥ ማህበረ ቅዱሳን

02/26/2023

ቅድስት

ቤተ ክርስቲያናችንን መዝሙር ንባቡን ከዜማው አስማምቶ አጠናክሮ ያስተላለፈልን ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በጾመድጓው በዓቢይ ጾም ለሚገኙትን እሑዶች ሁሉ የተለየ መዝሙር ስለሠራላቸው እያንዳንዱ እሑድ በመዝሙሩ ስም ይጠራል ። በዚህም መሰረት የዚህ ታላቅ ጾም ሁለተኛው እሑድ ቅድስት ተብሎ ተሰይሟል። ቅድስት የሚለው ቃል ግሱ “ቀደሰ” ሲሆን ለየ አከበረ መረጠ የሚል ትርጉም ይይዛል።

ቅድስት ማለት የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች ማለት ነው። ቅዱስ የሚለው ቃል እንደ የአገባቡ ለፈጣሪም ለፍጡርም ያገለግላል። ለፈጣሪ ሲነገር እንደ ፈጣሪነቱ ትርጉሙ ይሰፋል ይጠልቃል ለፍጡር ሲነገር ደግሞ እንደ ፍጡርነቱ እና እንደ ቅድስናው ደረጃ ትርጉሙ ሊወሰን ይችላል።

እግዚአብሔርን ቅዱስ ስንል የባህሪይው የሆነ፣ ኃጢአት የማይስማማው ፣ ለቅድስናው ተወዳዳሪ ተፎካካሪ የሌለው፣ ወደር የማይወጣለት፣ ዘለዓለማዊ የሆነ ማለታችን ሲሆን ፍጡራንን ግን ቅዱሳን ስንል ቅድስናቸው የጸጋ የሆነ፤ ከእግዚአብሔር ያገኙት፤ እንደነጭ ልብስ ጽድቁም ኃጢአቱም እንደ ዝንባሌአቸው የሚስማማቸው፤ ለቅድስናቸው ማዕረግ ደረጃ የሚወጣለት እንደ ገድል ትሩፋታቸው መጠን ሊጨምርም ሊጎድልም የሚችል ማለታችን ነው። ከፍጡራን መካከል ለእግዚአብሔር የተለዩ ሁሉ በጸጋ የቅድስናው ተሳታፊ ሊሆኑ ይችላሉ። መላእክት፣ ሰዎች፣ መካናት፣ ዕለታት፣ አልባሳት፣ ንዋያት ሁሉ ለእግዚአብሔር እስከተለዩ ድረስ ከቅድስናው በረከት ይሳተፋ እንደየደረጃቸው ቅዱሳን ተብለው ይጠራሉ።

በዚህ ዕለት ስለ ቅድስና እንዲሁም ዘወትር በዕለተ ሰንበት ከሌሎች ቀናት በተለየ ሁኔታ ለጽድቅ ስራ እንድንበረታ፣ ለቅድስና እራሳችንን እንድንለይ ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ይሰበካል ይነገራል። የሚዘመረውም መዝሙር “ግነዩ ለእግዚአብሔር ወጸውዑ ስሞ ወንግርዎሙለአሕዛብ ምግባሮ ሀቡ ስብሐተ ለስሙ አክብሩ ሰንበተ ተገበሩ ጽድቀ ዝግቡ ለክሙ መዝገበ ዘበሰማያት ኀበ ፃፄ ኢያማስኖ ወኢይረክቦ ሰራቂ ድልዋኒክሙ ንበሩ ዘበላዕሉ ጸልዩ ኀበ ሀሎ ክርስቶስ፤ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ስሙንም ጥሩ፤ ሥራውንም ለአሕዛብ ንገሯቸው፤ ለስሙም ምስጋናን አቅርቡ፤ ሰንበትን አክብሩ፤ እውነትንም አድርጉ፤ ብል የማያበላሸው ሌባም የማያገኘው በሰማያት ያለ መዝገብን ለእናንተ ሰብስቡ፤ ተዘጋጅታችሁም ተቀመጡ፤ ክርስቶስ ወዳለበት ወደላይ አስቡ፡፡”

“በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ እንደ ዘመረልን በተለይ ሰንበት ነገረ እግዚአብሔር በተለየ ሁኔታ የሚዘከርባት፤ ኅሊናችን ከምድራዊው ሃሳብ ወጥቶ ወደ ሰማይያዊው የሚነጠቅባት፤ ለቅድስና የተለየች ቅድስት ዕለት መሆኗን ይጠቁማል። በቅዱስ መጽሐፍም “የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ” (ዘፀ. ፳፥፰) ተብሏል፡፡ የሰንበትን ቀን አስቀድሞ የቀደሰ የባረከ እራሱ እግዚአብሔር ነው” እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና“(ዘፍ.፪፥፫) እንግዲህ “የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ” የተባለው እግዚአብሔር አስቀድሞ የባረከውን የቀደሰውን እኛ ድጋሚ የምንቀድስ የምንባርክ ሆነን ሳይሆን በዕለተ ሰንበት እራሳችንን በተለየ ሁኔታ ለቅዱስ ተግባር እንድንለይ ለሥጋችን ከምንፈጽማቸው ተግባራት ይልቅ ለተግባረ ነፍስ እንድናደላ ያስረዳናል። ምንም እንኳን ለስጋችን ስንባክን ጊዜ ቢያጥረን በዕለተ ሰንበት ግን ቅዳሴ ከማስቀድስ ቅዱስ ቃሉን ከመስማት ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ከመቀበል እንዳናስታጉል በሥርዓት ቤተ ክርስቲያን ታዘናል፡፡
ሊቃውንቱ በፍትሐ ነገሥት «ተጋብኡ ኩሎ ዕለት ኀበ ቤተ ክርስቲያን ወፈድፋደሰ በዕለተ ሰንበት ወበበዓላት ወበዕለተ ትንሣኤ ዘውእቱ ዕለተ እሑድ፤ › ሁልጊዜ በቤተ ክርስቲያን ተሰብሰቡ፤ ይልቁንም በዕለተ እሑድ፣ በዕለተ ቀዳሚት፣ በጌታ በዓላት ወደ ቤተ ክርስቲያን ተሰብሰቡ፡፡” (ፍትሐ ነገሥት ገጽ ፪፻፶፬) ብለው ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ከሌሎች ቀናት በተለየ ሁኔታ ትኩረት የምንሰጥበት የምንቀደስበት ዕለት ቅድስት ሰንበት እንደሆነች ተናግረዋል። ሐዋርያዊው ቅዱስ አትናቴዎስም በቅዳሴው ላይ ሰንበት የተቀደስች እና ሕይወታችን እንዲቀደስባት የተለየች ቀን መሆኗን ሲያስረዳ እንዲህ ይላል፡፡ “ወንበል ዛቲ ዕለት እንተ ገብረ እግዚአብሔር ንትፈሣሕ ወንትሐሰይ ባቲ፤ ይህች ዕለት እግዚአብሔር የሠራት ያከበራት ዕለት ናትና በእርሷ ፈጽሞ ደስ ይበለን” ሰንበት ለክርስትያኖች ለመንፈሳዊ ደስታ የተለየች ቀን ናት። የመንፈሳዊ ደስታ ምንጩ በነፍስ የሚገኝ መንፈሳዊ በረከት ነው። ሰው የኃጢአትን ሸክም በንስሃ ሲያራግፍ፤ ነፍሱ በጸጋ እግዚአብሔር ስትቃኝ የሚሰማውን ደስታ በሌላ በምንም መንገድ ሊያገኘው አይችልም። ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ሰንበት ቅድስትና ለቅድስና የተለየች ቀን መሆኗን ያስተማረን አስቀድሞ በነብያት ትንቢት ያናግር የነበረ መንፈስ ቅዱስ አነሳስቶት ነው።

ስለ ሰንበት መለየትና መቀደስ እንዲሁም የመንፈሳዊ ሐሴት ቀን ለመሆኗ ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት መዝሙሩ እንዲህ ብሎ ነበር “እግዚአብሔር የሠራትቀን ይህች ናት፤ ሐሤትን እናድርግ፥ በእርስዋም ደስ ይበለን።” (መዝ. ፻፲፯፥፳፬) ቅዱስ ዮሐንስም ራእዩ ሰንበት የጌታ ቀን ስለመሆኗ እንዲህ ይላል “በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ” (ራእ. ፩፥፲) ሰንበት የእኛ ቀን ሳትሆን ለጌታችን የምንሰራባት የምንለይባት ፣ የምንቀደስባት፣ ነገረ እግዚአብሔርን የምንዘከርባት የጌታ ቀን ናት። ለቅድስና የተለየች ቅድስት ቀን ናት ። በተለይ የክርስቲያን ሰንበት እሑድ “በኵረ በዓላት” ትባላለች በኵር ታላቅ እና መጀመርያ ማለት ነው፤ የመዳናችን መሰረት የተወጠነባት የጌታ የጽንሰቱ ቀን ዕለተ ሰንበት ናት፤ የመዳናችን ማረጋገጫ፣ የእምነታችን መሰረት ፣ የበዓላት ሁሉ ዓቢይ ትንሳኤው የተፈጸመው በዕለተ ሰንበት ነው። እንግዲህ በዚች ቅድስት ዕለት፥ ለቅድስና በተለየች ዕለትስ ሥጋውንም ነፍሱንም በሚያርያረክስ ተግባር የተሰማራስ ለነፍሱ ምን ዋስትና ይኖረዋል?

ቅድስት በተባለች በሰንበት እሑድ ማንም በምንም ምክንያት ወደ ቤተ እግዚአብሔር ከመሄድ እንዳያስታጉል በስርአተ ቤተክርስትያን ተቀምጦልናል። ሌላው ቀርቶ በዕዳ በብድር በቀረጥ በግብር በአስራት በበኩራት ይሉንኝታ ፈርቶ ማንም ቅድስት በምትባል በእሑድ ሰንበት ቅዳሴ እንዳያስታጉል ማንም ማንንም በዚህች ቅድስት ዕለት ምንም አይነት እዳ እንዳይጠይቅ ታዟል።

“ወኢይኅሥሥ መኑሂ በይእቲ ዕለት ንዋዮ እምካልኡ ወኢይጽሐቅ አሐዱሂ እምእመናን በእንተ ኃሥሠ ዕዳ ። አው ተጻልኦ አው በዘይመስሎ ለዝንቱ። ወይሑሩ ቦቱ ኩሉሙ ሰብእ ኀበ ቤተ ክርስቲያን ወይምጽኡ ኲሉ ለለ ፩ ፩ እምእመናን ኅቤሃ በንጽሕ ወበትህትና ዘእንበለ ፍርሃት እምነ መኮንን ወእም በዓለ ዕዳ አው እምፈታሒ አው ዘይመስሎ። ወእመሰ ተሀበለ ፩ሂ ክርስቲያን ምክዕቢተ ይፍዲ፤ከምእመናን ወገን አንድስ እንኳ በእሑድ ቀን ለገንዘብ መትጋት፤ገንዘቤን አምጣ ብሎ መጣላት፣ ዋስ መያዝ አይገባውም ። ሁሉም ምእመናን ወደ ቤተክርስቲያን በንጽሕና በትሕትና ሆነው ይምጡ እንጂ ። ዳኛ ግብሬን፣ አበዳሪ ብድሬን ፣ኤጲስቆጶስ ዐሥራት በኵራት ፣ ነጋ ድራስ ቀረጥ አምጡ ይሉናል ብለው ሳይፈሩ ይምጡ። ከነጋድራሶች አንዱ እንኳ ወደ ቤተክርስትያን ከሚሄዱ ሰዎች ቀረጥ ይቀበል ዘንድ የድፍረት ሥራ የሠራ ቢሆን እጽፍ አድርጎ ይክፈል።” (ፍትሐ ነገሥት ገጽ ፪፻፶፰-፪፻፶፱) ቅድስት ቤተክርስቲያን ይህን ያህል ጥንቃቄ የምታደርገው ሰዎች በተለያየ ምክንያት ከቤተ እግዚአብሔር እንዳይርቁ ከዛም አልፎ ተበዳይም ሆነ በዳይ ፣በዕዳ የሚጠየቅም ሆነ የሚጠይቅ ሁለቱም በአንድነት ቅዱስ ቃሉን ሲሰሙ ዋሽቶ የሰው ዕዳ ያልከፈለውም ተጸጽቶ ይክሳል ወራት ብሶበት ቀን ጥሎት መክፈል ላልቻለውም ምህረት ይቅርታ እንዲያገኝ ቅዱስ ቃሉ ጸሎቱ ምክንያት ይሆነዋል ። በዚህም የተነሳ ሁለቱም ወገኖች በክፉ ከመፈላለግ ይልቅ የይቅርታ የምህረት ሰዎች ይሆናሉ። በዚህች በኵረ በዓላት በምትሆን በቅድስት በዕለተ ሰንበት የምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት ይባረካል ይቀደሳል በዚህ ታሳቢነት ዕለቱም ዕለተ ቅድስና መሆኑን ለማጠየቅ ቅድስት ተብሏል ።
ቅድስና የተፈቀደልን ብቻ ሳይሆን የታዘዝነውም ጭምር ነው “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ” (ዘሌ.፲፱፥፪) በዚህ ኃይለ ቃል ውስጥ ቅድስና እንደ ፈቃድም እንደ ትእዛዝም ሆኖ ተሰጥቶናል፤ እግዚአብሔር ያልፈቀደውን ነገር አድርጉ ሁኑ ብሎ አያዝም።የቅድስና ሕይወት መሰረቱ የእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ ሆኖ ሳለ ለመቀደስ የእኛ መሻት መፈለግ ዝንባሌም ወሳኝ ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው እንዲህ ሲል የጻፈልን “ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥” (ዕብ. ፲፪፥፲፬) ምንም አንኳን ቅድስና የተፈቀደና የታዘዘ ቢሆንም የውዴታ እና የነጻ ፈቃድ ውጤት እንጂ የምገደድበት አይደለም፡፡እግዚአብሔር ፍቅሩ ገብቶን ወደን እና ፈቅደን በፈቃዱ እና በትእዛዙ ስንመራ ያስደስተዋል እንጂ ተገደን ፈርተን ተንቀጥቅጠን እንድንገዛለት አይወድም፡፡

ወደ ቅደመ ነገራችን ስንመለስ ዕለተ ሰንበትም ቅድስት መባሏ ከላይ ያብራራነውን መሰረታዊ ሃሳብ በተከተለ መልኩ ነው። ዕለቲቱ ቅድስት መባሏ ዋና ዓላማ በሰዎች እና በእግዚአብሔር መካከል ለቅድስና ሕይወት ምልክት ማስታወሻ እንድትሆን ነው። በባህሪው ቅዱስ የሆነ አምላክ ዓለምን የማዳን ስራውን የጀመረበትን ጽንሰቱን እንዲሁም የማዳን ስራውም አጠናቆ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ዘላለማዊ ሕይወትን ያበሰረበትን ትንሳኤውን የምናስብበት በመሆኑ የዕለቱ ቅድስና የፈጣሪን ቅዱስ ተግባር የምናደንቅበት ከማንኛውም የሥጋ ሥራ ተለይተን የዋለልን ሁለታ ከፍ ከፍ እያድረግን እርሱን የምናመሰግንበት ዕለት ነው። ይህም እኛን ወደ በለጠ የቅድስና ሕይወት የሚያሸጋግረን ከመሆኑም በላይ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ፍቅር በየጊዜው እንድናስብና በፍቅሩም እንድንኖር ያግዘናል፡፡

ከጾሙ በረከት ያሳትፈን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር

02/23/2023

ኪዳነ ምሕረት

‹‹ኪዳን›› የሚለው ቃል ‹‹ተካየደ – ተዋዋለ፤ ቃል ኪዳን ተጋባ፤ ተማማለ›› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም ኪዳን፣ ውል፣ መሐላ፣ ቃል ኪዳን፣ የውል ቃል ማለት ነው /ዘዳ.፳፱፥፩፤ ኤር.፴፩፥፴፩-፴፫፤ መዝ.፹፰፥፫/፡፡ በሌላ በኩል ኪዳን የጸሎት ስም ሲኾን፣ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ፣ ከማረጉ በፊት ለሐዋርያት ያስተማራቸው ጸሎት ኪዳን ይባላል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከወዳጇ ከጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳን (ውል፣ ስምምነት) የተቀበለችበት ዕለት (የክብረ በዓል ስም) ደግሞ ኪዳነ ምሕረት ይባላል፡፡

በየዓመቱ የካቲት ፲፮ ቀን የምናከብረው ይህ በዓል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጎልጎታ በልጇ በመቃብር ላይ ኾና ‹‹ኦ ወልድየ ወፍቁርየ እስእለከ በእንተ ዘተሰባእከ እምኔየ ወበማኅፀንየ ዘጾረተከ፤ ልጄ ወዳጃ ሆይ ከሥጋዬ ሥጋ፣ ከነፍሴ ነፍስ ነሥተህ ሰው ስለመኾንህ፤ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ስለቻለችህ ማኅፀኔ፤ ከአንተ ጋር ከአገር ወደ አገር ስለመሰደዴ መጥተህ ልመናዬን ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ›› እያለች ስትጸልይ ጌታ እልፍ አእላፍ መላእክቱን አስከትሎ ወደእርሷ መጥቶ ‹‹ሰላም ለኪ ማርያም እምየ፤ እናቴ ማርያም ሰላም ላንቺ ይኹን! እንዳደርግልሽ የምትለምኚኝ ምንድን ነው?›› አላት፡፡ እመቤታችንም በስሟ የሚማጸኑትንና መታሰቢያዋን የሚያደርጉትን፣ ለችግረኛ የሚራሩትን፣ ቤተ ክርስቲያን የሚያንጹትን፤ ዕጣን ዘይትና መብአ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡትን፤ ለእመቤታችንና ለሃይማኖታቸው ካላቸው ፍቅር የተነሣ ልጆቻቸውን በስሟ የሰየሙትን ዅሉ እንዲምርላትና ከሞተ ነፍስ እንዲያድንላት ጠየቀችው፡፡

ጌታችንም ‹‹ይህን ዅሉ እንዳደርግልሽ መሐልኩ ለኪ በርእስየ ወበአቡየ ወበመንፈስ ቅዱስ ሕያው፤ በራሴ፣ በአባቴ እና በመንፈስ ቅዱስ ማልኩልሽ›› ብሎ ቃል ኪዳን ገብቶላት ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ በቅዳሴው ‹‹… ዳግመኛም በእናትህ በማርያም ተማፅነናል፤ ይህችውም አንተን በመውለድ እመቤታችንና የባሕርያችን መመኪያ ናት፡፡ አንተ ‹መታሰቢያሽን ያደረገ፣ ስምሽንም የጠራ፣ የዘለዓለም ድኅነትን ይድናል› ብለሃታልና …፤›› በማለት የሚማጸነው፡፡

በተአምረ ማርያም መጽሐፍ እንደተመዘገበው በዚህ ዕለት የሚታሰቡ ሁለት ተአምራት አሉ፤ ከእነዚህም አንደኛው የስምዖን ታሪክ ነው፡፡ ስምዖን የሚባል እንግዳ ተቀባይ ደግ ሰው ነበር፡፡ ሰይጣን ለምቀኝነት አያፍርምና ከዕለታት አንድ ቀን በእንግድነት ከቤቱ ገብቶ ‹‹ልጅህን አርደህ ካላበላኸኝ ሌላ ምግብ አልበላም›› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ስምዖን ሲያወጣና ሲያወርድ ቆየና ‹‹አብርሃም ልጁን ሰውቶ ነው የእግዚአብሔር ሰው የተባለው›› በማለት፣ ‹‹የእግዚአብሔርን እንግዳ›› ላለማሳዘን ሲል ልጁን አርዶ አቀረበለት፡፡ እንግዳ መሰሉ ሰይጣንም ሥጋውን ቅመስልኝ ብሎ ግድ አለው፡፡ ስምዖንም (በላዔ ሰብእ) አርዶ ያዘጋጀውን የልጁን ሥጋ በቀምሰ ጊዜ ሰይጣን ስላደረበት (ስለተዋሐደው) ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ቤተሰቦቹን፣ ጎረቤቶቹንና መንገደኛውን ዅሉ ይበላ ጀመር፡፡ በአጠቃላይ ፸፰ ሰዎችን ከበላ በኋላ አንድ በቍስል የተመታ ሰው አገኘና ሊበላው ሲል ‹‹ውኃ አጠጣኝ›› ብሎ በሥላሴ፣ በቅዱስ ሚካኤል፣ በቅዱስ ገብርኤል ስም ለመነው፤ እርሱም ዝም አለው፡፡

በመጨረሻም ‹‹በድንግል ማርያም ስም›› አለው፡፡ ስምዖን የእመቤታችንን ስም በሰማ ጊዜም ወደ ልቡናው ተመልሶ ‹‹እስኪ ቃሉን ድገመው›› አለው፤ በሽተኛውም መልሶ ‹‹ስለ ድንግል ማርያም ውኃ አጠጣኝ›› ብሎ ለመነው፡፡ ያን ጊዜ ‹‹ይህችስ እንደምታስምር በልጅነቴ ሰምቻለሁ›› ብሎ ጥቂት ውኃ ሰጠው፤ ውኃው ጕሮሮውን እንኳን ሳያርስለት ‹‹ጨረስህብኝ›› ብሎ ነጥቆት ሔደ፡፡ በሌላ ቦታም አንድ ገበሬ አግኝቶ ሊበላ ሲል ገበሬው ‹‹በላዔ ሰብ የምትባል አንተ ነህ?›› ባለው ጊዜ ‹‹ለካስ አመሌን ሰው ዅሉ አውቆብኛል›› ብሎ ዋሻ ገብቶ በመጸጸት በዚያው ሞተ፡፡ ነፍሱንም መላእክተ ጽልመት መጥተው ሲወስዷት እመቤታችን ‹‹ልጄ በማይታበል ቃልህ ይህችን ነፍስ ማርልኝ?›› አለችው፡፡ ጌታችንም ‹‹ሰባ ስምንት ነፍስ ያጠፋ፣ ፈጣሪውን የካደ ሰው ይማራልን?›› አላት፡፡ እመቤታችንም ‹‹በስሜ የተጠማውን ውኃ አጥጥቶ የለምን?›› ብላ ስምዖንን (በላዔ ሰብእን) አስምራዋለች፡፡ ነፍሱንም መላእክተ ብርሃን መጥተው ወደ ገነት አስገብተዋታል፡፡

ሁለተኛው ተአምር ደግሞ ከብሮ ከኖረ በኋላ ለድህነት በተጋለጠ አንድ ምእመን ላይ የተደረገ ነው፤ ከክርስቲያን ወገን የኾነ ሀብት አግኝቶ ያጣ አንድ ሰው ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ‹‹ከብሬ በኖርኹበት አገር ተዋርጄ አልኖርም›› ብሎ ጓዙን ጠቅልሎ ከአገሩ ወጥቶ ሲሔድ ሰይጣን ያዘነ ሰው መስሎ ደንጊያውን በምትሐት ወርቅ አስመስሎ ‹‹ሥላሴን፣ ጻድቃንን፣ ሰማዕታትንን፣ መላእክትን ካድልኝና ይህን ወርቅ እሰጥሃለሁ›› አለው፡፡ ዅሉንም ካደለትና ወርቁን ተቀብሎ ዞር ሲል ‹‹ምእመናን የሚመኩባት ድንግል ማርያም ‹የአምላክ እናት አይደለችም› ብለህ ካድልኝ›› አለው፡፡ ሰወየውም ‹‹እርሷንስ አልክድም›› ስላው በደንጊያ ቀጥቅጦ ገደለው፡፡ መላእክተ ጽልመት የሟቹን ነፍስ ሊወስዱ ሲሉ መላእክተ ብርሃንም አብረው ቀረቡ፡፡ እመቤታችንም ጌታችንን ‹‹ልጄ ይህችን ነፍስ ማርልኝ?›› አለችው፡፡ እርሱም ‹‹ከልብኑ ይትመሐር እምየ፤ እናቴ፣ ውሻ ይማራልን?›› አላት፡፡ እመቤታችንም፡- ‹‹‹ስምሽን የጠራውን፣ መታሰቢያሽን ያደረገውን እምርልሻለሁ› ያልኸው ቃል ይታበላልን?›› አለችው፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ምሬልሻለሁ›› አላት፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ‹‹ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ›› ባለው መሠረት ከቅዱሳን ጋር ያደረጋቸው ቃል ኪዳኖች ብዙዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ከላይ በተአምራቱ እንደተመለከትነው አንዱ ለእመቤታችን የሰጠው የአማላጅነት ኪዳን ነው፡፡ ማማለድ ማለት ስለሌላው መጸለይ፣ መለመን፣ የደረሰውን ችግር እንዲወገድ ማድረግ፣ ማስማር (ይቅርታ ማሰጠት) ማለት ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ከእግዚአብሔር በታች ከቅዱሳን ዅሉ በላይ ከፍ ከፍ ያለችና የከበረች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእግዚአብሔር በተሰጣት የማማለድ ሥልጣን ‹‹ሰአሊ ለነ ቅድስት፤ ቅድስት ሆይ ለምኚልን›› እያሉ ለሚለምኗት ዅሉ ከእግዚአብሔር እያማለደችና እየለመነች ምሕረትን እንደምታሰጥ ቀናውንና የተመሰገነውን ሃይማኖት የምንከተል ምእመናን ዅሉ እናምናለን፡፡ ምክንያቱም ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር እናትና አገልጋይ እንደመኾኗ ከዅሉም ቅዱሳን በበለጠ ለእግዚአብሔር ቅርብ ናትና፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድም ኾነ በሰው ዘንድ ባለሟልነትን ማግኘት ወይም ቅርብ መኾን ደግሞ አንድን ጉዳይ በቀላሉ ለማስፈጸም ይጠቅማል፡፡ ለምሳሌ፡-
- መልአኩ ቅዱስ ገብርአል በእግዚአብሔር ፊት የሚቆም ባለሟል በመኾኑ የድኅነትን ምሥጢር አብሣሪ ኾኗል /ሉቃ. ፩፥፲፱-፳፮/፡፡
- አስቴር የንጉሡ አርጤክስስ ሚስት በመኾኗ በወገኖቿ አይሁድ የታወጀውን የሞት አዋጅ አስለውጣለች /መጽሐፈ አስቴር ፫፥፲/፡፡
- ነቢዩ ሙሴ በእግዚአብሔር ፊት ባለሟል በመኾኑ ‹‹ይህንን ኀጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን እኔን ከጻፍከው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ?›› በማለት ለእስራኤላውያን ምሕረትን አሰጥቷል /ዘፀ.፴፪፥፲፬/፡፡

ስለዚህ የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትም እንደ ፀሐይ የበራ ሐቅ ነው፡፡ ይህንን እውነት ቅዱስ ያሬድ ሲመሰክር፡- ‹‹ወታስተሠርዪ ኀጢአተ ሕዝብኪ ተበውሀ ለኪ እምአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ወከመ ትኩኒ ተንከተመ ለውሉደ ሰብእ ለሕይወት ዘለዓለም፤ ለሕዝብሽ፣ ለወገኖችሽ የኃጢአት ይቅርታን ታሰጪ ዘንድ፤ ዘለዓለማዊ ሕይወትንም ለሚወርሱ ዅሉ መሸጋገሪያ ድልድይ ትኾኚ ዘንድ ከአብ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ዘንድ ሥልጣን አግኝተሻል›› በማለት አመስግኗታል /አንቀጸ ብርሃን/፡፡ አባ ጽጌ ድንግልም በማኅሌተ ጽጌ ድርሰታቸው፡- ‹‹ሶበሰ ኪዳንኪ ምክንያተ ድኂን ኢሀሎ ፈለገ እሳት ወደይን እም አሰጠመ ኩሎ፤ የድኅነት ምክንያት ቃል ኪዳንሽ ባይኖር ኖሮ የጥፋት እሳት፣ መርገም (ኀጢአት) ባጠፋን ነበር›› ብለዋል፡፡ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው፡– ‹‹ጥፋትን ያይደለ ይቅርታን አሳስቢ፡፡ መዓትን ያይደለ ምሕረትን አሳስቢ፡፡ ለጻድቃን ያይደለ ለኀጥአን አሳስቢ፡፡ ለንጹሐን ያይደለ ለተዳደፉት አሶስቢ፤›› ሲሉ ይማጸኗታል /ቅዳሴ ማርያም ቍ.፻፷፭-፻፸፩/፡፡

ስለዚህም ዘወትር በሥርዓተ ቅደሴአችን፡- ‹‹ድኅነትን የምንለምንሽ ክብርን የተመላሽ ቅድስት ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ ዅል ጊዜ ድንግል የምትኾኚ አምላክን የወለድነሽ የክርስቶስ እናት ሆይ ኀጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ወደ ልጅሽ ወደ ወዳጅሽ ወደ ላይ ጸሎታችንን አሰርጊልን፡፡ በእውነት የጽድቅ ብርሃን የሚሆን አምላካችንን ክርስቶስን የወለድሽልን ንጽሕት ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ ንጽሕት ድንግል ሆይ ለነፍሳችን ይቅርታን ያደርግ ዘንድ፤ ኀጢአታችንንም ያስተሠርይልን ዘንድ ወደ ጌታችን ለምኚልን፡፡ በእውነት ለሰው ወገን አማላጅ የምትሆኝ አምላክን የወለድሽ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ የኀጢአታችንን ሥርየት ይሰጠን ዘንድ በልጅሽ በክርስቶስ ፊት ለምኝልን፡፡ በእውነት ንግሥት የምትኾኚ ንጽሕት ድንግል ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ የባሕርያችን መመኪያ ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ አምላካችን አማኑኤልን የወለድሽልን ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት እውነተኛ አስታራቂ ሆነሽ ታስቢን ዘንድ እንለምንሻለን፡፡ ለነፍሳችን ይቅርታን ያደርግልን ዘንድ ኀጢአታችንንም ያስተሰርይልን ዘንድ፤›› በማለት እመቤታችንን እንማጸናታለን፡፡

በአጠቃላይ ‹‹ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ፤ ከመረጥኋቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ፤›› በማለት በነቢዩ ቅዱስ ዳዊት አድሮ ራሱ እግዚአብሔር ከመረጣቸው አበው ነቢያት፣ ጻድቃን፣ ቅዱሳንና ሰማዕታት ጋር ቃል ኪዳን እንደ ገባ፣ እንደሚገባ ተናግሯል /መዝ.፹፰፥፫/፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹እንግዲህ እርሱ ራሱ ካጸደቀ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች የሚቃወማቸው ማን ነው?›› በማለት እግዚአብሔር ሰዎችን እንደሚጠራ፣ እንደሚያከብር፣ እንደሚቀድስና ቃል ኪዳን እንደሚሰጥ ነግሮናል /ሮሜ.፰፥፴፫/፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ ስለ አንቺ የተነገረው ነገር ድንቅ ነው፤›› /መዝ.፹፮፥፫/ በማለት እንደተናገረው እግዚአብሔር አምላካችን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የገባው ቃል ኪዳን ከቅዱሳን ቃል ኪዳን ዅሉ ልዩ ነው፡፡ ይህም እንደምን ነው ቢሉ፡-

ለአምላክ እናትነት የተመረጠች ልዩ እናት በመኾኗ፤
አምላክ ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ከእርሷ በመወለዱ፤
ከመለለዷ በፊት፣ በወለደች ጊዜ፣ ከወለደች በኋላ ምን ጊዜም ድንግል በመኾኗ፤
በሁለቱም ወገን (በአሳብም በገቢርም) ድንግል በመኾኗ፤
አማላጅነቷ የወዳጅነት ሳይኾን የእናትነት በመኾኑ፤
ዓለም ይድን ዘንድ የድኅነት ምክንያት አድርጎ አምላክ ስለመረጣት ነው፡፡
ስለዚህ ብዙ ከንቱ አሳቦችን ትተን፣ እንደበላዔ ሰብእ በቃል ኪዳኗ ተጠቅመን፣ ንስሐ ገብተን፣ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ተቀብለን፣ የስሙ ቀዳሽ፣ የመንግሥቱ ወራሽ ለመኾን ያብቃን፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን አማላጅነት፣ የቅዱሳን ተራዳዒነት አይለየን፡፡

ዋቢ መጻሕፍት፡-

መጽሐፈ ስንክሳር
መዝገበ ታሪክ
ተአምረ ማርያም
አማርኛ መዝገበ ቃላት
ክብረ ቅዱሳን

Address

2020 27 Avenue
Northeast Calgary, AB
T2E7A6

Opening Hours

Monday 6pm - 8pm
Tuesday 6pm - 8pm
Wednesday 6pm - 8pm
Thursday 6pm - 8pm
Friday 6pm - 9pm
Saturday 6am - 10am
Sunday 4am - 12pm

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Hamere Noah Kidist Kidanemihret EOTC - Calgary posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Place Of Worship

Send a message to Hamere Noah Kidist Kidanemihret EOTC - Calgary:

Share