06/01/2026
የደስታ መንፈስ
የተወደደው መምህራችን ቅዱስ ጳውሎስ ከነገረን የመንፈስ ፍሬዎች አንዱ የደስታ መንፈስ ነው።
የሰዎች ደስታ ምክንያቱ ብዙ ነው፤ ባለጠጋ በሀብቱ ብዛት፣ ንጉሥ በግዛቱ ስፋት፣ ሊቅ በዕውቀቱ፣ ገበሬ በምርቱ፣ ወታደር በጀግንነቱ ጎልማሳ በሚስቱ ደስ እየተሰኘ ይኖራል።
ከእነዚህ ሁሉ የሚሻለውና የሚበልጠው የመንፈስ ቅዱስ ደስታ ነው።
ሌሎቹ ከላይ የዘረዘርናቸውም ሆነ ያልዘረዘርናቸው ከአንዱ ተነሥተው ለሌላ የሚሰጡ ናቸው። የባለጠጎች ሀብት ደስታን የሚያመጣው ከሌሎቹ በልጦ ሲታይ ነው፤ የንጉሥም ግዛት የሚሰፋው የሌሎችን በማጥበብ ነው። የወታደርም ጀግንነት ለደስታ የሚያበቃው ሌላውን ድል በመንሣት በሞት ወይም በስደት መቅጣት ሲያስችል ነው።
ከእግዚአብሔር እጅ የምንቀበለው የመንፈስ ቅዱስ ደስታ ግን ከአንዱ ሳይነጠቅ ለሁሉም እኩል የሚሰጥ በመሆኑ ልዩ የደስታ ምንጭ ያደርገዋል።
ለዚህ ነው ቅዱስ መጽሐፍ “በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው” ብሎ የተናገረው። በአንድ ጊዜ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ሁሉም ተቀበሉ።
ለሚመለከቷቸው ሰዎች ጉሽ የወይን ጠጅ ጠጥተው የጠገቡ የቤተ መንግሥት ብላቴኖች ይመስሉ ነበር፤ የሰዎችም ግምት እንዲሁ ነበር። እነሱን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ከወይን ጠጅ ይልቅ የሚያስደስት እንደሆነ ማን በነገራቸው?
ለእነዚህ ሰዎች ሐዋርያት የተቀበሉትን ታላቁን ጸጋ ማን በገለጠላቸው? የመንፈስ ቅዱስን ደስታ በወይን ጠጅ ስካር ከሚገኝ ደስታ ጋር ማነጻጸራቸው ሌላ ባያውቁ ነውና።
እግዚአብሔር ሰው ከሚያውቀው በላይ የሆነ ደስታን ለሰው ማምጣት ይችላል። ጥቂት ጊዜ ዝም ቢሉ ኖሮ የስህተት ንግግር ሳይናገሩ የሐዋርያትን የደስታ ምክንያት ማወቅ በቻሉ ነበር እነሱ ግን መታገስ አልተቻላቸውምና ሳይጠይቋቸው በልባቸው ያሰቡትን ሁሉ ተናገሩባቸው።
ቅዱስ ጴጥሮስ “ለእናንተ እንደመሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም ከቀኑ ሦስተኛ ሰዓት ነውና” ሥራ. 2፥15 ብሎ የስህተት ንግግራቸውን የንግግር መጀመሪያ አድርጎ ወንጌል መስበክ ጀመረ። የወንግጌል ዓላማ በተሳሳተ የሕይወት መስመር የሚነጉደውን ሕዝብ መመለስ ነውና ከስህተታቸው እንዲመለሱ አጥብቆ መከራቸው።
ሐዋርያት የተቀበሉት ጸጋ ሰዎችን በማዳን ወደ ሚበልጠው ደስታ እንዲሸጋገሩ የሚያደርግ ነውና ጴጥሮስ አስራ አንዱን ጓደኞቹን አስከትሎ ለሰዎች የሚድኑበትን ቃል ነገራቸው።
በእሳት አምሳል ወርዶ ሐዋርያትን ደስ ያሰኛቸው መንፈስ ቅዱስ በዚያ የተሰበሰቡትን ሕዝቡን በቃሉ ደስ ያሰኛቸው ጀመር።
በቋንቋቸው ሲናገሩ ቢሰሟቸው በጥቂቱ ደስ አላቸው፤ ከነቢያት ቃል ጠቅሰው በነገሯቸው ጊዜ ደግሞ ደስታ ተጨመረላቸው።
መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ደስ የተሰኙ ሐዋርያት በዚያው ቀን ለሦስት ሺህ ሰዎች የደስታ ምክንያት ሆኑ። መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው እንዲህ ነው ለሰዎች የደስታ እንጂ የኃዘን ምክንያት መሆን አይችልም።
መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው ብቻዬን ይድላኝ አይልም። መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው አንድ ጊዜ ተናግሮ የሰሙትን ሰዎች ሁሉ ተከታዮቹ ማድረግ ይችላል። ምክንያቱም የሚናገረው የማይለወጠውን እውነት ስለሆነ ነው።
መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው የሚሰሙትን ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ሳያደርሳቸው ከክርስቶስ ጋር ሳያገናኛቸው አይተዋቸውምና እነዚህን ሰዎች “በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ” አላቸው።
በዓል ለማክበር የተሰሰቡ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚፋጠኑ በኦሪት በነቢያት የሚያምኑ ቢሆኑም በዚህ ሁሉ አገልግሎታቸው ለኃጢአት ሥርየት የሚያበቃ ምንም አይነት አገልግሎት አልነበራቸውም። የኃጢአት ሥርዬት የማያሰጥ አገልግሎት እየደጋገሙ ሲያከናውኑ መኖር እንዴት የሚያሳዝን ነው።
ከዚህ የድግግሞሽ ከኃጢአት ነጻ የማያወጣ ሥነ ሥርዓት ነጻ ሊያወጣቸው ቅዱስ ጴጥሮስ መስበክ ጀመረ። ደስታቸውን ቃሉን በመስማት ይጀምራሉ፤ ቃሉን በመፈጸም ደስታቸውን ፍጹም ያደርጋሉ።
ቅዱሳን ሐዋርያት ደስታቸው ፍጹም የሚሆነው ሰዎችን ወደ ክርስቶስ በማቅረብ ነው፤ የሰዎችም ደስታ የሚጀምረው ከክርስቶስ ጋር በመገናኘታቸው ነው።
ለሚድኑትም ለሚያድኗቸውም የደስታ ቀን ነበር - በዓለ ሃምሳ። ይህ ደስታቸው ወደ ጾምና ጸሎት ፊታቸውን ዘወር እንዲያደርጉ አድርጓቸዋል። በመጀመሪያ በጸሎት ሲተጉ ሳሉ አገኛቸው ሥራ. 1፥14፤ ክዚያ በኋላ ደግሞ በጦምና በጸሎት ሲያመልኩት ተገለጠላቸው ሥራ. 13፥1-2 መንፈስ ቅዱስን የተቀበለ ሰው አገልግሎቱ እየሰፋ ይሄዳል እንጂ አይቀንስም። ነፍሳችን የመንፈስ ቅዱስን ደስታ የምትካፈለው አገልግሎት በጨመርን ቁጥር ነውና።
ሐዋርያት ለአገልግሎታቸው መጀመሪያና መንፈስ ቅዱስንም ተቀብለው ደስ ቢላቸው በታላቅ ደስታ ጀመሩትን ይህንን ታላቅ ጾም ስንጾም ለመንፈሳዊ አገልግሎታችን መከናወን ምክንያት የሚሆነንን የመንፈስ ቅዱስን ረድ ኤት እናገኛለን።
እንደ ሐዋርያትም የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የሆነውን የመንፈስ ደስታን እንቀበላለንና በፍጹም ልባችን ደስ እያለን ልንጾም ይገባናል።
እንኳን አደረሳችሁ።
ሰይጣንን ድል የምንነሣበት ጾም ያድርግልን።
©️ ስምዓኮነ መልአከ / Simakone Melak